Monday, 27 October 2014

ዝምታ ወርቅ አይደለም

ሰውዬው ከሚስቱ ሌላ አንዲት ሴት ወደደና እፍ ክንፍ አለ፡፡ ልጁን እና ሚስቱን እየተወ ከዚህችኛይቱ ጋር ማምሸት፣ ብሎም ማደር ጀመረ፡፡ በመጨረሻም አንድ ቀን ወደ ሚስቱ መጣና ድንገተኛ የሆነ ጥያቄ አቀረበ፡፡ «እኔ እና አንቺ እንድንፋታ እፈልጋለሁ፤ ለምን ብለሽ ምክንያቱን አትጠይቂኝ፡፡ መፋታት ብቻ እፈልጋለሁ፡፡ ደግሞም ሌላ ቀን አይደለም፣ ነገ እንዲሆን እፈልጋለሁ» አላት፡፡ ሚስቱ በሁለት ነገሮች ተጨነቀች፡፡ በአንድ በኩል ምንም ነገር አትጠይቂኝ ብሏታል፡፡ በሁለተኛ ነገር ልጇ ወደ ዩኒቨርሲቲ የመግቢያ ፈተና ልትቀመጥ ጥቂት ቀናት ቀርቷታል፡፡
«ባልፈልገውም፣ ባልስማማበትም፤ ካልክ የግድ እቀበለዋለሁ፡፡ ነገር ግን በኛ ምክንያት ልጃችን መጎዳት የለባትምና የአንድ ወር ጊዜ ያህል እንታገሥ፡፡» አለችው፡፡ እርሱም አሰበና «ጥሩ አንድ ወር መታገሥ አያቅተኝም፤ ነገር ግን በዚህ አንድ ወር ውስጥ ሽማግሌ መላክ፣ ምክንያቱን መጠየቅ የለም፤ ስለ ፍቺው ማናችንም ምንም ነገር ማንሣት የለብንም፤ በዚህ ቃል ግቢ» አላት፡፡ እርሷም «እስማማለሁ፤ ግን አንተም የምነግርህን ለመፈጸም ከተስማማህ ነው፤ ታድያ በዚህ አንድ ወር ጠዋት ጠዋት ከዕንቅልፌ ስነሣ፣ ማታ ማታም ወደ አልጋዬ ስሄድ ያኔ የሠርጋችን ዕለት አቅፈህ እንደ ወሰድከኝ አድርገህ አቅፈህ ትወስደኛለህ» ስትል ጠየቀችው፡፡ ነገሩ ያልጠበቀው እና ያልተለመደ ዓይነት ቢሆንበትም፣ ቀላል እና ሊያደርገው የሚችል ስለሆነ እሽ ብሎ ቃል ገባላት፡፡
አንዱ ወር ተጀመረ፡፡
ጠዋት ጠዋት ከዕንቅልፏ ስትነሣ አቅፎ፣ ከፍ አድርጎ፣ ወደ በረንዳ ካደረሳት በኋላ ወደ ሥራው ይሄዳል፡፡ ማታ ማታም እንዲሁ አቅፎ ወደ አልጋዋ ይወስዳታል፡፡ ስለ ፍችው አይነጋገሩም፡፡ እየዋለ እያደረ ሲሄድ የሰውነቷ ጠረን፣ የምትለብሳቸው ልብሶቿ፣ የዓይኖቿ እና የፀጉሯ ሁኔታ፣ የገላዋ ልስላሴ እና የአካሏ ቅርጽ እየሳቡት መጡ፡፡ በየቀኑ እያቀፈ ሲያወጣት እና ሲያስገባት ሰውነቷ እየቀለለው፤ ለርሱም እርሷን አቅፎ መሸከሙ አንዳች እንግዳ የሆነ የደስታ ስሜት እየፈጠረለት መጣ፡፡
ከራሱም ጋር ሙግት ጀመረ፡፡ «ለምንድን ነው እንፋታ ያልኳት፤ አሁን የሚሰማኝን ስሜት ያህል ስሜት ከአዲሷ ወዳጄ ጋር ለምን አይሰማኝም? ለምንስ ነበር ይህንን ነገር እንዳደርገው ቃል ያስገባችኝ ? ይህን የመሰለውን ገላዋን፣ እንዲህ የሚማርከውን ጠረንዋን፣ እንዲህ የሚያስደስተውን ፈገግታዋን፣ እንዲህ የተዘናፈለውን ፀጉሯን፣ እንዲህ ልዩ የሆነውን አካሏን እንዴት እስከ ዛሬ አላስተዋልኩትም ?እርሷ ናት ከኔ ጋር የነበረችው ወይስ እኔም ከርሷ ጋር ነበርኩ?»
የወሩ መጨረሻ እየደረሰ መሆኑን ሲያውቅ ከእርሷ መለየቱ ጨነቀው፡፡ እንዲያውም ይህ ሁኔታ የፈጠረበትን እንግዳ ስሜት እየወደደው መጣ፡፡ ነግቶ እና መሽቶ እርሷን አቅፏት እስከሚወስዳት በጉጉት መጠበቅ ጀመረ፡፡ በሌላም በኩል ደግሞ በዚህ ድርጊቷ በውስጡ ያሳደረችበትን ስሜት እያሰበ ያደንቃትም ጀመር፡፡ ብልህነቷን፣ አስተዋይነቷን እና በቀላል ድርጊት ቀልቡን ልትገዛው መቻሏን ሲያስበው «ምን ዓይነት አስገራሚ ሴት ናት?» ይላል፡፡
ወሩ ሊያልቅ ሁለት ቀን ሲቀረው የመፋታቱን ሃሳብ በውስጡ መረመረው፡፡ ነገር ግን አላገኘውም፡፡ በዚህ ሁኔታ መፋታቱ ደግሞ ለሕይወቱ የማይፈታ ዕንቆቅልሽ እንደሚሆንበት እያሰበ ተጨነቀ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በዚህ አንድ ወር ውስጥ ፍችን በተመለከተ ላለመነጋገር ቃል ተግባብተዋልና እንዴት አድርጎ ይናገር፡፡ ዛሬም በደስታ ስሜት አቅፎ ከአልጋዋ እንደወሰዳት ሁሉ ማታ ወደ አልጋዋ መለሳት፤ ከበፊቱ እጅግ በጣም ቀለለችው፤ አሳዘነችውም፡፡
በወሩ መጨረሻ፡፡
ወደ አዲሲቱ ወዳጁ ዘንድ ሄደና «የፍችውን ሃሳብ ሠርዤዋለሁ፡፡ እኔና ባለቤቴ ፍቅር የሌለን መስሎኝ ነበር፡፡ እኛ ግን ለካስ ፍቅር አላጣንም፡፡ ያጣነው ሁለት ነገሮች ብቻ ነው፡፡ መነጋገር እና መቀራረብ፡፡ ለዚህ ያደረሰንም አለ መቀራረባችን እና አለመነጋገራችን ብቻ ነው፡፡ አሁን ግን መነጋገር ባንችል እንኳን መቀራረብ ግን ችለናል፡፡ ዛሬ ደግሞ መነጋገር እንችላለን፡፡ ስለዚህ ሌላ የሚሆንሽን ፈልጊ» አላት፡፡
ሴትዮዋ ተናደደችና በጥፊ መታችው፤ ከአጠገቧ የነበረውንም ውኃ ቸለሰችበት፤ «ይሄ ለብዙው ኃጢአቴ የተከፈለ ቅጣት ነው» እያለ ወጥቶ ሄደ፡፡ ከዚያም ወደ አበባ መሸጫ ሱቅ ውስጥ ገባ፡፡ ያኔ ሲጋቡ የገዛላትን ዓይነት አበባ ገዝቶ ወደ ቤቱ ከነፈ፡፡ «ጓደኛዬ ትዳር ማለት አግብተው የሚኖሩት ሳይሆን በየጊዜው የሚጋቡት ነው ያለው እውነቱን ነው፡፡ ትዳር እንደ አሥራ ሁለተኛ ክፍል ፈተና አንድ ጊዜ አልፈውት ሰርተፊኬቱን የሚሰቅሉት አይደለም ያለው እውነቱን ነው፡፡ ትዳር እና ተክል ክብካቤ ይፈልጋሉ፡፡ እንዲሁ ቢያድጉ ይደጉ ተብለው የሚተው ነገሮች አይደሉም፡፡
«ልክ እዚህ ሀገር ችግኝ የመኮትኮት፣ የማጠጣት፣ የመከባከብ እና የማሳደግ እንጂ የመትከል ችግር እንደሌለብን ሁሉ፤ እኛም ጋር የመጋባት ችግር የለም፡፡ ፍቅር ግን ማግባትን ብቻ ሳይሆን ማጠጣትን፣ መኮትኮትን፣ ማረምን፣ ከብት እንዳያበላሸው አጥር ማጠርን፣ በየጊዜው ማዳበርያ መጨመርን ጭምር ይፈልጋል፡፡ በርግጥ በዕድሉ የሚበቅል ዛፍ እንዳለው ሁሉ በእድሉ የሚኖር ትዳርም ይኖር ይሆናል፡፡ ይህ ግን ሕይወትን ለራስ ጥረት ሳይሆን ለአጋጣሚዎች ብቻ አሳልፎ መስጠት ነው» ያለው እውነቱን ነው፡፡ እኔ አልሰማሁትም እንጂ እርሱስ ተናግሮ ነበር፡፡»
መኪናውን አቆመና ወደ ግቢው ውስጥ ገባ፡፡ በረንዳ ላይ ትጠብቀው የነበረችው ባለቤቱ የለችም፡፡ በሩንም አንኳኳ፡፡ የሚከፍት ግን አልነበረም፡፡ ደግሞ ሲያንኳኳ ገርበብ ብሎ የተዘጋው በር በራሱ ጊዜ ተከፈተ፡፡ ባለቤቱ ግን በዚህች በወሩ ሠላሳኛ ቀን ሳሎንም የለችም፡፡ እየተገረመም፣ ግራ እየተጋባም ወደ መኝታ ቤቱ ዘለቀ፡፡ አልጋው ላይ ፈገግ እንዳለች ጋደም ብላለች፡፡ አበባውን እንደያዘ ጠጋ አለና በእጁ ጉንጯን ነካው፡፡ ቀዝቅዟል፡፡ በቁልምጫ ጠራት፡፡ መልስ ግን አልነበረም፡፡ ግራ ተጋብቶ ዓይንዋን ገለጥ አደረ ገው፡፡ ሊገለጥለት ግን አልቻለም፤ በርከክ አለና ሰውነቷን ደባበሰው፤ ቀዝቅዟል፡፡
«የመጨረሻው ቀን ነው፤ ይህችን ቀን ማየት አልፈልግም፤ ለልጄ ስል እስከዛሬ ታግሻለሁ፤ በቃኝ» የሚል ጽሑፍ ራስጌዋ ላይ አገኘ፡፡
እርሷ ፍችውን አትፈልገውም፤ ስለዚህም ሳትፋታ ሞተች፡፡ በርሱ ውስጥ የነበረውን የሃሳብ ለውጥ አላወቀችም፤ ምክንያቱም ላይነጋገሩ ቃል ተግባብተው ነበርና፡፡ እርሷ የዛሬዋን ቀን በስጋት እና በጭንቀት ነበር የጠበቀቻት፡፡ የመለያያቸው ቀን፤ የሕይወቷን ግማሽ የምታጣበት ቀን፡፡ የማትፈልገውን ነገር የምታደ ርግበት ቀን ናትና፡፡ እርሱ ግን የዛሬዋን ቀን በጉጉት ነበር የጠበቃት፡፡ የሚነጋገሩባት ቀን፤ ፍችውን እንደተወው የሚነግርባት ቀን፤ ፍቅሩን የሚነግርባት ቀን፤ ይቅርታ የሚጠይቅባት ቀን፤ ለፍቅሩ ሲል ትን ሽም ብትሆን ቅጣት ከፍሎ የመጣባት ቀን፤ በእርሱ እና በባለቤቱ መካከል የመነጋገር እና የመቀራረብ እንጂ፣ የመዋደድ እና ስሜት ለስሜት የመስማማት ችግር እንደሌለ መረዳቱን የሚገልጥባት ቀን ናትና፡፡ ግን ምን ያደርጋል፤ ሁለቱም ይህንን በየልባቸው ያውቁታል እንጂ አልተነጋገሩም፤ ሃሳባቸውንም በሌላ መንገድ አልተለዋወጡም፡፡ በዚህ የተነሣም በችግሩ መፍቻ ቀን ዋናው ቸግር ተፈጠረ፡፡
ሁለት የትዳር ነቀርሳዎች፡- አለመቀራረብ እና አለመነጋገር፡፡ አብረው አንድ አልጋ ላይ እያደሩ፤ አብረው እየበሉ፤ አብረው እየኖሩ የማይቀራረቡ ባል እና ሚስት አሉ፡፡ አንድ አልጋ ላይ የሚተኙት አንድ አልጋ ላይ መተኛት ስላለባቸው ብቻ ነው፡ ከመጋባታቸው በፊት የነበራቸው ጉጉት እና ናፍቆት አሁን የለም፡፡ ሳይተኙ እንቅልፍ ይወስዳቸዋል፡፡ አብረው ይበላሉ፤ በአንድ ማዕድ መሆኑ፣ አንድ ጠረጲዛ ላይ መሆኑ እንጂ ያኔ በፊት ለምሳ ሲገባበዙ የነበረው ናፍቆት እና ጉጉት የላቸውም፡፡ ዝም ብሎ መብላት ብቻ፡፡
እያንዳንዷን ቀን ልዩ፣ ደስታ የሚፈጠርባት እና ከትናንት የተለየች ለማድረግ አይጥሩም፡፡ ዛሬም እንደ ትናንቱ፣ ነገም እንደ ዛሬ ነው፡፡
በስንት ልመና በስንት ጥየቃ፣
በስንት ደጅ ጥናት በስንት ጥበቃ፣
እንግዲህ ምን ቀረሽ አገባሁሽ በቃ፣
እንደተባለው ይሆንባቸዋል፡፡ አገባኋት በቃ፤ አገባሁት በቃ፤ ከንግዲህ ምን ቀረ? ብለው ያስባሉ፡፡ ሰው ተፈጥሮ አላለቀም፡፡ በየጊዜው ነው የሚፈጠረው፡፡ ፈጣሪም ሰውን እንደ ተወለደ እንዲያልቅ አላደረገውም፡፡ በየቀኑ፣ በየሰዓቱ፣ በየደቂቃው ላስተዋለው ሰው እንግዳ ፍጥረት ነው፤ አዳዲስ ነገር ይታይበታል፡፡ ይህ ግን መቀራረብን ይጠይቃል፡፡ ባል እና ሚስት ከተቀራረቡ ሳይፋቱ በየቀኑ ይጋባሉ፤ ጋብቻቸው እየታደሰ ይሄዳል፡፡ የትና ንቷ ሚስት ከዛሬዋ ትለያለች፤ የዛሬው ባልም ከትናንቱ የተለየ ነው፡፡ ለውጥ፣ ዕድገት፣ ብስለት፣ አለ፡፡ መልክም ተለውጧል፡፡ ግን ቀርቦ የሚያየው ያስፈልገዋል፡፡
የዚያ ባል ችግሩ ሚስቱን አግብቷት እንጂ ቀርቧት አያውቅም ነበር፡፡ አብሯት ይኖራል እንጂ ከርሷ ጋር አይኖርም ነበር፤ ምድር በፀሐይ ዙርያ ስለምትዞር ይመሻል ይነጋል እንጂ በእነርሱ የተለየ የሕይወት ጉዞ ምክንያት አይመሽም አይነጋም፡፡ በማክሰኞ እና በረቡዕ መካከል ከስሙ በቀር በሕይወታቸው ውስጥ ልዩነት የለውም፡፡
ሌላው ችግር ደግሞ ያለ መነጋገር ነው፡፡ መነጋገር ማለት በሚያውቁት ቋንቋ ማውራት ማለት አይደለም፡፡ እርሱንማ ከብትም ሲገናኝ እምቧ እምቧ ይባባላል፡፡ ይህ ግን መነጋገር አይደለም፡፡ በየጊዜው፣ በየሰዓቱ፣ ሁለመናን መለዋወጥ ማለት ነው፡፡ ካልተነጋገሩበት የምሥራች፣ የተነጋገሩበት መርዶ ይሻላል፡፡ ካልተነጋ ገሩበት ፍቅር የተነጋገሩበት ጠብ ይበልጣል፡፡ ካልተነጋገሩበት ስጦታ የተነጋገሩበት ንጥቂያ ይሻላል፡፡
ባል እና ሚስቱ ባለመነጋገራቸው ችግሩን በሁለት አቅጣጫ ፈቱት፡፡ የሁለቱም ፍላጎት ችግሩን ላንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ መፍታት ነበር፡፡ የሁለቱም ፍላጎት ፍቺ የሚባለውን ነገር ላለማየት ነበር፡፡ የሁለቱም ፍላጎት ሠላሳኛዋን ቀን መገላገል ነበር፡፡ ነገር ግን ባለ መነጋገር ምክንያት በሁለት አቅጣጫ ሆነ፡፡ እርሷ ሞትን መረጠች፤ እርሱ ደግሞ ይቅርታን መረጠ፡፡ ችግሩ የመጣው በዚህ ጉዳይ ላለመነጋገር ሲወስኑ ነው፡፡ እርሷ በጉዳዩ ትጨነቃለች፤ ለምን ይሆን ከኔ መለየት የፈለገው? የሚለው ጥያቄ ያሳስባት ነበር፡፡ በሃሳብ ብዛትም እየከሳች ሄዳ ነበር፡፡ ለዚህም ነበር በየቀኑ ሲያቅፋት ትቀልለው የነበረው፡፡ እርሱ ግን መቅለሏን እንኳን ለመጠየቅ ፈራ፡፡ እርሱ ከራሱ ጋር እንጂ ከእርሷ ጋር አይነጋገርም ነበር፡፡
እናም አንዳንድ ጊዜ አስፈላጊ ቢሆንም እንኳ፤ በትዳር ውስጥ ግን ዝምታ ወርቅ አይደለም፡፡

No comments:

Post a Comment