Tuesday, 5 May 2015

ታላቅ ህዝባዊ ስብሰባና የገቢ ማሰባሰቢ በኖርዌይ ኦስሎ ከተማ ተካሄደ!!

ዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ አዘጋጅነት በኢትዮጵያ ያለውን አፋኝ ዘረኛ የወያኔ አገዛዝን ለማስወገድ የሚደረገውን የሁለገብ ትግል ለመርዳትና አሁን ሀገራችን ያለችበትን አስከፊ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ለመምከር እ.ኤ.አ  አፕሪል 18, 2015 የተዘጋጀው ታላቅ ህዝባዊ ስብሰባና የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት የአርበኞች ግንቦት 7 ከፍተኛ ኃላፊ የሆኑት አቶ አበበ ቦጋለ እና የኢሳት ጋዜጠኛ ፋሲል የኔአለም እንዲሁም ከተለያዩ የኖርዌ ከተሞች በመጡ በርካታ ታዳሚዎች በተገኙበት በተሳካ ሁኔታ ተካሂዷል።

11156751_10153240544694441_1711534939_n16527_776277319135878_8932629015190402173_n

የዝግጅቱም መርሃ ግብር የድርጅቱ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አቢ አማረ እንግዶችን እንኳን ደህና መጣች በማለት በሃገራችን ያለውን አምባገነን ዘረኛ አገዛዝ በህዝባችን ላይ እያደረሰው ያለውን ግፍ ለማስቆም ሁላችንም በአንድ ላይ በመተባበር የሁለገብ ትግሉን በደገፍ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው በቅርቡ በደቡብ አፍሪካ እንዲሁም በሳኡዲ አረቢያ በወገኖቻችን ላይ የደረሰውን አሰቃቂ ግፍ አውስተው ለነኚህ ወገኖቻችን የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት በማስደረግ በይፋ ዝግጅቱን ያስጀመሩ ሲሆን በመቀጠል አቶ ዳዊት የወያኔን የግፍ አገዛዝ አውግዘው እርሳቸውም አገዛዙን ለማስወገድ ያለው ምርጫ ሁላችንም የሁለገብ ትግሉን መደገፍ እንደሚገባን ለህዝቡ ጥሪ አቅርበዋል።
ቀጣዩ ዝግጅት የነበረው በአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ የተደረሰውና የግንቦት 7 ህዝባዊ መዝሙር የሆነውን ላንቺ ነው ሀገሬ ላንቺ ነው ላንቺ ነው ኢትዮጵያ ላንቺ ነው የተሰኘውን ዝማሬ ከተለያዩ የኖርዌ ከተሞች የመጡ ወጣቶች በመድረክ ላይ አሰምተዋል። በመቀጠል የግብረኃይሉ ምክትል አስተባባሪ አቶ ደባሱ መለሱ የአርበኞች ግንቦት 7 ጥምረት ውህደትን አስመልክቶ እንዲሁም ያያዙንት የትግል ስልት በተመለከተ ሲያስረዱ ሁሉም ዜጋ በሀገሩ በእኩል የሚተዳደርባት ሀገር እንድትሆን ጥርጊያ መንገዱን እያደረጉልን የሚገኙ በመሆኑ የእኛ ድርሻ የሁለገብ ትግሉን መደገፍ እንዳለብን ጠቁመው የወያኔ ቡድን በሀገራችን ለ24 አመታት ስልጣኑ እንዲራዘም ያደረግነው እኛ ህብረት ባለማድረጋችን እንጂ ወያኔ በርትቶ ወይም ጠንካራ ሆኖ አለመሆኑን ተናግረው በየትኛውም ታሪክ ጥቂቶች ብዙሃኑን ያሸነፉበት ጊዜ አለመኖሩን አስታውቀው የከፋፍለህ ግዛን የወያኔ አገዛዝ በቅርቡ ለመጣል እንደሚቻል አሳውቀዋል።
በተጨማሪም ትግሉ ለምን በኤርትራ በኩል እየተካሄደ እንዳለና በዛ በኩል የሚደረገው ትግል ምን ጥቅም እንዳለው ለታዳሚው በዝርዝር በማስረዳት ኑ ተነሱና በጋራ ደጀንነታችን ሀገራችንን እናድን የሚል ጥሪ አቅርበው ኢትዮጵያ በልጆችዋ ተጋድሎ ወደነበረችነት ትመለሳለች ብለው መልክታቸውን ቋጭተዋል።
ቀጣዩ ተናጋሪ የነበሩትአቶ ዮሃንስ አለሙ  የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ የድጋፍ ድርጅትኖርዌይ ሊቀመንበር ና የግብረሀይሉ ሰብሳቢ ሲሆኑ ሀገራችን ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ሁኔታ ለዜጎቿ ምቹ ያልሆነ መሆኑ ጠቁመው ሁላችንም እራሳችንን መጠየቅ ያለብን እኔ ለሀገሬ ምን ማድረግ አለብኝ ምንስ አድርግያለሁ ብለን ማሰብና ውጠት ጠባቂዎች ብቻ ከመሆን ለውጤት መስራት እንዳለብን አሳስበው እኛ በኖርዌይ የምንኖር ሀገራችንን ነፃ ለማውጣት ተከታታይ ስራዎችን መስራት የምንችል በመሆኑ ለወደፊት ተከታታይ ትግል ማድረግ እንዳለብንና እንዴት መታገል እንደሚቻልም የተወሰኑ የትግል ስልት ነጥቦችን ዘርዝረዋል። እኛም መሰደዳችን አንገብግቦን ሀገር እንዲኖረን መታገል አለብን ብለን መነሳት አለብን ብለው ለአርበኞቻችን የማይነቃነቅ ደጀን እንሁን በማለት ለታዳሚው ጥሪያቸውን አስተላልፈው በሁለገብ ትግል ነፃነታችንን እንጎናፀፋለን ሲሉ ንግግራቸውን ጨርሰዋል።
በመቀጠል የኢሳት ጋዜጠኛ ፋሲል የኔአለም በመጀመሪያ አቋሙን ለታዳሚው ሲገልፅ በዚህ ታላቅ ስብሰባ ላይ የተገኘው እንደኢሳት ጋዜጠኛ ሳይሆን እንደ አንድ ነፃነቱን ናፋቂ  ኢትዮጵያዊ በመሆኑ ታዳሚው ሀሳቡን የራሱ የፋሲል የግል አስተሳሰብ እንጂ የኢሳት እንዳልሆነ በዚህ መልኩ እንዲረዱት አቋሙን በግልፅ ካስቀመጠ በኋላ የኢትዮጵያ የነፃነት ትግልና በኤርትራ ካለው ግንባር ጋር ስለነበራቸው ቆይታ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥቷል። ከምርጫ 97 ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ያለውን የነፃነት ትግል ሲዳስስ የተቃዋሚ ድርጅቶቹን የሚተቹትን በመተቸት የሚደገፉትን በመደገፍ የግል አስተሳሰቡን ሰፋ አድርጎ አቅርቧል። በኤርትራ ውስጥ ስላለው የአርበኞች ግንቦት 7 ወታደራዊ አቅምም ሲናገር በቂና አስተማማኝ ኃይል እንዳለ በአይኑ ያየውን መስክሮ በጣም ቆራጥ የሆኑ ታጋዮች እንደሆኑም በመናገር በፎቶ ግራፍና በቪዲዮ የተደገፉ ማስረጃዎችን አሳይትዋል።
የአርበኞች ግንቦት 7 ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ አበበ ቦጋለ በሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ሰፊ ዳሰሳና ትንታኔ ሲያደርጉ ኢትዮጵያዊ ህዝብ በሀገሩ የመኖር ዋስትና በማጣት በተለያየ አለም ተበትኖ ያለው ወገን እየደረሰበት ያለውን ግፍና መከራ ደካማ እኩይ የወያኔ ዘረኛ አገዛዝ ጫንቃችን ላይ በመሸከማችን መሆኑን በሚገባ ለታዳሚው በማስረዳት የአርበኞች ግንቦት 7 ሰራዊት አቅም ያለው ሰራዊት መሆኑን አስረድተው በቅርቡም ከደሚት ነፃ አውጪ ጋር በመዋሃድ አብሮ ለመስራት በንግግር ላይ መሆናቸውንና ከሌሎችም ሌሎችም በኤርትራ የሚገኙ ነፃነት ታጋዮች ወደ አንድነት እየመጡ በመሆኑ ከእለርሱ ጋርም በጋራ ለመስራት ከፍተኛ ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። ወደዚህ ስብሰባ የመጡትም ሰራዊቱ ህይወቱን ሰውቶ ሀገሩን ነፃ ለማውጣት ትግሉን መጀመሩን ጠቁመው እንኳንስ ሀገርን ነፃ የማውጣት ትግል ቀርቶ የየእለት ኑሯችን እንኳን ያለ ገንዘብ ማከናወን እንደማንችል ተናግረው ትግሉን አንድ እርምጃ ወደፊት ለማስኬድ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸውና የህዝቡን ደጀንነት እንደሚፈልጉ ተናግረው ብሄራዊ ውርደትን ለማስቆም በጋራ መስራት እንዳለብን አስረድተዋል።
በመቀጠል በዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት ወጣቶች ክፍል የተዘጋጀ የብቻ የሆነ ትግል ያደክማል አንድ መሆን ግን ይጠቅማል የሚል ትግል በአንድነት ውጤት እንደሚያመጣና አንድነት ኃይል መሆኑን የሚገልፅ ድራማ የቀረበ ሲሆን አዝናኝና ቀስቃሽ ባህላዊ ሙዚቃ ከውዝዋዜ ጋር እንዲሁም ምግብና መጠጥ ተዘጋጅቶ ነበር።
የውይይት ጊዜም ተዘጋጅቶ ታዳሚዎቹ ለተጋባዝ እንግዶቹ ጥያቄዎቻቸውን እና አስተያየቶቻቸውን በማቅረብ ሰፋ ያለ የውይይት ጊዜ ነበረ። በመጨረሻም የጨረታ ጊዜ በደማቅ ሁኔታና በታላቅ ፉክክር ለጨረታ ቀርቦ የነበረውን የኢትዮጵያ ባንዲራ በከፍተኛ ገንዘብ ለአሸናፊው ተሽጧል። የዲሞክራሲያዊ ለውጥ ድጋፍ ድርጅት ም/ሊ አቶ ዳንኤል የፕሮግራም መዝጊያ ንግግር አድርገው ዝግጅቱ በተያዘለት ሰአት ተጠናቋል።
ይህንን ዝግጅት ከፍተኛ በሆነ ሀገራዊ ስሜትና ቅስቀሳ ከመጀመሪያ ጀምሮ እስከመጨረሻ መድረኩን ሲመሩ የነበሩት የወጣቶችና የሴቶች ክፍል ኃላፊ ወ/ሪት የሺሃረግ በቀለ እና የወጣቶች ክፍል አመራር አቶ ይበልጣልጋሹነበሩ።
የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ

No comments:

Post a Comment