Sunday, 1 February 2015

የባቡር መስመሩ ከተማዋን ለሁለት መክፈሉ ነዋሪዎችን ግራ አጋብቷል

የባቡር ሐዲዱን ያለ ጫማ ማቋረጥ ለከፋ አደጋ ያጋልጣል 

የባቡር መስመሩ የዲዛይን ማሻሻያዎች ሊደረጉበት ይገባል -ባለሙያዎች 

የባቡር መስመሩ ከተማዋን  ለሁለት መክፈሉ ነዋሪዎችን ግራ አጋብቷል

      የአዲስ አበባ ከተማ የቀላል ባቡር ፕሮጀክት ሥራ ከሞላ ጎደል በመጠናቀቁ በነገው ዕለት የቅድመ አገልግሎት ሙከራ ሊያካሂድ ነው፡፡ ታላላቅ የመንግስት ባለስልጣናትን፣ ታዋቂ ግለሰቦችንና የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችን በሚያካትተው የቅድመ አገልግሎት ሙከራ ቃሊቲ ጉምሩክ አጠገብ ከሚገኘው የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ዲፓ ግቢ ተነስቶ እስከ መስቀል አደባባይ ባለው የባቡር መስመር ላይ ያደርጋል፡፡ 
በዚህ ዓመት አጋማሽ ላይ ግንባታው ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ወደ ስራ ይገባል የተባለው  የቀላል ባቡር ፕሮጀክት፤ በአንዳንድ አካባቢዎች የግንባታ ሥራው ገና ያልተጠናቀቀ ቢሆንም ግንባታው በተጠናቀቀባቸውና የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ ሥራው ባለቀባቸው አካባቢዎች በተለይም ከቃሊቲ ዲፓ እስከ መስቀል አደባባይ በሚደርሰው መስመር ላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ተለቋል፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል በተለቀቀበት አካባቢ መግባትና የባቡር ሃዲዱን ያለ ጫማ በባዶ እግር ማቋረጥ እጅግ ለከፋ አደጋ ሊያጋልጥ እንደሚችል ተገልጿል፡፡ 
ህብረተሰቡ በባቡር መስመር አጠቃቀሙ ላይ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው ባለመደረጉና ስለ ጉዳዩ በበቂ ሁኔታ በመገናኛ ብዙሃን አለመነገሩ የሚያደርሰውን አደጋ የከፋ እንደሚያደርገውም አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል፡፡ 
አዲሱ የቀላል ባቡር ፕሮጀክት የከተማዋን ውበት የሚያጠፉ፣ ለእግረኛም ሆነ ለተሽከርካሪዎች  የማያመች እንደሆነ የጠቆሙት አስተያየት ሰጪዎች ግንባታው በበቂ ጥናትና ባለሙያ የተሰራ ነው ለማለት እንደሚያስቸግር ተናግረዋል፡፡ የባቡር መስመር ግንባታው ከተማዋን ለሁለት የከፈለ፣ እግረኛውንም ሆነ ተሽከርካሪዎችን ግምት ውስጥ ያላስገባና በከተማዋ ነዋሪዎች ላይ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን የሚያስከትል እንደሆነም ነዋሪዎች ይገልፃሉ፡፡ 
ለሃያ ስድስት ዓመታት ኑሮአቸውን በካናዳ ያደረጉትና በያዝነው ወር መጀመሪያ ላይ ወደ አገራቸው መምጣታቸውን የገለፁልን አቶ አብርሃም ተስፋዬ፤ የቀላል ባቡር ትራንስፖርት በአገራችን መጀመሩ ደስ የሚያሰኝ መሆኑን ጠቁመው በከተማዋ ውስጥ የሚታየውን የትራንስፖርት እጥረት በእጅጉ የሚቀርፍ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ የባቡር መስመሩ ግንባታ የተካሄደበት መንገድ ግን በየትኛውም ዓለም የሌለና በእጅጉ ያስገረማቸው እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ 


“በርካታ አገራትን የማየት ዕድሉን አግኝቻለሁ፡፡ በብዙዎቹ የባቡር ትራንስፖርቶችም ስጠቀም ኖሬአለሁ፡፡ እዚህ አገር እንዳየሁት አይነት የባቡር መስመር ግን አይቼ አላውቅም፡፡ በሌላ ዓለም የባቡር መስመሮች ዝርጋታ አብዛኛውን ጊዜ ከመኪና መስመሩ ጋር እኩል በሆነ ሌቭል የሚሠራ ነው፡፡ ተንጠልጣይ መስመሮች በተወሰኑ ቦታዎች ላይ ሊኖር ይችላል፡፡ ሙሉ በሙሉ ከተማውን ለሁለት ከፍሎ ግንብ አጥር እያደረጉ የባቡር ሃዲዱን በተንጠልጣይ ድልድዮች ላይ የሰሩ አገራት ግን ከኢትዮጵያ በስተቀር አላጋጠመኝም፡፡ ባለሙያ ባለመሆኔ ሙያዊ የሆኑ ነገሮችን ለመናገር ባልችልም ከተማውን ለሁለት ከፍሎ ያጠረው ግንብ ግን የህብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ኑሮ በእጅጉ የሚጐዳ መሆኑን ለመናገር እችላለሁ” ብለዋል፡፡ 
ስማቸው እንዲገለፅ ያልፈለጉና በአንድ አለማቀፋዊ ድርጅት ውስጥ የሚሰሩ የኮሙኒኬሽን ኤክስፐርት ስለዚሁ ጉዳይ በሰጡን አስተያየት፤ የተለያዩ የአውሮፓንና በርካታ የአፍሪካ አገራትን በስራቸው አጋጣሚ የማየት ዕድሉን እንዳገኙ ጠቅሰው፤ በአገራችን የተሰራውን የባቡር ሃዲድ የሚመስል ግን በየትኛውም አገር እንዳላጋጠማቸው ተናግረዋል፡፡ 
“የባቡር መስመሮች እንዲህ እንደ አገራችን ከተማን ለሁለት በሚከፍልና ለእግረኛም ሆነ ለአሽከርካሪዎች አመቺ ባልሆነ መንገድ ተሰርተው አላየሁም፡፡ ባለሙያዎቹ ግንባታውን ሲያካሂዱ እነዚህ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገው ግንባታው የከተማዋን ውበትና የነዋሪውን ምቾት በጠበቀ መልኩ እንዲካሄድ ማድረግ ይገባቸው ነበር ብለዋል፡፡ በመኖሪያ አካባቢያቸው ባለ የህፃናት ማቆያ ውስጥ ህፃን ልጇን የምታውል እናት፤ ልጇን ወደ ማዋያው ለማድረስ ቀደም ሲል ከቤቷ በራፍ ላይ የሚገኘውን አስፋልት ማቋረጥ ብቻ ይጠበቅባት ነበር ያሉት ኤክስፐርቱ፤ በአሁኑ ወቅት ግን  በባቡር መንገዱ ምክንያት ልጇን በሁለት ታክሲዎች ሄዳ በወዲያኛው ማዶ በሚገኘው የህፃናት ማዋያ ውስጥ ለማስገባት መገደዷን በምሳሌነት ጠቅሰው ይህ ከጊዜ፣ ከገንዘብና ከጉልበት አኳያ በነዋሪው ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ያሳያል ብለዋል፡፡ 


ይህን ሃሳብ የጎጃም በረንዳው ነዋሪ አቶ አብዮት አሰፋም ይጋሩታል፡፡ “ለዓመታት በንግድ ቤትነት (በቡና ቤት ንግድ ድርጅትነት) ሳስተዳድረው ለቆየሁት ድርጅቴ እገለገልበት የነበረውና ከቡና ቤቴ ፊት ለፊት ይገኝ የነበረው መጋዘን በባቡር መስመር ዝርጋታው ምክንያት እንኳን በእግር በተሽከርካሪም የማይደረስበት ሩቁ ሆኗል፡፡ ለቡና ቤቱ የሚያስፈልጉ ነገሮችን ከመጋዘኑ ለመውሰድ በመኪና ሀብተጊዮርጊስ ድልድይ ድረስ ሄጄ መዞር ይኖርብኛል፡፡ ይህ ደግሞ በእጅጉ አስቸጋሪና ለስራዬም እንቅፋት የሆነ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡ 
በጦር ኃይሎች ሆስፒታል አካባቢ በስራ ላይ እያለ ያገኘሁት ዋና ሳጅን አበራ ድረስ የተባለ የትራፊክ ፖሊስ ስለጉዳዩ አስተያየት እንዲሰጠኝ ጠይቄው፤ በጦር ኃይሎች አካባቢ የግንባታ ስራው ገና አለመጠናቀቁን ገልፆ ግንባታው ለእግረኛም ሆነ ለአሽከርካሪ አመቺ በሆነ መንገድ የተሰራ አለመሆኑ የትራፊክ ፍሰቱን አስቸጋሪ ሊያደርገው ይችላል የሚል ግምት እንዳለው ጠቁሟል፡፡ በከፍተኛው ፍርድ ቤት ያገኘኋቸው የህግ ባለሙያ በበኩላቸው፤ “ፍርድ ቤቱ በርካታ አቅመ ደካሞች ሁሉ የሚስተናገዱበት መንግስታዊ ተቋም ነው፡፡ ባለጉዳዮች መረጃዎችን ፎቶኮፒ አድርገው እንዲያመጡ ሲነገራቸው የት ሄደው ማድረግ እንደሚችሉ ይጠይቁናል፡፡ የት እንበላቸው፡፡ ከተማዋ እንደሆነ በበርሊን ግንብ ታጥራለች፤ አንዲት ወረቀት ኮፒ ለማድረግ ታክሲ ይዘው ጦር ኃይሎች ድረስ መሄድ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ግንቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ለፍርድ ቤቱ ሰራተኞችና ለባለጉዳዮች ምግብ ያቀርቡ የነበሩ ምግብ ቤቶችንም ጭምር ከጨዋታ ውጪ ያደረገ በመሆኑ ጉዳቱ ለባለጉዳይ፣ ለሰራተኛውና ለሆቴል ባለቤቶችም ተርፏል” ብለዋል፡፡ 
ከጦር ኃይሎች መስቀል አደባባይ፣ ዑራኤል፣ ሃያ ሁለት መገናኛ፣ ጉርድ ሾላ፣ ሲኤምሲና ሃያት ድረስ፣ ከጊዮርጊስ አውቶብስ ተራ ሰባተኛ፣ አብነትና ጦር ኃይሎች ድረስ የሚዘልቀው የቀላል ባቡር መስመሩ፤ በየሰባት መቶ ሜትር ርቀት የእግረኛና የተሽከርካሪ ማቋረጫ እንደሚኖረው ተገልፆ የነበረ ቢሆንም አሁን ባለው ሁኔታ የእግረኛም ሆነ የተሽከርካሪ ማቋረጫን ለማግኘት ከሁለት ኪሎ ሜትሮች በላይ መጓዝ ያስፈልጋል፡፡ የባቡር መስመር ግንባታውን አስመልክቶ ሙያዊ አስተያየት እንዲሰጡን የጠየቅናቸው አርክቴክት ሚካኤል ሽፈራው፤ የባቡር መስመሮች በበርካታ የዓለም አገራት ሲሰሩ የመሬቱን አቀማመጥ ተከትለው መሬት ለመሬት በመሄድ፣ ከአስፋልት መስመሮች ጋር እንዲሰሩ የሚደረጉ መሆኑን ጠቁመው፤ በአገራችን የተሰራውን ዓይነት ግንባታ ለመስራት የመሬቱ  ወጣ ገባነት የሚያስገድድ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ 
“የአዲስ አበባ የመሬት አቀማመጥ ወጣ ገባነት ያለበት በመሆኑ፣ ይህንን ለመጠበቅ ሲባል የባቡር ሃዲዱን ከመሬት በላይ ማንጠልጠል ግድ ሊሆን ይችላል፡፡ ስሎፕ በባቡር መንገድ ግንባታ ላይ እጅግ አስፈላጊና ወሳኝ ነው፤ ሆኖም ሌሎች አርክቴክታል መንገዶችን ተጠቅሞ፣ መንገዱ ለባቡሩም ለእግረኛውም ሆነ ለተሽከርካሪ አመቺ ሊሆን የሚችልበትን መንገድ መጠቀም ይቻላል ብለዋል፡፡ የኤሌክትሪክ ባቡሮች በባህርያቸው ድምፅ አልባዎች ናቸው ያሉት አርክቴክቱ፤ በድንገት ሊደርሱና በሃዲዱ ላይ በሚያቋርጡ ሰዎች ላይ አደጋ ሊያደርሱ ይችላሉ፡፡ በዚህም ምክንያት መንገዶቹ ታጥረው እግረኞች እንዳይገቡበት መከልከሉ ተገቢ ቢሆንም የእግረኞችና የተሽከርካሪዎች ማቋረጫ መንገድ ያስፈልጋቸው ነበር ብለዋል፡፡ “የባቡር መስመሩ የዲዛይን ችግሮች አሉበት፤ የዲዛይን ችግሩ ደግሞ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ማስከተሉ አይቀሬ ነው፤ እንደቀለበት መንገድ ማለት ነው፡፡ የዲዛይን ችግሮቹ ግን ዘለዓለማዊ ናቸው ማለት አይደለም፡፡ ሊሻሻሉና ሊቀየሩ የሚችሉ ናቸው፡፡” ያሉት አርክቴክቱ፤ በሂደት የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎቱ እየተሰጠም ማሻሻያዎች ሊደረጉ የሚችሉበት መንገድ ይኖራል ብለዋል፡፡ በባቡር መስር ዝርጋታው ላይ የመንገድ መብራቶች ጉዳይ እየተዘነጋ ያለ ይመስላል ያሉት ባለሙያው፤ የመንገድ መብራት የሚመስሉ ነገሮች በመስመሩ ላይ አለመታየታቸው ያልተለመደ ነገር ነው ብለዋል፡፡ በተንጠልጣይ ድልድዮቹ ስር ያሉ ክፍት ቦታዎች ለእግረኛም ሆነ ለተሽከርካሪ የማይሆኑ መሆናቸውን የጠቆሙት አርክቴክቱ፤ በሌላው ዓለም እነዚህ ቦታዎች ለመዝናኛነት የሚያገለግሉ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡ “እነኚህን ቦታዎች በኃላፊነት ተረክቦ ለሚያስተዳድር አካል በመስጠት መዝናኛዎች፣ ሰዎች አረፍ ብለው ከተማውን እያዩ የሚጫወቱባቸው ቦታዎች ማድረግ እንደሚቻል፣ ይህ ካልሆነ ግን ቦታዎቹ የቆሻሻ መጣያና የወንጀል ፈፃሚዎች መሸሸጊያ በመሆን ለነዋሪው ከፍተኛ ስጋት ሊሆኑ ይችላሉ” ባይ ናቸው፡፡ 
በነገው ዕለት የቅድመ አገልግሎት ሙከራ የሚያደርገው የአዲስ አበባ ከተማ የቀላል ባቡር ፕሮጀክት፤ በተለያዩ አካባቢዎች በተለይም በጦር ኃይሎች፣ በአውቶብስ ተራ፣ በሰባተኛ፣ አብነት አካባቢ ግንባታው ያልተጠናቀቀ ሲሆነ ለአቅመ ደካሞችና ለህሙማን ይሰራል የተባለው የመወጣጫ (ሊፍት) ግንባታ ግን በየትኛውም መስመር አልተጀመረም፡፡ በእነዚህ ጉዳዮች ዙሪያ ማብራሪያ የጠየቅናቸው የኮርፖሬሽኑ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደረጀ ተፈራ፤ ለባቡሩ የቅድመ አገልግሎት ሙከራ በስራ መወጠራቸውን ምላሽ ሊሰጡን እንደማይችሉ ገልፀውልናል፡፡ 
http://www.addisadmassnews.com/index.php?

No comments:

Post a Comment