Thursday, 23 July 2015

ለእናት ሀገር ሲባል፣ ማን ይፈራል….!

በሰላማዊ ትግል ጓዶቻችን የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እና፣ መልካም ህልም አላሚዎቹ የዞን 9 ጦማርያን ያለምንም ወንጀል በስርዓቱ ወደር የለሽ ፍራቻ ምክንያት ብቻ ከንጹህ ህሊናቸውና ከመልካም ስራቸው ጋር ወደ ማጎሪያ ቤት በተወረወሩ ጊዜ፣
‹‹በሉ እናንተ ሂዱ የእኛም ወደዚያው ነው፣
ድሮም መንገደኛ ፊትና ኋላ ነው›› ብለን ነበር፡፡ 
ይህን ብለን ሳናበቃ ግን በዚህ ሁኔታ የሀገራችን እጣ ፋንታ ምንድነው? የሚል ጥያቄ በውስጣችን ይመላለስ የነበርን የዛሬዎቹ አባሪ ተከሳሾች የሆንን ወጣቶች መደበኛ ያልሆነ ውይይት ጀመርን፡፡ በዚህ ውይይታችንም አምባገነኑን የወያኔ አገዛዝ ሊያስወግደው ቀርቶ ሊያሳምመው እንኳን በማይችል ጉንተላ መሳይ ትግል ውስጥ ሆነን ለሀገራችን የሚጠበቅብንን ያህል ዋጋ ሳንከፍል ጓዶቻችንን ተከትሎ ወደ ማጎሪያ ቤት መጓዝ ለምንወዳት ሀገራችን የሚፈይደው ነገር ምንድነው? ትግሉስ ከኛ ምን ይፈልጋል? የሚሉ የወቅቱን ወሳኝ ጥያቄዎች በማንሳት ከራሳችን ምላሾችን ለማግኘት ሞክረን ያገኘነው ምላሽም ለትግሉ ማበርከት ያለብንን አስተዋጽኦ ሳናበረክትና የአቅማችንን ሁሉ ሳንሰራ ጓዶቻችንን ተከትለን ወደ ማጎሪያ ቤቱ መጓዝ ለሀገራችን የሚጠቅማት ነገር እንደሌለና በማንኛውም መንገድ አምባገነኑን ስርዓት ሊያስወግደው በሚችል ትግል ውስጥ መሳተፍ የወቅቱ ግዴታችን መሆኑን ነበር፡፡
እናም 6 ወራት ከፈጀ ሰፊ ውይይት በኋላ ምርጫችን ሁሉን አቀፍ ትግል መርጦ ለሀገር ነጻነት በሚታገለው፣ ሀገራችንን ከፋሽስታዊው አገዛዝ ነጻ ለማውጣት ሌት ተቀን ሞትን ተጋፍጠው የሚተጉ አባላትና ትግሉን ስኬታማ ለማድረግ በልበ ሙሉነት ለስልጣን ሳይሆን ለሞት የሚሽቀዳደሙ መሪዎች ወደተሰባሰቡበት፣ በአገዛዙ ፓርላማ ‹‹ሽብርተኛ›› የሚል የዳቦ ስም ወደተሰጠው ‹‹ግንቦት 7›› ወደተሰኘው ነጻ አውጪ ድርጅት አደረግን፡፡ ድንቅ ምርጫ!! መቼም የማንጸጸትበት ሁሌም በኩራት ደጋግመን የምንናገረው ምርጫ!! 
ይህን ውሳኔያችንን ተከትሎ ነበር ዛሬ በእስር ላይ የምንገኘው ሦስት አባሪ ተከሳሾች የድርጅቱ ህዝባዊ ኃይል ታጋዮች ወደሚገኙበት አካባቢ ጉዞ የጀመርነው፣ (በእርግጥ በዚህ ‹‹እናት ሀገር ትቅደም›› ጉዟችን ባህር ዳር ስንደርስ ‹‹ወላጅ እናት ትቅደም›› ብሎ ተሰናብቶን የተመለሰ አንድ ‹‹ጀግና›› ወዳጃችንም አብሮን ነበር፡፡) እነዚህን ቆራጥ የኢትዮጵያ አንበሶች ከመገናኘታችን በፊት ሊቀበለን ከመጣው ደሴ ካህሳይ ጋር ሆነን በደህንነት አባላት ተብየዎቹ የስርዓቱ ወንበር ጠባቂዎች እጅ ወደቅን እንጂ፡፡
ይሁንና በስርዓቱ ጠባቂዎች እጅ መውደቃችን ውሳኔያችንን በድጋሜ እንድንመረምር አላደረገንም፤ ዛሬም በአቋማችን ጽኑ ነን፡፡ ዛሬም የኢትዮጵያውያን ነጻ አውጭ ድርጅት የሆነው የግንቦት 7 አባላት ነን፡፡ ይህንንም በኩራትና በልበ ሙሉነት ለማዕከላዊ ደብዳቢዎች (መርማሪዎች?) አስረድተናቸዋል፡፡ ይህንንም ያደረግነው ምርጫችን ትክክል መሆኑን ስለምናምን እንጂ የደብዳቢዎቻችንን ጭካኔ ቀላል ይሆንልናል በማለት አይደለም፡፡ ይልቁንም ይህን መናገራችን ደብዳቢዎቻችንን አበሳጭቶ ኖሮ ሴትን ልጅ ራቁቷን አቁሞ ከሚደረግ የጭካኔ ምርመራ አንስቶ ዓይንን ታስሮ ውሃ እየደፉ እስከመደብደብ የደረሰ ግፍ በደብዳቢዎቹ መሪ ኮማንደር ተክላይ ጭምር ተፈጽሞብናል፡፡ በምርመራው መሐልም ግንቦት 7 አሸባሪ ድርጅት ነው ብለን እንድንናገር፣ ወደ ትግሉ የገባነው አሜሪካ ባሉ የድርጅቱ አመራሮች ተታልለን ነው እንድንል ሀገር ውስጥ ፍጹም ሰላማዊ ትግል ማድረግን የመረጡ የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችን ከግንቦት 7 ጋር ይገናኛሉ እንድንል በአላዋቂዎቹ ደብዳቢዎች ይነገረን ነበር፡፡ 
አሰቃቂው ምርመራ የአንዳችንን ስቃይ በአንዳችን በማስፈራራት ‹‹እሱን ከምንደበድበው እሷን ራቁቷን ከማቆማት እመን/እመኝ የሚለው ማስፈራሪያ ነበር፡፡ ሆኖም ለክፉ ስራቸውና ለሀሰት ምስክር ቆጣሪነታቸው የሚተባበር አስተዳደግም ሆነ የትግል ልምድ አልነበረንምና በቃላችን ጸንተን አካላችን እንጂ መንፈሳችን ሳይጎዳ የተለመደውን የሽብርተኝነት ክስ ተጎናጽፈን ወደ ቃሊቲና ቂሊንጦ ማጎሪያ ቤቶች ተዛውረናል፡፡ 
በማጎሪያ ቤቶቹ ሊጠይቁን የመጡ አንዳንድ የሰላማዊ ትግል የቀድሞ ጓዶቻችንም የወሰነው ውሳኔ የተሳሳተ እንደነበር በጓዳዊነት መንፈስ ሊያስረዱን ሞክረዋል፡፡ ጥቂቶቹም ውሳኔው የወጣትነት ጀብደኝነት ነው ሲሉ ሊሞግቱን ሞክረዋል፡፡ አንዳቸውም ግን ትግሉን አስመልክቶ ላነሳንላቸው ጥያቄ ምልሽ ሊሰጡን አልሞከሩም፡፡ ሁላችንም ይህን መንገድ ከመምረጣችን በፊት በሀገር ውስጥ በሚደረገው የፓርቲ ፖለቲካ ትግል ውስጥ ከፓርቲ አባልነት እስከ ከፍተኛ አመራርነት ድረስ በመሳተፍ የአቅማችንን ያህል አስተዋጽኦ አድርገናል፡፡ ነገር ግን ዛሬም በትግሉ ውስጥ ያልተፈቱት እንቆቅልሾች ያልተመለሱት ጥያቄዎች ያስጨንቁናል፤ እና ዛሬም በአደባባይ እንጠይቃለን፡፡ 
ለመሆኑ በሰላማዊ ትግል ውስጥ የሚከፈለው ዋጋ እና የሚገኘው ውጤት ተመጣጣኝ የሚሆነው መቼ ነው? አራት ሰዓት የሚቆይ አንድ ሰላማዊ ሰልፍ ሲባል እስከመቼ በስርዓቱ ጨካኝ አሽከሮች ነፍሰ ጡር እናቶች ጽንሳቸውን በድብደባ ብዛት ያስወርዳሉ? እስከመቼ ወጣቶች በድብደባ ብዛት አካላቸው ይጎድላል? ህዝብ ተስፋ የሚያደርግባቸውና በታጋዮች የህይወት መስዋዕትነት ጭምር የተከፈለባቸው ፓርቲዎችስ በአንድ ሌሊት ፈርሰው ለድርጎኛ ፖለቲከኞች መሰጠታቸው መቼ ይቆማል? ህይወታቸውን ለሀገራቸው ሰጥተው ሌት ተቀን የሚሰሩ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችን ለተራ ስልጣን ሲባል በብዕር ስም እየተደበቁ ስማቸውን ማጠልሸትስ ትግሉን የት ያደርሰዋል? 
‹‹በድንጎላ ኮሎኔል ማራኪ››ዎቹ ታጋዮች ጓደቻችንን በድንጋይና በዱላ ድብደባ እየገደሉ እያስረከቡን ዛሬም ምላሻችን መግለጫ ነው? (ሳሚና ተሰማ ነፍሳችሁን ይማር) በቀቢጸ ተስፋ ወደ ‹‹እናት ሀገር›› ኬንያ የሚሰደደው ታጋይስ ማቆሚያው ምንድነው? እነዚህን እንቆቅልሾች ሳንፈታ የምናደርገው የትግል ጉዞስ የት ያደርሰናል?
እናም በውሳኔያችን አልተሳሳትንም ስንል ከእነዚህ ሁኔታዎች ተነስተን ረዘም ላለ ጊዜ በመወያየት የወሰድነው አቋም እንጂ በወጣትነት ስሜትና በጀብደኝነት ያደረግነው ባለመሆኑ ነው፡፡ በሰላማዊ ትግል የአጭር ጊዜ ቆይታችን ብርሃኑ ተ/ያሬድ ለ19 ጊዜያት፣ ፍቅረማርያም አስማማው ለ9 ጊዜ፣ እየሩሳሌም ተስፋው ለ7 ጊዜ በአገዛዙ እስር ቤቶች በግፍ ለእስር ተዳርገናል፡፡ በአንዱም ክስ አገዛዙ ጥፋተኛ ሊያስብለን ቀርቶ ክስ ለመመስረት እንኳን የሚያበቃ ምክንያት ሳይኖረው ለሳምንታት እያጎረ በመልቀቅ ማናለብኝነቱን በሚገባ አሳይቶናል፡፡ ስለሆነም ይህን መንገድ መርጠናል፤ በሰላማዊ ትግል ብቻ የሚያምኑ ወዳጆቻችንም የሚታገሉት ለሃሳብ ነጻነት ነውና ይህን ሀሳባችንን ሊያከብሩልን ይገባል፡፡ 
ጓዶች ይህቺ ኢትዮጵያ ናት፣ ታላቋ ኢትዮጵያ!! ቴዎድሮስ እናታለም የሚላት፣ በላይ ዘለቀ፣ አሉላ አባነጋ፣ አቢቹ፣ አብዲሳ አጋ፣ በጽናት የተዋደቁላት ኢትዮጵያ!! የእስክንድር ነጋ፣ የአንዱዓለም አራጌ፣ የእነ ኡስታዝ አቡበክር፣ የእነ ተመስገን ደሳለኝ፣ የእነ ርዕዮት ዓለሙና የእነ እማዋይሽ፣ የእነ ንግስት ሀገር ኢትዮጵያ!! የእነ ፋሲል የኔዓለም፣ የእነ መሳይ መኮነን፣ የእነ ሲሳይ አጌና…የሌሎችም ጀግኖች ሀገር ኢትዮጵያ!! የእነ አብርሃ ደስታ፣ የእነ በፍቃዱ ኃይሉ ሀገር ኢትዮጵያ!! የእነ ሳሙኤል አወቀ፣ የእነ ተሰማ ወንድሙ ሀገር ኢትዮጵያ!! የእነ ይልቃል ጌትነት፣ ዮናታን ተስፋዬ ሀገር ኢትዮጵያ!! የእነ አበበ ካሴና የታላቁ ታጋይ አንዳርጋቸው ጽጌ ሀገር ኢትዮጵያ!! (አንዲ ሁሌም ጀግናችን ነህ!!) እኛ ደግሞ የእነዚህ ወንድሞችና እህቶች ነን፡፡ 
በመቃብራችን ላይ ካልሆነ ኢትዮጵያ አትደፈርም፡፡ በመስዋዕትነታችንም ካልሆነ ኢትዮጵያ አትገነባም፡፡ እጃችን ቢታሰርም መንፈሳችንን ሊያስሩት አይችሉም፡፡ 
ዛሬም የጀግኖች አንበሶቻችን የድል ጩኸት በጆሯችን ይሰማናል፡፡ የበሰበሰውን ዛፍ ለመጣል የተዘረጋው የአንበሶች ክንድ ይታየናል፡፡ ይህ ክንድ የበሰበሰውን ዛፍ ሳይጥል አይሰበሰብም፡፡ በብስባሹ ውድቀት ውስጥም ዴሞክራሲ ያብባል፣ ፍትሃዊነት ይነግሳል፣ እኩልነት ይሰፍናል፡፡ ይህ በወኔ እስር ቤት ያሉ ወጣቶች የቀቢጸ ተስፋ ህልም አይደለም፡፡ ተደጋግሞ በታሪክ የታየ አሁንም በቅርብ የሚፈጸም እውነት እንጂ!!
ጓዶቻችን በምንም ሁኔታ ውስጥ ሆነን ከእናንተ ጋር ነን፡፡
ማን ይፈራል ሞት 
ማን ይፈራል ሞት 
ለእናት ሀገር ሲባል….!!
1. እየሩሳሌም ተስፋው (ከቃሊቲ እስር ቤት) 
2. ብርሃኑ ተ/ያሬድ (ከቂሊንጦ እስር ቤት)
3. ፍቅረማርያም አስማማው (ከቂሊንጦ እስር ቤት)
(ምንጭ፦ ናትናኤል መኮንን)

Sunday, 19 July 2015

ሊቀመንበራችን ትግል ሜዳ ውስጥ ነው!

ከአርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዴሞክራሲ ንቅናቄ የተሰጠ መግለጫ

July 19, 2015
def-thumb

ሐምሌ 12 2007 ዓ.ም.
ህወሓት በኢትዮጵያዊያን እና በኢትዮጵያ ላይ ያሰፈነው ዘረኛና ፋሽስታዊ አገዛዝ እንዲያበቃ፤ በምትኩም ፍትህ፣ ነፃነት፣ እኩልነትና ዲሞክራሲ የሰፈኑበት የፓለቲካና የኢኮኖሚ ሥርዓት እንዲመሠረት እና የሀገራችን አንድነት በጠንካራ መሠረት ላይ ለማኖር አርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ ተገዶ የገባበት የመረረ የአመጽ ትግል መጀመሩን ይፋ ማድረጉ ይታወቃል። በዚህም መሠረት ኢትዮጵያዊያን የነፃነት አርበኞች በጀግነትና በጽናት እየታገሉ ነው።
ይህ ትግል በባርነትና በነፃነት መካከል የሚደረግ ወሳኝ ትግል ነው። የዚህ ትግል ውጤት የእኛ የዚህ ዘመን ትውልድ ሕይወት ብቻ ሳይሆን የአገራችንን የወደፊት ታሪክ፤ የልጅ ልጆቻችንን ሕይወት ይወስናል። በዚህም ምክንያት ይህንን ትግል በድል መወጣት ግዴታችን ነው። በዚህ ወሳኝ ወቅት ለነፃነት ግድ ያለው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ከጎናችን ሊቆም ይገባል።
አርበኞች ግንቦት 7 አመራሩን ሁኔታዎች በፈቀዱ መጠን እና ትግሉ በሚጠይቀው ቦታ እንዲገኙ የሚያደርግ መሆኑ ሲገልጽ ቆይቷል። አሁን ትግሉ በደረሰበት ደረጃ የአመራሩ በትግሉ ሜዳ ውስጥ መገኘት አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት ሊቀመንበሩን ጨምሮ አመራሩን ወደ ትግሉ ሜዳ አንቀሳቅሷል። በዚህም መሠረት የንቅናቄው ሊቀመንበር ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ወደ ትግል ሜዳ ወርዷል።
ትግሉ መሯል። ወሳኝ የሆነ ትግል ውስጥ ገብተናል። የትግሉ መሪዎች የሕይወት መስዋዕትነት እሚከፈልበት ቦታ ይገኛሉ። በአሁኑ ሰዓት የንቅናቄው አመራር በተሟላ ሁኔታ በትግሉ ሜዳ ውስጥ እንዲገኝ ማድረግ ተችሏል። ኢትዮጵያዊያን እጅ ለእጅ ተያይዘን ዘረኛው የህወሓት አገዛዝን ከጫንቃችን ለማስወገድ ቆርጠን እንድንነሳ አርበኞች ግንቦት 7 ጥሪ ያደርጋል።
ኢትዮጵያን ከህወሓት አገዛዝ ነፃ የሚያወጣው አርበኞች ግንቦት 7 ብቻ አይደለም። ስለሆነም ከሌሎች ድርጅቶች ጋር የሚደረገው ትብብር ቀዳሚ ትኩረት ከተሰጣቸው ሥራዎች አንዱ ነው። አርበኞች ግንቦት 7 ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ድርጅቶች ጋር በመተባበር የተቀጣጠለው ሕዝባዊ አመጽ ለድል እንዲበቃ ይታገላል። ኢትዮጵያዊያንም በያሉበትም በተመሳሳይ ልዩነቶቻቸውን አቻችለው በህወሓት ፋሽስታዊ አገዛዝ ላይ ክንዳቸውን እንዲያነሱ አርበኞች ግንቦት 7 ጥሪ ያደርጋል።
እነሆ የአርበኞች ግንቦት 7 ሊቀመንበር ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ በአካል ትግል ሜዳ ውስጥ ይገኛል። የሚችል ሁሉ እንዲከተል፤ መከተል የማይችል በያለበት ሁኖ ሁለገብ ትግሉን እንዲያጧጥፍ አርበኞች ግንቦት 7 ጥሪ ያደርጋል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!
አርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዴሞክራሲ ንቅናቄ

Thursday, 16 July 2015

የአንድዋለም ወንጀል አገሩን መዉደዱ ነው


አማኑኤል ዘሰላም

አቶ ብርሃኑ ወንድማገኝ በነአንዱዋለም አራጌ ላይ ክስ ያቀረበ አቃቤ ሕግ ነው። ይህ የሕግ ሰው ነኝ ባይ ካድሬ፣ በወያኔ ኢቲቪ ቀርቦ «አንዱዋለም አራጌን በተመለከተ፣ የግንቦት ሰባትን ተእልኮ ለማስፈጸም አገር ዉስጥ በሕቡእ (ስዉር) ይንቀሳቀሳል። በሰላማዊ ትግል እንታገላለን የሚሉ የፓርቲዎችን ሽፋን አድርጎ ሲንቀሳቀስ የነበረ በመሆኑ በቂ ማስረጃ አቅርበናል» ሲል ነበር የተናገረው።

አንዱዋለም ያደረጋቸው የነበሩ እንቅስቃሴዎችን በሙሉ ሲያደርግ የነበረው በግልጽና በገሃድ ነዉ። ለተለያዩ ፓልቶክ ክፍሎች፣ አገር ዉስጥና በዉጭ ለሚገኙ ሜዲያዎች በርካታ ቃለ መጠይቆችን ሰጥቷል። በአገር ቤት፣ በአንድነት ፓርቲ ዉስጥ ሆነ በተለያዩ ቦታዎች በተደረጉ ዉይይቶችና ስብሰባዎች ያቀረባቸው ንግግሮች በሙሉ የተደበቁ አይደሉም። ዉጭ ካሉ ኢትዮጵያዊያን ጋር ብዙ ጊዜ በስልክ ሃሳቦችን ተለዋዉጧል። በስልክ ያደረጋቸው ንግግሮችም፣ 24 ሰዓት የሰላማዊ ተቃዋሚ መሪዎችን ስልክ በሚጠልፈው ቴሌ ዘንድ የተሰሙ ናቸው። ቤቱና ቢሮዉ ከላይ እስከ ታች ተበርብረዉ ፣ የሚስጥራዊ የኮሚኒኬሽን መሳሪያዎች፣ ቦምቦች፣ ፈንጂዎች፣ ሚስጥራዊ ሰነዶች አልተገኙም። ኤሜሎቹ በሙሉ ተነበዋል። አንዱዋለምን ከግንቦት ሰባት ጋር የሚያገናኝ፣ በሕቡእ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሆነ የሚያመለክት አንዳች መረጃ አቃቤ ሕግ አላቀረበም። መረጃዎች ቢኖሩ ኖሮ፣ «እንኳን ዘንቦብሽ ድሮም ጤዛ ነሽ» እንደተባለ፣ ዜጎችን በማዋረድና በማሳነስ የሚታወቀዉ የወያኔ ኢቲቪ፣ ይሄን በስፋት ያወራልን ነበር።

አንዱዋለም አራጌ ከታሰረ በኋላ አቃቤ ሕጎች መረጃ ማቅረብ ባለመቻላቸው፣ የዉሸት መረጃዎች ማሰባሰብ የግድ ሆነባቸው። የታሰሩ ሌሎች የአንድነት አባላትን ማግባባት ጀመሩ። «በአንዱዋለም ላይ እኛ ተናገሩ የምንላችሁን ከተናጋራችሁ እንፈታቹሃለን» ብለው እጆቻቸዉን ጠመዘዙ። ብዙዎች በአንዱዋለም ላይ የዉሸት መረጃ ማቅረቡ ሕሊናቸውን ስለከበደው ፍቃደኛ አልሆኑም። ነገር ግን ተስፋሁን አናጋው፣ የሚባል ደካማ ሰው ተገኘና የዉሸት ምስክርነት ቀረበ። እንግዲህ በአገዛዙ ካድሬዎች ተቀናብረው ከቀረቡ የዉሽት ምስክርነቶች ዉጭ፣ ቅንጣት የምታክል፣ አንዱዋለምን ሽብርተኛ ወይንም ከግንቦት ስባት ጋር የሚሰራ መሆኑን የሚያሳይ መረጃ አልቀረበም። ወያኔዎች በዉሽት ምስክርነት ነው የእድሜ ልክ እስራት የበየኑበት። 

የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ለአገር ማሰብ፣ ለመብት መቆም፣ “አንዲት ኢትዮጵያ” ማለት ወንጀል የሆነበት ኢትዮጵያ ናት። ብርቅዬ የተማሩ፣ ከራሳቸው ይልቅ ለሌሎች የሚያስቡ ልጆቿ ወደ ወህኒ የሚወረወሩባት አገር ናት። አሳዛኝ አገር ሆናለች።

ሆኖም ተስፋ የሚሰጡ ብዙ ነገሮች እየታዩ ነው። አንዱዋለም አራጌ ቢታሰርም፣ እጅግ በጣም ብዙ አንድዋለም አራጌዎች ፈርተዋል። እንደ ሃብታሙ አያሌው፣ ዳንኤል ሺበሺ፣ አንጋው ተገኝ፣ ገበየሁ ሲሳይ፣ ስንትየሁ ቸኮል፣ ሃዲያ ሞሃመድ፣ መሳይ ተኩ ..የመሳሰሉ የአንድነት ሰዎች አንዱዋለም አራጌን በወህኒ ተቀላቅለዋል። ሆኖም ሌሎች ብዙ ከየቦታው እየተነሱ ነው። ታጋይ ቢታሰር ትግል አይቆምም። ጥቂቶችን በማሰር የነጻነትና የለዉጥ ጥያቄን ማፈን አይቻልም።

በመሆኑም ከአንዱዋለም አራጌ ጎን እንቆማለን። አላማው አላማችን ነው። እነርሱን “ሽብርተኛ” ቢሉትም ለኛ ወንንድማችን፣ ጀግናች፣ መሪያችን ነው። እኛም አንዱዋለም አራጌዎችን ነን። እርሱ በአካል ድምጹን ማሰማት ባይችልምም፣ እኛ እርሱን ሆነ የነጻነትና የፍትህ ድምጽ እንደ መብረቅ እናስተጋባለን።

አንድዋለም አራጌና ሌሎች ጀግኖቻችን በሙሉ እስኪፈቱ፣ አገራችን ኢትዮጵያም ራሷ እስክትፈታ ትግሉ ይቀጥላል!

Friday, 10 July 2015

የሰሜን ግንባር እየታመሰ ነው!

July 10,2015

(ኢ.ኤም.ኤፍ) የግንቦት ሰባት አርበኛ ጦር በተለይ በሰሜን ኢትዮጵያ የጦር እንቅስቃሴ ማድረግ ከጀመረ በህላ፤ በሰሜን ግንባር የትርምስ ዜናዎች ደርሰውናል። ከዚህ በታች አርበኞች ግንቦት 7 ህዝብ ግንኙነት ያገኘውን መረጃ ዋና ዋናዎቹን እናቀርብላችኋለን።
የአርበኞች ግስጋሴ
የአርበኞች ግስጋሴ
የዳባት ፖሊሶች ታስረዋል
በሰሜን ጎንደር ዳባት ወረዳ ፖሊስ ፅ/ቤት ውስጥ የከረረ ተቃውሞ በፖሊስ አባላቱ በመነሳቱ በርካታ ቁጥር ያላቸው ፖሊሶች መታሰራቸው ተሰማ፡፡
ቅዳሜ ዕለት ሰኔ 27 2007 ዓ.ም ዳባት ወረዳ ፖሊስ ፅ/ቤት በተካሄደው ስብሰባ ላይ የከረረ ተቃውሞ የተነሳ ሲሆን ተቃውሞውን ተከትሎ የበርካታ ፖሊስ አባላት እስር እና ከአካባቢው መሰወር ተከስቷል፡፡
በስብሰባው ላይ የተነሳው ተቃውሞ ዋነኛ ምክንያትና ሰበብ የፖሊስ ፅ/ቤቱ ዋና ኃላፊ ሆኖ የተሾመው ሰው ከትግራይ ክልል የመጣ የህወሓት አባል መሆኑ ነው፡፡
በስብሰባው ላይ ጠንካራ የተቃውሞ ድምፃቸውን ካሰሙት የዳባት ፖሊስ አባላት መካከል ካሳው ማሞ እና ሰጡ እጥናፉ የተባሉት ይገኙበታል፡፡ ካሳው ማሞ እና ሰጡ አጥናፉ “ተጠሪነታችን ለአማራ ህዝብ ሆኖ እያለ ለምን በህወሓት አባል እንመራለን? ተጠሪነታችን ለትግራይ ክልል ፖሊስ ሆኖ ከሆነ የተቋሙን ስም ቀይሩት፤ አለበለዚያ ከስራ አሰናብቱን… ዘረኝነት ይቁም…” በማለት ተናግረዋል፡፡
ከስብሰባው በኋላ ካሳው ማሞንና ሰጡ አጥናፉን ጨምሮ በስብሰባው ላይ የዘረኝነት አገዛዝ ተቃውሞ ድምፃቸውን ያሰሙ በርካታ የዳባት ፖሊስ አባላት እግረ ሙቅ እያጠለቁ ወደ ዘብጥያ ወርደዋል፡፡ ሦስት ፖሊሶች ደግሞ ድንገት ከአካባቢው የተሰወሩ ሲሆን በህወሓት ይታፈኑ ወይንም አምፀው ወደጫካ ይውጡ እስካሁን ምንም የታወቀ ነገር የለም፡
በህወሓቶች ቤት ውስጥ ታላቅ ሽብር ነግሷል
ከወልቃይቱ /ቃፍታ መሲን፣ ኮርጃሙስ፣ ማይ ሰገን፣ በዋል፣ ንኳል ሳግላ እና ማይ እምቧ…/ የአርበኞች ግንቦት 7 ወታደራዊ እርምጃ በኋላ ማለስልጣናቱ እንደተነፈሰ ፊኛ በመልፈስፈስ ኩምትርትር ጭምትርትር ብለዋል፡፡
የጦርነት ደመና ካጠላበት የኢትዮጵያ ጠቁር ሰማይ ስር በፍርሃት ተሸብበው የሚገኙት የህወሃት ባለስልጣናት እና ጀነራሎች የጨነቃቸውን ያክል ሰራዊቱን ወዲያ ወዲህ በማተራመስና በማንጓለል በድሃ ልጅ ዥዋዥዌ በመጫዎት ላይ ናቸው፡፡ ኤታማጆር ሹሙ “ጀነራል” ሳሞራ የኑስ ሰራዊቱ ኋላቀር እንደሆነ ህወሓቶች ባደረጉት ምስጢራዊ ስብሰባ ላይ አምኗል፡፡
አርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዴሞክራሲ ንቅናቄ ወታደራዊ እርምጃ መውሰድ ከመጀመሩ ከወራት በፊት ግን አገሪቱ በወታደራዊ አቅሟ ከዓለም አገሮች ጋር ተወዳድራ ከዓለም በ46ኛ ከአፍሪካ ደግሞ በ4ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች ብለው ያን የተለመደ የፕሮፖካንዳ ቱልቱላቸውን ነፍተው ነበር፡፡
አሁን ኋላቀር በማለት ያጣጣሉትን ለእርድ የተዘጋጀ ሰራዊት በአራቱም የአገሪቱ ማዕዘናት እየበተኑት ይገኛሉ፡፡ የሰሞኑ ወደ ሰሜን የሚደረገው እንቅስቃሴ እንዳለ ሆኖ ትናንት ጠዋት ከአዋሳ በሀገረ ማርያም በኩል ወደ ሞያሌ እና ሌሎች ጠረፎች አካባቢ በርካታ ሜካናይዝድና እና እግረኛ ጦር እንዲሁም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ፌደራል ፖሊስ ተጭኖ ተልኳል፡፡
የኦነግ ጎሬላ ተዋጊዎች፡
የሀገረ ማርያም ዓይን እማኞች 26 አሮጌ ታንኮች በሚንገራገጭ ድምፃቸው አካባቢውን በማወክ እንደ ኤሊ እያዘገሙ ሲያልፉ መቁጠራቸውን ለዜና ምንጮቻችን ተናግረዋል፡፡ ወደ ዚህ አካባቢ ጦር በገፍ እየተጫነ የሚገኘው የኦነግ ጎሬላ ተዋጊዎች ጥቃት ለመክፈት እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ የሚያረጋግጥ መረጃ ስለደረሳቸው መሆኑ ታውቋል፡፡
ከአፋር ነፃ አውጭዎቹ አርዱፍና ጋዲሌ ጋር በመቀናጀት ኦብነግ በአፋር ክልል ሰርጎ እንደገባ የሚያመላክት መረጃም ጭምር ስለደረሳቸው ወደ አፋር ክልልም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ጦር እያጓጓዙ ይገኛሉ፡፡
ከዚህ መተራመስና መታመስ ጋር ተያይዞ ጦር እየመሩ በየማዕዘናቱ በሚላኩት ወታደራዊ አዛዦችና የበላይ አለቆቻቸው መካከል የተካረረ ፀብ እየተፈጠረ መሆኑን ከመከላከያ ምንጮቻችን የደረሰን መረጃ ያረጋግጣል፡፡ የፀቡ መንስኤ እያንዳንዱ አዝማች “የተመደበልኝ የሰው ሃይል እንዲሁም ትጥቅና ስንቅ ያንሰኛል…” የሚል ሰበብ ማንሳቱ መሆኑ ታውቋል፡፡ ይህም የሚያመላክተው የህወሓት ወታደራዊ አዛዦች ወኔያቸውን መሽናታቸውን ነው፡፡
አፈናው ቀጥሏል
በሌላ በኩል ደግሞ የህወሓት ዘረኛ ቡድን ሰራዊት ከማተራመሱ ጎን ለጎን ህዝብ በገፍ እያፈነ ወዳልታወቀ ቦታ ይዞ መሰወሩን በርትቶበታል፡፡ በተለይም አዲስ አበባ፣ ባህር ዳር ጎንደር… በርካታ ሰዎች በታጠቁ ኃይሎች እየታፈኑ ወዳልታወቀ ቦታ በመወሰድ ላይ ናቸው፡፡
የሰሜን ጎንደር ዞን የአንድነት ፓርቲ ሰብሳቢ የነበረውና ጎንደር መምህራን ኮሌጅ ውስጥ የሚያስተምረው መምህር አለላቸው አታለለ ትናንት ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ የህወሓት የታጠቁ ቡድኖች ወደ መኖሪያ ቤቱ ገብተው አፍነው ወስደውታል፡፡ መምህሩ እስካሁን ድረስ የት እንዳለ አይታወቅም፡፡
በተጨማሪም የጎንደር እና አካባቢውን ገበሬዎች የህወሓት ካድሬዎች ዋጋውን መቶ በመቶ ቅድሚያ ካልከፈላችሁ በማለት ማዳበሪያ እንዳይወስዱ ከልክለዋቸዋል፡፡ ገበሬው የባሰውኑ በህወሃት ልቡ ሻክሯል…

Wednesday, 8 July 2015

ጥብቅ መልእክትና ማሳሰቢያ ለሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ

 ( አርበኞች ግንቦት ሰባትና ደህሚት ሰራዊት)

የአርበኞች ግንቦት ሰባትና ደህሚት ሰራዊት ዉድ የሆነችዉን ህይወታቸዉን ከፍላዉ ኢትዮጵያን ከዘረኛዉ፤ከከፋፋዪ፤ እዉነትና እዉቀት ከራቃቸዉ ጥቂት የባነዳ ልጆች ነፃ ለማዉጣትና የተከበረች፤ የተፈራች፤ ለዜጎቿ ምቹ የሆነች፤ ሁሎም ልጆቿ የሚቧርቁባትንና የሚበለፅጉባትን ኢትዮጵያን ለመመስረት ትግሉን መጀመሩን የሰማችሁ ይመስለናል፡፡ አገር ቤት ላለዉ ዘመዶቻችን መልእክቱን ንገሩ፡፡
በአርበኞች ግንቦት 7 አባል የማስተላልፈዉ ማሳሰቢያና ማስጠንቀቂያ የሚከተለዉን ይመስላል፡፡
1. በ ሚያዚያ ወር 2007 ዓም ወያኔ የግል የጦር መሳሪያ ምዝገባ እንዳካሄደ ይታወቃል፡፡ ይህን መሰረት አድርጎ በወያኔ ሎሌወችና ባንዳዎች መሰረት መሳሪያህን ሊያስወርድህ እንደሆነ ሰሞኑን ከአገኘሁት የደህንነት ሚስጥር አካፍልሀለሁ፡፡ ባነዳወችን በጥንቃቄ ተከታተል፡፡ ኢትዮጵያዊ ዋናዉ ጀግንነቱ ርስቱና ነፃነቱ የሆነችዉን የጦር መሳሪያዉን ለማንም ባንዳ የሚያስረክብ ስነ-ልቦና እንደሌላዉ ታሪካችን ያስረዳልና የታሪክ ተወቃሽ እንዳትሆኑ ንቁና ባንዳዎችን ተከታተሉ፡፡ ማንንም የወያኔ ባንዳ እንዳታምኑ፡፡ መሳሪያህን ሊያስወርድ ከሞከረ በቡድን ሁነህ ለነፃነትህ ሸፍት ፡፡ የወያኔ ሰራዊትን በቡድን ሁነህ በማጥቃት መሳሪያዉን ተረከብ ነገር ግን የወንድምህን ህይወት በከንቱ እንዳትቀጥፍ ተጠንቀቅ፡፡ ቤት ያፈራዉን መግበዉ ልብስም አልብሰዉ፡፡ የነፃነት ታጋዮችን እንዲቀላቀልም መንገድ ምራዉ፡፡
2. የወያኔ ቁጥር አንድ ተላላኪ ባንዳ ሀይለማርያም ደሳለኝ ጦርነቱን ከወንድማችንና ከእህታችን የኤርትራ መንግስትና ህዝብ ነዉ ሲል 100 ፐርሰንት የግሉ ባደረገዉ የዝንጀሮዉ ምክርቤት ጋር መምከሩን በ ኢትዮጵያ ስም በሚነግድበት ቴሌቪዝንና ሬድዮ ማስተላለፉ ይታወቃል፡፡ ይህ የተለመደ ቀልድ ነዉ፡፡ ይህ የነፃነት ጦርነት 100 ፐርሰንት የምርጫ ካርዱን ከ 1997 ጀምሮ ለሶስት ተከታታይ ምርጫ በተዘረፈዉ የኢትዮጵያ ህዝብ የቁርጥ ቀን ልጆችና ጥቂት በስርአቱ የበለፀጉና የህዝብን ገንዘብ ለግል ጥቅማቸዉ ካደረጉ ወያኔዎች፤ባንዳዎችና ተላላኪዎች መካከል እንጂ ከ ኤርትራ ህዝብና መንግስት ጋር አይደለም፡፡ የኤርትራን ህዝብ ሞክሩት እኛም ከጎናቸዉ እንሆናለን፡፡ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት የቀለዳችሁብንን አንረሳዉም፡፡ የባድመ መሬት ሲወረር ሉአላዊ ግዘታችን ተወረረ ብላችሁ የጎንደር ድንበርን መሬት ለሱዳን ሰጥታችሁ ቁራጭ መሬት እያላችሁ መቀለዳችሁን አትርሱት፡፡ ለኢትዮጵያ ሉአላዊነት ብትጨነቁ ሱዳን ላይ እንዝመት ትሉን ነበር፡፡
3. በአንዳንድ  ከተሞች የትግራይን ህዝብ ይሁንታ ለማግኘት በግንቦት ሰባትና በሌላዉ ብሄር ስም ( በተለይም በአማራዉ) ወያኔ በትግረኛ ተናጋሪዎች ድርጅትና ነብስ በድብቅ በመግደልና ድርጅታቸዉን በቦንብ በማፈራረስ የትግራይ ህዝብ እንዲነሳና ሌላዉም ህዝብ ይህን እኩይ ተግባር በመኮነን ከነፃነት ታጋዮች እንዳይሰለፍ የተለመደ በሀዉዜን ህዝብ ላይ የሰራዉን ሴራ ሊሰራ መዘጋጀቱንና የዶኪመንተሪ ፊልምም ሊሰሩ ስለተዘጋጁ የትግይ ተወላጅ የሆናችሁና በሌላዉ ክልልና በትግራይ የምትኖሩ ትግረኛ ተናጋሪወች ጥንቃቄ እንድታደርጉ አደራ እንላለን፡፡ ወያኔ መቸዉንም ቢሆን መጀመሪያ የሚነግደዉ በእናንተ ደምና ስም ነዉ፡፡ ሌላዉም ብሄር በወያኔ ፕሮፖጋንዳ የደነዘዛችሁ በወንድሞቻችሁንና በእህቶቻችሁን ላይ ምንም አይነት እርምጃ እንዳትወስዱ አደራ እያልን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ከማኝኛዉም ጥቃት እንድትጠብቁና ኢትዮጵያዊ ግዴታችሁን እንድትወጡ አደራ እንላለን፡፡
4. ወያኔ ሰሞኑን ዉድ የኢትዮጵያ ልጆችን ለዚህ ቅዱስ ጦርነት በየቀበሌዉ ማስታወቂያ ለጥፎ እየመለመለ ወደ ስልጠና ጣቢያዎች ከማስገባቱም በላይ አምስት ወር ያለሞላቸዉን ሰልጣኞችን ወደ ግንባር እያመላለሰ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ ልጆችህን ለዚህ የሰይጣን አማልክት ለሚከተሉ የባንዳ ልጆች እንዳትልክ ማስገንዘብ እንፈልጋልን፡፡ ግንባር ላይ ላለዉ ልጅህም መሳሪያዉን ወደ ባንዳዎች እንዲያዞር መልክት ላክ፡፡
5. ተደራጅታችሁ በሲቪል መስሪያ ቤቶችና በግል ተቋማት ዘረፋ ሊካሄድ ስለሚችል ባንኮችን፤ ሆቴሎችን፤ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ከዘረፋ ጠብቁ፡፡ ለተወሰነም ጊዜ ቢሆን ቤታችሁ ዉስጥ ችግር እንዳይኖር የምትመገቡትን አዘጋጁ፡፡ የደርግ መንግስት ሲወድቅ የትምህርት ቤት ወንበርና ጠረጴዛ የሀክምና ተቋማት ቁሳቁስ ሳይቀር መዘረፉን እንዳትረሳ፡፡ አገራችንን ከዜሮ መጀመር ሸክሙ ለእኛዉ ነዉ፡፡
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ
ምንጭ ethiopianvoices.

Friday, 3 July 2015

በህወሓት አገዛዝ እየተሰቃዩ ላሉ ወገኖቻችን ደህንነት የሚደረገው ዓለም አቀፍ ጫና ይቀጥል!

July 3, 2015
def-thumb
ከሣምንት በፊት የብሪታኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን የሚመለከት አንድ መግለጫ አውጥቷል። በዚህ መግለጫው፣ አንዳርጋቸው ጽጌ ለአንድ ዓመት ሙሉ መሠረታዊ የሆኑ የታሳሪዎች መብት እንኳን ተነፍጎት ባልታወቀ እስር ቤት የሚገኝ መሆኑ እና በእንግሊዝ ባለሥልጣናትና በቤተሰቦቻቸው እንዲጠየቅ፣ ቋሚ የቆንስላና የህግ ምክር እንዲያገኝ በተደጋጋሚ የቀረበው ጥያቄ በወያኔ አገዛዝ ውድቅ መደረጉ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው መልካም ግንኙነት የሚያሻክር መሆኑ ከወትሮው ጠንከር ባሉ ቃላት ገልጿል። አዲስ አበባ የሚገኘው የብሪታኒያ አምባሳደርም እንደዚሁ ከተለመደው ዲፕሎማሲያዊ ለስላሳነት ወጣ ያለ ያለ መግለጫ አዲስ አበባ ውስጥ ለሚታተመው ሪፓርተር ጋዜጣ ሰጥቷል። እነዚህ የሰሞኑ የእንግሊዝ መንግሥት መግለጫዎች በቀና የሚታዩ ቢሆንም የብሪታኒያ መንግሥት ማድረግ ይገባው ከነበረው እና ማድረግ ከሚችለው አንፃር ሲታይ ብዙ ይቀረዋል። የአውሮፓ ኅብረት የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጉዳይ በተደጋጋሚ አንስቷል። የተባበሩት መንግሥታትም የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ አያያዝ ጉዳይ ምርመራ እንዲደረግበት እንቅስቃሴ ጀምሯል። ከላይ የተዘረዘሩት ኩነቶች፣ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ያለሟቋረጥ የሚያደርጉት ውትወታ ውጤት እያመጣ መሆኑ ያሳያል። ይህ ጥረት ለወደፊቱም ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።

በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ “አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ አስልጥኖ አሰማርቷችኋል” ተብለው እንደተለመደው በሀሰት የተከሰሱ ወገኖቻችን “አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ኢትዮጵያ ውስጥ ስለሚገኙ መከላከያ ምስክር እንዲሆኑን ይታዘዝልን“ ብለው ሲጠይቁ ዳኛ ተብየው “የት እንደሚገኙ የማይታወቁ ሰውን በመከላከያ ምስክርነት ማቅረብ ይከብዳል” ብሎ ሲናገር ተደምጧል። አቶ አንዳርጋቸው ለምስክርነት ይቅረብ አይቅረብ ብይን ሊሰጥበት ቀጠሮ ተይዟል።
አርበኞች ግንቦት 7፡ የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ፣ የነፃነት አርበኛው የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የእስር አያያዝ ሁኔታ ዓለም ዓቀፍ የዲፕሎማሲ አጀንዳ በሆነበት በዚህ ወቅት በህወሓት አገዛዝ በተሾመ ዳኛ “የት እንደሚገኙ የማይታወቁ” መባሉ አሳሳቢ ጉዳይ አድርጎ ይመለከተዋል። አርበኞች ግንቦት 7፣ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን የተከሳሾች፣ የአቃቤ ህጉና የዳኛው ምልልስ ለተባበሩት መንግሥታት፣ ለአውሮፓ ኅብረትና ለእንግሊዝ መንግሥት እንዲደርስ እንዲያደርጉም ያሳስባል።
አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ብቻ ሳይሆን በህወሓት እስርቤቶችና ከእስር ቤቶች ውጭ ባልታውቁ ቦታዎች ታስረው እየተሰቃዩ የሚገኙ ወገኖቻችን ሁሉ እና መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃ የሚወጣው፣ ኢትዮጵያዊያን በሚያደርጉት ሁለገብ ትግል ነው ብሎ አርበኞች ግንቦት 7 ያምናል። ስለሆነም ራሳችንን፣ ወገኖቻችንና አገራችን ነፃ ለማውጣት የምናደርገው ትግል ማጠናከር ግዴታችን ነው። እኛ ራሳችን እንጂ ማንም ነፃነታችንን አያጎናጽፈልንም።
ይህ እንዳለ ሆኖ ግን የህወሓትን እኩይ ተግባራት በዓለም አደባባዮች ማጋለጥ፤ የህወሓት አገዛዝን ወዳጅ ማሳጣት እና በእስር ላይ የሚገኙ ወገኖቻችንን ደህነት የሚያሻሽሉ ተጽዕኖዎችን መፍጠር እጅግ አስፈላጊ ተግባር በመሆኑ፣ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን፣ በህወሓት እጅ ለወደቁ ወገኖቻችን ድጋፍ የሚያሰሙትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ያሳስባል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

የሳሙኤልን ገዳይ መደበቅ ያልቻለው ድራማ

ጌታቸው ሺፈራው
ዜጎች በተራ ‹‹ወንጀል›› 14 ከዚህ አለፍ ሲል 28 ቀን እየተቀጠሩ በሚመላለሱበትና በሚጉላሉበት ሀገር፣ አባሪው እንኳ ባልተያዘበት ሁኔታ፣ ይህ ነው የሚባል ምርመራ ሳይደረግ የሳሙኤል አወቀ ገዳይ በ17 ቀን ውስጥ 19 አመት እስራት እንደተፈረደበት ተሰምቷል፡፡ ትናንት ችሎቱን የተከታተሉት ሰዎች በግምት ከምሽቱ ሶስት ሰዓት አካባቢ አዲስ አበባ ለሚገኙት የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች የነበረውን ድራማ በስልክ ሪፖርት ያደርጋሉ፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችን ስልክ የሚጠልፈው ኢህአዴግ ሪፖርቱ ‹‹ሳሙኤልን አልገደልነውም›› የሚለውን ድራማቸውን የሚያራክስ መሆኑን ተረድቷል፡፡ የፍርድ ቤቱ ድራማ ቀድሞ በሰማያዊ በኩል እንዳይወጣ ጉዳዩ ለሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች ሪፖርት ከተደረገ ከደቂቃዎች በኋላ በራሱ ካድሬዎች በኩል ቀድሞ ‹‹ፍርዱን!›› ይፋ አደረገ፡፡ ዛሬ ደግሞ እነ ፋና እየተረባረቡበት ነው፡፡ ከምንም በላይ ወንጀሉን የግል ሲያደርጉት ድምፀታቸው ግን ሳሙኤልን ማን እንደገደለው ግልጽ እያደረገባቸው ነው፡፡
ሳሙኤል አወቀ ከአንድ አመት በላይ ካድሬዎችና ደህንነቶች ‹‹እንገድልሃለን›› እያሉ እየዛቱበት መሆኑን በማህበራዊ ገጹ አስቀምጧል፡፡ በፖለቲካ አመለካከቱ ምክንያት በፖሊስ ታድኖ ታስሯል፡፡ ከሀገር ውጣልን ብለውት ‹‹አልሰደድም›› ብሎ ነገረ ኢትዮጵያ ላይ ጽፏል፡፡ ከደህንነት፣ ካድሬዎችና የፖሊስ አዛዦች የሚደርስበት ማስፈራሪያና ዛቻ ከሶስት ጊዜ በላይ በነገረ ኢትዮጵያ ተዘግቧል፡፡ ለአብት ያህል ሰኔ 10/2006 ዓ.ም ነገረ ኢትዮጵያ ላይ ‹‹ጠበቃው በፖሊስ እየታደነ ነው›› በሚል ዜና ‹‹ህዝብ እየተበደለ ነው ብለህ የአስተያየት መስጫ ሳጥን ላይ አስተያየት ሰጥተሃል:: አገር ለቀህ ካልተሰደድክ እንገድልሃለን›› መባሉ በዋቢነት ተቀምጧል፡፡
የደንበኞች አስተያየት መስጫ ላይ የጻፍከው አንተ ነህ ተብሎ በተከሰሰበት ወቅት የምስራቅ ጎጃም ዞን ፍትህ መምሪያ ኃላፊ አቶ ሸጋዬ መንግስቴ ዳኞች በተገኙበት ‹‹በማንኛውም ጊዜ መንገድ ላይ ይዛችሁ ማሰር ትችላላችሁ፡፡ ዴሞክራሲያዊም ሆነ ሰብአዊ መብት የሚባል አይሰራም›› ብለውታል፡፡ የደብረማርቆስ ፖሊስ ኮማንደር ‹‹አስደፋሃለሁ!›› ብሎ ዝቶበታል፡፡ ከመገደሉ አንድ ወር በፊት እግሩን ሰብረውታል፡፡ ከመገደሉ ሁለት ሳምንት በፊት በተፈጠረበት ከፍተኛ ስጋት ‹‹ብታሰርም መንፈሴ አይታሰርም፣ ከገደሉኝም ትግሌን አደራ›› ሲል ተናዝዟል፡፡
ሳሙኤል አወቀ ድብደባ ሲፈፀምበት፣ ከዛም በኋላ ሲገደል በድንገት መብራት መጥፋቱን የአካባቢው ነዋሪዎች እማኝነታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ሳሙኤል አወቀ የተገደለው ከምሽቱ 1፡30 አካበቢ ነው፡፡ በዚህ ወቅት እሱን ሌት ተቀን ይከታተሉት የነበሩት ፖሊሶች እንኳን በቦታው አልነበሩም፡፡ የተገደለው መሃል ከተማው ላይ ሆኖ እያለ ፖሊስ የደረሰው ከአንድ ሰዓት ተኩል በኋላ ከምሽቱ 3 ሰዓት ላይ ነው፡፡ ከ1፡30 በኋላም በቦታው የደረሰው ፖሊስም ሳሙኤልን በግል የሚያውቀው መሆኑ ምን አልባት ‹‹አርፈህ ተቀመጥ!›› ተብሎም ስላልቻለ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ያም ሆኖ ተሰቃይቶ እንዲሞት ስለተፈለገ በሚመስል መልኩ ፖሊስ ደርሶ እስኪጣራ ተብሎ ሀኪም ቤት እንዳይደርስ ተደርጓል፡፡
የሳሙኤል አወቀ ገዳዮች ከተባሉት መካከል አንዱ ወዲያውኑ ማታ እንደተያዘ ተነገረ፡፡ ተባባሪዎቹ ግን ሊያዙ አልቻሉም፡፡ እንግዲህ ተባባሪዎቹ ባልተያዙበት፣ በዚህ ፍትህ በሚራዘምበት ሀገር የሳሙኤል አወቀን ገዳይ ሰኔ 25/2007 ዓ.ም በተገደለ በ17 ቀን ውስጥ የ19 አመት እስር ተፈርዶበታል ተብሏል፡፡ በትናንትናው ዕለት በዋለው ችሎት የሳሙኤል ቤተሰቦችና ሌሎች ወጣቱን የሚያውቁት ግለሰቦችም ተገኝተው እንደታዘቡት፣ አቶ ተቀበል ገዱ 19 አመት ተፈረደበት በተባለበት ችሎት ዳኛው ስለ ፍርድ ሂደቱ ምንም ነገር አላነበቡም ተብሏል፡፡ ፍርዱ ሲነበብ ሳሙኤል እንዴት እንደተገደለ በምርመራና በፍርድ ሂደቱ የተገኙት ሀቆች መገለጽ አለባቸው፡፡ ግን ደግሞ የሚያሳጡ ሆኑና በፍጥነት 19 አመት እንደተፈረደበት ተናግረው ወጥተዋል፡፡
ገዳይ ተብሎ የተያዘው አቶ ተቀበል ገዱ ‹‹እኔ ሳሙኤል አወቀ የሚባለውን ሰው አላውቀውም፡፡ ግደለው ተብዬ ገንዘብ ስለተሰጠኝ ነው የገደልኩት፡፡›› ማለቱ ከእስር ቤት ሾልኮ ወጥቷል፡፡ ‹‹ማን ነው ገንዘቡን የከፈላችሁ?›› ሲባል ደግሞ ‹‹እኔ እሱንም አላውቀውም፡፡ ለእኔ ገንዘቡን የሰጠኝ ያልተያዘው ጓደኛዬ ነው፡፡ እንድንገድልለት የፈለገውም ሰውም የሚያውቀው እሱ ነው›› ማለቱን እስረኞቹ ተናግረዋል፡፡
በተመሳሳይ ከዚህ በፊት በዋለ ሌላ ችሎት ገዳይ የተባለው ሰው ‹‹ለምን ገደልከው?›› ሲባል ሻይ ቤት ውስጥ በተፈጠረ አለመግባባት ሳሙኤል ቀድሞ በዱላ ስለመታው እንደገደሉት ገልጾአል፡፡ ይሁንና ይህ ከሳሙኤል ግላዊ ባህሪ ጋር የሚሄድ አይደለም፡፡ ይህንንም ገዳይ ተብሎ የተያዘውና የተፈረደበት አቶ ተቀበል ገዱ እንደገና እጁን አውጥቶ ዳኛው እድል ሲሰጡት ‹‹ቅድም ሻይ ቤት ውስጥ ስለተጣላን ነው የገደልኩት ያልኩት አቃቤ ህጉ በል ስላለኝ ነው፡፡ አላውቀውም፡፡›› እንዳለ ችሎቱን የተከታተሉት ይናገራሉ፡፡

ሳሙኤል በተገደለ ማግስት ካድሬዎች ግድያው ከጥብቅና ጋር በተያያዘ ነው በሚል ጉዳዩን ከኢህአዴግ ካድሬዎችና ደህንነቶች እራስ ለማውረድ ጥረው ነበር፡፡ በወቅቱም ሳሙኤል የተገደለው ለጥብቅና ቆሞለት ከነበረው አርሶ አደር ጋር አለመግባባት በመፈጠሩ ነው እያሉ ለማስመሰል ጥረዋል፡፡ ይሁንና በትናንትናው የፍርድ ቤት ውሎ ፍርድ ቤቱ ለገዳዩ ማቅለያ ሲያቀርብ ‹‹የቀን ሰራተኛ በመሆንህና በዚህ ስራም ቤተሰብን የምትደጉመው አንተ በመሆንህ አንቀፁን ከ38 ወደ 31 አውርደንልሃል›› ሲሉ ተደምጧል፡፡ በዚህም መጀመሪያ ካሉት ከአርሶ አደርነት ወደ ቀን ሰራተኝነት ቀይረውታል፡፡ ይህም መጀመሪያ ግድያው ፖለቲካዊ አይደለም ለማለት ካድሬዎች ከደንበኝነት ጋር ያያዙትን ውድቅ የሚያደርግ ነው፡፡ በእርግጥ የውስጥ ምንጮች እንደሚሉት መጀመሪያ አካባቢ አቃቤ ህግ ሳሙኤል የተገደለው ከደንበኝነት ጋር በተያያዘ ለማስመሰል ጥረው ነበር፡፡ ይህኛው ድራማ አላስኬድ ሲል በትዕዛዝ እንዲቋረጥ ተደርጓል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሳሙኤል አወቀን ቤተሰቦች ለማስተዛዘን ወደ ጎጃም ያቀኑት የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችና አባላት አባይ በርሃ ላይ ተይዘው እስከ ምሽቱ 2፡30 ከታሰሩ በኋላ ቢፈቱም ወደ ለቅሶው እንዳይሄዱ መኪና እና ቁሳቁሶቻቸውን መነጠቃቸው ይታወሳል፡፡ በወቅቱ መርማሪዎቹ በተደጋጋሚ ይጠይቁት የነበረው ጥያቄ ‹‹ሳሙኤልን ማን ገደለው?›› የሚል ነበር፡፡ ይህም የሚያሳየው መረጃዎች ያጋለጡትን የሳሙኤል ገዳይ በድራማ ለመደበቅ ያደረጉት መንደፋደብ ነው፡፡ ከመጀመሪያው ጀምሮ እስከ ትናንትናው የፍርድ ውሎና አሁንም ድረስ የቀጠለው ፕሮፖጋንዳ የሚያሳየው ሳሙኤል በፖለቲካ አመለካከቱ የተገደለ መሆኑን ነው፡፡ ይህን ለመሸፈን ፍርድ ቤት አድርጎት የማያውቀውን እጅግ የተፋጠነ ‹‹ፍርድ›› ሰጥቷል፡፡ መጀመሪያ ከደንበኝነት ጋር በተያያዘ ነው የተገደለ ብለው አሁን የማያውቀው የቀን ሰራተኛ ነው የገደለው ብለዋል፡፡ እነሱ ‹‹ሻይ ቤት ውስጥ ተጣልተን ነው የገደልኩት›› እንዲልላቸው ቢፈልጉም እሱ ግን እንደገና ‹‹ይህን እነሱ ናቸው በል ያሉኝ›› ብሎ መስክሮባቸዋል፡፡ ገዳይ ተብሎ ለተያዘው ሰው ገንዘብ የሰጠው አባሪ አልተያዘም፡፡ በእርግጠኝነት አምልጦ አይመስለኝም፡፡ ግድያውን ካቀነባበረው ሰው ጋር የሚያገናኝ ድልድይ በመሆኑ እንዳይያዝ ስለሆነ እንጅ፡፡ ሆኖም ይህ ሁሉ ድራማ ገዳዩን መደበቅ አልቻለም፡፡ ከምንም በላይ ድራማው ሳሙኤል ባለፈው አንድ አመት በሚዲያና በማህበራዊ ደረ ገጹ ያሰፈራቸው እማኝነቶችና ሌሎችን መረጃዎች ያጋለጡትን ገዳይ መደበቅ አልቻለም፡፡