የአርበኞች ግንቦት 7 የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ ሊቀመንበር ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ
ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያቀረቡት አስቸኳይ ጥሪ
የተከበራችሁ ወገኖቼ፤ ከሰላሳ በላይ የሆኑ ወገኖቻችን አይ ሲስ በተሰኘ ህሊና ቢስ፣ ፀረ-ሰው እና ፀረ-ስልጣኔ ቡድን በሊቢያ በአሰቃቂ ሁኔታ የመገደላቸው መርዶ ከትናንት ወዲያ ሚያዝያ 11 ቀን 2007 ዓም ደርሶን ኢትዮጵያዊያን በያለንበት በመሪር ሀዘን ውስጥ ነን። ዛሬ “እግዜር ያጥናህ” ወይም “እግዜር ያጥናሽ” የሚባል ሰው የለም። ሁላችንም ሀዘንተኞች ነን። ካጣናቸው ቁጥራቸው በብዙ እጥፍ የሚበልጥ ወገኖቻችን አሁንም በአራዶች መዳፍ ውስጥ መሆናቸው ሀዘናችን እጅግ የበረታ ያደረገዋል። ቁጥራቸው በትክክል የማይታወቅ ሆኖም በሺህ የሚገመቱ ኢትዮጵያዊያን ዛሬም ሊቢያ ውስጥ ናቸው። በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን አሁንም ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ናቸው። ሌሎች በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ደግሞ በየመን ከሰማይም ከምድርም በቦንብና በጥይት እየተማገዱ ነው።
ለምንድነው ኢትዮጵያዊያን እንዲህ እሳት ውስጥ ለመማገድ የምንደፍረው? መልሱ ግልጽ ነው። አገር ውስጥ ተስፋ የለም፤ ወያኔዎች ተስፋችንን አጨለሙት። ከሳዉዲ በመከራ የተመለሱ ወንድሞቻችን ናቸው በሊቢያ በኩል ለመሰደድ ሲሞክሩ በአይ ሲስ ተይዘው የታረዱት። ወያኔዎች አገራችንና ክብራችን ዘረፉን። ወያኔዎች ስብዕናችንን ገፈፉን።
የዘመኑ ጥቂት የህወሓት ቱጃሮች ፎቆችን እየገነቡ በነሱ መጥገብ እኛ እንድናገሳላቸው ይፈልጋሉ። የኢትዮጵያ ሕዝብ መራቡ፣ መታረዙ፣ መደህየቱ እውነት ነው፤ ሆኖም ግን “ተራብኩ”፣ “ታረዝኩ”፣ “ደኸየሁ” ብሎ መናገር አይችልም። እውነት መናገር ያስቀጣል፣ ያስወነጅላል። በፍርደ ገምድል ችሎት እውነት መናገር “ሽብርተኛ” ያስብላል። እስር ቤቶችን የተሞሉት ለእውነት፣ ለፍትህ፣ ለነፃናትና ለእኩልነት በቆሙ ሰዎች አይደለምን?
በአይ ሲስ ያሳረደን ማነው? መልሱ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ግልጽ ነው። ያዋረደን፣ በአይ ሲስ ቢላዋ ያሳረደን ህወሓት ነው። እንደ አገርና እንደ ሕዝብ የደረሰብን ውርደት የትም ብንሄድ የምናመልጠው አልሆነም። በአገር ውስጥ የደረሰብንን ውርደት ለማምለጥ ስንሰደድ ውርደት ተከትሎን ይመጣል።
ወገኖቼ፤ ለኛ ለኢትዮጵያዊያን ከኢትዮጵያ የተሻለች አገር ሊኖረን አይችልም። ዛሬ የመሸሻ ጊዜ አይደለም። አገራችንን ከወያኔ ነጥቀን፤ በአገራችን ኮርተን በሰላም መኖር እንሻለን። ይህ መብታችን ነው። አገራችን የኛ ነች። አገራችን የጥቂት ወያኔዎች መፈንጫ አይደለችም።
ወገኔ፤ ዛሬ ሚያዝያ 13 ቀን 2007 ዓም በአርበኖች ግንቦት 7 ስም የማደርግልህ ጥሪ አድምጠኝ። በሀይማኖት፣ በብሔር፣ በጾታ ልዩነት ሳታደርግ ዛሬ በአንድነት እንደተሳህ አንድነትህን እንደጠበቅህ ቀጥል። አንድነትህን ለመሸርሸር ወያኔ የማይፈነቅለው ድንጋይ አይኖርም፤ ለወያኔ ዱለታ ጆሮህን አትስጥ። የወያኔ አገዛዝ እንዲያበቃ በአንድነት ተነስ። ዛሬ የጀመርከው ትግል እዳር ሳይደርስ እረፍት የለንም።
አርበኞች ግንቦት 7፣ ከትግራይ፣ ከኦሮሚያ፣ ከአፋር፣ ከኦጋዴን፣ ከጋምቤላ፣ ከቤሻንጉል ድርጅቶች ጋር በመጣመር የአገር አድን ኃይል የመገንባት ሥራውን እያጠናቀቀ ነው። እኛ ልጆችህ በብሔርም ሆነ በሀይማኖት ሳንከፋፈል፤ ከትግራይ እስከ ኦጋዴን፤ ከአፋር እስከ ጋምቤላ ሁሉንም የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ባካተተ ስብስብ ውስጥ አብረን ህወሓትን እየታገልን ነው። ይህ ትግል ግን የአንተ የኢትዮጵያ ሕዝብ ትግል ነው። የትግሉም የአገሪቷም ባለቤት አንተ ነህ። ስለሆነም ተነስ! “እንቢኝ” በል። ዘርፈ ብዙ የትግል ስልቶችን በመጠቀም ወያኔን አዳክም። የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ! በትግልህ ፍሬ የአገርህ ባለቤት ሁን።
የመከላከያና የፓሊስ ሠራዊት አባላት ሆይ!እናንተ የሕዝብ አካላት ናችሁ። የደረሰብንን ብሔራዊ ውርደት እያያችሁ፤ እሮሮዓችን እየሰማችሁ በሕዝብ ላይ መተኮስ በራሳችሁ ጭንቅላት ላይ መተኮስ ማለት መሆኑን ለደቂቃ እንኳን አትዘንጉ። ይልቁኑ ዛሬውኑ ነፃነትና ፍትህ ከጠማው ወገናችሁ ጎን ቁሙ።
የኢትዮጵያ ወጣቶች፤ የወጣትነት የፈጠራ ችሎቻችሁ መፈተኛው አሁን ነው። ለእያንዳንዱ ጥቃቅን ጉዳይ መመሪያ እስኪሰጣችሁ አትጠብቁ። እያሰላችሁ፣ እያጠናችሁ፣ እያደባችሁ፣ ወያኔን ታገሉ።
የታፈረች፣ የተከበረችና የበለፀገች ኢትዮጵያን እውን እናደርጋለን።
ብርሀኑ ነጋ
የአርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ ሊቀመንበር
ሚያዝያ 13 ቀን 2007 ዓም
No comments:
Post a Comment