Sunday, 14 December 2014

ኘሮፌሰር አሥራት ታህሳስ 11/1985 በደብረ-ብርሃን ከተማ መስቀል አደባባይ ካደረጉት ንግግር የተወሰደ

የኢትዮጵያን አንድነት በመደገፍ በዚህ ስብሰባ ላይ የተገኛችሁ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ፣
የዚህ መከረኛ ትውልድ ነፃ አውጭ የሆናችሁ ወጣቶች
ክቡራትና ክቡራን ወገኖቼ
ከሁሉ በፊት በእናንተ ውድ ወገኖቼ መካከል በዚህ አደባባይ ላይ ተገኝቼ ስለውድ ሀገራችሁ ስለኢትዮጵያ ህልውና እንዲሁም በየቦታው በግፍ በመጨፍጨፍ ላይ ስለሚገኘው ወገናችን ስለዐማራው ሕዝብ የወደፊት መኖር ወይም አለመኖር ጉዳይ፣ ለመወያየት ላበቃኝ ሁሉን ማድረግ ለሚችለው አንድ አምላካችን ምሥጋና አቀርባለሁ፡፡
የተወደዳችሁ ወገኖቼ!
ይህ የአለንበት ዘመን ሀገራችን ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ሕዝብ በከፍተኛ ችግር ላይ የወደቀበትና ፈታኝ ከሆነ የጥፋት ማዕበል ውስጥ የተገባት ወቅት ነው፡፡
በተለይም የኢትዮጵያ የታሪክ ጠላቶች ኢትዮጵያን ለማጥፋትና ለማዳከም ሲያውጠነጥኑ የኖሩት ዕቅድና ስልት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ መሆን የጀመረበት ወቅት ስለሆነ በኢትዮጵያዊነታችን ለምናምን ሁሉ አሳሳቢ ብቻ ሳይሆን እጅግ ፈታኝ የሆነ ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡
ይህ ሀገራችንንና ሕዝቡን ከጥፋት ማዕበል ውስጥ ያስገባ ችግርና ወጥመድ በኢትዮጵያዊያኖች የተጠነሰሰና የተፈጠረ ሳይሆን በውጭ ጠላቶቻችን የታቀደና ለተግባራዊነቱም ገንዘብ ዕውቀትና ቁሳቁስ ተመድቦለት በከፍተኛ ደረጃ ክትትል የሚደረግበት ከመሆኑም በላይ፣ ዓለም በአንድ ኃይል መዳፍ እጅ የመግባቷን ሁኔታ ሲያበስር የኢትዮጵያ ጉዳይ ደግሞ ከራሷ ሕዝብ በቀር ሌላ ዳኛና ተቆርቋሪ የሌላት መሆኑን መገንዘብ ይኖርብናል፡፡
የኢትዮጰያ ጠላቶች ኢትዮጵያን ለማጥፋት ሲያቅዱና ሲዘምቱ ለረጅም ጊዜ የኖሩ ቢሆንም እንደዛሬው ኢትዮጵያን ባዶውን ያገኙበት ጊዜ በታሪክ አልታየም፡፡ ይህ የሀገራችን ባዶነት ሊከሰት የቻለው ከረጅም ጊዜ የጠላቶቻችን የውስጥ ቡርቦራ በኋላ ሕዝቡ እንዲከፋፈል፣ በራሱ ልጆች ላይ ዕምነት እንዲያጣ፣ ሞራሉንም፣ ታሪኩንም፣ ሃይማኖቱንም በአጠቃላይ ሁለንተናውን ሁሉ እንደምሰጥ ውስጥ ውስጡን ሲበሉት የቆዩ በመሆናቸው ነው፡፡
ከዚህ በቀር በአሁኑ ወቅት በድንገት በዓለም ላይ የተከሰተው የፖለቲካ ሁኔታ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ችግር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረገ መሆኑ ይታያል፡፡
ከዚህ የተነሳ፣ የዓለምን ሕዝብ የጋራ ሕልውናና የታናናሽ ሀገሮችን ደህንነት በማስጠበቅ ረገድ፣ ከፍተኛ ሀላፊነት የሚጠበቅበት የተባበሩት መንግሠታት ድርጅትም፣ የዓለም ታላላት ኃይሎች ሚዛን ባልታሰበ ሁኔታ በድንገት ስለተዛበ በአንድ ኃይል አመራር ሥር ወድቆ ለዳግመኛ የታሪክ ትዝብት ተጋልጦ ይገኛል፡፡
የራሱ ሚዛን በመዋለል ላይ የሚገኘው የዓለምን ሁኔታ በብቸኛ ኃያልነት የሚመሩት ወገኖች፣ በየትኛውም አካባቢ ያለውን ፍላጐታቸውን ለማርካትና ጥቅማቸውን ለማመቻቸት የሚችሉ ቡድኖች በሥልጣን ላይ እንዲቆናጠጡ ከማድረግ ባሻገር የሀገሩን ሕዝብ ጩኸት የሚሰሙበት ጆሮአቸውን ይሁነኝ ብለው ደፍነውታል፡፡
ስለሆነም በማንኛውም አገር ውስጥ ምንም ዓይነት ችግርና በሕዝብ ላይ የሚፈፀም ዕልቂት ቢከሰት፣ ከነሱ ስልትና ጥቅም አንፃር የሚያሳስባቸው ሆኖ እስካላዩት ድረስ ስሜት ሊሰጣቸውና የዕልቂቱም ሰቆቃ የሚቀሰቅሳቸው አይደለም፡፡
ይህ የውጭ ሀይሎች ስልት፣ ይህች የምንኖርባትን ክፍለ ዓለም ማለትም የአፍሪካን ቀንድና እንዲሁም በአውሮፓና በዩጐዝላቢያም ምድር ሕዝብን እርስ በርሱ በማፋጀት የሚፈጽሙት ደባ በገሀድ እየታየ ነው፡፡
በማስታጠቅና የነሱ ደጋፊ ትከሻ በመሆን በሌላ በኩል ደግሞ የመሳሪያ ፋብሪካቸው ገበያ እንዲያገኝ፣ የጦር መሳሪያዎችን በግፍ በማቅረብ ሕዝቡን እርስ በርሱ በማፋጀት ረገድ ወኪሎቻቸው የነሱን ዓላማ ለማራመድ የሚችሉበትን በረቀቀ ጥናት የተደገፈ ተክህኖ ይሰጣቸዋል፡፡ ይህ እርስ በርስ የማፋጀት ስልታቸውም ትኩረት የሚያደርገው በረጋው ማህበረሰብ ውስጥ ጐሳን፣ ቋንቋንና ሃይማኖትን ለሕዝቡ አጉልቶ በማሳየተና በዚህ አንፃር በመከፋፈል ነው፡፡
በኢትዮጵያ ላይ የውጭው ኃይል ትኩረት ማድረግ ከጀመረ ብዙ ምዕተ-ዓመታት ያለፈ ቢሆንም በይበልጥ ስልታዊ ዕቅዱን በተጠና ሁኔታ ማራመድ የተጀመረው በታላቁ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት በዳግማዊ ምኒልክ መሪነት ኢትዮጵያ በአድዋ ላይ ካስመዘገበችው ድል በኋላ ነበር፡፡
በነጮች ዕውቀት የተገነባውን የወቅቱን ኃይል ሀገር ጦር በአፍሪካ ምድር የሚቋቋመው ኃይል የለም በሚባልበት በዚያ ጨለማ ዘመን ኢትዮጵያ ያስመዘገበችው የጦር ሜዳ ድል ወደ አፍሪካ ያጣጠረውን የውጭ ኃይል እንደገና እንዲያሰላስልና እንዲያስብ ስላደረገው ሕዝብን ማሸነፍና መያዝ የሚችለው በጦርነት ብቻ ሳይሆን እራሱን በራሱ እንዲጐዳና እንዲከፋፈል በማድረግ የሕዝቡ ኃይል በቀላሉ ሊፈራርስ የሚችልበትን ስልት በመቀየስ ጭምር መሆኑን እንዲያምኑበት አድርጓቸዋል፡፡
ስለሆነም ኢጣሊያ በአድዋ ላይ የደረሰባትን አሳፋሪ ሽንፈት መነሻ በማድረግ 40 ዓመት ሙሉ ሲጠና ሲታቀድና ከሞላ ጐደል ከሰሜን ኢትዮጵያ በተወሰደው የኢትዮጵያ አካል የሆነውን የኤርትራን መሬት መቆናጠጫ በማድረግ የኢትዮጵያ ሕዝብ እርስ በርሱ የማባላቱ ተግባር በግንባር ቀደምነት ተጀምሮ ነበር፡፡
የተወደዳችሁ ወገኖቼ!!
የወገንና የሀገር ጉዳይ በመሆኑ ብዙ በመናገር ጊዜያችሁን እንዳባከንኩ ይሰማኛል፡፡
ሆኖም የአባቶቻችንን የሚያኮራ ታሪክ በማስደፈርም ሆነ ባለማስደፈር በውርደትም ሆነ በኩራት ለማስረከብ ባለብን የዜግነት ግዴታ አነፃር በአሁኑ ጊዜ በታሪክ ፊት ተጋልጠን የምንገኝበትን እንደገና ላስታውሳችሁ እገደዳለሁ፡፡
በጠላት ወረራ ጊዜ የኢትዮጵያ ሕዝብ በ3 ተከፍሎ እንደነበር አስታውሱ አንደኛው ወገን ውርደትን በመጥላት በነፃነቱና ለክብሩ ሲል ቤት ንብረቱን ትቶ ወደ አርበኝነቱ በመግባት የዱር ገደሉን ኑሮ በመጀመር ታራክ ሠርቶ ያለፈና የኖረ፣ ሁለተኛው አገር ሲረጋ እመለሳለሁ ብሎ ሕይወቱን ለማዳን ሲል የተሰደደ፣ ሦስተኛው ለሆዱ አድሮ የጠላት መሳሪያ በመሆን ወገኑን ከሚጨፈጭፈው የኢጣሊያ ጦር ጋር ያበረ ነበር፡፡
ሆዱን ለመሙላትና የማይቀረውን ሞት ለጊዜው ለማዘግየት ሲል የውርደትን መንገድ የመረጠው በትዝብት ውስጥ ወደቀ እንጂ የኢትዮጵያ አርበኞች ድል አድራጊነት አልቀረም፡፡
ለሀገሩና ለወገኑ ክብርና ደህንነት ደረቱን ለጥይት በመስጠት የቆረጠው አርበኛም ያለቀኑ አልወደቀም፣ አልሞተም እንዲያውም ከተፈጥሮ ሞቱ በኋላም ቢሆን በታሪክ ውሰጥ እየኖረና ኢትዮጵያንም በታሪክ እያኖረ ነው፡፡
ወገኑን የከዳውና ለሆዱ ያደረው ባንዳም ከውርደት በቀር ትረፍ ሕይወትና ትርፍ ኑሮ አልኖረም፡፡ ዛሬም እንደነዚህ ያሉ የሕዝብ ጠላቶች ለማንም የማይበጁ ማንኛውንም የሀገርና የወገን ጉዳይ ለጥቃቅን ጥቅማቸው የሚሸጡ፣ የትውልድ አተላ ስለሆኑ እግዚአብሔር በቸርነቱና በኃይሉ ቀናውን አስተሳሰብ እንዲሰጣቸው እየተመኘን ይህን ከመሰለው የትውልድና የታሪክ አተላነት የሚላቀቁበትን ልብ ለማግኘት በቂ ጊዜ ስላላቸው ማሰብና ደጋግመው ማሰላሰል ከዚያም ስለአቋማቸው መወሰን የኖርባቸዋል፡፡
በዚህም መሠረት ለወገን ውድቀትና መጠቃት ለሀገር መዋረድና መበታተን ለዲሞክራሲና ለሰብአዊ መብት መታፈን መሳሪያ የሚሆኑ ሆዳም ዐማሮች ካሉ አጥበቀን እንመክራቸዋለን፡፡
በተለይ ወጣቱ የአባቶቹን ዓላማ ያለጥርጠር እንደሚያነሳ ሙሉ ዕምነት አለኝ፡፡
መዐሕድ ለዐማራው ሕዝብ ሕጋዊ መብት መጠበቅ ለኢትዮጰያ አንድነትና ሉዓላዊነት መከበር የሚያደርገውን ትግል በቆራጥነት መቀጠሉን ይገፋበታል፡፡ የተቋቋመበት ዓላማው ስለሆነ በማንኛውም ቦታ የሚፈጽሙትን ኢ-ዲሞክራሲያዊ ድርጊቶች በማጋለጥና በመቃወም ቻርተተ በፈቀደው መሠረት የሕዝቡን ሠላማዊና ዲሞክራሲያዊ እንቅስቃሴ በግንባር ቀደምትነት ማስተባበሩን ይቀጥላል፡፡
በመጨረሻም ላሳሰባችሁ የምፈልገው ዛሬ ዓለም በሥነ ጥበብ መጥቃ በመሄድ ሀገረን በማልማት የሕዝብን የማህበራዊ ፍላጐት በመርካት ከፍተኛ እርምጃ የሚካድበት ጊዜ መሆኑን ነው፡፡ በዚህም መሠረት ሀገራቸው ምድረ በዳ የሆኑ አገሮች እንኳ በሠላም በመሥራታቸው ለሕዝባቸው ብዙ ጥቅም እያስገኙ ናቸው፡፡ ኢትዮጰያ ሀገራችን በምድር ላይ ያለች ገነት መሆኗን ሙሶሎኒ ሳይቀር ሲመሰክር ለወታደሮቹ ባደረገው ንግግር “ይህችን የምድር ገነት ውረሱ” ነው ያላቸው፡፡ ስለዚህ ሁላችንመ ሕዝብም ሹማምንትም በሰላምና በእኩልነት ተፈቃቅሮ መሥራቱ፣ ጥቅሙ የሁላችንም መሆኑን ተገንዝበን በመሐላችን ያለውን ልዩነት ከማስፋፋት ይልቅ በመሐላችን ሊጐለብት የሚችለውን ስምምነታችንን እንዲጠናከር በማደርግ አርቀን እንድንመለከት ጥሪ አቀርባለሁ፡፡
ኢትዮትጵያ በልጆቿ መሰዋዕትነት አንድነቷና ነፃነቷ ተከብሮ ለዘለዓለም ይኖራል

No comments:

Post a Comment