Thursday, 29 January 2015

ምርጫ ቦርድ አንድነትና መኢአድን ለእነ ትግስቱ አወሉና ለእነ አበባው መሃሪ ሰጠ

ሰበር ዜና

• ‹‹እውቅናውን የሰጠነው ለቦርዱ ለሚታዘዘው ነው›› ፕ/ር መርጋ በቃና


ምርጫ ቦርድ አንድነትን ለእነ ትግስቱ አወሉ፣ እንዲሁም መኢአድን ለእነ አበባው መሃሪ መስጠቱን ዛሬ ጥር 21/2007 ዓ.ም በሂልተን ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አሳወቀ፡፡ ምርጫ ቦርድ በመግለጫው ‹‹የእነ በላይ በፍቃዱ ቡድን›› በጠቅላላ ጉባኤ እንዳልተመረጠ፣ አምስት አባላት ያሉት አስመራጭ ኮሚቴ አባላት እንዳልመረጠ፣ የተመረጡበትም 51 ሲደመር አንድ መርህ አለመሆኑን፣ ጠቅላላ ጉባኤ ሲያደርግ ሪፖርት አለማድረጉንና ለአባላቱና ለፓርቲው ክብር የሌለው በመሆኑ ፓርቲውን ማስቀጠል እንደማይችል ገልጾአል፡፡


በሌላ በኩል የትግስቱ አወሉ ቡድን መርህ ይከበር እያለ እየታገለ በመሆኑ፣ የኢ/ር ግዛቸው ካቤኔ አባላት ተገፍተው የወጡ በመሆናቸው፣ ጠቅላላ ጉባኤ አድርገው ለቦርዱ ሪፖርት እንዳደረጉ፣ ‹‹የእነ በላይ ቡድን›› ፈቃደኛ ባለመሆኑ እንጂ እነሱ ችግራቸውን በውይይት ለመፍታት ፈቃደኛ በመሆናቸው እንዲሁም ለአባላቶቻቸውና ለፓርቲው ክብር ስላላቸው እውቅናውን ለእነሱ ሰጥቻለው ብሏል፡፡ ምርጫ ቦርድ በመግለጫው ‹‹ምርጫ የሚገባ ፓርቲ በማስፈለጉ፣ ‹‹የእነ በላይ ቡድን ፓርቲውን የሚያስቀጥለው ባለመሆኑና ፓርቲውን እንደ ፓርቲ እንዲቆይ ስለሚፈለግ ዛሬ ጥር 21 ቦርዱ ባደረው አስቸኳይ ስብሰባ እነ ትግስቱ አወሉ ወደ ምርጫ እንዲገቡ ወስኗል›› ብሏል፡፡


ፕ/ር መርጋ በቃና ‹‹የእነ ትግስቱ አወሉ ቡድን ያካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ የተሟላ ስለመሆኑ በምን ታረጋግጡልናላችሁ?›› በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ‹‹ሁለቱም ችግር አለባቸው፡፡ እኛ ያየነው በአንጻራዊነት ነው፡፡ የእነ ትግስቱ አወሉ ቡድን ችግር ቢኖርበትም ከዛኛው የተሻለ ነው፡፡ እውቅናውን የሰጠነው ለቦርዱ ለሚታዘዘው ነው፡፡›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡


በተመሳሳይ እነ ማሙሸት አማረ በጠቅላላ ጉባኤ ባለመመረጣቸው፣ ለተከታታይ 3 ወራት ወርሃዊ መዋጮ ያላወጣ አባል ከአባልነት የሚሰረዝ በመሆኑና ከፓርቲ አባልነትም ስለተባረሩ እንዲሁም ህገ ወጥ ማህተም በማሳተማቸው እውቅና እንዳልሰጣቸው ገልጾአል፡፡ በሌላ በኩል 2005 ዓ.ም ላይ አበባው መሃሪ የተመረጡበት ጠቅላላ ጉባኤ የተሟላ እንዳልነበር ቢታመንም በተደረገ ምርመራ የተሟላ መሆኑ በመታወቁ፣ በትክክለኛው ማህተም ስለሚጠቀም፣ ጠቅላላ ጉባኤ አድርጉ በተባለበት ወቅት ጠቅላላ ጉባኤ በማድረጉና ሪፖርቱንም ስላቀረበ ወደ ምርጫው እንዲገባ ወስኛለሁ ብሏል፡፡


አንድነት የተሰጣቸው የእነ ትግስቱ ቡድን፣ እንዲሁም መኢአድ የተሰጣቸው የእነ አበባው መሃሪ ቡድን በአሁኑ ወቅት ሁለቱንም ፓርቲዎች ወክሎ ጽ/ቤት ከሚገኘው የፓርቲ አመራር ጋር አለመግባባት በመፍጠራቸው በውጭ የሚገኙ መሆናቸው ይታወቃል፡፡

No comments:

Post a Comment