Wednesday, 10 December 2014

ከመተባበርና አንድ ከመሆን በላይ ታላቅነት የለም – የሰማያዊ ከፍተኛ አመራር

“አምናለሁ። አንድ ሆኖ ለአንድ ሀገር መቆም ብንችል እውነት ይሄ ታላቅነት ነው። ከዚህ በላይ ታላቅነት አለ ብዬ አላስብም፡፡”
“በፍቅር በሰላማዊ መንገድ በመነጋገር የማንንም ሰው ሀሳብ ማሸነፍ ይቻላል ብዬ አምናለሁ።”
Untitled
ወ/ሮ ሃና ዋልለልኝ ይባላሉ። የሰማያዊ ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የሴቶች ጉዳይ ኃላፊ ናቸው። ፍኖተ ነጻነት ባወጣው 86ኛ እትሙ ቃለ መጠይቃ ካደረገላቸው የተወሰደ ነበር። ከቅአለ መጠይቅቁ የተወሰነዉን እንደሚከተለው አቅርበናል።
ፍኖተ ነፃነት፡- በመጪው ምርጫ ላይ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ምንድን ነው የሚጠበቀው?
ወይዘሮ ሀና፡ – ከተቃዋሚዎች የሚጠበቀው እርስበርሳችን በመስማማትና ትንንሽ ልዩነቶቻችንን በማስተካከል ባለችው ቀዳዳ፣ ጠባብ ቀዳዳ ማለት እችላለሁ ሾልከን ለውጥ ለማምጣት መትጋት ነው፡፡ የረጅም ጊዜ ልምድ አለ፤ ከዛ ውስጥ ደግሞ ነጥረው የሚወጡ ሰዎች ይኖራሉ፤ የሚታዩም አሉ። ጥሩ ጥሩ ወጣቶችም እያደጉና እያበቡ ነው። እነዚህን ነገሮች ወደ ተግባር ወይም ወደ ውጤት በመቀየር ለምርጫ ራስን ማዘጋጀት ያስፈልጋል። ምክንያቱም ሀገሪቷ ላይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በምርጫ የሚመጣ ስልጣን ብናገኝ በእውነት ይህቺ ሀገር ታላቅ ትሆናለች። ጥሩ ነገርም ይታይባታል፡፡ስለዚህም እርስ በእርሳችን በብዙ ፍትጊያ ውስጥ አልፈን በብዙ ዘረኝነት ውስጥ አልፈን እዚህ ደረጃ መድረስ ራሱ ትልቅነት ስለሆነ ይሄን ብናደርግ ደግሞ የተሻለ ትልቅ ሰው እንሆናለን ብዬ አምናለሁ። እርስ በርሳችንም እንከባበራለን፤ እንቻቻላለን፤ መቻቻሉ ግን በመተማመን ውስጥ መሆን አለበት ብዬም አምናለሁ።
ፍኖተ ነፃነት፡- በፖለቲካ ፓርቲዎች አብሮ በመስራት ላይ ሁለት አይነት አስተሳሰቦች በአደባባይ ሲራመዱ እናስተውላለን። ፓርቲዎች አንድ ላይ ተባብረው መስራት አለባቸው የሚል ወገን አለ፡፡ አንዳንዱ ደግሞ ብቻቸውን ነጥረው መውጣት አለባቸው ይላል፡፡ባንቺ አመለካከት አሁን ካለው የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ አውድ አንጻር የትኛው ያዋጣል
ወይዘሮ ሀና፡- ፓርቲዎች ነጥረው ይወጣሉ የሚለው ነገር የእኔም ሀሳብ ነበረ። ጥረቱ ጥሩ ነው። ባልተሄደበት መንገድ መሄድ የአስተዋይነት ምልክት ነው። ባለንበት እንቁምና ባለንበት እንርገጥ የሚል አስተሳሰብ መኖር የለበትም። ሁልጊዜ የሰው ልጅ አዲስ ነገርን ይፈልጋል። አዳዲስ ነገሮችን ማምጣት ይፈልጋል። ስለዚህ ያልተደረጉ ነገሮችን መሞከርና ማድረግ ጤናማነት ነው። ያ ደግሞ የማይሳካበትን ሁኔታ ካወቅን ወይም ደግሞ በፊት አብሮ መስራቱ አይጠቅምም ብለን ከነበረ አሁን ይጠቅማል ወደሚለው ነገር ላይ አስተሳሰባችን ከመጣ ደግሞ ያንን ተቀብሎ ማራመድ ምንም የሚጎዳ ነገር አይደለም።
ሁለቱም ሀገርን ለመጥቀም ለውጥን ለማየት ከመፈለግ የመነጨ እስከሆነ ድረስ ጤናማ ናቸው፡፡ ለየብቻ መስራት የሚያዋጣ ነው ብለን እርግጠኛ ስንሆን ብቻችንን መስራት ይኖርብናል። እኔ አሁን ያለኝ እምነት አብሮ መስራት ታላቅ ያደርጋል ነው። ሁለተኛው ነገር ደግሞ ከአንድ ብርቱ ሁለት መድሃኒቱ የሚለው ተረት ቀላል አይደለም። በሶስት የተገመደ ገመድም ምን ያህል ጠንካራ እንደሆነ እናውቃለን። ከዚህ በፊት ለብቻችን ነጥረን እንውጣ የሚለውን ሀሳብ ከሚያራምዱት ውስጥ ነበርኩኝ። ያም የተደረገበት ምክንያትም ከመገፋት ወይም ደግሞ አቅምንና ያለንን እውቀት ለማውጣትእንዳንችል ከመደረግ አንፃር ነው። ሆኖም ግን ያንን ነገር ለውጠን የአብሮ መስራታችንን ብቃታችንን ክህሎታችንን አሳድገን አብሮ በመስራት ለውጥ ማምጣት፣ ራሱን የቻለ ስኬት ነው ብዬ አምናለሁ። አንድ ሆኖ ለአንድ ሀገር መቆም ብንችል እውነት ይሄ ታላቅነት ነው። ከዚህ በላይ ታላቅነት አለ ብዬ አላስብም፡፡ ራስን ለሀገር መሰዋት ማድረግ ያስፈልጋል። በነገራችን ላይ እኔ መስዋዕት የምለው የመሞት የመታሰርን ብቻ አይደለም፡፡ ትልቁ መስዋዕትነት ማለት ፍላጎትን ሁላ ማሸነፍ መቻልን ራስ ወዳድነትን ማሸነፍ መቻልንና ለሌሎች መኖር መቻልን ነው፡፡ ለሌሎች መኖርን መልመድ መቻል አለብን። በአፍ ሳይሆን በተግባር ይሄን ካደረግን የማይፈነቅል ድንጋይ አይኖርም።
ፍኖተ ነፃነት፡- የፓርቲዎች የውስጥ ዴሞክራሲ ምን መሆን አለበት ትያለሽ? በየፓርቲዎቹ ውስጥ ያሉ አስቸጋሪ ባህርያቶችስ ምንድን ናቸው?
ወይዘሮ ሀና፡- ብዙ ጊዜ ችግራችን መደማመጥ አለመቻል ነው ብዬ አስባለሁ። እንደገና ደግሞ እኔ አውቃለሁ የሚሉ ሰዎች ካሉ የሌላውን ሀሳብ የሚገፉ ከሆነ የመናገር መብትን የሚገድቡ ከሆነ ሁልጊዜ ችግር መፈጠሩ አይቀርም፡፡ ከዛ ይልቅ ግን መደማመጥ ቢኖር በጠረጴዛ ዙሪያ መነጋገር ቢኖር ስህተት ያለበትም ሰው ስህተቱን እንዲያምን በሀይል በጠብና በቁጣ ሳይሆን በፍቅር በሰላማዊ መንገድ በመነጋገር የማንንም ሰው ሀሳብ ማሸነፍ ይቻላል ብዬ አምናለሁ።
በሀሳብ ላይ መፋጨት በጣም ጠቃሚ ነው። የተሻለና የነጠረ ሀሳብ እንድናመጣም ያደርጋል። ያ ሰው ምንም ቢሆን ሀሳቡንም ማዳመጥ ማክበር ያስፈልጋል። እንደዚህ አይነት ነገሮችን አዳብረን ብንሄድ አሁንም ደግመዋለሁ የማንፈነቅለው ድንጋይ ይኖራል ብዬ አላምንም።
ፍኖተ ነፃነት፡- በመጨረሻ ማስተላለፍ የምትፈልጊው መልዕክት ካለ
ወይዘሮ ሀና፡- ማስተላለፍ የምፈልገው አንደኛ ለፓርቲዬ ማለትም ለሰማያዊ ፓርቲ ነው። ሰማያዊ ፓርቲ በውስጡ ምርጥ ምርጥ ወጣቶች አሉ፡፡ ብዛትም ባይሆን አንድ ሰው ለውጥ ያመጣል ብዬ አስባለሁ። ያንን ሰው ግን በአግባቡ መጠቀም መቻል አለብን ጓደኞቼን በጣም አከብራቸዋለሁ እወዳቸዋለሁ የአስተሳሰብ ልዩነታችንን በጣም አደንቃለሁ፤ በአስተሳሰብ ልዮነታችን ውስጥ ብዙ የተደበቁ ነገሮች ይወጣሉ ብዬ ስለማምን ስላየሁም ማለት ነው። ጥሩ ነገሮች ብቻ ሳይሆን የተደበቁ ስህተቶችም ይወጣሉ። ይህንን በደንብ አይቻለሁ፡፡ ይሄንን ነገር በደንብ አከብራለሁ። በውስጥ የሚሰራውንም ስራ በርቱ ግፉበት እላለሁ፡፡በተለይ በማንም ፓርቲ ውስጥ ያላየነውን የኦዲትና የኢንስፔክሽን ስራ አከብራለሁ ለዚህም በእውነት አድናቆቴን
ማስተላለፍ እፈልጋለሁ። ጥሩ እየሰራ ነው። ፓርቲ ውስጥ ላሉ ችግሮች እስከ ቅጣት ድረስ በመሄድ ለማስተካከል የተሞከረውን ነገር ሳላደንቅ አላልፍም።
በሁለተኛ ደረጃ ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎችንም አከብራለሁ አደንቃለሁ ብዙ ትምህርቶችን እንድማር አድርገውኛል አሁን ለደረስኩበት ብስለት እንድደርስ የእነዚህ ፓርቲዎች መፈጠር ጥሩ አጋጣሚና እድል ፈጥሮልኛል። ሀቀኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የጭቆናውን አመት ለመቀነስና በጭንቅ ላይ ያለችን ሀገር ለመታደግ መፍጠን አለባቸው። አሁን የዕንቅልፍ ጊዜ አይደለም፡፡የምንፈጥንበትን የሩጫ ሂደትና ቀስ የምንልበትን እንደገና ደግሞ አሯሯጭ የምንሆንበትን መለየት መቻል አለብን።
የኢትዮጲያ ህዝብንም የምለው ነገር ይኖራል፡፡ የኢትዮጲያ ህዝብ ሆይ! ተስፋ አትቁረጥ፤ ተስፋ የሚቆርጥ የሞተ ብቻ ነው። በቁም ያለ ሰው የሚፈልገውን ነገር እጁ ውስጥ እስካላስገባ ድረስ ተስፋ አይቆርጥም። እስከ መጨረሻ ህልፈተ ህይወቱ ድረስ ማድረግ ያለበትን በሙላ ያደርጋል። ሰው እንሁን፤ ስብእናችንን እንጠብቅ፤ እርስ በእርሳችን እንከባበር፤ እንተማመን፤ መተማመን አንድነትን ያመጣል፤ አንድ ከሆንን ደግሞ የማንሰራው ነገር አይኖርም። ከዓለም በታች ጭራ የሆነችውን ሀገር ከፍ እናደርጋታለን፡፡ለዚህ ደግሞ እግዚአብሔር ይርዳን ማለት እፈልጋለሁ። አመሰግናለሁ።
- See more at: http://www.andinet.org/archives/14445#sthash.j0S0MAO2.dpuf

No comments:

Post a Comment