Thursday, 4 December 2014

ለሁሉም እምነት ተከታይ ኢትዮጵያውያን የተላለፈ ጥሪ

ከ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር

የተለያየ እምነት ተከታይ የሆኑ ኢትዮጵያውያን በአገር ላይ የመጣን ችግር በጋራ ሲከላከሉ ዘመናትን አስቆጥረዋል፡፡ የተቀያየሩት መንግስታት ሳይወስኗቸው፣ እምነታቸው ሳይለያያቸው በጋራ ችግሮቻቸውን ሲፈቱ ቆይተዋል፡፡ በእየ እምነቶቻችን ያሉት ጥልቅ ስነ ምግባሮች ጥቃቅን ልዩነቶቻችንን ተሻግረው አብሮ ለመኖራችን ዋነኛ ሚስጥሮች ናቸው፡፡ በዚህ በኩል እምነቶቻችን ኢትዮጵያውያን ለተሳሰርንበት ድር ትልቅ ሚና እንዳላቸው መናገር ይቻላል፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያውያን ይህን ታሪካዊ መስተጋብር ሲያደርጉ እምነታቸውን በነጻነት ያራምዱ ነበር ማለት አይደለም፡፡ እንዲያውም ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ጊዜያት እምነታቸውን በነጻነት እንዳይከተሉ የተለያዩ በደሎች ደርሰውባቸዋል፡፡ የእምነት ነጻነታቸውን ለማረጋገጥ በተደረገ ትግልም ከፍተኛ ዋጋ ከፍለዋል፡፡



ህወሓት/ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ከመጣበት ጊዜም ጀምሮ እንደሚያከብር ቃል ከገባቸውና በህገ መንግስቱም ካሰፈራቸው ጉዳዮች መካከል የእምነት ነጻነት አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ ሆኖም ይህን መብት በየ መድረኩ ለፕሮፖጋንዳነት ከመጠቀምና የወረቀት ጌጥ ከመሆን አልፎ መሬት ላይ ሲተገበር አልታየም፡፡ ገዥው ፓርቲ ወደ ስልጣን ከመጣ ጊዜ ጀምሮ በህገ መንግስቱ ካስቀመጠውና በየ መድረኩ ከሚናገረው በተቃራኒ የእምነት ተቋም መሪዎችን ካድሬዎቹ በማድረግ ህዝብን ለመያዝ እየጣረ ይገኛል፡፡ ይህን የገዥው ፓርቲ አካሄድ የተቃወሙ ምዕመናን በአሸባሪነት፣ በጸረ ሰላም ኃይልነት፣ በአፍራሽነት...እና በሌሎችም ስርዓቱ በመፈረጃነት በሚጠቀምባቸው ስሞች ሲከስ፣ ሲያስርና እርምጃ ሲወስድ ኖሯል፡፡ ለአብነት ያህልም የሙስሊምና ክርስቲያን ኢትዮጵያውያን ስርዓቱ ከሚፈልገው ውጭ እምነታቸውን እንዳይከተሉ እያደረገ እንደሚገኝ መጥቀስ በቂ ነው፡፡


በኢህአዴግ አገዛዝ እምነቱን በነጻነት እንዳይከተል በደል ሲደርስበት ከቆዩት መካከል የሙስሊሙ ማህበረሰብ አንዱ ነው፡፡ ኢህአዴግ በአንድ በኩል የእምነት ነጻነትን እንደሚያከብር እየተናገረ በእውኑ ግን የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን መሪዎች እምነቱ ከሚፈቅደው ውጭ በቀበሌ እስከመምረጥ ደርሷል፡፡ እምነታቸው ባስቀመጠው መሰረት መሪዎቻቸውን መምረጥ እንዳለባቸው ድምጻቸውን ያሰሙ የእምነቱ ተከታዮች በስርዓቱ ከፍተኛ በደል ደርሶባቸዋል፡፡ ህገ መንግስቱ ላይ የሰፈረው መብታቸው እንዲከበር በመጠየቃቸው ብቻ ጸረ ኢትዮጵያ፣ አሸባሪ፣ አክራሪና ሌሎች ስሞች ተለጥፎባቸዋል፡፡ በርካቶች በዘግናኝ እስር ቤቶች ታጉረዋል፣ በቅዱሱ የረመዳን እለት ሳይቀር በስርዓቱ ታጣቂዎች በጭካኔ ተደብድበዋል፤ የእስልምና እምነት ስርዓት ከሚፈቅደው ውጪ መስጊዶቻቸው ተደፍረዋል፡፡


በተለይ ባለፉት 3 አመታት መብታቸው እንዲከበር በሰላማዊ መንገድ የጠየቁት ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ላይ እየተፈጸመ የሚገኘው ታሪካዊ በደል ስርዓቱ የእምነት ነፃነትን በማታለያነት ከመጠቀም ውጭ በህገ መንግስቱ ያሰፈረውን መብት እንደማያከበር፣ ከዚህም አልፎ ጸረ እምነት ስለመሆኑ ቋሚ ማሳያ ነው፡፡

ስርዓቱ የተጠናወተው እምነትን በመሳሪያነት የመጠቀም፣ የእምነት መሪዎችን ካድሬ የማድረግና ህዝብን የመሸበብ መጥፎ አባዜ በክርስትና እምነት ተከታዮች ላይም በግልጽ ሲንፀባረቅ ቆይቷል፡፡ ወደ ስልጣን ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ ክርስትና እምነትን ከቆዩ ስርዓቶች ጋር በማዛመድ በጠላትነት ፈርጆታል፡፡ የእምነቱ መሪዎችንም መሳሪያ ለማድረግ የሚቻለውን ያህል ደክሟል፡፡ ከዚህ አለፍ ሲል ደግሞ ኢትዮጵያውያንን በእምነታቸው ለመከፋፈልና ለማጋጨት ጥረት እንዳደረገ በርካታ መረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ ልክ እንደ ሙስሊሙ ማህበረሰብ፤ የክርስትና በተለይም የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታዮች የስርዓቱ መጥፎ አባዜ ገፈት ቀማሽ ሆነዋል፡፡

ኢህአዴግ መራሹ መንግስት ባለፉት 24 አመታት ኦርቶዶክስ ተከታዮችን ከሌሎች የእምነት ተከታይ ኢትዮጵያን ጋር ለማጋጨት ከመጣር ባለፈ ካድሬዎች በቤተ ክርስቲያን ጉዳይ እንዲወስኑ ትልቅ ስራ ሰርቷል፡፡ ይህ ጥረቱ በልማት ስም በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ እጅግ የሚከበሩ ገዳማትን እስከ ማፍረስ ደርሷል፡፡ በቤተ ክርስቲያን ስር የተቋቋሙና ከእሱ ካድሬያዊ መስመር ጋር ለመሄድ ያልፈቀዱ ተቋማትንና ግለሰቦችን ማጥቃቱንም ቀጥሏል፡፡ በማህበረ ቅዱሳን ላይ ሊወስድ ይችላል የሚባለው እርምጃ እንደምሳሌ ማቅረብ ይቻላል፡፡ በሌሎች አማኞች ላይም ተመሳሳይ በደል እንደሚፈጸም ይታወቃል፡፡


ህወሓት/አህአዴግ የእምነት መሪዎችን ካድሬዎቹ ማድረግ የሚፈልገው የእሱ መሰረታዊ የፖለቲካ አቋም ስለ እውነት፣ ስለ አንድነት፣ ስለ ሰላም ከሚያስተምሩት የእምነት መርሆች ጋር ፍጹም ተቃራኒ በመሆኑ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን በእምነታቸው መሰረት ስለ አንድንት ሲሰበኩ የኢህአዴግ የመግዢያ መሳሪያ የሆነው ከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲው ዋጋ አልባ እንደሚሆን ግልፅ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን በየ እምነቶቻቸው ስለ ሰላም ሲሰበኩ ከኢህአዴግ የጦረኝነት ባህሪ ጋር ቢጋጩ የሚገርም አይሆንም፡፡ በእየ እምነቶቻቸው ስለ እውነት የሚሰበኩት ኢትዮጵያውያን መሰረቱን በሙስና፣ በሀሰትና በፈጠራ የተመሰረተ ስርዓት የሚጠብቃቸው እርምጃ አሁን ኢህአዴግ የሚወስደውን አይነት ቢሆን ሊገርም አይችልም፡፡ በመሆኑም በኢህአዴግና በምዕመናን መካከል የሚታየው ተቃርኖ በነጻነት እምነትን የመከተልና የጸረ እምነትነት ነጭና ጥቁር ተቃርኖ ነው፡፡


እንዲህም ሆኖ ግን በርካታ ኢትዮጵያውያን በእምነታቸው ለመጽናት ከፍተኛ መስዋዕትነት እየከፈሉ ይገኛሉ፡፡ ለዚህም በእስር ላይ የሚገኙት፣ እንዲሁም ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መንገድ በጁምዓ እለትና ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ በጽናት ትግላቸውን የቀጠሉት ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ትልቅ አርዕያ ናቸው፡፡ ስርዓቱ በጥይትና በቆመጥ ሊገታው ያልቻለው ይህ የሙስሊሙ ማህበረሰብ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ከራሱ አልፎ ለሌሎቹም ተምሳሌት የሚሆንና ሊደነቅ የሚገባም ነው፡፡ በተመሳሳይ በየ ገዳሙና በሌሎችም ተቋማት የሚገኙ የክርስትና እምነት ተከታዮች ኢህአዴግ ከሌሎች ጋር ለማጋጨት ሲጥር፣ በእምነታቸው ጣልቃ ሲገባና መሪዎቻቸውን ሊመርጥ ሲሞክር በመቃወም ትግላቸውን ቀጥለዋል፡፡


የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር ይህን ገዥው ፓርቲ በኢትዮጵያውያን ምዕመናን ላይ የሚፈጽመውን በደል እና ምዕመናኑ የእምነት ነጻነትን ለማስከበር የሚያደርጉትን ትግል ከልብ ይደግፋል፡፡ ይህን ሲያደርግ ሀይማኖት ኢትዮጵያውያንን ያስተሳሰረ ትልቅ ድር እንደሆነ፣ ትውልዱን በመልካም መንገድ ለመቅረጽ ካለው ትልቅ ሚና አንጻር እና ከምንም በላይ ደግሞ ኢትዮጵያውያን የእምነት ነጻነት ሊከበርላቸው የሚገባ መሰረታዊ መብት በመሆኑ ነው፡፡ በመሆኑም ስርዓቱ እየፈጸመው የሚገኘውን ታሪካዊ ስህተት የትኛውም ኢትዮጵያዊ ሊቃወመው የሚገባ እንደሆነ እናምናለን፡፡


ትብብሩ የአንድ ወር መርሃ ግብር አውጥቶ ሲንቀሳቀስ የመርሃ ግብሩ አንድ አካል ካደረጋቸው መካከል አማኞች በየፊናቸው ለአገራቸው 
እንዲጸልዩ የጠየቀበት ይገኝበታል፡፡ ይህን ስናደርግ ኢትዮጵያውያን አማኞች በአገራቸው ላይ የሚመጣን አደጋ፣ በራሳቸውና በሌሎች ላይ የሚፈጸምን በደል በጋራ በመከላከል ያላቸውን ተሞክሮ፣ አቅምና ታሪካዊ ግዴታም ግምት ውስጥ በማስገባት ነው፡፡ መርሃ ግብሩን ይፋ ካደረግንበት ጊዜ ጀምሮ ለጥሪው አመርቂ መልስ ማግኘታችን ምዕመናን ለለውጥ ያላቸውን ፍላጎት አረጋግጦልናል፡፡ ወደፊትም ከገጠመን መከራ እንድንወጣ ኢትዮጵያውያን ምዕመናን በእምነታቸው ላይ ከሚደርስባቸው በደል ሳይበግራቸው ከጎናችን እንደሚሆኑ ጥርጥር የለንም፡፡

ትብብሩ ህዳር 27/28 ‹‹ነጻነት ለፍትሓዊ ምርጫ›› በሚል የ24 ሰዓት ሰላማዊ ሰልፍ ያደርጋል፡፡ ይህ መርሃ ግብር ለኢትዮጵያውያን ምቹ ስርዓት ለመመስረት የሚያስችል የትግል ጉዞ እንደሚሆንም እናምናለን፡፡ በመሆኑም ፀረ እምነት በሆነው የገዥው ፓርቲ አካሄድ እምነታቸው እየተረገጠ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የእምነት ነጻነታቸውን ለማረጋገጥ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የአዳር ሰልፉን ቅስቀሳ እንዲደግፉና በሰልፉም በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ እናቀርባለን፡፡


ታሪካዊ ግዴታችን በመወጣት የእምነት ነጻነታችንን እናረጋግጥ!


ያለ መስዋዕትነት ድል የለም!

No comments:

Post a Comment