Wednesday, 1 October 2014

የፓርቲዎቹ አባላት ጠበቃ

የፓርቲዎቹ አባላት ጠበቃ ደረሰብኝ ባሉት ጫና ለጊዜው ሥራቸውን ማቆማቸውን አስታወቁ

Oktober 1,2014
በ  አሸናፊ ደምሴ
በሕገመንግስቱ መሠረት ለደንበኞቼ አገልግሎት መስጠት አልቻልኩም፤ ከፍርድ ቤትና ከፖሊስም ማስፈራሪያ ደርሶብኛል ያሉት የአንድነት፣ የሰማያዊና የዓረና ፓርቲ አባላት ጠበቃ አቶ ተማም አባቡልጉ ራሳቸውን ማግለላቸውን አስታወቁ። ደንበኞቼ የምርመራ ቃላቸውን ለፖሊስ ከመስጠታቸው በፊት ላገኛቸው ሲገባ ይህ አልተደረገም ያሉት ጠበቃው፤ የጊዜ ቀጠሮው ችሎት እስኪጠናቀቅ ድረስ ለቀጣዩ አንድ ወር ደንበኞቻቸውን እንደማያገኙና ሕግን ባልጠበቀ መንገድ ለሚከናወን ተግባር የፕሮፓጋንዳ ሽፋን መሆን እንደማይፈልጉ አስታውቀዋል።
ጠበቃ ተማም አባቡልጉ ለአንድነት ፓርቲ አባላቱ ለሀብታሙ አያሌውና ለዳንኤል ሺበሺ፤ ለአረናው አብርሃ ደስታ እና ለሰማያዊ ፓርቲው የሽዋስ አሰፋ ጠበቃ ሆነው በማገልገል ላይ ይገኙ የነበሩ ሲሆን፤ ደረሰብኝ ባሉት ጫና እና ኢ-ሕገመንግስታዊ አሰራር ምክንያት ከደንበኞቻቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለጊዜውም ቢሆን ማቋረጣቸውን ለፓርቲዎቹ አመራሮች መግለፃቸውን አስረድተዋል። ይህም በመሆኑ ሦስቱ ፓርቲዎች (ማለትም አንድነት፣ ዓረና እና ሰማያዊ) በእስረኞቹ ላይ እየደረሰ ያለውን ኢ-ፍትሐዊ ድርጊት በተመለከተ ዛሬ መስከረም 21 ቀን 2007 ዓ.ም በአንድነት ቢሮ ጋዜጣዊ መግለጫ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።
እንደማንኛውም ጠበቃ ደንበኞቼን ማግኘት ቢኖርብኝም፤ ላገኛቸው አልቻልኩም፤ በፍርድ ቤት የምናቀርባቸው አቤቱታዎች እና ስሞታዎች በሙሉ ያለበቂ ምክንያት ውድቅ ይደረጉብናል፣ ይባስ ብሎም ኢ-ፍትሐዊ አሰራር በመኖሩ ለስርዓቱ ሕጋዊ ከለላ መሆን አልፈልግም የሚሉት አቶ ተማም አባቡልጉ፤ በዚህም ምክንያት የታሰሩት የፖለቲከኛ እስረኞች ምንም ዓይነት ሕጋዊ ከለላ ማግኘት አልቻሉም ሲሉ ነገ በሚደረገው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደሚያነሱ ምንጮች ጠቁመዋል።
በጥቅምት 15 ቀን 2007 ዓ.ም ተጠርጣሪዎቹ በጊዜ ቀጠሮ ችሎት የሚቀርቡት ያለጠበቃ ቢሆንም፤ ምናልባትም ከወር በኋላ ዐቃቤ ሕግ ክስ የሚመሰርት ከሆነ፤ በችሎት ተገኝቼ ደንበኞቼን አገለግላለሁ የሚሉት ጠበቃ ተማም አባቡልጉ፤ ደንበኞቼ ቃላቸውን ከመስጠታቸው በፊት እኔን ማግኘት ሲገባቸው ሳያገኙኝና ቃላቸውን ሰጥተው ከፈረሙ በኋላ ባገኛቸው ምን አደርግላቸዋለሁ? ሲሉ ጥያቄ አዘል ኀሳባቸውን ይሰነዝራሉ። ከዚህም ባሻገር ደንበኞቼ ከተጠረጠሩበት ጉዳይ ውጪ በሆነ መልኩ የሚደረግባቸው ምርመራ በፓርቲ ጉዳይ ላይ ሆኗል ሲሉ ቅሬታቸውን የሚያቀርቡት ጠበቃው፤ ለዚህም ጠንካራ አባል ማነው? የገንዘብ ምንጫችሁ ከየት ነው? የሚሉ ጥያቄዎች ቀርበውላቸው እንደነበር ደንበኞቼ ለፍርድ ቤት ቀርበውም አመልክተዋል ሲሉ ያስረዳሉ።
      ይህም በመሆኑ የተላላኪነት ስራ ከመስራት ውጪ የምፈይደው ነገር የለም በሚል ለጊዜው ከደንበኞቼ ጋር መገናኘቱን አቁሜያለሁ ያሉት ጠበቃ ተማም፤ በዚህ አጋጣሚ ደንበኞችዎ ምን ሊያጋጥማቸው ይችላል ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፤ “የሚደርስባቸው ሁሉ ደርሶባቸዋል፤ እኔም ኖሬ ምንም አይነት የሕግ ከለላ አላገኙም” ሲሉ መልሰዋል።
ምንጭ፡ ሰንደቅ ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment