Tuesday, 4 February 2014

ወያኔን ያሸበረው የግንቦት 7 መንገድ ምንድነው? Source, http://www.ginbot7.org/2014/01/30/

የትግራይን ሕዝብ ከብሄር ጭቆና ነጻ አወጣለሁ በሚል ጠባብ ዓላማ ተደራጅቶና ታጥቆ ለበትረ ሥልጣን የበቃው ህወሃት ወይም 
ሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ሥልጣን ከተቆጣጠረ 23 አመት ሊሞላው እነሆ ጥቂት ወራቶች ብቻ ቀርተውታል።
ለጋራ ቤታችን ለሆነቺው አገራችን ኢትዮጵያና በአስተዳደር በደል ለከፋ ድህነት ለተዳረገው መላው ሕዝቦቿ የሚሆን አንዳችም ራዕይ ሳይኖረው ለመንግሥትነት ሥልጣን የበቃው ይህ ቡድን ላለፉት 23 ዓመታት ከግል ኑሮአቸው አሻግረው የአገርንና የወገንን ጥቅም ማየት የማይችሉ ወይም የማይፈልጉትን በዙሪያው አሰባስቦ እያካሄደ ካለው ዘርፈ ብዙ የሃብት ምዝበራ ወንጀል በተጨማሪ እየፈጸመ ያለው የመብት ጥሰትና አፈና ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም።
ሰሞኑን እያፈተለኩ በመውጣት ላይ ከሚገኙ ምስጥራዊ የድምጽ መረጃዎች ለማረጋገጥ እንደተቻለው ደግሞ ለጥቂቶች የሃብትና የብልጽግና ምንጭ የሆነው ሥልጣን ከእጃቸው እንዳይወጣ በአንድ በኩል በምርጫ ስም እንዴት አድርገው ሕዝቡን ቀፍድደው የምርጫው ተሳታፊ ማድረግ እንደሚችሉ ሲዶልቱና በሌላ በኩል ደግሞ በቁጥጥራቸው ሥር የሌሉትንና ለሥልጣናቸው ያሰጉናል ያሉዋቸውን የደሃዉን ልጅ በማጋፈጥ እንዴት በጦርነት እንደሚጨፈልቁዋቸው ሲመክሩ ተሰምተዋል።
ከወያኔው ቁንጮ አንዱ የሆነው በረከት ስሞን በየደረጃው ላሉት የአገዛዙ ሹሞችና ካድሬዎች ባደረገው ገለፃ መሬትን የመንግሥት ባደረገው ኮሚኒስታዊ አዋጅ ምክንያት የመንግሥት ጭሰኛ ለመሆን የተፈረደበትን ሰፊውን አርሶ አደር “ተኛ ስንለው ይተኛል፤ ቁም ስንለው ይቆማል ፤ እንደፈለግን ብንበድለው እንኳ አያማርረንም ” እያለ ሲዘባበትበት ተደምጦአል ። በአንድ ለአምስት ኮሚንስታዊ አደረጃጀት ተጠርንፎ የወያኔ የንግድ ድርጅቶች ብቻ የሚያቀርቡትን ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ያለውዴታው እንዲራገፍበትና ከአቅሙ በላይ ዕዳ እንዲቀፈቅፍ የተፈረደበት የኢትዮጵያ አርሶ አደር በዚህ አይነት ንቀት ደረጃ የሚዘባበትበትን መሪ ከወያኔው በረከት ስሞን በፊት ገጥሞት አያውቅም ። ለወደፊትም ሊያይ አይፈልግም ። ወያኔን ሥልጣን ላይ ለማምጣት የሰሜኑ ክፍለአገራችን አርሶ አደር የተጫወተው ሚና ተዘንግቶ በበረከት ስሞን እንዲህ መዋረዱ እጅግ ያሳዝናል። ለነገሩ ከፍተኛ የህይወት መስዋዕትነት ከፍሎ ለድል ያበቃው የትግራይ ሕዝብ ቁም ስቅሉን እያየ አይደል?
ሌላው አስገራሚ ክስተት በአገር ደህንነት ሥራ ላይ የተሰማሩ ዜጎች ባደረጉት ዝግ ስብሰባ ታማኝነታችን ለአገራችን ነው ወይስ የሥርዓቱን አገዛዝ ዕድሜ ለማራዘም? ብለው ላነሱት ጥያቄ የጠቅላይ ሚንስትር ተብዬው የህግ አማካሪ ጌታቸው ረዳ የሰጠው መልስ ነው። ደህንነት ብቻ ሳይሆን የመከላኪያ ሠራዊትና ፖሊስ ጭማር ታማኝነታቸውና ግዴታቸው ሥርዓቱን ሥልጣን ላይ ማቆየት መሆን አለበት ሲል ጌታቸው እንቅቹን ነግሮአቸዋል ። በምላሹ “ላለፉት 23 አመታት እያደረግነው ያለው ይሄው ሆኖ ሳለ አሁን ምን ብታስቡ ነው ጥያቄ ያነሳችሁ?” የሚል ይመስላል ። ይባስ ብሎም ሥርአቱን ለመጠበቅ ያልቻለና በግንቦት 7 መንገድ የሚጓዝ ደህንነት ሠራተኛ የተስፋየ ገብረስላሴን ያህል የደህንነት እውቀት ቢኖረውም ሆነ እስራኤል አገር የዓመታት ስልጠና ያገኘ ቢሆን ዋጋ የለውም ብሏቸዋል።
ለመሆኑ ወያኔዎች እንደመርገም የቆጠሩትና ተከታዮቻቸውን የሚያስፈራሩበት የግንቦት 7 መንገድ ምንድ ነው።?
ግንቦት 7 የፍትህና፤ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ አገራችን ኢትዮጵያ የእያንዳንዱ ዜጋ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብት የተከበረባት፤ የኢኮኖሚ ብልፅግናና ማኅበራዊ ፍትህ የሰፈነባት ፤ የዜጎች ሕይወት፣ ደህንነትና ጥቅም የተከበረባት እና የሕዝቧ አንድነትና ትስስር የጠነከረባት ሃገር ሆና ማየትን ብቸኛ ራዕይ አድርጎ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኝ ድርጅት ነው። ይህንን ራዕይ እውን ለማድረግ ደግሞ እስከ ዛሬ በጠመንጃ ኃይልና በጉልበተኖች ጡንቻ ከአንዱ ወደሌላው የሚፈራረቀው የመንግሥት ና የፖለቲካ ሥልጣን በሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ሂደት የሚያዝበትን ፤ የሃገሪቱ ዜጎች ምርጫ በተግባር የሚገለፅበት፤ ማኅበራዊና የፖለቲካ ችግሮች በዲሞክራሲያዊ መንገድ የሚፈቱበት እና ዲሞክራሲያዊ ባህል የሚበለፅግበት ብሄራዊ የፖለቲካዊ ሥርዓት መገንባት አማራጭ የሌለው ነው ብሎ ያምናል።
ይህ ደግሞ ያለምክንያት አይደለም። ወያኔ የዓለም አቀፍ ድጋፍ ለማግኘት ሲል ለዲሞክራሲያዊ ምርጫ በሩን ከፈት አድርጎ በነበረበት ምርጫ 97 ወቅት ከተገኘው ልምድና ከተመዘገበው ውጤት ሕዝባችን በአምባገነኖችና በከፋፋዮች ለመገዛት አለመፈለጉን በግልጽ አስመስክሮአል።
ንቅናቄያችን ግንቦት 7 ሕዝባችን በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በነቂስ ወጥቶ መሪዎቹን የመረጠበትንና ድሉን የተነጠቀመበትን ታሪካዊ የግንቦት 7 1997ን ቀን ምን ጊዜም አይረሳም። መጠሪያ ስሙንም በዚያ ታሪካዊ ቀን የሰየመው ሕዝብ የተነጠቀውን ድል በማስመለስ ፍትህ የሰፈነባት፤ የበለጸገችና የተከበረች አገር ባለቤት እንሆን ዘንድ ነው። ሁላችንም አትራፊ እንጂ ተጎጂ ለማንሆንበት ለዚህ ቅን አለማና ራዕይ ደንቃራ ሆኖ የተገኘው ወያኔና ለግል ጥቅማቸው ሲሉ ከወያኔ ጋር የተጣበቁ አንዳንድ ባዕዳን አገሮች ናቸው።
ወያኔ የግንቦት 7 መንገድ የሚለው ለዚህ ክቡር ዓላማ ሲባል እንቅፋት የሆነውን ሥርዓቱን በሁለ- ገብ ትግል አስገድዶ ለሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር አካል ማድረግ ካልተቻለ ደግሞ በተባበረ ትግል አስወግዶ በምትኩ በሕዝብ ለሕዝብ ከሕዝብ የሚመጣ ሰላማዊ የመንግሥት ሥርዓት መመሥረትን ነው። ይህንን የተቀደስ አላማ ለማክሸፍና የተጀመረውን ትግል ለመጨፍለቅ ሲባልም ወደ ሥልጣን ለመምጣት በጦርነት ማግዶ ካስጨረሳቸው የደሃ ልጆች በእጥፍ የሚበልጡትን መልምሎ በጸረ ሽምቅ ውጊያ ከማሰልጠን ጎን ለጎን ለግንባታ ቢውል ስንት ፋይዳ ሊያስገኝ ይችል የነበረ በርካታ ገንዘብ በማፍሰስ ተቃዋሚ ድርጅቶችን ድምጽ ለማፈንና ለመሰለል እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።
ለአገራችን ሉአላዊነት ጠቀሜታው እስከዛሬ ምንም ባልታወቀ ጦርነት ወደ መቶ ሺ የሚጠጉትን ያስጨፈጨፈ፤ የተልዕኮ ጦርነት ለማካሄድ በመንግሥት አልባዋ ጎረቤት ሱማሌ እስከዛሬ ቁጥራቸው ያልተገለጸ ወገን ያስፈጀ ፤ ለሥራ ፍለጋ ውትድርና የገቡትን ወጣቶች ለይቶ በሰላም አስከባሪ ስም በድንበር ዘለል ጦርነቶች እየማገደ ገንዘብ የሚቀበል፤ ስለአገርና ስለወገን ምን ሊገደው ይችላል?
ትናንት ትግል ላይ በነበሩበት ወቅት የቀደምቶቹ መንግስታት ልጆቻቸውን ለትምህረት ወደ ፈረንጅ አገር እየላኩ የደሃውን ልጅ በጦርነት ይማግዳሉ በማለት በጅምላ ሲከስ የኖረ ዛሬ በተራቸው ልጆቻቸውን ብቻ ሳይሆን ዘርማንዘሮቻቸውን ታይቶ በማይታወቅ ብዛት ወደ ፈረንጅ አገር ለትምህርት እየላኩ ለነጻነታችንና ለክብራችን የምንታገለውን እርስ በርስ ለማጨራረስ ሲዶልቱ ዝም ብሎ መመልከት ከየትኛውም ቅን ዜጋ የሚጠበቅ አይሆንም።
ስለሆነም የበላይ አዛዦቻቸው በሚሰርቁት የሕዝብ ገንዘብ ፎቅ ላይ ፎቅ እየገነቡ ሃብት በሚያካብቱት አገር ሠራዊቱን እረፍት ለመንሳት ሆን ተብለው በሚቀሰቂሱት ግጭቶች ከአንዱ ማዕዘን ወደ ሌላው ማዕዘን ያለ ዕረፍት እየተንከራተተ ያለው የመከላኪያ ሠራዊት ፤ የፖሊስና የደህንነት ኃይል ለአገዛዙ አልታዘዝም በማለት ተገዶ ሥልጣን ለሕዝብ እንዲያስረክብ የማድረግ ወገናዊ ሃላፊነቱን እንዲወጣ ግንቦት 7 የፍትህ የነትጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ጥሪውን ያቀርባል።
የግንቦት 7 መንገድ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘመናት የተጠማውን ፍትህ እኩልነትና ነጻነት በአገራችን ለማስፈን አሁን ሥልጣን ላይ ያለው የጎጠኞችና የዘራፊዎች ስብስብ በማስገደድ ወይም በማስወገድ ሰላማዊ ህጋዊና ዲሞክራሲያዊ የሥልጣን ሽግግር እንዲኖር ማድረግ ነው። ይህንን ደግሞ የሚፈሩት በሥልጣን ቱርፋትና በሃብት ዘረፋ የሰከሩ ብቻ ናቸው።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ    
                                                               Posted by A.G

No comments:

Post a Comment