Friday, 25 July 2014

ለብሔራዊ አንድነትና ነፃነት – ህወሓትን ከትግራይ ሕዝብ መነጠል!!!

በአለፉት ጥቂት ሣምንታት በወያኔ የተፈፀሙ የእብደት ተግባራትን ስናጤን ከፊት ለፊት ኢትዮጵያችንን እየጠበቀ ያለው መንታ መንገድ አመላካች ነው። ይህ ከፊት ለፊት የሚጠብቀን መንታ መንገድ አንዱ ወደ ብሔራዊ አንድነት፣ ነፃነትና ብልጽግና ሌላው ወደ እርስ በርስ ትርምስና ውድቀት የሚያመሩ ናቸው። የአንድነት፣ የነፃነትና የብልጽግና መንገድ ለመያዝ መስመራችንን ማስተካከል ያለብን ከአሁኑ ነው።
ለመሆኑ ከላይ ያልነውን ለማለት ያስቻሉን በአለፉት ጥቂት ሣምንታት በወያኔ የተፈፀሙት ተግባራት ምንድናቸው?

አንደኛ፤ ወያኔ፣ ዓለም ዓቀፍ ህግንና ሥርዓትን በጣሰ መንገድ ከየመን ባለሥልጣናት ጋር በማበር የንቅናቄዓችንን ዋና ፀሐፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ማፈኑ በአለፉት ጥቂት ሣምንታት ውስጥ ውስጥ የተደረገ አብይ ክስተት ነው። ይህ የወያኔ የውንብድና ተግባር ኢትዮጵያዊያንን በእጅጉ አስቆጥቷል። ወያኔ፣ ለሀገር ነፃነትና ለእኩልነት የሚታገልን አንድ ታላቅ ሰውን ማፈንኑና ከእይታ ከልሎ እያሰቃየው መሆኑ በሕዝቡ ውስጥ ያለው ቁጣ ወደ መገንፈል አስጠግቶታል። አቶ አንዳርጋቸው በጠላት እጅ ከወደቀም በኋላ ኢትዮጵያዊያንን አሰባሳቢ ኃይል ሆኗል።
ሁለተኛ፤ ሰላምተኞቹን ብሎገሮችንና ጋዜጠኞችን በሽብርተኝነት በመክሰስ በቋፍ ላይ የነበረውን የወጣቶች ትዕግሥት እንዲሟጠጥ አድርጓል። ስለኢንተርኔት አጠቃቀምና ጥንቃቄ ሥልጠና መውሰድ በክስ ቻርጁ ውስጥ መካከቱ ሥርዓቱ ከእውቀት ጋር የተጣላ መሆኑ በግልጽ አሳይቷል። ከዚህም በተጨማሪ በህጋዊ ፓርቲዎች ውስጥ በንቃት የሚሳተፉ ወጣት መሪዎችን መርጦ በማሠርና በሽብርተኝነት በመወንጀል የወያኔ የአፈና መዋቅር ወጣቱ ላይ ማነጣጠሩ ግልጽ ሆኗል።
ሦስተኛ፤ እጅግ ሰላማዊና ጨዋነት በተሞላበት መንገድ አቤቱታቸውን በማቅረብ ላይ የነበሩትን ሙስሊም ወገኖቻችንን ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ በመደብደብ እና በጅምላ በማሠር በወያኔ መድብለ ቃላት ውስጥ “ሰላማዊ ትግል” የሚባል ነገር አለመኖሩ፤ ተቃውሞ ሁሉ “ሽብር” እንደሚባልና በሽብርተኝነት እንደሚያስከስስ በማያሻማ ሁኔታ አረጋግጧል። ይህም የሥርዓቱ አውሬዓዊ ባህሪ መገለጫ ሆኗል።
አራተኛ፤ አፈናውና እስሩ ወደ ትግራይም በመዛመቱ ወያኔ የቆመበት ምድር እየራደ መሆኑ አመላካች ሆኗል። ትግራይ ውስጥ የነበረው አፈና ድብቅ የነበረ ከመሆኑም በላይ ከወያኔ የውስጥ ሽኩቻ ጋር ሲያያዝ ቆይቷል። አሁን ግን ሁኔታዎች እየተቀየሩ ነው። አገራዊ ርዕይ ያነገቡ፤ ወያኔን በጽናት ለመታገል የቆረጡ የትግራይ ወጣቶች ወደፊት እየመጡ ነው። እነዚህ ወጣቶች የተጫነባቸውን ድርብርብ ጫና በመበጣጠስ ከተቀረው ኢትዮጵያዊ ወገናቸው ጎን መቆማቸውን በተግባር እያረጋገጡ፤ ለዚህም መስዋዕትነት እየከፈሉ ናቸው።
ከላይ የተዘረዘሩት አራት ጉዳዮች በጋራ ሲታዩ የተበታተነ የሚመስለው እና በተለያዩ ስልቶች የሚደረገው ትግል የሚሰባሰብበትና የሚቀናጅበት ወቅት ላይ መደረሱ አመላካቾች ናቸው። ዛሬ የምንገኘው የተለያዩ የትግል ስልቶች እንዲናበቡና እንዲደጋገፉ ማድረግ እጅግ አስፈላጊ የሆነበት ወቅት ላይ ነው።
በተለይም ወያኔ፣ መሸሸጊያ ምሽጉ አድርጎ በሚቆጥረው ትግራይ ውስጥ እየዳበሩ የመጡት የአመጽም አመጽ-የለሽ ትግሎችም አስተዋጽኦ ከፍተኛነት ሌላው ኢትዮጵያዊ እንዲረዳ ማድረግ ጊዜ የማይሰጠው ተግባር ነው። የወያኔ የአፈናና የመጨቆኛ መዋቅሮች የህወሓት አባላት በሆኑ የትግራይ ዘውጌ ማኅበረሰብ አባላት የሚዘወሩ መሆኑ እውነት ነው። ይህ ማለት ግን ህወሓት የትግራይ ሕዝብ ወኪል ወይም ጠበቃ ነው ማለት አይደለም። ትግላችን ከወያኔ ፋሽስታዊ አገዛዝ ጋር መሆኑ እና የትግራይ ሕዝብ የዚህ ትግል አጋር፣ የውጤቱም ተጠቃሚ መሆኑ ማስረገጥ ተገቢ ነው።
ከፊት ለፊታችን ካሉት መንታ መንገዶች መካከል የአንድነትን፣ የነፃነትና የብልጽግናን መንገድ ለመምረጥ የትግራይ ሕዝብ በስፋት ትግሉን እንዲቀላቀል ማድረግ ተገቢ ነው። ትግራይ የህወሓት የግል ጓዳ መሆኗ የማብቂያ ጊዜ ማፋጠን ይቻላል። በዲሞክራሲያዊ ትግል ውስጥ ያሉ ሁሉ በዚህ ጉዳይ ላይ የጋራ ግንዛቤ ከያዙ ወያኔን ማንሳፈፍ የሚቻልበት እድል በስፋት ተከፍቷል።
ስለሆነም፣ ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ዘረኛውና ፋሽስታዊው ህወሓትን ከትግራይ ሕዝብ መነጠል አንዱ የትግላችን ስትራቴጂ ሊሆን ይገባል ይላል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!
                                                                                                                             Posted By A.G

Sunday, 6 July 2014

ከግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ የተሰጠ ልዩ መግለጫና ተግባሪዊ የመጀመሪያ እርከን የትግል ጥሪ

July 6, 2014

ከግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ የተሰጠ ልዩ መግለጫና ተግባሪዊ የመጀመሪያ እርከን የትግል ጥሪ
ሁላችንም አንዳርጋቸው ጽጌዎች ነን!!!

ሰኔ 29 ቀን 2006 ዓ.ም
በየጊዜው እየከረረና እየገረረ የመጣው ትግላችን “ሁላችን አንዳርጋቸው ጽጌዎች ነን” ወደ ተባለ አዲስ ምዕራፍ ተሸጋግሯል። ይህ ጽሁፍ የዚህን የትግል ምዕራፍ ምንነትና ይዘት በአጭሩ ያብራራል። በዚህ ጽሁፍ ላይ የሰፈሩት ዓረፍተ ነገሮች ተነበው የሚታለፉ ሳይሆን በተግባር የሚተረጎሙ ሥራዎች ናቸው።
አንዳርጋቸው ጽጌን መሆን ምን ማለት ነው? አንዳርጋቸው ጽጌ ለፍትህ፣ ለነፃነት፣ ለዲሞክራሲና ለእኩልነት በጀግንነት የቆመ፤ ትግሉ የሚጠይቀውን መስዋዕትነት ሁሉ ሲከፍል የነበረና አሁንም እየከፈለ ያለ መሪያችን ነው። አንዳርጋቸው ጽጌን መሆን ማለት ልክ እንደሱ ትሁት ሆኖም ግን ቆራጥ፤ ሆደ ሰፊ በዚያው ልክ ደግሞ መራር፤ አስተዋይና ብልህ ሆኖም ተግባር ተኮር መሆን ማለት ነው። አንዳርጋቸው ጽጌን መሆን ማለት ወያኔን ለማስወገድ መደረግ የሚገባውን እርምጃ ለመውሰድ የተዘጋጀ ሰው መሆን ማለት ነው። አንዳርጋቸው ጽጌን መሆን ማለት ለአገርና ለትውልድ ቤዛ መሆን ማለት ነው።
ወያኔ፣ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ላይ ካተኮረባቸው ምክንያቶች አንዱ የወያኔን የዘር ፓለቲካና ፕሮፖጋንዳ በሚያመክን መልኩ በተግባር ትግል ውስጥ ካሉ የኦሮሞ፣ የአፋር፣ የኦጋዴን፣ የጋምቤላ እና ሌሎች ዘውግ ተኮር ድርጅቶች ጋር ንቅናቄዓችን ተግባራዊ ትብብር ማድረግ የሚችሉበት ደረጃ ድረስ ማቀራረብ የቻለ መሪ መሆኑ ነው። ከሁሉም በላይ ለወያኔ የጉሮሮ ቁስል የሆነበት ደግሞ ከትግራይ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ትህዴን) ጋር ግንቦት 7 የፈጠረው ጠንካራ ትብብር ነው። ከትህዴን ጋር በመሆን አቶ አንዳርጋቸው ወያኔ በትግራይ ሕዝብ ጀርባ መንጠልጠል እንዳይችል አድርጎታል። እናም አንዳርጋቸው ጽጌን መሆን ማለት ከዘረኝነት ፀድቶ መገኘት ማለትም ጭምር ነው። አንዳርጋቸው ጽጌን መሆን ማለት በኢትዮጵያዊያን እኩልነት እና እኩል ባለመብትነት ከልብ ማመን እና ለእኩልነት በጽናት መታገል ማለት ነው።
አንዳርጋቸው ጽጌን ለመሆን የግድ የግንቦት 7 አባል መሆንን አይጠየቅም። አንዳርጋቸው ጽጌን ለመሆን ለመልካም ዓላማዎች መሳካት ዋጋ ለመክፈል መዘጋጀትን እንጂ የግድ ከአንድ ወይም ከሌላ ድርጅት ጋር መወገንን አያሻም። ያም ሆኖ ግን አንዳርጋቸው ጽጌን የሆነ ሰው በጠንካራ ድርጅት የታገዘ ትግል አስፈላጊነት ይረዳል።
በመጨረሻም አንዳርጋቸው ጽጌን መሆን ኦኪሎ ኦኴኝ፣ አንዱዓለም አራጌ፣ ርዕዮት ዓለሙ፣ እስክንድር ነጋ፣ በቀለ ገርባ፣ ኦልባና ሌሊሳ እና እዚህ ዘርዝረን ልንጨርሳቸው የማንችላቸው ጀግኖቻችንን ሁሉ መሆን ማለት ነው።
“የሁላችንም አንዳርጋቸው ጽጌዎች ነን” ዘመቻ ትኩረቶችን በየጊዜው የምንገልጽ ሲሆን ከዛሬ ጀምሮ በሥራ ላይ መዋል ያለበት የዓለም ዓቀፍ ዘመቻው የመጀመሪያ እርከን ትኩረቶች ከዚህ በታች ቀርበዋል
የዘመቻው የመጀመሪያው እርከን ትኩረቶች
ይህ የመጀመሪያ እርከን ሶስት ቦታዎች ላይ ያተኩራል፡- የመን፣ ብርታኒያ እና ወያኔ
 የመንን በተመለከተ
የየመን መንግሥት የዓለም ዓቀፍ ህግም ሆነ የየመን የራሷን ህግ በመተላለፍ መሪያችንን ለእርድ አሳልፎ ሰጥቶብናል። ከመጀመሪያው ጀምሮ ለየመን መንግሥት የተደረገው ተማጽኖ ሰሚ ጆሮ አላገኘም። እስካሁንም ድረስ የየመን መንግሥት አቶ አንዳርጋቸውን ማሠሩና ለወያኔ አሳልፎ መስጠቱ በይፋ አላመነም። እኛ ባለን መረጃ መሠረት በአይሮፕላን ማረፊያው ከማገት ጀምሮ በልዩ በረራ ወደ ኢትዮጵያ እስከ መላክ ድረስ ያለውን የውንብድና ሥራ በየመን በኩል ሆኖ የሠራው ቀጥታ ተጠሪነቱ ለየመን ፕሬዚዳንት የሆነው የስለላ ድርጅት ነው። በዚህም ሳቢያ የየመን መንግሥት ሊቀለበስ የማይችል እና በቀላሉ የማይፋቅ ታሪካዊ ስህተት ፈጽሟል። የየመን መንግሥትና ሕዝብ ይህን እንዲያውቁት ማድረግ ወቅቱ የሚጠይቀው የተግባር እንቅስቃሴ አካል ነው።
የመንን በተመለከተ የሚቀጥለው ሳምንት ዘመቻችን ግብ ቁጣችንን የየመን ፕሬዚዳንት እና የየመን መንግሥት ብቻ ሳይሆን የየመን ሕዝብም እንዲያውቅ ማድረግ ነው። የሚከተሉት ተግባራት ለአብነት ያህል ተጠቅሰዋል።
  1.  ለየመን ፕሬዚዳንት አዲስ መረር ያለ ደብዳቤ ተጽፎ በፋክስና በኢሜል በየመን መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶችና ኤምባሲዎች አድራሻዎች መላክ። በመልዕክት መጨናነቅ ከሚገባቸው የየመን ተቋማት አንዱ አዲስ አበባ የሚገኘው የየመን ኤምባሲ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ሆናችሁ በዘመቻው የምትሳተፉ የሕዝብ ስልኮችን እንድትጠቀሙ፤ የኢንተርኔትና የፋክስ መልክቶችን ስትልኩ ራስን ለጉዳት በማያጋልጥ መንገድ መደረግ ይኖርበታል።
  2. የየመን ኤምባሲዎችን ሥራ ማወክ በሚችሉ ሰልፎችና ተቃውሞዎች ማጨናነቅ። የፕሬዚዳንቱን ፎቶና የአገሪቱን ባንዲራ ማቃጠል። ይህ በውጭ አገራት ብቻ መደረግ ያለበት ነው።
  3. በውጭ አገራት በየከተሞች ለሚገኙ የየመን ኮሚኒቲዎች ደብዳቤ መፃፍና መንግሥታቸውን እንዲቃወሙ መገፋፋት፤ ይህንን ካላደረጉ ግን የመናዊያን ከመንግሥታቸው ጎን ተሰልፈው በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት እንዳወጁ የምንቆጥረው መሆኑን በማያሻማ መንገድ መንገር፤
  4. በየመን አየር መንገድና በማናቸው የየመን ቢዝነስ ላይ እቀባ ማድረግ፤ በቢዚነሶቻቸው ላይ አሉታዊ ቅስቀሳ ማድረግ። ይህ ተግባር በኢትዮጵያም ከኢትዮጵያ ውጭም በሚገኙ ኢትዮጵያዊያን መተግበር የሚኖርበት አቢይ ተግባር ነው።
  5. በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የየመን ቢዝነስን መርጦ ምርቶቶቻቸው እና አገልግሎቶቻቸው እንዲጠሉ ማድረግ። ከእንግዲህ በየመን ገንዘብ የተሠራ ወይም ከየመን የመጣ ብስኩትም ይሁን ሲጃራ የወገናች ደም የነካው እቃ ነው።
 ብርታኒያን በተመለከተ
የእንግሊዝ መንግሥት ማድረግ የነበረበትን እና ማድረግ ይችል የነበረውን ሁሉ አድርጓል ብለን አናምንም። እርምጃው ፈጣን አልነበረም፤ አሁንም አይደለም።
ስለሆነም እንግሊዝን በተመለከተ የዘመቻችን ግብ የእንግሊዝ መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት በመንፈጉ መክሰስ እና ከአሁን በኋላም ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ እንዲከታተለውና መሪያችንን እንዲያስፈታ መወትወት ነው። የሚከተሉት ተግባራት ለአብነት ተዘርዝረዋል።
  1. የእንግሊዝ መንግሥትን በህግ መክሰስ (ይህ በንቅናቄው ጽ/ቤት የሚሠራ ነው)፤
  2. ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አዲስ ደብዳቤ ጽፎ በፋክስና በኢሜል ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና ለኤምባሲዎች በብዛት መላክ። አንዱ ትኩረት የሚደረግበት ኤምባሲ አዲስ አበባ የሚገኘው የእንግሊዝ ኤምባሲ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ በዘመቻው የሚሳተፉ ወገኖች አስፈላጊው ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል።
  3. በለንደን በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደጃፍ፤ በሌሎች አገሮች ደግሞ በእንግሊዝ ኤምባሲዎች ቁጣ የተቀላቀለበት የተቃውሞ ሰልፎችን ማካሄድ።
 ወያኔን በተመለከተ
ወያኔን በተመለከተ የሚደረጉ ትግሎች በሙሉ ወያኔን ከስልጣን ማስወገድን ያለሙ መሆን ይኖርባቸዋል። ወያኔም ለመጣል ትልቁን ድርሻ የሚያበረክተው ሕይወታቸውን ለመስጠት የቆረጡ ወገኖቻችን የሚያደርጉት ተግባር ነው፤ እንቀላቀላቸው።
በተለያዩ ምክንያቶች ወሳኙን ትግል መቀላቀል የማይችሉ ወገኖቻችን በያሉበት ሆነው ይህንኑ የሚያግዙ ተግባራት መፈጸም ይኖርባቸዋል። እነዚህ ተግባራት፣ የወያኔ ባለሟሎች በገቡበት እየገቡ በማሳፈር እረፍት በመንሳት፤ የፈፀሟቸውን ወንጀሎች በአደባባይ በመናገር እንዲሸማቀቁ በማድረግ፤ ማንነታቸው ለሸሪኮቻቸው ወይም ለሥራ ባልደረቦቻቸው በመንገር ወዳጅ በማሳጣት፣ ቢዚነሶቻቸው እንዲከስሩ በማድረግ የፋይናንስ አቅማቸውን በማዳከም ረገድ የሚኖራቸው አስተዋጽኦ ቀላል እንዳልሆነ ሊጤን ይገባል። ከዚህ አኳያ ሊደረጉ ከሚገቡ ተግባራት የሚከተሉት በምሳሌነት ተዘርዝረዋል።
  1. በየአገሩ በተለያዩ ሽፋኖች ተሰግስገው ያለት ወንጀለኞች የወያኔ ሹማምንትና ደጋፊዎችን ለፍርድ ማቅረብ፤
  2. የወያኔ ኤምባሲዎች ሥራ መሥራት የማይችሉበት ሁኔታ መፍጠር፤
  3. የወያኔ አባላትና ደጋፊዎችን ከያሉበት (በሰፈር፣ በዩኒቨርስቲዎች፣ በንግድ የተሰማሩ ..) በማደን ማስነወር፣ ማግለል፣ ማዋረድ፤ ከእነሱ ጋር አንዳችም የንግድም ሆነ የሥራ ትብብር አለማድረግ፤ በሥራዎቻቸው ላይ አሉታዊ ቅስቀሳዎችን ማካሄድ። ይህ ኢትዮጵያም ውስጥ በስፋት በሥራ ላይ መዋል ይኖርበታል።
  4. ለሥራ ወይም ለሽርሽር የሚዘዋወሩ ከፍተኛ የወያኔ ባለሥልጣኖችና የጦር መኮንኖችን እየተከታተሉ ማሸማቀቅ፣ ማስነወር፣ መገታተር፤
  5. የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ በወያኔ መንግሥት የሚመሩ ቢዝነስች ላይ እቀባ ማድረግ፤ በእነሱ ላይ አሉታዊ ቅስቀሳ ማድረግ። ይህ በኢትዮጵያም በውጭ አገራትም መደረግ ይኖርበታል።
  6. በዌስተር ዩኒየን እና በወያኔ ደጋፊዎች በኩል ገንዘብ ወደ ኢትዮጵያ አለመላክ፤ በየአካባቢው አማራጭ መላኪያ መንገዶችን መፈለግ።
  7. ከወያኔ ጋር የሚሠሩ የውጭ አገር ድርጅቶች ከወያኔ ጋር ያላቸውን ሽርክና እንዲያቋርጡ መወትወት፤ አልሰማ ካሉ በቢዝነሳቸው ላይ አሉታዊ ቅስቀሳ ማካሄድ።
  8. የምዕራብ አገራት ዩኒቨርስቲዎች ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ግኑኝነት እንዲመረምሩ ማሳሰብ። በወጉ ሳያስተምሩ ለወያኔ ሹማምንቶች ዲግሪ የሚያድሉ ዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆችን ማስጠንቀቅ፤ ተግባሮቻቸውን ለተማሪዎቻቸው ጭምር መንገር (ለምሳሌ University of Greenwich ከ International Leadership Institute ጋር ያለውን ግኑኝነት እንዲሰርዝ፣ እስከዛሬ የሰጣቸውንም የማስትሬት ዲግሪዎች እንዲመረመር የሚጠይቅ ደብዳቤ ጽፎ በብዛት በፋክስ መላክ፤ ተመሳሳይ ደብዳቤ Open University እና ከወያኔ ጋር ተሻርከው ለሚሠሩ ዩኒቨርስቲና ኮሌጆች መላክ)
  9. ይህ ዘመቻ ለጊዜው በወያኔ ላይ ያነጣጠረ ቢሆንም፣ የሕዝቡን የነፃነትና የፍትህ ጥረት የሚያደናቅፉ የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ አገር ዜጎች በሆኑ ቱጃሮች የተያዙ ቢዝነሶችም የዘመቻው ዒላማ ሊሆኑ ይችላሉ።
በመጨረሻም የወጣቱ የማያልቅ የፈጠራ ችሎታ ከላይ በዝርዝሩ ውስጥ ያልተካተቱ ሆኖም ግን ውጤታማ የሆኑ የተቃውሞ መግለጫ ዘዴዎች ያፈልቃል ብለን እናምናለን። ስለሆነም ዘመቻውን በየአካባቢው በሚገኝ ሀሳብና ፈጠራ ማዳበር ይቻላል።
ይህ ዘመቻ ወያኔን ከስልጣን ለማባረር ምድር ላይ ከምናደርገው የመረረ ትግል ጋር ሲቀናጅ የሚፈለገውን ውጤት ስለሚያስገኝ ለነፃነቱ ግድ ያለው ዜጋ ሁሉ በሙሉ ሃይሉና አቅሙ ተሳትፎ እንዲያደርግ ግንቦት 7 የፍትህ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ አገራዊ ጥሪ ያቄርባል ::
በመስዋዕትነት ድልን እንቀዳጃለን !!!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ !!!
                                                                                    Posted by A.G

Friday, 4 July 2014

የመን አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ለወያኔ ፋሽስቶች አሳልፋ መስጠቷን በማስመልከት የወጣ መግለጫ Source G7.

የመን አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ለወያኔ ፋሽስቶች አሳልፋ መስጠቷን በማስመልከት የወጣ መግለጫ

የመን አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ለወያኔ ፋሽስቶች አሳልፋ መስጠቷን በማስመልከት የወጣ መግለጫ
ሰኔ 27 ቀን 2006 ዓ.ም
የግንቦት 7፣ የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ዋና ፀሐፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ሰኔ 16 ቀን 2006 ዓ.ም ለሥራ ጉዳይ በየመኒያ አየር መንገድ አይሮፕላን ተጉዞ በትራንዚት ሰንዓ ከተማ እያለ በየመን መንግሥት ፀጥታ ኃይሎች በሕገወጥ መንገድ ታግቶ መቆየቱ ማስታወቃችን ይታወሳል።
የየመን መንግሥት በህገወጥ መንገድ ያገተብንን የንቅናቄዓችንን አመራር በአስቸኳይ እንዲፈታ በተለያዩ መንገዶች ላለፈው አንድ ሣምንት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። የአገሩን የረዥም ጊዜ ጥቅም ማየት የተሳነው የየመን መንግሥት ከኢትዮጵያ ሕዝብ ይልቅ አምባገኑን ወያኔ መርጦ መሪያችንን ለእርድ አሳልፎ ሰጥቶብናል። በዚህም ሳቢያ የየመን መንግሥት ይቅርታ የማያሰጥ፤ ዘመን የማይሽረው ታሪካዊ ስህተት ፈጽሟል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ለወዳጅ ጎረቤት ትሁትና ቀና ቢሆንም ጥቃት በሚያደርስበት የቅርብም ሆነ የሩቅ ጎረቤት ላይ ግን ቁጣውን የሚመጥን የአፀፋ እርምጃ መውሰድ ያውቅበታል።
የወያኔ ፋሽስቶች አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን በማሰቃየት ትግላችንን ማቀዝቀዝ እንደማይችሉ ልናረጋግጥላቸው እንወዳለን። እንዲያውም በግልባጩ ቁጣና እልሃችን በእጥፍ ድርብ በመጨመር ትግላችንን ያጦዘዋል። ወያኔ፣ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን በውንብድና ጠልፎ መውሰዱ የትግሉን ሜዳ አስፍቶታል፤ የትግሉንም ዓይነት አብዝቶታል። ይህ ደግሞ የወያኔ ፋሽስቶችን ከፍ ያለ ዋጋ ያስከፍላቸዋል።
የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ህገ ወጥ እገታ ከተሰማ ዕለት ጀምሮ የፓለቲካ ልዩነት አጥር ሆኖ ሳይከልላችሁ ከጎናችን ለቆማችሁ የፓለቲካ ድርጅቶች፣ የሲቪክ ማኅበራትና ዜጎች ሁሉ ምሥጋናችንን እናቀርባለን። በወገናዊ ተግባራችሁ ልባችን ተነክቷል። ከዚህ በላይ ደግሞ ለቀጣዩ ወሳኝ ፍልሚያም እንደምንቆም እና የወያኔን እድሜ እንደምናሳጥር እምነታችን አጠንክሮልናል።
ከዛሬ ጀምሮ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ አንዳርጋቸው ጽጌን ሆኗል። ዛሬ ዘጠና ሚሊዮን አንዳርጋቸው ጽጌዎች በአንድነት ተነስተዋል። በአንድ አንዳርጋቸው ጽጌ ላይ የደረሰው ጥቃት ሰበብ ሆኖ የተቀሰቀሰው የሕዝብ ቁጣ የወያኔ ፋሽስቶችን ይጠራርጋል። በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ላይ ለደረሰውና ለሚደርሰው ጥቃት እያንዳንዱ የወያኔ ሹም በግል ዋጋ ይከፍላል። ከእንግዲህ በምሬት የተነሳሳው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሚወስደው እርምጃ ተጠያቂው ራሱ ወያኔ መሆኑን እውን ሆኗል። በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እስር የክተት አዋጅ ታውጇል። ለፍትህ፣ ለነፃነት፣ ለሀገር፣ ለእኩልነት ግድ ያለህ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ተነስ!!!
በመስዋዕትነት ድልን እንቀዳጃለን።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!
                                                                                               Posted by A.G