Friday, 9 May 2014

በሱዳን ኢትዮጵያውያን የምሬትና የድረሱልን ጩኸት !

 በሱዳን ኢትዮጵያውያን የምሬትና የድረሱልን ጩኸት !

ሱዳኖች በእኛ ሃገር በእኛ ምድር እንዳሻቸው ይሆናሉ ። ወገኔ ቀን ዘንብሎ እና አማራጭ አጥቶ የሚሰደድባት ሃገር የምንዋረድባት ሃገር ሆና ከፍታብናለች። ርህሩህ የሱዳን ዜጎች ለእኛ ከፍተው ባይከፉም የአልበሽር መንግስት ግን እየጎዳን እየበደለን ለመሆኑ የመከራው ገፈት ቀማሽ የሆኑትን በእንባ የታጀበ ልብ ሰባሪ ጩኸት እና ሮሮ ሰምቻለሁና ከፍቶኛል። ጩኸታቸውን ሰምቻለሁና አሰማችሁ ዘንድ ግድ ብሎኛል። መንግስታቸውን መከታ ያደረጉት ሱዳኖች በእኛ ምድር በኩራት ተከብረው የባለ ጸጋን ኑሮ ይኖራሉ። እኛ መሬታችን ተገፋ ሲባለም ሆነ ሰብዕናችን ሲጣስ ዋቢ መከታአጠናል። እናም ቀን ዘንብሎ ኑሯቸውን ለማሸነፍ በሱዳን ስደት ላይ የሚገኙ ዜጎቻችን አሽከር ሆነው ከሚኖሩት ወዛቸውን አንጠፍጥፈው ለሚኖሩባት ምድር ግፍ ተንሰራፍቷልና የሰሚ ያለህ እንላለን። በስደት ህይወት እየተሳደዱ ፣ እየተፈናቀሉ ፣ እየተገፉና ፣ ዘብጥያ እየወረዱ ነው። ዜጎቻችን የሚያንገላቱት ሃገር ዜጎች በሃገራቸው ባለሃብት ኢንቨስተር ሆነው ይፏልላሉ የሚሩባት ሃገር ዜጎች እየተጎዱ ነው ። ዜጎቻችን በሱዳን በከፋ የመብት ረገጣ ተከበዋል! አደጋ ላይ ናቸው: ( ጀሮ ያለው ይስማ !

በአረባዊቷ ሃገር በሱዳን ያለውን ስቅየት ያረዳኝ ወንድም በመዲናዋ በካርቱም ከአስርት አመታት በላይ የስደትን ህይዎት ገፍቷል። ወደ ሶስተኛ የበለጸጎ ሃገሮች ለመሻገር ተደጋጋሚ ሙከራው ከሽፏል። የሃገሪቱን ህግና ስርአት አክብሮ ሲኖር ስደትን ሶስት ጉልቻ መስርቶ ልጆች ወልዶ የሞቀ ትዳሩን ፈጣሪን ተመስገን ብሎ ኑሮን በመከራ ሲገፋ "ጨለማው ይነጋልን " ስንቅ አድርጎ ነበር። የሱዳን ስደት ግን ዛሬ ዛሬ ከወትሮው እየከፋ መምጣቱን በምሬት በስልክ አጫውቶኛል።

የወዳጀን እና የአንድን አባት እማኝ ምስክርነት የሰማሁበትን ስልክ ዘጋሁት ። ህመማቸው ዘልቆ ቢያም ቢከፋኝ ፣ ዝም ብየ መቆዘም ያዝኩ ... የማደርገው ግራ ቢገባኝ ከመጨዋወታችን አስቀድሞ መረጃውን የላከልኝ ወዳጀ መልዕክት መላልሸ ማንብ ያዝኩ ... የስደቱ ክፋት ፣ የመጣው ክፉ ጊዜ ህመሙ አመመኝ: ( የወዳጀን መልዕክት ደጋግሜ አነበብኩት! ያማል! በሚያመው መልዕክት የማለዳ ወጌን ልቋጨው ወደድኩ ...መልዕክቱ እንዲህ ይላል ...

"ሰላምና ጤንነት የምመኝልህ ወዳጀ ነብዩ እንደምን ሰነበትክ ...
ነብየ አንተ ከታሰርክ አንስቶ በዚህ አንድ ወር ውስጥ እዚህ ሀገረ ሱዳን ውስጥ አንተ ለወገንህ ስትል ያንን ግፍ መከራ በማጋለጥህ የታስርክበትን አይነት ግፍ እየተፈጸመብን ነው። ... ወገኖቻችን አፈሳ ቤት ለቤት ተጀምሮ ሙቀቱ ከ47 አስከ 50 ℅ በሚደርስበት እስር ቤት ውስጥ እየተሰቃዩ ይገኛሉ ። በተለይ እምድሩማን ከሚባለው ዋናው የሴቶች እስር ቤት ውስጥ ከሁለት መቶ በላይ ሴት እህቶቻችን በመሰቃየት ላይ ይገኛሉ ። አጠቃላይ ወደ አንድ ሸህ የሚገመቱ አትዮጸያውያን በተለያዩ አስር ቤት ውስጥ ታጉረዋል። ይህንን ዘመቻ በመፍራት ወደ ሊቢያ የነጉደውን ቁጥሩን ለማወቅ ይከብዳል ። በርካቶች እንደሞቱና ከ700 በላይ ዳንጉላ አውራጃ ሊቢያ ደንበር ተይዘው እዛው ተፈርዶባቸዋል። በትላንትናው እለት ደግሞ አንድ የስደተኛው አባት ቄስ ማሩ ቤት ገብተው ልጆቻቸውን አስርወባቸዋል ። የሚገርመው እኒህ አባት ከብዙ አመታት በፊት ከወያኔ ቤተክርስትያን አብረውን ተባረው የግብፅ ኮፕቲክ እህት ቤ/ክርስትያን መፀለያ ቤተክርስትያን ፈቅደውልን እኛን ስደተኛውን የሚያገለግሉ አባት ናቸው። ... ዝርዝሩ ሰፊ ነው ። ይህንን ግፍ አፈሳ በተመለከተ ዲያስፖራው ማህበረሰብ እሮሮቻን ይሰማ ዘንድ በ አንዳንድ የህዋ ሰሌዳ ዌብሳይት እየደረሰብን ያለውን ግፍ ሰሚ ያገኘ ዘንድ ተፅፎ ነበር። ... ድምጻችን የሚሰማበትን መንገድ ፈልግልን ከዚህ የከፋ ነገር ከመድረሱ በፊት መላ እሮሮችን አሰማልን;; እኔም ብሆን በነሱ አይን ስር ስላለሁ በጥንቃቄ ነው የምኖረው። ይህንን ግፍ ዩ ኤችሲ አር UNHCR አሳምሮ ያውቀዋል ። አንዳችም ያደረጉልን የለም ። ከፍቶን ጨንቆናል! እባካችሁ ድረሱልን!
ጭንቅ ላይ ያለሁት ወዳጅህ ከሱዳን
ካርቱም "
መልዕክቱ እንዲህ ተቋጨ ፣ እኔም ከዚህ በላይ የምለው የለም ፣ አበቃሁ!
ቸር ያሰማን !

ከነቢዩ ሲራክ                                                                                                                             Posted by A.G

No comments:

Post a Comment