ከሥርጉተ ሥላሴ 20.11.2014 /ሲዊዘርላንድ ዙሪክ/
ሰሞኑን በተከታታይ የማነባቸው ሁሉ በምርጫ ላይ ያተኮሩ ናቸው። ቢሆን መልካም በነበረ። ህልሙ እሱ ስለሆን። ነገር ግን ምርጫ በዬትኛው ነፃነት ነው የሚከወነው? በዬጊዜው ጠንካሮችን እዬገበሩ አዲሶቹ እስኪለማመዱ ጊዜ እዬተገደለ፤ ለተመክሮና ለልምድ አዲስ – ገብ እስኪዋህድ ድረስ ወያኔ ያሻውን እንደ ልቡ እንዲከውን ነውን? ይህ አዟሪታማ ጉዞ የዛሬ አራት ዓመትም ይመጣል። ቀጣዩን አራት ዓመትም መሰሉን ለመከወን አቅዶ እንዳሻው ከባለ ጊዜ ጋር ደልቆ ይነጉዳል። ምርጫ ይመጣል – ይሄዳል። ተጠቃሚውና አትራፊው ግን በውጪ ድጋፍ ለጋሾች ሆነ በፈላጭ ቆራጭነት አገር ቤት – ወመኔው ወያኔ ነው።
አንድ ሰው ወይንም ሁለት ሰው ወይንም አምስት ሰው ከተቃዋሚ ቢመረጥ እንኳን ቋት የማይገፋ ልፊያ እንጂ ለነፃነት ትግሉ የሚፈይደው አንዳችም ነገር የለውም። የምርጫ ሂደትን ማካሄድ ቀርቶ ምርጫ ለማሰብ ንጹህ ነፃነት ያስፈልጋል። መንፈስ ከገዢዎች እስር ቤት በነፃ መለቀቅ አለበት። ህሊና ከሥውር እግርቤት መፈታት አለበት። ቃሊቲ ወይንም ቅሊንጦ ወይንም ጦላይ ወይንም ዝዋይ ያሉት ብቻ አይደሉም እሰረኞች። በኢትዮጵያ ከወያኔ ቀጥተኛ ደጋፊዎች በስተቀር ሁሉም ሰው እስረኛ ነው። ስለነገ፤ ወጥቶ ስለመግባቱ፤ የግል ቤቱ የእርሱ ስለመሆኑ አንድም ሰው እርግጠኛ አይደለም። ቋንቋ ጠፍቶ ጥቅሻ የወልዮሽ መግባቢያ ቋንቋ በሆነበት ሁኔታ ላይ እንዴት ነው በንጹህ አዬር – ባደገው የዴሞክራሲ መንፈስ ሰው ሃሳቡን ፍላጎቱንና ስሜቱን የመግልጽ አቅሙን የሚገለጸው? እንዴት? ይቻላልን? … በገፍ የሚታሰሩት ወገኖቻችን እኮ ሃሳባቸውን ሙሉን ሳይሆን ቅንጣቢ ተነፈሳችሁ ተብለው እኮ ነው ይህ ሁሉ መከራና አሳር እስከነቤተሰቦቻቸው የሚከፍሉት …..
እርግጥ ነው የተቃዋሚ ፓርቲዎች በአቅምና በመንፈስ ጠንክረው መደራጀታቸው ተፈላጊ ነገር ነው። አመራሩ ጥራት ባለው ሁኔታ ከህሊና ግንባታ ጀምሮ መሰናዶ ማደረጉም – ወሸኔ ነው። ነገ ኢትዮጵያ ሀገራችን የህብር ብሄር ፓርቲ ቀለማም ሥልጡን እስቤ፣ በነፃ የድምጽ ውድድርና ፉክክር የሚመራት እንደትሆን እንፈልጋለን። ይህ ማለት ግን በዬአራት አመቱ ወያኔ በሚነድፈው የማላጋጫ ትልሙ ማሟቂያነት መሆን ማለት አይደለም። የመመሥረታቸው አመክንዮን እኮ ወያኔ በትእቢት ገድሎታል። ምሥረታቸው እኮ ወያኔን በምርጫ ተወዳድሮ ለማሸነፍ ነበር። ግን ሁኔታው አለን? ትንሽ ብጣቂ የመተንፈሻ ቧንቧ እንኳን አላቸውን? መሪዎቻቸው ሃሳብን በሃሳብ አታግለው አሸናፊውን ሃሳብ ህዝብ እንዲደግፈው ማደረግ ይችላሉን? የኛ የነፃነት ትግሉ አካል ፓርቲያት እኮ ልክ ባዕድ ሀገር የመኖር ያህል ነው ያለባቸው ፍዳ። በሀገራቸው መሬት እኩልነታቸው ተረግጦ የመሰብሰቢያ ቦታና አደባባይ ተክልክለው በባይታዋርነት የሚቀቀሉበት ሁኔታ ነው ያለው፤ እንኳንስ ሥልጣንን ለመጋራት – እውነቱ ይሄ ነው።
አሁን ለምርጫው ስንት ወር ቀርቶታል? መሃል ሃገር የአፍሪካ ዋና ከተማ በሆነው አዲስ አበባ እንኳን ህዝብን መሰብሰብ አልተቻለም። እንኳንስ ሌላ ክ/ሀገራት ሆነ ወረዳ። ወደ ታች በተወረደ ቁጥር ደግሞ በቃ! ካራ / ቢላዋ / ተስሎ፣ ገመድ ተዘጋጅቶ፣ ተሰቅሎ ለመታረድ የመዘጋጀት ያህል ነው። እኛ ከምንሰማው ሆነ ከምናስበው በላይ እጅግ የከፋ ነው …. የባለጊዜ ጊዜኞች ዬራሳቸውን ጉልት ገንብተው አጋድመው ነፃነትን – ሰብዕዊነትን የሚርዱበት ለወሬ ነጋሪ ፍርፋሪ መረጃ በማይገኝበት ሁኔታ የታፈነና የተዘጋ ነው። ስለዚህ በዚህ በአለቀ ጊዜ በዬትኛው የኢኮኖሚ አቅም፤ በዬትኛው የማበረታቻ ድጋፍና፤ በዬትኛው የወያኔ ቅን መንፈስ ነው ተቃዋሚዎች ለውድድራቸው የሚያስፈልጋቸውን ማናቸውም ተግባር ሊከውኑ የሚችሉት። ሰው መተንፈስ ካልቻለ ይሞታል። እኔ እንደማስበው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውሙት አዬር ነው።
ማገዶነቱ ሆን ግብርነቱ በተናጠል ከሆነ ጥቃቱ ሰፊ ነው። በወል ከሆነ ግን ጥቃቱም ሆነ ግብርነቱ ይቀንሳል። በሌላ በኩል የጥንካሬና የኃይል ምንጩ ደግሞ አቅምን ማድመጥ መቻል ነው። አቅምን አድምጦ በአቅም ልክ መንቀሳቀስ ለውጤት ያበቃል። አሁንም እኔ እንደማስበው ተቃዋሚ ፓርቲዎች አቅም የላቸውም። ስለምን? አቅማቸውን ሆነ ሃይልና ጉልበታቸው ጠብንጃና ካቴና በማናለኝበት ስላፈኑት። ስለዚህ ተቃዋሚዎች መጀመሪያ ማድረግ የሚኖርባቸው አቅማቸውን የቀማቸውን ሁኔቴ ማስለወጥ ነው።አቅማቸው ውጤታማ እንደሚሆን ስለሚያውቅ ነው ወያኔ በቀጥታ ጥቃቱን በአቅም ላይ የሚሰነዝረው።
አንደ እኔ ወደ ሁለተኛው ደረጃ ከመሄድ በፊት የመጀመሪያ ደረጃውን በድል አድራጊነት መወጣትን ይጠይቃል።ንቦችን እያቀበሉ በምርጫ ተወዳድረን እናሸንፋለን ማለት ግራ ነገር ነው። ምክንያቱም ከአርት ዓመት በኋላም ይሄው አሁን የሚታዬው ነገር ይደገማል። ተቃዋሚዎች የማያዳግም ተግባራትን በከወኑ ቁጥር ማለት የህዝብን መንፈስ እልምተው በአንድ አቅጣጫ ግፊት ፈጥሮ ሃይሉን መጠቀም በቻሉ ጊዜ ግን ነገን አብርተው ወደ ቀጣዩ ሂደት መሸጋገር ይችላሉ። በስተቀር ….. ግን ኢትዮጵያ በአረም ተውጣ ተክሎቿ በመጫጫት እንደ ጨለመባት ትቀጥላለች …. በጎሳ አገዛዝ ሥር – ተጎሳቁላ፤
ብዙኃኑ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ቁጭ ብለው መምከር ያለባቸው የተቀሙትን ነፃነት ለማስመለስ ህሊናዊ ሥራዎች ላይ በእጅጉ ማተኮር አለባቸው፤ በማደራጀት ተግባራት ላይ ተግተው መሥራት ይኖርባቸዋል። ይህም ቢሆን ቀላል አይደለም። ፈተናቸው ስቃያቸው – ግብርነታቸው መጠነ ሰፊ ነው። ነገር ግን ሳይሰለቹ ነገን ለማልማት ዛሬን አድምጠው በረጅሙ አስበው ግን ከትንሿ ነጥብ ተነሰተው ግዙፉን ትውልዳዊ ድርሻ ለመወጣት መተለም ይኖርባቸዋል።
መሰናዷቸው ብቃት ካለው ወያኔ ብቻውን ተወዳድሮ የሚያደርገው የምርጫ ማሸነፍ በሁለት እግሩ ሳይቆም አፍረክርከው የህዝብን ሥርዓት መገንባት ይችላሉ። ይህን ለማድረግ ግን ለማያገኙት ፍሬ፣ ለማያፍሱት ምርት ጊዜ አለማባከኑን፤ ጉልበት አለማፍሰሱን፣ በቅጡ ሊያምኑበትና ጠንከር ካለ ውሳኔ ላይ ሊደርሱበት ይገባል።ፍላጎታቸው በምርጫ ላይ ሳይሆን የወያኔ ዬዬአራት ዓመት ዬማላገጫ ዬምርጫ ዘመኑ እንዴት ሊያከትም እንደሚችል፤ በዚህ ላይ ጠንከረው ቢሰሩበት ወያኔ ምርጫውን አሸነፍኩ ባለበት ማግስት ፎቁ ተደርምሶ ከነቅል ቋንቋራው አመድ ሊሆን ይችላል።
…. ወይንም የምርጫ መሰናዶ ላይ እያለ ነገ ምርጫ ሊካሄድ በዋዜማው እሱ ባሰናዳውና ባማቻቸው ላይ የብዙኃኑ ነፃነት ቁብ ሊል ይችላል … ማን ያውቃል? ተቃዋሚ ፓርቲዎች የበለሃሰብ አላጋጩን ዬምርጫ መንፈስን ለወያኔ ሸልመው፤ እነሱ ግን ለዘለቄታ ፍትህና ርትህ ተከታታይነት ያለው፣ ከመሬት የተነሳ፣ መሬትም የያዘ፣ የህዝብ ተደማጭነትና አክብሮት ያልተነፈገው የተረጋጋ ተግባር መከወን አለባቸው። የነቶሎ ቶሎ ቤት ለዘላቂ ነፃነት ግጥሙ አይደለም። ተቃዋሚዎች በሌላ ጉዳይ ሳይወጠሩ፣ በተቀጥላ ፍላጎት ላይ ብክነት ሳያመጡ ስክን ያለ ተግባር ከከወኑ ሚሊዮኖች ያሸንፋሉ።
የኛ የነፃነት ታጋይ ፓርቲዎች ጥድፊያውን ለወያኔ ይሸልሙት። እነሱ ግን ነፍስን ለሚታደግ፣ የእናት ልጆችን በመሬታቸው ላይ የሚያሰባስብ፣ ውብ ጠረን ያለው መርሃ ግብር ነድፈው ይንቀሳቀሱ። እርሃብ እራሱ ወያኔን ከሥሩ ይፈነቅለዋል። እራህቡን ማናገር፣ ቁሞ እራሱ እራህብ – እራህቡን እንዲገልጽ ማበረታታ፤ ለዘለአለም ከራህብ ፍውሰት ዬማስገኘት አስፈላጊነትን መተርጎም እራሱ እራህብ እንዲችል ማደረግ ከቻሉ መስዋዕትነታቸው ከግቡ ይደርሳል።
አብዛኛው የብዙ ነገር ራህብተኛ ነው። ለምሳሌ በአንድ ትልቅ ድርጅት ውስጥ በኃላፊነት የሚሰራ ሰው … የእህል ራህብ ላይኖርበት ይችላል። ግን የነፃነት ራህብ ይኖርበታል። ድብን እያለ ነው የሚኖረው። በዘሩ፣ በእምነቱ፣ በብቃቱ፣ በፈጠራ ሥራው፣ በተስፋው፤ በሁሉም ላይ በወያኔ ቁጥጥር ሥር መሆኑን ያውቀዋል። ሳይወድና ሳይፈልግ በቦታው ብቻ በቀጥታ የፓርቲ አባል እንዲሆን መገደድ ብቻም ሳይሆን ግዴታውን እንዲያሟላም ይጫነዋል – ወያኔ። … በዬትም ሁኔታ ኢትዮጵያ ውስጥ ከምርጥ ዘር በስተቀር ነፃነት ያለው ሰው አይኖርም። ከምርጥ ዘርነት ያፈነገጡትም ቢሆኑ ህሊናቸውም መንፈሳቸውም በሁለት ወገን የተወጠረ – ንጹህ አዬር ያጠረው ህይወት ነው የሚኖራቸው። … ስለዚህ በሁሉም ዘርፍ ያለውን ራህብ ቀስቅሶና አደራጅቶ ሃይል መፍጠር፤ ሃይሉ አቅም ሆኖ ነፃነትን አምጦ እንዲወልድ የማድረጉ ጉዳይ ነው አጀንዳ ሊሆን የሚገባው።
በሌላ በኩል ልብ ብሎ እያንዳንዱን ስንኝ ላነበበው የጸሐፊ ዮፍታሄ ግሩም ድንቅ የነገ መንገድ መሪ ጹሑፍ ሀገር ቤትም ሆነ ውጪ ሀገር በተግባር መተርጎም ከተቻለ፤ ማለት አድማጭ መሆን ከቻልን ቁልፉ ይገኛል። የወያኔ ሃይል እኛው ነን። ከእኛ የሚጠበቀው ትንሹ መስዋዕትነት ወያኔ ከእኛ የሚየገኘውን ሃይል ማሳጣት የምንችለባቸውን ተግባራት ላይ ዓይናችንም ሆነ መንፈሳችን ማረፍ አለበት። ሰው ከራሱ ጋር፤ ሰው ከመንፈሱ ጋር፤ ሰው ከአካሉ ጋር መምክርና መደማመጥ – መስማማት ከቻለ ወላዊ ጉዳይን በአንድ አማክሎ ጌጥ ማደረግ ብዙም አይቸግርም። እራስን ማሸነፍ ነው ወያኔን ሊገድለው የሚችለው ጉለበታም ውሳኔ። ማሸነፍ እራስን የሀገር ገዳይ ጠላትን ለመግደል ቀላሉ መፍትሄ።
አቅል አቅምን መርቶ ለድል እንዲበቃ የጎደለንን ቦታ እንፈትሸው።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።
No comments:
Post a Comment