Friday, 31 January 2014

ልፋ ያለው በሕልሙ ዳውላ ይሸከማል! ጠርናፊና ተጠርናፊ (ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም ) Source www.ecadforum.com

  January 31, 2014    ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም

ጥር 2006
ሰሞኑን እንደአዲስ ሆኖ የሚወራው ስለጥርነፋ ነው፤ ጥርነፋ ከዲያብሎስ ፋብሪካ የወጣ የክፋትና የጭቆና መሣሪያ ነው፤ ሰዎችን በመጨቆንና በማሰቃየት፣ ምቾትና እንቅልፍ በማሳጣት፣ ፍርሃትንና ስጋትን በማሰራጨት ሕዝብን ለጥ-ጸጥ አድርጎ ለመግዛት የሚፈልጉ ጠርናፊዎች፣ አምባ-ገነኖች፣ ጨቋኞች፣ አፋኞች፣ ዘራፊዎች፣ ወሮበሎች፣ ምድራዊም ሆነ ሰማያዊ ሕግ የማይገዛቸው፣ አምላካቸው አድርገው የሚያገለግሏቸው ሎሌዎችን በሆዳቸው ገዝተው የሚያሰልፉ ናቸው፤ እንኳን የገጠር ልጆችና አኛም የአዲስ አበባዎቹ መሰንከል ምን እንደሆነ እናውቃለን፤ እንስሳትን (በቅሎዎችንና አህዮችን፣ አንዳንዴ በገግና ፍየልም) የፊት እግር ከኋላ እግር ጋር በአጭር ገመድ እያሰሩ እንደልባቸው እንዳይንቀሳቀሱ ማድረግ ነው፤ ሀብት በመሆናቸው ቢጠፉ ባለቤቶቹ ይጎዳሉ፤ ስለዚህ በየአካባቢያቸው ያለውን እየጋጡ ችለው እንዲኖሩ ለማድረግ ቀላሉ ዘዴ መሰንከል ነው፡፡Prof. Mesfin Woldemariam : is an Ethiopian Human Rights activist and philosopher
ለሰውም ቢሆን ዓላማውም ዘዴውም አንድ ነው፤ ልዩነቱ የሰው ልጅ እንቅስቃሴው አካላዊ ብቻ ሳይሆን አእምሮም መንፈስም ስላለው መሰንከሉ አካላዊ ብቻ አይሆንም፤ እንዳያስብ አእምሮውን ማፈን ግዴታ ይሆናል፤ ለአምባ ገነኖች ችግር የሚመጣው የሰዎች አእምሮ ሲያስብ ነው፤ ያሰበውንም መናገርና መጻፍ ሲጀምር ነው፤ ‹‹መጥፎ ሀሰብ››፣ ማለትም ለጨቋኞቹ የማይበጅ ጥሩ ሀሳብ በንግግር፣ በጽሑፍ፣ በራድዮና በቴሌቪዥን ቢተላላፍና ብዙ ሰዎች ቢሰሙት አገር ይረበሻል፤ ሰው ሁሉ ሽብርተኛ ይሆናል፤ አገዛዙ ሕዝቡን ለመሰንከል ብዙ ዘዴዎች አሉት፤ በስም ማጥፋት እንዳልከሰስ ዘዴዎቹን አልናገርም፤ ነገር ግነ ክፉ እንቅልፍ ይዞት የሄደ ካልሆነ በቀር የማያውቃቸው የለም፤ የማያውቅ ካለ በየቤቱ እየመጡ ይተዋወቁታል፡፡
ወያኔ የትግራይን ሕዝብ አንድ ለአሥር ጠርንፎ ከሃያ ዓመታት በኋላ ውሉ ጠፋበትና ጥርነፋው ላላ! የቂል ነገር ለትግራይ ያልተሳካውን ጥርነፋ በቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይም ለመዘርጋት አቅዷል ይባላል፤ የወያኔ መሪዎች በአዲስ አበባ ቤቶችን አፍርሰው መንገድ ከሠሩ በኋላ ባቡር ትዝ ሲላቸው መንገዱን አፍርሰው ሀዲድ ለመሥራት ይሞክራሉ፤ ጥርነፋ በትግራይ እንዳልሠራ እያዩ በቀሩት ክልሎች ያሉትን ሰዎች ለመጠርነፍ ይፈልጋሉ፤ ጭንቅላተቸው ውስጥ ያለው ምንድን ነው ያሰኛል፤ እንኳን እንዲህ መክሸፉ በተግባር እየታየ ይቅርና ማሰብ ለሚችል በሀሳብም ደረጃ የከሸፈ ነገር ነው፤ እንስሳትን መሰንከል ቀላል ነው፤ ጉልበትን በበለጠ ጉልበት ማሸነፍ ነው፤ መናገርን መሰንከል ግን አይቻልም፤ ምላሱ ቢቆረጥበትም ሰው ሌላ መንገድ ይፈልጋል፤ በደርግ ዘመን ከኤንሪኮ በር ላይ የማይጠፋ ወፍራም ድሪቶ የሚለብስ ዲዳ ሰው ነበር፤ አንዳንድ ቀን ያየውን ‹‹ሲያወራ›› አንዳንዶች ያስይዘናል በማለት ይሸሹት ነበር፤ ያያቸው ወታደሮች መሆናቸውን በራሱ ላይ መለዮ በእጁ ያሳይና ሹመታቸውን ደግሞ በትከሻው ወይም በክንዱ ላይ እያመለከተ ሰዎችን ጨረሷቸው ለማለት በእጁ አፉን ጥርግ ያደርጋል፤ እኛ እንደሰማነው ወታደሮቹም እየገባቸው በየጊዜው ይደበድቡት ነበር፡፡
ማሰብን መሰንከል ደግሞ ከመናገርን ወይም መጻፍን ከመሰንከል የበለጠ አስቸጋሪ ነው፤ ለኢጣልያ የገበረው ባንዳ ሁሉንም አየነው፤ አማኑኤል ደግ ነው፤ እያለ የኢጣልያኑን ቄሣር አሞገሰና በጊዜው በላበት፤ በኋላ የአጼ ኃይለ ሥላሴ አገዛዝ ሲመለስና ሲቋቋም ባንዳው ተገልብጦ ኢየሱስ ክርስቶስን ማለቴ ነው አለ! ሰምና ወርቅ የሚባለው የተፈጠረው ሀሳብን የመግለጽ መሰንከልን ለማክሸፍ ነው፤ ማሰብን መሰንከል እስካልተቻለ ድረስ ሀሳብን መግለጽን መሰንከል አይቻልም፡፡
የሰንካዮችን ጭንቅላት አልፎ ሊሄድ የማይችል አንድ ታሪክ ደጋግሞ ያረጋገጠው ነገር አለ፤ ልፋ ያለው ዳውላ ይሸከማል፤ እንደሚባለው ጨቋኞችና አፋኞች እንደእንስሳ ለሆዳቸው ብቻ የሚገዙ ታማኝ አገልጋዮችን እየመለመሉ ዙሪያቸውን ያጥራሉ፤ ነገር ግን የሆዳሞቹ አገልጋዮች በሀሳብ ወረርሺኝ ሲመታና ሲነቃ አፋኞች ማሰብን ለመሰንከል ባለመቻላቸው የራሳቸው ታማኝ አገልጋዮች ይገለብጧቸዋል፤ ይህ የታሪክ እውነት ቢገባቸው ማሰብን መሰንከል መሞከሩ ቀርቶ ሀሳብን መግለጽንም ለመሰንከል አይሞክሩም ነበር፤ ምክንያቱም ማሰብ በሚቻልበትና ሀሳብን በነጻነት መግለጽ በሚቻልበት አገር ሀሳብ አይፈነዳም፤ ሀሳብ እንደሚፈነዳ፣ ከፈነዳም በኋላ እንደወረርሺኝ መንደር ሳይመርጥ፣ ጎሣ ሳይመርጥ፣ የቋንቋና የሃይማኖት ልዩነት ሳያግደው፣ ሀሳብ ብቻ ሊያግደው የሚፈልገውን ኃይል ሁሉ በዘዴ እያሽመደመደ ይንቀለቀላል፤ ይስፋፋል፡፡
አብርሃም ሊንከን አለ እንደሚባለው ‹ጥቂት ሰዎችን ሁልጊዜ ማታለል ይቻላል፤ ሁሉንም ሰው ለጥቂት ጊዜ ማታለል ያቻላል፤ ነገር ግን ሁሉንም ሰው ሁልጊዜ ማታለል አይቻልም፤› ለጥቂት ጊዜ የታለሉት ማታለልን ይማሩና ያታልላሉ! የተኙ መስለው ያሸልባሉ፤ የሚያለብሱ መስለው ያራቁታሉ፤ የሚያከብሩ መስለው ያዋርዳሉ፡፡
በመጨረሻም ተጠርናፊዎች ጠርናፊዎች ይሆኑና መክሸፍ ይቀጥላል! ጠርናፊም እስኪጠረነፍ ሌላ ነገር አላስተማረም፤ ተጠርናፊም ራሱን ከጥርነፋ እስኪያወጣ የተማረው ሌላ ነገር የለም፤ ማስረጃ ከተፈለገ ተቃዋሚ በሚባሉት ቡድኖች ውስጥ ሞልቶአል!!
መጨረሻም በኢጣልያ የአገዛዝ ዘመን አምስት ለአንድ ጥርነፋ ማለት አንድ ኢጣልያዊ ለአምስት አበሻ ማለት ይሆንና አንድ ጠርናፊና አምስት ተጠርናፊዎች በቋንቋና በባህል የማይግባቡ፣ በታሪክም ሆነ በማኅበረሰብ ኑሮ ዝምድና የሌላቸው፣ የወደፊቱም ሕይወታቸው በተረጋገጠ የበላይነትና የበታችነት ደረጃ የተወሰነ ስለሚሆን ጥርነፋው ትርጉም ያለው ሊመስል ይችላል፤ አምስት አበሻ ለአንድ አበሻ መጠርነፍ ግን በጠርናፊም ሆነ በተጠርናፊ በኩል ብርቱ የማሰብ ችግር (ከመንግሥተ ሰማያትም ቢሆን አመጣሃለሁ! ያለው ሰውዬ ዓይነት) ከሌለ በቀር ከንቱ ነው፤ በቀላሉ አንድ ለአምስት በማድረግ ዓላማውን መገልበጥ ይቻላል! አንድና አምስት ስድስት ነው፤ እንዲሁም አምስትና አንድ ስድስት ነው፤ ሁለትና አራት ስድስት ነው፤ ሦስትና ሦስትም ስድስት ነው፤ በነዚህ ቁጥሮች ውስጥ ሰው የምንለው ማንን ነው? ከብት የምንለው ማንን ነው? ሁሉም ሰዎች ከሆኑ ጠርናፊና ተጠርናፊ አይኖርም፡፡
                                                             Posted by A.G

No comments:

Post a Comment