በሀገራችን ላይ የተንሠራፋውን አምባገነናዊ ሥርዓት ገርስሶ ለመጣል የመጨረሻ አማራጭ የሆነውን የትጥቅ ትግል በማካሄድ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ሠራዊት በጠላት ላይ የሚወስዳቸውን ወታደራዊ የማጥቃት እርምጃዎች አጠናክሮ በመቀጠል በታህሳስ 23 ቀን 2006 ዓ/ም በሰሜን ጎንደር በላይ አርማጭሆ ወረዳ ልዩ ስሙ ገራርዋ ባምብላ ወንዝ በተባለው ቦታ መሽጎ የአካባቢውን ህብረተሰብ ሲያሰቃይና ሲያንገላታ ከነበረው የወያኔ 24ኛ ቴዎድሮስ ክ/ጦር እና ከፀረ-ሽምቅ ታጣቂ ኃይሎች ጋር ባደረገው ውጊያ 24 የጠላት ወታደሮችን ገድሎ 11 በማቁሰል የግንባሩ ሠራዊት አንፀባራቂ ድል አስመዝግቧል፡፡ በዚሁ ዕለትም በተደረገው እልህ አስጨራሸ ውጊያ የወያኔ 24ኛ ቴዎድሮስ ክ/ጦር ከኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ሠራዊት የሚደርስበትን የተኩስ ናዳ መቋቋም ተስኖት ሙትና ቁስለኛውን እያዝረከረከ እግሬ አውጪኝ በማለት መፈርጠጡን ታውቋል::
ይህ በእንዲሀ እንዳለ የአካባቢው ነዋሪዎች የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ሠራዊት በጠላት ላይ ባስመዘገበው ከፍተኛ ወታደራዊ ድል መደሰታቸውና ወደፊትም ሀገራዊና ሕዝባዊ አላማን አንግቦ የህብረተሰቡን እምባ በማበስ ግንባር ቀደም በመሆን ለሀገርና ለወገን ደራሽነቱን እያስመሰከረ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ሠራዊትን በመደገፍ የቆመለትን አላማ ከግብ ለማድረስ ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀው ግንባሩ በተከታታይ ጊዜያቶች የሚወስዳቸው ወታደራዊ ጥቃቶችና የሚያስመዘግባቸው አንፀባራዊ ድሎች የወገንን አንጀት በማራስ በአንፃሩ ደግሞ የጠላትን አንገት በማስደፋቱ እጅግ ደስተኛ መሆናቸውንም ገልፀዋል፡፡
በመጨረሻም የአካባቢው ህብረተሰብ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ሠራዊት የጀግና አቀባበል ያደረጉለት ሲሆን ወታደራዊ የማጥቃት እርምጃው ተጠናክሮ እንዲቀጥል የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ለማበርከት ከግንባሩ ሠራዊት ጎን በመሰለፍ ሀገራዊ ግዴታቸውን ለመወጣት ቆርጠው መነሳታቸውን አስታውቀዋል፡፡
Posted by A.G
No comments:
Post a Comment