Thursday 30 January 2014

የወያኔን የሚዲያ አፈና ማመከን የጊዜው አጣዳፊ ተግባር ነው :: Source " www.ginbot7.org"


 ዘረኛዉ የወያኔ አገዛዝ የአገራችንን በትረ ሥልጣን ከተቆጣጠረበት ጊዜ ጀምሮ ህዝባችን ስለራሱና ሰለአገሩ ምንም አይነት መረጃ ከአማራጭ የመገናኛ ብዙሃን ምንጮች እንዳያገኝ ያሉትን ዕድሎች በሙሉ ድርግም አድርጎ ዘግቶ ኖሮአል።
የወያኔ መሪዎችና ተሿሚዎች በየግላቸው ምንም ቁብ በማይሰጡትና ተቃዋሚዎች እንዲያከብሩት ነጋ ጠባ በሚወተውቱት የአገሪቱ ህገመንግሥት አንቀጽ 29 ዕውቅና ካገኙ የዜግች መብቶች አንዱ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ ተፈጥሮአዊ መብት ሆኖ ሳለ እየተካሄደ ያለውን የሥልጣን ብልግናና አገሪቱን እያራቆተ ያለውን ዘረፋ በመተቸታቸው ብቻ በአንድ ወቅት እንደ አሸን ፈልተው የነበሩ የነጻ ጋዜጣ አዘጋጆችና አሳታሚዎች በሽብርተኝነት ተወንጅለው ከፊሉ ከአገር እንዲሸሽ ሌላው አፉን ዘግቶ እንዲቀመጥ አለያም የፈጠራ ክስ እየተመሰረተባቸው እስር ቤት እንዲማቅቁ ተደርገዋል። አሁንም በመደረግ ላይ ናቸው። በወያኔ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽና የዜጎች መረጃ የማግኘት መብት አፈና የአሜሪካና የጀርመን መንግሥታት በየግላቸው የሚያስተዳድሩዋቸው የአሜሪካና የጀርመን ድምጽ ሬዲዮኖች እንኳ ከጥቃቱ ማምለጥ ስላልቻሉ እነሆ እስከዛሬ ያልተቋረጠ የማጥላላት ዘመቻ ይካሄድባቸዋል።
ዜጎች ሃሳባቸውን በነጻነት መግለጽ ከቻሉና ከየትኛውም መዲያ መረጃ የማግኘት መብታቸው ከተረጋገጠ ሥልጣን ላይ ውሎ እንደማያድር ጠንቅቆ የተረዳው የወያኔ አገዛዝ በዚህ የሚዲያ አፈና ተግባሩ በመቀጠል ከሰሞኑ የኢትዮጵያ ሳታላይት ቴለቪዥንና ሬዲዮን እንዲሁም ህዝብ አልፎ አልፎ ሃሳቡን ለመግለጽ በሚገለገልባቸው ጥቂት የአገር ውስጥ ህትመቶች ላይ የተለመደውን የጥቃት ጅራፉን ለማሳረፍ ታጥቆ ተነስቶአል። ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ በመረጃና ደህንነት መሥሪያ ቤቱ ተዘጋጅቶ የህወሃት ቀድሞ ታጋዳላዮች በሚቆጣጠሩትና እንደግል ንብረታቸው በሚፈነጩባቸው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ሬዲዮ የተሰራጨው ዘገባ እንደሚያመለክተው ከአሁን ቦኋላ ማንኛዉም የመንግስት ባለስልጣን፤ የገዢዉ ፓርቲ አባላትና የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ምንም አይነት ቃለመጠይቅ ለኢትዮጵያ ሳተላይት ቴለቪዥንና ሬዲዮ እንዳይሰጡ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶአል። ማስጠንቀቂያውን ተላልፎ በተገኘ ማንም ሰው ወይም ድርጅት ላይ የአሸባሪነት ወንጀል ክስ እንደሚመሰረትበትም ዛቻና ማስፈራሪያ በተለመደው የቃላት ጋጋታ ተገልጾአል።
ይህ ከሰሞኑ የወያኔ ብሄራዊ መረጃ ደህንነትና ኮሚኒኬሽን መስሪያቤት ያወጣዉ ማስጠንቀቂያ አዘል መግለጫ የሚያሳየን ነገር ቢኖር ወያኔ ኢትዮጵያ ዉስጥ ዜጎች የሚናገሩትን ፤ የሚጽፉትን፤ የሚያነቡትንና የሚሰሙትን ብቻ ሳይሆን የሚያስቡትንና ሊደግፉት ወይም ሊቃወሙት ይችላል ተብሎ የሚጠረጠረውን ሁሉ አስቀድሞ ለመቆጣጠር ፍላጎቱ ያለው መሆኑን ነው።
ከሰሞኑ መግለጫ የተለየ ነገር ቢኖር ህዝባችንን በፍርሃት አንገት ለማስደፋት ሲባል የወያኔ ፓርላማ በሽብርተኝነት የፈረጀውን ንቅናቄያችንን ግንቦት 7ንና የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴለቪዥንን በአንድነት የመፈረጅ ስልት ይፋ መደረግ መቻሉ ብቻ ነው።
የወያኔን ቁንጮዎች ጨምሮ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ይገነዘበዋል ብለን እንደምናምነው የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴለቪዥን ኢሳት የተቋቋመው የአገራቸው ጉዳይ የሚያንገበግባቸው ቅን ዜጎች ባዋጡት የገንዘብ መዋጮና በሚሰጡት ያልተቋረጠ የእውቀትና የፋይናንስ ድጋፍ ነው። ተቋሙ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ላለፉት 22 አመታት በወያኔ የሚዲያ ሞኖፖሊ ተይዞ የኖረውን የአገራችንን አየር ክልል ሰንጥቆ በመግባት ህዝባችን ስለ አገሩና ስለራሱ ጉዳይ በቂ መረጃ እንዲያገኝ በመጣር ላይ ያለ ብቸኛ መገናኛ ብዙሃን ሆኖ በማገልገል ላይ የሚገኝ ነው።
ሃቁ ይሄ ሆኖ ሳለ ለምንድነዉ ታዲያ ላለፉት ሁለት አመታት ስብሀት ነጋን ጨምሮ የተለያዩ የገዢዉ ፓርቲ ቱባ ቱባ ባለስልጣናት ሳይቀሩ በተደጋጋሚ ቀርበዉ በስነ ስርኣት የተስተናገዱበትን ይህንን ሚዲያ የወያኔ ፓርላማ ቀደም ሲል በአሸባሪነት ከፈረጀው ንቅናቄያችን ግንቦት 7 ጋር መወንጀሉ ለምን ይሆን ? መልሱ ቀላል ነው። ከአገዛዙ ያልወገኑ ማናቸውም ሚዲያዎች እንደሚያደርጉት ኢሳት ስርጭቱን ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ነጋ ጠባ በኢትዮጵያ ቴለቪዥንና ሬዲዮ የሚደሰኮረው ልማትና ዕድገት ተጠቃሚው ሥልጣንን የሙጥኝ ያሉ የቀድሞ ታጋዳላዮችና የቅርብ ዘመዶቻቸው እንጂ ህብረተሰቡ አለመሆኑን በግልጽ ከማጋለጥ ባለመቆጠቡ ጥርስ ውስጥ ገብቶአል። ከዚህም በተጨማር ለምዕራባዊያን ፍጆታና ድጋፍ ማግኛ በየአምስት አመቱ የሚደረገው የምርጫ ተውኔት ወቅት ስለተቃረበ ተቃዋሚዎች አጋጣሚውን ተጠቅመው በዚህ ሚዲያ ያብጠለጥሉኛል፤ የስልጣን ብልግናውንና የሙስናውን ጉዳይ ይዘከዝኩታል የሚል ፍርሃትና ስጋትም አለው። በእርግጥ ዝክዘካው በይስሙላ ምርጫው ላይ ምንም ለውጥ እንደማያመጣ እኛ የጉዳዩ ባለቤቶች ቀርተን ምዕራባዊያን ለጋሾችም አያጡትም። ሆኖም ግን ወያኔ ፈርቶአል ተረብሾአል። ስለዚህም ኢሳትና አሁን በአክራሪ ድርጅቶች ልሳንነት የተፈረጁት የአገር ውስጥ ህትመቶች ከምርጫው በፊት መጥፋት ይኖርባቸዋል። ያ ካልሆነ በመላው አገሪቱ የሰፈነው የሥልጣን ብልግናና የሃብት ዘረፋ የፈጠረው የኑሮ ውድነት ያስመረራቸው ሚሊዮኖች የመጪውን ምርጫ ውጤት አስታከው ሆ ብለው አደባባይ ሊወጡና የአገዛዙን የሥልጣን እድሜ ለማሳጠር ተቃዋሚዎች ለሚያካሄዱት ትግል መሳሪያ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሎ ተፈርቶአል። ግንቦት 7 የፍትህ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ከብዙ የወያኔ ጥቃትና አፈና ተርፈው አገር ውስጥ በመታተም ላይ በሚገኙ 8 መጽሄቶች እና ለኢትዮጵያዊያን ብቸኛ የመረጃ ምንጭ ሆኖ በማገልገል ላይ በሚገኘው የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴለቪዥንና ሬዲዮ ላይ የተጀመረውን አዲሱን ዘመቻ በቸልታ አይመለከተውም።
መረጃ ሃይል ነውና አገራችን ውስጥ ፍትህ እንዲሰፍን፡ በመልካም አስተዳደር እጦት ሥር እየሰደደ የመጣው ድህነት እንዲቀረፍና ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር የሚሻ ዜጋ ሁሉ ወያኔ በሚዲያ ላይ የጀመረውን ጥቃት ለማስቆም ከጎናችን እንዲሰለፍ ግንቦት 7 የትግል ጥሪውን ያቀርባል።
ወያኔ በመረጃና ደህንነት መሥሪያቤቱ አማካይነት ያስተላለፈው የሰሞኑ ማስፈራሪያና ማስጠንቀቂያ በተለይም በሰላማዊና ህጋዊ ትግል ወያኔን መቀየር ይቻላል በማለት አገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱትን የፖለቲካና የስቪክ ድርጅቶች መተንፈሻ ለማሳጣት ሆን ተብሎ የተቀነባበረ መሆኑን ህዝባችን እንዲረዳና በህዝባዊ እምቢተኝነት ሴራውን ለማክሸፍ መነሳት ጊዜው ግድ የሚል የወቅቱ አንገብጋቢ የትግል ጥሪ መሆኑን ግንቦት 7 የፍትህና የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ያስገነዝባል።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!
                                                                                               posted by A.G

Saturday 18 January 2014

ዛሬ የሚያስፈሯሯችሁን እስከ ዘላለሙ የማትሰሙበት ግዜ ይመጣልና አትፍሩ Source official site for Ginbot 7


ህወሃት የሚያራምደው የዘረኝነት ፖለቲካና፤ የተዘፈቀበት የሙስና አዘቀት ሊወጣ ከማይችልበት አዙሪት ውስት ከተውታል።ከእንግዲህ ወዲህ ለህወሃቶች የቀራቸው አንድ አማራጭ ብቻ ነው። ሁሉንም ዜጎች በዘረኝነት ሰንሰለት አስሮ ቀጥቅጦ እና አፍኖ መግዛት ቀጣዩ ቅዥታቸው ነው።
የዚህ አፍኖ የመግዛት ቅዥታቸው መገለጫም ዜጎች ህወሃት ስለሚፈፅመው ወንጀል ምንም ዓይነት መረጃ እንዳያገኙ ማድረግ አንዱ ነው።ህወሃት የሚፈፅመው ወንጀል ከህዝብ ዓይንና ጆሮ ተሠውሮ እንዲረሳ ይመኛል። ይሄን ምኞቱን እውን ለማድረግም ሌሎች ነፃ ሚዲያዎችን አሸባሪ ማለት ወይም ደግሞ ሌላ የተሰወረ አጀንዳ ያላቸው እያለ ማላዘንን ሥራየ ብሎ ተያይዘውታል። ከሰሞኑ አዲስ አበባ ውስጥ የሚታተሙ ስምንት የግል ህትመቶችን አሸባሪዎች በማለት ክስ መስርተዋል። አስቀድመው ፈርደው ከጨረሱ በኋላ ክስ መመሥረት የህወሃቶች የተለመደ የፍትህ ሥርዓት ነው። በአገሪቷ ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ግዜ ከመንግስት ቁጥጥር ውጪ ሁኖ የተቋቋመውን ኢሳትንም አሸባሪ እያሉ ሰሚ አልባ ጩኸት እየጮኹ ነው። የኢሳት ቴሌቭዥንና ሬዲዮንን የሚሰማም በአሸባሪነት ይከሰሳል እያሉ በየዜጎች ደጅ እየተንከላወሱ ለማስፈራራት እየሞከሩ ነው።
እኛ ግን እንዲህ እንላለን !!! አትፍሩ ! አትፍሩ ! አትፍሩ ! ኢሳትን ሰምታችኋል ብሎ የሚያስፈራሯችሁን ለዘላለሙ የማትሰሟቸው ግዜ እየመጣ ነው። የነፃነት ጎህ ቀዶ ሁላችን የፈለግነውን ሰምተን፤ ያልፈለግነውንም የምንተውበት ዘመን እሩቅ አይደለም። ግንቦት ሰባት የፍትህ የነፃነት እና የእኩልነት ንቅናቄም የተቋቋመው ዜጎች ያለማንም ጣልቃ ገብነት የወደዱትን ወስደው፤ የጠሉትን መተው የሚችሉበትን መንገድ ለማመቻቸት ነው። ዘረኞቹ በደምና አጥንት ታውረው ጭካኔን ከጀግንነት ቀላቅለው እኛ ብቻ ወንድ ባሉበት መንደር ሌላ ጀግና ኢትዮጵያዊ ወንድ ገስግሶ የሚመጣበት ዕለት እየደረሰ ነውና እንዳትፈሩ እንመክራችኋለን። ህወሃቶች ዜጎችን ከሰው በታች አድርገው ለመግዛት እንዲመኙ ያደረጋቸው እብሪት የሚተነፍስበት ዘመን እሩቅ አይሆንምና አሁንም አትፍሩ።
ህወሃቶች ከእነርሱ ቁጥጥር ውጪ ያሉ ነፃ ሚዲያዎችን እንደማይታገሱ የታወቀ ነው። ለምን ቢሉ የወንጀላቸው ብዛት፤ የክፋታቸው ጥልቀት ሳይነገር ተሠውሮ እንዲቀር ስለሚመኙ ነው። ይህን ምኞታቸውን እውን ለማድረግም ራሳቸው የሠረቱን ህግ ውልቅልቁን አውጥተው ያፈራርሱታል። ዜጎች መረጃ የማግኘት መብት አላቸው ተብሎ እነርሱ “ህገ-መንግስታችን” እያሉ በሚጠሩት ላይ በማያሻማ ሁኔታ የተቀመጠ ቢሆንም እነርሱ ግን ለራሳቸው ህግ መታመንን አልመረጡም። እንዲያውም እነርሱ ሞተንለታል የሚሉትን ህግ አፈር አስገብተው ራሳቸው ህግ ሆነው ተፈጥረዋል። እነርሱ ህግ ሁነው በመፈጠራቸውም በየዜጎች ደጅ እየተንከላወሱ ኢሳትን ብትሰሙ ወዮላችሁ እያሉ ያስፈራራሉ። ዜጎች ግን የሞኝ ዘፈናቸውን መልሰው መልሰው ለሚያላዝኑ ኢሕአዴጋዊያን ዛቻ የሚንበረከኩ አይሆኑም። አገራቸውን በተመለከተ ማንኛውንም መረጃ ለመስማት ያላቸውን ነፃነትም ለምናምንቴዎች አሳልፈው የሚሰጡ አይሆኑም።
ጎሬቤታችን ኬኒያ ከአስር በላይ የግል ቴሌቭዥን ጣቢያዎች አሏት።በርካታ በአጭር ሞገድና በኤፊኤም ሞገዶች የሚተላለፉ ሬዲዮኖችም አሏት። የኬኒያ መንግስት ለዜጎቹ ክብርና ፍቅር ስላለው የተቻለውን ያክል ነፃ ሚዲያ እንዲኖር ይጥራል። ለህዝቡ ክብርና ፍቅር የሌለው ህወሃት ግን በወረቀት ላይ በፃፈው ህግ ዜጎች መረጃ የማግኘት መብታቸው ያልተገደበ ነው ቢልም በተግባር ግን የዜጎችን መረጃ የማግኘት መብት ያፍናል። ነፃ ሚዲያ እንዳይፈጠር ለማድረግ፤ የተፈጠሩትንም ለማጥፋት ግዜውንና የአገሪቷን ሃብት በከንቱ ያባክናል። ህወሃት ከድሃ ጉሮሮ እየነጠቀ ኢሳትን ለማፈን በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር አባክኗል። የአገሪቷ የህግ ተቋማትም ሌቦችንና ነፍሰ ገዳዮችን መከታተል ትተው በነፃነት እንፃፍ ብለው የተነሱ ጋዜጠኞችን በማሳደድ የአገሪቷን የሥራ ሠዓትና ሃብት በከንቱ ያባክናሉ። ህወሃቶች ይሄው ናቸው። አገር፤ ወገን፤ ህዝብ የሚባል ነገር በሂሊናቸው ያልተፈጠረ፤ እነርሱ ብቻቸውን ሌላውን ተጭነው መኖር የሚፈልጉ፤ የጨካኞችና የእብሪተኞች ስብስብ መሆኑን መዘንጋት አያስፈልግም።
የተከበራችሁ ያገራችን ዜጎች !
አገራችሁን በተመለከተ መረጃ ማግኘት የዜግነት መብታችሁ መሆኑን እንዳትረሱ። ይሄም እነርሱ “ህገ-መንግስት” ብለው በሚጠሩት ላይም በግልፅ ተቀምጧል። ይሄን በህግ ደንግጎ ሲያበቃ ኢሳትንና ሌሎችን ነፃ ሚዲያዎችን መስማት አትችሉም ሲል የማውቅላችሁ እኔ ነኝና የምትሰሙትንና የምታዩትን የምመርጥላችሁ እኔ ነኝ እያለ መሆኑን አስታወሱ። ይሄ ማለት አዋቂው እኔ እንጂ እናንተማ ክፉን ከደጉ ለመለየት ገና አልደረሳችሁም ማለት መሆኑንም መገንዘብ ያስፈልጋል።መንግስት ነኝ ብሎ በአገሪቷ ጫንቃ ላይ የተቀመጠው ህወሃት-ኢሕአዴግ ህዝቡን የማያከብር ብቻ ሳይሆን ለህዝብ ያለው ንቀትም ወሰን የሌለው ሁኗል። ይሄ ዘረኛና ዘራፊ ቡድን ክብራችንን አዋርዶና አንገታችንን አስደፍቶ ሊገዛን አይገባውም። ፍርሃት ይብቃ። ህወሃት እየፈጠረ ያለው ፍራቻን መሸሸ አይገባም፤ ይሄን ፍርሃት መጋፈጥ የጀግና ተግባር ነውና ለክብራችሁና ለነፃነታችሁ ስትሉ ፍርሃቱን ተጋፈጡት እንጂ አትሽሹት።
በዚያ በጨካኞች መንደር ሁናችሁ በሠላማዊ ትግል ብቻ ለውጥ እናመጣለን ብላችሁ የተደራጃችሁ የፖለቲካ ድርጅቶችም መረጃ የማግኘት፤ መረጃ የመሰብሰብ እና የማሰራጨት መብታችሁ ነው ብለን ልንነግራችሁ አንዳዳም። በነፃ ሚዲያ መናገርም ሆነ ለማንኛውም ሚዲያ መረጃ የመስጠት ማንም የሚሰጣችሁ መብት እንዳልሆነ ታውቃላችሁ። እኛ እንደምንገምተው ኢሳትም ሆነ ሌሎች ነፃ ሚዲያዎች የእናንተም ሃብት ናቸው። ህወሃት-ኢሕአዴግ አትስሙ ወይም ደግሞ አትናገሩ ሲላችሁ ያንን የእብሪተኛ ትዕዛዝ አለመቀበላችሁን ለነፃ ሚዲያዎች መረጃ በመስጠትና ሃሳባችሁን በነፃው ሚዲያ በመግለፅ እምቢተኝነታችሁን በማሳየት ለምትመሩት ህዝብ አርአያ እንድትሆኑ ብናሳስባችሁ ደፈሩን እንደማትሉ ተስፋ እናደርጋለን። ከዚህ አንፃር ሰማያዊ ፓሪትና አንድነት ያወጡትን መግለጫ በአድናቆት የምንመለከተው መሆኑን ለማስታወቅ እንወደላን።
ለህወሃት-ኢሕአዴጎች !
ራሳችሁን ከአሸባሪ ምግባርና መዝገብ ማስፋቅ ሳትችሉ የነፃነት ፍላጎት ያላቸውን ሁሉ አሸባሪ እያላችሁ ማላዘናችሁን የምታቆሙበት ግዜ እየመጣላችሁ ነው። እናንተ ከላይ ሁናችሁ ህዝቡ ከሥር ሁኖ እናንተን ተሸክሞ ለዘላለም እንደማይኖር አበክረን ልናሳውቃችሁ እንወዳለን።በየሰው ደጅ ካድሬዎቻችሁን ልካችሁ ኢሳትን አትስሙ እያላችሁ የማስፈራራት እብሪታችሁ ረገብ የሚልበት ግዜ እየመጣላችሁ ነው። ዛሬ ህዝባችንን የእኛን ብቻ ስሙ፤ የእነርሱን አትስሙ ማለታችሁ ለህዝባችን ያላችሁን ንቀት የሚያመላክት ነው።ህዝባችንን እንደናቃችሁና እንዳዋረዳችሁ አትቀጥሉም። የነፃነትን ፍላጎት አፍናችሁ አታቆሙትም። የፍትህ ጥማታችንን በአፈሙዝ ልትገቱት አትችሉም። የእኩልነትን ጥያቄ በውሸትና በዛቻ አታዳፍኑትም። እውነት እውነት እንላችኋለን ወንጀላችሁ ሳይነገር፤ በስውር የዘረፋችሁት በአደባባይ ሳይገለጥ አይቀርም። እኛም ቀንና ማታ ለዚያ ግብ ሳናገራግር እየሰራን ነው። በአገራችን የነፃነት ጎህ ሳይቀድ ለሽፋሽፎቶቻችን እንቅልፍ፤ ለስጋችንም ዕርፍት አይሆንም። የዘረኞችና የዘራፊዎች ጀንበር ሳትጠልቅ፤ የእኩልነት ናፋቂዎች ጎህ ሳትቀድ አናርፍም። ያነገታችሁት መሣሪያ የሸንበቆ ምርኩዝ እስከ ሚሆን የጀመርነውን ትግል ዕለት ዕለት እያጎለበትነው እንቀጥላለን።
ህወሃት-ኢሕአዴጎች ሆይ ስሙ! ይሄን ህዝብ ከሚችለዉ በላይ ገፍታችኋታል። ህዝቡም ሊሸከማችሁ ከሚገባ በላይ ተሸክሟችኋል።እንዲህ ህዝባችንን መፈናፈኛ አሳጥታችሁ እና እስከ ልጅ ልጆቻችሁ ረግጣችሁ ለመግዛት ያለማችሁት ህልም በህልምነቱ ብቻ እንደሚቀር ቅንጣት ታክል ጥርጣሬ አይግባችሁ። ትግላችን ጥሩ መሠረት ይዟል። ከዚህ በኋላ ወደ ኋላ የሚመልሰን ምድራዊ ኃይል የለም።እውነት እውነት እንላችኋለን ለዘላለም ኢትዮጵያዊያንን አዋርዳችሁ የመግዛት ህልማችሁ ቅዥት መሆኑን ደግመን ልንነግራችሁ እንወዳለን።
በህወሃት-ኢሕአዴግ ውስጥ ሁናችሁ የነፃነት፤ የፍትህ እና የእኩልነት ጥያቄያችንን የምትጋሩን ወገኖቻችን እሰክ አሁን የምታደርጉት የውስጥ ትግል ፍሬ እያፈራ ነው። ፍሬውን በራሪ ወፍ እንዳይለቅመው የተለመደው ጥንቃቄ እንዳይለያችሁ ይሁን። አሁን ህዝቡ መረጃ እንዳያገኝና፤ መረጃ እንዳይሰጥ የሚሞከረው ሙከራ ህገ-መንግስት ተብየውን የሚጥስ መሆኑን ታውቃላችሁ። ይሄን ካድሬው ሁሉ እንዲገነዘበው የውስጥ ትግሉ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል። ራሱ ያወጣውን ህገ መንግስት አፈራርሶ ከትቢያ የሚቀላቅል ቡድን በምን ሞራል ብቃት ነው ሌላውን ህገ-መንግስቱን ሊንዱ ነበር እያለ የሚከሰው ? በኢትዮጵያዊያን ላይ የተጫነው ህገ-መንግስት በህወቶች ሲፈርስ ትክክል ፤በሌላው በተግባር እንዲውል ሲጠየቅ ደግሞ ስህተት ሁኖ በአሸባሪነት የሚያስከሥሥ መሆኑን ግንዛቤ መጨበጥ ይጠቅማል።
በመጨረሻም በህወሃት-ኢሕአዴግ የጭቆና ቀንበር ሥር ለምትንገላቱ ወገኖቻችን ሆይ ! አትፍሩ። ይህን የሚያስፈራራችሁን አካል እስከ መጨረሻው የማትሰሙበት ዘመን እየመጣ ነው። አሁን ፍርሃታችሁን ግደሉት።የምትሰሙትንና የምታዩትን እኔ ነኝ የምመርጥላችሁ ከሚል እብረተኛ እጅ ራሳችሁን ለማላቀቅ የግንቦት ሰባት ንቅናቄ እያደረገ ያለውን የነፃነት፤ የፍትህና የእኩልነት ትግል ተቀላቀሉ።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!     

                                                                                                    posted by A.G

Thursday 16 January 2014

የኢትዮጵያን ታሪክ ጥላሸት የመቀባት አባዜ (ፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም) Source ECADF

January 16, 2014
ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም
ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ
ጥር 7 ቀን 2006 ዓ.ም
በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ያለው ገዥው አካል በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ ንጉስ የነበሩት የዳግማዊ አጼ ምኒልክ መቶኛ የሙት ዓመት በዚህ በያዝነው ዓመት (በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር) እየተከበረ ባለበት ወቅት ሙሉ ጊዜውን በመስጠት ንጉሱ የሰሩትን ታላቅ ስራ ሁሉ በማጣጣል እና ጥላሸት በመቀባት ዘመቻ ላይ በመጠመድ ታሪክ የማጠልሸት ድራማውን በመተወን ላይ ይገኛል፡፡ የታሪክ ማጠልሸት ዘመቻው በዋናነት እየተከናወነ ያለው ለገዥው አካል ቅርበት ባላቸው ታማኝ ሎሌዎች፣ የጥቅም ተጋሪዎች እና የእራሳቸው ስብዕና በሌላቸው አሻንጉሊቶች አማካይነት ነው፡፡ ገዥው አካል ሲያስነጥሰው መሃረብ ይዘው በሚቀርቡ አጎብዳጆቹ አማካይነት የጥላቻ መርዛማ ቃላትን፣ የሚቆጠቁጡ ባዶ ዲስኮሮችን እና እርባናየለሽ ምዕናባዊ ስዕል በአዕምሮው ላይ እየፈጠረ አጼ ምኒልክ የግዛት ማስፋፋት ጥማታቸውን ለማርካት ሲሉ በዜጎች ላይ የጭካኔ ተግባራትን እንደፈጸሙ በማስመሰል ለምንም የማይጠቅሙ እርባናየለሽ እና ተራ አሉባልታዎችን በማሰራጨት ላይ ይገኛል፡፡
የገዥው አካል ድንጉላ አገልጋዮች በማናቸውም የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በመሰማራት ታሪካዊ ቅጥፈቶችን፣ አሳሳች ዘገባዎችን፣ የሀሰት ታሪክ ፈጠራዎችን፣ ሆን ተብሎ በሀሰት ላይ የተመሰረቱ መረጃዎችን እና ነጭ ውሸቶችን እንደ በቀቀን እየደጋገሙ በማሰራጨት ላይ ይገኛሉ፡፡ የዕኩይ ዓላማው አራማጆች በታላቁ የኢትዮጵያ መሪ ላይ ግነታዊ ኩምክና በመስራት፣ በማዋረድ እና እውነተኛውን ስብዕናቸውን ጥላሸት በመቀባት የስሜት ፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ውስጥ በመዘፈቅ ጌቶቻቸውን ለማስደሰት በታለመ ዕኩይ ምግባር ላይ ተጠምደው ይገኛሉ፡፡ የታላቁ መሪ ነብስ ከስጋቸው ከተለየች ከአንድ መቶ ዓመታት የጊዜ ቆይታ በኋላ የተቀበረን ጉዳይ በማንሳት ታላቁን መሪ ሰይጣናዊ ስብዕና እንደነበራቸው ለማስመሰል በማሰብ የዕኩይ ምግባር ጎተራዎቹ የቻሉትን ያህል ጥረት ለማድረግ ሞክረዋል፡፡ አቶ መለስ ዜናዊ በህይወት ከተለዩ ሁለት ዓመታት እንኳን ሳይሞላቸው የዕኩይ ምግባራት ቋቶቹ የኢትዮጵያ አዳኝ መልዓክ ሊያደርጓቸው ይፈልጋሉ፡፡The regime wants to completely overwrite the history of Atse Menelik.
በአሁኑ ጊዜ በዳግማዊ አጼ ምኒልክ ላይ በተከፈተው የገፍ ወይም የኃይል የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ወይም ደግሞ የአጼ ምኒልክን የሙት መንፈስ ደጋግመው በማንሳት ፍጹም ጥላቻ እና የጥላቻ አመለካከት እንዲንሰራፋ በገዥው አካል ስልታዊ እና የተቀነባበረ ዘመቻ የማካሄድ አመክንዮ ለማንም ቢሆን ሊደንቅ አይገባም፡፡ ሀቁ አንድ እና አንድ ብቻ ነው፡፡ የኸውም የምኒልክን ስም ጥላሸት በመቀባት (ሰይጣናዊ ስብዕና በመስጠት) በሚሽከረከር ጉዳይ ላይ ብቻ የሚቆም ጉዳይ አይደለም፡፡ ነገር ግን በቅርቡ በህይወት የተለዩትን የገዥውን አካል የአለቆች ሁሉ አለቃ (Capo di tutti capi) አቶ መለስ ዜናዊን በመላዕክነት ቀብቶ ለማቅረብ የታቀደ ዕኩይ ምግባር ነው፡፡
ዳግማዊ ምኒልክን ጥላሸት የሚቀቡ ሙትመንፈሶች፣
በዳግማዊ አጼ ምኒልክ ላይ እየተካሄደ ያለው ከፍተኛ ጥላሸት የመቀባት የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ያነጣጠረው የኢትዮጵያን ታሪክ በመፋቅ በአቶ መለስ ዜናዊ የመላዕክነት የህይወት ታሪክ (የመላዕክነት ትረካ) በመተካት የታላቋን ሀገር ትክክለኛ ታሪክ እንደገና ለመጻፍ፣ አዛብቶ ለመጻፍ፣ ገልብጦ ለመጻፍ፣ አወዛግቦ ለመጻፍ፣ በመቀባባት የሚያምር አስመስሎ ለማቅረብ እና እውነተኛውን ታሪክ ለማስወገድ በመደረግ ላይ ያለ ከንቱ ሙከራ ነው፡፡ የአጼ ምኒልክን ታሪክ በመሰረዝ የዘመናችን የ”አፍሪካ ታላቁ መሪ” በማለት የመለስ ዜናዊን ታሪክ ለመጻፍ ይፈልጋሉ፡፡ በሀሰት እምነት ላይ በመመስረት መለስ “አዲሱ የአፍሪካ መሪ ዝርያ“፣ መለስ “የዴሞክራሲያዊ ልማታዊ መንግስት ቀያሽ”፣ መለስ “በዓለም አቀፋዊ የሙቀት እና የአየር ጸባይ ለውጥ የአፍሪካ ጠበቃ”፣ መለስ “ከጂ-8 እና ጂ-20 መሪዎች ጋር በመሆን ክርናቸውን የሚያሳዩ አፍሪካዊ መሪ”፣ መለስ “የቻይና-አፍሪካ የትብብር መድረክ የቤጂንግ ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ጉባኤ ሊቀመንበር”፣ መለስ የሶማሌ ጅሃዲስቶች እና አሸባሪዎች አስወጋጅ”… ተብለው ከእውነተኛ ስብዕናቸው ውጭ በሆነ መልኩ እንዲመለክባቸው ይፍልጋሉ፡፡
የታላቁን መሪ የዳግማዊ ምኒልክን ስብዕና ጥላሸት በመቀባት አቶ መለስን ቅብዓ መልዓክ (የተቀባ መልዓክ) ለማድረግ ይፈልጋሉ፡፡ ለመሆኑ አጼ ምኒልክን ጥላሸት የሚቀቧቸው ለምንድን ነው? ምክንያቱም አጼ ምኒልክ በአመራር ጥበባቸው እና በትግላቸው ግጭትን በመፍጠር ሲናቆሩ ከነበሩት ባላባቶች፣ ለስልጣን ብቻ ከሚቋምጡ ከተለያዩ አካባቢያዊ ንጉሶች፣ ከተለያዩ ልዕልቶች የቅምጥል የአገዛዝ ስርዓት፣ እና ከጎጣዊ ምስለኔዎች የተበታተነ አገዛዝ በማላቀቅ ዘመናዊቷን የአፍሪካ ብሄር ታላቋን ኢትዮጵያን በመመስረታቸው ብቻ ነው፡፡ የዕኩይ ምግባር አራማጆች አጼ ምኒልክን ጥላሸት ይቀቧቸዋል፣ ምክንያቱም ምኒልክ ታላቆቹን የአውሮፓ ኢምፔሪያሊስት ኃያላን በጦር ሜዳ ውሎ በማሸነፍ አንጸባራቂ ድል በመቀዳጀት የኢትዮጵያን ዘለቄታዊ ነጻነት ያጎናጸፉ እና የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ያስከበሩ ጀግና መሪ በመሆናቸው ነው፡፡ ጥላሸት ይቀቧቸዋል ምክንያቱም ምኒልክ እውነተኛ የአፍሪካ መሪ በመሆናቸው ነው፡፡ የአጼ ምኒልክን ስም በማጥፋት እና ለኢትዮጵያ ህዝብ ያበረከቱትን የውርስ ትሩፋታቸውን በማንቋሸሽ ለአቶ መለስ ክብር ለመስጠት እና ከእርሳቸው የሚገኘውን ውርስ ብጹዕ/ቅዱስ ለማድረግ ይፈልጋሉ፡፡
ገዥው አካል የአጼ ምኒልክን ታሪክ በእራሱ ታሪክ ለመተካት ይፈልጋል፡፡ አጼ ምኒልክ የባቡር ሀዲድ በመዘርጋት የመጀመሪያው አፍሪካዊ መሪ ነበሩ፡፡ ይህንን አንጸባራቂ ታሪክ በመለወጥ አቶ መለስ ረዥም፣ ቆንጆ እና ቀላል የባቡር ሀዲድ ሲስተም በኢትዮጵያ ለማምጣት የመጀመሪያው መሪ ነበሩ በማለት የታሪክ ባለቤትነት ሽሚያን ለማጎናጸፍ ይፈልጋሉ፡፡ አጼ ምኒልክ የስልክ እና የቴሌግራፍ አገልግሎትን በአፍሪካ አህጉር በማስተዋወቅ የመጀመሪያው አፍሪካዊ መሪ ነበሩ፡፡ እ.ኤ.አ በ1889 አሌክሳንደር ግራህም ቤል “የድምጽ መነጋገሪያ መሳሪያ” የፓተንት ዕውቅና ካገኙበት 13 ዓመታት በኋላ እና በአጼ ምኒልክ ቤተመንግስት የመጀመሪያው የስልክ መስመር በተዘረጋበት ጊዜ በቴክኖሎጂው ሁኔታ ጭንቀት ውስጥ ገብተው የነበሩት የቤተክህነት ሰዎች ይህ የሰይጣን ስራ ነው በማለት ንጉሱ እንዲያስወግዱት በጠየቋቸው ጊዜ አጼ ምኒልክ ለቴክኖሎጂው ጠቀሜታ ካላቸው ጽኑ እምነት አኳያ ሳያስወግዱት ቀርተዋል፡፡ በአስርት ዓመታት ጊዜ ውስጥ አጼ ምኒልክ አዲስ አበባን በምስራቅ ኢትዮጵያ ከምትገኘው የሀረር ከተማ ጋር የሚያገናኝ የስልክ መስመር በመዘርጋት መርቀው ከፈቱ፡፡ ያንን አንጸባራቂ ታሪክ ወደ ጎን በማለት የአሁኖቹ ገዥዎች በኢትዮጵያ ዘመናዊ የመገናኛ ቴክኖሎጂ ሲስተምን በኢትዮጵያ ያመጡ አቶ መለስ ዜናዊ እንደሆኑ አድርገው ያቀርባሉ፡፡ እውነታው ግን በተገላቢጦሽ  በአፍሪካ የስልክ እና የቴሌግራፍ መስመር በመዘርጋት ግንባርቀደም የነበረችው ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከአፍሪካ በመጥፎ የተንቀሳቃሽ ስልክ እና የኢንተርኔት አግልግሎት አጠቃቀም ሳቢያ በመጨረሻው እረድፍ ላይ ትገኛለች፡፡ ባለፈው ሳምንት የዎል ስትሪት መጽሄት/Wall Street Journal እንደዘገበው በኢትዮጵያ ውስጥ አርሶ አደሮች የተንቀሳቃሽ ስልኮች ቢይዙም “ችግሩ የግንኙነት መስመር ለማግኘት ብዙ ማይሎችን (ኪሎሜትሮችን)መጓዝ ይጠበቅባቸዋል፡፡“ በማለት የችግሩን አሳሳቢነት አመላክቷል፡፡ ኢትዮጵያ በመጥፎ የኢንተርኔት አገልግሎት አጠቃቀም ከአፍሪካ ከመጨረሻዎቹ ሀገሮች በሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡
የዘመኑ ገዥዎቻችን አጼ ምኒልክ የሴቶችን ጡት ቆርጠው የሚጥሉ ጨካኝ ንጉስ እንደሆኑ አድርገው ታሪክን አዛብተው ለመጻፍ ይፈልጋሉ፡፡ ጨካኝነት ከተነሳ ዘንድ ከአቶ መለስ ዜናዊ የበለጠ ጨካኝ እና አረመኔ ይኖራልን? አቶ መለስ እራሳቸው እ.ኤ.አ በ2005 በተደረገው ሀገራዊ ምርጫ መጭበርበር ምክንያት ተቃውሟቸውን ለመግለጽ በወጡ ያልታጠቁ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ለአነጣጥሮ ተኳሽ ጦራቸው ትዕዛዝ በመስጠት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲገደሉ አድርገዋል፡፡ ይህንን እልቂት አስመልክቶ በእራሳቸው በአቶ መለስ ልዩ ትዕዛዝ ጉዳዩን እንዲያጣራ የተሰየመው የአጣሪ ኮሚሽን ምርመራውን አካሂዶ ባቀረበው ዘገባ መሰረት በአቶ መለስ ቀጥታ ትዕዛዝ እና ቁጥጥር አማካይነት የፖሊስ እና የደህንነት ኃይሎች በዕቅድ ተይዞ እና ሆን ተብሎ ታስቦበት 193 ሰላማዊ ሰዎች እንዲገደሉ እና ሌሎች 763 ሰዎች ደግሞ ከባድ ቁስለኛ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡ እ.ኤ.አ በ2004 አቶ መለስ እራሳቸው ለታጣቂዎቻቸው ትዕዛዝ በመስጠት በምዕራብ ኢትዮጵያ በጋምቤላ 400 ሰላማዊ ዜጎች እንዲያልቁ አድርገዋል፡፡ ኦጋዴን እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የተካሄደውን የአየር ድብደባ እና መንደሮችን በማቃጠል የጥቃት ሰለባ ያደረገው ወንጀል  የተፈጸመው በአቶ መለስ ስልጣን ልዩ ትዕዛዝ ነበር፡፡ በአቶ መለስ ትዕዛዝ በኦጋዴን ታጣቂ ኃይሎች ሴቶችን አስገድደው ደፍረዋል፣ መንደሮችን አቃጥለዋል፣ ህዝቡን በሽብር ቆፍን ውስጥ ለመሸበብ ሲባል “የመቀጣጫ ግድያዎችን” ማለትም በህዝብ ፊት በአደባባይ በስቅላት እንዲሁም ጭንቅላትን ቆርጦ የመጣል ወንጀሎች እንዲፈጸሙ ተደርጓል፡፡ የተባበሩት መንግስታት የሂዩማን ራይትስ ዎች ተሟጋች ዳይሬክተር/United Nations Advocacy Director for Human Rights Watch ስቴቭ ክራውሻው በኦጋዴን አካባቢ  በሰላማዊ ዜጎች ላይ የተፈጸመውን ወንጀል “ትንሿ ዳርፉር” በማለት አመሳስለው ገልጸውታል፡፡
ገዥዎቻችን አጼ ምኒልክን የኦሮሞ ህዝቦች ጠላት እንደሆኑ አድርገው ታሪክን በመበረዝ የታሪክ ድሪቶ አቀነባብረው እንደገና የጎደፈ ታሪክ ለመጻፍ ይታትራሉ፡፡ አቶ መለስ በህይወት ቢኖሩ ኖሮ እሳቸው እና የዕኩይ ምግባር አጋሮቻቸው በኦሮሞ ህዝብ ላይ እስከ አሁን ድረስ ያልተነገረውን እና ለመናገር የሚዘገንነውን በሰው ልጆች ላይ የፈጸሙትን ወንጀል ወደ ፍትህ አደባባይ በማቅረብ እንዲታይ ለማድረግ ከበቂ በላይ መረጃዎች አሉ፡፡ እ.ኤ.አ በ2012 ፍሪደም ሀውስ/Freedom House የተባለው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ባቀረበው ዘገባ መሰረት አቶ መለስ እና አገዛዛቸው በኦሮሞ ህዝብ ላይ ሰፊ የሆነ የአድልኦ እና የጭቆና መረብ በመዘርጋት ተግባራት ላይ ተጠምደው ቆይተዋል፡፡ አቶ መለስ የኦሮሞ ነጻነት ግንባርን እንቅስቃሴ በመገደብ ብዛት ያላቸው ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ የሚጠረጠሩ የድርጅቱን አባላት እና መሪዎችን ከህግ አግባብ ውጭ በቁጥጥር ስር በማዋል በማጎሪያ እስርቤት አስገብተው ሲያሰቃዩ ቆይተዋል፣ አሁንም በመሰቃየት ላይ ይገኛሉ፡፡ እ.ኤ.አ በ2001 የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት የነበሩት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ስልጣናቸውን ሲለቁ እንደተናገሩት “ወደ 25,000 የሚሆኑ የኦሮሞ ህዝቦች ከኦሮሞ ህዝቦች ነጻነት ግንባር ጋር በተያያዘ የገዥው አካል ክስ ምክንያት በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች እና በአዲስ አበባ ከተማ እስር ቤቶች ታስረው በመማቀቅ ላይ ነበሩ፡፡” በማለት ይፋ አድርገዋል፡፡ የመለስ የትግል ጓድ እና የቀድሞው የመከላከያ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ስዬ አብርሃ በሚያስገርም ሁኔታ እንደተመለከቱት “ቃሊቲ እስር ቤት ኦሮምኛ ይናገራል፣ በዚሁ ግቢ በአንድ በመቶዎች የሚቆጠሩ እስረኞችን በሚይዝ ካምፕ ውስጥ 99 በመቶ የሚሆኑት እስረኞች ኦሮሞዎች ናቸው፡፡ አብዛኞቹ እስረኞች ደግሞ የታሰሩበት ምክንያት ምን እንደሆነ አያውቁም፣ ሆኖም ግን የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ተጠርጣሪ በመባል ዓመታትን በእስር ቤት በማስቆጠር ላይ ይገኛሉ፡፡“ በማለት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡
እ.ኤ.አ በ2006 ጂሃዲስቶች (አሸባሪዎች) የሶማሌን አገር ወረዋታል እና የሶማሌ መንግስት ጣልቃ ገብቸ ጂሃዲስቶችን እንዳስወጣለት “ጋብዞኛል” በሚል ተንኮልን ያዘለ ሰበብ ምክንያት አቶ መለስ በሶማሌ አገር ላይ ወረራ አካሂደዋል፡፡ አቶ መለስ በቴሌቪዥን ቀርበው እንዲህ ብለዋል፣ “የአገራችንን ሉዓዋላዊነት ለማስከበር እና በእስልምና ፍርድ ቤቶች ህብረት እና በሌሎች ጸረ ኢትዮጵያ ኃይሎች በመታገዝ የሚያደርሷቸውን ተደጋጋሚ አደጋዎች ለመግታት ሲባል የኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት ወዳልፈለገው ጦርነት እንዲገባ ተገድዷል፡፡“ በተመሳሳይ መልኩ በዴሴምበር 27 2006 የአቶ መለስ ሰራዊት እና ታንኮች የሞቃዲሾን ከተማ ወረሩ፡፡ እ.ኤ.አ በኦገስት 2007 የአቶ መለስ ሰራዊት በሶማሌ ውስጥ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ተገታ፣ በሰው ህይወት ላይ የደረሰው ኪሳራ አስደንጋጭ ነበር፡፡ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን የሶማሌ ዜጎች ህይወት የተቀጠፈ ሲሆን ከ870,000 በላይ የሚሆኑት ዜጎች ደግሞ ሞቃዲሾን ለቀው ለመሰደድ ተገደዋል፡፡ በ2006 በሞቃዲሾ ከተማ ወደ 1.2 ሚሊዮን ገደማ የሚሆን ህዝብ ነበር፡፡ ከአቶ መለስ የሶማሌ ወረራ በኋላ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች “ከአፍሪካ በጣም አስቀያሚ አስከፊ የሰብአዊ መብት ሁኔታ ያለበት“ በማለት የሶማሌን የሰብአዊ መብት አያያዝ በተጨባጭ ገልጸውታል፡፡
አጼ ምኒልክ ከአውሮፓውያን ወራሪ ኃይሎች ጋር የመከላከል ጦርነትን በማካሄድ በድል አድራጊነት ተወጥተዋል፡፡ አጼ ሚኒልክ የአውሮፓ ኃያል ከሚባል አገር ጋር ጦርነት በማድረግ በጦር ሜዳ ድል አድርገው ወራሪው ኃይል በመጣበት እግሩ ጓዙን ጠቅልሎ እንደ ውሻ ጅራቱን በእግሮቹ መካከል ወትፎ እንዲመለስ በማድረግ በአፍሪካ ታሪክ የመጀመሪያው መሪ መሆናቸው የሚካድ ጉዳይ አይደለም፡፡ አጼ ምኒልክ ወራሪውን የኢጣልያንን ጦር አምባላጌ እና መቀሌ ላይ ድል አድርገዋል፡፡ እንዲሁም እ.ኤ.አ በ1896 አድዋ ላይ ወሳኙን ፍልሚያ በማድረግ የአድዋን ጦርነት በድል አድራጊነት ተወጥተዋል፡፡ “ኋላቀር አፍሪካውያን ጥቁሮች” ወታደሮች  ኃያሉን የአውሮፓ ኢምፔሪያሊስት የጦር ኃይል ያሸንፋል የሚል እምነት በማንም አውሮፓዊ የተገመተ አልነበረም፡፡ አጼ ምኒልክ በዘመናዊ መሳሪያ ትጥቅ፣ በስልት እና በቁሳቁስ አቅርቦት በዘመኑ በጣም የተጎዱ መሪ ቢሆኑም ቅሉ የብሩህ አዕምሮ ባለቤት እና ወታደራዊ ስልት የሚያውቁ በመሆናቸው ውጊያውን በማካሄድ ጦርነቱን አሸንፈው በአንጸባራቂ ድል በመታጀብ የነጮችን የበላይነት እና አይበገሬነት ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ በማስወገድ ለጥቁር ህዝቦች በአጠቃላይ ለአፍሪካውያን ደግሞ በተለይ የኩራት ፈርጥ ለመሆን በቅተዋል፡፡ ብዙ የአውሮፓ ኃያላን አገሮች አጼ ምኒልክን በማታለል እና በማጭበርበር ከኢትዮጵያ ግዛት ቆርሰው በመውሰድ ኢትዮጵያን ቅኝ ተገዥ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ1889 አጼ ምኒልክ  በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የሚገኙ ግዛቶችን አስመልክቶ ከኢጣሊያ መንግስት ጋር የውጫሌ ስምምነትን አጸደቁ፡፡ በውል ስምምነት ሰነዱ የኢጣሊያንኛው ትርጉም ከኢትዮጵያ የአማርኛ ትርጉም ጋር የማይመሳሰል መሆኑን አጼ ምኒልክ እንደተገነዘቡ እና ኢትዮጵያ በኢጣሊያን ጠባቂነት የሚለውን ሀረግ ሲመለከቱ የውል ስምምነቱን በማውገዝ አፈረሱት፡፡
የገዥው አካል አፈቀላጤዎች አቶ መለስ ኢትዮጵያ የአህጉሩ ታላቅ አገር እንድትሆን ጥረት ያደረጉ እና የአህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ መሪ እንደሆኑ በማድነቅ እና ስብዕናቸውን ከፍ ከፍ በማድረግ የአሁኑን የኢትዮጵያ ታሪክ ደልዘው በእርሳቸው ተተክቶ እንዲጻፍ ነው በመዋተት ላይ የሚገኙት፡፡ አቶ መለስ የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት እና ሉዓላዊነት ያስከበሩ መሪ እንደሆኑ አድርገው ለማሳየት ይፈልጋሉ፡፡ እውነታው ግን የተገላቢጦሹን ያመላክታል፡፡ እ.ኤ.አ ከ1998-1999 ድረስ የባድሜን የግዛት ወሰን ለማስከበር በተካሄደው የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ጦርነት የአቶ መለስ ጦር የ80,000 ኢትዮጵያውያንን ህይወት ያለምንም ወታደራዊ ስልት በጭዳነት ለመስዋዕትነት ዳርጎ ወታደራዊ ድልን ተቀዳጅቶ ነበር፡፡ በወገኖቻችን የህይወት እና ንብረት መስዋዕትነት የተገኘውን ድል ሰራዊቱ ገና አጣጥሞ ሳይጠግብ የኢትዮጵያው መሪ አቶ መለስ ከመቅጽበት በመገለባበጥ ባድሜን በዓለም አቀፋዊ የስምምነት ውል በማስቀየድ ለኤርትራ መንግስት ቡራኬ ብለዋል፡፡ በምንም ዓይነት መልኩ በየትኛውም አገር አንድ ወታደራዊ ኃይል እጅግ ከባድ መስዋዕትነትን ከፍሎ ያገኘውን አንጸባራቂ ድል ለተሸናፊው ጠላቱ በፈቃደኝነት መልሶ የሰጠበት የጦርነት ታሪክ የለም፣ ተመዝግቦም አያውቅም፡፡ እ.ኤ.አ በ1991 ወታደራዊውን አምባገነን ደርግን በትጥቅ ትግል ካስወገዱ በኋላ በአሜሪካ መንግስት አደራዳሪነት የሽግግር ስምምነቱ በሚፈረምበት ወቅት እኒሁ የኢትዮጵያው መሪ አቶ መለስ በኤርትራ የወሰን ግዛት ዳርቻ ላይ የምትገኘውን ከቀይ ባህር ጋር በመግቢያ እና በመውጫነት ለኢትዮጵያ ህዝብ የባህር በር በመሆን አገልግሎት የምትሰጠውን የአሰብን ወደብ ወደ ኢትዮጵያ ግዛት እንድትካለል የቀረበውን ሀሳብ አልቀበልም በማለት አሁንም በድጋሜ ለኤርትራ መንግስት ቡራኬ በመስጠት ይደልዎ ብለዋል፡፡ አቶ መለስ የኢትዮጵያን ግዛት ለባዕድ ኃይል በመስጠት ታላቋን አገር ወደብአልባ በማድረግ በፈጸሙት የአገር ክህደት ወንጀል ብቸኛው ተጠያቂ ናቸው፡፡ አሁንም ተከታታይነት ያለውን የትራጄዲ ድራማ በመቀጠል በሚስጥር በተደረጉ ስምምነቶች የይስሙላው ፓርላማ ለስሙ እንኳ መከረበት ሳይባል ምንም ሳይታሰብበት በጥድፊያ እኒሁ የኢትዮጵያው “መሪ” አሁንም የኢትዮጵያ አንጡራ ግዛት የሆነውን መሬት ለሱዳን መንግስት እንደ የገና ስጦታ የእጅ መንሻ ቡራኬ አድርገውታል፡፡ እኒሁ የኢትዮጵያው መሪ አቶ መለስ በድብቅ እና ታማኝነት በጎደለው መልኩ የአገሪቱን እጅግ በጣም ለም የሆነውን በሚሊዮኖች ሄክታር የሚቆጠር መሬት ዕዳቸውን እንኳ ውል ባለው መልክ ለመክፈል ለማይችሉ የአየር ባየር ጭልፊት ነጋዴዎች አሁንም ለእጅ መንሻ አቅርበዋል፡፡
አጼ ምኒልክ የኢትዮጵያን አንድነት በማጠናከር ዘመናዊ የመንግስት መዋቅር ዘርግተዋል፡፡ አቶ መለስ ግን ምዕናባዊ ዘመናዊነትን አምጥተዋል፡፡ አቶ መለስ ያለሐኪሞች እና መድኃኒት ሆስፒታል ገንብተዋል፡፡ በአንድ ወቅት ሐኪሞች አያስፈልጉንም በማለት በይፋ ተናግረዋል፡፡ ብቃት ያላቸው የዩኒቭርስቲ መምህራን እና ፕሮፌሰሮች፣ መጻህፍት፣ ቤተ መጻህፍት፣ ወይም ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ሳይኖር ዩኒቨርስቲዎችን ገንብተዋል፡፡ የመጸዳጃ ሲስተም የሌላቸውን ህንጻዎች ገንብተዋል፡፡ አጼ ምኒልክ ኢትዮጵያን የምዕራቡ ዓለም ስልጣኔ ትሩፋት ተቋዳሽ እንድትሆን አድርገዋል፡፡ አቶ መለስ “ልማታዊ መንግስት” የሚል እርባናየለሽ ህልዮት ከምስራቅ ኢስያ ሀገራት አምባገነኖች ኮርጀው በማምጣት ኢትዮጵያን ወደ ኋላ መልሰዋታል፡፡ እ.ኤ.አ በ1991 ስልጣን ከያዙ በኋላ አቶ መለስ ዘመናዊውን የኢትዮጵያ መንግስት አወቃቀር በማፈራረስ ወዲያውኑ አገሪቱን ክልል እየተባለ በሚጠራው ወይም የአፓርታይድ አይነት ባንቱስታንስ ወይም ክልሊስታንስ የተባለ የመከፋፈል ተልዕኮውን አጠናቀቀ፡፡ አቶ መለስ በሀሰት ላይ በመመስረት ባለሁለት አሀዝ የኢኮኖሚ ዕድገት አስመዝግበናል፣ እና “ኢትዮጵያ ነዳጅ ወደ ውጭ ከማይልኩ የሰብ ሰሀራ አፍሪካ አገሮች መካከል ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት የምታስመዘግብ አገር ናት” በማለት በሸፍጥ ለማሳመን በመወትወት ላይ ይገኛሉ፡፡ እውነታው ግን ኢትዮጵያ በዓለም ከሚገኙ የመጨረሻዎቹ ደኃ አገሮች ከመጨረሻው በሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ አገር መሆኗን “ኢትዮጵያ ለምንድን ነው ደኃ የሆነችው?” በማለት ቀደም ሲል ባዘጋጀሁት ትችቴ ላይ በግልጽ አስቀምጨዋለሁ፡፡
አጼ ምኒልክ የኢትዮጵያ “ህዳሴ” መሪ ነበሩ፡፡ አገራቸውን ለማጠናከር እና ዘመናዊ ለማድረግ ወሳኝ የሚባሉ እርምጃዎችን ወስደዋል፡፡ ለዘመናዊ ቴክኖሎጂ ልዩ ትኩረት በመስጠት ለአገራቸው አዲስ ዓይነት የግንኙነት ስርዓት እንዲዘረጋ  አድርገዋል፡፡ አጼ ምኒልክ አገራቸው ኢትዮጵያ የስልክ እና የቴሌግራፍ እንዲሁም ዘመናዊ የፖስታ አገልግሎት ተጠቃሚ እንደትሆን አድርገዋል፡፡ አጼ ምኒልክ የኤሌክትሪክ አገልግሎት በአዲስ አበባ ከተማ እንዲጀመር አድርገዋል፡፡ የመጀመሪያዋን በሞተር ኃይል የምትንቀሳቀስ አውቶሞቢል ወደ ሀገራቸው ያስገቡ አጼ ምኒልክ ናቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የማሪያ ቴሬዛ ገንዘብን የማይመች የገንዘብ መገበያያን በዚያን ዘመን በዓለም ገበያ ላይ በመገበያያነት አገልግሎት ስራ ላይ ይውሉ በነበሩ በመዳብ የወርቅ ቁራጭ የገንዘብ ሳንቲሞች በመተካት ዘመናዊ የገንዘብ ግብይትን በኢትዮጵያ አስጀምረዋል፡፡ አጼ ምኒልክ ከምንም ከማንም በላይ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ቅድሚያ ይሰጡ ነበር፡፡ አጼ ምኒልክ እ.ኤ.አ በ1894 ከጅቡቲ እስከ አዲስ አበባ የሚዘልቅ የባቡ ሀዲድ መስመር ለመዘርጋት ከፈረንሳይ መንግስት ጋር የስምምነት ውል ፈረሙ፡፡ በተመሳሳይ ዓመት የአውሮፓ ኃያላን አገሮች አፍሪካን እንደ ቅርጫ ስጋ የሚከፋፍለውን የአውሮፓ ቅኝገዥዎች የበርሊን ጉባኤን  አካሄዱ፡፡ በዚያን ጊዜ ፈረንሳዮች የነበራቸውን ኃይል በመተማመን ከባቡር ሀዲዱ ጋር በተያያዘ መልኩ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለመዳፈር ሲሞክሩ አገር ወዳዱ መሪ ፈረንሳዮችን ጭጭ እንዲሉ አድርገው በ1906 የአገራቸውን ሉዓላዊነት ካስጠበቁ በኋላ ነው ቀዝቀዝ ማለት የጀመሩት ሐዲዱም መሰራት የቀጠለው ፡፡ እንግዲህ እንዲህ የነበረውን አንጸባራቂ ታሪክ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ያለው ገዥው አካል የውሸት የአቶ መለስን ትረካ በማጉላት የህዳሴው መሪ፣ በአፍሪካ ታሪክ እስከ አሁን ድረስ ታይቶ የማይታወቅ የኤሌክትሪክ ኃይል ግድብ ገንቢ፣ የድልድዮች ገንቢ፣ የመንገዶች እና የባቡር ሀዲዶች…  በማለት ታሪክን አዛብቶ ሸውራራ ታሪክ ለመጻፍ እየተውተረተረነው ያለው፡፡
አጼ ምኒልክ የፊውዳል መንግስታት የበላይ የነበሩ መሪ ነበሩ፡፡ በወቅቱ በአገር ውስጥ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ በነበረበት ጊዜ ማድረግ የሚፈልጉትን ማድረግ የሚችሉ አፍሪካዊ መሪ ነበሩ፡፡ በእግዚአብሄር በአላህ ፈቃድ አንዲት የተባበረች እና የተከበረች ኢትዮጵያን ለተተኪው ትውልድ አውርሰው አልፈዋል፡፡ የአቶ መለስ ጠንካራው የውርሳቸው ትሩፋት በአፍሪካ የመጀመሪያውን ፈላጭ ቆራጭ አምባገነናዊ አገዛዝ ማውረሳቸው ነው፡፡ በሁፊንግተን ፖስት ትችቴ/Huffington Post Commentary በግልጽ እንዳስቀመጥኩት “ዴሞክራሲ የህዝብ፣ በህዝብ፣ ለህዝብ የቆመ የመንግስት አስተዳደር ከሆነ የማፊያ አገዛዝ/thugocracy ደግሞ (የወሮ በላ) የሌቦች፣ ለሌቦች በሌቦች የቆመ የወሮ በላ መንግስት አስተዳደር ነው፡፡“ በግልጽ አባባል የማፊያ አገዛዝ የሚሽከረከረው በወሮበላ ሌቦች እና በዘራፊዎች ነው፡፡ በማፊያ የአገዛዝ ስርዓት የፖለቲካ ስልጣንን ሙዝዝ ብሎ መያዝ እና እንደ መዥገር መጣበቅ ዋናው ተግባሩ ሲሆን ገዥው አካል የህዝብን ገንዘብ በመዝረፍ እና ለብዙሀኑ ህዝብ ህልውና የቆሙትን መሰረታዊ አገልግሎቶች ውሱን ሀብቶች በመቀራመት ግላዊ ሀብትን ለማጋባስ ነው፡፡
የአቶ መለስ የማፊያ (የወሮ በላ) አገዛዝ በሰነድ ብቻ ተመዝግቦ የሚያዝ ሳይሆን በቀድሞው የመከላከያ የትግል ጓደኛቸው ጭምር የአይን ምስክርነት የተሰጠበት ጉዳይ ነው፡፡ ገና ከጫካ ትግል ሲጀምሩ አቶ መለስ እና የትግል ጓዶቻቸው የሌቦች አስተዳደራዊ ስርዓት ነበር የዘረጉት፡፡ እ.ኤ.አ በ1980ዎቹ የመጀመሪያ ዓመታት ለረሀብ ሰለባ ለወደቀው የትግራይ ህዝብ እርዳታ ተብሎ ከእርዳታ ሰጭ ድርጅቶች የተላከውን ከ10 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚሆን ገንዘብ ከተሰጠበት ዓላማ ውጭ አማጺው ቡድን ለጦር መሳሪያ መግዣ እና እራሳቸውን ማበልጸጊያ አድርገውታል፡፡ በቅርብ እየወጡ ያሉ ዘገባዎች እንደሚያመላክቱት ከግማሽ በላይ የሚሆነው የአገሪቱ ኢኮኖሚ በአቶ መለስ ባለስልጣኖች፣ ደጋፊዎች፣ ሎሌዎች፣ ጓደኞች፣ የስራ ባልደረቦች እና ሌሎች ቁጥጥር ስር ተቀፍድዶ ይገኛል፡፡ ሙስናን በሚመለከት የዓለም ባንክ “ሙስናን በኢትዮጵያ መመርመር” በሚል ርዕስ የተወሰኑ አገሮችን ባናሙናነት ወስዶ በማጥናት ባወጣው ባለ500 ገጽ የግኝት ዘገባ መሰረት ሙስና እና የህዝብን ሀብት መዝረፍ በኢትዮጵያ ዋና መገለጫ ሆኗል በማለት ደምድሟል፡፡ ዘራፊነት አና ሙስና የአቶ መለስ የመጨረሻው ውርሳቸው ነው፡፡
አጼ ምኒልክን መጥላት ይወዳሉ፣
ጥላቻ የነብሳችን የመጨረሻው የበሽታ ምልክት ነው፡፡ ጥላቻ ኢምክንያታዊ ነው ወይም አመክንዮ የለውም፡፡ በጥላቻ ላይ የተጻፉ በርካታ ሳይንሳዊ ጽሁፎች እንደሚያመለክቱት  በጥላቻ የተመረዙት ምንጊዜም ይጠላሉ ምክንያቱም ይፈራሉ፣ ደህንነት አይሰማቸውም፣ ምቀኞች ናቸው፣ ወይም ደግሞ እራሳቸውን ይጠላሉ ምክንያቱም የጥላቻቸው መነሻ እና መድረሻ እነዚሁ በጥላቻ የተሞሉት ግብዞች ናቸውና፡፡ ከሁሉም በላይ በጥላቻ የተሞሉት ወገኖች እራሳቸውን ይጠላሉ ምክንያቱም ብቁነት የጎደላቸው፣ ኃይልየለሽነት፣ ተስፋቢስነት፣ እና የእረዳትየለሽነት ስሜት የተጠናወታቸው ነው፡፡
ማንዴላ እንዲህ ብለው ነበር፣ “ሰው በቆዳው ቀለም፣ ወይም ደግሞ በማንነቱ፣ ወይም በኃይማኖቱ ምክንያት ብቻ ማንም ማንንም ሊጠላ አልተወለደም፡፡ ሰዎች መጥላትን መማር አለባቸው፣“ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ በስልጣን ላይ ያሉትን የገዥው አካል ኃላፊዎች ሁኔታ  በማስብበት ጊዜ በማንዴላ ፍልስፍናዊ ግምገማ ላይ አምነት ማጣት ይቃጣኛል፡፡  ማንዴላ እንዲህ በማለትም አክለዋል፣ “መጥላትን የሚማሩ ከሆነ ፍቅርን ሊማሩም ይችላሉ፣ ምክንያቱም ፍቅር ከተቃራኒው የበለጠ በሰው ልጅ ልብ ውስጥ የመስረጽ ተፈጥሯዊ ባህሪ አለውና፡፡“ ተቃራኒውን በተጨባጭ የሚያመላክቱ በርካታ መረጃዎች ቢኖሩም የማንዴላ መርሆዎች በስልጣን ላይ ባሉት ባለስልጣኖች ሁሉ ሊተገበሩ እንደሚችሉ ጽኑ እምነት አለኝ፡፡
በመርህ እና በተግባርም እንደሚታየው በጋንዲ መርሆዎች መሰረት ለመኖር ጥረት ማድረግ አለብን፣ “ኃጢያተኛውን ሳይሆን ኃጢያቱን እንጥላ፣“ በጥላቻ የተመረዙትን የምንጠላ ከሆነ የእነርሱ የመስታወት ነጸብራቅ እንሆናለን፣ እራሳችንም የምንጠላቸውን እንሆናለን፣ እንደ ሰው ስብዕና አቶ መለስን እና መሰሎቻቸውን የምንጠላ ከሆነ እነርሱኑ ሆን ማለት ነው፡፡ የምንጠላ ከሆነ ምግባራቸውን እንጅ እንደ ሰው እራሳቸውን መሆን የለበትም፡፡
ጥላቻ ጠንካራ ኃይል ነው፡፡ በናዚዝስቶች የተሰራጨው ጥላቻ አገሮችን በጠቅላላ እንዲጠፉ አድርጓል፡፡ በሩዋንዳ የተከሰተው ጥላቻ የሚሊዮኖችን ሩዋንዳውያን ህይወት ቀጥፏል፡፡ በዳርፉር የተቆሰቆሰው ጥላቻ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የሱዳን ዜጎችን ህይወት አጥፍቷል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በተከሰተው የኃይማኖት ጥላቻ በናይጄሪያ እና በመካከለኛው አፍሪካ ሬፑብሊክ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በመሞት ላይ ይገኛሉ፡፡ በምንም ዓይነት መንገድ ወደ ጥላቻ መግባት የለብንም፡፡
በዓለም ላይ ሁለት ዓይነት ህዝቦች እንዳሉ አምናለሁ፡፡ “ጎረቤትህን እንደ እራስህ ውደድ“ የሚለውን ወርቃማ ህግ የሚከተሉ ህዝቦች አሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ “የመዳብ ህግ” እያልኩ በምጠራው “ጎረቤትህን እንደ እራስህ ጥላ“ እያሉ የሚኖሩ ህዝቦች አሉ፡፡ በጥላቻ የተሞሉ ሰዎች የእራሳቸውን እረዳትየለሽነት፣ የደህንነት እጦት ስሜት፣ የጥፋተኝነት ስሜት እና በጥላቻቸው መሳሪያነት ድርጊቶችን በመለወጥ አሸናፊነትን የሚጎናጸፉ ይመስላቸዋል፡፡ ሌሎችን በመጥላት የራሳቸውን የበታችነት ስሜት እና የእራስን ዋጋ ዝቅ አድርጎ የማየት ችግራቸውን በማስወገድ እራሳቸውን ከፍ ያደረጉ ይመስላቸዋል፡፡ አጼ ምኒልክን የሚጠሉ ሰዎች በእርግጥ አይጠሏቸውም፣ እራሳቸውን የሚጠሉ እና ምኒልክን ለመሆን የሚያስቡ ምኒልክ የሚያደርጓቸውን ነገሮች ሁሉ ተምሳሌት ለማድረግ የሚጥሩ ናቸው፡፡
በአሁኑ ጌዜ በኢትዮጵያ በስልጣን ላይ ላሉት ሁሉ አዝንላቸዋለሁ፡፡ በእርግጥ በጣም አዝንላቸዋለሁ፡፡ እነዚህ በጥላቻ የተሞሉት ወገኖች የኢትዮጵያን ታላላቅ መሪዎች እና የኢትዮጵያን ታሪክ ጥላሸት በመቀባት በቅርቡ በህይወት የተለዩትን መሪያቸውን እና የሁለት አስርት ዓመታት ኃጢያታቸውን በማስሰረይ ብጹ የሚያደርጓቸው ይመስላቸዋል፡፡ የአጼ ምኒልክን እና የቀዳማዊ ኃይለስላሴን በጎ ተግባራት ጥላሸት በመቀባት የአቶ መለስን ስብዕና የሚገነቡ ይመስላቸዋል፡፡ የአጼ ምኒልክን ሐውልት ከህዝባዊ ቦታዎች በማራቅ እና የአቶ መለስን እርካሽ ወረቀት ፎቶግራፎች በየመንገዶች ላይ በመለጠፍ አቶ መለስን ወደ መልዓክነት ያቀረቧቸው ይመስላቸዋል፡፡ አቶ መለስ የአጼ ኃይለስላሴ ሀውልት ከንክሩማህ ቀጥሎ በአፍሪካ ህብረት ቅጥር ግቢ ውስጥ እንዳይቆም ሽንጣቸውን ገትረው ተከራክረዋል፡፡ ሆኖም ግን ንክሩማህ እራሳቸው የአጼ ኃይለስላሴ ያልተጠቆጠበ ጥረት ባይኖር ኖሮ የአፍሪካ ድርጅት እውን መሆን አይችልም ነበር በማለት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ያሉት ባለስልጣኖች የጥላቻቸው ባህሪ እና አተገባበር ነጻብራቅ ረዘም ያለ ጊዜ የቆየ ቢሆንም ለዚህ ምክንያታዊ መግለጫ አላገኘሁለትም፡፡ ብዙ ሰዎች በፍርሀት እና በጭንቀት ላይ ያሉ ሰለ ወደፊት ምንይመጣል አያሉ ነው ምክንያቱም በቀጣይነት የሚከሰተው ሁኔታ የማይታወቅ እና ለመተንበይም አስቸጋሪ የሆነበት ሁኔታ ሰለሆነ ነው፡፡ ያለፈውን ጊዜ፣ የጥንት 19ኛውን ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ የሚፈሩትን ሰዎች በትክክል ለመረዳት አልችልም፡፡ በሞያዬ ካለኝ ልምድ አንጻር ያለፈውን ጊዜ የሚፈሩ እና የሚሸበሩ ወንጀለኞ ይሄዉም በፊት በፈፀሙት ወንጀል የሚያዙ ሰለሚመስላቸውና  ሰለሚፈሩ ነው:: በስልጣን ላይ ያሉ አምባገነኖች ስልጣናቸውን ከህግ አግባብ ውጭ በመጠቀም የሰላማዊ ዜጎችን መብት የጣሱ እና የደፈጠጡበትን ወንጀል ለመደበቅ ሲሉ ጥላቻን በማራመድ እና ከፋፍሎ መግዛትን አጀንዳቸው አድርገው ይይዙታል ከሚል መደምደሚያ ላይ ደርሻለሁ፡፡ በኢትዮጵያውያን ልዩ ልዩ ጎሳዎች ላይ ጥልቅ ጥላቻና እና ፍርሀትን በመፍጠር ለፈጸሟቸው እኩይ ተግባራት ተጠያቂ እንዳይሆኑ እና ኃላፊነትን እንዳይወስዱ የጥላቻ መንፈስን እንደ መርህ በመያዝ ያራምዳሉ፡፡ በህዝቦች መካከል ጥላቻን በመዝራትም በኢኮኖሚያዊ ችግሮች ምክንያት ተወጥረው ያሉትን ዜጎች ሀሳቦች ለማስቀየሻ ይጠቀሙበታል፡፡
በጥላቻ የተሞላን ሰው እንደ እራስህ ውደድ፣
ወርቃማው ህግ እንዲህ ይላል፣ “ጎረቤትህን እንደ እራስህ ውደድ፡፡“ እኔ ደግሞ እንዲህ እላለሁ፣ “የሚጠላህን እንደ እራስህ ውድ፡፡“ ከመጥላት ይልቅ መውድደ የተሻለ ነገር ነው፡፡ ጥላቻ ወርዋሪውን ተመልሶ እንደሚጎዳ ቦንብ ነው፡፡ መጀመሪያ ከሚወረውረው ሰው እጅ ይወጣል ተመልሶ ግን በጥላቻ የተሞላውን ሰው እራሱን ይጎዳዋል፡፡ የማንዴላን አባባል በመዋስ፣ ጥላቻ የነብስ መርዝ ነው፡፡ በጥላቻ የተሞሉት በሚጠሉበት ጊዜ መርዝን ይጠጣሉ እናም የሚጠሏቸው እንዲሞቱ ይጠብቃሉ፡፡ በስልጣን ላይ ያሉ ሁሉ ጥላቻን ማራመድ እንዳለባቸው ልዩ ምክር የሚሰጥ ለየት ያለ የፍልስፍና ዓይነትም አለ፡፡ ጥላቻ ሁልጊዜ የተጠላውን ሰው የተወደደ እና የተከበረ ስብዕና ያለው እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ በስልጣን ላይ ተቆናጥጠው ያሉ ወገኖች በዱሮዋ ደቡብ አፍሪካ ከነበሩት የአፓርታይድ መሰል የመንፈስ ጓዶቻቸው ትምህርቶችን ሊማሩ ይገባል፡፡ የአፓርታይድ ጌቶች የማንዴላን ስብዕና፣ አመራር እና ክብር ለበርካታ አስርት ዓመታት ለማዋረድ ፈለጉ፡፡ ማንዴላ አሸባሪ እና ኮሙኒስት ናቸው በማለት ማንኛውንም ዓይነት የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ከፈቱባቸው፡፡ ይንንም ምክንያት በማድረግ ማንዴላ በእስር ቤት በቆዩባቸው ጊዚያት ሁሉ ምንም ዓይነት የፎቶግራፍ ምስላቸው እንዳይወጣ አደረጉ፡፡ ሆኖም ግን ያልታሰቡ አጋጣሚዎች ተከሰቱ፡፡ በሂደት ጊዜ እያለፈ እና የጸረ አፓርታይድ ንቅናቄው እየተጠናከረ ሲሄድ ማንዴላን አሳንሶ የማየት አባዚያቸው የማንዴላን የመላዕክነት ደረጃ ከፍ እያደረገ ወደ ዓለም አቀፋዊ ተምሳሌነት እንዲሸጋገሩ እገዛ አደረገላቸው፡፡ ከዚህ ሊወሰድ የሚችለው ታላቅ ቁምነገር የአጼ ምኒልክን እና የአጼ ኃይለስላሴን ስብዕና ዝቅ ለማድረግ ጥረት ባደረጉ ቁጥር እነዚህ መሪዎች በኢትዮጵያ የወጣቶች ትውልድ የአስተሳሰብ አድማስ ዘንድ የበለጠ ክብር እና ሞገስን እየተቀዳጁ ታዋቂ እየሆኑ ይሄዳሉ፡፡ በእነዚህ መሪዎች ላይ የማያቋርጥ እና ዘለቄታዊ ያለው የማዋረድ ዘመቻ ባደረጉ ቁጥር የቀድሞው ትውልድ ጉዳዩን የበለጠ እንዲገመግመው እና አቋሙን እንዲያጠናክር ያደርገዋል፡፡
ፍቅር ከጥላቻ በላይ ዘልቆ መሄድን ይጠይቃል፡፡ ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ እና ማንዴላ በሰዎች እና በህብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ ፍቅር ያለውን የማይበገር የአሸናፊነት ኃይል፣ እንዲሁም ፍቅር በዘር፣ በጎሳ እና በኃይማኖት የተዘራን የጥላቻ ካንሰር የመፈወስ ችሎታ እንዳለው በግልጽ አስተምረውናል፡፡ ማንዴላ ለመጥላት እና በቀልን ለመፈጸም ምክንያት አላቸው፡፡ ለ27 ዓመታት የማንዴላ ስም የእስረኛ ቁጥር 46664 ነበር፡፡ እ.ኤ.አ በፌብሯሪ 1990 ጧት ከእስር ቤት ተለቅቀው ከእስር ቤቱ በር ሲወጡ ከሚሊዮን ዶላር ዋጋ በላይ የሚያወጣውን ፈገግታቸውን አሳይተዋል፡፡ ለ27 ዓመታት ከቤተሰቦቻቸው ነጥለው በእስር ቤት ውስጥ ባማቀቋቸው የአፓርታይድ ጌቶች ላይ ምንም ዓይነት የጥላቻ ስሜት አላሳዩም፡፡ ማንዴላ ታላቅ ትምህርት አስተምረውን አልፈዋል፣ እንዲህ በማለት፣ “እየተራመድኩ ወደ በሩ በምቃረብበት ጊዜ ይህ ሁኔታ ወደ ነጻነት እየመራኝ እንደሆነ አስብ ነበር፡፡ የበቀልተኝነት ስሜቴን እና ጥላቻዬን እዚያው እስር ቤት ጥዬው ካልወጣሁ እዚያው እስር ቤት እንዳለሁ እቆጥረዋለሁ፡፡“ በማለት የጥላቻን መጥፎነት በግልጽ ተናግረዋል፡፡ ማንዴላ ፍጹም የጥላቻ እስረኛ አልነበሩም፡፡ እስረኛው የአፓርታይድ ጥላቻ ነበር፣ እናም አስረኞቹ የአፓርታይድ አለቆች እና ጌቶች ነበሩ፡፡ ማንዴላ ከእስር ቤት በመውጣት በጥላቻ ሰንሰለት ከአፓርታይድ ግንብ ጋር የታሰሩትን እውነተኞቹን የአፓርታይድ እስረኞች ከጥላቻ፣ ከፍርሀት፣ እና ከበቀልተኝነት ነጻ ለማውጣት ተንቀሳቅሰዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ በስልጣን ላይ ያሉት ገዥዎች በጥላቻቸው የሚቀጥሉ ከሆነ በደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ በስልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ የደረሰው ዕጣ ፈንታ የሚደርስባቸው መሆኑን መገንዘብ ይኖርባቸዋል፡፡ በአፓርታይድ የአገዛዝ ዘመን ጊዜ “ነጻዎቹ” ነጮች እውነተኛው የማይቀረው የብዙሀን አገዛዝ በሚመጣበት ጊዜ ለብዙ ጊዜ በጭቆና ቀንበር አስረው ሲያማቅቋቸው የነበሩት ጥቁር አፍሪካውያኖች ምን ሊያደርጓቸው እንደሚችሉ ሌት እና ቀን ያሰላስሉ ነበር፡፡ በጥቁር አፍሪካውያን ላይ የነበራቸው ጥላቻ እንቅልፍየለሽ ሌሊቶችን ብቻ እንዲያሳልፉ አላደረጓቸውም፣ ሆኖም ግን ልቦቻቸው፣ አዕምሯቸው እና ነብሳቸው እንዲሁም ስብዕናዎቻቸውም ጭምር እንዲሰበሩ አደረጋቸው እንጅ፡፡ ሙት መንፈሶች አደረጓቸው፣ ነጻ ሆነው ባሏቸው ኃብቶቻቸው ለመደሰት ባለመቻል የቁም ሙት አደረጓቸው፣ እንዲሁም በኤሌክትሪክ እና በእስር ቤት የሽቦ አጥር ታጥረው የእራሳቸው ጎረቤቶች የእስር ቤት በሮች ሆኑባቸው፡፡ በእርግጥ በጦር ካምፕ የሚኖሩ ህዝቦች ሆኑ፡፡
ምንጊዜም የተሻለ መንገድ አለ፡፡ የጥላቻ ትችት ከማቅረባችን በፊት እውነተኛውን ነገር ለማወቅ የበለጠ ጽናት ሊኖረን ይገባል፡፡ ስለዳግማዊ አጼ ምኒልክ፣ ስለ አጼ ኃይለስላሴ፣ ስለ ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም እና ስለ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እውነኛውን ነገር ማቅረብ ይኖርብናል፡፡ እነርሱን መጥላት ሳይሆን ከስህተቶቻቸው እንማር፣ እኛ በህይወት ያለነው የእነርሱን ስህተት መድገም የለብንም፡፡ ጥላሸት በመቀባት ላይ ላለመሰማራት ከእነርሱ ስህተት እንማር፣ ነገር ግን የእርቅን መንገድ በመፈለግ የእነርሱን ስህተቶች እናርም፡፡ ከኢትዮጵያ ወጣቱ ትውልድ ጋር ህብረት በመፍጠር ማንም ወንድ ወይም ሴት በማንነቱ/ቷ፣ በዘሩ/ሯ ሳይሆን ሰው በመሆኑ/ኗ፣ አፍሪካዊ/ት እና ኢትዮጵያዊ/ት በመሆናቸው ብቻ በመመልከት አዲሲቷን ፍቅር የነገሰባት ኢትዮጵያ ለመገንባት እንነሳ፡፡ ማንም ወንድ ወይም ሴት ባለው/ላት ስልጣን በመመካት ባልታጠቁ ዜጎች እና በሰላማዊ ሰዎች ላይ የጦር እልቂት ሊያዝዝ/ልታዝዝ የማይችሉበት እና ይህ ዓይነቱ አስተሳሰብም ሊወገድ የሚችልበት ነጻ ህሊናን በመፍጠር አዲሲቷን ፍቅር የነገሰባት ኢትዮጵያ ለመገንባት እንነሳ፡፡ በእያንዳንዱ/ዷ ግለሰብ የጎሳ፣ የእምነት ወይም የቋንቋ ልዩነት ሳንፈጥር በአንድነት በመሆን የእያንዳንዱ/ዷ ዜጋ መብት እና ክብር የሚጠበቅበትን ህብረተሰብ ለመፍጠር እንነሳ፡፡ በዚህ ዓይነት ሁኔታ ነው የወደፊቱን ብሩህ ዘመን ለመፍጠር የምንችለው፡፡ ለብዙ ጊዜ በመቆየት በጊዜ ደመና ተሸፍኖ የደበዘዘውን ነገር ቆፍሮ በማውጣት እና ጥላሸት በመቀባት አይደለም ፍቅር የነገሰበትን የወደፊቱን ትውልድ መገንባት የምንችለው፡፡
በጥላቻ ንግግር አንዘን ወይም ደግሞ አንቆጣ፡፡ ምንም ዓይነት እርባና የለውም፡፡ ይልቁንም ጥላሸት የመቀባት ዘመቻውን በሰከነ መልክ እናጋልጥ፡፡ መላዕክ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት ስህተት እና ውሸት መሆኑን እና የኢትዮጵያን ታሪክ ጥላሸት ለመቀበት እና ለመበረዝ የሚደረገውን መዋተት እናጋልጥ፡፡ ከጥላቻ አራማጆች ጋር በማበር እራሳችንን ወደ ጭቃ እና የሚያጣብቅ ቆሻሻ ውስጥ አንጣል፡፡ እንዲህ የሚሉትን የጆርጅ በርናርድ ሻውን ምክሮችን በፍጹም መርሳት የለብንም፣ “ከብዙ ጊዜ በፊት ከአሳማ ጋር ማጥ ዉስጥ ላለመታገል ትምህርት አግኝቻለሁ፣ ለመታገል ከሞከርክ ቆሻሻ ትሆናለህ፣ አሳማው ግን ማጡን የነብሱን ያህል ይወደዋል፡፡“ ጥላቻን ሙያ አርገው ከሚኖሩ ሰዎች ጋር የጥላቻ ቃላትን መለዋወጥ ከአሳማ ጋር በጭቃ ማጥ ውስጥ የነጻ ትግል ውድድርን እንደማድረግ ይቆጠራል፡፡
ጥላቻን ወደ ፍቅር መለወጥ
በጥላቻ መንፈስ የተሞሉት ወገኖች ይጥሉ እና ይዋሹ፡፡ ስለዚያ ጉዳይ የምናደርገው አንዳች ነገር የለም፡፡ በእራሳችን የሀይል ንፍቀ ክበብ ውስጥ ያለን ልዩ ችሎታ እራሳችንን ከጥላቻ ወደ ፍቅር ከመቀየር ላይ ነው፡፡ በእርግጥም አሉታዊ ኃይሎችን ወደ አዎንታዊ ኃይሎች የመቀየር ችሎታ አለን፡፡ ከጥላቻ ወደ ፍቅር ለመቀየር እንችላለን፣ ይህን የምናደርገው ግን ነገሩ ቀላል ስለሆነ አይደለም ይልቁንም የበለጠ ከባድ ስለሆነ እንጅ፡፡ ፍቅር በግለሰብ ደረጃም ይሁን፣ በሌሎችም ይሁን፣ በማህበረሰቡ ወይም በአጠቃላይ በህዝቡ ላይ ይሁን ለተግባራዊነቱ ታላቅ ስራ መስራትን ይጠይቃል፡፡
ከማህተመ ጋንዲ እና “እውነተኛው ኃይል”/Satyagraha ከሚሉት አቀራረባቸው እስቲ ትምህርት እንቅሰም፡፡ ጋንዲ እንዲህ በማለት ገለጻ አድርገዋል፣ “እውነት/satya ፍቅርን በማጎናጸፍ የመንፈስ ጽናትን ይወልዳል፣ እናም ከኃይል ጋር ተመሳሳይ በመሆን ያገለግላል፡፡“ ዓላማው በጥላቻ የተሞላው/ችው እንዳያስገድድ/እንዳታስገድድ በማድረግ ሀሳባቸውን ለማስለውጥ ነው፡፡ በተግባራዊነት ሁኔታው ስንመለከተው ዓላማው በጥላቻ የተሞላውን/ችውን ጥላቻ ማራመድ የእራሱን/ሷን ልብ፣ አዕምሮ እና ነብሳቸውን የሚጎዳቸው መሆኑን በማሳመን እንዲቀየሩ ለማድረግ ነው፡፡ ከማንኛውም ጉዳትን ከሚያመጡ ነገሮች ሁሉ የሚጠብቁን እራስን፣ ማህበረሰቡን እና አገርን መውደድ ነው፡፡ በጥላቻ ከተሞሉት ወገኖች ፍቅር የተሞሉ ወገኖችን ለማፍራት እውነተኛውን ኃይል/Satyagraha በተግባር እናውል፡፡
ከዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ የምንማራቸው በርካታ ቁምነገሮች አሉ፣ እንዲህም በማለት ያስተምሩናል፣ “ጨለማን ጨለማ አያስወግደውም፣ ብርሃን ብቻ ነው ያንን ማድረግ የሚችለው፡፡ ጥላቻን ጥላቻ ሊያስወግደው አይችልም፣ ፍቅር ብቻ ነው ያንን ማድረግ የሚችል፡፡“ ብለዋል፡፡ እንዲህ በማለትም አስተምረዋል፣ “ይቅርታ የማድረግ ችሎታችንን ማሳደግና ማጠናከር ይኖርብናል፡፡ ይቅርታ የማያደርግ/የማታደርግ ሰው ለማፍቀር ኃይል የለውም/የላትም፡፡ በመጥፎነታችንም ላይ ጥሩ ነገሮችም አሉ፡፡ በመጥፎ ነገሮቻችን ላይም  ጥሩ ነገሮች አሉ፡፡ ይህንን ሁኔታ ባወቅን ጊዜ ጠላቶቻችንን ከመጥላት በመጠኑም ቢሆን እንታቀባለን፡፡“ ይቅርታ አድራጊነት እና እርቅ ብቸኞች የጥላቻ ፈውስ እና መድኃኒቶች ናቸው፡፡
ከዘመናችን ታላቅ ቀልድ አዋቂ ከቻርለስ ቻፕሊን እንኳ ትምህርት መቅሰም ይኖርብናል፡፡ እንዲህም ይለናል፣ “የሰው ልጅ ጥላቻ ያልፋል፣ እና አምባገነኖችም ይሞታሉ፣ እናም ከህዝቦች የነጠቁት ስልጣን ተመልሶ በህዝቡ እጅ ይገባል፡፡ ስለሆነም የሰው ልጅ ሟች እስከሆነ ድረስ ነጻነት ከናካቴው ሊጠፋ አይችልም፡፡“ ነጻነት በጥላቻ ከተሞሉት የሰው ዘሮች ሁሉ የበለጠ እድሜ አለው፡፡ በጎሳ ማንነት መፈረጅን እርግፍ አድርገን እንተው እና ሰው በመሆናችን ብቻ በኢትዮጵያዊነታችን እና በአፍሪካዊነታችን እንኩራ፡፡
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በስልጣን ላይ ላሉ የማስተላለፈው መልዕክት፣
በኢትዮጵያ በስልጣን ላይ ሆነው ጥላቻን ለሚያራግቡት አጭር መልዕክት አለኝ፡፡ በአሁኑ ጊዜ የምትቆሰቁሱት የዘር እና የጎሳ ጥላቻ ፍላጻ በአንድ ወቅት ተመልሶ እራሳችሁ ላይ ይሰካል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የአጼ ምኒልክን ክብር እና ዝና ለማንቋሸሽ በታለመ ዕኩይ ምግባር ጡት ቆራጭ አረመኔ ነበሩ በማለት በመሳለቅ እና በማፌዝ ላይ ትገኛላችሁ፡፡ በአሁኑ ጊዜ አጼ ምኒልክን እንዲጠሉ የሚሰበክላቸው ሰዎች ነገ ደግሞ አቶ መለስን እንዲጠሉ የማይሰበክበት ምክንያት አይኖርም፡፡ የእናንተ ታላቁ ባለራዕይ መሪ አቶ መለስ በኦጋዴን፣ በጋምቤላ፣ በአዲስ አበባ እና በሌሎችም ቦታዎች በንጹሃን ዜጎች ላይ በፈጸሟቸው የጅምላ እልቂቶች ሳቢያ በድንጋይ እና በእብነበረድ በተቀረጹ ሃውልቶች ላይ ሆነው ሁለተኛው ሮዶልፍ ግራዛኒ በመባል የሚታወሱበት ጊዜ እሩቅ አይሆንም፡፡ ዛሬ ጓደኞች ብላችሁ የያዛችኋቸው ሰዎች ነገ ቀንደኛ ጠላቶቻችሁ ሆነው ይቀርባሉ፡፡ ዛሬ የእናንተ ጠላቶች አድርጋችሁ ጥላሸት የምትቀቧቸው ሰዎች ነገ ጽዋው ሞልቶ እጣ ፈንታችሁ ደርሶ የዘራችሁትን የምታጭዱበት ጊዜ ሲመጣ የእናንተ ጓደኞች ሆነው ይቀርባሉ፡፡
ዳግማዊ አጼ ምኒልክ መልዓክ ወይም ጭራቅ አልነበሩም፡፡ ሰይጣን ወይም ደግሞ እግዚአብሄርም አልነበሩም፡፡ የተቀሩት የአፍሪካ አገሮች በኃአውሮፓ ኢምፔሪያሊስት ኃይሎች ሲቆራረሱ፣ መጫወቻ ሲሆኑ፣ ሲነሱ ሲጣሉ፣ ሲበጠሱ ሲቀጠሉ፣ ሲሸጡ እና ሲለወጡ እንዲሁም ሲጋዙ በነበረበት ጊዜ አጼ ምኒልክ ደግሞ ኢትዮጵያን ሲያጠናክሩ እና ሲያዘምኑ የነበሩ የተከበሩ አፍሪካዊ ንጉስ ነበሩ፡፡ ዳግማዊ አጼ ምኒሊክ በአንድ መለኪያ ብች ይገምገሙ፣ በእውነት! የታሪክ ሰዎች እውነታውን መናገር አለባቸው፣ እና ሁሉንም እውነታዎች፣ ሌላ ምንም ነገር ሳይሆን ስለምኒልክ ያለውን እውነታ ብቻ፡፡ ለአጼ ምኒልክ 100ኛ ሙት ዓመት መታሰቢያ ሲባል እ.ኤ.አ በ1909 በኒዮርክ ታይምስ ባሮን ዲ ጃርልስበርግ የተባለ የቤልጄም አሳሽ ለዳግማዊ አጼ ምኒልክ ምስክርነት ለጋዜጣው ቃል በመስጠት የተዘገበውን በከፊል ምስከርነት እውነታ መረጃ  እንደሚከተለው አቅርቤዋለሁ፡፡ ይህ ታሪካዊ የምስክርነት መረጃ ዳግማዊ አጼ ምኒልክን ከሰሯቸው ስራዎች አንጻር በትክክለኛው የታሪክ ሚዛን ላይ በማስቀመጥ እንዲገመገሙ ያስችላል የሚል ጽኑ እምነት አለ፡፡
ዳግማዊ አጼ ምኒልክ የዘውድ ስልጣኑን ለመቆናጠጥ ትግል ማድረግ ከጀመሩበት ከ20 ዓመታት በኋላ አቢሲኒያን ከከፊል የኋላቀርነት አገዛዝ በማውጣት ወደ አውሮፓውያን የንጉሳዊ ህገመንግስት የአገዛዝ ስርዓት ምሳሌነት አሸጋግረዋታል… እራሳቸውን ነጻ እና በእራስ የሚተማመኑ አድርገው የሚቆጥሩት ዘ እምነገደ የይሁዳ አንበሳ ስዩመ እግዚአብሔር የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት ዘ ኢትዮጵያ የኢጣሊያንን የቅኝ ግዛትነት ፍላጎት አምባ ጋሪማ ላይ ጦርነት ገጥመው በአሸናፊነት እንዳንኮታኮቱት… አጼ ምኒልክ ከአጼ ዮሀንስ ህልፈተ ህይወት በኋላ እ.ኤ.አ ኖቬምበር 4 1889 የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት ሆነው ሲሰየሙ የአቢሲኒያን መንግስት ከመሰረቱት የአካባቢያዊ መንግስታት በሙሉ ቅቡልነት አልነበራቸውም፡፡ ከብዙ ድካም እና ትግል በኋላ ነው እነዚህን የአካባቢ ገዥዎች እና ንጉስነታቸውን አንቀበልም ያሉትን አማጺ ገዥዎች በማሳመን እና በኃይል በማንበርከክ በመጨረሻ ስኬታማ ለመሆን የበቁት… ከዚያ በኋላ የአጼ ምኒልክ ዋና ዓላማ የነበረው የአውሮፓን ስልጣኔ ወደ አገራቸው ማስገባት ነበር፡፡ ንጉሱ የፊውዳሉን ህግ በማፈራረስ በእርግጥም በግዛታቸው እስከ አሁንም ድረስ ጨርሶ እንዳልጠፋ እና ባሮችን ነጻ በማውጣት የባሪያ ንግድን በማጥፋት በግዛታቸው በሙሉ ከክፍያ ነጻ የሆነ የትምህርት ስርዓትን ዘርግተዋል፡፡ በዚህም መሰረት እንደማንኛውም የአውሮፓ ሀገር ሁሉ በቀጣዮቹ ትውልዶች ትምህርት በመላ የአቢሲኒያ ግዛት ውስጥ የሚስፋፋ ይሆናል፡፡
ምኒልክ በመላ አፍሪካ በስልጣን ላይ ካሉ መሪዎች ሁሉ ልዩ ባህሪ ያላቸው ናቸው፡፡ እንደ የዲፕሎማሲ ሰው፣ እንደ ገንዘብ ኃላፊ፣ እንደ ወታደር ከሌሎች ወንድማዊ ንጉሶች የቅርበ መረጃዎችን በመውሰድ በእራሳቸው አካሄድ እንደሚመስላቸው የሚተረጉሙ ንጉስ ናቸው፡፡ እንደ ወታደር እና እንደ የዲፕሎማሲ ሰው የኢጣሊያኖችን በአቢሲኒያ መሸነፍ ለንጉሱ እንደ መልካም አጋጣሚ ምን ያህል ጠቃሚ የሆኑ ንጉስ መሆናቸውን አሳይተዋል፡፡ በቅርብ ዓመታት ደግሞ የገንዘብ ብልህ ጥንቁቅ  አያያዝ ምኒልክን ልዩ ያደርጋቸዋል፡፡ ስለገንዘብ እንደ ወጣትም፣ የዙፋን ስልጣናቸውን ከመያዛቸው እና በዙፋኑ ላይ ከተቀመጡም በኋላ በፓሪስ የስቶክ ገበያ ትንበያን/Paris Bourse ላይ ተሳትፎ ማድረጋቸው መልካም ተፈጥሯዊ ችሎታ ያላቸው መሆኑን ያመላክታል፡፡ እነዚህ ጠቃሚ ትንበያዎች የነበሩ ሲሆን ምኒልክ የዙፋን ስልጣኑን ከያዙ በኋላ ለመቋረጥ ችለዋል… የገንዘብ አሰራር ስርዓታቸውን በማስፋት እስከ ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ድረስ በማስፋት በአሜሪካ የባቡር ሀዲድ ካምፓኒዎች ላይ ትልቅ የድርሻ ባለቤት ለመሆን በቅተዋል፡፡ ከአሜሪካ የሴኪዩሪቲ ሰርቲፊኬቶች እና ከፈረንሳይ እና ከቤልጄም ባለሀብቶች ጋር ከ25 ሚሊዮን ዶላር ያላነሰ መዋዕለ ንዋይ በስራ ላይ እንዲውል አድርገው ነበር፡፡
በጣም የሚያስገርመው የአቢሲኒያው ደብዛዛ ንጉስ በሁሉም ነገሮች ላይ ያላቸው ሁለገብ እውቀት ነው፡፡ በጣም ምጡቅ የቋንቋ ችሎታ የነበራቸው ሲሆኑ ፈረንሳይኛ፣ እንግሊዝኛ እና ጣሊያንኛ ቋንቋዎችን አቀላጥፈው መናገር ይችላሉ፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ለመንግስታዊ ስራቸው ሙሉ ጊዜ ሰጥተው የሚሰሩ ሲሆን በአውሮፓ የሚዘጋጁ ጽሁፎችንም የመከታተል ዕድል ስላላቸው እና በትኩረት ስለሚከታተሉ አዲስ መጽሀፍ በወጣ ቁጥር ስለደራሲው ሲጠየቅ አዲስ አይሆኑም፡፡ ባዲሳባ ቤተመንግስት በሰዎቻቸው በሚታወቁበት መጽሀፍትን በማሰባሰብ ስራቸው እውቅና እንዲሰጣቸው ሲባል በተዘጋጀው ስብሰባ ላይ በተገኙበት ዕለት በቤተ መጻህፍታቸው ከ20 ሺህ ያላነሱ ጥራዞች መገኘታቸው ልዩ ኩራት እንዲሰማቸው አድርጓል፡፡ የምኒልክ መጻህፍትን የማሰባሰብ የትርፍ ጊዜ ስራ በጥንት የአፍሪካ እና የኢስያ ስልጣኔዎች ዘመንም የሚደረግ ነበር፡፡
በአጼ ምኒልክ ላይ የጥላቻ ዘመቻ ከሚያደርጉት ወገኖች ጋር የማቀርበው መደራደርያ 
በዳግማዊ አጼ ምኒልክ ላይ የጥላቻ ዘመቻ ስለማሰራጨት ጉዳይ የማቀርበው መደራደርያ አለኝ ፡
በአጼ ምኒልክ ስብዕና ላይ የምታደርጓቸውን ውሸቶችና  ቅጥፈቶች  የምታቆሙ ከሆነ እኔም ስለአቶ መለስየምናገራቸውን እውነቶች መናገር አቆማለሁ ᎓
                                                                                         Posted by A.G

Monday 13 January 2014

ሕገ- መንግስት ወይስ ዶክመንተሪ ፊልም? (ተመስገን ደሳለኝ) ....መቼም አገዛዙ ዓለማዊ ፍላጎታቸውን እስካሟላላቸው ድረስ ሀገር፣ ሕገ-መንግስት፣ ሕሊና… ደንታ ሳይሰጧቸው ሕዝብን በማሸበር የስርዓቱ ዕድሜ ይረዝም ዘንድ ‹ከፍርሃት ጋር ወደፊት!!› ለማለት የማያመነቱ ሰዎችን በዙሪያው የኮለኮለው ለእንዲህ አይነቱ ጊዜ ነው፡፡ ምንጭ ኢትዮሚድያ 12 01 2014



አምስተኛው ዙር አገር አቀፍ ‹‹ምርጫ›› እንደወትሮው ሁሉ በቀጣዩ ዓመት ሊደረግ በዕቅድ ተይዟል፤ ወሬውም ከወዲሁ ለፖለቲካ ፍጆታነት እየዋለ ነው፤ ኢህአዴግም በበኩሉ ‹አውራ ፓርቲ›ነቱን ከቀደመው በበለጠ አጠናክሮ የሚቀጥልበትን ሴራ ፈትሎ በመግመድ ውሎ ማደሩን ገና በማለዳ እያቀላጠፈው መሆኑን እየታዘብን ነው፡፡ አቶ መለስ ዜናዊ (ከልቡ ባይሆንም) በ1996 ዓ.ም ወርሃ ሐምሌ ላይ በተደረገ የግንባሩ ጉባኤ ‹‹የሚቀጥለው ምርጫ እንከን-አልባ ይሆናል›› ሲል ‹ቃል› ገብቶ የነበር ቢሆንም፣ ከስድስት ዓመት በኋላ በተካሄደው አራተኛው ዙር ‹‹ምርጫ›› በግላጭ ‹እንከን-አልባ ድል› በሚል ሲቀይረው ቅንጣት ታህል ሀፍረት አልተሰማውም ነበር፡፡ ግና! ‹አንድ ለእናቱ› እንዲል አቤ ጎበኛ፣ የተቃውሞውን ስብስብ የምትወክል አንዲት ወንበር ሾልካ ወደ ምክር ቤቱ በመግባቷ፣ ፓርቲው ዛሬም ድረስ እንደ እግር እሳት እያንገበገበችው መሆኑን በተለያየ መንገድ እያሳየን ነው፡፡ 

 የሆነው ሆኖ ኢህአዴግ ከዚህ ትምህርት በመውሰድ በሚቀጥለው ዓመት በሚደረግው ‹‹ምርጫ›› እንዲህ አይነት‹እንዝህላልነትን› ለማረም በከፍተኛ ዝግጅት መጠመዱን የሚጠቁሙ መረጃዎች እያፈተለኩ ነው፡፡ መቼም የጉዳዩ እውነትነት ከተረጋገጠ፣ ምናልባትም በ2012 ዓ.ም ልክ እንደ ኤርትራ ወይም እንደ ቻይና ‹ልማታዊ መንግስት እንጂ ምርጫ የሚባል ነገር አያስፈልግም! የምርጫ ፖለቲካ የኒዎ-ሊበራሊስቶች አጀንዳ ነውና!!› ከማለት የሚመለስ አይመስለኝም፡፡ ማን ያውቃል? …እንዲህ እንደዛሬው የሶስት ሺ ዓመት ታሪክ ያላትን እና የዘጠና ሚሊዮን ሕዝብ አገርን ፍርሃት በመንዛት አሸንፎ ከቆየ የምናየው ይሆናል፡፡ 

 ከዚህ ባለፈ ቀጣዩን ‹‹ምርጫ›› በፍፁማዊ ጠቅላይነት ለመጨረስ እያደረገ ያለው መሰናዶ በሶስት የተከፈለ ነው፤

 የመጀመሪያው ለመላው የድርጅቱ አባላት (የመንግስታዊ ተቋማት ኃላፊዎችን ጨምሮ) የተዘጋጀው ፓኬጅ ነው (ሰሞኑን በተለያዩ ከተሞች ስለ ‹አውራ ፓርቲ› አስፈላጊነት እና የ‹ልማታዊ መንግስት›ን ጠቀሜታ በተመለከተ እየተሰጠ ያለው ሥልጠናም የዚሁ አካል እንደሆነ ሰምቻለሁ)፤ 

ሁለተኛው መራጩ ሕዝብ ላይ በተናጥል አተኩሮ ለመተግበር እየተሞከረ ካለው ቀመር ጋር የሚያያዝ ሲሆን፤ ይህም እንደ ቀድሞው ሁሉ ለአቅመ-ምርጫ የደረሰውን ህዝብ በኮንዶሚንየም፣ በመልካም አስተዳደር እና በማይጨበጡ የተስፋ ፕሮፓጋንዳዎች ማማለልን የሚያካትት ነው፤ የመጨረሻው ደግሞ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና የግሉ የህትመት ሚዲያ ላይ ያነጣጥራል፤ በዚህ ፅሁፍም አጀንዳ የምናደርገው አገዛዙ በዚህኛው ግንባር ከሚያስወነጭፋቸው የ‹ጦር መሳሪያዎች› በዋነኛነት በዘጋቢ ወይም በዶክመንተሪ መልክ የሚያዘጋጃቸው ፊልሞችን የተመለከተ ነው፡፡ 

 ስውሩ አጀንዳ… 

 በርግጥ ይህ አይነቱ አሰራር ዛሬ የተጀመረ አይደለም፤ ባለፉት ሃያ ዓመታት በሙሉ ሲተገበር የነበረ ነው፡፡ በተለይ ሕዝባዊ ተቃውሞን የመሰለ ለሥልጣን የሚያሰጋ ድንገቴ አጋጣሚ ሲከሰት የሚመረቱት ፊልሞች ቁጥርም እንዲሁ ይጨምራል፤ እንደ ምሳሌም የ1993ቱን የህወሓት ክፍፍልን ተከትሎ በየአካባቢው የሕዝብ ማጉረምረም በበረታበት ወቅት፣ የሰሜን አፍሪካ አብዮት በጋመበት ማግስት እና የእስልምና እምነት ተከታዮች ሕገ-መንግስታዊው የኃይማኖት ነፃነት እንዲከበርላቸው በአደባባይ በጠየቁባቸው ጊዜያት በ‹‹ዘጋቢ ትዕይንት›› ስም የተሰራጩትን ብቻ መመልከቱ በቂ ነው ብዬ አስባለሁ (በነገራችን ላይ እንዲህ አይነት ጭብጥ ያላቸው ፊልሞች ደራሲያን፣ የስርዓቱ ዋነኞች ‹ኤጲስ-ቆጶሳት› እንጂ ተቋሙ የሰበሰባቸው ብላቴና ልማታውያን ጋዜጠኞች አይደሉም) 

 ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የመረጃ ምንጮቼ እንዳረጋገጥኩት ‹ዶክመንተሪ ፊልሞች› የሚዘጋጁት በሁለት መንገድ ነው፤ የመጀመሪያው በኢቲቪ ባልደረቦች ሃሳብ አመንጪነት በፕሮፓጋንዳ ላይ የሚያተኩር ሲሆን፣ በሚመለከታቸው ባለሥልጣናት ይሁንታን ሲያገኝ እንዲተላለፍ የሚደረግ ነው፡፡ ሌላኛው ደግሞ፣ በጉምቱ የፓርቲው መሪዎች የጭብጥ አሰናጅነት ሙሉ ድራማው አልቆለት በቀጥታ አየር ላይ እንዲውል ወደ ጣቢያው የሚላከው ነው፡፡ በዚህ ዘውግ የሚመደቡት አብዛኛዎቹ ፊልሞች ተቃዋሚ ፓርቲዎችን፣ በግል ሚዲያ ላይ የተሰማሩ ጋዜጠኞችን፣ የኃይማኖት መሪዎችን እና ዓለም-አቀፍ ተቋማትን በመወንጀልና በመዝለፍ ላይ የሚያውጠነጥኑ ናቸው (የቅርቦቹን እንኳ ለማስታውስ ያህል ብንጠቅሳቸው ይህንኑ ያስረግጣሉ፡- ‹አዲስ አበባን እንደ ባግዳድ›፣ ‹አኬልዳማ›፣ ‹ጀሀዳዊ ሀረካት›፣ ‹ሽብርተኝነት በኢትዮጵያ› እና የመሳሰሉት) 

 በጥቅሉ እስከ 2004 ዓ.ም መገባደጃ ድረስ የእነዚህ ፊልሞች ደራሲ አቶ መለስ ዜናዊ የነበረ ሲሆን፤ ከእርሱ ህልፈት በኋላ የኮሚኒኬሽን መ/ቤት (ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የጠቅላይ ሚንስትሩ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር አማካሪዎች) በደህንነት እና ፀረ-ሽብር ግብረ ኃይል ስም እንደሚያዘጋጁት ውስጥ-አወቅ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ኢቲቪ በእንዲህ አይነት ጭብጥ ዙሪያ በሚያውጠነጥኑ ፊልሞች ላይ ምንም አይነት ተሳትፎ አያደርግም፤ ሳይቀንስና ሳይጨምር ለሕዝብ ማስተላለፍ አማራጭ ያልተተወለት ብቸኛ ግዴታው ነው፤ የህወሓቱ ሰው ገራገሩ የተቋሙ ስራ አስኪያጅ ዘርዓይ አስግዶምም ቢሆን ይህ ኃላፊነት ሲሰጠው ትጉህ አገልጋይነቱ ለማን እንደሆነ ጠንቅቆ ያውቀዋልና፣ 

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በፍፁም ፈቃደኝነት ሥራውን ከማሳለጥ በቀር የሚቃወምበት ወይም የኤዲቶሪያል ነፃነቴን አላስገፋም ብሎ የሚቀብጥበት አንዳችምክንያት የለውም፡፡ በግልባጩ ውዳሴ መለስ፣ ስደት፣ የአባይ ቁጭት፣ የኮንዶሚንየም ቤቶችንና መሰል ጉዳዮችን በተመለከተ ደግሞ ሩቅአላሚዎቹ ‹‹ልማታዊ ጋዜጠኞች››፣ እንቅልፍ አጥተው የሚጨነቁበትና እርስ በእርስ ለመቀዳደም የሚተጉበት አጀንዳ ስለመሆኑ ራሱ በረከት ስምዖንም ገና ድሮ የገባው ይመስለኛል (በነገራችን ላይ በየጊዜው ጥቂት የጣቢያው የተለያዩ ፕሮግራም አዘጋጆች እና የዘጋቢ ፊልም ባለሙያዎች የቻይናን የሚዲያ ተሞክሮ አጥንተው እንዲመጡ እንደሚደረግ ይታወቃል) 

 ለዚህ ፅሁፍም እንደ ማሳያ የምጠቅሰው፣ ባለፈው ሳምንት ‹‹ሽብርተኝነት በኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ ለተመልካች የቀረበው ዘጋቢ ፊልም፣ ሙሉ በሙሉ በብሔራዊ መረጃ መ/ቤት ስም የተዘጋጀ ሲሆን፣ በንባብ የተሳተፉት ሁለቱ ‹‹ጋዜጠኞች››ም የኢቲቪ መደበኛ ባልደረቦች እንዳልሆኑ ከምንጮቼ አረጋግጫለሁ፡፡ ምንም እንኳ የፊልሙ ‹ባለቤት› የሆነው የደህንነት ቢሮ በሽብርተኝነት ዙሪያ የሚያውጠነጥን ነው ቢለንም፣ እንዲተላለፍ የተፈለገው ዋነኛ መልዕክት በቀጥታ ከቀጣዩ ምርጫ ጋር የተያየዘ ነው ወደሚል ጠርዝ የሚገፉንን ማሳያዎች መምዘዝ የሚቻል ይመስለኛል፡፡ እንዴት ሆኖ? የሚለውን ጥያቄ በአዲስ ርዕስ ሥር እናፍታታው፡፡ 

 ከፍርሃት ጋር ወደፊት! 


 በዚህ ፊልም ላይ ዋነኛ አጋፋሪ ሆነው የቀረቡት ሶስት ሰዎች ናቸው፤ የኮሚኒኬሽን ጽ/ቤት ሚኒስቴር ሚንስትር ዲኤታ ሽመልስ ከማል (ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በእንዲህ አይነት ፊልሞች ላይ የመሪ-ተዋናይነትን ገፀ-ባህሪ ወክሎ መጫወቱን እየተካነው እንደሆነ እኔም ራሴ እመሰክርለታለሁ¡)፣ የፌደራሉ ዋና ዓቃቢ-ሕግ ብርሃኑ ወንድማገኝ እና አቶ ዘሪሁን ተሾመ (ይህ ሰው ደግሞ አሉባልታና ጠቀሜታቸው ረብ-የለሽ የሆነ ወሬዎችን በማቅረብ የሚታወቀው የ‹ዛሚ-90.7› ሬዲዮ ባለቤት ሚሚ ስብሃቱ የትዳር አጋር ነው) ከትዕይንቱ መካከል የሚታወሱ ፊቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ድራማው ተጀምሮ እስኪያልቅ ድረስ ተሰፍሮ የተሰጣቸውንና በፈጠራ ታሪክ የተሞላውን ‹ስክሪፕት› ቃል-በቃል ሸምድደው መምጣታቸውን በግልፅ በሚያሳይ መልኩ ሲያነበንቡ ላስተዋላቸው ተመልካች ‹‹ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች›› የጣሉባቸውን ግዴታ በቁርጠኝነት ለማስፈፀም ‹ቀራኒዮ› ድረስ የሚጓዙ ሊመስለው ቢችል አይፈረድበትም¡ መቼም አገዛዙ ዓለማዊ ፍላጎታቸውን እስካሟላላቸው ድረስ ሀገር፣ ሕገ-መንግስት፣ ሕሊና… ደንታ ሳይሰጧቸው ሕዝብን በማሸበር የስርዓቱ ዕድሜ ይረዝም ዘንድ ‹ከፍርሃት ጋር ወደፊት!!› ለማለት የማያመነቱ ሰዎችን በዙሪያው የኮለኮለው ለእንዲህ አይነቱ ጊዜ ነው፡፡ 

 የሆነው ሆኖ ፊልሙ ከቀድሞዎቹ አንፃር እንኳ ሲመዘን የወረደና አሰልቺ ቢሆንም፣ ያን ያህል ከተደሰኮረለት የ‹‹ሽብርተኝነት ጉዳይ›› ባሻገር ሁለት ያደፈጡ ስውር ዓላማዎች ያሉት ይመስለኛልና፣ እነርሱን ነጣጥለን እንመልከት፡፡ 

 ፩ 
 የቀደሙ ልምዶችን ተንተርሰን ስናብሰለስለው፣ የዘጋቢ ትዕይንቱ ድብቅ ዓላማ ተደርጎ ሊጠቀስ የሚችለው የመጀመሪያው የቢሆን ሃሳብ፣ ኢህአዴግ ከምርጫው መዳረሻ በፊት በተቃውሞ ፖለቲካው ውስጥ ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ ያሉ የተወሰኑ የአመራር አባላትን እና ጥቂት ጋዜጠኞችን እንደተለመደው ከግንቦት 7 ጋር አቆራኝቶ ለማሰር እየተዘጋጀ ነው የሚል ይሆናል፡፡ በርግጥም ይህንን መከራከሪያ ከመቀበል ሌላ አማራጭ የሚያሳጡ ሁለት ገፊ ምክንያቶች አሉ፤ አንዱ ፓርቲው ቀጣዩን ምርጫ ከትግል ዘመኑ ጀምሮ ይመራው ከነበረው ጉልበታሙ አቶ መለስ ውጪ የሚያደርገው መሆኑ ያሳደረበት ስጋት ወደ ጭፍን አምባገነንት እንዲቀየር ከማስገደድ አልፎ፣ ይህንኑ የሰውየውን ህልፈት ተከትሎ የተከሰተው የኃይል መከፋፈል ያነበረው የመሳሳት ተፅእኖ ይመስለኛል፤ እነዚህ ኩነቶችም ስርዓቱ ህልውናውን ካፀናበት አምባገነናዊ ባህሪው አኳያ ድንገቴ እርምጃ እንዲወስድ መግፋታቸው የሚጠበቅ ነው፡፡ 

 ሁለተኛው ደግሞ ካደረ ተሞክሮው የሚነሳ ነው፤ ይኸውም በ2002ቱ ምርጫ ዋዜማ በተልካሻ ምክንያት የአንድነት ለፍትሕና ዴሞክራሲ ሊቀ-መንበር የነበረችውን ብርቱካን ሚደቅሳን እስር ቤት በመክተት ፓርቲውን እና የተቃውሞ ደጋፊ ኃይሉን እስረኛ በማስፈታት አጀንዳ እንዲጠመድ ያደረገበት ስልት እና ሁነቱ የፈጠረው ማሕበረሰባዊ የፍርሃት ድባብ ያስገኘለት ጠቀሜታን ሊከልሰው መሞከሩ አይቀሬ መሆኑ ነው፡፡ በአናቱም በወቅቱ ከፍተኛ ተነባቢነት የነበራትን የ‹‹አዲስ ነገር›› ጋዜጣ አዘጋጆች ምርጫው አራት ወር ብቻ ሲቀረው በግልፅና ስውር ጫና ጋዜጣውን ዘግተው ከሀገር እንዲሰደዱ ያደረገበት መንገድም የዚሁ አፈና ጉትያ እንደነበረ አለመዘንጋቱ፣ በቅርብ ከሚፈጠሩ ተመሳሳይ ክስተቶች ጋር ለማያያዝ ያስችላል፡፡ 

 ፪ 
 ሌላኛው የዘጋቢ ፊልሙ ዓላማ በቀጣዩ ምርጫ ለውጥ ፈላጊውን የህብረተሰብ ክፍል ወደ ተቃውሞ ጎራ ሊያሰባስብና መነቃቃት ሊፈጥር ይችላል የሚል ብርቱ ጥርጣሬ ያሳደረበትን የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን (ኢሳት) ጣቢያን በመርገም (በሽመልስ ከማል አነጋገር ‹‹ውጉዝ ከመአርዮስ›› በማለት) የተቀናቃኝ ድምፆች በተከበበላቸው ሞገድ ብቻ እንዲሰሙ ማስገደድ ነው፡፡ ይህ ሁናቴ አገር ውስጥ ያሉ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች እና ጋዜጠኞች ለጣቢያው ቃለ-ምልልስ እንዳይሰጡ በፍርሃት ቆፈን መሸበብንም ያከተተ ነው፡፡ 
አስደንጋጩ ጉዳይ ደግሞ መከራከሪያ ሆኖ የቀረበው ሕገ-መንግስታዊው ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ሳይሆን፣ ለሚዲያ ተቋሙ የብሶት መግለጫዎችን መስጠትም ሆነ ኢ-ፍትሀዊ አሰራርን ማጋለጥ በሽብርተኝነት እንደሚያስከስስ የሚተርክ ‹‹ዶክመንተሪ ፊልም›› መሆኑ ነው፡፡ በርግጥ ለዚህ ማስፈራሪያ እንደ መደገፊያ የተጠቀሙት ፀረ-ሽብር ሕጉ በግብረ-አበርነት ተጠያቂ የሚያደርግበትንየተለጣጭነት ባህሪውን አፅንኦት በመስጠት እንደነበረ ታዝበናል፡፡

 በፊልሙ ላይ አቶ ዘሪሁን ምሬት በዋጠው ድምፅ ‹‹ኢሳት የግንቦት 7 ወፍጮ ነው!›› የሚል መፈክር ሲያሰማ፣ ሽመልስ ከማል ደግሞ የአዋጁ ዋነኛ ዓላማ ከዚህ ቀደም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ‹አሸባሪ› ተብለው ከተፈረጁት ድርጅቶች ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንዳይኖር ለማድረግ እንደሆነ ምሎ-እየተገዘተ ተመልካቹን በፍርሃት ለማንበድበድ ሲሞክር ተስተውሏል፡፡ ይሁንና የአቶ 
ሽመልስን እርግጠኛነት ለማመን አመክንዮ መጠቀም የግድ ይሆናል፤ እናም ኢሳት የእነዚህ ድርጅቶች ዓላማ አራማጅ መሆኑን ለማሳየት ምን ተጨባጭ ማስረጃ አቀረባችሁ? ለሚለው ጥያቄ እየነገሩን ካለው እንቶ-ፈንቶ ባለፈ በማስረጃ የተደገፈ መልስ መስጠት የሚኖርባቸው ይመስለኛል፡፡ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የኤርትራ መንግስት ከሰጠው አምስት መቶ ሺህ ዶላር ውስጥ ሁለት መቶ ሺውን ለኢሳት ሥራ ማኪያሄጃ እንዲውል መወሰኑን በስልክ ሲናገር ከማሰማት በዘለለ ማለቴ ነው፡፡ 

 እግረ-መንገድ ለመጥቀስ ያህል የዚህ ፅሁፍ ዓላማ ኢሳትን መንግስት ለምን ወነጀለው በሚል ግብረ-መልስ መስጠት አለመሆኑን 
ማስገንዘቡ አስፈላጊ ይመስለኛል፤ መነሻ ምክንያቴ እንደ ሚዲያ ተቋምነቱ ከእኔ ሞያ ጋር በቀጥታ መገናኘቱ ሲሆን፤ ለምን ይህ ሆነ? 
ያልኩበት ተጠየቅም የሕግ የበላይነት ጉዳይ ብቻ በመሆኑ ነው፡፡ ምክንያቱም የተመለከትነው ፕሮግራም ኢሳት እስከ ዛሬ ባሰራጨው ዘገባ ላይ ‹አሸባሪ› ሊያስብለው የሚያስችል ትዕዛዝ ያስተላለፈበትን ወይም ንፁሃን ኢትዮጵያውያንን በተጠመደ ፈንጂ ዶግ-አምድ እንዲሆኑ መቀስቀሱን የሚያጋልጥ ሳይሆን፣ በሰላማዊም ሆነ በትጥቅ ትግል ከተደራጁ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር አባላት ጋር ያደረገውን ቃለ-መጠይቅ ብቻ በመደጋገም ነው፡፡ ለዚህም ይመስለኛል የዘጋቢ ፊልሙ ድብቅ ዓላማ ስርዓቱ በሀገር ውስጥ ያሉትን ጥቂት የግል የሕትመት ሚዲያዎች በፈርጣማ የፖለቲካና ቢሮክራሲ ክንዱ ደቁሶ ካኮሰመነ በኋላ፣ በተወሰነ መልኩም ቢሆን ድምፅ ላጡት ድምፅ መሆን እየቻለ የመጣውን እና ለተፎካካሪ ፓርቲዎች አማራጭ የሚዲያ ምህዳር የፈጠረውን የቴሌቪዥን ጣቢያ ከተለመደው የአፈና መንገድ /ጃሚንግ/ በተለየ ስልት ከጨዋታ ውጪ ለማድረግና በቀጣዩ ምርጫ ‹አውራ ፓርቲ›ነቱን ለማስጠበቅ የሚያደርገው ዝግጅት ነው እንድንል 
የተገደድነው፡፡ 

 ከዚህ ቀደም እነ እስክንድር ነጋ በግንቦታ 7 አባልነት ተወንጅለው በታሰሩበት ወቅት አቶ መለስ ዜናዊ ለፓርላማው ‹‹ክምር ማስረጃ አለን›› ቢልም፣ ጉዳዩ ፍርድ ቤት ሲቀርብ ግን በጨበጣ እንደገባበት ማየታችን አደባባይ የወጣ ሀቅ ነበር፤ በርግጥም ማስረጃ ሆኖ የተቆጠረው ራሱ ያዘጋጀው ‹‹አኬልዳማ›› የሚል ‹‹ዘገቢ ፊልም›› እንደነበረ ስንመለከት፣ ይህ ስርዓት አስቀድሞ የተናገረበት ጉዳይ ስህተት መሆኑ እንዳይጋለጥ ምንም ነገር ከማድረግ እንደማይመለስ እንታዘባለን (በነገራችን ላይ በወቅቱ በፍትህ ጋዜጣ ‹‹አኬልዳማው! የአይሁድ ወይስ የኢህአዴግ?›› በሚል ርዕስ የዘገባውን ፈጠራነት በተጠናከረ ማስረጃ ለማጋለጥ ከተሞከረ በኋላ እንዲህ የሚል ምክር አዘል ቁም-ነገር ተላልፎ እንደ ነበር አይዘነጋም፡- 

‹‹ሆሊውድ የሚሰሩ አስፈሪ (ሆረር) ፊልሞች እንኳ ቢያንስ ከ16 ዓመት በታች ያሉ ልጆች እንዳያዩአቸው የሚከለክል ሕግ አለ፣ ኢቲቪ ግን የተበጠሰ አንገት፣ የተገነጠለ ክንድ፣ የተቆረጠ እጅ፣ የተፈረከሰ ጭንቅላት… እያሳየ፣ ‹13 ዓመት የሞላው ሕፃን በሙሉ ሊያየው ይችላል› ማለቱ ኃላፊነት የጎደለው አሰራር ነው›› 

 ባለፈው ሳምንት በቀረበው ፊልም ላይ ቢያንስ ይህ ሁኔታ ታርሞ ከ16 ዓመት በታች ያሉ ልጆች ሊያዩት እንደማይገባ ከሚያስጠነቅቅ መልዕክት ጋር መተላለፉ ስርዓቱ ምክር መስማት ጀመረ እንዴ? እንድንል የሚያጭር ነው፡፡ በርግጥም በሌሎች ጉዳዮችም እንዲህ ቢያዳምጡን ኖሮ፣ እየዋጣቸው ካለው ጥልቅ ጨለማ ራሳቸውን መታደግ የሚችሉበት በርካታ ዕድል ነበር፡፡) 

 የሆነው ሆኖ በዚህና መሰል ፊልሞች ላይ የሚነሳው ሌላው ለትዝብት የሚያጋልጠው ጉዳይ የደህንነት ተቋሙ ሁሉንም ዜጋ 
አብጠርጥሬ አውቃለሁ የሚለው ማንአህሎኝነቱ ነው፡፡ አስቂኙ ጉዳይ ግን በአዋጅ የተቋቋሙት የመረጃው መስሪያ ቤት እና የፀረ-ሽብር ግብረ-ኃይል፣ ያሻቸውን ዜጋ ቤት (በስውርም በግልፅም) መበርበር፣ ስልክ መጥለፍ፣ የኢ-ሜል እና የማሕበራዊ ሚዲያዎችን አካውንት ‹የሚስጥር ቁልፍ ቃላት› ሰብሮ መፈተሽ… ከሚያስችል ያልተገደበ ሥልጣን ጋር የሚንቀሳቀሱ ቢሆንም፣ ሽብርተኝነትን ለመከላከል እንደ አዋጭ መፍትሄ የወሰዱት ‹ዶክመንተሪ ፊልም›ን እስኪመስል ድረስ በሳምንት አንዴ መመልከቱ የተለመደ መሆኑ ነው፡፡ ርግጥ እንዲህ አይነት ትዕይንቶች ተጨማሪ ስርዓታዊ ጠቀሜታቸው ማህበራዊ ተቀባይነታቸው የጎላ ዜጎችን በስቅየት (ቶርቸር) እያንበረከኩ በቴሌቭዥን መስኮት አንገት አስደፍተው በማቅረብ ትውልዱ ተጠራጣሪና ድንጉጥ እንዲሆን ያላቸው አስተዋፆኦ አንዱ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ይህው ቃል በሚከሰሱት ንፁሀን ላይ ተመልሶ እንደ ማስረጃ ተቆጥሮ፣ ከአስር ዓመት እስከ ዕድሜ ልክ የሚደርስ ቅጣት በ‹ካንጋሮው› ፍርድ ቤት እንዲጣልባቸው የሚያደርገው ግፈኝነት ነው፡፡ ለዚህም ቅጥ ያጣ አምባገነንነት አይደፈሬ ሥልጣኑ የሰጠውና ገና ሲረቅቅ ጀምሮ ጠንካራ ተቃውሞ ሲቀርብበት የነበረውን የፀረ-ሽብር አዋጅን የሕጋዊነት ከለላ አድርጎ እየተባባሰ በመጣ መልኩ መጠቀሙን መቀጠሉ ነው፡፡ 
ከጥቂት ሳምንታት በፊት የታተመው ‹‹ኒውስ ዊክ›› መፅሄት ‹‹Ethiopia declares war on gay men›› በሚል ርዕስ ባስነበበው አደገኛ መጣጥፍ አዋጁን ያብጠለጠለበት ሀረግ የትችቶቹን ሙሉ መንፈስ የሚጠቀልል ይመስለኛልና እዚህ ጋር ልጥቀሰው፡- ‹‹የፀረ-ሽብር ሕጉ መንግስት ሽብርተኝነት ብሎ የሚያስበውን ጉዳይ በ‹መፃፍ፣ ማቀናበር፣ ማተም ወይም ማሰራጨት› የሚከሰውን ዜጋበሃያ ዓመታት እስር እንዲቀጣ ፈቅዶለታል፡፡›› 

 እነዚህን ነገሮች ጠቅልለን ስንመለከት ገዥው ፓርቲ ለሀገሪቱ ስጋት እንደሆነ የሚነግረንን ሽብርተኝነት ራሱ ባዘጋጀው ሕገ-መንግስት ሳይሆን፣ በዶክመንተሪ ፊልም ጎርፍ ለመግታት ነው የተዘጋጀው ወደሚል ጠርዝ ይገፋናል፡፡ በርግጥ የፓርቲው አላማ ሥልጣኑን መጠበቅ ነውና ሕገ-መንግስቱን ወዲያ ጥሎ ዘጋቢ ፊልሞች ላይ ቢንጠለጠል እንዴት ልንገረም እንችላለን?! 

 ወደ የፍርሃት ‹ሪፐብሊክ› 

ይህች መከረኛ ሀገር በደርግና በኢህአዴግ ከተሠጣት ቅጥያዎች አንዱ ‹‹ሪፐብሊክ›› የሚል እንደሆነ ይታወቃል (የደርጉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሲል፤ ይህኛው ደግሞ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ነች ይለናል)፡፡ ዝርዝር ሃተታውን ትተን ከዚህ ፅሁፍ አውድ አንፃር የሪፐብሊክን ብያኔ ሕዝባዊ መንግስትነት የሚል ትርጓሜ ሰጥተን ማለፍ ይበቃል፡፡ ይሁንና የተሻገርናቸው ሁለት አስርታት የሚያስረግጡት ብቸኛ እውነት ቢኖር ሀገሪቱ ከዚህ የተጠያቂ መንግስት ምስረታ ተፃራሪ የሆነውን መንገድ መምረጧን ነው፡፡ ከላይ ለማሳያነት የጠቀስኩት ዶክመንተሪ ፊልምም ሆነ ተያያዥ አፋኝ ሕጎቹ እና ፖለቲካዊ አተገባበራቸው በፍርሃት የሚርድ ማሕበረሰብ በመፍጠር፣ ቀጣይ አስርታቱን ካለአንዳች መደነቃቀፍ ረግጦ መግዛትን ዋነኛ ግብ ያደረጉ ናቸው፡፡ ይህን ተቋማዊነትን ተደግፎ የሚካሄደው መንግስታዊ ሽብር፣ በአንዳች ክስተት ብርክ በሚያናውጣቸው ዜጎች ማሕበረሰቡ እየተሞላ እንደሚሄድ ግልፅ ነው፤ ከፌደራላዊ ወደ ፍርሃት ሪፐብሊክ እየተደረገ ባለው በዚህ ጉዞ፣ ሀገሪቱን ከዝግመታዊ ሞት ለመታደግ የበረቱ መዳረሻቸውን ስርዓቱ አዘጋጅቷል፡፡ እናም ዋጋው ምንም ቢሆንም በአደባባዩ ላይ የሚደረግ የተቃውሞን እንቅስቃሴ፣ ኢህአዴግን ከሥልጣን የማውረድ ብቻ ከመሆን መታለፉን በሚገባ ልናስብበት እንደምንገደድ ይሰማኛል፡፡ እነርሱ ከሚቀጥለው ምርጫ በፊትም ሆነ በኋላ ሕዝባዊ ምህዳሩን ምንም አይነት የተቃውሞ ድምፅ የማይሰማበት ምድረ-በዳ ለማድረግ ይህን ያህል ርቀት መጓዛቸውን ስንመለከት ምርጫችን ሁለት ብቻ ይሆናል፡፡ ቀጣዩን ትውልድ በፍርሃት ሪፐብሊክ ውስጥ ትቶ ማለፍ፣ አሊያም አደባባዩን በጨኸት መሙላት፡፡ 



                                                                                      posted by A.G










Sunday 12 January 2014

‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ የጥላቻ ፖለቲካ ማብቃት አለበት››

ኢንጂነር ግዛቸው ሺፈራው፣  የአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር

የምርጫ 97ን ቀውስ ተከትሎ ወደ እስር ቤት ከገቡት የቀድሞዎቹ የቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ (ቅንጅት) አመራሮች መካከል አንዱ የነበሩት ኢንጂነር ግዛቸው ሺፈራው፣ በቅርቡ የአንድነት ለፍትሕና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ሊቀመንበር ሆነው ተመርጠዋል፡፡ ስለአዲሱ ሊቀመንበርነታቸው፣ ስለመጪው ዓመት ምርጫና ሌሎች ጉዳዮች ነአምን አሸናፊ አጋግሯቸዋል፡፡


ሪፖርተር፡- አንድነት የወጣቶች ፓርቲ ነው ይባላል፡፡ ነገር ግን አመራሩ ላይ ወጣቶች አይታዩም በማለት የሚተቹ አሉ፡፡ የእርስዎን ዳግም ሊቀመንበር ሆኖ መመረጥንም እንደ ምሳሌ ያነሱታል፡፡ ለምንድነው ወጣቶች ወደ አመራር የማይመጡት? 


ኢንጂነር ግዛቸው፡- ይህንን ጥያቄ መጠየቅ ያለባቸው መራጮች ናቸው፡፡ መራጮችንና የአንድነት አባላትን መጠየቅ ነው፡፡ በመሠረቱ አንድነት የወጣቶች ፓርቲ ነው፡፡ ባለፈው ሥራ አስፈጻሚም ሆነ በብሔራዊ ምክር ቤቱ የወጣቱ ተሳትፎ ከፍተኛ ነበር፡፡ በጠቅላላ ጉባዔው ሰባ በመቶ አካባቢ ወጣት ነው፡፡ የተወዳደርኳቸው ሰዎችም ወጣቶች ናቸው፡፡ ስለዚህ ይህ ነገር መጠየቅ ያለባቸው አባላትና ጉባዔው ናቸው፡፡
መጠየቅ ያለበት እኔ ፍላጎት ኖሮኝ ወጣቶችን ወደታች ገፍቼ ድርጅታዊ ሥራ ሠርቼ ብመጣ ኖሮ ነበር፡፡ ወጣቶችን ወደታች ተጭነሃል ማለት ይቻል ነበር፡፡ ዋናው ማየት ያለብን ጠቅላላ ጉባዔውና አጠቃላይ ሒደቱ ዲሞክራሲያዊ ነበር ወይስ አልነበረም ነው፡፡ በእኔ ግምት አንድነት ፓርቲ ለዲሞክራሲያዊ አሠራር ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ ፓርቲዎች የሚበልጠው ያለ አይመስለኝም፡፡ ለዚህም የምገልጸው በምክር ቤታችንም በሕገ ደንባችን መሠረት የምንሰበሰበው በሦስት ወር አንዴ ነበር፡፡ ምክር ቤቱ ግን በዓመት እስከ 20 ጊዜ ይሰበስባል፡፡ ምክንያቱም የጀመርነውን አጀንዳ በምናደርገው ሰፊ ውይይት መጨረስ አንችልም፡፡ አጀንዳ ጨርሰን አናውቅም፡፡ አራት አጀንዳዎች ቀርበው እንደሆን ሁለቱን ጨርሰን ሁለቱን ደግሞ ለሚቀጥለው ጊዜ እናስተላልፋለን፡፡ ይህ ደግሞ የዲሞክራሲያዊ ውይይት ነፀብራቅ ነው፡፡
እኔ እንዲያውም ቅስቀሳ አላደረግኩም፡፡ የእኔ ተወዳዳሪዎች ቅስቀሳ አድርገዋል፡፡ ስለዚህ ምርጫው ዲሞክራሲያዊ ነው ወይም አይደለም? የሚለው ነው ጥያቄው፡፡ ዲሞክራሲያዊ ነበር፡፡ ለምን ወጣቶች አልመጡም ለሚለው የእነሱ ምርጫ ነው፡፡ እኔ በአብዛኛው የተመረጥኩት በወጣቶች ነው፡፡ ምናልባት ከዚህ በፊትም እንዳደረግኩት ወጣቶችን የማሳተፍ አመለካከትና ባህሪ አለኝ፡፡ እኔ አመራር በነበርኩበት ጊዜ በሕገ ደንቡ መሠረት በሥራ አስፈጻሚ 13 አባላት ነው የሚኖሩት፡፡ እኔ ግን ወጣቶች ወደፊት እንዲቆጠሩ ስድስት አባላት ድምፅ የመስጠት ሥልጣን ሳይኖራቸው አስገብቻለሁ፡፡ ደንቡ ስለማይፈቅድልኝ ነው እንጂ ባለድምፅ ሆነው መግባት ይችሉ ነበር፡፡ ደንቡ ግን አይፈቅድም፡፡ ስለዚህ ድምፅ አልባ ከመሆናቸው በስተቀር ሙሉ በሙሉ የአመራር አባል ነበሩ፡፡
አቶ ግርማ ሰይፉም የዚያ አባል ነበሩ፡፡ ሌላው ወጣቱን ለዚህ ቦታ ማንም አልከለከለውም፡፡ አንዳንድ ጊዜ የተሳሳተ አመለካከት አለ፡፡ ሜካኒካል ይሆናል፣ ኮታ ይሆናል፡፡ ወጣቶች መምጣት አለባቸው፡፡ የኮታ ጉዳይ አይደለም፡፡ ይህ የመብት ጉዳይ ነው እንጂ የሚሰጣቸው ስጦታ አይደለም፡፡ ስለዚህ በአንድነት ፓርቲ ለወጣቶችም ሜዳው ክፍት ነው፡፡ ነገ ጠዋት የላቀ ከመጣ ምክር ቤቱ በወጣት ሊተካ ይችላል፡፡ ከፖለቲካም አንፃር መታየት ያለበት ስብጥሩ ነው፡፡ ከወጣቶችም፣ ከጐልማሶችም፣ ከአዛውንትም ያ ስብጥር ነው መሆን ያለበት፡፡ ወጣትም ሆኖ ሽማግሌም ሆኖ የራሱ የሆነ ችግር አለበት፡፡ ያንን የሚያቻችለው መቀላቀሉ ነው፡፡


ሪፖርተር፡- በተቃዋሚውም ሆነ በገዥው ፓርቲ ውስጥ ያሉት የ60ዎቹ ትውልድ አባላት አመራርነት የሚያበቃውና ወጣቶች በሰፊው ወደ መሪነት የሚመጡት መቼ ነው? 


ኢንጂነር ግዛቸው፡- በእኔ በኩል በአመዛኙ በአንድነት ፓርቲ ውስጥ የ60ዎቹ ትውልድ ፖለቲካ የሚለው አይሠራም፡፡ ባለፈው አላየነውም አሁንም አይታይም፡፡ የአንድነት ዕድሜ ስድስት ዓመት ነው፡፡ በስድስት ዓመት ጊዜ ውስጥ አራት ፕሬዚዳንቶችን ለውጧል፡፡ የመጀመሪያዋ ብርቱካን ሚደቅሳ ነበረች፡፡ የወጣቶች ተወካይ ነበረች፣ የ60ዎቹ አይደለችም፡፡ ከዚያ እርሷ ስትታሰር እኔ ተጠባባቂ ሆኜ ኃላፊነቱን ተረከብኩ፡፡ ከዚያ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ሆነ፣ አሁን እኔ መጣሁ፡፡ ማንም ፓርቲ በስድስት ዓመት ውስጥ አራት ፕሬዚዳንት የቀየረ የለም፡፡ ይህ የሚያሳየው የአንድነትን ዲሞክራሲያዊነት ነው፡፡ በመሠረቱ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ብቃት ባለው ከ60ዎቹ በኋላ ባለው ትውልድ መተካት አለበት፡፡ ያ የእኔ እምነት ነው፡፡ የ60ዎቹ ፖለቲከኞች መጪውን ትውልድ አብቅተው መተካት እንዳለባቸው እምነቴ ነው፡፡


ሪፖርተር፡- አሁን አንድነትን እንደ ምሳሌ ከወሰድነው መጀመሪያ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ወጣት መሪ ነበሩ፡፡ ከዚያ እሳቸው ሲታሰሩ እርስዎ መሪ ሆኑ፡፡ ቀጥሎ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣ አሁን ደግሞ ተመልሰው እርስዎ መጡ፡፡ በአንድነት ውስጥ ከወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ውጪ ያው የ60ዎቹ ትውልድ አባላት ስለሆናችሁ ከዚያ አንፃር ለማለት ፈልጌ ነው? 


ኢንጂነር ግዛቸው፡- ትክክል ያልሆነ ምዘና ነው፡፡ ምንድነው የ60ዎቹ ፖለቲከኞች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ቅድም እንዳልኩህ ስብጥሩን ነው ማየት ያለብን፡፡ ብርቱካን በነበረችበት ጊዜም ሆነ አሁን ሥራ አስፈጻሚ ውስጥ የነበሩ ግለሰቦች ጥቂት ናቸው፡፡ ምናልባት በጣት የሚቆጠሩ [እኔ፣ ነጋሶ፣ አስራት]፡፡ ነገር ግን ሥራ አስፈጻሚ ውስጥ የነበሩት አብላጫዎቹ ከ60ዎቹ በኋላ የመጡ ትውልዶች ናቸው፡፡ በአሁኑ ብሔራዊ ምክር ቤት ውስጥ ከ35 ዓመት ዕድሜ በታች ያሉት 72 በመቶ ናቸው፡፡ የ60ዎቹ አሉበት፡፡ ነገር ግን በአብላጫው ወጣቶች ናቸው፡፡ በእኔ ካቢኔ ውስጥ የ60ዎቹ ትውልድ ያለነው ሁለት ሰዎች ነን፡፡ ከ15 ሰዎች አንድ ሰው የ60ዎቹ ሆኖ ላይ ስለተቀመጠ የ60ዎቹ ተፅዕኖ አለ ለሚባለው ምዘናው ትክክል አይመስለኝም፡፡ መታየት ያለበት ይዘቱ ነው፡፡ የ60ዎቹ ትውልድ አባላት እንዲያውም የት እንዳሉ ግራ ይገባኛል፡፡ አንዳንድ ቦታ መሪ ስለሆነ ብቻ ነው፡፡ የፓርቲው መዋቅር መፈተሽ ካለበት የ60ዎቹ የፖለቲካ ተሳፊዎች ወጥተው ዳር የቆሙ ይመስለኛል፡፡ ደግሞም የተፈጥሮ ሒደት ነው፣ የፖለቲካም ሒደት ነው፣ የታሪክም ሒደት ነው፡፡ መታየት ያለበት የግለሰቦች የ60ዎቹ ትውልድ መሆን ሳይሆን ስብጥሩ ውስጥ ስንት አሉ የሚለው ነው፡፡


ሪፖርተር፡- አሁን እንደ አዲስ የአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር ሆነው መጥተዋል፡፡ ለፓርቲው ምን አዲስ ነገር ይዘው መጡ? 


ኢንጂነር ግዛቸው፡- እኛ ፓርቲያችንን የምንመራው በሥርዓት ነው፡፡ ፓርቲው በ2002 ዓ.ም. የስትራቴጂ ዶክመንቱንና የአምስት ዓመት ዕቅዱን በመጽሐፍ መልክ አውጥቶታል፡፡ የአነድነት ፓርቲ መሠረታዊ ራዕይና ግብ በዚያ ውስጥ ነው የሚታየው፡፡ እዚያ ውስጥ ያለውን ሁኔታ ነው ሁላችንም በቀጣይነት እየገነባን የምንሄደው፡፡ ነገር ግን በ2002 እና በ2003 ዓ.ም. ያወጣነው የስትራቴጂ ግንባታ ከወቅቱ ሁኔታ ጋር መዛመድ አለበት፣ መቀነባበር አለበት፡፡ ስለዚህ በዚያ መንገድ አንዳንድ ለየት ያሉ ሙከራዎች አካሂዳለሁ፡፡
የመጀመሪያው ሙከራዬ አንድነት ምናልባት ካሉት ፓርቲዎች በጉልህ ጠንክሮ የሚታይና መዋቅሩ ታች ድረስ የወረደ ነው፡፡ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ እንዲያው እንደ ሌላው ጉልበት ወይም አቅም አለን ባንልም በቂ የመንቀሳቀስ ችሎታ አለን የሚል ግምት አለኝ፡፡
ይህንን የአመራር መርህ ከአንድነት አቅምና ሕዝባዊ ገጽታ አንፃር የተለየ (Rebranding) እንዲሆን አደርጋለሁ፡፡ ለምሳሌ አንዱ ያደረግኩት ሥራ አስፈጻሚውን በአብዛኛው ወጣትና አዲስ ነው ያደረግኩት፡፡ በትምህርታቸው ብቁ የሆኑ ናቸው፡፡ በትምህርት ብትሄድ አሁን ከ15 ሰዎች ስድስቱ ሁለተኛ ዲግሪ አላቸው፡፡ ሰባቱ የመጀመርያ ዲግሪ አላቸው፡፡ ሁለቱ ደግሞ ዲፕሎማ አላቸው፡፡ አሁን ይኼ አዲስ ምልክት (New Branding) ነው፡፡ ሁለተኛ እነዚህን ሰዎች ስመድብ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ችሎታ እንዲኖራቸው አንዱ መሥፈርት ነበር፡፡ አሁን ዘመኑ ወደዚያው እያመራ ነው፡፡ ስለዚህ በኢንፎርሜሽን ግንኙነታችን ከውጭው መረጃ እኩል አንድነት መራመድ አለበት፡፡
ሌላው ትኩረት የምሰጠው ወጣቶችን የማብቃት ሥራ ነው፡፡ ወጣቶች በቅተው ፓርቲውን እንዲመሩ አደርጋለሁ፡፡ አሁን እኔ እዚህ ሆኜ ወጣቶችን ነው ወደፊት እንዲሮጡ የማደርገው፡፡ ይህን ካደረግኩ በኋላ በእኔ እምነት ክርክርም መካሄድ አለበት፡፡ እስካሁን የተካሄደው የተቃዋሚ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ ውጤት አላስገኘም፡፡ ይኼ ምንም የምንክደው አይደለምና ይህ ለምንድን ነው የሚለው ብዙ ጊዜ ይረብሸኛል፡፡ ወይ ማቆም አለብን ወይ መሥራት አለብን፡፡ እስካሁን ኢትዮጵያ ውስጥ የተበጣጠሱ ዘጠና ፓርቲዎች አሉ፡፡ ከዘጠናዎቹ ደግሞ ጉልህ የሆኑት አሥር አይሆኑም፡፡ አሥሩም አብረው መሥራት አልቻሉም፡፡ በጥምረትም በግንባርም አልተቻለም፡፡ ለምንድን ነው? ለአሥሩም ቢሆን አሥር መሪዎች አሉ፣ አሥር ፕሮግራሞች አሉ፡፡ አሥሩም እንግዲህ አሥር መሪ ኖሮዋቸው ፖለቲካ ይመራሉ የሚል እምነት የለኝም፡፡ ስለዚህ በብሔራዊ ምክር ቤትና በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውሳኔ አስገኛለሁ የሚል እምነት አለኝ፡፡
በእኔ እምነት እንግዲህ አንድነት ፓርቲ ግንባርና ጥምረት ውስጥ አይገባም፡፡ ወደ ውህደት አንድ አመራር አንድ ፕሮግራም ወዳለው እንቅስቃሴ እንገባለን የሚል እምነት አለኝ፡፡ ይህ የእኔ ሐሳብ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ስብሰባ ላይ ፈንጥቄያለሁ፡፡ ይህ መሆን አለበት፡፡ የተጀመሩት ውህደቶች በሚቀጥሉት ሦስት ወራት  ማለቅ አለባቸው ብሎ ጠቅላላ ጉባዔው ወስኗል፡፡ ወይ እንዋሀዳለን ወይ እንለያያለን፡፡ ስለዚህ በዚህ ሁኔታ አንድ የማየው እስከ 2007 ዓ.ም. ወይም በዚህ ዓመት ለእኔ የውህደት ዓመት ነው ብዬ የምገምተው፡፡ ወይ እንዋሀዳለን አለበለዚያ በሰላም ተለያይተን ሁላችንም ጉልበታችንን በየአካባቢው በትብብር እናጠናክር የሚል አመለካከት አለኝ፡፡
ይህን ካደረግኩ በኋላ ከኢሕአዴግ ጋር ገንቢ ግንኙነት (Constructive Engagement) እንዲኖረን እፈልጋለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የጥላቻ ፖለቲካ ማብቃት አለበት፡፡ ኢሕአዴግ ተቃዋሚዎችን የሚያያቸው እንደ ጠላት ከዚያም አልፎ እንደ ሽብርተኛ ነው፡፡ ይኼንን ነገር ለሚያስብ ሰው እኮ በጣም ነው የሚያስደነግጠው፡፡ በእኛም በኩል ኢሕአዴግን የምናየው እንደ አውሬ ነው፡፡ ምናልባት የሠራውን ሥራ ሁሉ ዋጋ (Credit) ያለመስጠት አለ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ፖለቲካችን ኢሕአዴግን መቃወም ብቻ ሆኖአል፡፡ ያ መቆም አለበት፡፡ ትልቁ ኳስ ያለው ኢሕአዴግ ዘንድ ነው፡፡ እኔ በበኩሌ ወደፊት በማደርገው እንቅስቃሴ ገንቢ ግንኙነት አድርገን ያለውን የፖለቲካ ምኅዳር ለሁላችንም እኩል ማድረግ አለበት፡፡ ኢቴቪ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቴሌቪዥን ጣቢያ ነው፡፡ ለምንድነው የኢሕአዴግ ብቻ የሚሆነው? መብት እኮ አለን፡፡ ለኢቴቪ ደብዳቤ ጽፈናል፡፡ የጻፍነው ምንድነው የኢሕአዴግን ኮንፈረንስ ከባህር ዳርና የኢሕአዴግን ብሔራዊ ምክር ቤት በቀጥታ ስታስተላለፉ ነበር፡፡ የእኛን ግን አልዘገቡም፡፡ ለኢሕአዴግ 99 በመቶ ሰጥተው ለእኛ ግን አንድ በመቶ እንኳን አይሰጡንም፡፡ ይኼ ሁሉ ቁልጭ አድርጐ የሚያሳየው የኢሕአዴግን ድክመትና ስህተት ነው፡፡


ሪፖርተር፡- ለብዙ ፓርቲዎች የእንዋሀድ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ነገር ግን ከዚህ ቀደም እንደታየው ብዙ ውህደቶች ምርጫ ሲደርስ ከመሰባሰብ በዘለለ ብዙም ሲገፉበት አይስተዋልም፡፡ የ97ቱን ቅንጅት ማስታወስ ይቻላል፡፡ ከዚህ አንፃር አሁን እርስዎ የሚያቀርቡት ሐሳብ በምን ይለያል? ከዚህ ቀደም ተሞክረው እንደከሰሙት እንደማይሆንስ ማረጋገጫው ምንድነው? 


ኢንጂነር ግዛቸው፡- የቅንጅት ራሱን የቻለ ጉዳይ አለው፡፡ ቅንጅት አልተዋሀደም ነበር፡፡ ለዚህም ነው ቅንጅት ግንባር ደረጃ አልደረሰም የሚባለው፡፡ ለቅንጅት ከፍተኛውን ድቀት ያስከተሉት የኢሕአዴግና የቅንጅት መሪዎች ናቸው፡፡ በወቅቱ ኢሕአዴግ ያልጠበቀው የፖለቲካ አድማስ ነው የመጣበት፤ በ97 ምርጫ አልጠበቀውም ነበር፡፡ አራቱ ፓርቲዎች ማለትም መኢአድ፣ ኢዴፓ፣ ቀስተ ደመናና ኢዴሊ ሆነው ቅንጅት የተመሠረተው ኅዳር ላይ ነበር፡፡ ኅዳር ላይ ተመሥርተን ግንቦት ላይ ነው ከፍተኛ ዕርምጃ ያሳየነው፡፡ ያ ሁኔታ ኢሕአዴግ ያለውን ግምት በጣም ነው ያዛባው፡፡ ኢሕአዴግ አቅም አይፈጥሩም የሚል ግምት ነበረው፡፡ ገና ስንፈጠር በምርጫው አካባቢ አዲስ አበባን ሙሉ ለሙሉ ተቆጣጠርን፡፡ የምርጫው ዕለት ምሽት በአጠቃላይ የምርጫው ሒደት ተናጋ፡፡ በዚያ ምክንያት ቅንጅት ከፍተኛ ውድቀት ውስጥ ገባ፡፡ ኢሕአዴግ ትኩረት አደረገብን፡፡
በዚያ ምክንያት እኛም ወደ እስር ቤት ገብተን ከዚያ ደግሞ ወጣን፡፡ ያው ነገሩ ትክክል ስላልነበር መውጣት እንደነበረብን እኔ አምናለሁ፡፡ ከወጣን በኋላ ደግሞ እኛ አንድ መሆን አልቻልንም፡፡ በእስር ቤት ውስጥ ብሶት ተፈጠረ፡፡ እንደገና ቅንጅትን ለአቶ አየለ ጫሚሶ ሰጡት፡፡ በዚያ በዚያ በመካከላችን ችግሩን በሰከነ ሁኔታ ለማራመድ አልቻልንም፡፡ በዚህ በኩል የራሱ የኢሕአዴግም የእኛም ድክመት ነበር፡፡ ከዚያ በፊትም በተፈጠሩት ስብስቦች እንደዚሁ የመሪዎች ብዛት ነው ችግሩ፡፡ አሁን እኔ የምለው ውህደት ከሆነ አንድ መሪ ሊኖር ይችላል፡፡ ውህደቱም መፈጸም ያለበት በዲሞክራሲያዊ መርሆዎች መሆን አለበት፡፡ ውህደት ላይ ዲሞክራሲያዊ ባህል መፍጠር አለብን፡፡ አመራር አንድ መሆን አለበት፡፡ ሕግ፣ ሥነ ሥርዓትና ደንቡ መታየት አለበት፡፡ እናም ዲሲፕሊን ሊኖረን ይገባል፡፡ የባህሪ ለውጥም ያስፈልገናል፡፡ ከዚህ አንፃር አንደኛ እኛ አመራሮች የባህሪ ለውጥ ያስፈልገናል፡፡ ያ እስከሆነ ድረስ እኔ ውህደት ይወድቃል ብዬ አላስብም፡፡ አልተሞከረም፡፡ በተጨባጭ ብሔራዊ ዕይታ ያለው ውህደት እኮ እስካሁን አልተካሄደም፡፡


ሪፖርተር፡- ከዚህ ከውህደቱ ጋር በተያያዘ የርዕዮተ ዓለም ጉዳይስ እንዴት ነው የሚታየው? ብሔራዊ የሆነ ፓርቲ ይኖራል፤ ኅብረ ብሔራዊ የሆኑ ፓርቲዎችም ይኖራሉ፡፡ ይህስ ለውህደቱ እንቅፋት አይሆንም? 


ኢንጂነር ግዛቸው፡- እኔ ሁላችንም ወደ ብሔራዊ ምክክር መምጣት አለብን የሚል እምነት አለኝ፡፡ ለምሳሌ ብሔር ተኮር የሆነ ፓርቲ ከእኛ ጋር ሲዋሀድ ብሔራዊ ቅርፅ መያዝ አለበት፡፡ አለበለዚያ ብሔር ተኮርና ኅብረ ብሔር ሊዋሀዱ አይችሉም፡፡ ምንድነው ጠቃሚው ነገር? ዲሞክራሲ እስከሆነ ድረስ ለምሳሌ የእኛ ፕሮግራም የግለሰብንም የቡድንንም መብት ያከብራል፡፡ የብሔረሰብ ጉዳይ ከሆነ የቡድን ጉዳይ ነው፡፡ ያ እስከተጠበቀ ድረስ ማንኛውም የብሔር ፓርቲ እኛን ይቀላቀላል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ያ ነው ጠቃሚው ነገር፡፡ የፕሮግራሙ ዕይታ ብሔር ተኮር የሆኑትን ፓርቲዎች ፍላጐት ማሟላት አለበት፡፡ የብሔረሰቡ ቋንቋ፣ የብሔረሰቡ የመወሰን መብትና ባህል ማሟላት አለብን፡፡ ይኼ የኢትዮጵያ ነፀብራቅ ነው፡፡ አንዴ ወደ ላይ አንዴ ወደ ታች የምንልበት ጉዳይ አይደለም፡፡ እኩልነት እስካለ ድረስ የብሔረሰብ ጉዳይ አይነሳም ባይ ነኝ፡፡ ፍትሕ፣ እኩልነት፣ ነፃነትና ዲሞክራሲ እስካሉ ድረስ ችግር ያለ አይመስለኝም፡፡


ሪፖርተር፡- አንድነት አሳካዋለሁ ወይም በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ አመጣዋለሁ የሚለው የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ምንድነው? ኢንጂነር ግዛቸው፡- የእኛ ሊበራል ዲሞክራሲ ነው፡፡ ሊበራል ዲሞክራሲ ሆኖ የቡድንና የግለሰብ መብትን አንድ ላይ እናከብራለን፡፡
ሪፖርተር፡- በሊበራል ዲሞክራሲ የቡድንም የግልም መብት ይከበራል ብለዋል፡፡ ነገር ግን የፍላጐት መጋጨት አይኖርም? በቡድን መብትና በግለሰቦች መብት መካከል ማለት ነው? 


ኢንጂነር ግዛቸው፡- ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ነው የሚወሰነው፡፡ በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ስንት ሰዎች ናቸው እንደዚህ የሚሉት? ሊኖርም ይችላል፡፡ ይህ ተፈጥሮአዊ ነው፡፡ አሥር ሰዎች ሁለቱን አባረው ማካሄድ አይችሉም የሚል ይኖራል፡፡ 90 በመቶ ከደገፈው የ90 በመቶ ይሆናል ለሚለው የዲሞክራሲ ውሳኔ ነው የሚጠይቀው፡፡ እኛም ተወያይተንበታልና የሚወሰነው በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መሠረት ነው፡፡


ሪፖርተር፡- በሚቀጥለው ዓመት የሚካሄድ አገር አቀፍ ምርጫ አለ፡፡ አንድነት እንደ አንድ ተቃዋሚ ፓርቲ በምርጫው ለመሳተፍና ተጨባጭ ውጤት ለማስመዝገብ ምን ምን ሥራዎችን እየሠራ ነው?


ኢንጂነር ግዛቸው፡- አንደኛ የራሳችንን አቅም እየገነባን ነው፡፡ ከጠቅላላ ጉባዔያችን ዕይታ አግኝተናል፡፡ በዚያ ዕይታ ለምሳሌ የውህደቱ አንዱ ዓላማ በምርጫ የማሸነፍ ጉዳይ ነው፡፡ ምክንያቱም አንድነት ብቻውን ከሚሮጥ ሦስትና አራት ፓርቲ ሆነን ልክ እንደ ቅንጅት ብንሮጥ የተሻለ ውጤት እናገኛለን በማለት፣ በውህደቱ ለምርጫው አንድ የጐለበተ አቅም ለመፍጠር የምናደርገው ስትራቴጂ ነው፡፡ ሁለተኛው ፕሮግራማችንንና ርዕዮተ ዓለማችንን ልክ እንደ ሚሊዮኖች ንቅናቄ ወደታች እናወርደዋለን፡፡ አንድ የሕዝብን ዕይታ የሚስብ ከምርጫ 2007 ጋር የሚገናኝ ፕሮግራም እናወጣለን፡፡ ሕዝብን ለማንቀሳቀስ ከዚህ በተጨማሪ አንድነት የዲሞክራሲ ምርጫ ፓርቲ ነው፡፡ ለማንኛውም ሁልጊዜ ለምርጫ ይዘጋጃል፡፡ አሁን ስትራቴጂያችንን ከልሰን ከወቅታዊ ሁኔታ ጋር አማራጭ ፖሊሲዎችን እንቀርፃለን፡፡ ከአማራጭ ፖሊሲዎች በመነሳት የምርጫ ማኒፌስቶ እናዘጋጃለን፡፡ በእኔ ዕይታ እስከ ሰኔ ድረስ ካለፈም እስከ ነሐሴ ድረስ አንዱና ትልቁ ሥራችን ይህንን የምርጫ ፖሊሲና ማኒፌስቶ ማዘጋጀት ነው፡፡ ከዚያ ብቁ የሆኑ ዕጩዎችን ከካቢኔያችን ውስጥ እንመለምላለን፡፡ ከየቦታው ብቁ የሆኑ ታዛቢዎችንም እንመርጣለን፡፡ ይህ ሒደት ነው፡፡ ሕዝባዊ ስብሰባ እናካሂዳለን፡፡ እንደዚሁም ሕዝባዊ ንቅናቄ ይኖረናል፡፡ እየሄድን ራሳችንን ወደ ሕዝብ የምናወርድበት፡፡ ይህን ሁሉ ለማድረግ ግን የምርጫ ፓርቲ ብንሆንም ምርጫ ውስጥ ጥልቅ ብለን አንገባም፡፡ ሜዳው ለሁላችን እኩል መሆኑን እናረጋግጣለን፡፡ ስለዚህ ከላይ እንዳልኩት ለዚህ ነው ገንቢ ግንኙነት (Constructive Engagement) ከገዥው ፓርቲ ጋር የምናደርገው፡፡ ይኼ ሜዳ ለሁላችንም እኩል እንዲሆን ነው የምንፈልገው፡፡ ኢትዮጵያ የጋራችን ነች፡፡ ኢሕአዴግ አንድ ፓርቲ ነው፡፡ እኛም አንድ ፓርቲ ነን፡፡
የምርጫው ሕግ በሕገ መንግሥቱና በምርጫ ቦርድ ሕግ መሠረት መካሄድ ስላለበት ያንን እንጠይቃለን፡፡ ምርጫ ቦርድ የኢሕአዴግ ከሆነ፣ ሚዲያው የኢሕአዴግ ከሆነ፣ የፍትሕ አካላቱ የኢሕአዴግ ከሆኑ እኛ ያን ጊዜ የምንወስነው ውሳኔ ይኖራል፡፡ ነገር ግን ከትዝብትም ጭምር እስካሁን ያሉት ተቋማት ለእኔ ዲሞክራሲያዊ አልነበሩም፡፡ የ2002 ምርጫ በጣም ያዘንኩበት ምርጫ ነበር፡፡ በ21ኛው ክፍለ ዘመን 99.6 በመቶ የሚያገኝ ፓርቲ የለም፡፡ በዓለም ላይ ዲሞክራሲያዊ በሆነና ውድድሩ በእኩል ሜዳ ላይ ተካሂዶ በእዚህ ውጤት ማሸነፍ አይቻልም፡፡ በዓለም ዙሪያ በአብዛኛው መንግሥት በቅንጅት እየተፈጠረ ነው፡፡ እንግሊዝን ውሰድ የኮንሰርቫቲቭና የሌበር ፓርቲ ቅንጅት ነው፡፡ ጀርመን፣ ጣሊያንና ኖርዌይም እንዲሁ ቅንጅት ነው፡፡ ምክንያቱ በዲሞክራሲያዊ ሥርዓቱ ውድድሩ ነፃ ነው፡፡ እናም ስለዚህ 99.6 በመቶ በጭራሽ ሊሆን አይችልም፡፡ እንኳን እንደ ኢትዮጵያ ያለ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችና የኅብረተሰብ ክፍል ባህሪ ባለበት አገር ይኼ አይቻልም፡፡ ይኼ ነገር መለወጥ አለበት፡፡ እናም ለምርጫ እንዘጋጃለን፡፡ ነገር ግን ሜዳው ሁላችንንም እኩል ማስተናገድ አለበት፡፡


ሪፖርተር፡- የመጫወቻ ሜዳው ለሁላችሁም እኩል መሆኑን እንዴት ማረጋገጥ ትችላላችሁ?


ኢንጂነር ግዛቸው፡- ለምሳሌ በምርጫ 97 ሚዲያው ትንሽ ወደ ኢሕአዴግም ቢያደላ ተከፍቶ ነበር፡፡ እንዲያውም የእነሱ ሜዳ ከፍ የእኛ ሜዳ ዝቅ ቢልም፣ ነገር ግን የመወዳደርያ ቦታ ነበረው፡፡ የቴሌቪዥንና የሬዲዮ ክርክሮች ለሕዝብ የወጡት በ97 ምርጫ ነበር፡፡ በ2002 ምርጫ ሚዲያው ታፍኖ ነበር፡፡ ሚዲያው የሕዝብ ጥያቄ አላስተናገደም፡፡ ዝም ብሎ ለይስሙላ ቴሌቪዥን ጣቢያ ተሂዶ አንዳንድ ነገሮች መነጋገራችንን ሕዝብ ሊሰማው ይችላል፡፡ ነገር ግን በሆነ እጅ ቁጥጥር ሥር የወደቀ ነበር፡፡ ያ መሆን የለበትም፡፡ እናም ትልቁ ምሳሌ የ97 ምርጫ የሚዲያ ጉዳይ ነበር፡፡ ሚዲያው ያን ጊዜ ተከፍቶ ነበር፡፡ በእኩልነትም ባይካሄድም ያን ጊዜ እንደ እኩል ነው የወሰድነው፡፡ እንደዚያ መሆን አለበት፡፡


ሪፖርተር፡- ከሽብርተኝነት ጋር በተያያዘ አንድነት የፀረ ሽብር ሕጉ ይሰረዝ የሚል አቋም ይዞ እየተከራከረ ነው፡፡ አሁን ደግሞ በመላው ዓለም ሽብርተኝነት ትልቅ ሥጋት ሆኗል፡፡ በእኛ አገር የፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ አጠቃቀም ተቃዋሚዎችን ፀጥ ለማሰኘት ነው የሚለው እንዳለ ሆኖ፣ አንድነት እንደ ፓርቲ አማራጭ የፀረ ሽብር ሕግ አለው ወይ ይሰረዝ ሲል ምን ማለት ነው?


ኢንጂነር ግዛቸው፡- መጀመርያ ሽብርተኝነትን መዋጋት የኢሕአዴግ ብቻ አይደለም፡፡ የማንኛውም ዜጋ ነው መሆን ያለበት፡፡ ይኼ ሽብርተኝነት ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴው አስከፊ፣ ከሰው ልጅ ባህሪ በተለየ የሰው ልጅን መንፈስ የሚሰብር፣ የሰው ልጅነትን የሚቀንስ ነው፡፡ አንድነትም ሆነ እኔ እንደ አንድነት አመራር እንደዚሁም እንደ ዜጋም እንዋጋለን፡፡ የእኛ ችግር የፖለቲካ መሣሪያ አይሁን ነው፡፡ የአንድነት አባላትና እኔ ከኢሕአዴግና ከገዥው ፓርቲ በምንም መልኩ አናንስም፡፡ ይህን ችግር ለመዋጋት፡፡ ይኼ የዜግነት ግዴታዬ ነው፡፡ ማንም ቢሆን ወገኑ እንደዚያ ሲጠፋበት ካልተዋጋ ከሰውነትም ከሰብዕናም መውጣት አለበት፡፡ ነገር ግን የእኛ አጽንኦት የፀረ ሽብር፣ የፕሬስና የመያዶች ሕግ የፖለቲካ መሣሪያ መሆን የለባቸውም ነው፡፡ የፖለቲካ መሣርያ ከሆኑ መሰረዝ አለባቸው ነው፡፡ የሕዝብ ተሳትፎ ያለበት ይሁን ነው፡፡ የሁላችንም የጋራ ሥጋት ነው፡፡ ሁላችንም መሳተፍ አለብን፡፡ የፀረ ሽብር አዋጅ ሲወጣ እኛ አልተሳተፍንበትም፡፡ ፓርላማውም እንደሰማሁት በጥልቀት አልተሳተፈበትም፡፡ ይህ አዋጅ የሕዝቡ አዋጅ መሆን አለበት፡፡ በኢትዮጵያ ማንም ከማንም ያነሰ የለም፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ በሽብርተኝነት ስትጠቃ እኔ የመጀመርያው ተዋጊ ነኝ፡፡


ሪፖርተር፡- የፓርቲያችሁ ድረ ገጽ አብዛኛውን ጊዜ ቶሎ ቶሎ መረጃዎች ሲጫኑበት አይታዩም፡፡ በአብዛኛው የቆዩ መረጃዎች ናቸው ያሉበት፡፡ የእርስዎን ሊቀመንበር ሆኖ መመረጥ እንኳን በትኩሱ ይፋ አላደረገም፡፡ አሁን ደግሞ እንደዚህ ዓይነት የመረጃ ዘዴዎችን መጠቀም ወደ ሕዝብ ዘንድ ለመድረስ ዓይነተኛ ሚና ስለሚኖረው ድረ ገጻችሁ ለምንድነው መረጃዎችን ቶሎ ቶሎ ለሕዝብ የማያደርሰው?


ኢንጂነር ግዛቸው፡- ያለፉትን መውቀስ አይሁንብኝና ድክመታችን ነው፡፡ እኔም አይቼዋለሁ፡፡ ዘገምተኛ ነው፡፡ አሁን ‹‹አክቲቭ›› እናደርገዋለን፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ተነጋግረንበታል፡፡ ጠንካራ የሆነ የሚዲያ ግሩፕ አለን፡፡ ነገር ግን እነርሱ ያንን ረስተው በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ነው ያሉት፡፡ ስለዚህ ጉዳይ አንስቼ ተነጋግረናል፡፡ የተነጋገርነውም አንደኛ ድረ ገጾችን ዘገምተኛና የነቃ አይደለም፡፡ ሰዎችን የሚስብ ባለመሆኑ ይህ ድረ ገጽ በሥነ ሥርዓት አሁን ለኢትዮጵያውያንም፣ ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡም አንድነት የሚሠራውን በየቀኑ ማንፀባረቅ አለበት፡፡ ድረ ገጹ ወቅታዊነት ይጐድለዋል፡፡ ሁኔታዎችን ብልጭ የሚያደርገው ጊዜው ካለፈ በኋላ ነው፡፡ በሚቀጥሉት ሦስት ወራት እንዲስተካከል የሕዝብ ግንኙነት ይሠራዋል፡፡


ሪፖርተር፡- ላለፉት ዓመታት ፖለቲካው ላይ ብዙም አይታዩም ነበር፡፡ አሁን ደግሞ እንደገና ተመረጡ ሲባል እሳቸው ፖለቲካ አልተውም እንዴ የሚል ጥያቄ ተነስቷል፡፡ እርስዎ ከፖለቲካ ወጥተው ነበር? 


ኢንጂነር ግዛቸው፡- አይደለም፡፡ አንደኛ ለአንድ ዓመት ያህል ተራ አባል ነበርኩ፡፡ ተራ አባል መሆንም አንዳንድ ጊዜ ወደ ላይም ወደታችም ያሳይሃል፡፡ ከዚያ ወደ ምክር ቤት አስገቡኝ፡፡ ብሔራዊ ምክር ቤት ከገባሁ አንድ ዓመቴ ነው፡፡ እዚያ በንቃት እሳተፍ ነበር፡፡ ነገር ግን ራሴን ከሚዲያ አግልዬ ነበር፡፡ እንዲሁ ዝም ብዬ የምናገረው ነገር የለኝም ብዬ ራሴን ከሚዲያው አውጥቼ ነበር፡፡ በመሠረቱ ወደዚህ መምጣትም መቶ በመቶ የእኔ ፍላጐት አልነበረም፡፡ የፓርቲ አባላት ፍላጐት ነው፡፡ የፓርቲ አባላት ፍላጐት በመሆኑ ምክር ቤትም እንደነበርኩ ይኼ ሐሳብ ተንሸራሽሮአል፡፡ ከዚያ በኋላ ያልጨረስከው ነገር ስላለ ግባና እስቲ ጨርሰው የሚል ነው፡፡ እኔ እንግዲህ ያመጣኝ ምርጫው ነው፡፡


ሪፖርተር፡- ፖለቲካ በቃኝ ብለው ነበር? 


ኢንጂነር ግዛቸው፡- ፖለቲካ በቃኝ አላልኩም፡፡ የፖለቲካ አመራርነት ግን ይበቃኛል ብዬ ነበር፡፡ ከፖለቲካ አልወጣሁም ነገር ግን ከፖለቲካ አመራርነት ወጥቼ ነበር፡፡ ይህንን እኔ የማምንበት ነው፡፡ ሌላ ለምን አናይም? አንዳንድ ጊዜ ጥላ አጥልተን መኖሩንም እኔ አልፈልገውም፡፡ አንዳንድ የፖለቲካ መሪዎች ጥላ ሁነው እነርሱ ብቻ ተሰይመው ታች ያለውን አጥልተውበት፣ ታች ያለው ዝም ብሏል፡፡ እንደዚያ መሆንም አልፈልግም፡፡ ያንን ጥላዬን ከአመራርነት አውጥቼ ልጆቹ ወደ ፀሐይ ወጣ ይበሉ ብዬ ነበር፡፡

                                                                                                                                                     posterd by A.G

Saturday 11 January 2014

የፓርቲያችንን ህጋዊ እንቅስቃሴ ለፖለቲካ ፍጆታ ማዋል የገዥውን ፓርቲ የፕሮፓጋንዳ ውድቀት እና ኢ-ህገመንግሥታዊነት የሚያሳይ ነው!!! Source UDJ

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)             
UNITY FOR DEMOCRACY AND JUSTICE PARTY              
(UDJ)

 የፓርቲያችንን ህጋዊ እንቅስቃሴ ለፖለቲካ ፍጆታ ማዋል የገዥውን ፓርቲ የፕሮፓጋንዳ ውድቀት እና ኢ-ህገመንግሥታዊነት የሚያሳይ ነው!!!


                 ከአንድነት ለዴሞክራሲ እና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) የተሰጠ መግለጫ!!!ፓርቲያችን አንድነት የተቋቋመለትን ሕዝባዊ ዓላማ መሰረት በማድረግ በኢትዮጵያ ውስጥ ከ50 ዓመት በላይ ትግል ተደርጎበት እውን መሆን ያልቻለውን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሳይሸራረፍ ለማስፈን፤ አምባገነኑን ስርዓት በሰላማዊ ትግል ለመለወጥ እንዲሁም የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ለማድረግ ህግን መሰረት አድርጎ እየሰራ ይገኛል፡፡ በዚህ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የማስፈን ትግልም ፓርቲያችን፣ አመራሩና ቁርጠኛ አባላቱ ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍለዋል፤ እየከፈሉም ይገኛሉ፡፡ ዋጋ በከፈሉና ዋጋ እየከፈሉ ባሉ አመራሮቻችንና አባሎቻችን መራራ ትግል ምስጋና ይሁንና በመላ ኢትዮጵያ ሕዝባዊ መሰረት በመጣል ከኢትዮጵያ ህዝብ ጎን መሆናችንንም አረጋግጠናል፡፡ ይህ የፓርቲያችን ጥንካሬ የራስ ምታት የሆነበት ገዥው ፓርቲ ግን ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ህዝባዊ መሰረታችንን ለመናድ በስም ማጥፋት፣ በፍረጃና ባልዋልንበት እንደዋልን የማስመሰል ስራውን አጠናክሮ በመቀጠል በህዝቡ ዘንድ ያለንን መልካም ስማችንን ለማጉደፍ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ እየሰራ ይገኛል፡፡


አንድነትም የገዥውን ፓርቲ ኢ-ህገ መንግስታዊ የሆነ እኩይ ተግባር ተገቢ እንዳልሆነ፣ ለሀገርና ለህዝብ እንደማይጠቅም፣ የህዝብን ጥያቄ በዶክመንተሪ ጋጋታ መመለስ እንደማይቻል፣ ከፍረጃና ከሴራ ተላቅቆ በሰከነ መንገድ ወደ ውይይት እንዲመጣ በተደጋጋሚ መክረናል፤ ሀገራዊ ጥሪም አቅርበናል፡፡ ነገር ግን አምባገነኑ ስርዓት የሚቆጣጠራቸውን የመንግስት ተቋማት በመጠቀም አሁንም በዶክመንተሪ ስም ከማጥፋት፣ ከመፈረጅና ከማስፈራራት መላቀቅ አልቻለም፡፡


ሰሞኑን በተከታታይ 3 ክፍል ተላልፎ ይቀጥላል በተባለውና የፀረ-ሽብር ግብረ ሃይል ከኢቲቪ ጋር በመሆን አዘጋጅቶታል በተባለው ተከታታይ የዶክመንተሪ ፕሮግራም ላይ መሰረት የተደረገው ፓርቲያችን በመላ ኢትዮጵያ ህዝባዊ ንቅናቄ በመፍጠር እንዲሰረዝ እንቅስቃሴ ያደረገበት የፀረ ሽብር ህጉ ላይ ነው፡፡ አንድነት የፀረ-ሽብር ህጉ ይሰረዝ ሲል አሳማኝ መከራከሪያዎችን በማንሳትና በሰላማዊ መንገድ ቢሆንም ገዥው አካል ግን እንደተለመደው ማስተላለፍ ከፈለጉት አላማ ጋር የፓርቲያችንን ስም በማይገባ ቦታ በማንሳትና ለሚመለከተው አካል በህጉ መሰረት አሳውቀን ባካሄድናቸው ሰላማዊ ሰልፎች እና ህዝባዊ ስብሰባዎች ላይ ያስተላለፍናቸውን  አቋሞች  የሃሰት ትርጉም እየሰጠ የተለመደ የዶክመንተሪ ድራማው ማድመቂያ ሲያደርገን ተስተውሏል፡፡  የፓርቲ አመራሮች በህጋዊ ሰላማዊ ሰልፎች ላይ ያደረጉትን ንግግር ቆርጦ በመጠቀም በህዝብ ዘንድ ያለን ተቀባይነት ላይ ተፅዕኖ ለማሳረፍ የታቀደ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሁሌም ምርጫ ሲቃረብ እንደሚያደርጉት ሁሉ በ2007 ዓ.ም ለሚካሄደው ሀገራቀፍ ምርጫ የተቃውሞ ጎራውን በፀረ-ሰላምነት ለመፈረጅ እየተደረገ ያለ የኢህአዴግ የምርጫ እንቅስቃሴ ክፍልም ነው፡፡


በዚሁ ዶክመንተሪ ላይ መቀመጫውን በውጭ በማድረግ የተለያዩ ዜናዎችንና ፕሮግራሞችን በማሰራጨት የሚታወቀውን ኢሳት (ESAT) ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ ፓርቲያችን ለአባላቱ እና ለደጋፊዎቹ መልዕክት ማስተላለፉን እንዲሁም እንደፓርቲ ለማንኛውም ሚዲያ የፓርቲያችንን ሰላማዊ እንቅስቃሴ በተመለከተ ስንጠየቅ የመመለስ መብታችንን በሚጋፋ መልኩ የፓርቲያችንን አቋም አዛብቶ ለማቅረብ ሞክሯል፡፡


ይህም የኢህአዴግን  የፖለቲካ ባህሪ እና አቋም በግልፅ ያሳየ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በፓርቲያችን ዕምነት ኢህአዴግ በሚጠላቸው እና በሚያጥላላቸው ሚዲያዎች ሃሳብን መግለፅ በየትኛውም መመዘኛ አሸባሪነት ሊሆን አይችልም፡፡ የኢህአዴግ መንግስት ሲያስነጥሰው ከሚያለቅሱለት የፕሮፓጋንዳው ፍጆታዎች ከሆኑት ሚዲያዎች ውጪ የኔ ያልሆኑ የሌላ ናቸው ብሎ የሚያምን በመሆኑም ፍረጃው ህጋዊ አግባብነትም ሆነ መረጃ የሌለው ባዶ ፍረጃ መሆኑ ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡


ከሁሉም በላይ ህገ መንግስታዊ መሰረት የሌለው ቢሆንም እንኳ ቢያንስ ራሳቸው ላወጡት ህግ  ታምነው ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በማቅረብ ሳያስወስኑ አንድን የሚዲያ ተቋም ያውም ለአንድ አላማ የተቋቋመ የፀረ-ሽብር ግብረሃይል ‹‹የአሸባሪ ድርጅት ልሳን ነው›› ወይም ‹‹አሸባሪ ነው›› በማለት ሲፈርጅ ስናይ አሁንም የሀገራችን ፖለቲካ ፓርቲና መንግስት የተደበላለቁበት፣ አንድ ድርጅት እንደፈለገው የሚፈርጅበት ስርዓት እንዳለ የሚጠቁም ነው፡፡


ፓርቲያችንም ይህንን ህገ ወጥ ፍረጃ በቀላሉ የማይመለከተው መሆኑን እየገለፅን ገዥው ፓርቲ ከድርጊቱ እንዲቆጠብ፤ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንም ለተፈፀመብን የስም ማጥፋት ከተጠያቂነት የማያመልጥ መሆኑን እያሳወቅን አሁንም ህገ-መንግስት የሚጥሰውንና ተቀናቃኝ ሃይሎችን ለማሸማቀቅ እያገለገለ ያለው የፀረ-ሽብር አዋጅ እንዲሰረዝ ሰላማዊ ህዝባዊ ትግላችንን በማጠናከር እንደምንቀጥል እንገልፃለን፡፡ የህዝብ ልዕልና እና የህግ የበላይነት እንዲከበር ትግሉ የሚጠይቀንን መስዋዕትነት እንደምንከፍል ለመላው የኢትዮጵየ ህዝብ በድጋሚ እናረጋግጣለን፡፡                         
 አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ

                                ታህሳስ 29 ቀን 2006 .

                                       አዲስ አባባ                                                  posted  by A.G

UDJ SEAL