Friday, 15 November 2013

አንድ አንዳርጋቸውን መግደል የነፃነቱን ትግል ማስቆም አይቻልም

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ብሔራዊ ደህንነት አማካሪ የጠቅላይ ሚንስትሩን ቢሮ በርግዶ ገባ። ግንቦት ሰባትን በተመለከተ እቅዳችንን ልነግርህ ነው የመጣሁት ሲል ነገሩን ጀመረ።

እሺ ምንድ ነው እቅዱ ?

የአንዳርጋቸውን፤ ጓደኞቹንና አንዳንድ የኤርትራ ባለስልጣኖችን ለመግደል ዝግጅቱ ተጠናቋል። ኤርትራ ድረስ ሂዶ “መስዋዕትነት” ለመክፈል የሚችል አንድ ሰው አግኝተን ልከናል። ግዳጁን ፈፅሞ ሲመጣ አንዳንድ ነገሮች እናደርግለታል። እርሱም ተስማምቷል።ጥቅምት 28 የምስራች እንሰማለን። እስከ
ዛው ግን ፍተሻዎች እንዲጠናከሩ ወጥተህ ተናገር።

ሰውየው “already” ተልኳል ማለት ነው ?

አዎን ከተላከ አምስት ወር ሁኖታል።

የሚሳካ ይምስላችኋል ?

አዎን . . በሚገባ! እኛ ሞክረነዉ ያልተሳካ ምን ነገር አለ? . . . ጌታዬ። በደንብ ነው የሚሳካው። ዛሬ እዚህ መጥቼ የማሳስብዎት ይህ ጉዳይ ሲታቀድም ሲፈጸምም አልሰማሁም ብለዉ እንደ እግር ኳሱ እንዳያሳፍሩን ብዬ ነዉ።

አይዟችሁ እናንተም አታሳፍሩኝም እኔም አላሳፍራችሁም። እሺ ሰምቼያለሁ። አለ “አማኝ ነኝ ባዩ” ደሳለኝ ኃ/ማሪያም ምንም ዓይነት ወንጀል ያልሰሩ የአገሪቷ ምርጥ ልጆች ደማቸው በከንቱ እንዲፈስ እየተስማማ።

“ድሃ በህልሙ ቅቤ ባይጠጣ ንጣት በገደለው “ሲሉ አመሳጠሩ የሃገራችን ሰዎች።

“ቀፎው ነው እንጂ ሲም ካርዱ ከእኛ ነው” የተባለለትና እና በነፍሰ ገዳዮቹ ወንበር የተቀመጠውን የደሳለኝ ኃ/ማሪያምን ጉዳይ በዚህ እናበቃለን።

ህወሃቶች የንጹሃን ዜጎችን ደም በከንቱ ሲያፈሱ የኖሩ ነብሰ ገዳዮች እንደሆኑ የሚታወቅ ነው። አሁንም ክብሬንና ነፃነቴን የሚሉ ዜጎችን ይዘው ደብዛቸውን ለማጥፋት ብዙ ዓይንና ብዙ ጆሮዎችን በየቦታው አቁመናል እያሉ ያቅራራሉ። ይሄን ሁሉ ዓይንና ጆሮ ይዘንስ የሚያሸንፈን ማን ነው ? ሲሉም ይደመጣሉ። እነርሱ እንደሚሉት ዓይኖቻቸው ማየት፤ጆሮዎቻቸውም መስማት የሚችሉ አይደሉም። የህወሃት ዓይኖች ማየት የተሳናቸው እውራን፤ ጆሮዎቻቸውም ማድመጥ የማያውቁ ደናቁርት እንደሆኑ የታወቀ ነው። ህወሃቶች ይህን የማይሰማ ጆሮና ፤ማየት የተሳነውን ዓይን ይዘው እየተደናበሩ፤ ይህን ለመደበቅ ህይዎት ያላቸው መስለው ይታያሉ። አዎን ህወሃቶች ጭው ባለ በርሃ ላይ ብቻችሁን እንደቆማችሁ እወቁ። የሚነገረው እና የሚሆነው በሙሉ ስለተሰወረባችሁ በብዙ ሚሊየኖች መሃከል ብቻችሁን እርቃናችሁን ቀርታችኋል። ብዙ ሚሊዮን ዓይኖች እና ጆሮዎች በእናንተ ላይ መተከላቸውን ልናስታውሳችሁ እንወዳለን።


ግንቦት ሰባት የፍትህ፤የነፃነት እና የእኩልነት ንቅናቄ እንደ ህወሃት-ኢህአዴግ ጆሮዉ የተደፈነና አይኑ የታወረ ድርጅት አይደለም። ግንቦት ሰባት ንቅናቄ የሚያይ ዓይን፤ የሚሰማ ጆሮና የሚያስተዉል ልቦና ያለው ህያው ንቅናቄ ነው። የግንቦት ሰባት ንቅናቄ ጥያቄ ግልፅ ነው። ነፃነት ! ፍትህ ! እና ዲሞክራሲ ! ናቸው። እነዚህ ጥያቄዎች በአግባቡ መልስ እንዲያገኙ የሚከፈለውን መስዋዕትነት ለመክፈል ተነስተናል ጉዞ ጀምረናል፤ ሺ አንድአርጋቸውን ፈጥረናል። ልብ ይበሉ ነፃነት ፍትህ እና ዴሞክራሲ ለሰው ልጆች የተሰጡ ክቡር ስጦታዎች ናቸው። ህወሃት እነዚህን ክቡር ስጦታዎች ከዜጎች ላይ ነጥቆና ህዝብን ረግጦ መቀጠል የለበትም። ህወሃት የዜጎችን ነፃነት ነጥቆ ፤ ፍትህን አጓድሎና ህዝብን ረግጦ እንደከዚህ በፊቱ በሠላም እኖራለሁ ብሎ የሚያስብ ከሆነ ተሳስቷል። በህወሃት ቅዥት አገራችን ተጎድታለች። ህዝቧም ለማያባራ ጉስቁልናና ውርደት ተዳርጓል። ብዙዎችም አገር አልባ ሁነው በየሰው አገሩ መፃተኛ ሁነው እንዲኖሩ ተገደዋል። በእኛ እምነት በአገራችን ላይ እየደረሰ ላለው ውርደት በዋናነት ተጠያቂው ህወሃት ነው። ህወሃት የኢትዮጵያ ዋነኛው ጠላት ነው የምንለውም ዜጎቻችንን ለጉስቁልናና ለውርደት ስላደረገም ጭምር ነው። እኛ ይህን አገር በቀል ጠላት ከሥሩ ነቅለን ለመጣል ተነስተናል። ከዚህ ትግል የሚያቆመን ምንም ዓይነት ምዳራዊ ኃይል እንደሌለ ህወሃቶች እንዲያውቁት እንፈልጋለን። ህወሃቶች አንገታችንን አስደፍተው አይገዙንም። ጥቁር ደም ያፈራቻቸው የቁርጥ ቀን ውድ ልጆቿ የነጻነት ታሪክ በጥቁር ቀለም ይጻፍ ዘንድ የሚያደርጉትን ሀገርን የማዳን ጥሪ እንዲህ በቀላሉ መግታት ከቶ አይቻልም። ወያኔዎች አትደናበሩ! ጋሬጣውን መለየትን ለእኛ ተውሉን።

ታዲያ ይህን ንቅናቄ አንድ አንዳርጋቸውን በመግደል ማስቆም የሚቻል የሚመስለው ጅላ ጅል ቡድን አገሪቷን እየገዛ በመሆኑ ተቆጭተናል። አንዳርጋቸውን መግደል ሌሎች በርካታ ኢትዮጵያዊ አንዳርጋቸውን መፍጠርና ትግሉንም የሚያጠናክር እና የሚያፋፍም መሆኑን አልተረዱም። የኢትዮጵያ ህዝብ የእምቢተኝነት፣ የአልገዛም፣ የነጻነት ታሪክን ለማስከበር መሰዋእትነትን ለመክፈል ዝግጁ መሆንን ከአንዳርጋቸው ከተማረ ቆይቷል። መቆጨታችን ግን እንዲሁ በቁጭት ብቻ የሚቀር የሚመስለው ካለም ድግሞ ተሳስቷል። ይሄ ቁጭት በየደረሱበት የንፁሃንን ደም በከንቱ ማፍሰስ አገር መምራት የሚመስላቸውን ህውሃቶች ከተንጠለጠሉበት ዙፋን አውርደን በልካቸውና በአቅማቸው እንዲኖሩ ለማድረግ የጀመርነውን ትግል ይበልጥ አጠናክረን እንድንቀጥል ያደርገናል። ህወሃት ውስጥ እንደ ሰው ማሰብ የሚችል ግለሰብ ካለ አሁን ቆም ብሎ እንዲያስብ እናሳስበዋለን። ጀንበር ሳትጠፋባችሁ ለነጻነት፣ ለዲሞክራሲና ለፍትህ የሚደረገውን ትግል ተቀላቀሉ። እርግጥ ነው ለነፃነት የሚደረገው ትግል በየመስኩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና ህወሃትም የእጁን እንደሚያገኝ ምንም ዓይነት ብዥታ እንዳይኖራችሁ ልንነግራችሁ እንወዳለን።

ግንቦት ሰባት የቆመበት መሠረት ፅኑ፤ ዓላማውም ህዝባዊ ነው። በዚህ በፀና መሠረት ላይ ህዝባዊውን ዓላማ አንግበው የተነሱ ሚሊዮኖች አሉ። እነዚህ ሚሊየኖች የሌሉበት ሥፍራ የለም። ከቤተ-መንግስት እስከ እርሻ ማሳ፤ ከስለላ ተቋማት እስከ አገሪቷ መከላከያ ኃይል፤ ከሃይማኖት ተቋማት እስከ መንግስት መሥሪያ ቤቶች፤ ከዘመናዊ ትምህር ተቋማት እስከ ተከበሩ ገዳማት ድርስ ለክብራቸው ዘብ የቆሙ ሚሊየኖች አሉ። እነዚህ ሚሊኖች የቆሙት መረቅ የበዛበትን ወጥ ዓላማ አድርገው ሳይሆን በፀናው መሠረት ላይ ለተተከለው ክቡር ዓላማ ነው። ይህ ክቡር ዓላማ ነፃነት፤ ፍትህ ፤እኩልነት እና የህግ የበላይነት እንጂ ሌላ አይደለም። እነዚህ ሚሊየኖች አትኩረው ማየት የሚችሉ ድንቅ ዓይኖች ያሏቸው፤ አጥርተው ማድመጥ የሚችሉ ክቡራን ጆሮዎች ያሏቸው መሆናቸውን ህወሃቶች እንዲያውቁት እንወዳለን።

ግንቦት ሰባት ማንንም ፍርሃት እና ድንጋጤ ውስጥ መክተት አይፈልግም።እንዲያውም ግንቦት ሰባት ንቅናቄ የሚታገለው ዜጎች ሁሉ ከፍርሃት ነፃ ሁነው በደስታ እንዲኖሩ ለማስቻል ነው። ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን ካሁን ወዲያ ከግንቦት ሰባት ንቅናቄ ዓይንና ጆሮ የሚያመልጥ አንዳችም ነገር እንደማይኖር የሚያሳድደን ቡድን እንዲያውቀው እንፈልጋለን። ዓይንና ጆሯችን በሁሉም ሥፍራ በንቃትና በጥንቃቄ ነገሮችን እየተከታተሉ ይገኛሉ።

ህወሃቶች ከትዕቢታችሁ ብዛት የተነሳ የህዝቡን ምክር መናቃችሁን እናውቃለን።የወገኖቻችንንም ድምፅ ጫጫታ እያላችሁ እንደምትሳለቁም እናውቃለን። ይሄ እንደማይጠቅማችሁ ብዙ ግዜ ነግረናችኋል። የህዝቡን ምክር ስሙ፤ የወገኖቻችሁንም ድምፅ አድምጡ ብንላችሁ በእምቢታችሁ ፀንታችኋል። ልቦናችሁ እንደ ፈርዖን ልብ ደንድኗል።ልብ ማደንደን እንኳን እናንተን ለመሠለ ደካማ ፍጡር ይቅርና በዘመኑ እኔ “እምላክ” ነኝ እሰከ ማለት ለደረሰው ለፈርዖንም አልበጀም። እንዲህ ዓይነት የልብ ድንዛዜ እናንተ በዚያ ጠባብ ዓላማችሁ ጣልነው ለምትሉት ለመንግስቱ ኃ/ማሪያምም አልረባውም። አሁንም የእኛ ምክር አጭርና ግልፅ ነው። የመዘዛችሁትን የበቀል ሰይፍ ወደ ሰገባው መልሱ። የዘጋችሁትን በር ክፈቱ። የነጠቃችሁትን የዜጎች ነፃነት መልሱ። በህዝቡ ላይ ያወረዳችሁትን የፍርሃት ድባብ አስወግዱ። የተከላችሁትን የዘረኝነት እሾህ ንቀሉ። ከእውነት ጋርም ታረቁ። እንዲህ ብታደርጉ የዚያችን አገር በረከት ትበላላችሁ፤ እምቢ ብትሉ ግን የሚበላችሁን እሳት ማጥፋት አይቻላችሁም። መጥተናል!!

እኛም ከምን ግዜውም በላይ ተጠናክረናል። የትግል ዘርፋችን ሰፍቷል። በሁሉም አቅጣጫ መረባችን ተዘርግቷል። ከዚህ መረብ የትም አታመልጡም። ማምለጫ መንገዳችሁ አንድ ብቻ ነው። እርሱም የህዝቡን ድምፅ መስማት፤ እውነተኛ መልስ መስጠት እና ለህግ ተገዢ መሆን። አበቃን።

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !!!

No comments:

Post a Comment