Friday, 21 November 2014

ሰበር ዜና "የአ.አ አስተዳደር ለህዝብ ሰላምና ደህንነት ሲባል በሰማያዊ ፓርቲ ላይ እርምጃ እወስዳለሁ አለ"

ሰበር ዜና

የአ.አ አስተዳደር ለህዝብ ሰላምና ደህንነት ሲባል በሰማያዊ ፓርቲ ላይ እርምጃ እወስዳለሁ አለ
• ‹‹ማስጠንቀቂያውን እንደ ቁም ነገር አንቆጥረውም›› ኢ/ር ይልቃል ጌትነት
• ‹‹ስርዓቱ ምን ያህል ዝቅጠት ውስጥ እንደገባ ያሳያል›› አቶ ግርማ በቀለ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ህዳር 7/2007 ዓ.ም ሰማያዊ ፓርቲ ያስተባበረው የ9ኙ ፓርቲዎች የአደባባይ ህዝባዊ ስብሰባ ፀረ
 ህገ መንግስት በመሆኑና ነዋሪዎችን ሰላምና ፀጥታ በማወኩ በቀጣይ ተመሳሳይ እንቅስቃሴ ካደረገ ለህዝብ ሰላምና ደህንነት 
ሲባል እርምጃ እወስዳለሁ ሲል አስጠነቀቀ፡፡

አስተዳደሩ ትናንት ህዳር 11/2007 ዓ.ም በጻፈው ደብዳቤ፤ ህዳር 6 ቀን ‹‹ነጻነት ለፍትሃዊ ምርጫ›› በሚል በሰማያዊ ፓርቲ 
አመራሮችና አባላት ለህዝብ የተሰራጨው በራሪ ወረቀት ህገ ወጥ መሆኑን፣ ህዳር 7/2007 ዓ.ም በኢንጅነር ይልቃል ጌትነት 
መሪነት ሊደረግ የነበረው አደባባይ ስብሰባ ህገ ወጥ እንደነበርና በወቅቱ የስብሰባው ተሳታፊዎች ከፖሊስ ጋር ግብ ግብ 
ከመግጠማቸውም በተጨማሪ የአካባቢውን ህዝብ ሰላምና ፀጥታ አውከዋል ሲል ከሷል፡፡ አስተዳደሩ አክሎም ፓርቲው 
የአደባባይ ብጥብጥና ሁከት በመፍጠሩ እርምጃ እወስዳሉ ሲል ማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ልኳል፡፡



በሌላ በኩል ሰማያዊ ፓርቲ በቀን 5/3/2007 ዓ.ም ለአስተዳደሩ የእውቅና ደብዳቤ ያስገባ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን የሰማያዊ 
ፓርቲና የትብብሩ አመራሮች አስተዳደሩ የላከው ደብዳቤ ከገዥው ፓርቲ ፍርሃት የመነጨ በመሆኑ ከእንቅስቃሴያቸው 
እንደማይገታቸው ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብርና የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች 
ደብዳቤው ስርዓቱ የደረሰበትን መጠነ ሰፊ የፍርሃት ደረጃና ትግሉን ይበልጥ አጠናክረን መቀጠል እንዳለብን የሚያሳይ ነው ሲሉ 
ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡




   
                                                                                                                                                                                                                                                                                               
ማስጠንቀቂው የደረሰው ሰማያዊ ፓርቲና የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ‹‹የረዥም ጊዜ 
የመንግስት ታሪክ ባላት አገር የከተማ አስተዳደር ነኝ ያለ አካል እንዲህ አይነት ደብዳቤ መጻፉ ኢትዮጵያ ምን ያህል ውድቀት 
እንደገጠማትና እኛም እንደ ህዝብ የውረደት ካባ መከናነባችን በግልጽ የሚያሳይ ነው፡፡ እንደ ሰማያዊ አሊያም የትብብሩ 
ሊቀመንበርነት ሳይሆን እንደ አንድ ይህን ያህል ውርደት እንደገጠማት አገር ዜጋ ሀፍረት ይሰማኛል፡፡›› ሲሉ አስተዳደሩ 
የላከው ደብዳቤ ላይ አስተያየታቸውን ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡

ማስጠንቀቂያው በቀጣይ የፓርቲውም ሆነ የትብብሩ እንቅስቃሴ ላይ የሚያመጣው ችግር ካለ በሚል ለኢንጅነር ይልቃል 

ላነሳነላቸው ጥያቄም ‹‹ደብዳቤው የኢህአዴግ ፍርሃት ገደብ መልቀቁንና ትግሉም ይበልጥ መጠናከር እንዳለበት የሚያሳይ 
ነው፡፡ ኢህአዴግ ሰላማዊ ህዝባዊ እንቅስቃሴን ብቻ ሳይሆን የራሱን ጥላም አለማመን ደረጃ ላይ መድረሱን ያሳያል፡፡ እኛ 
ይህን የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ እንደቁም ነገር አንቆጥረውም፡፡ ይበልጡንም ለትግሉ በተጠናከረ መንገድ ንድንነሳሳ 
ይገፋፋናል›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ የትብብሩ ፀኃፊና የኦሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ግርማ በቀለ ‹‹ማስጠንቀቂያው 
ትብብሩ በየሳምንቱ ያቀዳቸውን መርሃ ግብሮች ለማደናቀፍ ያለመ ነው፡፡ ከአንድ የመንግስት መስሪያ ቤት እንዲህ አይነት 
አሳፋሪ ደብዳቤ መጻፉ ስርዓቱ ምን ያህል ዝግጠት ውስጥ እንደገባ ያሳያል፡፡ ሆኖም ማስጠንቀቂያው ከእንቅስቃሴያችን 
አይገታንም፡፡ እንዲያውም ለዚህ የስርዓቱ ዝቅጠት የሚመጥን ስልት ነድፈን በጋራ እንድንሰራ ያደርገናል፡፡›› ሲሉ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡

No comments:

Post a Comment