Monday, 10 November 2014

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት(መኢአድ)ከባድ አደጋ ውስጥ ነው:: ሲሉ አባላቱ ገለጹ -ከምኒሊክ ሳልሳዊ

አቶ ማሙሸት አማረ :- አዲሱ የመኢአድ ፕሬዝዳንት ተስፋና ተግዳሮት
ከዚህ ጉዳይ ጋር የተያያዘዉን መኢአድን የተመለከተ የአቶ ሸንቁጥ አየለን ጽሁፍ ያንብቡት ::
=======================================
- “መኢአድን ለማዳን እንረባረብ::” የጠቅላላ ጉባዬ አባላቱ
- ከድርጅቱ የተባረሩ የወያኔ ቅጥረኞች በእርቅ ስም ወደ ድርጅቱ ተመልሰዋል::(አባላት)
- ጠቅላላ ጉባዬው የተካሄደው ፍጹም አምባገነንነት በሞላበት ሁኔታ ነው::


በኢትዮጵያ በአንጋፈነቱ የሚታወቀው እና በፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ የተመሰረተው መአሕድን የተካው በኢንጂነር ሃይሉ ሻውል ሲመራ ቆይቶ አቶ አበባው መሃሪ የተረከቡት የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ፓርቲ (መኢአድ)ከባድ የመፈረካከስ አደጋ ከፊቱ ተደቅኗል ሲሉ የድርጅቱ ምንጮች ለምንሊክ ሳልሳዊ በላኩት መረጃ ገልጸዋል::
መኢአድ ከአንድነት ፓርቲ ጋር የሚያደርገውን ውህደት ተከትሎ ገዢው ፓርቲ ከድርጅቱ የተባረሩትን እነ አቶ ማሙሸት እና ኮሎኔል ታምሩን አደራጅቶ ውህደቱን በመበጥበጥ በመኢአድ ቢሮ ውስጥ ከዚህ ቀደም በተደረገ ስብሰባ ላይ ደህንነቶችን እና ፖሊሶችን አስከትሎ በመምጣት ከፍተኛ የሆነ ብጥብጥ አንስተው የነበረ ቢሆንም ሳይሳካላቸው ቀርቷል::
ውህደቱ የጉሮሮ ላይ አጥንት የሆነበት የወያኔው መንግስት ምርጫ ቦርድን ተገን በማድረግ መኢአድን በማጉላላት ውህደቱ እንዳይፈጸም ከፍተኛ ደባ ከቅጥረኞቹ ከነማሙሸት ጋር በመሆን ሲፈጽም ቆይቶ በስተመጨረሻ ኢንጂነር ሃይሉን በማስገደድ የተባረሩ አባላትን አቶ አበባው መልሶ እንዲያስገባ ካላስገባ ስልጣኑን እንዲለቅ በሚል ጫና የበላይ ጠባቂነታቸውን ተገን በማድረግ የወያኔ ስራ አስፈጻሚዎች ወደ ድርጅቱ ሰርገው በመግባት ድርጅቱ አደጋ ውስጥ መሆኑን የድርጅቱ አባላት በምሬት ተናግረዋል::
ኢንጂነር ሃይሉ ሻውል ከዚህ ቀደም ከወያኔ ጋር ከድርጅቱ እውቅና ውጪ በራሳቸው ፍቃድ ከሟቹ መለስ ዜናዊ ጋር የምርጫ ደንብ የሚል ስምምነት ተፈራርመው ድርጅቱ እንዲዳከም እና ለወያኔዎች በሩን እንዲከፍት ያደረጉ ሰው ቢሆንም ቀደም ብለው ለትግሉ የከፈሉት አስታውጾ ታይቶ የድርጅቱ የበላይ ጠባቂ እና አማካሪ ቢደረጉም በድርጅቱ ማህተም የተባረሩ ቅጥረኞች ወደ ድርጅቱ እንዲመለሱ አድርገዋል ሲሉ አባሎቹ ተናግረዋል::ኢ/ር ሀይሉ ሻውል በፍጹም አምባገነንነት ጉባኤተኛውን አፍነው እርሳቸው በሚፈልጉት መልኩ በእርቅ ጭምብል አንዱን አስወጥተው አንዱን አስገቡ፡፡ ሲሉ የጠቅላላ ጉባዬ አባላቱ ተናግረዋል::
በዚህ መረጃ ላይ ተጨማሪ መረጃ አሊያም የመቃወሚያ ሃሳብ ያላቹ በስነስርአት ሂደቱን ንገሩን:; እንጣጥ እንጣጥ ስድብ አልፈልግም::
=======================================
አቶ ማሙሸት አማረ :- አዲሱ የመኢአድ ፕሬዝዳንት ተስፋና ተግዳሮት
=======================================
መግቢያ – በሸንቁጥ አበበ
——-
“የቱ ይቀድማል?:- በዲክራሲያዊ መርህ ላይ የቆመ ሀገር ወይስ ዲሞክራሲን ሊሸከም የሚችል ባህል ላይ የቆመ ማህበረሰብ ?” በሚለዉ ጽሁፌ የፖለቲካ ፓርቲዎቻችን የዉይይትና የክርክር ባህል አለመዳበርን በማስመልከት የተወሰኑ ፓርቲዎችን እያነሳሁ ወቅሼአቸዉ ነበር:: ፓርቲዎች ዉስጥ በግለሰብ ወይም በቡድን ደረጃ የሀሳብ ክፍፍል ሲነሳ ፓርቲዎች በሀሳብ የመሸናነፍ ባህል እንዳላዳበሩ ምሳሌ አድርጌ ካቀረብኩት ፓርቲ አንዱ የመላዉ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ነበር:: እንዲህም ስል ፓርቲዉን በሀሳብ ሸንቆጥ አድርጌዉ ነበር:-
“መኢአድ ዉስጥ ችግር ከተፈጠረ አራት አመታት አለፉ:: በርካታ የእርቅ ጥረቶች እንደተደረጉ የኢትዮጵያ ሰዉ አስተዉሏል :: በልዬ ልዩ ሚዲያዎችም ላይ ተደምጧል:: ሆኖም በሃሳብ የተለያዩት ሰዎች አንድም ቀን ቁጭ ብለዉ ተደማምጠዉ በሀሳብ ተፋጭተዉ እና ልዩነታቸዉን አቻችለዉ መፍትሄ ላይ ሲደርሱ አልታዬም:: አንዱ ሌላዉን ይወነጅላል:: አንዱ አንዱን ሰርጎ ገብ ነዉ : ባንዳ ነዉ ሲል ስሙን ያጠፋል:: ደግሞ አንዱ እሱ ብቸኛ የድርጅቱ ተጠሪ ይሆንና ሌላዉን ለማግለል ዳዉላ ሙሉ ከዚያም ዘሎ ከቶንም ስፍር የበለጠ ሀሰትና ዉሸት ይደረድራል:: እናም መደማመጥና መነጋገር ብሎም በሀሳብ መፋጨትና ወደ መቻቻል መድረስ ቦታም አላገኙም:: አስቂኙ ነገር ታዲያ መኢአድ ዉስጥ ተከፋፍለዉ ያሉ ብድኖች ሳያፍሩ ስለ ብሄራዊ እርቅ ጉዳይ ሲናገሩ መስማት የተለመደ ነገር መሆኑ ነዉ:: እራሱን ከራሱ ጋር በሀሳብ ተከራክሮና ተወያይቶ ለማስታረቅ ያልቻለ ቡድን ስለብሄራዊ እርቅ ሲያወራ መስማት እጅግ አስቂኝ ነገር ነዉ::”
ይሄን ወቀሳ ያወረድኩበት በመኢአድ ላይ ብቻ አይደለም ነበር:: ሌሎችም የሀገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎችንም አጣቅሸ ነበር:: ሆኖም ዛሬ ትኩረቴን መኢአድ ላይ አድርጌአለሁ:: ምክንያቱም ዛሬ መኢአድ ማንም ኢትዮጵያዊ ያላሰበዉን እና ያልጠበቀዉ የዲሞክራሲ ማማ ላይ ተፈንጥሮ ወጥቶ ተገኝቷልና::
ለራሱ ሀሳብና ህሊና ብቻ ተገዥ የሆነዉ ደፋሩ : እዉቁና ወጣቱ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ባንድ ወቅት የመኢአድ ሰዎች እርስ በርስ ንክሻ እና አለመግባባት ብቻ ሳይሆን በፕሮፌሰር አስራት የሙት አመት ላይ እንኳን ሲጣሉ ቢያስተዉል ” ዛሬ የፕሮፌሰር አስራት ሙት አመት ብቻ ሳይሆን የመኢአድም ሙት አመት ነዉ” ሲል መጻፉን አስታዉሳለሁ::
እኔም ሆንኩ ተመስገን ደሳለኝ በመኢአድ ላይ ትችቶችን ያወረድንበት ወደን ሳይሆን በሚጠበቅበት ስፍርና ቁመት ልክ ሆኖ አልገኝ ስላለን ነበር:: መኢአድ ከ2003 ዓም እስከ አሁኑ ጥቅምት 30/ 2007 ዓም ድረስ ለአራት አመታታ ያሳለፈዉ ዉጣ ዉረድ እና አባላቱም በአምስት ቡድን ተከፋፍለዉ ያደረጉት ሽኩቻ ጉድ የሚያስብል ብቻ ሳይሆን ወይ የኢትዮጵያ ፖለቲካ የሚያሰኝ ነበር:: አንድ ፓርቲ አምስት ቡድን ተከፋፍሎ መልሶ ሊድን የሚችለዉ እንዴት ነዉ?
የመላዉ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ወደ ዲሞክራሲ የከፍታ ጉዞ ?
========================================
ለአራት አመታት በአምስት ቡድኖች ተከፋፍለዉ የማያቋርጥ አሉባልታ: ስድብ ወቀሳና ክስ ላይ ተጠምደዉ የነበሩ ሀይሎችን ወደ አንድ ማምጣትና በዉይይት ችግራቸዉን ፈትተዉ እርቅ ወርዶ አንድ የፖለቲካ ሀይል ሆነዉ እንዲቀጥሉ ማድረግ ይቻላል? ለአራት አመታት ያስተዋልነዉ ነገር አይቻልም የሚል ፍጹም አስተማማኝ ድምዳሜ ላይ መድረስ ነበር:: ለዚህም ነዉ ከንግዲህ የመኢአድ ነገር አከተመለት የተባለዉ ነበር::
የሆኖ ሆኖ በጠንካራ ሽማግሌዎች እረዳትነት እያንዳንዱን አምስት የተለያዬ ቡድን በማነጋገር : በተለያዬ ወቅት አመራር በመሆን የተመረጡትን ሀይሎች ሁሉ በማካተት እንዲሁም አንድንም ወገንን ያላገለለ : ከገጠር እስከ ከተማ ያለዉን አመራር በማካተት ጠቅላላ ጉባኤ በማድረግ አስገራሚ ዉጤት ላይ የደረሰ ፓርቲ ሆኖ ወጥቷል:: ዉጤቱን አስገራሚ ያደረገዉም የጠቅላላ ጉባዔዉ ሂደት እጅግ ጠንካራ: በበርካታ ሙግቶች : ክርክሮች : ፊት ለፊት በሚነሱ የተፋጠጥ አካሄዶች እዲሁም አንድም እዉነት ሳይቀር እዚችዉ እህዝብ ፊት ትፋት የሚል አካሄድ የታጀበ መሆኑ ነበር::
እያንዳንዱ ቅሬታ አለኝ የሚል ቡድን ከስድስት መቶ ተሰብሳቢ በላይ ባለበት እዉነት ስትሞግተዉ ወይ ያቀረቅራል ወይም እዉነትን ተርትሮ ለተሰብሳቢዉ ያስረዳል;: ተሰብሳቢዉ ያደምጣል: አፋጣጭ ጥያቄን ይጠይቃል ብሎም ደግሞ ብይንን ይበይናል:: መሸወድ አይቻልም:: ብዙሃን እዉነትን እሰዉ ፊት ላይ ያነባታል: ብዙሃን እዉነትን ከሰዉ ኪስ ዉስጥ በርብሮ ያወጣታል:: አሉባልታ ተናግሮ ማምለጥ አይቻልም:: ፊት ለፊት ላሉባልታዉ መልስ የሚሰጥ ወገን አለና:: ከሁሉም በላይ ደግሞ አይኑን እና ጆሮዉን አንቅቶ የሚያስተዉል ከስድስት መቶ በላይ ህዝብ አለና:: የትም መደበቅ አይቻልም:: የዲሞክራሲ ዉበቱ ህዝብ ፊት እራቁትን ስለሚያስቆም ነዉ::
እናም እያንዳንዱ ቡድን ከጥቅምት 28 እስከ ጥቅምት 30/2007 ዓም በተደረገዉ እልህ አስጨራሽ ግን ደግሞ የዲሞክራሲ የከፍታ ማማ ላይ የረገጠ ሊባል በሚችል የጠቅላላ ጉባዔ ሂደት ዉስጥ ያለዉ አማራጭ ወደ አንድ መምጣትና በጋራ ለዲሞክራሲ መታገል መሆኑን በደንብ የተማረበት: እያንዳንዱንም ለሌላው ወገን ያስተማረበት ወቅት ሆኖ አልፏል:: ለሶስት ቀናት በዘለቀዉ የስብሰባ ሂደት ዉስጥ እስከ ለሊቱ ስድስት ሰዓት ድረስ በማምሸት የተደረገዉ የዲሞክራሲ ከፍታ ላይ የደረሰ የሀሳብ ፍጭት: ክርክር: እና ዉይይት እጅግ ገንቢና ለወደፊት የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ጥሩ ልምድ ጥሎ ያለፈ አስተምህሮት ይመስላል:: እዚህች ጋ በተለያዩ ፓርቲዎች ስር የታቀፉ ፖለቲከኞቻችን ፈገግ ሲሉ ይታዩኛል:: እኛማ የዲሞክራሲዋን ቁልፍ ጨብጠናታል ሲሉ ፈገግ ማለታቸዉ አንዱ የዲሞክራሲ ድቀት መገለጫ መሆኑን እናጣቅስና እንለፈዉ::
ሀይሉ ሻዉል ከ28-30/3007 ዓም ባሉት መጨረሻ የፖለቲካ ቀኖቻቸዉ ዉስጥ የሰጡት አመራርም ብዙዎቹን አስገርሟል:: “ከንግዲህ እኔ ከማንም ጋር ጸብ የለኝም:: እያንዳንዳችሁም እርስ በርሳችሁ መታረቅና በመሃከላችሁ ያለዉን ጸብ ንዳችሁ አብራችሁ መስራት አለባችሁ::” ይሄን አቋማቸዉን የተፈታተኑ አንዳንድ ወገኖች ቢኖሩም የብዙሃኑም ተሰብሳቢ ዋና ምርጫ ዲሞክራሲያዊ ሂደትን ማዬት እንጅ ብጥብጥ ስላልነበረ ነገሮች ሁሉ በሰላማዊ መንገድ መጠናቀቅ ችለዋል:: በዉነቱ ሂደቱ እጅግ አስጨናቂ እንደነበረ ከ20 በላይ ተሰብሳቢዎችን አንድ ባንድ ቃለ መጠይቅ በማድረግ ተረድቻለሁ:: ብዙዎች እንዳሉትም በመጀመሪያ አካባቢ ሂደቱ ከመክበዱ የተነሳ አንድ አጀንዳ ላይ አንድ ቀን የመዋል አካሄድ እንደነበርም አብራርተዉልኛል::
አቶ ማሙሸት አማረ :- አዲሱ የመኢአድ ፕሬዝዳንት ተስፋና ተግዳሮት
=================================================
ማሙሸት አማረ የመኢአድ አዲስ ፕሬዝዳንት ሆኖ በከፍተኛ ድምጽ ተመርጧል:: ማሙሸት አማረ ገና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲት የአንደኛ አመት ተማሪ ሆኖ ዩኒቨርስቲ እንደ ገባ ወገን ሀገርህ አይደለም ተብሎ ካባቶቹ ሀገር ሲባረርና ገደል ሲገፈተር የምን ትምህርት ነዉ ሲል ከፕሮፈሴር አስራት ጋር የፖለቲካ የትግል አዉድማ በወጣት እድሜዉ የተቀላቀለ ሰዉ ነዉ:: አቶ ማሙሸት በፖለቲካ ሂወት ዉስጥ እየተመላለሰም በርካታ የትምህርት ዘርፎችን በማጥናት እራሱን ለአመራር ብቁ ያደረገ ሰዉ ነዉ :: በማርኬቲን ዲፕሎማ: በሊደርሽፕ/አመራር/ ዲፕሎማ እንዲሁም በማኔጅመንት ዲግሪዉን አጠናቋል:: በአሁኑ ሰዓት ደግሞ በፖለቲካ ሳይንስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ትምህርቱን የቀጠለ ብርቱ የሰላማዊ ትግል መሪ ነዉ::
ለአስራ ሁለት አመታት የታሰረ ሰዉ ቢሆንም በኢትዮጵያ ፖለቲካ የማይማረር : በዲሞክራሲ ሂደት የሚያምን እና የሚያምንበትን ሀሳብ ፊት ለፊት የሚያራምድ ፖለቲከኛ ነዉ:: በቅርበት የሚያቁትም እንደሚገልጹት ለሚያምንበት ነገር ብቻ የሚኖር ሰዉ ሲሉ ይገልጹታል::
ማሙሸት በሀሳብ ልዩነት ያምናል:: በክርክር ያምናል:: ሰዉ አክባሪ እንደሆነ የሚነገርለት ማሙሸት ተናግሮ የማሳመን አቅሙን አብረዉት የሰሩ ሁሉ ይመሰክሩለታል:: ከ28-30/2007 ዓም በተደረገዉ ጠቅላላ ጉባዔ ላይም ይሄንኑ ተናግሮ የማሳመን ችሎታዉን እንዳስመሰከረ ብዙዎች ተስማምተዉለታል:: ሆኖም ማሙሸት አንድ ነገር አይሆንለትም:: ይሄዉም እዉሸትና መስሎ ማደር:: ይሄ ነገር ለፖለቲካ ሂወቱ ዋናዉ ተግዳሮትም አዎንታዊ ገጽታም ሆኖ ከፊቱ የተደነቀረ ይመስላል::
ለአራት አመታት ከማሙሸት አማረ ጋር በሀሳብ ተለያይተዉ የከረሙትና በማሙሸት ላይ ክፉኛ ቂም ይዘዉ የነበሩት ኢ/ር ሀይሉ ሻዉል ከማሙሸት ጋር ሲታረቁ ማሙሸት ለአቶ ሀይሉ በሽማግሌዎች ፊት ያቀረበላቸዉ አንዱ ጥያቄ “ለመሆኑ እኔ እርስዎን ሰድቤዎታለሁ?” የሚል ጥያቄ ነበር:: ሀይሉም ” እረ በፍጹም” ሲሉ መለሱ:: ማሙሸትም በማስከተል ” ታዲያ ሚዲያዉ ሁሉ ማሙሸት አማረ አቶ ሀይሉን ሰደባቸዉ እያለ ሲያናፍስ እርስዎ ዝምታን የመረጡት ለምን ነበር?” ሲል ጠየቀ:: ሀይሉም መለሱ “እኔ ለያንዳንዱ ሚዲያ ያሉባልታ ወሬ ምላሽ ልሰጥ የምችልበት እድሜ ላይ አይደለሁም” ሲሉ መለሱ::
“እኔና አንተ የተጣላንዉ አንተ ለእኔ አልታዘዝም ስላልክ ብቻ ነዉ” ሲሉ አስከትለዉ ሀይሉ ተናገሩ:: ማሙሸትም ለአቶ ሀይሉ ሲመልስ ” እኔ ለእርስዎም ሆነ ለማንም ህገወጥ በሆነ መንገድ የምታዘዝ ሰዉ አይደለሁም:: ከእርስዎም የተጣላንዉ እርስዎ የድርጅቱን ህገ ደንብ ጥሰዉ ያለስልጣንዎት የማይገቡ ዉሳኔዎችን ስለወሰኑ ነዉ::አሁንም ሆነ ወደፊት የድርጅትን ህገ ደንብ የሚጥስ መሪ አምባገነን መሪ ነዉ:: የተጣላንዉም እርስዎ ህግ ስለጣሱ ነዉ:: አሁን ያለዉን አምባ ገነን ስርዓት እየታገልን በተቃዋሚ ፓርቲዎች ዉስጥ ደግሞ የፓርቲ አምባ ገነንነትን አናበረታታም:: ማንኛዉንም አይነት አንባገነንነትን እንታገለዋለን እንጅ:: ” ሲል ቁርጥ ያለ መልስ መለሰ::
ማሙሸት በማስከተል እንዲህ አለ “አባቴ ገና ዩኒቨርስቲ አንደኛ አመት ተማሪ እያለሁ ጠርቶ “ወገን እያለቀ ዝም የምትሉት ምንድን ነዉ? ከፕሮፌሰር አስራት ጋር ተነስታችሁ ታገሉ:: ለእዉነት ሙት” ሲል ለእዉነት ብቻ እንድኖር መመሪያ ሰጥቶኛል:: እዉነትን ማንም ከጣሳት ከዚያ ሀይል ጋር በሀሳብ ሙግት መግጠሜ አይቀርም:: ከርስዎም ጋር የሆነዉ ይሄዉ ነዉ::” ሲል አስገራሚዉን ያባቱን ታሪክ ተናገረ:: ግን በዚህ ዘመን እንዲህ አይነት አባቶች አሉ እንዴ የሚያስብል ነገር ነዉ::
እናም ሀይሉ ሻዉል ጠቅላላ ጉባዔዉ በተደረገበት ቀን አንድ አስገራሚ ነገር ተናገሩ ” እናንተ ይሄን ማሙሸትን አታቁትም:: እሱ የሚለዉ እዉነት ብቻ ትዉጣ ነዉ:: እንደ ፖለቲከኛ የሚያድበሰብሰዉ ነገር የለም:: የሚፈልገዉ እዉነቷን ብቻ ነዉ:: በአንደበቱ ሁለት ወይም አንድ ነገር አይናገርም:: አንድ ነገር ብቻ ይናገራል:: እሱም እዉነት ብቻ::”
የጠቅላላ ጉባዔዉ ተሰብሳቢ በአቶ ሀይሉ ንግግር እየተገረመ እያለ ድርጅቱን ለተወሰነ ጊዜ በፕሬዝዳንትነት የመሩት አቶ አበባዉ ደግሞ (ከማሙሸት ጋር ጸብ የነበሩ ናቸዉ) ብድግ ብለዉ ” አቶ ማሙሸት ድርጅትን በመክዳት ወይም በገንዘብ ወይም በሌላ በምንም መጥፎ ባህሪ አይታማም :: የሱ ችግር ሀይለኝነት ብቻ ነዉ:: ተጋፋጭ ነዉ:: እልህኛ ነዉ” ሲሉ ስለ ማሙሸት አማረ ያላቸዉን አመለካከት አካፈሉ::
እንግዲህ እነዚህና ከሌሎችም በርካታ ምንጮች የሰበሰብኋቸዉ መረጃዎችን ስተነትናቸዉ ማሙሸት አማረ አሁን በተረከበዉ የፕሬዝዳንትነት ሀላፊነት ቦታ ላይ የሚያሳካቸዉ በርካታ አዎንታዊ ጉዳዮች እንደሚኖሩ መገመት ይቻላል:: እንዲሁም የሚገጥሙት ተግዳሮቶች ቀላል የሚሆኑ አይመስለኝም::
እነዚህ አሉታዊና አዎንታዊ ፈተናዎች ከኢትዮጵያ ባህላዊ ጽንፍ ዉስጥ መንጭተዉ የሚዎጡ ጭብጦች ናቸዉ:: በኢትዮጵያ እዉነት ወዳዱ ሰዉ ፍጹም እዉነት ወዳድ ነዉ:: ሸፍጠኛዉ ደግሞ ጽንፈኛ ሸፍጠኛ ነዉ:: ፕሮፌሰር ሰባስኪ የተባለ የጣሊያን ፕሮፌሰር የኢትዮጵያ ታሪክ በፋሽስት ኢጣሊያ ወረራ ወቅት በሚለዉ መጽሀፉ (እምሻዉ አለማዬሁ ወደ አማርኛ ተርጉሞታል ) አንድ አስገራሚ መረጃን አካፍሎናል:: ጣሊያኖች ስለ ሀበሻ ስነ ልቦና ጥናት አደረጉ:: በርግጥ ጥናቱ ወታደራዊ ጥናት ስለነበረ ያተኮረዉ የሀበሻን ሰዉ ስነልቦና ከወታደራዊ ጭብጥ አንጽር የመተንተን ስራ ላይ ነበር::
እናም የጥናቱ ዉጤት አስገራሚ ነበር:: አጭር የጥናቱ ድምዳሜም ሀበሻ ጀግና ከሆነ ፍጹም ጀግና ነዉ:: ከአፍሪካ ምድር የጀርመንን ጦር ጠራርገህ ለማስወጣት ከፈለግህ ጀግኖቹን የሀብሻ ወታደሮችን መልምል:: ሆኖም ደግሞ አበሻ ፈሪ ከሆነም ፍጹም ፈሪና አድር ባይ ነዉ:: ስለዚህ ምልመላችን ለመለዬት ከባድ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል የሚል ነበር::
ልክ እንደ ጣሊያኖቹ ጥናት ሁሉ ኢትዮጵያ ባህል ዉስጥ እዉነተኛ ሰዎች ሁለት አይነት ጽንፈ ላይ የተንጠለጠለ ቦታ አላቸዉ:: አንድኛዉ ማማቸዉ የጀግናና የተወዳጅነት ማማ ሲሆን ሁለተኛዉ ማማ ደግሞ የተጠላ ማማ ነዉ:: ገትጋታ ተብለዉ የመጠላታቸዉ እድልም የዚያኑ ያህል ሰፊ ነዉ::
ለዚህ እንግዲህ ብቸኛዉ መፍትሄ ሁል አቀፍ የሆነ የጋራ አመራር እንዲኖር ማድረግ እንዲሁም የተለያዩ ሀሳቦች የሚያንጸባርቁ ቡድኖችን ማበረታታት ወሳኝ ነዉ:: ማሙሸት አማረ ትልቁ የቤት ስራዉ የሚሆነዉም ይሄዉ ነዉ:: እርግጥ ነዉ ባዋቀረዉ ካቤኔ ዉስጥ አካታች ስራን እንደሰራ ብዙዎች መስክረዉለታል:: በተለያዩ ጎራ ተከፋፍለዉ የነበሩትን ልዩ ልዩ አመራሮች ሁሉ ጥሩ አድርጎ በካቢኔዉ ዉስጥ ማካተቱም ለወደፊት ሰፊ የሀሳብ ምንጭ ያለዉ አመራርን በድርጅቱ ዉስጥ እንዲፈጠር ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር እንዳሰበ እንዲሁም ሁሉም አካላት በትክክል እንዲታቀፉ መፈለጉን አመላካች ነዉ:: የሆነ ሆኖ ግን ወደፊትም ሰፊ መሰረት ላይ የቆመ ሰፊ ማህበረሰብን የሚያካትት የአመራር ሀይል የመመስረት ጠንካራ ጥረት የሚጠበቅበት ይመስለኛል::
ከዚህ በተጨማሪም ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር በትብብር የመስራት እና የላቀ ሀገራዊ የዲሞክራሲ እሴት ላይ መስራት ሌላዉ ትልቁ የቤት ስራዉ የሚሆን ጉዳይ ይሆናል:: በተለይም የኢትዮጵያ ሰዉ እፊት ጀምሮ ፓርቲዎች ወይ ተባበሩ አለዚያ ተሰባበሩ የሚለዉ አቋሙ ወደፊት እየጠነከረ እንደሚመጣ ይጠበቃል:: እናም መኢአድ ለዚህ የህዝብ የልብ ትርታ የሚሰጠዉ ምላሽ የማሙሸት አማረ ያመራር ብቃትን ከሚፈትኑ ጥቂት ጉዳዮች ዉስጥ አንዱ የሚሆን ይመስላል::
ሌሎች ፓርቲዎች ከመኢአድ ተሞክሮ ምን ሊቀስሙ ይገባል?
==============================
መኢአድ ለአራት አመታት በተለያዩ ቡድኖች ተከፋፍሎ የዳከረዉን መዳከር ከቶ እንዳይደገም ደግሞም እንዳይታሰብ ብለዉ ሌሎች ፓርቲዎች ተሞክሮ ሊሆናቸዉ የሚችል አስተምህሮት መርምረዉ ማዉጣት ያለባቸዉ ይመስለኛል:: እኛ ሀገር የፖለቲካ ትንታኔ ማድረግ: ከአንድ ሂደት ምን ተማርን ብሎ መወያዬት : ሀሳብ ለሀሳስብ ለመለዋወጥ መነሳሰት ፈጽሞ ባህላችን አይደለም:: በተለያዩ ፓርቲዎች ጥላ ስር ታቅፈዉ ያሉ ሀይሎች በተለይም አሁን በተለያዩ ብድኖች ተከፋፍለዉ ያሉ ሀይሎች ቁጭ ብለዉ ትንታኔ መስሪያ ግዜአቸዉ ይመስለኛል::
ህጋዊ መፈንቅለ ስልጣን ተደረገ ብሎ አንዱ ወገን ሲጮ አንድኛዉ ወገን አትንጫጫ ብሎ አፍ ለማሲያዝ ከመሄድ የመኢአድ ተሞክሮ ምን ይመስላል ብሎ መጠዬቅና መወያዬት ብልህነት ይመስለኛል:: ጠንካራ ዉይይትና ክርክር ሁሉንም የሀሳብ ልዩነቶች ባይፈታቸዉም ዲሞክራሲያዊ ከፍታ ላይ መዉጣት ግን ያስችላል:: ዲሞክራሲ ከፍታ ላይ የወጣ ሀይል ደግሞ ሀሳቦችን ዲሞክራሲያዊ በሆነ አካሄድ ወደ ጋራ ስምምነት ያመጣቸዋል:: ከመኢአድ መማር የሚቻለዉ ይሄን ነዉ::
በዚህ አጋጣሚ እግዚአብሄር በሰጠን ጥቂት የጽሁፍ ጸጋ ሀሳባችንን የምናካፍል ሁሉ በኢትዮጵያ ያለዉ የፖለቲካ ባህላዊ እሴት ያብብ ዘንድ እያንዳንዱ ወገን ወደ ዲሞክራሲ ከፍታ ይራመድ ዘንድ የምንጽፈዉ ጽሁፍ : የምንሰነዝረዉ ሀሳብ ዋጋ ያገኝ ዘንድ ለሚመለከተዉ ሁሉ እናሳስባን:: ሆኖም ማንንም አንማጸንም::

No comments:

Post a Comment