Monday 16 October 2017

7ኛው የኢሳት ክብረ በዓል በኖርዌይ በኦስሎ ከተማ በደማቅ ሁኔታ ተከበረ


 #Ethiopia #ESAT #ESAT_Norway በኖርዌይ በኦስሎ ከተማ ቅዳሜ 14/10/2017 በተዘጋጀው አዝናኝ እና ትምህርት ሰጭ 7ኛው የኢሳት ክብረ በዓል በደማቅ ሁኔታ ተከብሮል᎓᎓ ዝግጅቱን ካደመቁት እንግዶች መሃከል የኢሳት ጋዘኛ ፋሲል የኔአለም ከአምስተርዳም እንዲሁም ከለንደን ከተማ የመጣችው ታዋቂ ዘፋኝ ሃነሻ ሰለሞን የኢሳት 7ኛ ዓመት ክብረ በዓል ልዩና ትምህርት ሰጭ ፣ አዝናኝ እና በተለይ የኢሳት ሚዲያ ከተቋቋመ ጀምሮ የአገራችን ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተ የተገፀበት ነበር᎓᎓ የህዝባችን አይን፣ ጆሮ እና ድምፅ ለሆነልን ኢሳት በተዘጋጀውና ትልቅ ፉክክር የታየበት የገቢም ማሰባሰቢያ ጨረታም በስታቫንገር ከተማ የኢሳት ደጋፊ ነዋሪዎች አሸናፊነት የተዘጋጀውን ሽልማት ከጋዜጠኛ ፋሲል የኔዓለም ተቀብለዋል᎓᎓ በዝግጅቱም ከትኬት፣ከተለያዩ የገቢማሰባሰቢያዎች፣ ከምግብና ከመጠጥ እና ከጨረታ ጥሩ ድጋፍ ተደርጎአል ᎓᎓ በዚህ አጋጣሚ የእስታቫንገር ከተማ ከሌሎች ከተሞች በበለጠ በትኬትም ሽያጭ ሆነ ጨረታውንም ለማሸነፍ ላደረጋችሁት ትብብር ታልቅ ምስጋና ይድረሳችሁ᎓᎓ ከጎናችንም በመሆን ትብብር ላደረጋችሁልና ለማድረግ እየፈለጋችሁ በተለያየ ምክንያት ያልተመቻችሁ በሙሉ ወደፊት በምናዘጋጀው ዝግጅቶች ቅንነታችሁ እና ድጋፋችሁ አይለየን !
በአብዩ ጌታቸው ከስታቫንገር
16/10/2017







Wednesday 22 June 2016

አንድአርጋቸው ፅጌ

ሰኔ 16 2006 የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ታጋይ ቆራጡና ጀግናው አንድአርጋቸው ፅጌ በብዙ ሚሊዮን ዶላር በሕገ-ወጥ መንገድ በየመን ትብብር በፋሽስታዊው ወያኔ እጅ ስር የገባበት ሰኔ 16 2008 የዛሬው ቀን ሁለተኛ ዓመቱን አስቆጠረን ᎓᎓ አንድአርጋቸው የጀመረው የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ትግል እና መስዋትነት ብዙ ሚሊዮኖችን ኢትዮጵያውያን ወደ ትግል አለም እንዲቀላቀሉ አድርጎአል᎓᎓
__________________________________________________
ዶ/ር ወንድሙ (ለንደን) ስለ አንድአርጋቸው ፅጌ ከትዝታዎቼ አንዱ በማለት እንዲህ ብለው ነበር᎓᎓
" አንድ የወያኔ ወዳጅ የብርቲሽ የፓርላማ አባልና የመንግስት ባለስልጣን ወያኔን ለመርዳት በፈረንጆቹ አቆጣጠር 2005 ዓ᎐ም ላይ "ለኢንቨስተሮች "እዚያው ፓርላማ ውስጥ የምሽት ስብሰባ በሚስጥር አዘጋጀ᎓᎓ አንድ ወንድም ሚስጥራቸውን ማወቅ ብቻ ሳይሆን የግብዣ ወረቀትም መግኘት ቻለ ᎓᎓ ያንን የግብዣ ወረቀት " ከእኔ ይልቅ አንተ ብትገባበት ይሻላል" ብሎ ድምፄን አጥፍቼ እንድገባ መክሮ ሰጠኝ᎓᎓ እንዳለው ተሽሎኩልኬ ስገባ ፣ አንድአርጋቸውና ዶ/ር ብሪም በዚያው መንገድ ገብተው አገኘኋቸው᎓᎓ ተመሰጣጥረን ተቀመጥን᎓᎓ አልተመካከርንም ᎓᎓ ዕድሉን እናግኝ እንጂ፣ ሶስታችንም የአገራችንን ጉዳይ ለመናገር ብቁ እውቀት ነበረን᎓᎓
ያ ባለስልጣን ለነዚያ "ኢንቨስተሮች " ና በወረንጦ ተለቅመው ለታጋበዙ ታዳሚዎች ፣ወያኔ የሚያስተዳድራት ኢትዮጵያ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ለሚፈልጉ ባላሃብቶች ገነት እንደሆነች ፣ ዲሞክራሲ በአገሪቱ እንዳበበ ፣ ልማት በየቦታው እንደተተከለ ፣ርሀብ ኢትዮጵያ ውስጥ ጨርሶ ጠፍቶ ለታሪክ ምዝገባ ብቻ እንደበቃ ᎐᎐᎐ የወያኔን አስቀያሚ ገፅ "በሜክአፕ" ቀባብቶ ያለምንም ሀፍረት አቀረበው ᎓᎓ በንግግሩ መጨረሻ ላይ ለጥያቄ መድረክ ተከፈተ ᎓᎓ ኢንቬስተር ሁሉ በጉጉት ጥያቄውን አዥጎደጎደ᎓᎓ መልስ ተሰጠ᎓᎓ እኔ እጄን ባወጣ፣ባወጣ ሰርጎ- ገብ ኢትዮጵያዊ መሆኔ ሳይነቃ አልቀረምና ተዘጋሁ᎓᎓ዶ/ር ብሪ በጣም ቀላ ስለሚል የዓረብ ቱጃር መስሏቸው ነው መሰለኝ ዕድል ሲሰጡት ፣ በሚያስገርም ሁኔታ ሰውየው የካበውን ሁሉ በመረጃ በተደገፈ አስተያየት ደርምሶት አረፈው᎓᎓ ያንን ውርጅብኝ መካድ ስለማይቻል " የራስህን ሃሳብ የመግለጽ መብት አለህ" ተብሎ ሊታለፍ ተሞከረ ᎓᎓ አንድአርጋቸው ለመጀመሪያ ግዜ እጁን አወጣ ᎓᎓ አንድአርጋቸው ሲመቸው በኢትዮጵያን ካልሆነ በስተቀር በእይታ የትውልድ ሃገሩን ለመለየት አስቸጋሪ ነው ᎓᎓ ናይጄራዊ ቱጃር ሳይመስለው አልቀረም ᎓᎓ ዕድሉን ሰጠው ! በቀጥታ እንግሊዞቹ ላይ ነበር አንድአርጋቸው ያነጣጠረው᎓᎓ "እናንተ ብርቲሾች ስትባሉ፣ሁለት አይነት ዲሞክራሲ ነው ያላችሁ᎓᎓አንዱ ለዜጎቻችሁ ያለገደብ የሚሰጥ ነው᎓᎓ ሌላው በማንኪያ እየተጨለፈ ለታዳጊ አገሮች የሚሰጥ !እንደ ኢሕአዴግ ያለ አሻንጉሊታችሁንማ ፣ ነፍስ-ገዳዮች መሆናቸውን እያወቃችሁ፣ ዜጎቻቸው ላይ የሚያደርሱት ግፍ፣ጭፍጨፋ፣ በደልና ፍጅት፣ በተባዮች ላይ የሚፈፅሙት እንጂ በሰው ላይ የሚደርስ ስቃይ መስሎ አይታያችሁም ᎓᎓ እኛም ኢትዮጵያን እኮ እንደ ብርቲሽ ዜጎች ዲሞክራሲ ይርበናል ፣ ፍትህ ይጠማናል ፣እኩልነት ይናፍቀናል ᎓᎓ ገዳዩን፣ወንጀለኛውን፣አገር አጥፊውን ጉልበተኟ ገዢ እንዲህ አሰማምረው ሲያቀርቡት ትንሽ እንኳን አይሰቀጥጦትም?" ሲል ቤቱ ተረበሸ! ሰብሳቢውም ባለስልጣን ዕቅዱ ሁሉ እንደተኮላሸበት ሲረዳ ፣"ሌላ ስብሰባ አለኝ" ብሎ ተሰብሳቢውን ጥሎ ውልቅ አለ᎓᎓ ሶስታችን ክፍሉን ተቆጣርን ᎓᎓ ተሰብሳቢው እውነተኛ የበለጠ ዕውነተኛ ማስረጃ ለማግኘት ሶስታችንን ከበበን ᎓᎓የሚያስፈልገውን ማስረጃ ሁሉ ሰጥተን አድራሻ ተቀያይረን እየሳቅን ወጣን ᎓᎓ ከዚያችን ዕለት ጀምሮ ነፍሴ ከአንድአርጋቸው ጋር ተቆራኘች !ከዚያ በኋላ የትግል ጓዶች ሆንን᎓᎓ አብረን ብዙ ብዙ ቁምነገሮችን ሰርተናል᎓᎓ እሱ ቅንጅቶችን ለመርዳት ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ ከቅንጅት ባላስልጣኖች ጋር ሲታሰር በለንደን የተቃውሞ ረሀብ-አድማ ከመቱት መሃል አንዱ ነኝ ᎓᎓ ዛሬም ወንድሜ ጠላቶቹ ሕገ-ወጥ መንገድ እጃቸው ሲያስገቡት፣ ከእጃቸው ፈልቅቀን እስከምናወጣ ድረስ ከሚታገሉት መሀል አንዱ በመሆኔ ታድያለሁ᎓᎓እኔም አንድአርጋቸው ፅጌ ነኝ᎓᎓"
ምንጭ"አሻራ" መፅሄት ገፅ 20

Saturday 9 April 2016

ትግሉ ሰፊ የምሁራን ተሳትፎ ይሻል!



April 8, 2016

ኢትዮጵያ በበብዛትም ይሁን በጥራት በውጭው አለምም ይሁን በሀገር ውስጥ የሚኖሩ ብዙ ምሁራን ያፈራች ሀገር ነች። በጅጉ የሚያሳዝነው ግን በሀገሪቱና በሕዝቧ ችግር ላይ ሀሳብ ሲሰጡ ፣ ባደባባይ ሲከራከሩና ሲታገሉ የሚታዩት በጅጉ ጥቂቶች ናቸው። ርግጥ ነው ተከታታይ መንግስታት በምሁራን ላይ ያደረሱት ጥቃትና ማግለል ከፍተኛ መሆኑ ይታወቃል። በዚህም ምክንያት ብዙዎች መከራን ከህዝብ ጋር ከመጋፈጥ ይልቅ አጎንብሶ ማሳለፈን የመረጡበት ሁኔታ አለ። ቁጥራቸው ጥቂት ያልሆኑም ለግል ጥቅማቸው ቅድሚያ በመስጠት ከጨቋኝ ገዥዎች ጋር በመተባበር የሚሰሩ መኖራቸውም አይካደም። አብዛኛው ምሁራን በተለይም በብዙ የሀገሪቱ ጉዳይ ላይ ጠለቅ ያለ እውቀት ያላቸው ጭምር ሀገሪቱን ከገባችበት ማጥ ለማውጣት በሚደረገው ትግል ውስጥ እየተሳተፉ አይደለም። ይህ ዛሬ ባለው ችግርም ይሁን በታሪክ ፊት አሳዛኝ ነው።
ሀገራችን ዛሬ መስቀለኛ መንገድ ላይ ነች። የተማሩ ልጆቿ መላ እንዲመቱ በመጠየቅ ላይ ትገኛለች። ይልቁንም በሀገራችን ያለው ችግርና ሀገሪቱ እየሄደች ያለችበት መንገድና አቅጣጫ በተለይ ምሁራንን እንቅልፍ ሊነሰ ይገባል። ዕውነታው ከዚህም አልፎ የሀገሪቱን አሳዛኝና አደገኛ ሁኔታ ለመቀየር በሚደረገው ትግል ውስጥ ከፍተኛ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ግድ ይላል። የመንግስት ግፍና ሰቆቃ በበዛበትና የሀገራችን ሕልውና አደጋ ላይ በወደቀበት በአሁኑ ሰዓት ምሁራን ላለመሳተፍ ምክንያት ማቅረብ የማይችሉበት ወቅት ላይ ደርሰናል። እንደማንኛውም ሀገር ምሁራን የኢትዮጵያ ምሁራን በሀገራችን ውስጥ ሰላምና ዲሞክራሲ እንዲሰፍንና ፍትሕ የሰፈነበት ስርዓት እንዲመሰረት ሊሸሹት የማይገባ ትልቅ ሚና አላቸው።
ዛሬ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚኖሩ ዜጎች መንግስት በልማትና በልማት እያመካኘ የሚያካሂደውን ሰፊ ዝርፊያ እንዲሁም ወያኔ ሩብ ምዕተ አመት ሙሉ በብሄረሰብ እኩልነት ስም እየማለ የሚያደርሰውን ያንድ ብሄረሰብ ጉጅሌ የበላይነት ማስፋፋት እምርረው በመታገል ላይ ናቸው። መስዋዕትነቱን እየከፈሉ የሚታገሉትና የሚወድቁ የሚነሱት ወጣቶችና ምስኪን ገበሬዎች ናቸው። እነዚህ ወገኖቻችን ሕይወታቸውን ሳይቀር ሲገብሩ በየቀኑ እየሰማንና እያየን ነው። ይህንን የህዝብ ጥያቄና ትግል ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ምሁር ተመልካች ሆኖ ሊቀመጥ አይገባም። ትግሉን ከመምራት ጀምሮ እስከ ተራ ታጋይነት ባሉት ረድፎች ሁሉ ምሁራን ቀጥተኛ ተሳትፎ ሊያደርጉ ይገባል። ሰለትግሉ እቅጣጫም ሆነ ስለሀገሪቱ መጻዔ ዕድል ሃሳብ ማመንጨትና ማሰራጨት ይኖርበታል። ሀገራችን የደለቡ ችግሮቿን ተቋቁማ ፍትሕ ዲሞክራሲና እኩልነት የሰፈነባት ሀገር የሚያደርጋትን የምህንድስና ስራ አስቀድሞ ማሰብና ማመቻቸት ይኖርበታል። ርግጥ ነው ይህን መሰል ተሳትፎ የሚያደርጉ ምሁራን አሁንም አሉ። ቁጥራቸው ግን ሊሆን ከሚገባው ጋር ሲወዳደር በጅጉ አነስተኛ ነው።
ምሁርነት ከፍተኛ የትምህርት ደረጃ መቀዳጀት ብቻ እንዳልሆነ የታወቀ ነገር ነው። ምሁርነት ምሉዕ የሚሆነው መላውን የተፈጥሮ ከባቢ ከህዝብ ማህበራዊ ሕይወት ጋር አጣምሮ የሚያስብ አዕምሮን በዕውነት ላይ ለተመሰረተ ሀሳብና ዕውቀት ክብር መስጠትን ለተግባራዊነቱ መሟገትን የጨመረ ሲሆን ነው ። በመሆኑም ሁሌ እንደሚባለው ምሁርነት የጋን መብራትነት አይደለም። ምሁርነት በጨለማ ውስጥ ችቦ ሆኖ ብርሃን መፈንጠቅን ይመለከታል። ምስዋዕትነትንም ይጠይቃል።
ያለንበት ወቅት ለኢትዮጵያ ምሁራን ከፍተኛ ፈተናም ዕድልም ይዞ ቀርቧል። ይህ ልሽሽህ ቢሉት የማይሸሽ ፈተና ከመሆኑ ባልተናነሰ በታሪካችን እንድ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ የጎላ አሻራን ለማኖርም ትልቅ የታሪክ ዕድል ነው። ይህ ፈተና ከፍተኛ ያርበኝነት ስሜትንና ሀላፊነት መውሰድን ይጠይቃል። አገር በተወሳሰበ ችግር ምክንያት ወደ አረንቋ እየገባች ምንም ሳይሰሩ መቀመጥ ወይም ዝም ብሎ ከመመልከት የበለጠ ለምሁር ሂሊና የሚከብድ ነገር ሊኖር አይችልም:: በጣም ላስተዋለ ሰው እንዲህ አይነት ዝምታ ሐጢያትም ነው። በእንዲህ አይነት ፈታኝ ወቅት የኢትዮጵያ ምሁራን ሀገሪቱን ወደተሻለ አቅጣጫ እንድትሔድ ላለመታጋል ምንም ምክንያት ማቅረብ አይችሉም። ሀሳብ የሚሰራጭባቸው የሀሳብ ክርክር የሚካሔድባቸው መድረኮች ፣ አደባባዮች ፣ የመገናኛ መሳሪያ አይነቶች የፖለቲካና የሲቪክ ማህበሮች ባገር ውስጥም በውጭም ያሉት መሳተፊያ ናቸው።
ድርጅታችን አርበኞች ግንቦት 7 ምሁራን በሰፊውና እንደየፍላጎቶቻቸውና ችሎታቸው ሊሳተፉ የሚችሉባቸው በርካታ የትግል መስኮች አሉት። የሀገሪቱን ውስብስብ ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉ የጥናት ውጤቶች ፣ ሀሳቦች ፣ ምክሮችም ሆነ ቀጥተኛ የምሁራን ተሳትፎ ለማስተናገድ አመቺ ሁኔታ ያለበት ድርጅት ነን። ወደፊትም የምሁራን ተሳትፎ እንዲጎለብት ሁኔታዎችን ይበልጥ ለማመቻቸት እንሰራለን። ዽርጅታችን የሀገራችን ችግር የሚወገደውና ዲሞክራሲና የዜጎች እኩልነት የሚረጋገጠው በበሰለና ከተራ ዜጋ እስከ ብስል ምሁራን በሚያከሂዱት ክርክርና የበሰለ ሃሳብ ላይ ተመስርቶ መሆኑን ያምናል። አሁን ያለው የሀገራችን ምሁራን ተሳትፎ ደረጃ ሁላችንም ከምንጠብቀው በታች በጅጉ ያነሰ መሆኑ ሁላችንንም ከማሳዘን አልፎ የሚያስቆጭና የሚያንገበግብ ሆኖአል:: አገርና ህዝብ ድረሱልኝ እያለ በሚጣራበት በዚህ የታሪክ አጋጣሚ አይቶ እንዳላየ ሰምቶ እንዳልሰማ የተለያዩ ምክንያቶችን እየደረደሩ ማለፍ ይቻል ይሆናል። ይዋል ይደር እንጂ ለነጻነቱ ቀናዕ የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ የደረሰበትን አፈናና ጭቆና እምቢኝ ብሎ ነጻነቱን ሲቀዳጅ ግን ከታሪክ ፍርድና ከህዝብ ትዝብት ማምለጥ አይቻለም።
አርበኞች ግንቦት 7 በአገር ውስጥም ሆነ በተለያየ ምክንያት በአለም ተበትኖ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ምሁር ለወገን ደራሽነቱንና አለኝታነቱን አሁኑኑ ይወጣ ዘንድ ወገናዊ ጥሪውን ያቀርባል::
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!

Sunday 20 December 2015

አዲስ አበባዎች ሊነሱ ነው !

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የሚከተሉትን መፎክሮች አንግበው መንግስት በአገሪቱ ላይ እየወሰደ ያለውን መንግስታዊ ውንብድና ለመቃወም እየተዘጋጁ መሆናቸው ታወቀ፡፡ የውስጥ ወሬ ምንጮቻችን እነደገለፁት መቸ በይፋ እንደሚጀምሩት በምስጥጢር ተይዝዋል በማለት ክፍለ ሀገር ያሉ(በኦሮሚያ፣በአማራ፣በደቡብ፣…) የተጀመረውን ትግላቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል፡፡
ማህበረሰቡ፡- 1. በኦሮሚያና በአማራ እየተደረገ ያለው ደም ማፋሰስ ይቁም!
                2. በልማት ስም ህዝብን ከይዞታቸው ማፈናቀሉ ይቁም!
                3. መሬት የህዝብ እንጂ የመንግስት አይደለም!
                4. የብሄር ፖለቲካ ይቁም! ሆን ተብሎ ብሄርን ከብሄር የማጋጨት ሴራው ይምከን!
                5. መንግስት የከፋፍለህ ግዛው ስትራትጅውን ያቁም!
                6. በርሀብ አለንጋ እየተገረፉ ያሉ ዜጎች አስቸኳይ መፍትሄ ይሻሉ!
                7. የታሰሩ የፖለቲካና የህሌና እስረኞች ይፈቱ!
                8. የአቡነ ጴጥሮስ ሀውልት ወደቦታው ይመለስ!
                9. የፍትህ ስርአቱ ይስተካከል!
               10. መንግስት አይን ያወጣ ውሸቱን ያቁም!
               11. መሰረት የሌላቸው መግለጫዎች፣የውሸት ፕሮፖጋንዳዎች፣ዛቻና ማስፈራሪያዎች ይቁሙ! ህዝቡ እውነቱን                          የውቃል! ማንም
 አያምናችሁም!                               
               12. ኢህድግ የሚሰማ ጀሮ፣የሚያይ አይን የለውም! በእብሪት ተወጥሯል!
               13. ኢህድግ የበሰበሰ ድርጂት ነው! ህዝብን ማሰተዳደርና አገርን መምራት ተስኖታል!
               14. ታፍነን አንግዛም፣አባቶቻችን አላወረሱንም!
               15. ዝርፊያው ይቁም!ሙሰኞችና ኪራይ ሰብሳቢዎች ለፍርድ ይቅረቡ!
               16. በጎንደር ዳርቻ ለሱዳን በሚሥጥር የተሰጠው መሬት ይመለስ!
               17. አሸባሪው ህዝብ ሳይሆን መንግሰት ነው!
               18. አሰመሳይ መንግስት ሊሆን አይችልም!
               19. የአንድ ብሄር የበላይነት ይቁም!
               20. መንግስት ውሸት፣ማጭበርበር እና ሌብነትን ባገሪቱ ላይ አንግሷል!
               21. ባገሪቱ ላይ ያሉ አደገኛ እፆች(ጫት፣ሲሻ፣አሸሽ፣…) ይወገዱ! መንግስትም ከማምረት ይቆጠብ!
               22. ህገመንግስቱ ይከበር! አፋኝ ህጎች ይሻሩ!
               23. ህንፃ፣ባቡር፣… ለኛ ምናችንም አይደለም፤በቅድሚያ ነፃነት!
               24. መንግስት የግል ጥቅሙን ትቶ በአገሪቱ የወደፊት እጣ ፈንታ ላይ የጋራ ውይይት ይጥራ! ከማንኛውም ተቃዋሚ                     ሀይል ጋር ብሄራዊ እርቅ ያካሂድ!
              25. የሽግግር መንግስት ይቋቋም! ፍትሀዊ ምርጫ እንደገና ይካሄድ!
              26. ዳግመኛ ደርግን አናስተናግድም!

ተማሪዎች፣መምህራን እና የመንገስት ሰራተኞች፡-
              1. መንግስት ማህበረሰቡን ማጋጨት ያቁም!
              2. በማህበረሰቡ ላይ የሚደረገው ማዋከብ ይቁም!
              3. ፍታዊ የሀብት ክፍፍል ይኑር!
              4. በአገሪቱ ላይ ወጥ የሆኑ መመሪያች ይኑሩ!
              5. የትምህርት ጥራት ይጠበቅ!
              6. መልካም አስተዳደር እንሻለን!
              7. የታክስ ማሻሻያ ይደረግ!
              8. የደመወዝ ጭማሪ ይደረግ!
              9. የአርከን ጭማሪ ይፈቀድ!የደረጃ እደገቱ ማሻሻያ ይደረግ!
             10. የውሎ አበል፣የትርፍ ሰአት ክፍያ፣የትራንስፖርት እና የቤት አልዋንስ ይሻሻሉ!
             11. ስራ ቅጥር/ስልጣን በደብዳቤ ሳይሆን በውድድር/በብቃት ይሁን!
             12. መንግሰት የውሸት ድራማ መስረቱን ያቁም!
             13. መንግስት ከመንገድ/ከህንፃ ይልቅ በቅድሚያ ማህበረሰቡን ያልማ!
             14. መንግስት ነጋዴ ነው!
             15. መንግሰት የህዝብ አገልጋይ አንጅ ህዝብ የመንግሰት አገልጋይ መሆን የለበትም!
             16. አገሪቱ “አርቲፊሻል” እድገት ላይ መመስረት የለባትም! ማጭበርበሩ ይብቃ!
             17. ከ2 ጊዜ በላይ ታክስ እየተደረግን ነው! (ደመወዝ ሲከፈል-የስራ ግብር፣እቃ ስንገዛ-ቫት እና የሰርቪስ አገልገሎት፡፡ ስለሆነም 35%+15%+5%=55% ደመወዛችን ታክስ ይደረጋል!)  በቃ! በቃ! በቃ! በቃ! በቃ! በቃ!………………..
እነዚህን መፎክሮች በጋራ በማሰማት ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ እነዳሰቡና መንገስት ለሚወስደው ማንኛውም እንቅስቃሴ እነደማይታገሱትና የመግደል ሙከራ ካደረገም አስፈላጊውን ምላሽ እነደሚያደርጉ ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ አንደሆነ በምሬት ተናግረዋል፡፡ 
 ማንም ሀይል እነደማያደራጃቸው የገለፁ ሲሆን የአመፁ መንስኤ የመንግሰት ብልሹ አሰራር፣አፈና፣ማዋከብ፣ መግደል፣ማፈናቀል፣ግፍ፣አድሎ፣ማሰር፣የኑሮ ውድነቱ፣ፍትህ ማጣቱ፣ብሄርን ከብሄር ማጋጨቱ፣የስነ ልቦና ጫናው ተደማምረው ከፍተኛ የሆነ ትኩሳት ስለፈጠሩባቸው ከዚህ የባሰ ምን ይመጣል ወይ ሞት ወይ ነፃነት በማለት ከሰፊው የኢትዮጵያ ማሀበረሰብ ተቃዋሚዎችጋር ለመቀላቀል እነደወሰኑ ለወሬ ምነጫችን ተናግረዋል፡፡
የመንግስትን ሀይል ለመቋቋምም ሰላማዊ አመፁ ለሊት ላይ በመጀመር መንግሰትን አከርካሪውን ለመስበር አስበዋል፡፡ ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል (ሴት፣ወንድ፣ አዋቂ፣ህፃን፣አረጋውያን፣ የሀይማኖት አባቶች፣መምህራን፣የቢሮ ሰራተኞች፣ሙስሊም፣ ክርስቲያን፣ሹፌሮች፣ነጋዴዎች፣ጎዳና ተዳዳሪዎች፣ተማሪዎች….) ወደ ጎዳና መውጣት የመጀመሪያው የሰልፉ/የአመፁ ምእራፍ ነው፡፡ ማንኛውንም ንብረት ማውደም “በህግ” የተከለከለ
ነው፣ከላይ የተዘረዘሩትን መፎክሮች ማሰማት ብቻ በቂ ነው፡፡ መምህራንና የመንግስት ሰረተኞችም ከሚቀጥለው ሰኞ ጀምረው የስራ ማቆም አድማ እንደሚያደርጉም አበክረው ገልፀዋል፡፡መቸም ቢሆን ከዚህ በኋላ ትግሉ እንደማይቆም አክለው ገልፀዋል!!
በተጨማሪም ከህዝብ አብራክ የወጣውን ፌድራል ፖሊስንና መከላከያ ሰረዊትን ከጎናቸው እንዲቆም ጠይቀዋል፡፡
ሼር በማድረግ የትግሉ አጋር ይሁኑ!
ድል ለጭቁኑ የኢትዮጵያ ህዝብ!!!!!.

Friday 4 December 2015

የወገኖቻችን ስቃይ፣ ችግርና ብሶት በያለንበት ይሰማን፤ ለመፍትሔውም በጋራ እንነሳ!

 የአርበኞች ግንቦት 7 መግለጫ


December 3, 2015

በአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ሰበብ በከተማዋ ዙርያ ያሉ ወገኖቻችንን ማፈናቀል በመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የተፈፀመ ጥቃት ነው። በማስተር ፕላኑ ሰበብ የሚፈናቀሉ ገበሬዎች የሁላችን ወላጆች፣ ወንድሞችና እህቶች ናቸው። በማስተር ፕላኑ ሰበብ የምንፈናቀለው ሁላችንም ነን። ይህን መሰሪ ፕላን በመቃወም ላይ ያሉት የኦሮሞ ተወላጅ ወገኖቻችን ትግል ፍትሀዊ በመሆኑ አርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ ከጎናቸው ይቆማል።


በዚሁ ወቅት በጎንደር ሌላ አሳዛኝ ጉዳይ ተከስቷል። ህወሓት ከሶስት ሺህ በላይ ዜጎቻችንን ያጎረበት እስር ቤት በእሳት ሲጋይ ዜጎች ተቆልፎባቸው እንዲነዱ ተደርጓል። ከእሳቱ በእድል ያመለጡት በጥይት ታድነዋል። ኢትዮጵያዊያን እንዲህ ዓይነቱን ጭካኔ የሚያውቁት በፋሺስት ጣሊያን ወረራ ጊዜ ነው። ይህን ጥቃት በመቃወም ላይ ያሉ የአማራ ተወላጅ ወገኖቻችን ትግል ፍትሀዊ በመሆኑ አርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ ከጎናቸው ይቆማል።



ግፍ ያልተፈፀመበት የኢትዮጵያ ክፍል ባይኖርም ሰሞኑን በአማራና በኦሮሚያ ላይ በርክቷል። በሁለቱም የአገራችን ክፍሎች የንፁሀን ደም እየፈሰሰ ነው፤ በሁለቱም ቦታዎች የእናቶች ዋይታና እሪታ ጎልቶ እየተሰማ ነው። የህወሓት አገዛዝ የትውልድ ቦታ፣ ቋንቋና ዘር ሳይለይ በኢትዮጵያዊያን ሁሉ ላይ የተደቀነ አደጋ መሆኑ ከምንጊዜውም በላይ ዛሬ ግልጽ ሆኗል።

ለዚህ የምንሰጠው ምላሽ ምንድነው? ዛሬም ኦሮሚያ ውስጥ የሚፈፀመው በደል የኦሮሞ፤ አማራ ውስጥ የሚፈፀመው በደል የአማራ ጉዳይ አድርገን እንወስዳለን? መቸ ነው ኦሮሚያ ላይ ለደረሰው ጥቃት አማራዉ፤ አማራ ላይ ለደረሰው ጥቃት ኦሮሞው የሚቆረቆረው?

የሁላችን የጋራ ጠላት የሆነው ህወሓት መኖሩ በዘውግ የተከፋፈለውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ወደ አንድነት የሚያመጣ ታላቅ ኃይል ሊሆን ይገባል። ይህ የመከራና የመጠቃት ወቅት የምንቀራረብበት ወቅት ሊሆን ይገባል። ይህ የመከራ ወቅት በህወሓት ላይ በጋራ የምንነሳበት ወቅት ሊሆን ይገባል። ዛሬ በኢትዮጵያ ያሉ የተለያዩ ማኅበረሰቦች በሙሉ በፀረ-ህወሓት ትግል መቀናጀት ይኖርባቸዋል። ይህ ማድረግ ግዴታችን ነው።

ለችግሮቻችን መፍትሄ የምናገኘው ችግሮቹ ከተፈጠሩበት እርከን በላይ ሆነን ስናስብ እንጂ ችግሮቹ በፈጠሩበት ደረጃ ላይ ቆመን መሆን አይችልም። ችግሮቹ ከተፈጠሩበት እርከን በላይ ለመሆን አገር አቀፍ እይታ መኖሩ እጅግ ተፈላጊ ጉዳይ ነው። ኢትዮጵያን ሁሉ በተለይም የአማራና የኦሮሞ ልሂቃን ይህንን ጉዳይ አበክረው እንዲያስቡበት አርበኞች ግንቦት 7 በጽኑ ያሳስባል።

ግፍ ሞልቶ የፈሰሰበት ወቅት ላይ እንገኛለን። የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች የሆኑት ሕፃናት በፌዴራል ፓሊስ ጥይት የሚገደሉበት አሳዛኝ ወቅት ላይ ነን፤ ዜጎች በር ተዘግቶባቸው በእሳት እየጋዩ ነው። ሰፊ እና ለም የእርሻ መሬት ለሱዳን በስጦታነት ለመስጠት ዝግጁቱ የተጠናቀቀበት ወቅት ላይ ነን። 

ከአስር ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ተርቧል። በፍትህ እጦት እስር ቤቶች በንፁሃን ዜጎች ተሞልተዋል። ውሀ፣ መብራትና የቴሌፎን አገልግሎት ብርቅ ሊሆኑ ነው። ይህ ሁሉ እየሆነ ግን የሥርዓቱ አገልጋዮችና ደጋፊዎች በህንፃ ላይ ህንፃ እየገነቡ በድሀው ላይ ይሳለቃሉ። የህወሓት አገዛዝ ድህነትን፣ ችጋርን፣ ስደትን፣ የእርስበርስ ግጭቶችን እያባባሰ ኢትዮጵያን እየጋጠ የሚኖር አገዛዝ ነው። 

አገዛዙ በቀደደልን ቦይ ከተጓዝን ችግሮችን ማባባስ እንጂ ማርገብ እንኳን አንችልም። ይህንን ሥርዓት በቃህ ማለት የአማራ ወይም የኦሮሞ አጀንዳ አይደለም፤ ይህ የሁላችንም – የኢትዮጵያዊያን – ጉዳይ ነው።

ለቀምት፣ ሀረር፣ ሱልልታ እና ሌሎች በርካታ የኦሮሚያ ከተሞች ውስጥ ለደረሱ ጥቃቶች ባህር ዳር፣ ጎንደር፣ ደሴ፣ ሀዋሳ፣ መቀሌ፣ አሶሳ፣ ሁመራ፣ ጋምቤላ ውስጥ ተቃውሞ መሰማት አለበት። በጎንደርና ባህርዳር ለደረሰውም ጥቃት አዳማ፣ ጅማ፣ ሆሳዕና፣ ጅግጅጋ፣ አክሱም ላይ ተቃውሞ መሰማት አለበት። በማንኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ለሚደርሰው በደል መላዋን ኢትዮጵያ ሊያሳምም ይገባል። መከፋፈላችን መከራችን አብዝቶታል፤ የህወሓት እድሜን አርዝሟል፤ ይብቃ!

አርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ የመከራ ጊዜዓችን እንዲያጥር በዘውግ ሀረግ፣ በብሔርና እና በሀይማኖትና ሳንታጠር የወገናችን ህመም ይሰማን፤ ተሰምቶንም ለጋራ ትግል እንነሳ ይላል።

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!