Tuesday, 18 November 2014

ጊዜው የሕዝባዊ እምቢተኝነት ነው!!!


በአሁኑ ወቅት በአገራችን በከተሞችና በገጠሮች እየታዩ ያሉ ምልክቶችን በጥንቃቄ የመረመረ ማንኛውም ሰው የሚከተሉትን መታዘቡ አይቀርም።
በአንድ በኩል፣ ወያኔ የተወገደባት፣ ፍትህ የሰፈነባትና የበለፀገች ኢትዮጵያ እውን ሆና የማየት ተስፋችን እየለመለመ ነው። በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ ዉስጥ ለረጂም ዓመታት በሕዝብ ላይ ሰፍኖ የነበረው የፍርሀት ደመና እየገለጠ በመሆኑ ተዘግተው የቆዩ አንደበቶች መናገርና “ይኸ ሁሉ ግፍ ለምን?” ብለው መጠየቅ ጀምረዋል። ይህንን መነቃቃት በአስተሳሰብም፣ በተግባርም፣ በኪነጥበብም እያየነው ነው። የኢትዮጵያ ወጣቶች ለውጥ በአገራችን ሊመጣ እንደሚችል ከማመን አልፎ ራሳቸውን በለውጥ አምጭ ኃይልነት መመልከት ጀምረዋል። በርካታ ወጣቶች ወያኔን በትጥቅ ለመገዳደር የወሰኑ ወገኖቻችንን እየተቀላቀሉ በዚህም ምክንያት ጉልበታቸውን እያፈረጠሙ ነው። የለውጡ እርሾ ከሲቪሉ አልፎ በመከላከያ ሠራዊቱ እና በኢሕአዴግ ድርጅቶች ውስጥም እየተብሰለሰለ ነው። የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት፣ ህወሓት ኢትዮጵያን ለማጥፋት የሚጠቀምበት ኃይል መሆኑ እያበቃ በአንፃሩ የትግሉ አጋር የሚሆንባቸው ሁኔታዎች እየታዩ ነው። በሁሉም የሠራዊቱ ክፍሎች ጉምጉምታው ወደ ጩኸት እየተቀየረ በመሆኑ ሠራዊቱ በአለቆቹ ላይ የሚነሳበት ጊዜ እሩቅ አይደለም። በተለያዩ ምክንያቶች ህወሓትን ወይም ህወሓት የፈጠራቸውን ድርጅቶች የተጠጉ በአጠቃላይ ኢሕአዴግ በሚባለው ስብስብ ውስጥ የሚገኙ ወገኖቻችንም “ለመሆኑ ማንን ነው እያገለገልን ያለነው?” ብለው በመጠየቅ ላይ ናቸው። በዚህም ምክንያት ወያኔ ውስጡ እየተረበሸ ነው። ከኢትዮጵያም ውጭ በሚገኘው ኢትዮጵያዊ ዘንድ ያለው ቁጣና ዝግጁነት ከወትሮው እጅግ የላቀ ነው። በአጭሩ፣ በሁሉም አቅጣጫ፣ ደረጃ በደረጃ የሕዝባዊ እምቢተኝነት እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል።
በአንፃሩ ደግሞ፣ የጨለማ ንጉሥ የሆነው ወያኔ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብን ወደ ፍርሀት ቆፈን ለመመለስ እስሩን ከመቸውም በላይ ያጧጧፈበት ጊዜ ነው። በትግራይ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ በአፋር በሶማሊ … በመላው ኢትዮጵያ ብሩህ ራዕይ የሰነቁ ወጣቶችና አዛውንት ታድነው እየታሰሩ ናቸው። የወያኔ እስር ቤቶች በአርቆ አስተዋይ ዜጎቻችን ተሞልተዋል። ወትሮም ከፍተኛ የነበረው ስደት ብሶበታል፤ ለእውነት በጽናት የቆሙ ጋዜጠኞች ወይ ታስረው፣ አልያም ተሰደው አልቀዋል። የወያኔ የግዴታ ስልጠና አገሩን እያመሰው ነው። የኢትዮጵያዊያን ኑሮ በእጦቶች የታጀበ ሆኗል። የነፃነት እጦት፣ የፍትህ እጦት፣ የመብራት እጦት፣ የስኳር እጦት፣ የዘይት እጦት፣ የታክሲ እጦት፣ የመኖሪያ ቤት እጦት፣ እጦት፣ …. እጦት።
እነዚህ ሁለት ተፃራሪ እውነታዎች ሁለት ተፃራሪ ኃይሎች ለወሳኝ ፍልሚያ ፊት ለፊት መፋጠጣቸዉን በግልጽ ያሳያሉ። ዛሬ አገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ነፃነትና ባርነት፣ ፍትህና ጭቆና፣ ደስታና ሀዘን፣ ተስፋና ተስፋ መቁረጥ፣ ብልጽግናና ድህነት፣ እውቀትና ድንቁርና፣ ብርሃንና ጨለማ፣ ለወሳኝ ግጥሚያ ተፋጠዋል። ይህ ፍጥጫ የኢትዮጵያን የወደፊት እጣ ፈንታን በመወሰን ረገድ አቢይ ሚና የሚኖረው ወሳኙ ግጥሚያ – ሕዝባዊ እምቢተኝነት – መጀመሩን አብሳሪ ነው። የነፃነት፣ የፍትህ፣ የተስፋ፣ የብልጽግና፣ የእውቀትና የብርሃን ወገኖች ነን የምንል ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ይህንን ፍልሚያ በድል መወጣት ግዴታችን ነው።
ወያኔ ታጋዮችን ቢያስር ትግሉን አያስርም። በእጦት ኑሮዓችን በማመሰቃቀል በድህነት ሊያንበረክከን ቢሻም፣ በፍጹም አንበረከክለትም። በተዘረፈ የድሆች ድካም ህንፃዎችን ቢገነቡም የራስ ባልሆነ ጌጥ አንኮራም። የወያኔ የሆነ የኛ አይደለም፤ የእነሱ መክበር የኛ መክበር አይደለም። ወያኔ እና የኢትዮጵያ ሕዝብ ገዢና ተገዢ፤ በዳይና ተበዳይ፣ ገፊና ተገፊ ናቸው።
ተበዳይና ተገፊ የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ በዘረኞች፣ ሙሰኞችና ከፋፋዮች የህወሓት ባለሥልጣኖቻቸውና ሎሌዎቻቸው ላይ ይነሳሉ። የተጀመረው ሕዝባዊ እምቢተኝነት አመቺ በሆኑ መንገዶች ሁሉ ይጧጧፋል።
የወያኔ ትዕዛዛትን መሻር፤ በሥራ ላይ መለገም፤ ግብር አለመክፈል፤ አድማ መምታት፤ የወያኔ ካድሬዎችን ማግለልና ማዋረድ፤ የነፃነት ኃይሎችን መደገፍ፤ የፓሊስና የጦር ሠራዊት አባላትን ማቅረብ እና በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ እነሱም የትግሉ አካል እንዲሆኑ ማበረታታት፤ ህሊና ያላቸው የኢሕአዴግ አባላት የሕዝቡን ትግል እንዲያግዙ ማበረታታት … – እነዚህንና እነዚህን የመሳሰሉ በርካታ የትግል ስልቶች ከአሁን ጀምሮ በተከታታይ በሥራ ላይ መዋል ይኖርባቸዋል። የወያኔን የጭቆና ምሽግ ከውስጥ መሸርሸር፤ ከውጭ መደርመስ ይኖርበታል። የመሸርሸርና የመደርመስ ሥራዎች ተደጋግፈው እንዲሄዱ ማድረግ ይገባል። ጊዜው የእምቢተኝነት ነው።
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የዲሞክራሲና የነፃነት ንቅናቄ የኢትዮጵያ ሕዝብ አጠገቡ ባሉት መሪዎቹ አስተባባሪነት በአንድነት እንዲነሳ ጥሪ ያቀርባል፤ በመላው ዓለም ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንም በኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረገው ሁለገብ ትግል በጽናት እንዲደግፉ ያሳስባል። ይህንን ትግል በድል መወጣት ግዴታችን ነው፤ እንወጣዋለንም!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!



    No comments:

    Post a Comment