ሚያዝያ ፳፫ (ሃያ ሦስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከመንግስት የጸጥታ ሃይሎች የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው በዚህ ሳምንት ብቻ 9 ሺ 405 ወጣቶች ድንበር አቋርጠው ወደ ሱዳን ሲጓዙ በድንበር ጠባቂ ፖሊሶች ተይዘዋል።
ፋሲል የኔአለም ዝርዝሩን ያቀርበዋልበሰሜን ጎንደር ዞን ቆላማ ወረዳዎች በተደረጉ 2 የዳሰሳ ጥናቶች በቀን ከ150-250 በዓመት ደግሞ ከ 54,000 እስከ 90,00 ኢትዮጵያውያን ወደ ሱዳን ይሻገራሉ፡፡ ጥናቱ በመላው አማራ ወይም በመላው አገሪቱ ያለውን የስደት ቁጥር አይዳስስም።
በዚህ ሳምንት ብቻ ወደ ሱዳን ለመሻገር የሞከሩ 9 ሺ 405 ግለሰቦች በጸጥታ ሃይሎች ሲያዙ፣ የጃን አሞራ ፖሊስ ጽ/ቤት ለኢሳት በላከው መረጃ መሰረት በቁጥጥር ስር የዋሉት ሁሉም ሴቶች ናቸው። ከእነዚህ ሴት ስደተኞች ውስጥ 66 በመቶው ከ18 እስከ 24 እድሜ ያላቸው ሲሆን፣ 32 በመቶው ደግሞ ከ14 አመት በታች ናቸው። ወደ ሱዳን በመፍለስ ከፍተኛውን ቁጥር የያዙት የአርማጭሆ፣ በየዳ፣ ጃናሞራና ወገራ ወረዳዎች ሲሆን፣ በአካባቢው ያለው ድህነት ከሁሉም አካባቢዎች የከፋ ነው፡፡
ስደትን ከድህነት ማምለጫ አድርገው የወሰዱት በርካታ ህፃናትና ሴቶች በረሃ ላይ ሞተው የሚቀሩ ሲሆን ፣ ወደ ስደት በመሄድ ላይ እያሉ በተለያዩ ምክንያቶች ወደ መተማ ዮሃንስ ጤና ጣቢያ የመጡ 26ት ሴቶች በተቅማጥ፣ በመኪና አደጋ፣ በድብደባ ፣ራስን በማጥፋትና በሌሎችም ምክንያቶች ህይወታቸው አልፎአል። አለማቀፍ ስደተኞች ድርጅት /IOM/ በ2013 ባወጣው ጥናት ሳውዲ አረቢያ ፣ የመን፣የተባበሩት አረብ ኢምሬትና ወደ ሌሎች አገሮች በአመት ከ400ሺ-500 ሺ የሚሆኑ ዜጎች ከአገር ይወጣሉ።
በመተማ መስመር በቀን በአማካኝ ከ150-250 የሚሆኑ ሰዎች ወደ ሱዳን ፣ በአፋር መስመር ደግሞ በቀን በአማካኝ እስከ 80 የሚደርሱ ሰዎች ወደ ጅቡቲ ይሰደዳሉ።
ከአማራ ክልል ከሰሜን ወሎ እና የሰሜን ጎንደር ወረዳዎች፣ ከኦሮሚያ ክልል ደግሞ ከጅማ እና አርሲ አካባቢ የሚመለመሉ እድሜያቸው ከ18 ዓመት የማይበልጡ ሕፃናት ሴቶች በመተማ ሱዳን በኩል ይሻገራሉ። አብዛኞቹ ስደተኞች ሱዳን ከደረሱ በኋላ ሴቶች ለቤት ሠራተኝነት የሚቀጠሩ ሲሆን ወንዶች ደግሞ በእርሻ ቦታዎችና በኮንስትራክሽን ድርጅቶች በቀን ሠራተኝነት እንደሚሰማሩ መረጃዎች ያሳያሉ።
በአፋር ከልል ጅቡቲ መስመር የሚሰደዱት ደግሞ በአብዛኛው ከአማራ እና ከትግራይ ክልል የሚመጡ ሲሆን በተወሰነ መልኩም የኦሮሚያና የደቡብ ክልል ነዋሪዎች ይገኙበታል፡፡ በዚህ መስመር ከሚጓዙት ውስጥ አብዛኞቹ ከሚሴ፣ ባቲ፣ ወረኢሉ፣ ወረባቦ፣ ቢስቲማ፣ ቦከክሳ፣ ኮምቦልቻ፣ ጊራና፣ ዋድላናደላንታ፣ ወልድያ እና መርሣ ናቸው፡፡ አልፎ አልፎም ከሰሜን ሸዋ አካባቢዎች መነሻ በማድረግ በየቀኑ በቡድን በመሆን ከ10-80 የሚሆኑ ሰዎች በአንድ ላይ ተሰባስበው የአፋርን ክልል በማቋረጥ ከሀገር የሚወጡ ሲሆን በብዛት የሚሄዱባቸው መዳረሻ ሀገራትም ጅቡቲ፣ ሳውዲዓረቢያ፣ የመንና የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ናቸው፡፡
በኬኒያ በኩል ወደ ደቡብ አፍሪቃ የሚጋዙት ደግሞ በአብዛኛው ከደቡብ በተለይም ከከንባታና ከሀድያ አካባቢዎች የሚነሱ ዜጐች ናቸው። በእነዚህ መስመሮች ከሚወጡት ኢትዮጵያውያን መካከል ቁጥራቸው ቀላል የማይባል፣ በሊቢያና ሱዳን በረሃዎች ፣ በቀይ ባህርና በሜዲትራኒያን ባህሮች ህይወታቸው ያልፋል። ታሳክቶላቸው ወደ ተለያዩ አገራት የደረሱት ደግሞ በቅርቡ በሳውድ አረቢያ፣ የመን፣ ሊቢያና ደቡብ አፍሪካ እንደተመለከትነው አስከፊ የሆኑ ድርጊቶች ይፈጸሙባቸዋል።
መንግስት በአሁኑ ጊዜ የስደቱ ምንጭ ህገወጥ ደላሎች ናቸው ቢልም ብዙዎቹ ግን አይስማሙም። በአገሪቱ ውስጥ የተንሰራፋው ስር የሰደደ ድህነት፣ የመልካም አስተዳደር እጦት፣ ጭቆናውና ሙስና ዜጎችን ለስደት እየዳረጉ መሆኑን ብዙዎች ይስማማሉ። በገጠር የአገሪቱ ክፍል ያለው የእርሻ መሬት ጥበት ብዙ አርሶአደሮች መኖሪያቸውን እየተዉ ወደ ከተማና ወደ ውጭ እንዲሰደዱ እያደረጋቸው ነው። በከተማ ደግሞ የስራ አጡ ቁጥር ከመቼም ጊዜ በላይ ጨምሯል። በቅርቡ አይ ሲስ የተባለው አክራሪ እስላማዊ ታጣቂ ሃይል እንዲሁም በአገራቸው ያሉ ስደተኞች እንዲወጡ የሚጠይቁ ደቡብ አፍሪካውያን በኢትዮጵያ ስደተኞች ላይ የወሰዱት አስከፊ እርምጃ የአገሪቱ የመነጋገሪያ አጀንዳ በሆነበት ወቅት፣ አሁንም ሞትን ፊት ለፊታቸው እያዩ የሚሰደዱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ሲጨምር እንጅ ሲቀንስ አለመታየቱን መረጃዎች ያሳያሉ።
ኢትዮጵያውያን በአገሪቱ ውስጥ ይመለከተናል የሚሉ ወገኖች ሁሉ አፋጠኝ መፍትሄ ካላበጁ ፣ አገሪቱ በቀላሉ ወደ ማትመለስበት አስከፊ ሁኔታ ውስጥ ትወድቃለች በማለት እያሳሰቡ ነው።
No comments:
Post a Comment