Tuesday 23 June 2015

አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ በወያኔ የታፈኑበትን አንደኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ በኖርዌይ፣ ኦስሎ ተካሄደ

June 23, 2015

የግንቦት 7 ዋና ፀሀፊ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ በየመን የፀጥታ ሃይሎች ታግተው ለዘረኛውና አፋኙ የወያኔ ቡድን ተላልፈው የተሰጡበትን አንደኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ በኖርዌይ ደረጃ የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ የድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ በወጣቶች ክፍል አስተባባሪነት በጁን 23/ 2015 በእንግሊዝ ኢምባሲ ፊት ለፊት እልህና ቁጭት የተሞላበት ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ ተካሂዷል።

በሰልፉ ላይ ከተለያዩ የኖርዌይ ከተሞች የተገኙ በርካታ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በኖርዌጅያን የሰአት አቆጣጠር ከ13፡30 ስዓት ጀምሮ ታላቋ ብርታኒያ ለዜጋዋ አቶ አንዳርጋቸው ልዩ ትኩረት አድርጋ ከዘረኛው ወያኔ ነጻ በማውጣት ወደ ቤተሰቡ እንዲመለስ ለማሳሰብ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው የነጻነት ታጋዩን አንዳርጋቸውን በተመለከተ የተለያዩ መፎክሮችን አሰምተዋል።
በዝግጅቱ ወቅት ከተሰሙት መፎክሮች መካከል “አንዳርጋቸው የነጻነት ታጋይ እንጂ አሸባሪ አይደለም” አንዳርጋቸው ነጻ ይወጣ ዘንድ እንግሊዝ ግፊት ታድርግ”፣ “በአንዳርጋቸው ላይ ለአንድ ዓመት ሙሉ እየደረሰበት ያለው የስቃይና የመከራ ዘመን ይብቃ”፣ እንግሊዝ ዜጋሽ የት ነው?”፣ “እንግሊዝ! ዜጋሽ አደጋ ውስጥ ነውና ደህንነትና ጥበቃ ያዝፈልገዋል፣ የህግ ከለላም እንዲሁ” “አዎ! እኛ ሁላችን አንዳርጋቸው ነን!” ነጻነት፣ ፍትህና ዲሞክራሲ ያስፈልገናል” በማለት ከፍተኛ ሀገራዊ ስሜት በተንጸባረቀበት መልኩ ጩኸታቸውን አሰምተዋል።

በመቀጠልም አርበኞች ግንቦት ሰባት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የታፈኑበትን አንደኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የተሰጠውን መግለጫ ለተሳታፊዎች በድምጽ ተነቧል። መግለጫውም የአቶ አንዳርጋቸው በወያኔ መታገት ንቅናቄው የበለጠ እንዲጠነክርና ከሌሎች ድርጅቶች ጋር ውህደት በመፍጠር ትግሉን ወደፊት እንዲሄድ አድርጎታል እንጂ ወያኔ እንዳሰበው ትግሉ ወደ ኋላ እንዳልቀረ ይጠቅሳል።
በመግለጫው ማጠቃለያም በአቶ አንዳርጋቸው ላይ በአፈናው የተነሳ የደረሰው መከራ ስቃይ ብቻ ሳይሆን በአሁኑ ጊዜ ለፍትህ ፣ ለእኩልነትና ለነፃነት በመቆማቸው በወያኔ አረመኔዎች ቁም ስቅላቸውን የሚያዩ በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎች ሰቆቃ የሚያበቃው የኢትዮጵያ ህዝብ ተባብሮ በሚያደርገው ሁለ ገብ ትግል በመሆኑ ማንኛችንም በአቶ አንዳርጋቸውም ሆነ በሌሎች ወገኖቻችን ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት እንደራሳችን አድርገን የሚሰማን ወገኖች በሙሉ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ከታፈኑበት አንድ አመት ወዲህ የተጀመረውን ተስፋ የሚሰጥ እንቅስቃሴ አጠናክረን ወደ ውጤት በማድረስ የመጪው ዘመን የህዝብ የፍትህ የእኩልነትና የነፃነት ተስፋ የሚለመልምበት የወያኔ አምባገነን ስርአት እድሜ የሚያጥርበት ዘመን እንዲሆን ሁላችንም የምንችለውን ሁሉ እንድናደርግ ወገናዊ ጥሪ አስተላልፈዋል።
በመጨረሻም በዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ የተዘጋጀውን ደብዳቤ በተወካዮች አማካኝነት ለኢምባሲው ከተሰጠ በኋላ የተለያዩ መፈክሮችን በማሰማት ዝግጅቱ በታቀደለት ስዓት በተሳካ ሁኔታ ተጠናቋል።

የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ የድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ

Thursday 18 June 2015

የሰማዕታት ደም ይጮሃል፤ ይጣራል !!!


ከሰማያዊ ፓርቲ የተሰጠ ጥልቅ የሐዘን መግለጫ!

አንድ በስልጣን ላይ የተቀመጠ አካል ተቀዳሚ ተግባር የዜጎችን ደህንነት መጠበቅ መሆኑን ጤነኛ አዕምሮ ያለው የሰው ልጅ የሚገነዘበው ጥሬ ሃቅ ነው፡፡ እንደ እርግማን ዛሬ በኢትዮጵያ የስልጣን እርካቡን የተቆጣጠረው ቡድን የሚገዛቸውን ዜጎች የሚያያቸው እንደጠላት እንጅ የመንግስትን ጥበቃ እንደሚፈልጉ፤ በጠላትነት የፈረጃቸው ዜጎች በከፈሉት ግብር ስልጣን ላይ መቆየት መቻሉን እንኳን ባለስልጣናቱ መረዳት ተስኗቸዋል፡፡

ሰኔ 8 ቀን 2007 ዓ.ም በደብረ ማርቆስ ከተማ እጅግ በሚሰቀጥጥ ጭካኔ እንደ እባብ ተቀጥቅጦ የተገደላው የሰማያዊ ፓርቲ ቆራጥ ታጋይ ሳሙኤል አወቀ የስርዓቱ አገልጋዩች ለዓመታት ሲያስፈራሩት፣ ሲደበድቡት፣ ሰርቶ የመኖር መብቱን ሲጋፉት፣ ያልተሳከ የመግደል ሙከራ በተደጋጋሚ ጊዜ ሲፈፅሙበት መቆየታቸውን የሚያረጋግጡ በርካታ ማስረጃዎች ተይዘዋል፡፡ ሳሙኤል ሕይወቱ አደጋ ላይ እንደሆነችና ጥበቃ እንዲያደርጉለት የጠየቃቸው የፀጥታና የፍትህ አካላት በተገላቢጦሽ ተጨማሪ ዛቻና ማስፈራሪያ ያደርሱበት እንደነበር አይዘነጋም፡፡ አንድ ወጣት በተወለደበት ምድር በሕይወት የቆየባቸውን ጊዚያት በስጋት እንዲኖር ከተፈፀመበት ግፍ በተጨማሪ በሕይወት የመኖር መብቱ በአረመኔዎች እጅ ስትነጠቅ የህዝብን ፀጥታና ደሕንነት እናስከብራለን የሚሉ አካላት በመሃል ከተማ እንኳን ደርሰው ለመታደግ አቅሙም ሆነ ፍላጎቱ አልነበራቸውም፡፡

ሳሙኤል በአሰቃቂ ሁኔታ ከመገደሉ በፊት በተለያዩ ጊዚያት ለሚመለካታቸው አካላትና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያስተላልፋቸው የነበሩ መልዕክቶች እንደተጠበቁ ሆነው በተለይ ግንቦት 25 2007 ዓ.ም በራሱ ገፅ በሆነው “የፌስ ቡክ” ማህበራዊ ሚዲያ ካስተላለፈው መልዕክት መረዳት እንደሚቻለው በተደራጀ ሁኔታ ሕይወቱ አደጋ ላይ እንደሆነች አስረግጦ ተናግሯል፡፡ ሆኖም የሚሰማውና የሚጠብቀው ምንም አካል እንዳልነበረ ይልቁንም ለመገደሉ ተባባሪ የሆኑ የመንግስት አካላት እንደነበሩ ስጋቱን በገለፀ በቀናት ውስጥ ሕይወቱ በአሰቃቂ ሁኔታ መቀጠፏ ጉልሕ ማስረጃ ነው፡፡

በሰላማዊ ትግል ፅኑዕ እምነት የነበረው ሳሙኤል አወቀ ይደርስበት የነበረውን ለቁጥርና ለዓይነት አታካች የሆነ በደል ተቋቁሞ፣ ትግሉን እንዲያቆም ወይም የሚወዳትን ሕይወቱን አሳልፎ የሰጠላትን ሐገሩን ለቆ እንዲሰደድ ይህ ካልሆነ ግን የእሱን ሕይወት ለማጥፋት እጅግ ቀላል መሆኑን የስርዓቱ ባለስልጣናት እና ካድሬዎች ደጋግመው ቢነግሩትም በጭቆና ስር ለሚማቅቀው የኢትዮጵያ ሕዝብ የገባውን ቃል ከማጠፍ ይልቅ ሕይወቱን ለመሰዋት እንደሚቀለው የገባውን ቃል በተግባር አስመስክሮ አልፏል፡፡ በማሰርና በመደብደብ አላማውን እንደማያስቀይሩት፤ ከገደሉት ግን ቀሪ ታጋዮች በተለይም የእድሜ አቻዎቹ የሆኑ የእርሱ ትውልድ የሚሰዋለትን ዓላማ ከግብ እንዲያደርሱ “ትግሌን አደራ!! አደራ!!” በማለት ተማፅኖ አስቀምጧል፡፡

እኛም እንላለን፡፡ አደራህ ከባድ ነው፡፡ ቃልህን እናከብራለን፡፡ አላማህንም እናሳካለን!!!!

ይህ ስርዓት በህግም በሞራልም ኢትዮጵያን የማስተዳደር ብቃት የለውም፡፡ ወንጀለኞች ለፍርድ ይቅረቡ እያልንም አናላዝንም፤ ወንጀለኞቹ የመንግስት አካላት ናቸውና፡፡ በወንድማችንና ገና በለጋ እድሜው በተቀጨው የትግል አጋራችን ላይ የተፈፀመውን ግፍ አይቶ እንዳላዬ ዝም ያለ መንግስት ከዚህ የተሻለ መልካም ነገር ያመጣል ብለን አንጠብቅም፡፡ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ግን መልዕክት አለን፡፡ እስከ መቼ በግፍ እንገደላለን?!! ሸፍጠኞችስ እስከ መቼ ይዘባበቱብናል?!! ትግል ለውጤት የሚበቃው በተወሰኑ ቡድኖች ወይም ግለሰቦች መፍጨርጨር ብቻ ባለመሆኑ የግፍ ስርዓት እንዲያበቃ ሁላችንም የሚገባንን የዜግነት ድርሻ እንድንወጣ ጥሪ እናቀርባለን፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ በአባላቱና በደጋፊዎቹ በአጠቃላይም የተለየ አስተሳሰብ ስላላቸው ብቻ በካድሬዎች የሚታሰሩ፣ የሚገረፉ፣ የሚሳደዱ፣ የሚዋረዱና የሚገደሉ ዜጎች ለከፈሉት መራራ ፅዋ ክብር ይሰጣል፡፡ መስዋዕትነታቸውም በከንቱ እንዳይሆን እሰከመጨረሻው ይታገላል፡፡

ሳሙኤል “ብታሰርም፣ ብገደልም ይህን ሁሉ የማደርገው ለሐገሬና ለነፃነቴ ነው” ያልከው ቃልህ ከመቃብር በላይ ነው!!!! ቃልህን እናከብራለን፡፡ አላማህንም እናሳካለን!!! ትግል ይቀጥላል . . .

ሰኔ 10 ቀን 2007 ዓ.ም
አዲስ አበባ

"""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""
"""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""

በተያያዥ ዜና አንድ የአረና አባል በሶስት ሰዎች ታንቀው በምሽት ተገደሉ

ኣቶ ታደሰ ኣብርሃ የተባሉ የዓረና-መድረክ ኣባልና የምዕራባዊ ዞን የዓረና ኣመራር ኣባል ትናንት ማታ 09 / 10 / 2007 ዓ/ም በሶስት ሰወች ታንቀው ተገደሉ።


ኣቶ ታደሰ ኣብራሃ  በቓፍታ ሑመራ ወረዳ ማይካድራ ቀበሌ ኑዋሪ ሲሆኑ በዘንድሮው ምርጫ ወቅት በቀበሌው ኣስተዳዳሪዎች፣ካድሬዎች፣ የሚቀርቧቸው ሰዎች ከዓረና-መድረክ ኣባልነታቸው እንዲለቁ የተሸመገሉ፣ የተለመኑና በመጨረሻም ዛቻዎች ሲደርስባቸው እንደነበረ ይታወቃል።

ኣቶ ታደሰ ማታ 03:00 በ 3 ሰዎች ኣንገታቸው የታነቁ ሲሆን ሶስቱ ሰዎች ሙቷል ብለው የተዋቸው ቢሆኑም ሂወታቸው እስከ 09:15 ኣላለፈችም ነበር። 



ኣቶ ታደሰ ኣብራሃ የ48 ዕድሜ ጎልማሳ ነበሩ። ኣደጋው 3 ሰዎች እንደፈፀሙባቸው፣ በኪሳቸውም 300 ብር የነበረ ቢሆንም ሰዎቹ ሊወስዱት እንዳልቻሉ ተናገረው ነበር። የኣቶ ታደሰ ሬሳ በሑመራ ሆስፒታል ላለማስመርመር የማይካድራ ፖሊስ ትራፊክ በዓረና ኣባላት ላይ ከፍተኛ ጫና የፈጠሩ ሲሆን የተለያዩ የመንግስት ኣካላትም ምርመራው እንዳይካሄድ የተለያዩ ጫናዎች እንደፈጠሩ ኣባሎቻችን ከስፍራው ገልፀውልናል።



ሬሳው ወደ ሑመራ ወስዶ ለማስመርመር የሚጠቅም መኪና ለመከራይ ሲባል ኣባሎቻችን የተካራት ሞተር ሳይክ በፖሊስት ትራፊክ ተከልክላለች።


የኣቶ ታደሰ ኣብራሃ ቤት ኣካራይና ሌሎች ሰዎች ከኣደጋው በተያያዘ ጫና እየተፈጠረባቸው እንደሆነ ለማወቅ ተችለዋል።



የኣቶ ታደሰ ኣብራሃ ግድያ በሳምንት ውስጥ የወጣት ሳሙኤል ኣወቀንጨምሮ ለሁለተኛ ግዜ በፖለቲከኞች ላይ የተፈፀመ ግድያ ሲሆን ከ2007 ዓ/ም በዓረና- መድረክ ኣባላት ለሁለተኛ ግዜ የተፈፀመ ግድያ ያደርገዋል።

Sunday 14 June 2015

ከቴፒ ወጣቶች የምንማራቸው ቁም ነገሮች

June 10, 2015
def-thumb
በደቡብ ኢትዮጵያ ሸካ ዞን የሚገኙ የቴፒ ወጣቶች በህወሓት አገዛዝ የሚደርስባቸው በደል አንገሽግሿቸው ራሳቸውን አደራጅተው በአገዛዙ ላይ እርምጃ መውሰድ ከጀመሩ በርካታ ወራት ተቆጥረዋል። እነዚህ ወጣቶች ግንቦት 27 ቀን 2007 ዓ.ም. በአካባቢያቸው የሚገኝን አንድ የፓሊስ ጣቢያ ወረው እስረኞችን ማስፈታታቸው በመላው ኢትዮጵያ እንዲታወቁ ምክንያት ሆኗል፤ የአገዛዙ ሚዲያም ድርጊቱ መፈፀሙ በተዘዋዋሪም ቢሆን አምኗል።

ለፍትህ፣ ለነፃነት፣ ለዲሞክራሲ፣ ለእኩልነት እና ለአገር አንድነት ግድ ያለን ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ከቴፒ ወጣቶች የምንማራቸው በርካታ ቁም ነገሮች ያሉ ቢሆንም የሚከተሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው ብለን እናምናለን።
1. “ጥቂቶች ነን፤ ምንም ማድረግ አንችልም” ብለው ተስፋ ቆርጠው በደልን ለመቀበል አልመረጡም፤
2. ዓላማቸው ትልቅና ሀገራዊ ቢሆንም እርምጃዎቻቸው አካባቢ ተኮር አድርገዋል፤

3. የሚወስዷቸው እርምጃዎች በአቅማቸው መጠን እንዲሆኑ በማድረግ በራሳቸው ላይ ያለው መተማመን እንዲጎለብት ማድረግ ችለዋል፤
4. እንደሁኔታው በፍጥነት መሰባሰብና መበታተን የሚችል ቀልጣፋ ስብስብ ማደራት ችለዋል፤ እና
5. በከፍተኛ ሥነሥርዓት በመታነጽ ከቴፒ ሕዝብ ጋር ያላቸውን ትስስር አጠናክረዋል።

ሁላችንም ከእነዚህ ወጣቶች ልንማር ይገባል። በአምባገነን አገዛዝ ጉያ ውስጥ የሚደራጅ የአመጽ ኃይል የተለያዩ አደረጃጀቶች ሊኖሩት ይችላል። አንዱ አደረጃጀት የቴፒ ወጣቶች በተግባር ያሳዩን ነው – ተንቀሳቃሽ፣ ለግዳጅ ተሰባስቦ በፍጥነት የሚበተን፤ መልሶ ደግሞ የሚሰባሰብ ቀልጣፋ ድርጅት።
በምርጫ 97 በሰላማዊ መንገድ የሰጡትን ድምጽ ይከበርን ያሉ ወገኖታችን በአዲስ አበባ ከተማ በግፍ የተጨፈጨፉበት ሰኔ 1 ቀን 1997 ዓም 10ኛ ዓመት በሀዘን አስታውሰናል። ከዚያ ወዲህ በርካታ ወገኖቻችንን በሰላማዊና ህጋዊ ትግል አጥተናል፤ ብዙዎች ቆስለዋል፤ በሺዎች የሚገመቱ በእስር እየማቀቁ ነው። ሆኖም ግን ያ የትግል መስመር የትም አላደረሰንም። የህወሓት አገዛዝ እንዲያበቃ እና በምትኩም ሕዝብ በነፃነት የመረጠው አስተዳደር እንዲኖር የምንፈልግ ወገኖች ሁሉ ወደግባች የሚያደርሱንን አማራጮችን መፈለግ ግዴታችን ሆኗል።
አርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ “ሁለገብ ትግልን” እንደ ትግል ስትራቴጂ ሲመርጥ በውስጡ ብዙ አማራጭ ስልቶች መኖራቸውን እግንዛቤ በማስገባት ነው። የቴፒ ወጣቶች በተግባር ያሳዩን የተለያዩ የሁለገብ ትግል ስትራቴጂ አካል የሆኑ በርካታ የትግል ስልቶች መኖራቸውን ነው። ቴፔ የተደረገው እንዳለ ሌላ ቦታ ይደረጋል ማለት አይደለም። ከቴፒ የምንማረው ዋናው ቁምነገር በፈጠራ እና በአካባቢ እውቀት በታገዘ ስልት ወያኔ መፋለም ያለብን መሆኑ ነው።
አርበኞች ግንቦት 7 የቴፒ ወጣቶች ላሳዩት ተግባራዊ መነሳሳት አድናቆት እና ለከፈሉት መስዋዕትነት ያለውን ክብር እየገለፀ በሌላው የአገራችን ክፍሎች ያሉ ወጣቶችም ከቴፒ ወንድሞቻቸው ትምህርት እንዲቀስሙ ያበረታታል።
በዚህ አጋጣሚም በየቦታው በራስ አነሳሽነት የሚጀመሩ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች አካባቢ ተኮር ቢሆኑም እንኳን አገራዊ እይታ እንዲኖራቸው፤ ከሌሎች መሰል እንቅስቃሴዎች ጋር እንዲቀናጁና እንዲደጋገፉ ብሎም የሀገራዊ ትግሉ አካል እንዲሆኑ ማድረግ የሚያስፈልግ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ያስገነዝባል፤ ይህ ተግባራዊ እንዲሆንም ይሠራል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

Friday 5 June 2015

በቴፒ አቅራቢያ ከፍተኛ ውጊያ ተካሄደ

በቴፒ አቅራቢያ ከፍተኛ ውጊያ ተካሄደ- ታጣቂዎች ፖሊስ ጣቢያ ሰብረው በመግባት ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል

ግንቦት ፳፰ (ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በጋምቤላና ደቡብ ክልል አዋሳኝ ከተማ በሆነቸው ቴፔ ትናንት ሌሊት 11 ሰአት ላይ ለተሻለ ፍትህና ነጻናት እንታገላለን የሚሉ ታጣቂዎች በአንድ የፖሊስ ጣቢያ ላይ በወሰዱት እርምጃ 3 የሌሊት ተረኛ ፖሊሶች ሲገደሉ በርካታ እስረኞችንም አስፈትተዋል።
ቁጥራቸው ከ100 እስከ 150 የሚሆኑ በቴፒና አካባቢው የሚታየውን ዘረኝነትና የአስተዳደር በደል እንዋጋለን በማለት ራሳቸውን አደራጅተው ጫካ የገቡ ወጣቶች ባለፉት 9 ወራት ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ሲፈጽሙ ቢቆዩም ትናንት ሌሊት የፈጸሙት ጥቃት ከእስካሁኑ የተለየ ነው ተብሎአል።

የፖሊስ ጣቢያው በተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች አቅራቢያ የሚገኝ ሲሆን በአካባቢውም የመከላከያ ሰራዊት እና የፌደራል ፖሊስ አባላት ሰፍረው በአካባቢው ተደጋጋሚ ቅኝት ያደርጋሉ። ታጣቂዎቹ ከአንድ ቀን በፊት ለፖሊስ አባላት ጥቃት እንደሚፈጽሙ ማስጠንቀቂያ የላኩ ሲሆን፣ በቃላቸው መሰረት ሌሊት ላይ ፖሊስ ጣቢያውን ሰብረው በመግባት በጣቢያው ውስጥ ተከማችተው የሚገኙትን የጦር መሳሪያዎች እስከ እነ ጥይቶቻቸው እንዲሁም የተለያዩ ሰነዶችን ሰብስበው ወስደዋል። በሶስት ክፍል ታስረው የነበሩ እስረኞችን ሲለቁ፣ የራሳቸውን አባላት ይዘው ጠፍተዋል።
ተረኛ ፖሊሶች ተኩስ የከፈቱ ቢሆንም ታጣዊዎች በወሰዱት እርምጃ አንድ መቶ አለቃ ማእረግ ያለው ፖሊስና ሁለት ተራ ፖሊሶች ተገድለዋል። አንድ የባጃጅ ሹፌር የሆነ እስረኛም በተኩሱ ማሃል ህይወቱ አልፎአል። የመንግስት ወታደሮች ተከታትለው ጥቃት ለመፈጸም ባደረጉት ሙከራ ለታጣቂዎቹ መረጃ በማቀበል ሲተባበር የነበረን አንድ ሰው ገድለዋል። ሟቹ የሚቀብረው አጥቶ ጫካ ላይ ተጥሎ እስከ እኩለቀን መታየቱን የአይን ምስክሮች ተናግረዋል።
ታጣቂዎች የአካባቢው ህዝብ ድጋፍ እንዳላቸውም ነዋሪዎች ይናገራሉ። አንዳንድ ያነጋገርናቸው የከተማዋ ነዋሪዎች፣ ታጣቀዊዎች በወሰዱት እርምጃ የከተማው ህዝብ ደስታውን ሲገልጽ ታይቷል ብለዋል።
ከሁለት ሳምንት በፊት በቴፒ ከተማ እንድሪስ ቀበሌ ውስጥ 5 ሰዎች ከሌሊቱ 8 ሰአት ላይ በጥይት ተደብድበው ተገድለዋል። በወቅቱ ከተገደሉት መካከል አባትና ልጅ ይገኙበታል። ግድያውን የፈጸሙት ፖሊሶች ሲሆኑ፣ ማቾቹ በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎችን ይደግፋሉ በሚል ምክንያት መገደላቸውን ኢሳት በወቅቱ ዘግቦ ነበር።
ካለፈው ከመስከረም ወር ጀምሮ በቴፒና አካባቢዋ ያለው ግጭት ተባብሶ በመቀጠሉ ነዋሪዎች ከፍተኛ ስጋት ላይ መውደቃቸውንም፣ በእየለቱ በከተማዋ ውስጥ የጥይት ድምጽ እንደሚሰማና በርካታ ቁጥር ያላቸው የሸኮ መዠንገር ነዋሪዎች እየፈለሱ ወደ ቴፒ ከተማ በመግባት ላይ መሆናቸውን መዘገቡ ይታወሳል። የዞኑን ባለስልጣናት ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
ዘግይቶ በደረሰን ዜና ደግሞ ከሰአት በሁዋላ ቴፒ ከተማ አቅራቢያ በምትገኝ ፃኑ በተባለች ቀበሌ የመንግስት ሀይሎችና ታጣቂ ቡድኑ ባደረጉት ዉጊያ በርካታ የልዩ ሀይል ፖሊሶች ሲገደሉ በርካቶች ቆስለዉ አማን ሆስፒታል ገብተዋል ።

እስካሁን በደረሰን መረጃ 3 የአማፂያኑ አባላት ተገድለዋል::