አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)
UNITY FOR DEMOCRACY AND JUSTICE PARTY
(UDJ)
የፓርቲያችንን ህጋዊ እንቅስቃሴ ለፖለቲካ ፍጆታ ማዋል የገዥውን ፓርቲ የፕሮፓጋንዳ ውድቀት እና ኢ-ህገመንግሥታዊነት የሚያሳይ ነው!!!
ከአንድነት ለዴሞክራሲ እና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) የተሰጠ መግለጫ!!!ፓርቲያችን አንድነት የተቋቋመለትን ሕዝባዊ ዓላማ መሰረት በማድረግ በኢትዮጵያ ውስጥ ከ50 ዓመት በላይ ትግል ተደርጎበት እውን መሆን ያልቻለውን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሳይሸራረፍ ለማስፈን፤ አምባገነኑን ስርዓት በሰላማዊ ትግል ለመለወጥ እንዲሁም የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ለማድረግ ህግን መሰረት አድርጎ እየሰራ ይገኛል፡፡ በዚህ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የማስፈን ትግልም ፓርቲያችን፣ አመራሩና ቁርጠኛ አባላቱ ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍለዋል፤ እየከፈሉም ይገኛሉ፡፡ ዋጋ በከፈሉና ዋጋ እየከፈሉ ባሉ አመራሮቻችንና አባሎቻችን መራራ ትግል ምስጋና ይሁንና በመላ ኢትዮጵያ ሕዝባዊ መሰረት በመጣል ከኢትዮጵያ ህዝብ ጎን መሆናችንንም አረጋግጠናል፡፡ ይህ የፓርቲያችን ጥንካሬ የራስ ምታት የሆነበት ገዥው ፓርቲ ግን ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ህዝባዊ መሰረታችንን ለመናድ በስም ማጥፋት፣ በፍረጃና ባልዋልንበት እንደዋልን የማስመሰል ስራውን አጠናክሮ በመቀጠል በህዝቡ ዘንድ ያለንን መልካም ስማችንን ለማጉደፍ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ እየሰራ ይገኛል፡፡
አንድነትም የገዥውን ፓርቲ ኢ-ህገ መንግስታዊ የሆነ እኩይ ተግባር ተገቢ እንዳልሆነ፣ ለሀገርና ለህዝብ እንደማይጠቅም፣ የህዝብን ጥያቄ በዶክመንተሪ ጋጋታ መመለስ እንደማይቻል፣ ከፍረጃና ከሴራ ተላቅቆ በሰከነ መንገድ ወደ ውይይት እንዲመጣ በተደጋጋሚ መክረናል፤ ሀገራዊ ጥሪም አቅርበናል፡፡ ነገር ግን አምባገነኑ ስርዓት የሚቆጣጠራቸውን የመንግስት ተቋማት በመጠቀም አሁንም በዶክመንተሪ ስም ከማጥፋት፣ ከመፈረጅና ከማስፈራራት መላቀቅ አልቻለም፡፡
ሰሞኑን በተከታታይ 3 ክፍል ተላልፎ ይቀጥላል በተባለውና የፀረ-ሽብር ግብረ ሃይል ከኢቲቪ ጋር በመሆን አዘጋጅቶታል በተባለው ተከታታይ የዶክመንተሪ ፕሮግራም ላይ መሰረት የተደረገው ፓርቲያችን በመላ ኢትዮጵያ ህዝባዊ ንቅናቄ በመፍጠር እንዲሰረዝ እንቅስቃሴ ያደረገበት የፀረ ሽብር ህጉ ላይ ነው፡፡ አንድነት የፀረ-ሽብር ህጉ ይሰረዝ ሲል አሳማኝ መከራከሪያዎችን በማንሳትና በሰላማዊ መንገድ ቢሆንም ገዥው አካል ግን እንደተለመደው ማስተላለፍ ከፈለጉት አላማ ጋር የፓርቲያችንን ስም በማይገባ ቦታ በማንሳትና ለሚመለከተው አካል በህጉ መሰረት አሳውቀን ባካሄድናቸው ሰላማዊ ሰልፎች እና ህዝባዊ ስብሰባዎች ላይ ያስተላለፍናቸውን አቋሞች የሃሰት ትርጉም እየሰጠ የተለመደ የዶክመንተሪ ድራማው ማድመቂያ ሲያደርገን ተስተውሏል፡፡ የፓርቲ አመራሮች በህጋዊ ሰላማዊ ሰልፎች ላይ ያደረጉትን ንግግር ቆርጦ በመጠቀም በህዝብ ዘንድ ያለን ተቀባይነት ላይ ተፅዕኖ ለማሳረፍ የታቀደ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሁሌም ምርጫ ሲቃረብ እንደሚያደርጉት ሁሉ በ2007 ዓ.ም ለሚካሄደው ሀገራቀፍ ምርጫ የተቃውሞ ጎራውን በፀረ-ሰላምነት ለመፈረጅ እየተደረገ ያለ የኢህአዴግ የምርጫ እንቅስቃሴ ክፍልም ነው፡፡
በዚሁ ዶክመንተሪ ላይ መቀመጫውን በውጭ በማድረግ የተለያዩ ዜናዎችንና ፕሮግራሞችን በማሰራጨት የሚታወቀውን ኢሳት (ESAT) ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ ፓርቲያችን ለአባላቱ እና ለደጋፊዎቹ መልዕክት ማስተላለፉን እንዲሁም እንደፓርቲ ለማንኛውም ሚዲያ የፓርቲያችንን ሰላማዊ እንቅስቃሴ በተመለከተ ስንጠየቅ የመመለስ መብታችንን በሚጋፋ መልኩ የፓርቲያችንን አቋም አዛብቶ ለማቅረብ ሞክሯል፡፡
ይህም የኢህአዴግን የፖለቲካ ባህሪ እና አቋም በግልፅ ያሳየ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በፓርቲያችን ዕምነት ኢህአዴግ በሚጠላቸው እና በሚያጥላላቸው ሚዲያዎች ሃሳብን መግለፅ በየትኛውም መመዘኛ አሸባሪነት ሊሆን አይችልም፡፡ የኢህአዴግ መንግስት ሲያስነጥሰው ከሚያለቅሱለት የፕሮፓጋንዳው ፍጆታዎች ከሆኑት ሚዲያዎች ውጪ የኔ ያልሆኑ የሌላ ናቸው ብሎ የሚያምን በመሆኑም ፍረጃው ህጋዊ አግባብነትም ሆነ መረጃ የሌለው ባዶ ፍረጃ መሆኑ ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡
ከሁሉም በላይ ህገ መንግስታዊ መሰረት የሌለው ቢሆንም እንኳ ቢያንስ ራሳቸው ላወጡት ህግ ታምነው ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በማቅረብ ሳያስወስኑ አንድን የሚዲያ ተቋም ያውም ለአንድ አላማ የተቋቋመ የፀረ-ሽብር ግብረሃይል ‹‹የአሸባሪ ድርጅት ልሳን ነው›› ወይም ‹‹አሸባሪ ነው›› በማለት ሲፈርጅ ስናይ አሁንም የሀገራችን ፖለቲካ ፓርቲና መንግስት የተደበላለቁበት፣ አንድ ድርጅት እንደፈለገው የሚፈርጅበት ስርዓት እንዳለ የሚጠቁም ነው፡፡
ፓርቲያችንም ይህንን ህገ ወጥ ፍረጃ በቀላሉ የማይመለከተው መሆኑን እየገለፅን ገዥው ፓርቲ ከድርጊቱ እንዲቆጠብ፤ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንም ለተፈፀመብን የስም ማጥፋት ከተጠያቂነት የማያመልጥ መሆኑን እያሳወቅን አሁንም ህገ-መንግስት የሚጥሰውንና ተቀናቃኝ ሃይሎችን ለማሸማቀቅ እያገለገለ ያለው የፀረ-ሽብር አዋጅ እንዲሰረዝ ሰላማዊ ህዝባዊ ትግላችንን በማጠናከር እንደምንቀጥል እንገልፃለን፡፡ የህዝብ ልዕልና እና የህግ የበላይነት እንዲከበር ትግሉ የሚጠይቀንን መስዋዕትነት እንደምንከፍል ለመላው የኢትዮጵየ ህዝብ በድጋሚ እናረጋግጣለን፡፡ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ
ታህሳስ 29 ቀን 2006 ዓ.ም
አዲስ አባባ posted by A.G
No comments:
Post a Comment