ነገረ ኢትዮጵያ
ትናንት ሰላማዊ ሰልፉ ላይ ታፍሰው ከታሰሩት አመራሮች መካከል ጥረት አድርገን ነበር፡፡ አዲስ አበባ ፖሊስ ጣቢያ (ሶስተኛ) የታሰሩትን አመራሮችን መጠየቅ አይቻልም በመባሉ ማነጋገር ባንችልም ጨርቆስ ፖፖላሬ የሚገኙትን ሁለት አመራሮች መልዕክት እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡‹‹ከጉዟችን አንዲት ሴንቲሜትር ወደኋላ አንመለስም››
አቶ ግርማ በቀለ የዘጠኙ ፓርቲዎች ፀኃፊ
እኛ የታሰርነው ለቆምንለት አላማ ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ መብታችን ለማስከበር የሚቻለንን ሁሉ እናደርጋለን፡፡ ይግደሉን እንጅ እንወጣለን ብለናል፡፡ ይህን ያልነው ዴሞክራሲያዊ መብታችን ለማስጠበቅ መስዋዕትነት መከፍል የግድ ስላሚለን ነው፡፡ ያለ መስዋዕትነት ድል ልናገኝ አንችልም፡፡ ስንወጣ መስዋዕትነት እንደምንከፍል እናውቃለን፡፡ ግን ደግሞ ለአላማችን ታማኝ መሆን፣ ቃላችንም መጠበቅ ነበረብንና አድርገነዋል፡፡
ከታሰርን በኋላም ቢሆን አንዳንድ መረጃዎች ይደርሱናል፡፡ ህዝቡ በሞራል ድጋፍ ከእኛ ጋር እንደሆነ ሰምተናል፡፡ በእውነቱ ይህ የሚያበረታታ ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ከጎናችን ለቆማችሁ ሁሉ ምስጋና ማድረስ እፈልጋለሁ፡፡ እኛ አላማችን እና ግዴታችን እስከሆነ ድረስ መስዋዕትነቱን ለመክፈል ዝግጁ ነን፡፡ ከጉዟችን አንዲት ሴንቲሞትር ወደኋላ አንልም፡፡ እናንተም አብራችሁን እንደምትሆኑ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ትብብሩንም አጠናክረን እንደምንቀጥል ተስፋ አለኝ፡፡ በርቱ!
‹‹እኛ እንጸናለን፡፡ እናንተም ወደኋላ እንዳትሉ!››
ጌታነህ ባልቻ (የሰማያዊ ፓርቲ ጥናትና ስትራቴጅ ክፍል ኃላፊ)
ትግሉ ቆራጥነት ያስፈልገዋል፡፡ ለዚህ እኛ የተወሰነም ቢሆን እያደረግን ነው፡፡ እኛ በመታሰራችን ህዝቡ መደናገጥ የለበትም፡፡ እኛ የተወሰነች ነገር ስናደርግ ህዝቡም ማገዝ ይኖርበታል፡፡ በውጭም አገር ውስጥም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ከጅምሩ ጀምሮ እገዛ አድርገዋል፡፡ ግን ይህ አሁን ካለው የአገሪቱ ችግር አንጻር በቂ አይደለም፡፡ እኛ የተወሰነ ነገር ስናደርግ ህዝቡም ደጋፍ ማድረግ አለበት፡፡ እኛ ስንታሰር ህዝቡ ወደኋላ ማለት የለበትም፡፡ እኛ ስንታሰር ትግሉ ካቆመ ለስርዓቱ ትልቅ ድል ነው፡፡ ስለሆነም ትግሉ መቀጠል አለበት፡፡ እስካሁን ድጋፋችሁን ላደረጋችሁልን ሁሉ እናመሰግናለን፡፡ የእኛ መታሰር የትግሉ አንድ አካል ነው፡፡
እኛ እንጸናለን፡፡ እናንተም ወደኋላ እንዳትሉ!
No comments:
Post a Comment