Sunday, 29 December 2013

የአንዱዓለም አራጌ መልክት ከቃሊቲ ( እስቲ 2013 በድጋሚ ዞር ብለን እናብበው ) ሠላማዊ ትግል በአንድ ወይንም በሁለት ሠልፍ የሚቋጭ ሳይሆን አያሌ ስልቶችንና ሠፊና ቀጣይነት ያለውን እንቅስቃሴ የሚያካትት ነው፡፡ የፖለቲካ ባህላችንና አስተሳሰባችንን ከማዘመን ጀምሮ ገዢዎች ነፃነትን የማይፈሩበትን ስነ-ልቦና እንዲላበሱ ማድረግና ለበርካታ ዘመናት በጭቆና ደቅድቅ ጨለማ ውስጥ ያለችውን ሀገራችን የነፃነት ብርሃን ከደር እስከዳር የሚበራባት ሀገር እስክትሆን ድረስ መታገል ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ የላቀና የከበረ ምን ቁም ነገር ይኖራል? source UDJ

የአንዱዓለም አራጌ መልክት ከቃሊቲ (በሰላማዊ ሰልፍ ላይ የተነበበ)

ከሁሉ አስቀድሜ በዚህ ታላቅ ህዝባዊ ሠላማዊ ሠልፍ ለተገኛችሁ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼለእያንዳንዳችሁ በተናጠል ልባዊ የአክብሮትና የናፍቆት ሠላምታዬ በግፍ ከታሰርኩባት ጠባቧ ክፍል ይድረሳችሁ
Andualem Aragie (3)ኢትዮጵያውያን ለዘመናት እውን ያላደረግነውን የህዝባዊ ልዕልና ጥያቄና ሌሎች ከነፃነት እጦት ጋር የተቆራኙ በአገዛዙ የሚፈፀሙ አያሌ የአፈና ተግባሮችን ለመቃወም በተጠራው በዚህ ሠላማዊ ሠልፍ ላይ ከጎናችሁ መሠለፍ ባለመቻሌ ባዝንም፣ ከተሰለፋችሁላቸው ዓላማዎች አንዱ የእኔና የጓደኞቼን ከእስር መቀቀቅ የሚመለከትና የታሰርኩለትም ዓላማ አካል በመሆኑ በመንፈስ ከጎናችሁ እንዳለሁ አምናለሁ፡፡ በዚህም ታላቅ ደስታ ይሰማኛል፡፡
ኢትዮጵያ ህዝባዊ ልዕልና የሠፈነባት የነፃነትና የዴሞክራሲ ምድር ትሆን ዘንድ የቀደሙ ትውልዶች ከፍተኛ መሰዋእትነት ከፍለዋል፡፡ ሌላውን ትተን የዛሬ 4ዐ ዓመት የተደረገውን ትግል ብቻ መጥቀስ ጥሩ ማሳያ ይሆናል፡፡ የዛሬ 4ዐ ዓመት ‹‹ሕዝባዊ መንግሥት›› ለመመስረት በሚል በተደረገ ትግል ሊለካ የማይችል መስዋዕትነት ተከፍሏል፡፡ ነገር ግን ‹‹ከጎናቸው ተሰልፈን ታገልን የሚሉን ወገኖች ዛሬ የኢትዮጵያን ህዝብ እግረ ከወርች አስረው እየረገጡት ይገኛሉ፡፡
ዛሬም ከ4ዐ ዓመት በኋላ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሉዓላዊ ሥልጣኑ ባለቤት መሆን አልቻለም፡፡ ዛሬም ከ4ዐ ዓመት በኋላ ሕዝብ ከገጠር እስከ ከተማ በካድሬዎች ፈርጣማ መዳፍ እየታሸ ነው፡፡ ዛሬም ከ4ዐ ዓመት በኋላ ከማደናገሪያ ስልትነት ባለፈ የህዝብ የመናገርና የመፃፍ መብት አልተከበረም፡፡ ዛሬም 4ዐ ዓመት በኋላ አገዛዙን የሚቃወሙ ዜጎች በበሬ ወለደ ክስ በግፍ ይታሰራሉ፡፡ እኔና ጓደኞቼ ለዚህ ማሳያዎች ነን፡፡ ዛሬም ከ4ዐ ዓመት በኋላ የኢትዮጵያ ሕዝብ የመረጠው ሳይሆን አፈ-ሙዝ ያገነነው በምርጫ ተውኔት 99.6% የህዝብ ድምጽ በመዝረፍ ሀገራችንን በዓለም ፊት የሚያኮስስና የህዝቧን ክብር የሚያዋርድ ተግባር የሚፈፀምባት ሀገር ነች፡፡ ዛሬም ከ4ዐ ዓመት በኋላ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ በጥቂት የወቅቱ አምባገነኖች በገዛ ሀገሩ እስረኛ ሆኖ ይገኛል፡፡
ዛሬ እየተካሄደ ያለው ሠልፍ የኢትዮጵያ ህዝብ ከዘመናት እስራት ነፃ ለመውጣት የሚያደርገው አጠቃላይ ትግል አካል ነው፡፡ ኢትዮጰያውያን የየትኛውም ቋንቋ ተናጋሪዎች ብንሆን፣ የየትኛውም እምነት ተከታዮች ብንሆን፣ የየትኛውም ፖለቲካ ፓርቲ አባሎች ብንሆን፣ በየትኛውም የፆታና የእድሜ ክልል ብንገኝ ሁላችን አንድ የሚያደርግ ሰብአዊ ልዕልናችን ተከብሮ በነፃነት የመኖር ተቀዳሚ አጀንዳ አለን፡፡
ነፃነት ማንም በችሮታ ወይንም በአዋጅ የሚያረጋግጥልን ሳይሆን በነፃነት ለነፃነት የተፈጠርን ሉዓላዊ ፍጡራን መሆናችንን ከልብ ስናምን የምንጎናፀፈው ፀጋ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ትልቁ የነፃነት ጠላት እራስን ዝቅ አድርጎ ከማየት የሚመጣ ፍርሃት ነው፡፡ ፍርሃትን ያላሸነፈ ሕዝብ በአዋጅ ነፃ ሊወጣ አይችልም፡፡ አዋጅ መች ቸገረንና? ፍርሃትን ያላሸነፈ ህዝብ የነፃነቱ ባለቤት ሊሆን አይችልም፡፡ ፍርሃትን ያላሸነፈ ህዝብ ለልጆቹ ነፃ ሀገር ሊያወርስ አይችልም፡፡ የፍርሃትንና የግለኝነት ወረርሽኝ ማስወገድ ፈጽሞ ጊዜ የሚሰጠው ተግባር አይደለም፡፡ ፍርሃትንና ለኔነትን ድልነስታችሁ ዛሬ ለነኀነት መሰለፍ በመቻላችሁ የተግሉን የመጀመሪያና ወሳኝ መዕራፍ ተሻግራችኋል፡፡
ፍርሃትን በማሸነፍ ለነፃነት መታገል ወሳኝ የመሆኑን ያህል፣ ከቀደሙ ስህተቶቻችን መማር፣ ትግሉን በተጠናና በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት ማካሄድም የዚያኑ ያህል አስፈላጊና ወሳኝ ነው፡፡
እስከ አሁን በዝምታችን አምባገነኖች የልብ ልብ እንዲሰማቸው ብሎም አፍነው እንዲገዙን እድል ሰጥተናቸዋል፡፡ እስከ አሁን መብቶቻችንና ሰብአዊ ክብራችን በግደለሽነት እንዲረገጡ በመፍቀዳችን ኢትዮጵያና ሕዝቧ የጥቂት ገዢዎች አንጡራ ሀብት ሆናለች፡፡ እስከ አሁን በቁርጠኝነት ባለመታገላችን ዛሬም እንደ አዲስ ከአምባገነንነት ጋር ግብግብ መግጠም ግድ ሆኖብናል፡፡ የአፈናውን የክፋት ደረጃና የአገዛዙን አሙለጭላጭ የአፈና ስልቶች ግንዛቤ ውስጥ ያስገባና ዘመኑን የሚመጥን የፀና ሠላማዊ ትግል ማድረግ ከእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ይጠበቃል፡፡

Friday, 27 December 2013

ትንሽ ስለጃዋር መሀመድ Source D.C.E.S.O.N

ከዓለማየሁ መሀመድ

ሁለት ነገሮችን ላንሳ።

1. የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ትግል መሬት አንቀጥቅጥ ሆኖ ለሁለት ዓመት ገደማ ዘልቋል። በዚህ ትግል ውስጥ በሀገር ቤት ከስርዓቱ ጋር አንገት ለአንገት ተናንቀው ደም ህይወታቸውን ገብረው ትግሉ በማይናወጥ ጽናት ላይ እንዲቆም ያደረጉት ብዙሃኑ ሙስሊሞች ዋጋቸው በክብር መዝገብ ላይ ምንጊዜም ወርቃማ በሆነ ቀለም ተመዝግቦ ይቀመጣል። ከእነሱ ባሻገር በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ትግሉ መሬት ይዞ በሰከነ መልኩ እንዲጓዝ ያደረጉት አስተዋጽኦም የሚዘነጋ አይደለም። ጃዋር በዚህ ውስጥ ስሙ ሲጠቀስ ነበር። የሙስሊሞች ትግል ላይ ትንሽም ብትሆን አሻራው አርፎበታል። ያኔ ነው። በፊት። አሁንስ?Jawar Mohamed Muslim fundamentalist

2. የኦሮሞ ህዝብ ጭቆና ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ የተለየ ነው- አይደለም -የሚለው ክርክር ለጊዜው ይቆይና የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ለ40 ዓመታት ሲያቀነቅነው የነበረውና ውጤት ሳይኖረው ዘመናት የቆየው ትግሉ አሁን ‘’የኦሮሞን ህዝብ ትግል በኢትዮጵያ ጥላ ስር’’ የሚለው ሀሳብ አሸንፎ ሲወጣ ጃዋር ብቅ አለ። መጀመሪያ ላይ በሳል በሆኑ፡ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ፡ የሰውን ልጅ በአንድ መነጽር የሚመለከቱ የሚመስሉ ሀሳቦች በጃዋር አፍ ውስጥ ይዋኙ ነበር። ይህም በተቀረው ኢትዮጵያውያን ዘንድም ጃዋር ምናልባት ያረጀውን የኦነግ ጠባብ ብሄርተኝነት ከመቃብር አስቀመጦ የኦሮሞን ህዝብ ከዕውነተኛ ድል የሚያቀርብ አዲስ መንገድ ይጀምራል የሚል ብጣቂ ተስፋ ውስጣቸው የነበሩ ጥቂቶች አልነበሩም። ከመነሻውም የተጠራጠሩት፡ የተደበቀው ማንነቱ አንድ ቀን ይወጣል ብለው በጥርጣሬ ሲመለከተቱት የነበሩት ቁጥራቸው የትየለሌ ነበር። ሆኖም እኔም ሆንክ ጥቂቶች ጃዋርን እንደ አብሪ ኮከብ መመልከታችን አልቀረም። አሁንስ?

ጃዋር አሁን አይሰማም። መስማት የሚፈልገው የፈለገውን ብቻ ነው። በየአዳራሹ የሚሰማው ጭብጨባ ሰርቆታል። ቀልቡ አሁን ከሚኒሶታ እስከ ለንደን በተዘረጋው የ’ኦሮሞ ፈርስት’ ቅልጥ ያለ የወቅቱ ነጠላ ዜማ ላይ ሆኑዋል።

1. የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ትግል በእፎይታ ጊዜ ላይ ቢሆንም የጃዋር ‘ኦሮሞ ፈርስት’ በይፋ ከታወጀችና ‘ሜንጫ’ዋ በሚኒሶታ መድረክ ከተስተጋባች በኋላ የሙስሊሞች ትግል ላይ መጠነኛ ተጽእኖ መፈጠሩ አልቀረም። የሙስሊሙን ትግል የኢትዮጵያ ህዝብ ትግል አድርገው የተሰለፉ ወገኖች በጥቂቱ ማፈግፈጋቸው በመጠኑ ይታያል። ሜንጫ የሚለውን ቃል ጃዋር ሚኒሶታ ላይ ካፈነዳት ወዲህ በሙስሊሙ ማህበረሰብ ዘንድ እንኳን ውዥንብር ተፈጥሯል። እናም የሟችዋ ሚካያ በሃይሉ ዜማን ልዋሰው- “ሸማመተው”:: ህወሀት ሸመተ:: ትግሉ እንዲደበዝዝ ቀን ከሌት ይመኝ የነበረው ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ- ሸማመተው!!

2. ከምንጊዜውም በላይ የኢትዮጵያ ህዝብ አንድነቱን ለማሳየት፡ በጋራ ወደ ምር ነጻነት ለመምጣት እጅ ለእጅ እየተያያዘ ያለበት ወቅት ላይ እነጃዋር የኦሮሞ ብሄርተኝነትን ወደ ጠባቡ ጽንፍ ወስደውት ዘራፍ ማለት መጀመራቸው በተወሰነ ደረጃ ለህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ከሰማይ የወረደ አዱኛ ሆነለት:: አሁንም ሚካያ ትላለች -“ሸማመተው” – ህወሀት ሸመተ::

እነ ጃዋር እየተናገሩ ነው:: ‘ኦሮሞ ፈርስት’-‘ ማይ ካንትሪ ኢዝ ኦሮሚያ’ :: የህወሀት የፌስቡክና ትዊተር ሰራዊቶች ስማቸውን በኦሮምኛ ለማድረግ ከብርሃን ነበር የፈጠኑት:: እናም ‘ኦሮሞ ፈርስት’ መፈክራቸው ሆኖ አጼ ሚኒሊክ ላይ እርግማናቸውን ውእግዝ ከማርዮሱን እያዘነቡት ነው።

ጭብጨባው ቀልጧል። ነጠላ ዜማው ሰማይ ምድሩን አድምቆታል፡፡ እነጃዋር በህወሀት ነጠላ ዜማ ዳንሱን እያቀለጡት ነው። የሚሰማ ጆሮ የላቸውም። ልባቸው ሸፍቷል። አውቀው ይሁን ሳያውቁት ከህወሀት መንደር ዘልቀው የልፊያ ፖለቲካውን ተያይዘውታል። ጭብጨባ ክፉ ነው። ላላወቀበት ስካር ነው።

ሰሞኑን ከጨፌ ኦሮሚያ አንድ መረጃ ደርሶኛል። ሳይላመጥ አይቀርብም በሚል ለጊዜው ይዤዋለሁ። እነጃዋርን የተመለከተ ነው። ምናልባት መረጃውን በማስረጃ ማስደገፍ ከቻልኩኝ በድብቅ የተፈጸመውን የእነጃዋርንና ህወሀትን ጋብቻ ይፋ አደርጋለሁ።

እስከዚያው ጩኧቱን እየሰማን እንቆይ። መልካም ጋብቻ የምንልበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም።


                                                                                                     Posted by  A. G

Monday, 16 December 2013

ታላቅ ህዝባዊ ስብሰባ በኖርዎይ በርገን ከተማ በደመቀ ሁኔታ ተካሔደ Source DCESON Democratic Change in Ethiopia Support Organization Norway

በበርገን ከተማ ለመጀመርያ ግዜ በዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ የድጋፍ ድርጅት ኖርዎይ  በርገን ቅርንጫፍ አስተናጋጅነት በዲሴምበር 14፥2013 የተዘጋጀው ህዝባዊ ስብሰባ በደመቀ ሁኔታ የተጠናቀቀ ሲሆን ከ100 በላይ የሚገመት ህዝብ የተገኘ ሲሆን ከተለያዩ የኖርዎይ ከተሞች የተሰባሰቡ ኢትዮጵያውያን በዝግጅቱም ላይ ተገኝተዋል፥፥
በዝግጅቱ ላይ ተጋባዥ እንግዶች የነበሩት

1ኛ. ዶ/ር ታደሰ ብሩ የግንቦት7 የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ስራ አስፈጻሚ አባል
2ኛ. አቶ ዮሃንስ አለሙ የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት በኖርዎይ  ዋና ሊቀመንበር
3ኛ. ዶ/ር ሙሉአለም አዳም የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ በኖርዎይ የድርጅት አባል ናቸው፥፥
የውይይት መድረኩ ከመጀመሩ በፊት በሳውዲ አረቢያ እየተሰቃዩ፥ እየተገደሉ እንዲሁም በግፍ ኢሰብአዊ ድርጊት ለተፈፀመባቸው ወገኖቻችን የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት በማድረግ የተጀመረ ሲሆን የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ የድጋፍ ድርጅት ኖርዎይ  የበርገን  ቅርንጫፍ ጽ/ት ሰብሳቢ አቶ ሹሜ ወርቁ አጭር የመክፈቻ ንግግር ካረጉ በኋዋላ ተጋባዥ እንግዶቹ በየተራ ስለሚመሩአቸው ድርጅቶችና የወቅቱን የሃገራችንን አስከፊ የፖለቲካ ሁኔታ በተመለከተና ሁሉም የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች አብረው በስምምነት የሚሰሩበትን ሁኔታ ማምጣት እንዳለብን እንዲሁም ስለ  መደራጀት አስፈላጊነት ሰፋ ያለ ማብራርያ  ሰጥተዋል፥፥
ዶ/ር ታደሰ ብሩ ስለ ግንቦት 7 የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ዓላማ ራእይና ግብ እንዲሁም ስለውጭ እምቢተኝነት ሰፋ ያለ ማብራሪያ ከሰጡ  በኋላ ሁሉም ኢትዮያዊ ግንቦት7ትን እንዲቀላቀልና ሃገራችን ኢትዮጵያ ከገባችበት አዘቅት ውስጥ ተባብረን እንታደጋት በማለት  ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በተለያዩ ድርጅቶች ስር ተደራጅቶና ታቅፎ መንቀሳቀሱ ያለውን ጠቀሜታና የሐይማኖትና የሲቪክ ማህበራትን ማደራጀትና ማጠናከር ጠቃሚ መሆኑን አሳስበዋል፥፥ ፥፥
 አቶ ዮሃንስ አለሙ የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት በኖርዎይ  ዋና ሊቀመንበር ስለ ዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ አመሰራረትና የደረሰበትን ደረጃ እንዲሁም ያከናወናቸውን ተግባራት በተመለከተ በሰፊው ገለጻ  ያደረጉ ሲሆን  ከህዝቡም  ለቀረበላቸው ጥያቄም  ምላሽ ሰጥተዋል፥፥
በተጨማሪም ዶ/ር ሙሉዓለም አዳም በኖርዎይ የስደተኞች አኗኗር ዙሪያ ያለውን ችግር እንዲሁም ሁሉም የተቃቃሚ ድርጅቶች አንድ ላይ ሆነው እንዲሰሩ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን በመጨረሻም የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ የድጋፍ ድርጅት ኖርዎይ የበርገን ቅርንጫፍ በተቋቋመ በአጭር ግዜ ውስጥ የደረሰበት ደረጃም በእጅጉ አስደሳች እንደሆነ በመግለፅ ያላቸውን አድናቆት ገልጸው ህዝቡ ለነጻነት ለሚደረገው  ትግል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል፥፥
እንዲሁም በዝግጅቱ ላይ በሐና ሰመረ ሐቅ ተሰደደ በሚል ርእስ አጭር ግጥም የቀረበ ሲሆን በመቀጠልም በሎሚታ ገብረሚካኤል በምስል በተደገፈ በቀረበው የኢትዮጵያ የታሪክ ጉዞ ከነገስታት ስርአት እስከ ሐገራችን በወያኔ አገዛዝ ስር ወድቃ አሁን የደረሰችበትን ሁኔታ የሚያሳይ ዘገባ ለታዳሚው ቀርቧል፥፥
በመጨረሻም ለእንግዶቹ የተለያዩ ጥያቄዎች ቀርቦ ውይይት ከተደረገ በኋላ ዝግጅቱ የግንቦት 7 ህዝባዊ ሐይል መዝሙርን በመዘበር በተሳካ ሁኔታ ተጠናቋል፥፥
የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ የድጋፍ ድርጅት ኖርዎይ  የበርገን  ቅርንጫፍ ጽ/ት
ዲሴምበር 14፥2013
                                                                                                                                      A.G

Sunday, 15 December 2013

ሁለገብ-ገብ ትግል – ከኔልሰን ማንዴላ ጋር የምንጋራው የትግል ስትራቴጂ

ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄም በኔልሰን ማንዴላ ዜና እረፍት የተሰማውን ሐዘን በመግለጽ መግለጫ ያወጣ ቢሆንም የትግል ተሞክሯቸው ለአገራችን ስላለው ጠቀሜታ ተጨማሪ ቁም ነገሮችን ማንሳት አስፈላጊ ሆኖ አግኝቶታል።
ኔልሰን ማንዴላንና የትግል ጓዶቻቸው መሣሪያ እስከማንሳት ያደረሳቸው የደቡብ አፍሪቃ አፓርታይድ አገዛዝ ዋነኛው መገለጫው የባንቱስታን ሕግ ነበር። በዚህ ህግ መሠረት ደቡብ አፍሪቃ ዘርን መሠረት ያደረጉ አስር “ባንቱስታ” የተሰኙ “ራስ ገዝ” ግዛቶች ተቋቁመው ነበር። ያኔ በደቡብ አፍሪቃ አገዛዝ ሥር በነበሩ የደቡብ ምዕራብ ግዛቶች ደግሞ ሌላ አስር ባንቱስታዎች ነበሯቸው። በእያንዳንዱ ደቡብ አፍሪቃዊ መታወቂያ ባንቱስታው እንዲገልጽ ህጉ ያስገድዳል። የአንዱ ባንቱስታ ነዋሪ ያለልዩ ፈቃድ ወደሌላው ባንቱስታ መሄድ አይችልም። ከዚህም ሌላ ለነጮች ብቻ በተከለሉ ቦታዎች ጥቁሮች ለሥራ ካልሆነ በስተቀር ለሌላ ማናቸው ተግባር እንዳይገኙ ህጉ ያዛል። አፓርታይድ የደቡብ አፍሪቃ ዜጎችን በየዘር ክልሎቻው ውስጥ አጉሮ አገራቸውን እስር ቤታቸው እንዲሆን አደረገው። ይህንን ለመቃወም ኔልሰን ማንዴላ እና የወቅቱ ታጋዮች በመጀመሪያ ሰላማዊ ትግልን ሞከሩ፤ ያ አላዋጣ ሲል መሣሪያ አነሱ።
በአሁኑ ሰዓት ባንቱስታን መሰል የክልል አስተዳደር ያለው በአገራችን በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ነው። ልክ በአፓርታይድ ደቡብ አፍሪቃ እንደነበረው ሁሉ የኛም መታወቂያዎች ዘራችንና ክልላችንን ይገልፃል። በአፓርታይድ ደቡብ አፍሪቃ እንደነበረው ሁሉ እኛም ከክልላችን ውጭ ተንቀሳቅሰን መሥራትና መኖር አንችልም። ከቤንሻንጉል-ጉሙዝ እና ከደቡብ ክልሎች ተፈናቅለው ለጎዳና ኑሮ የተዳረጉት የአማራ አርሶ አደሮች የዚህ ፓሊሲ ሰለባዎች ናቸው።
ኔልሰን ማንዴላ እና ድርጅቱ ኤ. ኤን. ሲ. በሰላማዊ ትግል ብቻ አፓርታይድን ማስወገድ እንደማይቻል የተገነዘቡት ከስዊቶ እልቂት ነው። በስዊቶ እልቂት 176 ዜጎች እንደተገደሉ ይነገራል። እኛ አገር ብዙ ስዌቶዎች አሉ። በበደኖ፣ በአዋሳ፣ በሀረር፣ በጋምቤላ፣ በጎንደር፣ በኦጋዴን፣ በአዲስ አበባ እና በሶማሊያ የደረሱት እልቂቶች እያንዳንዳቸው የስዌቶን እልቂት ያክላሉ። በዚህም ላይ በሰቲትና በሁመራ የተደረገው ስልታዊ የዘር ማጥራት፤ የወጣቶች ያላባራ ስደት የዚሁ ፓሊሲ አስከፊ ውጤቶች ናቸው።
ሰላማዊ ትግል ብቻውን የደቡብ አፍሪቃ ዘረኛ አገዛዝን ማስወገድ አልቻለም። ሰላማዊ ትግል ብቻውን ወያኔ በአገራችን ላይ የጫነብን ዘረኛ አገዛዝ እንዲያበቃ ማድረግ ይችላል ብሎ ማመን አዳጋች ነው። ስለዚህም ነው ማንዴላ እንዳደረገው ሁሉ ግንቦት 7 ም ሁለገብ ትግልን እንደ ትግል ስትራቴጄ ለመያዝ የተገደደው።
ሁለገብ ትግል ሕዝባዊ አመጽ እና ሕዝባዊ እምቢተኝነትን አጣምሮ መያዝ ይጠይቃል። ሁለገብ ትግል መጨከንን ያም ሆኖ ለእርቅ አንድነት ለሀገር እና ለወገን የጋራ ጥቅም መሥራትን ይጠይቃል። ሁለገብ ትግል ዘረኝነትን በጽናት የመታገል ሆኖም ግን ይቅር ባይ መሆንን ይጠይቃል።
ግንቦት7፡ የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ሁለገብ የትግል ስትራቴጂን በአማራጭነት ሲወስድ ከወያኔ ዘረኛ አገዛዝ ጋር ተመሳሳይ የሆነውን የደቡብ አፍሪቃ አፓርታይድ ሥርዓትን ለመለወጥ የነበረውን ፍቱንነት በጥልቀት በማጤን ነው።
ዘላለማዊ እረፍት ለኔልሰን ማንዴላ
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

የምስራቅ ኢትዮጵያ ፖለቲካ ክፍል ፪ (ከጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ )

የምስራቅ ኢትዮጵያ ፖለቲካ ክፍል ፪ (ከጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ )

December 14, 2013
ባለፈው ሳምንት የምስራቅ ኢትዮጵያ ፖለቲካን ተጨባጭ እውነታዎችን ቃኝቼ ተከታዩን ክፍል በይደር አቆይቼው እንደነበረ ይታወሳል፤ እነሆም ዛሬ እንዲህ እቀጥላለሁ፡-Temesgen Desalegn Feteh newspaper editor
ሐረር እንደ ማሳያ
(መቼም ኢህአዴግ በብቸኝነት የሚኩራራበት የፖለቲካ ‹ስኬት›፣ ለዘመናት አንድ ሆኖ የኖረ ሕዝብን ‹ብሔር ብሔረሰቦች› በሚል ከፋፋይ የ‹ክርስትና ስም› እጥምቆ በአደባባይ ማስጨፈር ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ ርግጥ ነው በአንድ ወቅት በፍትህ ጋዜጣ ላይ ‹‹የብሔር ብሔረሰቦች መብት እስከ መጨፈር›› በሚል ርዕስ የታተመ መጣጥፍን ተከትሎ ‹ፀረ-ብሔር ብሔረሰቦች› ተደርጌ በተመሰረተብኝ ክስ ፍርድ ቤት መመላለሴ ዛሬም ድረስ መቋጫ አላገኘም፤ ርግጥ ነው ኢትዮጵያውያን ወንድም እህቶቼ በስታዲዮሞች እየተሰባሰቡ የራስ ፀጉራቸው ላይ ላባ ሰክተው፣ ቆዳ አገልድመው እየዘለሉ ትርኢት ከማሳየት ባለፈ የመልካም አስተዳደር፣ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ መብቶቻቸው ተጠቃሚ መሆን አልቻሉም፡፡ …እውነታው ይህ ቢሆንም ወደ አጀንዳችን /የከሸፈው ፌደራሊዝምን/ ወደ መፈተሹ በአዲስ መስመር እንመለስ፡፡
ቋንቋን መሰረት ያደረገው ኢህአዴግ ሰራሹ ‹ፌደራሊዝም› አወቃቀር የሀገሪቱ መፃኢ ዕድል የተቋጠረበት ‹የሰዓት ቦንብ› መሆኑን ለመረዳት የምስራቅ ኢትዮጵያዋን ሐረር እንደ መሳያ መውሰዱን ግድ የሚያደርጉ በርካታ ገፊ ምክንያቶች አሉ፡፡ እንደሚታወቀው የሐረር ከተማ አመሰራረት ብዙሃኑ ህዝብ ከሚኖርበት ‹ጀጎል› ከተሰኘው በግንብ የተከለለ ቅፅር ጋር ይያያዛል፡፡ በ16ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ራሳቸውን ከብሔር ወረራ ለመከላከል በአካባቢው ነዋሪዎች እንደታነፀ በርካታ ድርሳናቶች የሚናገሩለት ጥንታዊውና ታሪካዊው የጀጎል ግንብ በአምስት (ሐረር፣ ኤረር፣ ሠንጋ፣ ቡዳ እና በርበሬ በር በሚባሉ) በሮች የተከፋፈለ ነው፡፡
ጀጎል ከ40ሺ ለማያንሱ የክልሉ ነዋሪዎች መጠለያ ሲሆን፣ ከነዚህ ውስጥ ከዘጠኝ ሺህ በላይ የሕዝብ ቁጥር ያላቸው የሐረሪ ተወላጆች እንደሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ይህም ሆኖ መስከረም 30 ቀን 1997 ዓ.ም. ‹‹የሐረሪ ሕዝብ ክልል መንግስት ሕገ-መንግስት›› በሚል ርዕስ ተሻሽሎ የፀደቀው አዋጅ፣ ስርዓቱ በአደባባይ ከሚመፃደቅበት ቋንቋን መሰረት ያደረገ ‹ፌደራሊዝም› የሚቃረኑ እና ከዴሞክራሲ ባህሪያት ጋር የሚጋጩ በርካታ አንቀፆች የታጨቁበት መሆኑ ለጠቀስኩት ሀገራዊ ስጋት መነሻ ነው፡፡ ለማሳያም ያህል የክልሉ ምክር ቤት ይቋቋምበታል ተብሎ በሕገ-መንግስቱ ውስጥ የተካተተውን የምርጫ ሕግ መመልከት የሚችል ይመስለኛል፡፡ ይህ ሕገ-መንግስት ተሻሽሎ ከመፅደቁ ሶስት ዓመት ቀደም ብሎ በስታስቲክ ባለሥልጣን ይፋ የተደረገው መረጃ የክልሉ ነዋሪ ህዝብ ብዛት በጥቅሉ 131,139 እንደሆነ ይገልፅና በየብሔሩ ሲከፋፈል ደግሞ ኦሮሞ 41%፣ አማራ 22.77%፣ ሐረሪ 8.65%፣ ጉራጌ 4.34% ሶማሌ 3.87%፣ ትግራይ 1.53%፣ አርጎባ 1.26% መሆኑን ይዘረዝራል፤ በስፋት የሚነገሩ ቋንቋዎችም ኦሮምኛ 56%፣ አማርኛ 27.53%፣ ሐረሪ 7.33%፣ ሶማሊኛ 3.70%፣ ጉራጌኛ 2.91%… ነው ይለናል፡፡
በመሬት ያለው እውነታ ይህ ቢሆንም የክልሉ ሕገ-መንግስት ደግሞ በአንቀፅ 49 ‹‹የሐረሪ ሕዝብ ክልል ምክር ቤት›› በሁለት ጉባዔዎች እንደሚመሰረት ከገለፀ በኋላ፣ እነርሱም ‹‹የህዝብ ተወካዮች ጉባኤ›› እና ‹‹የሐረሪ ብሔራዊ ጉባዔ›› እንደሆኑ ይነግረናል፤ ይኸው አንቀፅ በቁጥር 2 እና 3 ላይ ‹የሕዝብ ተወካዮች› ሃያ ሁለት፣ የሐረሪው በብሔሩ ተወላጆች ብቻ የሚወከሉ 14 አባላት ይኖሩታል ይላል፡፡ ይህ ሁኔታ በምርጫ ወቅት እንዴት እንደሚተገበር ደግሞ በአንቀፅ 50 ላይ ‹‹የጉባዔዎች አከፋፈል፣ አወካከልና አመራረጥ›› በሚል ርዕስ ስር እንደሚከተለው ተብራርቷል ‹የሕዝብ ተወካዮች› ለተሰኘው ጉባኤ ከጀጎል ነዋሪዎች አራት፣ ከጀጎል ውጪ ከሚገኙ የከተማና የገጠር ቀበሌ ገበሬ ማህበራት 18 አባላት ይመረጡበታል፡፡ ለሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤ ደግሞ በክልሉና ከክልሉ ውጪ በሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች ከሚኖሩ የሐረሪ ብሔረሰብ ውስጥ 14 አባላት ይመረጡበታል፡፡ ይሁንና ሕጉ ብዙሃኑን የአካባቢው ነዋሪዎች የፖለቲካ ውክልና ከመንፈጉ በተጨማሪ ከክልሉ ተቋማትም ሆነ መብቶች እንዲገለሉ አድርጓቸዋል፡፡
በተለይም በራሱ በመንግስት መረጃ ሳይቀር በተወላጅነትም ሆነ ቋንቋውን በመናገር ከኦሮሞ ብሔር ቀጥሎ በሁለተኛነት የሚገኙት፣ እንዲሁም አብላጫውን የፖለቲካ ስልጣን ከያዘው ከሐረሪ ብሔረሰብ አባላት ከእጥፍ በላይ ቁጥር እንዳላቸው የተረጋገጠው አማርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች በዞን ደረጃ እንኳ እንዲዋቀሩ አለመደረጉ ‹ፌደራሊዝሙ› ከአፋዊነት አለማለፉን ያመላክታል (በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች በዞን ደረጃ እንዲዋቀሩ የተደረጉ ጥቂት የማይባሉ ብሔሮች እንዳሉ ልብ ይሏል) እንዲህ አይነቱ አደረጃጀት ሌላው ቢቀር እንኳ በዚህ ዘመን ፋሽን ከሆነው ‹‹ውጡ፣ ክልላችሁ አይደለም!›› ከሚለው ነውረኛ ፖለቲካ የመታደግ ጉልበት ሊኖረው የሚችልበት ዕድል ሰፊ ነው፡፡ በርግጥ ይህ ሁናቴ ዛሬም ድረስ መፅናቱ ‹ብሔረሰቡን እወክላለሁ› የሚለው የእነ አዲሱ ለገሰ ብአዴን ከተላላኪነት ያለፈ ሚና እንደሌለው የሚያመላክት ይመስለኛል፡፡
የሆነው ሆኖ የሙግቱ ዋነኛ መግፍኤ የጀጎል ነዋሪ ከሆኑት ውስጥ ከሶስት እጅ ለሚልቁት አራት፣ ለተቀሩት ጥቂት ሐረሪዎች ደግሞ አስራአራት የምክር ቤት ወንበር ከመስጠቱ ጋር ይያያዛል፡፡ በዚህ ሕግ መሰረት በጀጎል የምርጫ ክልል ከአራቱ ወንበሮች ውጪ ሐረሪ ያልሆነ የትኛውም ፓርቲም ሆነ ግለሰብ ለውድድር መቅረብ እንደማይችል በግልፅ ተደንግጓል፡፡ እንዲህ አይነቱ አናሳዎችን በብዙሃኑ ላይ የሚሾም ኢ-ፍትሃዊ የሥልጣን ክፍፍል አብዛኛውን የክልሉ ነዋሪ በገሃድ እየተንፀባረቀ ላለው ባይተዋር አገዛዝ ከማጋለጡም በላይ፣ ከመልካም አስተዳደር ጋር በአዋጅ የተፋታ እስኪመስል ድረስ በሙስናና በአድሎአዊነት ለተተበተበ ስርዓት ዳርጎታል፤ ይህ ሁኔታም በህዝቦች መካከል መከፋፈል እንዲፈጠርና በጥላቻ ምሽግ ውስጥ እንዲያደፍጡ ማስገደዱ አይቀርም፡፡
በጥቅሉ የብዙዎችን መብት ጨፍልቆና አንዱን ነጥሎ ተጠቃሚ የሚያደርግ ስርዓት ማንበር የማታ ማታ ጊዜውን ጠብቆ ከሚፈነዳ አደጋ ጋር ማላተሙና የብሔር ግጭት የመቀስቀስ መዘዝ ማስከተሉን አስቀድሞ ለማወቅ ነብይ መሆን አይጠበቅም፤ የኢህአዴግ ‹‹እኔ ከሌለሁ ኢትዮጵያ ትበታተናለች›› ፉከራም ይህን መሰል ተንኮል ከገመደው የክልል አወቃቀር ቀመር ጋር የተያያዘ ይመስለኛል፡፡ በርግጥ ወደ እንዲህ አይነቱ ድምዳሜ የሚገፋን የሃሳቡ አመንጪዎችም ሆኑ መበታተናችን አይቀሬ እንደሆነ የሚያረዱን ራሳቸው የኢህአዴግ መስራቾች መሆናቸው ነው፡፡ በተቀረ ‹የምንከተለው የፌደራል ስርዓት ቋንቋን መስፈርት ያደረገ ነው› እስከተባለ ድረስ በሐረሪ ያለው አስተዳደር በራሱ በኢህአዴግ አጋፋሪነት በፀደቀው ህገ-መንግስትም ጭምር ተቀባይነት እንደሌለው ከገዥዎቻችን የተሰወረ አለመሆኑ አከራካሪ አይደለም፡፡ በነገራችን ላይ የሐረሪ ብሔራዊ ሊግ ከፈለገ በክልሉ ምክር ቤት ሰላሳ ስድስቱም ወንበሮች ላይ የመወዳደር መብት ተሰጥቶታል፡፡
በግልባጩ ኦህዴድን ጨምሮ በሐረሪ ብሔረሰብ አባላት ያልተመሰረተ ማንኛውም የተቃዋሚ ፓርቲ ከሃያ ሁለቱ ወንበር ውጭ በአስራ አራቱ ላይ እጩ ማቅረብ እንደማይችል በሕግ ታውጇል፤ የስራ ቋንቋንም በተመለከተ በክልሉ ነዋሪዎች ከአማርኛ ቋንቋ በሁለት እጅ ያነሰ ተናጋሪ ያለው ሐረሪ እና በስፋት የሚነገረው ኦሮምኛ ብቻ እንዲሆኑ መደረጉም ራሱ አገዛዙ ከሚያቀነቅንለት የቋንቋ ‹ፌደራሊዝም› ጋር ይጣረሳል፡፡ በርግጥም የስርዓቱ ‹ኤጲስ ቆጶሳት› ደጋግመው ‹ለአስራ ሰባት ዓመታት የታገልነው ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአፍ መፍጫ ቋንቋው እንዲማር፣ እንዲዳኝ፣ እንዲተዳደር… ነው› የሚሉት ሀቲት ማደናገሪያ መሆኑን ለመረዳት ከዚህ የበለጠ ክስተት ሊኖር አይችልም፡፡
በአናቱም የክልሉ ፕሬዝዳንት እና ም/አፈ ጉባዔ ከሐረሪ ብቻ የሚመረጡ ሲሆን፣ ዋናውን አፈ-ጉባዔ ደግሞ በጋራ ሁለቱ ጉባኤዎች እንደሚመርጧቸው በአዋጅ ተደንግጓል፡፡ እንዲሁም በፌደራሉ ህገ-መንግስት ላይ የተካተተውና አጨቃጫቂው ‹‹የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት›› የተሰጠው በተናጠል ለሐረሪ ብሔረሰብ ብቻ ነው፡፡ ይህ አይነቱ ልዩ ችሎታም ሆነ ከላይ የተጠቀሰው ልጓም አልባ ሥልጣን በሌሎች ክልሎች በተመሳሳይ መልኩ ለሚገኙ ብሔሮች አልተሰጠም፤ ለምሳሌ በደቡብ ሲዳማ፣ ስልጤ፣ ጉራጌ…፤ በአማራ ክልልም የአገው ብሔረሰብ ከሐረሪ የበለጠ ቁጥር ቢኖራቸውም በዞን ደረጃ እንዲዋቀሩ ከመፍቀድ ያለፈ ያገኙት ልዩ መብት የለም፡፡
በነገራችን ላይ ሐረሪ እንዲህ ለሀገር አንድነት አስጊ በሆነ መልኩ እንዲደራጅ የተደረገው በተወላጆቹ ፍላጎት እና ጥያቄ ነው የሚል እምነት የለኝም፤ ምክንያቱም የብሔረሰቡ አባላት እንደማንኛውም ዜጋ በኢትዮጵያዊነታቸው የሚያምኑና የሚኮሩ መሆናቸውን ከታሪክ መረዳቱ አያዳግትም፡፡ እናም በግሌ የዚህ ሁሉ መግፍኤ ስልጣኑን ለማስጠበቅ ኤርትራን እና አሰብን የመሰለ የሀገር ጉሮሮ (ወደብ) ኃላፊነት በማይሰማው መልኩ አሳልፎ የሰጠው ኢህአዴግ እንደ መጠባበቂያ አስልቶ ያጠነጠነው የተንኮል ድር ይመስለኛል፡፡ የክልሉ ህገ-መንግስትም ሆን ተብሎ ወደ አንድ ወገን እንዲያጋድል መደረጉ (በአንዳች ክፉ ቀን ሊመዘዝ የሚችል አደገኛ የፖለቲካ አጀንዳ ማቀፉ) ከላይ የጠቀስኳቸውን ማሳያዎች ያስረግጥልናል፡፡
የኃይማኖት መቻቻል…
የሐረሪ ክልል ሌላኛው ችግር የኃይማኖት ልዩነት ያነበረው ውጥረት ለነዋሪው ሕዝብ ተጨማሪ ስጋት መፍጠሩ ነው፡፡ ከዓመታት በፊት በእንግሊዝ ዋና ከተማ ለንደን አልቃይዳ እንዳቀነባበረው የታመነውን የቦንብ አደጋ አድርሷል ተብሎ ተጠርጥሮ ከተያዘ በኋላ ዘግይቶ በነፃ የተለቀቀው ሐምዲ ኢስሐቅ የሐረሪ ተወላጅና የጀጎል ልጅ መሆኑ ክልሉ በማዕከላዊ መንግስቱ በአይነ ቁራኛ እንዲታይ አድርጎት እንደነበረ ይታወሳል፡፡ ሐምዲ በአደጋው ተጠርጥሮ ጣሊያን ሮም ውስጥ በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ለዜናው ከፍተኛ ሽፋን መስጠታቸውን ተከትሎ፣ በወቅቱ አንድ ጊዜ ብቻ ታትማ የጠፋችው ‹‹መዝናኛ›› መፅሔት ባቀረበችው ሰፊ ዘገባ እንዲህ በማለት ማስነበቧ አይዘነጋም፡- ‹‹በሐረር ጥብቅ የእስልምና ሃይማኖት ትምህርት ስር እየሰደደ ነው፡፡ አንዳንድ ሃይማኖተኞች እስከ ፓኪስታንና አፍጋኒስታን በመዝለቅ የእስላማዊ ትምህርትና ትግል ስልጠናን በመቅሰም እንደሚመለሱ ተረድቻለሁ፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት በቁጣና በቁጭት የሚመለከቱት ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡ ‹እውነት ከእኛ መካከል የተፈጠረው ሐምዲ ይህንን ሰርቶ ከሆነ አደንቀዋለሁ› ብሎኛል አንድ ወጣት፡፡››
በ2004 ዓ.ም. አፈንዲ ሙተቂ በተባለ ፀሐፊ ተዘጋጅቶ፣ የቅጂ መብቱን በመጋራት የሐረሪ ባህል፣ ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ ወጪውን በመሸፈን ‹‹ሐረር ጌይ›› በሚል ርዕስ ባሳተመው መጽሐፍ ላይም ሐረር ‹‹እስላማዊ ከተማ ናት›› ተብሎ መገለፁ በራሱ የሚያመለክተው ጉዳይ አለ፤ መቼም ዓለማዊቷን ከተማ ‹እስላማዊት›› እያለ የሚጠራን መጽሐፍ መንግስታዊው ተቋም አሳትሞ ማሰራጨቱ፣ ሃይማኖትና መንግስት የተነጣጠሉ ናቸው ብሎ በአዋጅ ለሚለፍፈው ኢህአዴግ መራሹ ስርዓት ምፀት ይመስለኛል፡፡ በርግጥም ‹‹ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴት ናት›› የሚሉትንም ሆነ፣ ሐረርን እስላማዊ ለማድረግ የሚያሴሩትን እንዲህ አቅፎና ደግፎ ‹በኃይማኖታችን መንግስት ጣልቃ አይግባ› ያሉ መዕምናን ተወካዮችን (መንፈሳዊ መሪዎችን) ሰብስቦ ማሰሩ አገዛዙ የመጨረሻው አፈና ደረጃ ላይ መድረሱን የሚያመላክት ነው፤ የፖለቲካ ተንታኞችም ‹መንግስታዊ ሽብርተኝነት› የሚሉት ይህ አይነቱን ተግባር ነው ብዬ አስባለሁ፡፡
ድሬዳዋ
ሌላኛው የምስራቅ ኢትዮጵያ ውጥንቅጥ የፖለቲካ መገለጫ የድሬዳዋ አስተዳደር ነው፡፡ ኢህአዴግ ወደ ሥልጣን በመጣባቸው የመጀመሪያዎቹ ዓመታትና በቀድሞዎቹ ስርዓታት ድሬ በሀገሪቱ ግንባር ቀደም የንግድ እንቅስቃሴ ከሚደረግባቸው ጥቂት ከተሞች አንዷ እንደነበረች ነዋሪዎቿ ዛሬም ድረስ በትዝታ ያስታውሳሉ፡፡ ለዚህም እንደምክንያት የሚጠቀሰው በዳግማዊ አፄ ምኒሊክ ዘመነ መንግስት ከአዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ እና ጁቡቲ ድረስ ተዘርግቶ የነበረው የባቡር መስመር ነው፡፡ ይሁንና ኢህአዴግ ትግል ላይ በነበረበት ወቅት ከፍተኛ ሕዝባዊ ተቃውሞ ያሰሙበት ከነበሩ የሀገሪቷ ከተሞች ድሬዳዋ አንዷ መሆኗ ቂም እንዲይዝባት ከመግፋቱም በላይ ‹የነፍጠኛ መከማቻ› ተብላ በ‹ጥቁሩ› መዝገብ መስፈሯ ባለፉት ሃያ ሁለት የስልጣን ዓመታት ባለችበት ትረግጥ ዘንድ በማይታየው የስርዓቱ ‹ክፉ እጅ› ለመዳመጥ ዳርጓታል፡፡
የሆነው ሆኖ ድሬ በተጧጧፈ የንግድ ሂደት ደምቃ የምትታይበት ያ የመኸር ዘመኗ እንደ ጉም በንኖ፣ ለአስከፊ ድህነትና ሥራ እጥነት እጅ መስጠቷን ለማስተዋል ከተማዋን ለጥቂት ሰዓታት ብቻ ተዟዙሮ መቃኘቱ በቂ ይመስለኛል፡፡ ርግጥ ነው የኢኮኖሚዋ ዋልታ ከምድር ባቡርና ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪክ (ኮተን) በተጨማሪ ሕጋዊም ባይሆን የኮንትሮባንድ ንግድ እንደነበረ ይታወቃል፡፡ ይሁንና ዛሬ ከሞላ ጎደል ሶስቱም የሥራ ዘርፎች በጥልቅ እንቅልፍ የተወሰዱ መስለዋል (ምንም እንኳ ከታማኝ ምንጭ ባላረጋግጥም ኮንትሮባንዱ ‹ፖለቲካዊ ቡራኬ› ማግኘት በቻሉ የስርዓቱ የጥቅም ተጋሪዎች በድብቅ እንደሚሰራ ይነገራል) ምድር ባቡርን በተመለከተ ግን በህይወት ለመኖሩ ደፍሮ የሚከራክር ይኖራል ተብሎ አይታሰብም፡፡
በርግጥ ለድርጅቱ መፍዘዝ ብሎም መክሰም እንደምክንያት የሚቀርበው ‹ኪሳራ› ቢሆንም ስማቸውን መናገር ያልፈለጉ፣ የተቋሙ የሒሳብ ሠራተኛ የነበሩ አንድ የድሬዳዋ ነዋሪ በዚህ አይስማሙም፤ እንደእርሳቸው አገላለፅ መስሪያ ቤቱ ለኪሳራ የተዳረገው የህወሓት ሰዎች ከጀርባ ባሴሩበት ደባ ነው፤ ‹‹በኤፈርት ስር ከተቋቋሙ ድርጅቶች አንዱ የሆነው የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት ላይ የተሰማራው ‹ትራንስ› ከጅቡቲ የሚጫኑ እንደ የዕርዳታ ስንዴና ማዳበሪያ መሰል ምርቶችን በጨረታ እንዲያሸንፍ ይደረግና በጣም እርካሽ በሆነ ዋጋ ለምደር ባቡር የኮንትራት-ኮንትራት ይሰጠዋል፤ ይህ ሁኔታም እየተደጋገመ ሲሄድ ድርጅቱን ለኪሳራ ዳረገው፤ በዚህ ላይ ማነጅመንቱ በተቋሙ ንብረትና ጥቅም ላይ ሙስና ሲፈፅም፣ የስርዓቱ መሪዎች አይተው እንዳላየ ያልፉ ነበር፤ ሠራተኛ ማህበሩ ሳይቀር በግልፅ ለፀረ-ሙስና ሪፖርት ያቀረበባቸው፣ ነገር ግን በሕግ ያልተጠየቁ የአስተዳደር ኃላፊዎች አሉ›› ሲሉ ገደል አፋፍ ስለቆመው የቀድሞ የድሬ ‹ደም-ስር› ምድር ባቡር በቁጭት ይናገራሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት የድርጅቱ ንብረት በሙሉ በመከላከያ ቴክኖሎጂ (መቴክ) ለሚመራው የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ተላልፎ ተሰጥቷል፡፡ ከሰራተኞቹም አብላጫው ተባርረው አምስት መቶ ለሚሆኑት ኢንዱስትሪው ከጥቅምት 30 ቀን 2003 ዓ.ም ጀምሮ ደሞዝ እየከፋላቸው እንደሚገኝና ከነበሩት 19 ሞተሮች (ባቡር) መካከልም አገልግሎት የሚሰጡት አራት ብቻ እንደሆኑ የድርጅቱ ቅርብ ሰው አረጋግጠውልኛል፡፡ ከአዲስ አበባ-መተሀራ እና ከካሳራት-ኤረር በጠቅላላ 114 ኪ.ሜ. ለሚሸፍን የድልድይ (ሀዲድ) ዕድሳት ይውል ዘንድ የአውሮፓ ህብረት የለገሰውን 60 ሚሊዮን ዩሮንም (ከ1.1 ቢሊዮን ብር በላይ የወሰደው የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ የረባ ስራ ሳይሰራ ‹‹ቄሱም ዝም…›› መሆኑ ብዙዎችን ግራ ከማጋባቱም በላይ በሀገሪቷ ኃላፊነት የሚሰማው መንግስት ያለመኖሩ ማሳያ ነው፡፡
በአናቱም መንግስት ሕገ-ወጡን የኮንትሮባንድ ንግድ በኃይል ሲያስቀር፣ ካለበት ኃላፊነት አኳያ አማራጭ የስራ ዘርፎችን አለመፍጠሩ ለችግሩ መባባስ ዋነኛ ምክንያት ሆኖ ይቀርባል፡፡ በተለይም በከፍተኛ ባለስልጣናት አንደበት ሳይቀር የ‹ደረቅ ወደብ› አገልግሎት መስጫ በድሬዳዋ እንደሚመሰረትና ለአካባቢው ነዋሪ አማራጭ የሥራ ዕድል እንደሚሆን ተደጋግሞ ከተነገረ በኋላ፣ ሃሳብ ተቀይሮ ሞጆ ላይ እንዲመሰረት መደረጉ ከተማዋ ‹አልቦ ተቆርቋሪ› መሆኗን እንደሚያሳይ በአንድ ወቅት የመስተዳደሩ ምክር ቤት አባል የነበሩ ግለሰብ ይናገራሉ፡፡ የግለሰቡ መከራከሪያ ‹‹ድሬዳዋ ለጁቡቲ ካላት ቅርበት አኳያ የከባድ መኪናዎችን ምልልስ ያፈጥነዋል፤ ይህ ደግሞ በወደብ ላይ ለሚከማቹ ጭነቶች የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ ያስቀራል›› የሚል ነው፡፡ በርግጥም ከአዲስ አበባ እምብዛም ከማትርቀው ሞጆ ይልቅ፣ ለእንዲህ አይነቱ አገልግሎት ድሬዳዋ የተሻለች መሆኗን ለመረዳት ጥናትና ምርምር የሚጠይቅ አይመስለኝም፡፡
የድሬ ፖለቲካ…
የድሬዳዋ ነዋሪዎችን በተመለከተ በ1998 ዓ.ም (በፈረንጆች 2007 ዓ.ም) በስታስቲክ ባለስልጣን የተደረገው ቆጠራ እንደሚያሳየው አጠቃላይ የሕዝብ ብዛቷ 341 ሺህ 834 ሲሆን፤ ኦሮሞ 45%፣ ሶማሌ 24.3%፣ አማራ 20.7%፣ ጉራጌ 4.5%፣ ትግራይ 1.2%፣ ሐረሪ 1.01% ቁጥር አላቸው፡፡ በስፋት የሚነገሩ ቋንቋዎች ደግሞ ኦሮምኛ 46.1%፣ አማርኛ 33.2%፣ ሶማሊኛ 13.4%… መሆናቸውን ይዘረዝራል፡፡ ይሁንና ድሬ በተፃፈው ሕግ እንደ ሀገሪቱ መዲና አዲስ አበባ በፌደራል መንግስት ስር መዋቀሯ ቢደነገግም፣ በገሃድ ያለው እውነታ የሚያሳየው (በተለይም ከምርጫ 97 በኋላ) ኦህዴድና ሶሕዴፓ (የሶማሌ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ) ባልተፃፈ ሕግ በሚፈራረቁበት አድሎአዊና ብልሹ መስተዳደር ውላ-ማደሯን ነው፤ በርግጥም ዛሬ በሥልጣን ላይ ካለው የኦህዴዱ አሳድ ዚያድ በፊት፣ የከንቲባነትና የምክትሉን ወንበር አንድ የምርጫ ዘመንን ዕኩል በመክፈል ሁለቱ ድርጅቶች በየሁለት ዓመት ተመንፈቁ ሲቀያየሩበት መቆየታቸው የሚያመላክተው ዓብይ ጉዳይ ፌደራሊዝሙ በሕይወት ለመኖሩ በ‹ሳይንስ›ም ቢሆን ሊረጋገጥ አለመቻሉን ነው፡፡
በድሬዳዋ የሚታየው ሌላኛው ‹ፌደራሊዝማዊ› ፌዝ፣ ከነዋሪው ሕዝብ ቁጥር ኦሮምኛ ተናጋሪው 46.1% ሆኖ ሳለ የሥራ ቋንቋ አማርኛ መሆኑ ነው፤ ማንነትን በ‹ቋንቋ› የሚወስነው ኢህአዴግ ድሬዳዋ ላይ ተመሳሳይ መንገድ አለመከተሉ (…መቀነቱ ማደናቀፉ) በኦሮሞ ተወላጆች ላይ የሚደረገውን ተቋማዊ ጫና የሚያመላክት ይመስለኛል፡፡ መቼም ሌላው ቢቀር እንኳ ቢያንስ ራሱ የቀረፀው ‹ፌደራሊዝም› ሁለቱንም የሥራ ቋንቋ ማድረግ የሚቻልበት በቂ መፍትሄ እንደማያጣ ግልፅ ነው፡፡ ይህ ኩነት ኦህዴድም ልክ እንደ ብአዴን ከተላላኪነትና ቱርጁማንነት ያለፈ የፖለቲካ ቁመና የለውም ወደሚል ጠርዝ ይገፋል (በነገራችን ላይ የአጀንዳው ተጠየቅ በዚህ መልኩ የቀረበው ከራሱ ከኢህአዴግ ርዕዮተ-ዓለም አንፃር እውነታውን ለመፈተሽ ሲባል ነው እንጂ በግሌ የብሔር ፖለቲካ ለኢትዮጵያችን ይበጃታል ብዬ ስለማምን አይደለም)
እንደ መውጫ
ቋንቋ ተኮር ፌደራሊዝሙ ኢህአዴግ ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ እንደ አዲስ ሀገር ማዋቀሪያ አማርጭ ፖሊሲ ተደርጎ ሲጠነሰስ የፌደራሊዝሙ ቅርፅ አገሪቱን ይበታትናል ከሚለው ድምፅ ባላነሰ፣ ደርዝ ያለው ሙግት ሆኖ ቀርቦ የነበረው በሀገሪቱ የረዥም ጊዜ የሕዝብ ለሕዝብ ፖለቲካዊ ግንኙነት በአንድ ቋንቋ ብቻ የሚወሰን ማህበረሰባዊ ቡድን (ብሔር) ካለመገኘቱ ባለፈ፣ ያንን የተወሰነ ቋንቋ የሚናገረው ስብስብ በአንድ በተወሰነ መልክዐ-ምድራዊ ቅፅር ውስጥ አይገኝም የሚል ነበር፡፡ ይህንን ክርክር ከዚህ ፅሁፍ አውድ አንፃር ተጨባጭ የሚያደርገው የጠቀስኳቸው ሁለቱ የምስራቅ ኢትዮጵያ አካባቢዎች ናቸው፡፡ በሁለቱም ክልል ውስጥ ከኦሮሞ እስከ ትግሬ፣ ከአማራ እስከ ሶማሌ… ከጠንካራ ኢኮኖሚያዊ አደረጃጀትና የየራስ ወጥ መለዮ ጋር መገኘታቸው መልክዐ-ምድራዊውን የፌደራሊዝም ቅርፅ ትክክለኛ አማራጭነት ለማስረገጥ በቂ ማሳያዎች ይመስሉኛል፡፡
ከዚህ ባሻገር የኢህአዴግ ‹ፌደራሊዝም› እንኳን ድርጅቱ ሥልጣን ላይ ባለበት ወቅት ቀርቶ፣ በሕዝባዊ ማዕበል በሚወድቅበት ጊዜም ቢሆን በአንድ ጀንበር መቀየር እንደማይቻል ቢታወቅም ሂደታዊ የእርምት አካሄድ ብቸኛው ፖለቲካዊ ትክክለኝነት ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ይህ ፌደራሊዝም የብሔር ግጭትን ከመከላከል በላይ ተራምዶ፣ ሰሞኑን እንዲያ ‹አሸሼ-ገዳሜ› የሚባልለትን በሕዝቦች መካከል አንድነት ሊያጠብቅ ቀርቶ በአግባቡ ባለመተግበሩ (ለምሳሌ በሐረሪና ድሬዳዋ የሚገኙ፣ ነገር ግን በክልሎቹ ስልጣን ውስጥ ያልተወከሉ ብሄሮች) የተፈጠሩት ኩነቶች ወደሰዓት ቦንብነት እየተቀየሩ የመጡትን የተለያዩ ቋንቋ ተናገሪዎች የእርስ በእርስ ትንቅንቆች መግራት ከማይችልበት ደረጃ ላይ እየደረሰ ነው፡፡ ይህ ኩነት “ደግሞ የእዚህች አገር ህልውናን ለመፈታተን ጥቂት ጊዜያቶችን ብቻ መጠበቅ የማይቀር ዕጣ ፈንታ ያደረገው ይመስለኛል፡፡

Thursday, 5 December 2013

ከኢትዮጵያ እሳት ወደ ሳውዲ አረቢያ እረመጥ፣ ከድጡ ወደ ማጡ ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም ትርጉም ከነጻነት ለሀገሬ



What “foreign minister” Adhanom said and did not even know he said it
Tedros Adhanom, the malaria researcher-turned-instant-foreign-minster


ባለፉት አስርት ዓመታት በመቶሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን/ት ዜጎች በአገራቸው ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አህጉር በተለየ መልኩ ተንሰራፍቶ እየተፈጸመ ካለው ጭካኔና ርህራሄ የጎደለው አምባገነናዊ ስርዓት ለማምለጥ ሲሉ እግራቸው ወዳመራቸው አገር በመሰደድ ላይ ይገኛሉ፡፡

የኢትዮጵያ “ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር” እንደዘገበው ከሆነ እ.ኤ.አ በ2012 በግምት 200,000 ኢትዮጵያውያት ሴቶች በውጭ አገር በአብዛኛውም በመካከለኛው ምስራቅ አገሮች የውጭ የስራ ዕድል ለመፈለግ ተገደዋል፡፡ ከእነዚህ ኢትዮጵያውያት ሰራተኞች አብዛኞቹ በኢትዮጵያ ተንሰራፍቶ ከሚገኘው አምባገነናዊ የእሳት ነበልባል አመለጥኩ የሚል እምነት ነበራቸው፣ ሆኖም ግን ወደ ሳውዲ አረቢያው የእሳት እረመጥ ተወርውረው እራሳቸውን አገኙት፡፡


በኢትዮጵያውያን ስደተኛ ሰራተኞችና በሌሎች በሳውዲ አረቢያ ጥገኝነት በጠየቁ ዜጎች ላይ ገደብ የለሽ አደን እየተካሄደ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ በዚህ ወር በየዕለቱ በሚባል መልኩ የሳውዲ አረቢያ ፖሊሶች፣ የደህንነት ኃላፊዎች፣ ወሮበሎች እና ህገወጦች ኢትዮጵያውያንን/ትን ሁሉ በየመንገዱ እያደኑ ይደበድባሉ፣ ያሰቃያሉ፣ አንዳንድ ጊዜም ይገድላሉ፡፡ የሳውዲ አረቢያ ፖሊሶች ኢትዮጵያውያን/ት ዜጎችን ሲደበድቡ የሚያሳየውን የዩቱቤ የቪዲዮ ምስል መመልከት ለህሊና የሚሰቀጥጥ ነገር ነው፡፡ የሳውዲ አረቢያ ወሮበሎችና ህገወጦች ኢትዮጵያውያን/ት ዜጎችን በየመንገዶች ሲያሳድዱ፣ ሲያጠቁና ሲገድሉ የሚያሳየው የቪዲዮ ምስል ለኩነቶቹ እውንነት ምንም ዓይነት ማብራሪያ አላስፈለገውም፡፡ በአሁኑ ጊዜ የሳውዲ አረቢያ ወሮበሎችና ጋጠወጦች በኢዮጵያውያን/ት ዜጎች ላይ እየፈጸሙት ያለው በቪዲዮ ማስረጃነት ተደግፎ የቀረበው የሰብአዊነት መብት ረገጣ ወንጀል በጣም የሚዘገንንና በሰለጠነ የሰው ልጅ ህሊና ሊታሰብ የማይችል ነገር ነው፡፡


ኢትዮጵያና ሳውዲ አረቢያ፡ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች፣


ኢትዮጵያና ሳውዲ አረቢያ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው፡፡ የሳውዲ አረቢያና የኢትዮጵያ ገዥዎች ከአንድ ጥለት የተቆረጡ ናቸው፡፡ የሳውዲ አረቢያ መንግስት በሰብአዊ መብት አያያዝ መዝገቡ በመጥፎ ተምሳሌነቱ ይታወቃል:: በተመሳሳይ መልኩ የኢትዮጵያ መንግስት በሰብአዊ መብት አያያዝ እንደ ሳውዲ አረቢያ ሁሉ ያስጠይፋል፡፡ የሳውዲ አረቢያው ገዥ ኢትዮጵያውያን/ት ዜጎችን በጣም ሰብአዊነት በጎደለው መንገድ ከግዛቱ በኃይል እንዲጋዙ/እንዲባረሩ የሚያደርግ መርህን ተከትሏል፡፡ በኢትዮጵያ ያለው ገዥ መደብም በተመሳሳይ መልኩ በሀገሩ ግዛት ውስጥ ኢትዮጵያውያንን/ትን ከሚኖሩበት ቀያቸው በግዳጅ ወደሌላ አካባቢ በማጋዝ አስደንጋጭ የሆነ የሀገር ውስጥ የማጋዝ (ሰፈራ) መርህን ተከትሏል፡፡ የሳውዲ ገዥ አናሳ የእምነት ተከታዮችን አሰቃይቷል፣ የኢትዮጵያ ገዥ መደብም እንደዚሁ አድርጓል፡፡ በሳውዲ ያለው ገዥ መደብ ዜጎችን በስፋት በዘፈቀደ በቁጥጥር ስር ያውላል፣ በእስር ቤት ያጉራል፣ ያሰቃያል፣ እንዲሁም በህግ ከለላ ጥላ ስር በሚገኙት ዜጎች ላይ ህገወጥ የእስር ቤት አያያዝን ያራምዳል፡፡ የኢትዮጵያ ገዥ መደብም በተመሳሳይ መልኩ የሳውዲ ገዥ የሚፈጽማቸውን የአፈና ድርጊቶች ሙሉ በሙሉ ይፈጽማል፡፡ የሳውዲ ገዥ የባሪያ ንግድን እ.ኤ.አ በ1962 በአዋጅ ካስቆመ በኋላ “ከፋላ” “kafala” (ተያዥ ያላቸው ስደተኛ ሰራተኞች፣ ሆኖም ግን በባሪያ ንግድ የአሰራር ሁኔታ የሚሰሩ) የሚል ቅጥያ በመስጠት ብዝበዛውን ቀጥሎበታል፡፡ እ.ኤ.አ በ2009 የባህሬን የሰራተኛ ሚኒስትር ማጅድ አል አላዊ ሲናገር ከፋላ የሚለውን የማደናገሪያ ቅጥያ ከባሪያ ንግድ ጋር አመሳስሎታል፡፡ እ.ኤ.አ የ2013 ዓለም አቀፍ የባርነት አመላካች አሀዝ/Index እንዳመለከተው 651,000 የሚሆኑ በባርነት ተይዘው ህይወትን በመግፋት ላይ የሚገኙ የኢትዮጵያ ዜጎች ሲኖሩ ከእነዚህም የዓለምን ሶስት አራተኛ ከሚይዙት ከመጀመሪያዎቹ አስር አገሮች ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗን በግልጽ አስቀምጧል፡፡


ሂዩማን ራይትስ ዎች/Human Rights Watch እ.ኤ.አ በ2013 ባቀረበው ዓለም አቀፋዊ ዘገባው የኢትዮጵያንና የሳውዲ አረቢያን የሰብአዊ መብት አያያዝ ሬከርድ በሚመሳሰል መልኩ እንደሚከተለው አቅርቦታል፤


በ2012… የኢትዮጵያ ባለስልጣኖች ሀሳብን በነጻ የመግለጽ፣ የመደራጀትና የመሰብሰብ መሰረታዊ መብቶችን መገደብን በስፋት ቀጥለውበታል፡፡ ሂዩማን ራይትስ ዎች ዘገባውን በመቀጠል በአዲስ አበባ ማዕከላዊ እየተባለ በሚጠራው የፌዴራል ፖሊስ የምርመራ ማዕከል ፣ እንዲሁም በሶማሊ፣ በኦሮሚያ እና በጋምቤላ ክልሎች እስር ቤቶችና በወታደራዊ ማዕከሎች የሚፈጸሙትን የማሰቃየት ድርጊቶች ዝርዝር ዘገባ አቅርቧል፡፡


የሙስሊሙን ህብረተሰብ አመጽ ተከትሎ በኦሮሚያና የአገሪቱ መናገሻ በሆነችው በአዲስ አበባ ከተማ አመጹን ለመግታት በሚል ሰበብ የደህንነት ኃይሎች ሰላማዊ ሰዎችን ከህግ አግባብ ውጭ በቁጥጥር ስር በማዋል፣ እስራትና ድብደባዎችን ፈጽመዋል፡፡ የፌዴራል ፖሊስ ድብደባን ጨምሮ በአገሪቱ ከፍተኛ የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ላይ መንግስት ጣልቃ መግባቱን እንዲያቆም የሚጠይቀውን የሙስሊሙን ህብረተሰብ ሰላማዊ ተቃውሞ ለመግታት ሲል መንግስት ከልክ ያለፈ ኃይልን ተጠቅሟል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት መሰረታዊ አገልግሎቶችን ለህብረተሰቡ ለማድረስ በሚል ሰበብ የመንደር ማሰባሰብ ተግባሩን እውን ለማድረግ በአምስት የአገሪቱ ክልሎች 1.5 ሚሊዮን የገጠር ሰፋሪዎችን የማሰባሰብ ስራ ቀጥሏል፡፡ በጋምቤላ ክልል ብዙ ሰፋሪዎች ከሚኖሩበት ቀዬ በኃይል ተፈናቅለው ብዙ መከራ ደርሶባቸዋል… በመንግስት ጥረት የሚከናወን የሸንኮራ አገዳ ልማትን ለማፋጠን ሲባል በኢትዮጵያ የታችኛው ኦሞ ሸለቆ የሚኖሩትን ኗሪ የፓስቶራል ህዝቦች መንግስት በኃይል አፈናቅሏል:: በደቡብ ኦሞ ዞን ወደ 200 ሺ የሚሆኑ የአካባቢው ኗሪ ህዝቦች መሬታቸውን ለሸንኮራ አገዳ ልማት ይፈለጋል በሚል ሰበብ መንግስት መሬታቸውን በመንጠቅ ወደ ሌላ ቦታ እንዲሰደዱ አድርጓል፡፡


ሳውዲ አረቢያን በሚመለከት ሂዩማን ራይትስ ዎች የሚከተለውን ዘገባ አቅርቧል፣


እ.ኤ.አ በ2012 ከህግ አግባብ ውጭ የሚከናወኑትን እስራቶችና ሰላማዊ ተቃዋሚዎችን የማዋከቡ ሁኔታ እየጨመረ በመምጣቱ ዜጎች ሰላማዊ ሰልፍ በማድረጋቸው ምክንያት የሳውዲ አረቢያ መንግስት የኃይል እርምጃን ተጠቅሟል… እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ፍትሀዊ ያልሆነ ፍርድን ተቀብለዋል፣ ወይም ደግሞ ከህግ አግባብ ውጭ ለእስራት ተዳርገዋል… እስረኞች ህጻናትን ጨምሮ ስልታዊ የህግ የበላይነት ጥሰት እና ፍትሃዊ ህግ የማግኘት መብት የመነፈግ፣ ከህግ አግባብ ውጭ እስራትና ማሰቃየት እንዲሁም ህገወጥ የእስር ቤት አያያዝ ደባ ይፈጸምባቸዋል… ባለስልጣኖች የ9 ሚሊዮን የውጭ ሰራተኞችንና የ9 ሚሊዮን የሳውዲ ሴቶችና ልጃገረዶች መብት ማስከበር አልቻሉም ወይም ጭቆናውን ቀጥለውበታል…
ወደ 1.5 ሚሊዮን የሚሆኑ የአገር ውስጥ ስደተኛ ሰራተኞች ከ2005 የሰራተኞች ህግ ውጭ ተደርገዋል… ባለፉት ዓመታት የኤሲያ ኤምባሲዎች ዘገባ እንደሚያመለክተው ከሀገር ውስጥ ሰራተኞች ቅሬታ እንደሚያሳየው በቀን ከ15 እስከ 20 ሰዓታት፣ በሳምንት ደግሞ 7 ቀናት እንዲሰሩ ከመገደዳቸውም በላይ ደመወዛቸውን ያለመክፈል ሁኔታም ተንጸባርቋል፡፡ የሀገር ውስጥ ሰራተኞች በአብዛኛውም ሴቶች በተደጋጋሚ ጊዜ ተገደው እንዲወልዱ ይደረጋል፣ ምግብ የማግኘት መብታቸውን ያጣሉ፣ እንዲሁም የጾታ ትንኮሳ፣ የአካልና የስነልቦና ጫናዎች ይደረጉባቸዋል፡፡
ሳውዲ አረቢያ ከእስልምና አስተህምሮ ውጭ የሌሎችን እምነቶች አስተምህሮዎችን ለመቀበል ትዕግስቱ የላትም፡፡ ባለፈው መጋቢት ወር ልዩ ልብስ ለባሹ ሸክ በአረቢያ ፔንሱላ የሚገኙ ማናቸውም ቤተክርስቲያኖች በሙሉ እንዲወድሙ ጥሪ አስተላልፎ ነበር…


“የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር” ቴዎድሮስ አድሃኖም ምን እንዳሉና ያሉትንም እንዳላወቁ፣
በኢትዮጵያ ያለው ገዥው አካል በሳውዲ አረቢያ በሚገኙ ኢትዮጵያውያን/ት ላይ በአሁኑ ጊዜ እየደረሰ ያለውን አስፈሪ ሁኔታ በማስመልከት የሚሰጠው ምላሽ ጭንቅላትን ይበጠብጣል፡፡ የወባ ትንኝ ተመራማሪውና ከመቅጽበት ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት የተቀየሩት ቴዎድሮስ አድሃኖም እንዲሁም እ.ኤ.አ ከ2015 ሀገራዊ ምርጫ በኋላ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ቦታ ይረከባሉ ተብለው የሚጠበቁት ባለስልጣን ስለሳውዲ አረቢያው የኢትዮጵያውያን/ት ሁኔታ አስመልክቶ በኖቬምበር አጋማሽ በአዲስ አበባ ላይ በተካሄደው በ3ኛው ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ዕቅድ ምጣኔ ጉባኤ ላይ ሲናገሩ ግራ ተጋብተዋል፣ እዚህና እዚያ የሚዋዥቅ ንግግርም አሰምተዋል፡፡ ቅንነት የጎደለው እርግጠኝነትና በባዶ ተስፋ የተሞሉ ቃልኪዳኖችን አነብንበዋል፡፡ ወገኖቻችን ወደ ትውልድ አገራቸው እንዲመጡ በደስታ ለመቀበልና ዓለም ቀፋዊ ተብብርን ማጠናከር አስፈላጊ እንደሆነ በየኋህነት/ሞኝነት አገላለጽ አስቀምጠውታል፡፡

እንደምታውቁት፣ ከሳውዲ አረቢያ እንደምታውቁት ኢትዮጵያውያንን ብቻ ቢያግዙም/ቢያባርሩም ቅሉ ሌሎችን ዜጎችም እንዳባረሩ እንረዳለን… ባለፉት አስርት ቀናት እንዳየሁትም፣ ምክንያቱም በቤተሰብ ምጣኔ ዕቅድ እንደምንለው ለልጃገረዶችና ለሴቶች ክብካቤ እናደርጋለን፣ ከጣቢያዎች እርዳታ በመፈለግ ከሚጮሁ ሴቶች በቀጥታ ጥሪዎች ደርሰውኛል… በመቶዎቸ የሚቆጠሩትን በእርግጠኝነት ተቀብለናል፣ በሺዎችና በአስር ሺዎች የሚቆጠሩትን እንቀበላለን ብለን እንጠብቃለን፣ በእርግጠኝነት ለመናገር የምፈልገው ዜጎቻችንን ወደ አገራቸው እንዲመጡ ለመቀበል ሙሉ በሙሉ ዝግጁ ነን፡፡


በጣም አዝኛለሁ፣ ስሜቴም ተጎድቷል፡፡ ለዚህም ነው ይህ ሁኔታ ከተጀመረ ወዲህ ባለው የጊዜ መደበላለቅ ምክንያት ወደዚህ ላለመምጣት ዶ/ር ተከስተን ጠይቄ የነበረው፡፡ ሆኖም ግን በዓለምአቀፋዊነት ትብብር መሰረት ህገወጦችን ማባረር/ከአገር ማስወጣት የምንችል ቢሆንም ይህንን ጉዳይ በሰከነና በሰለጠነ መልክ እናደርገዋለን፣ ምክንያቱም ይህ ድርጊት የጦርነት ሁኔታ አይደለምና፡፡ እንደዚህ ያለው ሁኔታ ተቀባይነት ሊኖረው የሚችለው አገሮች በጦርነት ላይ ሲሆኑ ብቻ ነው፣ ህዝብም በፈጠነ መልኩ ነገሩን ሊረዳው ይችላል፣ ነገር ግን በሰላማዊ ሁኔታ ሊሆን አይችልም፡፡


…በመሆኑም በዚህ መልክ በመጀመሬ አዝናለሁ፣ ይህ ሁኔታ እስከ አሁን ድረስ እየቆጠቆጠኝ የቆየ ጉዳይ ስለሆነ ነው፡፡
በእርግጥ በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ የአጭርና የረዥም ጊዜ መፍትሄ በማስቀመጥ ችግሮቹን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመፍታት ጥረት ስናደርግ ቆይተናል፣ ምክንያቱም ችግሮቹ ስር የሰደዱና ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መወገድ ያለባቸው በመሆናቸው ነው፡፡ እንደምታውቁት ኢትዮጵያ እያደገችና ባለሁለት አሀዝ የኢኮኖሚ እድገት ምጣኔ እያስመዘገበች ነው፣ በዚህም አካሄድ ከጨለማው ዋሻ የውስጥ ጉዞ በኋላ ከጫፍ ላይ ብርሀን ይታየኛል፣ እና ይህንን ያለጥርጥር ተግባራዊ እናደርገዋለን፣ በዚህም ጥረታችን ድህነትን ተረት እናደርጋለን፡፡ በትክክለኛው መንገድ ላይ ነን፣ ሆኖም ግን ዓለም አቀፋዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ እምነቴ የጸና ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ይሳካል ብለን አንጠብቅም፡፡


ነገሩን ለማታውቁት አንድ ነገር ላካፍላችሁ እፈልጋለሁ፡፡ ነብዩ መሀመድ ታላቁን የእስልምና እምነት አስተምህሮቱን ሀ ብሎ ሲጀምር በደረሰበት መሳደድ ምክንያት ደቀመዝሙሮቹን/ተከታዮቹን ወደ ኢትዮጵያ ነበር የላከው… ስለዚህ አዝናለሁ፣ ንግግሬንም እዚህ ላይ አቆማለሁ…ሆኖም ግን የሚሰማኝን ስሜት ሁሉ በዝርዝር በመግለጼ፣ ያለፉት 10 ቀናት በህይወቴ ካየኋቸው ነገሮች ሁሉ እንዴት መራር እንደነበሩና ይከሰታሉ ብለን የማንጠብቃቸው አስገራሚ ነገሮች እየሆኑ በማየቴ እዚህ በመካከላችሁ በመገኘት ለእናንተ ሀሳቤን በማካፈሌ ደስታ ይሰማኛል…::


በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያውያን/ት ዜጎች ላይ በሳውዲ አረቢያ መንግስት አየተፈጸመ ያለውን አስደንጋጭ የሰብአዊ መብት ረገጣ ወንጀል በማስመልከት የኢትዮጵያ “ቁንጮ የዲፕሎማት ሰው” እንደዚህ ያለ ተያያዥነት የሌለው፣ የተበታተነ፣ ዝብርቅርቅ ያለ እና እጅ እግር የሌለው ትንታኔ እና ገለጻ ሲያቀርቡ ስሰማ እጅጉን ነው ያዘንኩት፡፡ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከወባ ትንኝ ተመራማሪነትና ከመቅጽበት ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት በተቀየሩ ግለሰብ የአፍ ካራቴ ዥዋዥዌ ልምምድ መቀለጃ ሆነ! ማንም ሊያደርገው እንደሚችለው የአድሃኖምን ቅጥ አምባሩ የጠፋ ንግግር መሰረት በማድረግ የሚከተሉትን ጭብጦች መመርመር ተገቢ ይሆናል፡፡


1. አድሃኖም እንዲህ አሉ “…በቃላት ሊገለጽ በማይችል መልኩ በኢትዮጵያውያን/ት ዜጎች ላይ የሳውዲ አረቢያ መንግስት ያደረሰውን ሰቆቃ ሲያስታውሱ “እስከ አሁን ድረስ ነገሩ እየቆጠቆጣቸው“ እና አሁንም ድረስ “እንዳዘኑ“ እና የሳውዲ አረቢያ መንግስት በኢትዮጵያውያት ሴቶች ላይ በሚፈጽመው ደባ ምክንያት ሰብአዊ መብታቸው እየተረገጠ ያሉ ሴቶች እገዛ ለማግኘት በሚያሰሙት ጩኸት “ስሜታቸው እንደተጎዳ“ ተናግረዋል፡፡ ይኸ “ታላቁ የዘመኑ ውሸት!“ ሊባል ይችላል፡፡


ምናልባትም አድሃኖም በእንግሊዝኛ ቃላት መካከል ያለውን ጥቃቅን ልዩነት ማስተዋል ባለመቻላቸው በተለይም ቀጥተኛ ያልሆነውን የአነጋገር ዘየ/colloquialism ተከትለው ይሆናል በማለት አስተያየት መስጠት ይቻል ይሆናል፡፡ ሆኖም ግን እንደ ቁንጮ የዲፕሎማት ሰውነታቸው ለአላዋቂነት የቃላት አጠቃቀሞቻቸው ይቅርታ ሊደረግላቸው አይገባም (በእርግጥ የቃላት እና የሀረጎች አመራረጣቸው አመለካከታቸውንና ስሜታቸውን የሚገልጹ ቢሆንም)፡፡ በኢትዮጵያውያን/ት ላይ በሳውዲ አረቢያ መንግስት እየተደረገ ያለው ግፍ “እስከ አሁን ድረስ ነገሩ እየቆጠቆጣቸው“ እንደሆነ የሚገልጸው አባባል ተጎጂ ኢትዮጵያውያን/ት በሳውዲ አረቢያ ያሉበት ሁኔታ የንዴት ምንጭ እንደሆናቸውና ጥቂት እንዳሳሰባቸውም ጠቋሚ ነው፡፡ ይህ ትልቅ ጉዳይ አይደለም እንደማለት አነጋገር ነው ፡፡ በዓለም ላይ የየትኛውም አገር የዲፕሎማሲ ቁንጮ የሆነ ሰው በዜጎቹ ላይ ኢሰብአዊና ኃላፊነት የጎደለው አያያዝ መደረጉን አስመልከቶ “እስከ አሁን ድረስ ነገሩ እየቆጠቆጠው” መሆኑን ለሌላ አገር ሰው ሲናገር አልተሰማም፣ አልታየምም፡፡


አድሃኖም በውል ያላጤኑት ቢሆንም ቃላት በዓለም አቀፍ የዲፖሎማሲው ቋንቋ ትልቅ ትርጉም አላቸው፣ ቃላት የዲፕሎማቶች ዓላማ ማስፈጸሚያ መሰረታዊ ሀብቶች ናቸው፡፡ የዲፕሎማቲክ ሰዎች እነርሱ በመረጧቸው ቃላትና የቃላት አጠቃቀም ዓለም እንዲቆምና እንዲሄድ የማድረግ ወይም አንዳንድ ጊዜም ሆን ብለው ለትርጉም ልቅ የሆኑ ወይም ደግሞ ውሱን የሆኑ ቃላትን በመጠቀም ዓላማቸውን ለማሳካት የሚሄዱበት ዘዴ ነው፡፡ የዲፕሎማቶች ቃላት ግልጽና ድብቅ ትርጉም ባላቸው መልዕክቶች የተሽሞነሞኑ እና ድብቅ ዓላማን ለማሳካት የተዘየዱ ማስፈጸሚያ መሳሪያዎች ናቸው፡፡ በሰዋስዋዊው የቃላት አመሰራረትና በሚሰጡት ትርጉም ጥንቁቅነት በዲፕሎማሲው ቋንቋ ቃላት ሰላምን ያሰፍናሉ፣ ጦርነትን ያውጃሉ፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የዲፕሎማቶች ቃላት የዲፕሎማቶችን ግላዊ የሀዘን ስሜትና የስሜታቸውን መጎዳት ብቻ የሚገልጹ ሳይሆን ከዚህ በተጨማሪ የዲፕሎማቶቹን የሞራል ስብእና፣ የስቅይቱን ጥልቀትና የሀገራቸውን ህዝቦች ስሜት ሊያንጸባርቅ ይገባል፡፡


አድሃኖም በሳውዲ አረቢያ ያሉ ኢትዮጵያውያን/ት ዜጎች ሁኔታ “እስከ አሁን ድረስ ነገሩ እየቆጠቆጣቸው“ እንደሆነ ሲገልጹ ለሳውዲ አረቢያ መንግስት አደገኛ የሆነ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ሊገነዘቡ ይገባል፡፡ እንዲህም ብለው እየነገሯቸው ነው፣ አዲሱ የይስሙላው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ የዓለም አቀፉን የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ለማውገዝ በአፍሪካ ህብረት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ተገኝተው የተናገሩትን በመዋስ “የዘር አደን“ በኢትዮጵያውያን/ት ስደተኛ ሰራተኛ ዜጎች ላይ በሳውዲ አረቢያ ፖሊሶችና ጋጠወጦች በየመንገዱ እየተደረገ ያለውን ሁከትና ትርምስ አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡ ተገቢ የዲፕሎማሲ ንግግር ከተደረገ ይህንን አደገኛ ሁኔታ እንዲቀንስ ያደርገዋል፡፡


በአሁኑ ወቅት በሳውዲ አረቢያ እየተካሄደ ያለው ኢትዮጵያውያንን/ትን የማዋረድና ኢሰብአዊ የሆነ ድርጊት የመፈጸም ሁኔታ ትልቅና በጣም ትልቅ የሆነ አገራዊ ጉዳይ ነው፡፡ በግሌ ለምሳሌ በዋና የስራ ሰዓት ጊዜ የሚይዝ የትራፊክ መኪና መጨናነቅ የንዴት ደረጃየን ከፍ ያደርገዋል፣ የተሰጣቸውን የቤት ስራ ሳይሰሩ በሚመጡ ተማሪዎቼ ላይ የሚኖረኝ ንዴት ከልኩ ያለፈ ነው:: ሳውዲዎች በኢትዮጵያውያን/ት ላይ እየፈጸሙት ያለው ግፍ ግን እንድናደድ ብቻ አላደረገኝም፣ ደሜ እንዲፈላ ጭምር አደረገኝ እንጅ፡፡ የሳውዲ አረቢያ ፖሊሶች በኢትዮጵየውያን/ት ላይ ሲፈጽሙት የነበረውን አረመኒያዊና ኢሰብአዊ የሆነ ድርጊት ስመለከት እሳት ነበልባል ሆኛለሁ፡፡ የሳውዲ አረቢያ ወሮበሎችና ጋጠወጦች በኢትዮጵያውያን/ት ዜጎች ላይ ሲፈጽሙት የነበረውን አረመኒያዊና ጭካኔ የተሞላበት የሰብአዊ መብት ረገጣ ስመለከት በንዴት ድብን ብዬ አራሴን አስከ መሳት ደርሼ ነበር፡፡ በኢትዮጵያውያን/ት ስደተኛ ሰራተኞች ላይ በሳውዲ አረቢያ ወሮብሎችና ጋጠወጦች እየተደረገ ያለውን ኢሰብአዊና ከህግ አግባብ ውጭ እየተደረገ ያለውን ጀብደኝነት የሳውዲ ገዥው አካል እያየ ጆሮዳባ ማለቱ የበለጠ እንድበሳጭና እራሴን እንድስት አድርጎኛል፡፡ የሳውዲ መንግስት ዓለም አቀፍ ሕግን በጠበቀ መልኩ በኢትዮጵያውያን ስደተኛ ሰራተኛ ዜጎች መብት አያያዝ ላይ ምንም ነገር ባለማድረጉ በጣም ተበሳጭቻለሁ፣ አማርሪያለሁም፡፡ ኢትዮጵያውያን/ት በሳውዲ አረቢያ እየተፈጸመባቸው ያለው ግፍና መከራ አድሃኖምን ብዙም ያሳሰባቸውና ያስጨነቃቸው አይመስልም፡፡


በዓለም አቀፋዊ የዲፕሎማሲ ቋንቋ መርህ መሰረት ጠንካራና ፊትለፊት በመግጠም የሚደረግ እና አስታራቂና ዲፕሎማሲያዊ በሆነ ለስለስ ባለ ቋንቋ ለመጠቀም የራሱ ጊዜ አለው፡፡ በእውነቱ ይህ ታላቅ ሀገራዊ ውድቀት ነው፣ አድሃኖም በሁለቱ መካከል ያለውን ልዩነት በውል የተገነዘቡት አይመስለኝም፡፡


2. ሳውዲ አረቢያዎች በኢትዮጵያውያን/ት ላይ እንዲህ በፈጣን መልኩ እየፈጸሙ ያሉት ከአገር የማባረርና የማስወጣት ሁኔታ “አንድ አገር በጦርነት በወደቀችበት ጊዜ የተደረገ ቢሆን ኖር ተቀባይነት ሊኖረው ህዝብም ሊረዳው ይችል ነበር” ብለዋል አድሃኖም፡፡ ከዚህ አንጻር አድሃኖም ያልተገነዘቧቸው በርካታ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች፣ በጣም መሰረታዊ የሆኑ መርሆዎችና ህጎች መኖራቸውን ያሳያል፡፡ ከጦርነት ጋር በተያያዘ መልኩ ዜጎችን ከሀገር የማባረሩ ሁኔታን አስመልክቶ ያሉትን ህጎችና ልምዶች አንዳንድ ጊዜም የዘር ማጽዳት ድርጊቶች እንደሚፈጸሙ አድሃኖም የተገነዘቡ አለመሆኑን ይህ ሁኔታ በግልጽ ያመላክታል፡፡ እ.ኤ.አ 1990ዎቹ የመጀመሪያዎቹ ዓመታት ገደማ በሄርዞጎቪና እና ቦሲኒያ መካከል በተደረገው ጦርነት በርካታ የቦሲኒያ እስልምና እምነት ተከታዮች፣ ክሮሽያዎች፣ ሰርቦችና ቦሲኒያዎች ከትውልድ ቦታቸው የተቀነባበረ የማባረር/የማስወጣት ስልት በመጠቀም ተግባራዊ ተደርጎባቸዋል፡፡ ያ የጦር ወንጀለኝነት ነው፡፡ ይኸ እንዲሁ “ህዝብ በቀላሉ ሊረዳው የሚችል” ጉዳይ አይደለም አድሃኖም አንዳሉት፡፡ በጦርነት ጊዜ በኃይልና በማስገድደ ከአገር የማስወጣት አስፈላጊነት ለህዝቡ ደህንነት ሲባል በሚጠበቁ ሰዎች ወይም በጦር መሪዎች ላይ የሚፈጸም መሆኑን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት በ1949 የጸደቀው ስምምነት (IV) በጦርነት ጊዜ የሲቪል ሰዎችን ለመከላከል የተዘጋጀው ሰነድ በግልጽ ያሳያል፡፡ የስደተኞችን ጉዳይ አስመልክቶ በ1951 ስምምነት መሰረት በ1967 የስደተኞችን ሁኔታ አስመልክቶ የተዘጋጀው ፕሮቶከል እንዲሁም በአንቀጽ 3 በ1984 ማሰቃየትን በተመለከተ የተዘጋጀውን ስምምነት መሰረት በማድረግ ኢትዮጵያውያን/ት ስደተኞች ከማንኛውም ህገወጥ ማባረር/ማስወጣት ድርጊት መጠበቅ እንዳለባቸው በግልጽ ያሳያሉ፡፡ በጣም መሰረታዊ በሚባሉ የዓለም አቀፍ ህጎች፣ ደንቦችና መርሆዎች አንጻር አድሃኖም ያላቸው ግንዛቤ ሲመዘን በጣም አናሳ ሆኖ መገኘቱን ስናጤን እንደ ሀገር አሳሳቢ ሀገራዊ ኪሳራ መሆኑን ያሳያል፡፡


3. በአሁኑ ጊዜ በሳውዲ አረቢያ በሚገኙ ኢትዮጵያውያን/ት ላይ ለሚፈጸመው ሰቆቃና አንገብጋቢ ችግር መፍትሄው ዜጎቹ ከዚያ ሀገር የሚወጡበትን ስራ ማፋጠን እንደሆነ አድሃኖም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በሳውዲ አረቢያ በኢትዮጵያውያን/ት ስደተኞች ላይ የሚፈጸመውን የኃይል እርምጃ፣ አስገድዶ መድፈር፣ ግድያና ማሰቃየት ማስቆም ጊዜ የማይሰጠው አጣዳፊ፣ ወሳኝ፣ አንገብጋቢ እና ክብደት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ በእርግጥ አድሃኖም ይህንን ጉዳይ በሚመለከት እንደሚከተለው አስረግጠው ተናግረዋል፡፡ “በእርግጥ ችግሩን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመፍታት የረዥምና የአጭር ጊዜ መፍትሄዎችን በመንደፍ ጥረት ስናደርግ ቆይተናል፣ ምክንያቱም እነዚህ ችግሮች ለብዙ ጊዜ የቆዩና ስር የሰደዱ በመሆናቸው ነው“ በማለት አስተያየታቸውን ቋጭተዋል፡፡ እርግጥ ነው የረዥምና የአጭር ጊዜ መፍትሄዎች ሊቆዩ ወይም ጊዜ ሊወስዱ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን በሳውዲ አረቢያ ፖሊሶች፣ ወሮበሎች እና ህገወጦች በየዕለቱ እየተፈጸሙ ያሉ የውርደት ሰራዎች፣ ህገወጥ አያያዞች፣ ፍትህአልባነት እና ወንጀሎች በእንዲህ ያለ ሁኔታ ሊቆዩ በፍፁም አይችሉም፡፡ በአሁኑ ጊዜ በሳውዲ አረቢያ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን/ት ላይ እየተፈጸመ ያለው መጠነሰፊ ኪሳራ ነው፡፡ ስቅይቱን በፍጥነት ለማስቆም አድሃኖም ምንም ዓይነት ሀሳብ የሌላቸው እና መፍትሄዎችን ያላመላከቱ በመሆኑ ይህ አንገብጋቢ አገራዊ ኪሳራ ነው፡፡


አድሃኖም እንዲህ ይላሉ፣ በሳውዲ አረቢያ በሚኖሩ ትዮጵያውያን/ት ስደተኞች ላይ “እንዲህ ያለ ድርጊት ይፈጸማል ብለን በምንም ታምር አልጠበቅንም“፣ እንዲህም ይላሉ ለእራሳቸው፣ “ሁሉም ነገር የሚያስደንቅ ነው“፣ በመቀጠልም እንዲህ ይላሉ፣ “የረዥምና የአጭር ጊዜ መፍትሄዎችን ለማምጣት ለብዙ ጊዜ ጥረት አድርገናል“፡፡ ይህ የተምታታ እና የተዘበራረቀ አባባል እርስ በእራሱ የሚጣረስ ብቻ አይደለም፣ ሊታመን በማይችል መልኩ አሳሳች መግለጫ እና የአድሃኖምን የዋህነትና የዲፕሎማሲ እውቀት እጥረትና ችሎታ ማጣት የሚያሳይ መገለጫ እንጅ፣ በሳውዲ አረቢያ የኢትዮያውያንን/ትን ሁኔታ በሚመለከት “ሁሉም ነገር የሚያስደንቅ ነው“ የሚለው የአድሃኖም አባባል ተቀባይነት የሌለው ነገር ነው፡፡ ምክንያቱም እ.ኤ.አ በኤፕሪል 2013 አድሃኖምና የእርሳቸው ገዥው አካል የሳውዲ አረቢያ ገዥ በሀገሩ ውስጥ በህገወጥ መንገድ ገብተው ምንም ዓይነት ህጋዊ ሰነድ ሳይኖራቸው በሀገሩ የግዛት ክልል ውስጥ የሚገኙ የውጭ አገር ሰራተኞችን ህጋዊ ለማድረግ ወይም ደግሞ ወደየመጡባቸው አገሮች እንዲመለሱ እና ህገወጥ ማባረር፣ እስራትና ስቅይትን ለማስቀረት በማለት ያስተላለፈውን ትዕዛዝ በሚገባ ያውቃሉ፡፡ የአድሃኖም ገዥው አካልም በተመሳሳይ መልኩ በሳውዲ አረቢያ ውስጥ ምንም ዓይነት ህጋዊነት ሳይኖራቸው የሚሰሩና የሚኖሩ በርካታ ህገወጥ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን/ት እንዳሉ ከማመናቸውም በላይ አሳምረው ያውቃሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የሳውዲ ገዥ እ.ኤ.አ በጁላይ 2013 በሀገሩ ውስጥ የሚገኙትን ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ሳይኖራቸውና ምንም ሰነድ የሌላቸውን የውጭ አገር ዜጎች በማስመልከት ህጋዊ እንዲሆኑ ወይም ሀገር ለቀው እንዲወጡ አጽንኦ በመስጠት እ.ኤ.አ እስከ ኖቬምበር 2013 ድረስ ቀነ ገደብ መስጠቱን አድሃኖምና ገዥው አካላቸው በሚገባ ያውቁታል፡፡ ግና የአድሃኖም ገዥ አካል ከመስማት ባለፈ የአዋጁን እንደምታና ወደፊት በስደተኛ ዜጎቹ ላይ ሊያስከትል የሚችለውን በአዎንታዊም ሆነ በአሉታዊ ጉኑ ሊያየው ስላልፈለገ የወደፊቱን ማቀድም አልቻለም፣ በቀጣይነት በገፍ ወደ ሳውዲ አረቢያ በሚጓዙ ዜጎች ላይ እንዲሁም በሳውዲ አረቢያ ፖሊስና ወሮበሎች በቀጣይነት ስለሚደረገው ጥቃት የሚሉት ነገር አልነበራቸውም፡፡ በአጭሩ ምንም ነገር ሳያደርጉ እጃቸውን አጣጥፈው በመቀመጥ ሲመለከቱ በከንቱ ሳይጠቀሙበት ጊዚያቸውን አባክነዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ እ.ኤ.አ በኖቬምበር 2013 በሳውዲ አረቢያ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን/ት ስደተኛ ዜጎች ላይ ማህበራዊ ቀውስ ይደርሳል የሚለውን ሁኔታ እንዴት አድሃኖም በእርግጠኝነት መተንበይ አልቻሉም ይቻላል?

አድሃኖም ፈጣን የፖሊሲ እርምጃ ለመውሰድ ብቃት የሌላቸው ሰው መሆናቸውን የድርጊቶች ኩነት በተጨባጭ ያሳያል፡፡ እንደ “ቁንጮ የዲፕሎማሲ ሰው” ብዙ መማር ይጠበቅባቸዋል፣ እንዲሁም ወደፊት ሊከሰቱ በሚችሉ ነገሮች ላይ ትኩረት በመስጠት የነገሮችን የአመጣጥ ሁኔታና ችግሮችን አስቀድሞ በማየት ተጨባጭ መፍትሄ ለማምጣትና ወደተግባር ለመፈጸም የሚያስችል ብቃትን ሊጎናጸፉ ይገባል፡፡ ፈላስፋው ጎቴ የሚከተለውን ሲል እውነትም ትክክል ነበር፣ “ምንም ድንቁርናን በተግባር ከማየት የበለጠ አስደንጋጭ ነገር የለም ብሏል።
አድሃኖም ያልተናገሩት ወይም ያላደረጉት፤


በሳውዲ አረቢያ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን/ት ዜጎች ላይ እየተፈጸመ ያለውን የኃይል እርምጃ ለማስቆም የኢትዮጵያ ገዥው አካል ስላደረገው ሁኔታ አድሃኖም አንድም ያሉት ነገር የለም፣ ሆኖም ግን አገዛዙ ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ ዘለቄታዊ መፍትሄ ለመስጠት የረዥም እና የአጭር ጊዜ መፍትሄዎችን ለማምጣት ብዙ ርቀት የተጓዘ መሆኑን ከመግለጽ ውጭ ተጨባጭነት ያለው እርምጃ አልታየም፡፡ በተጨባጭ እየሆነ ያለው ግን አድሃኖም እና ገዥው አካላቸው አትዮጵያውያን/ት ስደተኛ ዜጎቻቸው በሳውዲ አረቢያ መንገዶች እንደ አውሬ እየታደኑ ኢሰብአዊ ድርጊት ሲፈጸምባቸው ከዳር ቆመው ጣቶቻቸውን በመቀሰር፣ ጭንቅላቶቻቸውን በመነቅነቅ ከመታዘብ ውጭ ሌላ መገለጫ የለውም፡፡ አድሃኖም በዜጎቻችን ላይ እየተፈጸመ ያለውን የኃይል እርምጃ ለማስቆም ምንም ጥረት አለማድረጋቸው ብቻ ሳይሆን ትንሿን ነገር ለዓም አቀፉ ማህብረሰብ በማሳወቅ በሳወዲ አረቢያ መንግስት ላይ ጫና እንዲደረግ እንኳን ሙከራ አላደረጉም፡፡ አድሃኖም ካልተናገሯቸው ወይም ካልፈጸሟቸው ጉዳዮች ውስጥ ከብዙ በጥቂቱ እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡


በጠንካራ ቃላት የተዘጋጀ የውግዘት መግለጫ፤ አድሃኖም እንዲህ ብለዋል፣ “ገዥው አካል የሳውዲ አረቢያ መንግስት በግዛት ክልሉ ውስጥ ባሉ ስደተኛ ሰራተኛ ዜጎቻችን ላይ ያደረሰውን ጭካኔ የተሞላበት የኃይል እርምጃ እናወግዛለን፣ ይህ በምንም ዓይነት መልኩ ተቀባይነት የለውም፣ የሳውዲ መንግስት ለጉዳዩ አጽንኦ በመስጠት ምርመራ እንዲደረግ ጥሪ እናደርጋለን፣ ዜጎቻችን ባሉበት በክብርና በመልካም ሁኔታ እንዲያዙ ሆኖ ዜጎቻችንን ወደ ሀገራቸው የምንወስድ መሆኑን እናሳውቃለን“ የሚል ነበር፡፡ “ተቀባይነት የለውም“ የሚለው ቋንቋ በሳውዲ አረቢያ ገዥ አካል፣ በፖሊስ ኃይሉ እና በወሮበሎች እየተፈጸመ ያለውን ዘገናኝ ጭካኔ፣ ለመናገር የሚዘገንን አረመኔነት፣ አስደንጋጭ ስቅይትና ወንጀለኝነት ለመግለጽ የሚጠቀሙበት የውግዘት ቃል ነው፡፡ እንደ አድሃኖም ግንዛቤ “ምርመራ“ ማለት የሳውዲ ገዥ ክፍል ከዚህ ከተፈጸመው ዘግናኝ ወንጀል አንጻር ጠንካራ እርምጃ ተወስዶ ማየት ነው፡፡


አድሃኖም “ተቀባይነት የለውም“ የሚለውን ቋንቋ በውል የተገነዘቡት አይመስልም፡፡ ይህ አባባል በዲፕሎማሲያዊ ቋንቋ የዲፕሎማሲ ሰዎች ምንም ነገር ሳይሉ አንድ ነገር እንዳሉ በማስመሰል የሚጠቀሙበት ባዶና መሰረት የለሽ ቃል ነው፡፡ ሁሉንም ነገር የሚል ትርጉም የያዘ ቃልም ነው…”ምንም ዓይነት ጠንቅ የለዉም አይኖረዉም ማለትም ነው”:: እንደዚህ ነው እንግዲህ የዲፕሎማሲያዊ ቋንቋ ባህሪያት፡፡ አንድ መስመር ዓረፍተ ነገር ሁለት የማይገናኙ ዓላማዎችን ሊያስተላልፍ የሚችል መልዕክት ሊኖረው ይችላል፡፡ በሳውዲ አረቢያ በሚኖሩ አትዮጵያውያን/ት ላይ እየተፈጸመ ያለው ድርጊት “ተቀባይነት የለውም” የሚል መልዕክት ለሳውዲ አረቢያ አምባሳደር በማስተላለፍ አድሃኖም በጉዳዩ ላይ የይስሙላ ስራን በመስራት ጉዳዩ አስኪረጋጋ ድረስ መጠቀሚያ ያደርጉታል፣ ከዚያ በኋላ ግን ሁሉቱም ወገኖች ወደነበሩበት ግንኙነት ተመልሰው የመሞዳሞ ስራቸውን ይቀጥላሉ፡፡ ቃሉን በትክክል ለመግለጽ “ተቀባይነት የለውም” የሚለው ቃል ብልህነት የጎዳላቸው ፉከራና ባዶ ኳኳታ በሚያሰሙ ምንም ነገር እና አንድም ነገር የማያደርጉ ሰዎች መገለጫ ነው፡፡


የጥገኛውን ሀገር አምባሳደር በመክሰስ የብጥብጡን ሁኔታ እንዲረዳና በፖሊስና በህገወጦች የሚፈጸመውን ህገወጥ ድርጊት በአስቸኳይ እንዲያስቆም ማድረግ፡ አድሃኖም የሳውዲ አረቢያ አምባሳደርን በመክሰስ እንዲህ ብለዋቸዋል፣ “የሳውዲ አረቢያ መንግስት ህገወጥ ስደተኞችን ለማስወጣት የተከተለውን መርህና የሳውዲ አረቢያ ባለስልጣኖች በህገወጥ ስደተኞች ላይ የወሰዷቸውን እርምጃዎች በተመለከተ ኢትዮጵያ ታላቅ አክብሮት አላት፡፡ እንዲሁም በሳውዲ አረቢያ በሚኖሩ ዜጎቻችን ላይ የተወሰደውን ህገወጥ አያያዝና ግድያ ታወግዛለች“ ይላል፡፡ ግን ሰው ምን ዓይነት አሽከርነትና ጫማ ላሽነት ውሰጥ ይዘፈቃል?! ለዜጎቹ የሚቆረቆር በምድር ላይ የሚኖር ማንም አገር ቢሆን የራሱን ዜጎች የስቃይ ሰለባ ላደረገ ሌላ አገር በምንም ዓይነት መልኩ ቢሆን “ክብር አለው” የሚል ቃል አይተነፍስም፡፡ አድሃኖም በጉዳዩ ላይ ጥልቅ ግንዛቤ ያላቸው አይመስልም፣ ምክንቱም ጉዳዩ ስለሳውዲ አረቢያ የግዛት ሉዓላዊነት ወይም ስለስደተኞች ፖሊሲ ጉዳይ አይደለም፣ ጉዳዩ የሳውዲ አረቢያ ገዥ አካል በኢትዮጵያውያን/ት ስደተኛ ሰራተኛ ዜጎች ላይ እየፈጸመ ስላለው የሰብአዊ መብት ረገጣ ተገቢውን እርምጃ የመውሰድና ያለመውሰድ ጉዳይ ነው፡፡


ከዚህም በላይ አደሃኖምም ሆነ ወይም ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው ከሳውዲ አረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር የሚኖርን ተቃውሞ በይፋ ለህዝብ አላሳወቁም፡፡ “የተቃውሞ ደብዳቤ” ወይም “የዲፕሎማቲክ ማስታወሻ” የአንድ መንግስት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለሌላው ጥፋት ለፈጸመው መንግስት ይቅርታ የማይደረግለትን የማይናወጥ አቋም በመግለጽ በይፋ ያሳውቃል፡፡ የተቃውሞ ደብዳቤው በምንም ዓይነት መልኩ ቢሆን “ተቀባይነት የለውም” የሚል ቃል አይጠቀምም፡፡ በጥቂቱም ቢሆን ስለ “”አሳሳቢ ጉዳዮች” እና ነገሮች መሻሻል ካላሳዩ ወደፊት “ጉዳት ሊያመጡ” የሚችሉ ጉዳዮችን በመጥቀስ ሊያሳውቅ ይችላል፡፡ አድሃኖም እንዳደረጉት እንቁጠረውና የተቃውሞ ደብዳቤ ለሳውዲ አረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የጻፉ መሆኑን ለህዝብ ይፋ ሊያደርጉ ይገባል፡፡


በሳውዲ አረቢያ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን/ት ዜጎች ላይ የተፈጸመውን የሰብአዊ መብት ረገጣ በሚመለከት የአፍሪካ ህብረት የውግዘት መግለጫ እንዲያወጣ ማድረግ፤ እ.ኤ.አ በ2015 አስከሚደረገው አገር አቀፍ ምርጫ ድረስ የአድሃኖምን ወንበር እያሟሟቁ የሚገኙት የይስሙላው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያ ደሳለኝ የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት የዝውውር ሊቀመንበር ናቸው፡፡ ኃይለማርያም ደሳለኝ የተባበሩት መንግስታት የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በአፍሪካ መሪዎች ላይ የዘር አደን ይፈጽማል በማለት የዘር አደናውን ለማስቆም የአፍሪካ መሪዎችን በማሰባሰብና በማስተባበር ቆላ ደጋ በማለት ጥረት ሲያደርጉ የቆዩ እና እንዲያውም የህብረቱ አባል አገራት የሮማ ስምምነተን በመጣስ ከአይሲሲ አባልነት እንዲወጡ በመሃንዲስነት ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸወ የሚታወስ ነው፡፡ ነገር ግን በመቶዎችና በሺዎች የሚቆጠሩ የአገራቸው ዜጎች በሳውዲ አረቢያ መንገዶች በፖሊሶች፣ በወሮበሎችና በህገወጦች “የዘር አደና” ጥቃት ሲፈጸምባቸው ትንፍሽ አላሉም፣ የጎመንዘር ቅንጣት የምታክል ድርጊት አልፈጸሙም፡፡(በነገራችን ላይ ይህ ሁሉ ስቃይ በኢትዮጵያውያን/ት ዜጎች ላይ ሲፈጸም የይስሙላው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በአገር ውስጥ ነበሩን? ኢትዮጵያውያን በሳውዲ አረቢያ “የዘር አደን” እየተፈጸመባቸው መሆኑን አስመልክቶ ቃል ትንፍሽ ሲሉ የሰማ ይኖራልን?)


አስቸኳይ ምርመር እንዲካሄድ ለተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን (UNHCR) ኮሚሽነር ማሳወቅ፣ ዩኤንኤችሲአር/UNHCR በተባበሩት መንግስታት በተሰጠው ኃላፊነት መሰረት “ዓለም አቀፍ የስደተኞችን ጥበቃ ማድረግና በስደተኞች ችግር ላይ ውሳኔ የመስጠት እንዲሁም ስደተኞችን የመምራትና የማስተባበር ስራ” ያከናውናል፡፡ ስደተኞች አግባብ ባልሆነ መልክ ሲያዙና የሰብአዊ መብት ጥሰት ካለ የመመርመር ስልጣን ተሰጥቶታል፡፡ አድሃኖም UNHCR ጉዳዩን እንዲመረምረው መጠየቃቸውን የገለጹበት ሁኔታ የለም፡፡ ምናልባትም ጥያቄ አቅርበው ከሆነ መጠየቃቸውን የሚገልጽ መረጃ አልቀረበም፡፡


እንዲህም ሆኖ UNHCR ስደተኛ ሰራተኞችን ግጭት ከተከሰተበት ቦታ ወደ ሌላ ለማዘዋወር የሎጅሰቲክስ እርዳታ ብቃት አለው፡፡ ለምሳሌ ያህል እ.ኤ.አ በ2011 በሊቢያ ጸረ መንግስት አመጽ በተቀሰቀሰ ጊዜ UNHCR በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኛ ሰራተኞችን ከሊቢያ ወደ ጎረቤት አገሮች በማመላለስ የተቀላጠፈ ስራ ሰርቷል፡፡


ጉዳዩ በተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን ኮሚሽነር/UNHCR እና በተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ጽ/ቤት/OHCHR ቀርቦ እንዲጣራ ቅሬታን ማስመዝገብ፤ ከOHCHR ዋና ዋና ተግባራት መካከል “የከፋ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ማጣራት” እና “የሰብአዊ መብት ጥበቃ ስራዎችን ማከናወን” ናቸው፡፡ የማጣራት ስራውን እንዲሰራ የሳውዲ ገዥ አካልን ከመጠየቅ ይልቅ አድሃኖም እንዲያጣሩትና ጣልቃ እንዲገቡ UNHCR እና OHCHRን መጠየቅ ነበረባቸው፡፡


የኢትዮጵያ ዜጎች ከሳውዲ አረቢያ ኤምባሲ ፊት ለፊት ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ እንዲያደርጉ መፍቀድ፤ ኢትዮጵያውያን/ት በሳውዲ አረቢያ በሚኖሩ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ላይ በተፈጸሙባቸው እና እየተፈጸሙባቸው ባሉት የሰብአዊ መብት ረገጣዎች ምክንያት ተዋርደዋል፣ ሀፍረትም ደርሶባቸዋል፡፡ አድሃኖም በኢትዮጵያ ጥገኝነት እንዲጠይቁ ነብዩ መሀመድ ተከታዮቹን ወደ ኢትዮጵያ ልኮ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያ በአንድ ወቅት ጥገኘነት የሚጠየቅባት ምቾትና እርዳታ የሚደረግባት ቅዱስ ቦታ ነበረች፡፡ ኒልሰን ማንዴላና ሌሎች የአፍሪካ ናሽናል ኮንግረስ ፓርቲ አመራሮች እ.ኤ.አ በ1962 ስልጠና ለመውሰድ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ነበር፡፡ በአጼ ኃይለ ስላሴ ልዩ ትዕዛዝ መሰረት ኒልሰን ማንዴላ የኢትዮጵያ ፓስፖርት እንዲሰጣቸው ተደርጎ ያለምንም ችግር ዓለምን ሲዞሩ ነበር፡፡ በአንድ ወቅት ኢትዮጵያውያን/ት በዓለም ላይ የሚከበሩና የሚሞገሱ ነበሩ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ደካሞችና በባርነት የሚገዙ ሆነዋል፡፡ ያሰቡትን በመናገራቸው ይደበደባሉ፣ ይታሰራሉ፡፡ አዲስ አበባ በሚገኘው የሳውዲ አረቢያ አምባሳደር ፊት ለፊት በመገኘት ተቃውሟቸውን በሰላማዊ መንገድ ለማሰማት ሲሞክሩ የሳውዲ አረቢያ ፖሊስ በሀገሩ ኢትዮጵያውያንን/ትን ባስተናገደበት መጥፎ አያያዝ ሞዴልነት በተመሳሳይ መልኩም በአዲስ አበባ እንዲደረግ ሆኗል፡፡ ተዋርደዋል፣ ርህራሄ በጎደለው መልኩ ተደብድበዋል፣ በቁጥጥር ስርም ውለዋል፡፡ የገዥው አካል አፈቀላጤ የሆነው ሽመልስ ከማል ገዥው አካል በሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፈኞች ላይ እርምጃ መውሰድ ይገባዋል ብሏል፣ ምክንያቱም ይላል፣ “አብዛኞቹ ሰላማዊ ሰልፍ አድራጊዎች በኢትዮጵያና በሳውዲ አረቢያ መካከል ጸንቶ የቆየውን ጠንካራ ግንኙነት የሚያበላሽና ጸረ አረብ የሆኑ መልዕክቶችን የያዙ በመሀናቸው ነው::


“ማንም ቢሆን ከሚቀርበው ጓደኛው ጋር የመስታወት ላይ ጠብ ያደርጋል የሚል ግምት የለኝም፡፡ አድሃኖምና ገዥው አካል እንዲያስታውሱት የምፈልገው ነገር…”ለመበሳጨት ዘገምተኛ የሆነውን እሱን ተጠንቀቁ፣ ለመምጣት ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ፣ ከመጣ ደግሞ ኃይለኛው እርሱ እንደሆነ እና ለብዙ ጊዜ የሚቆይ ነው፡፡ የተዋረደ ትዕግስተኝነት ወደ ቁጣ ይቀየራል::”


የአጣዳፊ ሁኔታውን ለመስራት ልዩ ግብረ ኃይል አያስፈልግምን? ኢትዮጵያ በሳውዲ አረቢያው እንደደረሰባት ዓይነት ኪሳራ በሚደርስባት ጊዜ ለዜጎቹ የሚያስብ ገዥ አካል ተገቢውን ምላሽ ለመስጠትና ለማስተባበር የአስቸኳይ ጊዜ ማስፈጸሚያ ግብረ ኃይል ያቋቁማል፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ቡድኖች ተመላሽ ስደተኛ ወገናቸውን ለማገዝ እንቅስቃሴ ያደርጋሉ፡፡ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች እገዛ እንዲያደርጉ ይጠየቃሉ፡፡ አነዚህ አልተደረጉም:: በሳውዲ አረቢያ ያለው የኢትዮጵያውያን/ት ሁኔታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያልፋል፣ ስለዚህም ብዙ ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለሳውዲ አረቢያ ኢንቨስተሮች በመስጠት የተለመደው ቢዝነስ በተለመደው ሁኔታ ይቀጥላል የሚል ስሌት በአድሃኖምና በገዥው አካል አቅዋም የተያዘ መሆኑም ይገልጣል፡፡


አድሃኖም ወደፊት አንደሚሉ ፤
አድሃኖምና ገዥው አካል ከሳውዲ አረቢያ ወደ ሀገራቸው ለሚመለሱትና ለሚቋቋሙበት የተመደበውን 50 ሚሊዮን ብር ተመድቧል ብለዋል:: ይህ ከባልዲ ውኃ አንዷ ጠብታ ናት፡፡ ይህም ገንዘብ ወደ 2 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ይሆናል፡፡ በዚህች በጣም ትንሽ በሆነች 2 ሚሊዮን ዶላር 200 ሺ ወይም ከዚያ በላይ የሚሆኑ ከስደት ተመላሾችን ለማስፈር፣ ለማዘዋወርና ለማጓጓዝ የሚያስችል አይደለም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ገዥው አካል ይህን ያህል ገንዘብ ለእነዚህ ተግባራት ተብሎ የተያዘ ለመሆኑ ማረጋገጫ የለም፡፡ እ.ኤ.አ ጁላይ 2013 የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት ባለሙያዎች ተልዕኮ መግለጫ መሰረት ኢትዮጵያ ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ ለምታስገባቸው ሸቀጦችና አገልግሎቶች ለሶስት ወራት ብቻ ሊያቆይ የሚያስችል የውጭ ምንዛሬ ክምችት እንዳላት ይፋ አድርጓል፡፡
አድሃኖምና ገዥው አካል ብዙም ሳይቆዩ ተመላሽ ዜጎቸን ለማጓጓዝና ለማቋቋም የልመና ኮሮጃቸዉን አንጠልጥለው ወደ ዓለም አቀፉ የመንገድ ልመና መውጣቸው የማይቀር ጉዳይ ነው፡፡ በእርግጥ የሚገኘውን እርዳታ ለመቀራመት የሚችሉ የራሳቸውን አትራፊ ያልሆኑ ድርጅቶችን አስቀድመው ያቋቁማሉ፡፡ አድሃኖም ይለምናሉ፣ እንዲህ በማለት፣ “ከሳውዲ አረቢያ ለሚመለሱ ስደተኛ ዜጎች ገንዘብ በጣም ብዙ ገንዘብ እንፈልጋለን፡፡“ ጋሻጃግሪዎቻቸው በህዳሴው ግድብ ወይም በሌላ መልክ እንደሚጠሩት እንዳደረጉት ሁሉ በዓለም ዙሪያ በመሰማራት ኑስ ሳንቲም ሳይቀር ልመናቸውን ያጧጡፋሉ፡፡ ለገዥው አካል መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጀቶች ይህ ሁኔታ ንፋስ አመጣሽ ዘረፋ ነው፡፡ በልመናው በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር እንደሚገኝ በመገመት እነዚህ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እጃቸውን በማሻሸት እና ለሀጫቸዉን በማንጠባጠብ ሰፍ ብለው ይጠባበቃሉ፡፡ ግን በልመና ብዙ ዕርዳታ ላያገኙ ይችላሉ፡፡ ለዚህም ነው በሳውዲ አረቢያ መንገዶች ላይ እጃቸውን በመዘርጋት ምጽዋት፣ ቢለምኑ አልደነቅም ያልኩት፡፡


ለኢትዮያችን አለቅሳለሁ፣ ለውዲቷ አገሬ! ግን “ከዋሻው መጨረሻ ብርሃን አለ“
አድሃኖም እንዲህ አሉ፣ “ከዋሻው መጨረሻ ብርሃን አለ፣ እና ይህን እውን እንደምናደርገው እናውቃለን፣ እና ድህነትን ተረት እንደምናደርገው ጥርጥር የለንም”፡፡ እኔ ደግሞ እላለሁ በኢትዮጵያ ምድር ውስጥ ከዘውዳዊነትና ከአምባገነንነት ዋሻ መጨረሻ ብርሃን አለ፡፡ ከአድማስ ባሻገር አዲስ ቀን አለ፡፡ መደጋገፍ አለብን፣ እጅ ለእጅ ተያይዘን ሁለት አስርት ዓመታት እና ከዚያ በላይ ከዘለቀው የጭቆና እና የመሰረታዊ የሰብአዊ መብቶች እጦት ዋሻ ውስጥ ተጉዘን በድል አድራጊነት መውጣት አለብን፡፡


በሳውዲ አረቢያ ያሉ ኢትዮጵያውያን/ት ያሉበትን አስከፊ ሁኔታ አስመልክቶ የተዘጋጁትን የእኔን ትንታኔዎች ያነበበ ሁሉ እኔ በጣም ህግ አጥባቂና ሲበዛ ትንታኔ ሰጭ እንደሆንኩ ሊናገር ይችላል፡፡ እንዲያውም ታላቁን የሰው ልጅ ሰቆቃ “ለመፈላሰፊያ ትምህርታዊ ክህሎት” አውሎታል ብለው ሊከሱኝ ይችላሉ፡፡ ይህን ሊሉ ይችላሉ ምክንያቱም ለዚህች ተወዳጅ አገሬ ምን ያህል እንዳለቀስኩና ምን ያህል ተስፋ እንደቆረጥኩ ስለማያውቁ ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ1948 በዚሁ ዓመት አፓርታይድ በአፍሪካ ህግ ሆነ፣ አላን ፓቶን እንዲህ ሲል ጻፈ…”ውዷ ሀገሬ አልቅሽ“… እና በደቡብ አፍሪካ ዕጣ ፈንታ ላይ ያለውን የታሟጠጠ ተስፋ ገለጸ፡፡ የእኔም በኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ ላይ ያለኝ ተስፋ ፓቶን ካለው ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ፓቶን ሲጽፍ፣
ለተገነጣጠለው ጎሳ፣ ለወደቀው ባህልና ህግ አልቅስ! አዎ! ለሞተው ሰውዬ ድምጽህን ከፍ በማድረግ አልቅስ፣ ፍቅሩን ላጣችው ሴትና ለልጆቹ አልቅስ፡፡ ለውድ ሀገርህ አልቅስ፣ እነዚህ ነገሮች በእራሳቸው የመጨረሻ አይደሉም፡፡ ፀሐይ በመሬት ላይ ብርሀኗን ትፈነጥቃለች፣ በተወዳጁ መሬት ሰው ባልተደሰተበት ላይ፡፡ የልቡን ፍርሃት ብቻ ያውቃል፡፡


አኔም በኢትዮጵያ “ለተበጣጠሰው ጎሳ” አለቅሳለሁ፡፡ ከሰውነት በታች ሆነው በሳውዲ አረቢያ ለሚሰቃዩት ወንድሞቸና እህቶቸ በዝምታ አለቅሳለሁ፡፡ በመካከለኛው ምስራቅ ለሚደፈሩት፣ ለሚደበደቡት እና በመስኮት ለሚወረወሩት፣ ከጣራ እና ከዛፍ ላይ ተሰቅለው ለሚሞቱትና በፈላ ውኃ ሰውነታቸውን ለሚጠበሱት እህቶቸ አለቅሳለሁ፡፡ በሳውዲ ሌባ ጭንቅላቱን ለሚበረቅሰው ወጣት አለቅሳለሁ፡፡ ነጻነት በማጣታቸው እና በሀገራቸው መብት እንደሌላቸው በመቆጠራቸው ምክንያት ሀገር ጥለው ለመሰደድ ለሚገደዱት ወጣት ወንዶች እና ሴቶች አለቅሳለሁ፡፡ ህይወታቸውን ለማሻሻል በማሰብ የየመንንና የሳውዲ አረቢያን በረሀዎች ሲያቋርጡ በሞት ለተለዩ ኢትዮጵያውያን አለቅሳለሁ፡፡ በየዕለቱ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሲኦሉ ሳውዲ አረቢያ ለሚበሩ ወጣት ኢትዮጵያውያት ቆነጃጅት አለቅሳለሁ፡፡
የ2005 ሀገራዊ ምርጫን ተከትሎ በኢትዮጵያ በየጎዳናው በግፍ ለተገደሉት ወጣት ወንዶችና ሴቶች፣ እንዲሁም አባቶች እና እናቶች አለቅሳለሁ፡፡ ለእህቴ ለርዕዮት ዓለሙ እና ለወንድሞች ለእስክንድር ነጋ፣ አንዷለም አራጌ፣ ውብሸት ታዬ፣ በቀለ ገርባ፣ አቡበከር አህመድ፣ እና በብዙ ሺዎች ለሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞች አለቅሳለሁ፡፡ መሪ በመምሰል በባዶ ልብስ ለተጀቦኑትና በሙሰኛ ሌቦች መዳፍ ስር ለወደቁት ኢትዮጵያውያን/ት አለቅሳለሁ፡፡


አዎ አለቅሳለሁ እናም አለቅሳለሁ፣ “ልቅሶዎቸ ያልተሳኩ ቢሆንም“ ለውዲቷ አገራችን አለቅሳለሁ፣ ግን እኮ ጩኸታችን ይሰማል፣ ደቡብ አፍሪካ ከአፓርታይድ የአምባገነንነት ዋሻ ወጥቷል፣ ኒልሰን ማንዴላም ቃል ገብተዋል…”በፍጹም በፍጹም እና በፍጹም ይህች የተዋበች መሬት ተመልሳ የአንዱ በአንዱ ላይ መጨቆኛ አትሆንም፣ ክብር የታጣባት የተዋረደች ዓለም አትሆንም“::
ኢትዮጵያውያን/ት እንደገና ክብራቸውን ይቀዳጃሉ፣ እና በአገር ውሰጥም ሆነ በውጭ የተከበሩ ይሆናሉ፡፡ “የዓለም ተዋራጂ” ሆነው አይቀጥሉም፡፡ እና በጥልቅ ከልብ አምናለሁ ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሄር ትዘረጋለች፣ እንደገና አናለቅስም፣ ሀሴትንም እናደርጋለን፡፡

ተዋርደን አንቀርም!! ኢ/ር ይልቃል ጌትነት (የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር) Interview Eng. Yilkal Getnet

ተዋርደን አንቀርም!! ኢ/ር ይልቃል ጌትነት (የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር)

ሳውዲ አረቢያ በዜጎቻችን ላይ እያደረሰች ያለውን ግፍና በደል በሰላማዊ ሰልፍ ለመቃወም ፓርቲያችን በወሰነው መሰረት ለሚመለከተው ክፍል አሳውቀን ነበር፡፡መቸም ህዝባችን በጭቆና ውስጥ ስለኖረ በመብቱና በግዴታው መሀል ያለውን ድንበር በውል ካለመረዳቱ የተነሳ ሰልፉ እንዲደረግ ስለመፈቀዱ በተደጋጋሚ ስንጠየቅ ነበር፡፡ህጉ የሚለው ግን ማስፈቀድ ሳይሆን ማሳወቅ ብቻ ነው፡፡በተቃራኒው መንግስት በተለያዩ ጉዳዮች ሳቢያ በእለቱ ለሰላማዊ ሰልፉ የደህንነት ከለላ መስጠት የማይችልበት ሁኔታ ከገጠመው ሰልፉን ለጠራው አካል ችግሩን ገልጾ ቀኑ እንዲተላለፍለት ይጠይቃል፡፡በመሆኑም ይህን መሰል ጥያቄ ከሚመለከተው መስሪያ ቤት ለፓርቲያችን ባለመቅረቡ በሙሉ ልብ ቅድመ-ዝግጅት ማድረጉን ተያያዝን፡፡


Interview Eng. Yilkal Getnet


ሁሌም ቢሆን መንግስት ሰበብ ፈልጎ ሊወነጅለንና ከመስመር ሊያስወጣን እንደሚፈልግ በሚገባ እናውቃለንና በጥቃቅን ጉዳዮች ላይ ሳይቀር ጥንቃቄ እናደርጋለን፡፡ለሚመለከተው መስሪያ ቤት ባሳወቅን በአስራ ሁለት ሰአታት ውስጥ ምላሽ ስላልመጣ ሙሉ በሙሉ ህጋዊነታችንን አረጋግጠናል ማለት ነው፣እነሱ ደግሞ ጠብ-መንጃ በእጃቸው አለና የፈለጉትን ሁሉ ማድረግ ይችላል፡፡

አቶ ሽመልስ ከማል ለሚዲያወች የሰጡትን ፍጹም ከእውነት የራቀ ውንጀላና ሰበብ አዳምጨዋለው፡፡ “ሰላማዊ ሰልፉን ያገድንበት ምክንያት ጸረ-አረብ መፈክሮች ስለነበሩ ነው“ብለዋል፡፡መጀመሪያ ደረጃ ሰልፉ ገና ከግቢው ፈቅ ሳይል ነው ያፈኑት፣ሆኖም የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም አንድ በአንድ እየሆንን ወደ ሰላማዊ ሰልፉ መዳረሻ ለመሄድ ስንሞክር የተወሰኑ አመራሮችን አራት ኪሎ አካባቢ ያዙን፣እነሱ ቀድሞውኑ ሰልፉ እንዳይካሄድ ስለወሰኑ ነው እንጅ ትንሽ እንኳ ተንቀሳቅሶ የሰልፉን ባህሪ ለመገምገም ምንም እድል አልሰጡንም፡፡

ለምሳሌ ሰልፉን እንደምናደርግ ይፋ ባደረግን ማግስት ከራዲዮ ፋና ተደውሎ አንዳንድ ጥያቄዎች ተጠይቄ ነበር፡፡በቃለ-መጠይቁ ሰላማው ሰልፉ በዜጎቻችን ላይ የሚደርሰውን በደል በመቃወም እንደምናደርግ ተናግረናል፡፡ጋዜጠኛው ለሰላማዊ ሰልፉ ተሳታፊዎች መልዕክት ካለ ብሎ በጠየቀኝ ወቅት የሳውዲ አረቢያ ሰንደቅ አላማ ላይ ያለው ምልክትና ጽሁፍ ሀይማኖትን የሚመለከት በመሆኑ ዜጎች በስሜታዊነት ባንዲራ እንዳያቃጥሉ፣እነሱ ቢያዋርዱንም እኛ ግን ክብር ያለን ዜጎች ስለሆንን ተቃውሟችንን ጨዋነት በተሞላበት ሁኔታ ማካሄድ እንዳለብን ተናግሬ ነበር፡፡ከሰላማዊ ሰልፉ በፊት በዚህና በተለያየ መንገድ በማያሻማ ሁኔታ መልዕክት ባስተላልፍም እነሱ ግን ይህን በመቁረጥ አላስተላለፉትም፡፡እነዚህና ሌሎች ምክንያቶች ሲደመሩ የአቶ ሽመልስ ከማል ንግግር ነጭ ውሸት መሆኑን ያስገነዝባል፡፡

ሁለተኛ የአንድ ሀገር መንግስት ዜጎቹ እየተደፈሩ፣በማጎሪያ ካምፕ በረሀብና በውሃ ጥም፣ሌላው ቢቀር መጸዳጃ ቤት እንኳ ተከልክለው ፍጹም ከሰውነት ክብራቸው ወርደው እየተበደሉ፣እየተገደሉ ባለበት ወቅት ገና ለገና ተቃዋሚ ፓርቲ በጠራው ሰልፍ ላይ በሚንጸባረቅ ጥላቻና ተቃውሞ የዲፕሎማሲ ግንኙነቴ ይበላሽብኛል ብለን መናገር እንችላለን?ሌላው ይቅር አንድ ክፉና ደጉን የለየ ሰው የሚያስበው ጤነኛ ሃሳብ ነው ማለትስ ይቻላል?

ከእገዳው ባሻገር የሚደንቀው ነገር ደግሞ በፓርቲያችን አመራሮችና አባላት ላይ የተደረገው ድብደባ ነው፣የሆነ ማስተላለፍ የፈለጉት ነገር ያለ ይመስላል፡፡የጭካኔያቸውን መጠን እንድናውቅ የሚደበድቡት አቅመ-ደካሞችን፣ሽማግሌወችንና ሴቶችን እየመረጡ በፍጹም አረመኔነት ነበር፡፡ይህን ተግባራቸውን ስመለከት የደረሱበትን የዝቅጠት ደረጃ መታዘብ ችያለው፡፡ከፖለቲካ ልዩነትም፣ከአምባገነንነትም በላይ ሰወቹ እንደታመሙ ነው ለመረዳት የቻልኩት፣ስር የሰደደ የቁስ ሰቀቀንና የስልጣን ጥም የተጣባቸው፣ለዚያ ሲሉም የትኛውንም አይነት ውርደት ለመቀበል የቆረጡና የሞራል ልዕልናቸውን ሙሉ በሙሉ ያጡ ሰዎች ናቸው፡፡ስነ-ልቦናቸው ክፉኛ ተቃውሷል እንጂ ሀገር እመራለው የሚል ቡድን እንዲህ ያለ ተግባር ይፈጽማል ለማለት እቸገራለው፡፡በአባላቶቻችን ላይ ክፍኛ ድብደባ ተፈጽሟል፣እስከዛሬም እግሮቻቸው መራመድ የማያስችላቸው፣የሚያነክሱ ሰዎች አሉ፡፡እውነት ለመናገር ይሄ እብደት ነው፡፡አንዲት እራሷን መከላከል የማትችል ሴትን ለሶስት መደብደብን ከዚህ በተሸለ ልገልጸው አልችልም፡፡

አንድ ማስገንዘብ የምፈልገው ነገር ለኛ ዋነው ጉዳይ የዜጎቹ ህጋዊነት ወይም ህጋዊ ያለመሆን ጉዳይ አይደለም፡፡በምንም አይነት መንገድ ሴቶች እየተደፈሩ፣ወንዶች በየስርቻው እንደ ውሻ ተቀጥቅጠው እየተገደሉ እንዲሁም በተለያዩ ቦታዎች ታጉረው ይህን ሁሉ መከራ መቀበላቸውን ልንታገሰው፣ወይም ከህጋዊነት አንጻር እየተራቀቅን ልንመለከተው አንችልም፣ስለ ህግም ከተወራ የሳውዲ አረቢያ መንግስት ጭፍጨፋው ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ባላቸው ላይ ጭምር ሲፈጸም እንደነበር አምኗል፡፡

ባለንበት የግሎባላይዜሽን ዘመን የአንዱ ሀገር ዜጋ ካለ ሀገሩ መገኘት አገር ይያዝ የሚያስብል አይደለም፡፡መውጣት ካለባቸው ጊዜ በመስጠት፣ከመንግስታቸው ጋር በመነጋገር በዘዴ ነገሩን መከዎን እየተቻለ አንድ ሀገርና መንግስት በሰዎች ላይ እንዲህ የጭካኔ ጥግ የሆነን አቋም ይዘው መንቀሳቀሳቸው ፍጹም ኢ-ሰብአዊነት ነው፡፡
ለኢትዮጵያውያን እንዲህ ያለ አስከፊ ጊዜ የለም፣እውነቱን ለመናገር ለአገዛዙ ሰዎች የነበረኝ ጭላንጭል ተስፋም አፈር ተደፍቶባታል፣እንዲህ ግልጽ የሆነ ጭፍጨፋ እየደረሰብን እንኳ በድፍረት ለመናገር አልፈለጉም፡፡ስለ ኢትዮጵያውያን መገደል ለማውራት ሲፈልጉ ሌላ ሀገር ይጠቅሱና እነሱም እኮ እየተገደሉ ነው ይላሉ፣ወገን ከምንለው የማህበረሰባችን አካል ይሄን መስማቱ ከጥቃቱ ይበልጥ ያማል፡፡

ለምሳሌ ኢቲቪ ስጉዳዩ ሲያወራ ህገ ውጥ ሊባል የሚችል ድርጊት ተፈጽሟል በማለት ነው፡፡ተመልከቱ! እንዴት ያለ ባዕድነት ነው?ኢትዮጵያውያን በድህነትም ውስጥ እንኳ ለክብራችን የመሞት ባህሪ አለን፣ይሄ ከቀደሙት አንጡራ ኢትዮጵያውያን የወረስነውና ዛሬም ያለን ሀብታችን ነው፡፡

ትናንት ፍየል ጠባቂ የነበረ በረኸኛ ይህን ክብራችንን ገፍፎ እንደውሻ ቀጥቅጦ ስርቻ ሲጥለን ያልተቆጣ መንግስት ኢትዮጵያዊ ነው?ከዜጎቹ የወጣና ለህዝቡ የቆመ እውነተኛ መንግስት ከዚህ የበለጠ የሚቆጣበት ጉዳይ ከወዴት ይመጣል? እውነተኛ መንግስት ቢሆን ኖሮ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የሳውዲ ካምፓኒዎችን በሰአታት ውስጥ ማባረር፣ኢምባሲውን ዘግቶ አምባሳደሩን ማሰናበትን የመሳሰሉ ውሳኔዎችን ያሳልፉ ነበር፡፡የሆነው ግን በተቃራኒው ነው፣የድፕሎማሲ ግንኙነቴ ሊበላሽ ይችላል ብሎ እኛ ድምጻችን እንዳናሰማ ደበደበን፣አፈነን፡፡በግልጽ እንደሚታየው የጥቅም ትስስሩ ነው አፋቸውን ያዘጋቸው፣ይህች ጥቅማቸው እንዳትቋረጥ በዜጎች ህይዎት መደራደርን መርጠዋል፡፡

ስነ ልቦናቸው የተቃወሰ በመሆኑና ተራ ስስታሞች በመሆናቸው እንጂ ኢንቨስትመንትም ሆነ ዲፕሎማሲ ግብአትነታቸው ለሰው ልጅ ነው፣እንደ አህያ ሲያፈጋ ከርሞ ሬሳቸውን ለላከ መንግስት እንዴት ተመጣጣኝ ምላሽ ለመመለስ ይገዳል?እንዴት እንደ ኢትዮጵያ ያለች ታሪካዊትና ለአፍሪካ የነጻነትና የኩራት ተምሳሌት የሆነች ሀገርን እየመሩ እንዴት ትናንት የነዳጅ ዘይት ባቆማቸው እረኞች ስትዋረድ ዝም ይላሉ?!::

እንዴት!በዜጎች ህይወት የተደራደረው አገዛዝ ማለፉ አይቀርም፣ለዚህ ጥርጥር የለኝም፡፡ታሪክ ለመጥቀስ ብዙ ርቀት መሄድ አያስፈልግኝም፡፡የቅርብ የሰሜን አፍሪካ አምባገነኖች የከፋ ፍጻሜ አለና፡፡ኢትዮጵያውያን ፍቅርም ጸብም እናውቃለን፣ሳውዲወችም የፈጸሙትን ግፍ ማወራረዳቸው አይቀርም፡፡በዚህ ክፉ ጊዜ ስለስብአዊ መብት ቆመናል የሚሉ አለም አቀፍ ተቋማት ዝምታን መምረጣቸው እውነተኝነታቸውን ለመመርመር ጥሩ እድል ይሰጠናል፡፡

መንግስት ቢኖረን ኖሮ ይሄ ሁሉ ውርደት ይፈጸምብን ነበር ብየ አላስብም፡፡በዚህ ሰአት ርዕሰ-መንግስት ብሆን ኖሮ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ትልቅ ድርጅት እንደመሆኑ፣ወደየትኛውም ሀገር የሚደረገውን ጉዞ አቋርጨ ዜጎቸን ማስወጣትን አስቀድም ነበር፡፡ያሄ ጥቂት ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ ሊያመጣብን ቢችልም ከከፋው የዜጎች ስቃይ ጋር ግን በአንድ ሚዛን ላይ አይቀመጥም፡፡የአደጋ መከላከያና ዝግጁነት ኮሚሽን የሚባል ድርጅት አለ፡፡በዜጎቻችን ላይ ጎርፍና ድርቅ ሲመጣ ብቻ ነው የሚንቀሳቀሰው? ይሄም ሰው ሰራሽ አደጋ ነው ሙሉ ሀይሉን ወደዚህ አዙሮ ሊንቀሳቀስ ይገባው ነበር፡፡

እርግጥ ነው ባቀድነው መሰረት ሰላማዊ ሰልፉ ሙሉ በሙሉ ስኬታማ እንዳይሆን አድርገውታል፡፡ጩኸቱ ግን ይቀጥላል……ባለን አቅም ሁሉ አፈናውንም፣ወከባውንም ተቋቁመን ለዜጎቻችንና ለኢትዮጵያዊነት እንታገላለን፡፡

አገዛዙ ይሄን ሰላማዊ ሰልፍ ሲያፍን ለኢትዮጵያ ህዝብ እንድ መልእክት አስተላልፏል፣ይህን መልእክት እንዲያስትላልፍ ማስገደዳችንም ለኛ ትልቅ ስኬት ነው፡፡የሳውዲ መንግስት ያሻውን ያደርግ ዘንድ የፈቀድኩት እኔ ነኝ፣በመሆኑም እሱን በመቃወም ግንኙነቴን አታበላሹ ብሎ እርምጃ በመውሰዱ ህዝቡ የነገሩ ቁልፍ የት እንዳለ፣የአጥቂወቹ በራስ መተማመን ምን ላይ እንደቆመ በጠራ ሁኔታ ለመመልከት እንዲችል ሆኗል፡፡

ይሄ ሁሉ ነገር እየተፈጸመ የተስተዋለ አንድ ነገር አለ፡፡የጠቅላይ ሚኒስትሩ ዝምታ እውነተኛ ማንነታቸው፣እውነተኛ በአገዛዙ ውስጥ ያላቸውን ቦታ ያሳየን ክስተት ነው፡፡እንደሚታወቀው እሳቸው በኢህአዲግ እንጂ በኢትዮጵያ ህዝብ የተመረጡ አይደሉም፡፡ኢህአዲግ የሚናገረው ከሌለ እርሳቸው የሚሉት አይኖርም፡፡እንደ አንድ ሀገርና ህዝብ መሪ ግን የመኮነንም ሆነ የማጽናናት ቃል ይጠበቅባቸው ነበር፡፡

ባሉበት ቦታ ያስቀመጣቸው ህወሀት ነው፤ድርጅቱ ደግሞ ይሄን አቋም አልወሰደም፡፡ስለዚህ እንደሚቆጣቸው ስለሚያውቁ ዝምታን መረጡ፣ቸልታንም አስበለጡ፡፡በሀገርም ሆነ በግለሰብ ደረጃ ከዚህ በላይ ሽንፈት ያለ አይመስለኝም፡፡

(ይህ ጽሁፍ በፋክት መጽሄት ተስተናግዷል፣ነገር ግን መጽሄቱ ላልደረሳቸው ሰዎች ይደርስ ዘንድ እዚህ ለማስተናገድ ወደድኩ፡፡)