በደቡብ ክልል ወላይታ ዞን 30 የሰማያዊ ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች መታሰራቸውን የዞኑ የፓርቲው አስተባባሪዎች ለነገረ ኢትዮጵያ አስታወቁ፡፡
ከዞኑ አስተባባሪዎች መካከል አቶ ታደመ ፍቃዱ እና ፓርቲውን በመወከል ለተወካዮች ምክር ቤት እጩ ተወዳዳሪ የሆኑት መምህር አለማየሁ አዴ እንደገለጹት በወላይታ ዞን ኦፋ ወረዳ ልዩ ስሙ ዋቺጋ አሼ በተባለ ቀበሌ 30 የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች ከትናንት በስቲያ (የካቲት 17/2007 ዓ.ም) ለእስር ተዳርገዋል፡፡
አቶ ታደመ ፍቃዱ እንዳስረዱት አባላቱና ደጋፊዎቹ የታሰሩት ‹‹ሰማያዊ ፓርቲን ለምን ትደግፋላችሁ፣ ለምን አባል ትሆናላችሁ...ፓርቲው እኮ ከምርጫ ታግዷል፣ ህገ-ወጥ ነው›› በሚል ሰበብ ስሙን እንኳን ‹‹ሰማያዊ ብላችሁ አትጥሩ›› ተብለው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ከታሳሪዎች መካከል አብዛኞቹ ወጣቶች መሆናቸውን የሚገልጹት መምህር አለማየሁ በበኩላቸው እስረኞችን እንዳነጋገሯቸው በመጥቀስ፣ ‹‹የምትመርጡት ማንን እንደሆነ እናውቃለን፣ ሌላ ፓርቲ መምረጥ የለባችሁም....ኢህአዴግን ነው መምረጥ የሚኖርባችሁ›› እያሉ እንደሚያስፈራሯቸው አስረድተዋል፡፡
መምህር አለማየሁ አዴ ‹‹አንተ ለምን ልትጠይቃቸው መጣህ›› ተብለው እንግልት እንደደረሰባቸው አስታውሰው፣ እስረኞቹ እስካሁን ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውንም ገልጸዋል፡፡ አባላትና ደጋፊዎቹ ይህ መረጃ እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስ በእስር ላይ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡
No comments:
Post a Comment