Sunday, 25 January 2015

ከአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ

የፍትህና የነፃነት ጥያቄያችን ደም በማፍሰስ አይቀለበስም!!!

ፓርቲያችን አንድነት ገዥው ፓርቲ፣ ምርጫ ቦርድና የገዥው ፓርቲ ልሳን በመሆን እያገለገሉ ያሉ ሚዲያዎች በመተባበር ከምርጫ ለማስወጣትና ተለጣፊ አንድነት ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት በመቃወም የተቃውሞ ሰልፍ መጥራቱ የሚታወቅ ነው፡፡
UDJ/Andinet party logo
የተቃውሞ ሰልፉን ጥር 17 ቀን 2007 ዓ.ም እንደምናከናውን ለአዲስ አበባ መስተዳድር ብናሳውቅም መስተዳድሩ በ12 ሰዓት ውስጥ በፅሁፍ ምላሽ መስጠት ባለመቻሉ ሰልፉ እውቅና አለው፡፡ መስተዳድሩ ግን የተጣለበትን ሃላፊነት ከመወጣት ይልቅ ወደ ጎን በመግፋት የተወሰኑና የማይታወቁ ግለሰቦች ፔቲሽን ተፈራርመው አምጥተዋል በማለት ብዥታ ለመፍጠር ሞክሯል፡፡ ፓርቲያችን ህጉን ጠብቆ ህጋዊ የሆነ ሰልፍ ለማካሄድ ቢሞክርም አሁንም ሃላፊነት በጎደለው ሁኔታ የፓርቲያችን ከፍተኛ አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች ጭካኔ በተመላበት ሁኔታ ከፍተኛ ድብደባ ተፈፅሞባቸዋል፡፡ በተደጋጋሚ እንዳየነው ፖሊስ ደንብ ማስከበር ሲገባው አድሎ ለፈፀመው አካል በመወገን ድብደባ መፈፀሙ ከወገንተኝነት ያልፀዳ መሆኑን እንድናረጋግጥ አድርጎናል፡፡
ጥያቄያችን አሁንም የፍትህ፣ የእኩልነትና ህግ እንዲጠበቅ የማድረግ ነው፡፡ ገዥው ፓርቲ የመንግስትነት ስልጣኑን በመጠቀም የስልጣን ዘመኑን ለማስረዘም እየከወነ ያለውን ሴራ ማስቆም ነው፡፡ ጥያቄያችን የነፃነትና ያልተሸራረፈ ዴሞክራሲ ይረጋገጥ የሚል ነው፡፡ ጥቄያችን ምርጫ ቦርድ የገዥው ፓርቲ አጋር መሆኑ ቀርቶ ገለልተኛ ሚናውን ይወጣ የሚል ነው፡፡ እነዚህ ጥያቄዎቻችን ደግሞ ደም በማሰስ፤ በድብደባም ሆነ በእስር ፈፅሞ አይቆሙም፡፡ ትግላችን የአንድ ፓርቲ የበላይነት አገዛዝ እስከሚያበቃ ድረስ የሚቀጥል ይሆናል፡፡
በሚቀጥለው ሳምንትም በተለያዩ ከተሞችና በአዲስ አበባ የሰላማዊ ተቃውሞ ድምፃችንን ከፍ አድርገን እናሰማለን፡፡ ትግሉ ይቀጥላል፡፡
ድል የህዝብ ነው!!

No comments:

Post a Comment