Friday, 27 December 2013

ትንሽ ስለጃዋር መሀመድ Source D.C.E.S.O.N

ከዓለማየሁ መሀመድ

ሁለት ነገሮችን ላንሳ።

1. የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ትግል መሬት አንቀጥቅጥ ሆኖ ለሁለት ዓመት ገደማ ዘልቋል። በዚህ ትግል ውስጥ በሀገር ቤት ከስርዓቱ ጋር አንገት ለአንገት ተናንቀው ደም ህይወታቸውን ገብረው ትግሉ በማይናወጥ ጽናት ላይ እንዲቆም ያደረጉት ብዙሃኑ ሙስሊሞች ዋጋቸው በክብር መዝገብ ላይ ምንጊዜም ወርቃማ በሆነ ቀለም ተመዝግቦ ይቀመጣል። ከእነሱ ባሻገር በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ትግሉ መሬት ይዞ በሰከነ መልኩ እንዲጓዝ ያደረጉት አስተዋጽኦም የሚዘነጋ አይደለም። ጃዋር በዚህ ውስጥ ስሙ ሲጠቀስ ነበር። የሙስሊሞች ትግል ላይ ትንሽም ብትሆን አሻራው አርፎበታል። ያኔ ነው። በፊት። አሁንስ?Jawar Mohamed Muslim fundamentalist

2. የኦሮሞ ህዝብ ጭቆና ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ የተለየ ነው- አይደለም -የሚለው ክርክር ለጊዜው ይቆይና የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ለ40 ዓመታት ሲያቀነቅነው የነበረውና ውጤት ሳይኖረው ዘመናት የቆየው ትግሉ አሁን ‘’የኦሮሞን ህዝብ ትግል በኢትዮጵያ ጥላ ስር’’ የሚለው ሀሳብ አሸንፎ ሲወጣ ጃዋር ብቅ አለ። መጀመሪያ ላይ በሳል በሆኑ፡ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ፡ የሰውን ልጅ በአንድ መነጽር የሚመለከቱ የሚመስሉ ሀሳቦች በጃዋር አፍ ውስጥ ይዋኙ ነበር። ይህም በተቀረው ኢትዮጵያውያን ዘንድም ጃዋር ምናልባት ያረጀውን የኦነግ ጠባብ ብሄርተኝነት ከመቃብር አስቀመጦ የኦሮሞን ህዝብ ከዕውነተኛ ድል የሚያቀርብ አዲስ መንገድ ይጀምራል የሚል ብጣቂ ተስፋ ውስጣቸው የነበሩ ጥቂቶች አልነበሩም። ከመነሻውም የተጠራጠሩት፡ የተደበቀው ማንነቱ አንድ ቀን ይወጣል ብለው በጥርጣሬ ሲመለከተቱት የነበሩት ቁጥራቸው የትየለሌ ነበር። ሆኖም እኔም ሆንክ ጥቂቶች ጃዋርን እንደ አብሪ ኮከብ መመልከታችን አልቀረም። አሁንስ?

ጃዋር አሁን አይሰማም። መስማት የሚፈልገው የፈለገውን ብቻ ነው። በየአዳራሹ የሚሰማው ጭብጨባ ሰርቆታል። ቀልቡ አሁን ከሚኒሶታ እስከ ለንደን በተዘረጋው የ’ኦሮሞ ፈርስት’ ቅልጥ ያለ የወቅቱ ነጠላ ዜማ ላይ ሆኑዋል።

1. የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ትግል በእፎይታ ጊዜ ላይ ቢሆንም የጃዋር ‘ኦሮሞ ፈርስት’ በይፋ ከታወጀችና ‘ሜንጫ’ዋ በሚኒሶታ መድረክ ከተስተጋባች በኋላ የሙስሊሞች ትግል ላይ መጠነኛ ተጽእኖ መፈጠሩ አልቀረም። የሙስሊሙን ትግል የኢትዮጵያ ህዝብ ትግል አድርገው የተሰለፉ ወገኖች በጥቂቱ ማፈግፈጋቸው በመጠኑ ይታያል። ሜንጫ የሚለውን ቃል ጃዋር ሚኒሶታ ላይ ካፈነዳት ወዲህ በሙስሊሙ ማህበረሰብ ዘንድ እንኳን ውዥንብር ተፈጥሯል። እናም የሟችዋ ሚካያ በሃይሉ ዜማን ልዋሰው- “ሸማመተው”:: ህወሀት ሸመተ:: ትግሉ እንዲደበዝዝ ቀን ከሌት ይመኝ የነበረው ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ- ሸማመተው!!

2. ከምንጊዜውም በላይ የኢትዮጵያ ህዝብ አንድነቱን ለማሳየት፡ በጋራ ወደ ምር ነጻነት ለመምጣት እጅ ለእጅ እየተያያዘ ያለበት ወቅት ላይ እነጃዋር የኦሮሞ ብሄርተኝነትን ወደ ጠባቡ ጽንፍ ወስደውት ዘራፍ ማለት መጀመራቸው በተወሰነ ደረጃ ለህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ከሰማይ የወረደ አዱኛ ሆነለት:: አሁንም ሚካያ ትላለች -“ሸማመተው” – ህወሀት ሸመተ::

እነ ጃዋር እየተናገሩ ነው:: ‘ኦሮሞ ፈርስት’-‘ ማይ ካንትሪ ኢዝ ኦሮሚያ’ :: የህወሀት የፌስቡክና ትዊተር ሰራዊቶች ስማቸውን በኦሮምኛ ለማድረግ ከብርሃን ነበር የፈጠኑት:: እናም ‘ኦሮሞ ፈርስት’ መፈክራቸው ሆኖ አጼ ሚኒሊክ ላይ እርግማናቸውን ውእግዝ ከማርዮሱን እያዘነቡት ነው።

ጭብጨባው ቀልጧል። ነጠላ ዜማው ሰማይ ምድሩን አድምቆታል፡፡ እነጃዋር በህወሀት ነጠላ ዜማ ዳንሱን እያቀለጡት ነው። የሚሰማ ጆሮ የላቸውም። ልባቸው ሸፍቷል። አውቀው ይሁን ሳያውቁት ከህወሀት መንደር ዘልቀው የልፊያ ፖለቲካውን ተያይዘውታል። ጭብጨባ ክፉ ነው። ላላወቀበት ስካር ነው።

ሰሞኑን ከጨፌ ኦሮሚያ አንድ መረጃ ደርሶኛል። ሳይላመጥ አይቀርብም በሚል ለጊዜው ይዤዋለሁ። እነጃዋርን የተመለከተ ነው። ምናልባት መረጃውን በማስረጃ ማስደገፍ ከቻልኩኝ በድብቅ የተፈጸመውን የእነጃዋርንና ህወሀትን ጋብቻ ይፋ አደርጋለሁ።

እስከዚያው ጩኧቱን እየሰማን እንቆይ። መልካም ጋብቻ የምንልበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም።


                                                                                                     Posted by  A. G

No comments:

Post a Comment