ከሰማያዊ ፓርቲ የተሰጠ ጥልቅ የሐዘን መግለጫ!
አንድ በስልጣን ላይ የተቀመጠ አካል ተቀዳሚ ተግባር የዜጎችን ደህንነት መጠበቅ መሆኑን ጤነኛ አዕምሮ ያለው የሰው ልጅ የሚገነዘበው ጥሬ ሃቅ ነው፡፡ እንደ እርግማን ዛሬ በኢትዮጵያ የስልጣን እርካቡን የተቆጣጠረው ቡድን የሚገዛቸውን ዜጎች የሚያያቸው እንደጠላት እንጅ የመንግስትን ጥበቃ እንደሚፈልጉ፤ በጠላትነት የፈረጃቸው ዜጎች በከፈሉት ግብር ስልጣን ላይ መቆየት መቻሉን እንኳን ባለስልጣናቱ መረዳት ተስኗቸዋል፡፡
ሰኔ 8 ቀን 2007 ዓ.ም በደብረ ማርቆስ ከተማ እጅግ በሚሰቀጥጥ ጭካኔ እንደ እባብ ተቀጥቅጦ የተገደላው የሰማያዊ ፓርቲ ቆራጥ ታጋይ ሳሙኤል አወቀ የስርዓቱ አገልጋዩች ለዓመታት ሲያስፈራሩት፣ ሲደበድቡት፣ ሰርቶ የመኖር መብቱን ሲጋፉት፣ ያልተሳከ የመግደል ሙከራ በተደጋጋሚ ጊዜ ሲፈፅሙበት መቆየታቸውን የሚያረጋግጡ በርካታ ማስረጃዎች ተይዘዋል፡፡ ሳሙኤል ሕይወቱ አደጋ ላይ እንደሆነችና ጥበቃ እንዲያደርጉለት የጠየቃቸው የፀጥታና የፍትህ አካላት በተገላቢጦሽ ተጨማሪ ዛቻና ማስፈራሪያ ያደርሱበት እንደነበር አይዘነጋም፡፡ አንድ ወጣት በተወለደበት ምድር በሕይወት የቆየባቸውን ጊዚያት በስጋት እንዲኖር ከተፈፀመበት ግፍ በተጨማሪ በሕይወት የመኖር መብቱ በአረመኔዎች እጅ ስትነጠቅ የህዝብን ፀጥታና ደሕንነት እናስከብራለን የሚሉ አካላት በመሃል ከተማ እንኳን ደርሰው ለመታደግ አቅሙም ሆነ ፍላጎቱ አልነበራቸውም፡፡
ሳሙኤል በአሰቃቂ ሁኔታ ከመገደሉ በፊት በተለያዩ ጊዚያት ለሚመለካታቸው አካላትና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያስተላልፋቸው የነበሩ መልዕክቶች እንደተጠበቁ ሆነው በተለይ ግንቦት 25 2007 ዓ.ም በራሱ ገፅ በሆነው “የፌስ ቡክ” ማህበራዊ ሚዲያ ካስተላለፈው መልዕክት መረዳት እንደሚቻለው በተደራጀ ሁኔታ ሕይወቱ አደጋ ላይ እንደሆነች አስረግጦ ተናግሯል፡፡ ሆኖም የሚሰማውና የሚጠብቀው ምንም አካል እንዳልነበረ ይልቁንም ለመገደሉ ተባባሪ የሆኑ የመንግስት አካላት እንደነበሩ ስጋቱን በገለፀ በቀናት ውስጥ ሕይወቱ በአሰቃቂ ሁኔታ መቀጠፏ ጉልሕ ማስረጃ ነው፡፡
በሰላማዊ ትግል ፅኑዕ እምነት የነበረው ሳሙኤል አወቀ ይደርስበት የነበረውን ለቁጥርና ለዓይነት አታካች የሆነ በደል ተቋቁሞ፣ ትግሉን እንዲያቆም ወይም የሚወዳትን ሕይወቱን አሳልፎ የሰጠላትን ሐገሩን ለቆ እንዲሰደድ ይህ ካልሆነ ግን የእሱን ሕይወት ለማጥፋት እጅግ ቀላል መሆኑን የስርዓቱ ባለስልጣናት እና ካድሬዎች ደጋግመው ቢነግሩትም በጭቆና ስር ለሚማቅቀው የኢትዮጵያ ሕዝብ የገባውን ቃል ከማጠፍ ይልቅ ሕይወቱን ለመሰዋት እንደሚቀለው የገባውን ቃል በተግባር አስመስክሮ አልፏል፡፡ በማሰርና በመደብደብ አላማውን እንደማያስቀይሩት፤ ከገደሉት ግን ቀሪ ታጋዮች በተለይም የእድሜ አቻዎቹ የሆኑ የእርሱ ትውልድ የሚሰዋለትን ዓላማ ከግብ እንዲያደርሱ “ትግሌን አደራ!! አደራ!!” በማለት ተማፅኖ አስቀምጧል፡፡
እኛም እንላለን፡፡ አደራህ ከባድ ነው፡፡ ቃልህን እናከብራለን፡፡ አላማህንም እናሳካለን!!!!
ይህ ስርዓት በህግም በሞራልም ኢትዮጵያን የማስተዳደር ብቃት የለውም፡፡ ወንጀለኞች ለፍርድ ይቅረቡ እያልንም አናላዝንም፤ ወንጀለኞቹ የመንግስት አካላት ናቸውና፡፡ በወንድማችንና ገና በለጋ እድሜው በተቀጨው የትግል አጋራችን ላይ የተፈፀመውን ግፍ አይቶ እንዳላዬ ዝም ያለ መንግስት ከዚህ የተሻለ መልካም ነገር ያመጣል ብለን አንጠብቅም፡፡ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ግን መልዕክት አለን፡፡ እስከ መቼ በግፍ እንገደላለን?!! ሸፍጠኞችስ እስከ መቼ ይዘባበቱብናል?!! ትግል ለውጤት የሚበቃው በተወሰኑ ቡድኖች ወይም ግለሰቦች መፍጨርጨር ብቻ ባለመሆኑ የግፍ ስርዓት እንዲያበቃ ሁላችንም የሚገባንን የዜግነት ድርሻ እንድንወጣ ጥሪ እናቀርባለን፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ በአባላቱና በደጋፊዎቹ በአጠቃላይም የተለየ አስተሳሰብ ስላላቸው ብቻ በካድሬዎች የሚታሰሩ፣ የሚገረፉ፣ የሚሳደዱ፣ የሚዋረዱና የሚገደሉ ዜጎች ለከፈሉት መራራ ፅዋ ክብር ይሰጣል፡፡ መስዋዕትነታቸውም በከንቱ እንዳይሆን እሰከመጨረሻው ይታገላል፡፡
ሳሙኤል “ብታሰርም፣ ብገደልም ይህን ሁሉ የማደርገው ለሐገሬና ለነፃነቴ ነው” ያልከው ቃልህ ከመቃብር በላይ ነው!!!! ቃልህን እናከብራለን፡፡ አላማህንም እናሳካለን!!! ትግል ይቀጥላል . . .
ሰኔ 10 ቀን 2007 ዓ.ም
አዲስ አበባ
"""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""
"""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""""
በተያያዥ ዜና አንድ የአረና አባል በሶስት ሰዎች ታንቀው በምሽት ተገደሉ
ኣቶ ታደሰ ኣብርሃ የተባሉ የዓረና-መድረክ ኣባልና የምዕራባዊ ዞን የዓረና ኣመራር ኣባል ትናንት ማታ 09 / 10 / 2007 ዓ/ም በሶስት ሰወች ታንቀው ተገደሉ።
ኣቶ ታደሰ ኣብራሃ በቓፍታ ሑመራ ወረዳ ማይካድራ ቀበሌ ኑዋሪ ሲሆኑ በዘንድሮው ምርጫ ወቅት በቀበሌው ኣስተዳዳሪዎች፣ካድሬዎች፣ የሚቀርቧቸው ሰዎች ከዓረና-መድረክ ኣባልነታቸው እንዲለቁ የተሸመገሉ፣ የተለመኑና በመጨረሻም ዛቻዎች ሲደርስባቸው እንደነበረ ይታወቃል።
ኣቶ ታደሰ ማታ 03:00 በ 3 ሰዎች ኣንገታቸው የታነቁ ሲሆን ሶስቱ ሰዎች ሙቷል ብለው የተዋቸው ቢሆኑም ሂወታቸው እስከ 09:15 ኣላለፈችም ነበር።
ኣቶ ታደሰ ኣብራሃ የ48 ዕድሜ ጎልማሳ ነበሩ። ኣደጋው 3 ሰዎች እንደፈፀሙባቸው፣ በኪሳቸውም 300 ብር የነበረ ቢሆንም ሰዎቹ ሊወስዱት እንዳልቻሉ ተናገረው ነበር። የኣቶ ታደሰ ሬሳ በሑመራ ሆስፒታል ላለማስመርመር የማይካድራ ፖሊስ ትራፊክ በዓረና ኣባላት ላይ ከፍተኛ ጫና የፈጠሩ ሲሆን የተለያዩ የመንግስት ኣካላትም ምርመራው እንዳይካሄድ የተለያዩ ጫናዎች እንደፈጠሩ ኣባሎቻችን ከስፍራው ገልፀውልናል።
ሬሳው ወደ ሑመራ ወስዶ ለማስመርመር የሚጠቅም መኪና ለመከራይ ሲባል ኣባሎቻችን የተካራት ሞተር ሳይክ በፖሊስት ትራፊክ ተከልክላለች።
የኣቶ ታደሰ ኣብራሃ ቤት ኣካራይና ሌሎች ሰዎች ከኣደጋው በተያያዘ ጫና እየተፈጠረባቸው እንደሆነ ለማወቅ ተችለዋል።
የኣቶ ታደሰ ኣብራሃ ግድያ በሳምንት ውስጥ የወጣት ሳሙኤል ኣወቀንጨምሮ ለሁለተኛ ግዜ በፖለቲከኞች ላይ የተፈፀመ ግድያ ሲሆን ከ2007 ዓ/ም በዓረና- መድረክ ኣባላት ለሁለተኛ ግዜ የተፈፀመ ግድያ ያደርገዋል።