ጥር ፲፬(አስራ አራት ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ኢህአዴግና ምርጫ ቦርድ አንድነት ፓርቲ ለሁለት እንደተሰነጠቀ በማስመሰል ያቀነባበሩት ሴራ መጋለጡን እና መክሸፉን ከፓርቲው ጽሕፈት ቤት የደረሰን ዜና ያመለክታል።
ምርጫ ቦርድ “የአንድነትን ጠቅላላ ጉባኤ ጠርተዋል” ሲላቸው የነበሩት አቶ አየለ ስሜነህ፤ በዛሬው እለት “አንድነት አንድ ነው፤ እናት ፓርቲዬን ለማዳን ተመልሻለሁ” በማለት በአንድነት ፓርቲ ጽ/ቤት መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በአንድነት ስም ተጠራ የተባለውን የዲ-አፍሪኩን ስብሰባም እነሱ እንዳልጠሩትና ህገ-ወጥ ነው ብለው እንደሚያምኑ አቶ አየለ ተናግረዋል፡፡
የአንድነት ፓርቲ የሚዲያ ክፍል፤ ህወሃት/ኢህአዴግ፣ ምርጫ ቦርድ፣ ራዲዮ ፋና እና በቅርቡ ኢቢሲ የተባለው የቀድሞው ኢቲቪ ተቀናጅተው ሲሰሩ የሰነበሩትን ፕሮፖጋንዳ የሚያጋልጥ ዘጋቢ ፊልም ይፋ እንደሚያደርግም አስታውቋል፡፡ዘግይቶ በደረሰን መረጃ መሰረት <<ወደ ቤቴ ተመልሻለሁ>> ወደ እናት ፓርቲያቸው የተመለሱት እና የ ኢህአዴግን እና የምርጫ ቦርድን ሴራ ያከሸፉት አቶ አየለ ስሜነህ ከደህንነቶች ማስፈራሪያና ዛቻ እየተሰነዘረባቸው ነው።
<< አንድነት ኖረም አልኖረም፣ ይሄ ትግል ጥርጥር በሌለው ሁኔታ ይቀጥላል>> ሲሉ አቶ በላይ ፈቃዱ ገልጹ። የአንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ሊቀመንበር አቶ በላይ ፈቃዱ ከድርጅታቸው ልሳን ከፍኖተ-ነጻነት ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ፤ ፓርቲያቸው ወደነጻነት ትግል የሚያመራ ከመሆኑ አንጻር ምርጫ ቦርድ ተገቢ ባልሆነ መንገድ ፓርቲውን ለመዝጋት መነሳቱ፤ ትግሉን አንድ እርከን ከፍ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።
<<ትግሉ ከርዕዮተ-ዓለም የዘለለ የነፃነት ትግል ነው፤ይህ ማለት ትግሉ የግድ ስልጣን መጨበጫ ብቻ ሳይሆን፤ ነፃ እና ገለልተኛ የዴሞክራሲ ተቋማት መፍጠሪያ ይሆናል ማለት ነው፡፡>> ያሉት ሊቀመንበሩ፤<< ስለዚህ አንድነት ኖረም አልኖረም፣ ይሄ ትግል ጥርጥር በሌለው ሁኔታ ይቀጥላል፡፡>>ብለዋል። አቶ በላይ አክለውም፦ << አሁን ሌላ አቋም ላይ ደርሰናል፤ እንዲህ አይነት “ምርጫ ቦርድ” ባለበት ሀገር የፓርቲ ፖለቲካ እንደማያዋጣ አቋም ይዘናል፡፡>> ብለዋል።
ፓርቲ፣ ለስልጣን የሚታገል ኃይል ነው ቢባልም መሠረታዊ የዴሞክራሲ ተቋማት በሌሉበት በፓርቲ ደረጃ ያንን ማሰብ እንደማይቻል ያስረዱት ሊቀመንበሩ፤ <<እዚህ ሀገር መደራጀት አትችልም፤ በራሪ ወረቀት መበተን አይቻልም፤ የደህንነት ክትትሉ ልብህን ያወልቃል፡፡ ይህ ከሆነ በፓርቲ ፖለቲካ ስልጣን መያዝ ይቻላል የሚለውን እምነት መልሰን መላልሰን መጠየቅ አለብን፡፡>> ብለዋል።
<< ጥያቄው የነፃነት ትግሉ እንዴት ይፋፋም? የሚል ነው ያሉት አቶ በላይ፤ << በመላ ሀገሪቱ ወደ 40 የሚጠጉ ቢሮዎች አሉን፤ ለነፃነት ትግሉ ድጋፍ መስጠት የሚፈልግ የትኛውም አካል ቢሮውን መጋራት ይችላል፡፡ ይህን አቋም የያዝነው ነውጥ-አልባ ትግል፤ ብቸኛው የነፃነት መንገድ ነው የሚለውን በሰፊ ጥሞና ስለደረስንበት ነው፡፡>>ብለዋል።
<< ከምርጫ ቦርድ ጋር የገባንበትን ጭቅጭቅ እንደ ትልቅ ዕድልም፣ ድልም አድርገን የምናየው የድሉ መንገድ ይህ ስለሆነ ነው>> ብለዋል የአንድነት ሊቀመንበር።
ከምርጫ ቦርድ ጋር በመግባባት ለመስራት በርካታ ጥረቶች ቢደረጉም ቦርዱ ፖለቲካዊ አቋም በመያዙ ሊሳካ አለመቻሉን ያወሱት ሊቀመንበሩ፤ <<ስርዓቱ፣ ለአፈና በቢሊየን የሚቆጠር ዶላር ፈሰስ እያደረገ ባለበት ሁኔታ ያለው አማራጭ ህዝባዊ ንቅናቄ ማድረግ እንደሆነና ይህንንም ለማሳካት ከሌሎች የዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ጋር መተባበር የግድ እንደሆነ አስምረውበታል።
No comments:
Post a Comment