Friday, 3 July 2015

የሳሙኤልን ገዳይ መደበቅ ያልቻለው ድራማ

ጌታቸው ሺፈራው
ዜጎች በተራ ‹‹ወንጀል›› 14 ከዚህ አለፍ ሲል 28 ቀን እየተቀጠሩ በሚመላለሱበትና በሚጉላሉበት ሀገር፣ አባሪው እንኳ ባልተያዘበት ሁኔታ፣ ይህ ነው የሚባል ምርመራ ሳይደረግ የሳሙኤል አወቀ ገዳይ በ17 ቀን ውስጥ 19 አመት እስራት እንደተፈረደበት ተሰምቷል፡፡ ትናንት ችሎቱን የተከታተሉት ሰዎች በግምት ከምሽቱ ሶስት ሰዓት አካባቢ አዲስ አበባ ለሚገኙት የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች የነበረውን ድራማ በስልክ ሪፖርት ያደርጋሉ፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችን ስልክ የሚጠልፈው ኢህአዴግ ሪፖርቱ ‹‹ሳሙኤልን አልገደልነውም›› የሚለውን ድራማቸውን የሚያራክስ መሆኑን ተረድቷል፡፡ የፍርድ ቤቱ ድራማ ቀድሞ በሰማያዊ በኩል እንዳይወጣ ጉዳዩ ለሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች ሪፖርት ከተደረገ ከደቂቃዎች በኋላ በራሱ ካድሬዎች በኩል ቀድሞ ‹‹ፍርዱን!›› ይፋ አደረገ፡፡ ዛሬ ደግሞ እነ ፋና እየተረባረቡበት ነው፡፡ ከምንም በላይ ወንጀሉን የግል ሲያደርጉት ድምፀታቸው ግን ሳሙኤልን ማን እንደገደለው ግልጽ እያደረገባቸው ነው፡፡
ሳሙኤል አወቀ ከአንድ አመት በላይ ካድሬዎችና ደህንነቶች ‹‹እንገድልሃለን›› እያሉ እየዛቱበት መሆኑን በማህበራዊ ገጹ አስቀምጧል፡፡ በፖለቲካ አመለካከቱ ምክንያት በፖሊስ ታድኖ ታስሯል፡፡ ከሀገር ውጣልን ብለውት ‹‹አልሰደድም›› ብሎ ነገረ ኢትዮጵያ ላይ ጽፏል፡፡ ከደህንነት፣ ካድሬዎችና የፖሊስ አዛዦች የሚደርስበት ማስፈራሪያና ዛቻ ከሶስት ጊዜ በላይ በነገረ ኢትዮጵያ ተዘግቧል፡፡ ለአብት ያህል ሰኔ 10/2006 ዓ.ም ነገረ ኢትዮጵያ ላይ ‹‹ጠበቃው በፖሊስ እየታደነ ነው›› በሚል ዜና ‹‹ህዝብ እየተበደለ ነው ብለህ የአስተያየት መስጫ ሳጥን ላይ አስተያየት ሰጥተሃል:: አገር ለቀህ ካልተሰደድክ እንገድልሃለን›› መባሉ በዋቢነት ተቀምጧል፡፡
የደንበኞች አስተያየት መስጫ ላይ የጻፍከው አንተ ነህ ተብሎ በተከሰሰበት ወቅት የምስራቅ ጎጃም ዞን ፍትህ መምሪያ ኃላፊ አቶ ሸጋዬ መንግስቴ ዳኞች በተገኙበት ‹‹በማንኛውም ጊዜ መንገድ ላይ ይዛችሁ ማሰር ትችላላችሁ፡፡ ዴሞክራሲያዊም ሆነ ሰብአዊ መብት የሚባል አይሰራም›› ብለውታል፡፡ የደብረማርቆስ ፖሊስ ኮማንደር ‹‹አስደፋሃለሁ!›› ብሎ ዝቶበታል፡፡ ከመገደሉ አንድ ወር በፊት እግሩን ሰብረውታል፡፡ ከመገደሉ ሁለት ሳምንት በፊት በተፈጠረበት ከፍተኛ ስጋት ‹‹ብታሰርም መንፈሴ አይታሰርም፣ ከገደሉኝም ትግሌን አደራ›› ሲል ተናዝዟል፡፡
ሳሙኤል አወቀ ድብደባ ሲፈፀምበት፣ ከዛም በኋላ ሲገደል በድንገት መብራት መጥፋቱን የአካባቢው ነዋሪዎች እማኝነታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ሳሙኤል አወቀ የተገደለው ከምሽቱ 1፡30 አካበቢ ነው፡፡ በዚህ ወቅት እሱን ሌት ተቀን ይከታተሉት የነበሩት ፖሊሶች እንኳን በቦታው አልነበሩም፡፡ የተገደለው መሃል ከተማው ላይ ሆኖ እያለ ፖሊስ የደረሰው ከአንድ ሰዓት ተኩል በኋላ ከምሽቱ 3 ሰዓት ላይ ነው፡፡ ከ1፡30 በኋላም በቦታው የደረሰው ፖሊስም ሳሙኤልን በግል የሚያውቀው መሆኑ ምን አልባት ‹‹አርፈህ ተቀመጥ!›› ተብሎም ስላልቻለ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ያም ሆኖ ተሰቃይቶ እንዲሞት ስለተፈለገ በሚመስል መልኩ ፖሊስ ደርሶ እስኪጣራ ተብሎ ሀኪም ቤት እንዳይደርስ ተደርጓል፡፡
የሳሙኤል አወቀ ገዳዮች ከተባሉት መካከል አንዱ ወዲያውኑ ማታ እንደተያዘ ተነገረ፡፡ ተባባሪዎቹ ግን ሊያዙ አልቻሉም፡፡ እንግዲህ ተባባሪዎቹ ባልተያዙበት፣ በዚህ ፍትህ በሚራዘምበት ሀገር የሳሙኤል አወቀን ገዳይ ሰኔ 25/2007 ዓ.ም በተገደለ በ17 ቀን ውስጥ የ19 አመት እስር ተፈርዶበታል ተብሏል፡፡ በትናንትናው ዕለት በዋለው ችሎት የሳሙኤል ቤተሰቦችና ሌሎች ወጣቱን የሚያውቁት ግለሰቦችም ተገኝተው እንደታዘቡት፣ አቶ ተቀበል ገዱ 19 አመት ተፈረደበት በተባለበት ችሎት ዳኛው ስለ ፍርድ ሂደቱ ምንም ነገር አላነበቡም ተብሏል፡፡ ፍርዱ ሲነበብ ሳሙኤል እንዴት እንደተገደለ በምርመራና በፍርድ ሂደቱ የተገኙት ሀቆች መገለጽ አለባቸው፡፡ ግን ደግሞ የሚያሳጡ ሆኑና በፍጥነት 19 አመት እንደተፈረደበት ተናግረው ወጥተዋል፡፡
ገዳይ ተብሎ የተያዘው አቶ ተቀበል ገዱ ‹‹እኔ ሳሙኤል አወቀ የሚባለውን ሰው አላውቀውም፡፡ ግደለው ተብዬ ገንዘብ ስለተሰጠኝ ነው የገደልኩት፡፡›› ማለቱ ከእስር ቤት ሾልኮ ወጥቷል፡፡ ‹‹ማን ነው ገንዘቡን የከፈላችሁ?›› ሲባል ደግሞ ‹‹እኔ እሱንም አላውቀውም፡፡ ለእኔ ገንዘቡን የሰጠኝ ያልተያዘው ጓደኛዬ ነው፡፡ እንድንገድልለት የፈለገውም ሰውም የሚያውቀው እሱ ነው›› ማለቱን እስረኞቹ ተናግረዋል፡፡
በተመሳሳይ ከዚህ በፊት በዋለ ሌላ ችሎት ገዳይ የተባለው ሰው ‹‹ለምን ገደልከው?›› ሲባል ሻይ ቤት ውስጥ በተፈጠረ አለመግባባት ሳሙኤል ቀድሞ በዱላ ስለመታው እንደገደሉት ገልጾአል፡፡ ይሁንና ይህ ከሳሙኤል ግላዊ ባህሪ ጋር የሚሄድ አይደለም፡፡ ይህንንም ገዳይ ተብሎ የተያዘውና የተፈረደበት አቶ ተቀበል ገዱ እንደገና እጁን አውጥቶ ዳኛው እድል ሲሰጡት ‹‹ቅድም ሻይ ቤት ውስጥ ስለተጣላን ነው የገደልኩት ያልኩት አቃቤ ህጉ በል ስላለኝ ነው፡፡ አላውቀውም፡፡›› እንዳለ ችሎቱን የተከታተሉት ይናገራሉ፡፡

ሳሙኤል በተገደለ ማግስት ካድሬዎች ግድያው ከጥብቅና ጋር በተያያዘ ነው በሚል ጉዳዩን ከኢህአዴግ ካድሬዎችና ደህንነቶች እራስ ለማውረድ ጥረው ነበር፡፡ በወቅቱም ሳሙኤል የተገደለው ለጥብቅና ቆሞለት ከነበረው አርሶ አደር ጋር አለመግባባት በመፈጠሩ ነው እያሉ ለማስመሰል ጥረዋል፡፡ ይሁንና በትናንትናው የፍርድ ቤት ውሎ ፍርድ ቤቱ ለገዳዩ ማቅለያ ሲያቀርብ ‹‹የቀን ሰራተኛ በመሆንህና በዚህ ስራም ቤተሰብን የምትደጉመው አንተ በመሆንህ አንቀፁን ከ38 ወደ 31 አውርደንልሃል›› ሲሉ ተደምጧል፡፡ በዚህም መጀመሪያ ካሉት ከአርሶ አደርነት ወደ ቀን ሰራተኝነት ቀይረውታል፡፡ ይህም መጀመሪያ ግድያው ፖለቲካዊ አይደለም ለማለት ካድሬዎች ከደንበኝነት ጋር ያያዙትን ውድቅ የሚያደርግ ነው፡፡ በእርግጥ የውስጥ ምንጮች እንደሚሉት መጀመሪያ አካባቢ አቃቤ ህግ ሳሙኤል የተገደለው ከደንበኝነት ጋር በተያያዘ ለማስመሰል ጥረው ነበር፡፡ ይህኛው ድራማ አላስኬድ ሲል በትዕዛዝ እንዲቋረጥ ተደርጓል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሳሙኤል አወቀን ቤተሰቦች ለማስተዛዘን ወደ ጎጃም ያቀኑት የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችና አባላት አባይ በርሃ ላይ ተይዘው እስከ ምሽቱ 2፡30 ከታሰሩ በኋላ ቢፈቱም ወደ ለቅሶው እንዳይሄዱ መኪና እና ቁሳቁሶቻቸውን መነጠቃቸው ይታወሳል፡፡ በወቅቱ መርማሪዎቹ በተደጋጋሚ ይጠይቁት የነበረው ጥያቄ ‹‹ሳሙኤልን ማን ገደለው?›› የሚል ነበር፡፡ ይህም የሚያሳየው መረጃዎች ያጋለጡትን የሳሙኤል ገዳይ በድራማ ለመደበቅ ያደረጉት መንደፋደብ ነው፡፡ ከመጀመሪያው ጀምሮ እስከ ትናንትናው የፍርድ ውሎና አሁንም ድረስ የቀጠለው ፕሮፖጋንዳ የሚያሳየው ሳሙኤል በፖለቲካ አመለካከቱ የተገደለ መሆኑን ነው፡፡ ይህን ለመሸፈን ፍርድ ቤት አድርጎት የማያውቀውን እጅግ የተፋጠነ ‹‹ፍርድ›› ሰጥቷል፡፡ መጀመሪያ ከደንበኝነት ጋር በተያያዘ ነው የተገደለ ብለው አሁን የማያውቀው የቀን ሰራተኛ ነው የገደለው ብለዋል፡፡ እነሱ ‹‹ሻይ ቤት ውስጥ ተጣልተን ነው የገደልኩት›› እንዲልላቸው ቢፈልጉም እሱ ግን እንደገና ‹‹ይህን እነሱ ናቸው በል ያሉኝ›› ብሎ መስክሮባቸዋል፡፡ ገዳይ ተብሎ ለተያዘው ሰው ገንዘብ የሰጠው አባሪ አልተያዘም፡፡ በእርግጠኝነት አምልጦ አይመስለኝም፡፡ ግድያውን ካቀነባበረው ሰው ጋር የሚያገናኝ ድልድይ በመሆኑ እንዳይያዝ ስለሆነ እንጅ፡፡ ሆኖም ይህ ሁሉ ድራማ ገዳዩን መደበቅ አልቻለም፡፡ ከምንም በላይ ድራማው ሳሙኤል ባለፈው አንድ አመት በሚዲያና በማህበራዊ ደረ ገጹ ያሰፈራቸው እማኝነቶችና ሌሎችን መረጃዎች ያጋለጡትን ገዳይ መደበቅ አልቻለም፡፡

No comments:

Post a Comment