ቅዱስ ሲኖዶስ: ‹‹እነማን ናቸው ከጀርባዎ ያሉት?›› ሲል ፓትርያርኩን ጠየቃቸው፤ በቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ተጠሪነት አንቀጽ ላይ የተጀመረው ውይይት በመካረር አደረ
- አቡነ ማትያስ÷ የሊቃነ ጳጳሳትንና ኤጲስ ቆጶሳትን ተጠሪነት ለፓትርያርኩ በማድረግ በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖት ሕገ ቤተ ክርስቲያን የመጨረሻው ከፍተኛ ሥልጣን ባለቤት የኾነውን የቅዱስ ሲኖዶሱን የበላይነት በፓትርያርኩ የበላይነት ለመተካት ከምልአተ ጉባኤው ጋራ መሟገታቸውን አጠናክረው ውለዋል፡፡
- የቅዱስ ሲኖዶስ አመራር ያላትን ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን፣ በፓትርያርኩ ዐምባገነናዊ አመራር ሰጪነት በመርገጥ በስም እንጂ በግብር የሥልጣን ልዕልና የሌለው ሲኖዶስ ለመፍጠር እየተጣጣሩ ነው፡፡
- ቤተ ክርስቲያን አንድነትን በሚጠይቅና ከፍተኛ የጥንቃቄ ርምጃዎችን በሚሻ የህልውና ጥያቄ ላይ እንዳለች ያጤኑ የምልአተ ጉባኤው አባላት፣ ፓትርያርኩ የልዩነት ነጥቦችን በማክረር ቤተ ክርስቲያኗን ለኹለት ለመክፈል ላደፈጡ ኃይሎች መሣርያ ሊኾኑ እንደሚችሉ ተገንዝበዋል፡፡
- ‹‹ቅዱስነትዎ በጣም ተቀይረዋል፤ እነማን ናቸው ከጀርባዎ ያሉት?›› ሲልም ጠቅላላውን ጉዳይ በጥልቅ አስተውሎት በመመርመርበቤተ ክርስቲያኗ እና በቤተ ክርስቲያኗ ላይ ብቻ አጠንጥኖ መሥራት እንደሚገባ አጽንፆት ሰጥቶበታል፡፡
- ልዩነት በተያዘባቸው የመነጋገርያ ነጥቦች ላይ ከሌላ አካል የተመከሩበት የሚመስለውን ብቻ እየተናገሩ አቋማቸውን ከማክረር በቀርማብራራትና መተንተን በእጅጉ እንደተሳናቸው የተነገረባቸው ርእሰ መንበሩ፣ ‹‹የነበረው ሕግ እንዳይሠራ የማሻሻያ ረቂቁም እንዳይጸድቅ›› የሚመስል ‹‹ሲኖዶሱን የመበተን›› አዝማሚያ እያሳዩ እንደመጡ ተስተውሏል፡፡
* * *
- በሥራ ላይ የሚገኘው የ፲፱፻፺፩ ዓ.ም. ሕገ ቤተ ክርስቲያን÷ ቅዱስ ሲኖዶስ ማለት ፓትርያርክ፣ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ጳጳሳትና ኤጲስ ቆጶሳት የሚያደርጉት ዓቢይ ጉባኤ እንደኾነ ይገልጻል፡፡ በአኹኑ የማሻሻያ ረቂቅም ቅዱስ ሲኖዶስ ማለት ‹‹ቅዱስ ፓትርያርክ፣ ሊቃነ ጳጳሳትና ኤጲስ ቆጶሳት የሚገኙበት ዐቢይ ጉባኤ ኾኖ ከፍተኛው የቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ፣ ሕግ አውጭና አስተዳደራዊ አካልነው፡፡›› ይላል፡፡
- ከቅዱስ ፓትርያርኩ ጀምሮ እያንዳንዱ ሊቀ ጳጳስና ኤጲስ ቆጶስ(ጳጳስ) ተጠሪነቱ ለቅዱስ ሲኖዶስ እንደኾነ ‹‹የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት›› በሚለው የማሻሻያ ረቂቁ አንቀጽ ፰(፪) ተቀምጧል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ርእሰ አበው (አበ ብዙኃን) የኾነው ፓትርያርኩ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤንና የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤን በሊቀ መንበርነት(በርእሰ መንበርነት) ይመራል፡፡ ይኸውም ለመላዋ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ‹‹የበላይ ጠባቂ፣ ለአንድነትዋና ለአስተዳደርዋ ከፍተኛ ሓላፊና ባለሙሉ ሥልጣን›› በመኾኑ እንደኾነ በሰበካ ጉባኤው ቃለ ዐዋዲ ደንብ አንቀጽ ፶፪(፩) ሰፍሯል፡፡
- ይህም ሲባል ጠቅላላው የቤተ ክርስቲያን ጉባኤ ከፖፑ ሥልጣን በላይ ነው የሚለውን መነሣሣት (anti-papal concilliarism) በመቃወም፣ ፖፑ ‹‹የማይሳሳት የክርስቶስ እንደራሴና የአብያተ ክርስቲያናት ኹሉ የበላይ›› አድርጋ የፖፑን የሥልጣን የበላይነት (Primacy) በቫቲካን የመጀመሪያው ጉባኤ እንዳጸደቀችው የሮም ካቶሊክ አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመጨረሻው ከፍተኛ የሥልጣን ባለቤት በመንፈስ ቅዱስ የሚመራውና የመንበረ ሐዋርያት ወራሽ የኾነው ቅዱስ ሲኖዶስ ነው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ቤተ ክርስቲያንን በበላይነት የመምራት፤ የማስተዳደር፤ የመጠበቅ፤ ፍትሕ መንፈሳዊ በሚፈቅደው መሠረት ሕጎችን፣ ደንቦችንና ልዩ ልዩ መመሪያዎችን የማውጣት፣ የማሻሻል፣ የመሻር የዳኝነት ሥልጣን አለው፡፡ ቤተ ክርስቲያንንና የቤተ ክርስቲያን ጉዳዮችን በተመለከተ ቅዱስ ሲኖዶስ የሚሰጠው ውሳኔ የመጨረሻ ነው፡፡
- በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ሕገ ቤተ ክርስቲያን አተረጓጎም፣ ‹‹የቅዱስ ሲኖዶስ አመራር›› ሲባል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የበላይ አካል የኾነውን በየደረጃው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ፣ ቅዱስ ፓትርያርክ፣ ቋሚ ሲኖዶስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ሥልጣንና ተግባር፣ አሠራርና ዓላማ ለቤተ ክርስቲያን ዓላማዎች ማስፈጸሚያ፣ አስተዳደራዊ መዋቅሮችና ተቋማት ማቋቋሚያና ማሠርያ መመሪያ የሚሰጥበት ነው፡፡
- ፓትርያርኩ የቅዱስ ሲኖዶሱን አካላትና የቤተ ክርስቲያንን አጠቃላይ ስብሰባ (አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ) በሰብሳቢነት ይምራ እንጂ በዐበይት ጉዳዮች ላይ ኹሉ ሲሠራ በቅዱስ ሲኖዶሱ ማስወሰን ይኖርበታል፡፡ በፊርማው የሚያስተላልፋቸው ሕጎች፣ መመሪያዎችና ውሳኔዎች ኹሉ በቅዱስ ሲኖዶሱ የወጡ መኾን አለባቸው፡፡ ሃይማኖትንና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን ከመጠበቅና ከማስጠበቅ ሓላፊነቱ ጎን ለጎን ቅዱስ ሲኖዶሱ ያወጣቸው ሕጎች፣ ያስተላለፋቸው መመሪያዎችና ውሳኔዎች በሥራ ላይ መዋላቸውን በመከታተልና በመቆጣጠር የቅዱስ ሲኖዶሱን የበላይነት(ልዕልና) የማስከበር ከፍተኛ ሓላፊነት አለበት፡፡
‹‹እነማን ናቸው ከጀርባዎ ያሉት?›› …
linkየአማሳኞች ዋነኛ ቡድን መሪ የኾነው ሊቀ ትጉሃን ዘካርያስ ሐዲስ÷ ትላንት ተሲዓት ስብሰባው በድንገት ከተቋረጠ በኋላ ምሽት ላይ ፓትርያርኩን አግኝተዋቸው እንደነበር ተናገረ፡፡ እንደ ሊቀ ትጉሃን ዘካርያስ አነጋገር፣ ፓትርያርኩ ከስብሰባው የወጡት ተብረክርከው ነበር፡፡‹‹ለማይኾን ነገር አሠቃያችኁኝ›› ብለው እንዳማረሯቸውም አልሸሸገም፡፡ ‹‹የወሰዱት አቋም ታሪካዊ ነው፤ በተለይ በማኅበረ ቅዱሳን ላይ›› በማለት ‹‹መብረክረክ›› ሲል የገለጸውን አካላዊና ሥነ ልቡናዊ ቁመናቸውን ‹‹ሲያክሟቸው እንዳመሹ›› የጠቀሰው ሊቀ ትጉሃን ዘካርያስ፣ መንግሥት የማኅበሩ ገንዘብ ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ማእከላዊ ካዝና መግባቱን እንደሚፈልግና በጉዳዩ የጀመሩትን ጠንክረው እንዲገፉበት አበረታተናቸው ደስ ተሰኝተዋል ብሏል፡፡የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትን የፓትርያርኩ ልዩ ሀገረ ስብከት በማድረግም በፀረ ተቋማዊ ለውጥ እና በፀረ ማኅበረ ቅዱሳን ቅስቀሳቸው ሆ ብለው አልነሣ ያሏቸውንና ‹‹በሸዋ ጳጳሳት በተለይ በአቡነ ማቴዎስ ይመካሉ›› ያሏቸውን የገዳማትና የአድባራት አለቆች ‹‹ከአዲስ አበባ ለማንኮታኮት›› ማቀዳቸውን ገልጧል – ‹‹እያንዳንዱ ጳጳስ ተሸማቅቆ እንዲሔድ እናደርጋለን፤ ማኅበረ ቅዱሳን የሸዋ ስብስብ ነው፤ ነገ ጠዋት የሸዋ አለቃ ከያለበት ደብር ሲጠፋ የምትገቡበት እናንተ ናችኹ፡፡››
No comments:
Post a Comment