Thursday, 26 February 2015

አብዛኞቹ የመንግሰት ጋዜጠኞች የኢህአዴግ አባላት መሆናቸውን መረጃዎች አመለከቱ



የካቲት ፲፱(አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በመንግስት የመገናኛ ብዙሃን ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ ጋዜጠኞች አብዛኞቹ የኢህአዴግ አባላት መሆናቸውን ኢሳት በደረሰው የአባላት ስም ዝርዝርና የስራ ድርሻ ሰነድ ለማረጋገጥ ችሎአል።

በቀድሞው ኢቲቪ በአዲሱ አጠራሩ ኢቢሲ እና በኢትዮጵያ ሬዲዮ  ስር የሚሰሩ ዳይሬክተሮች፣ የዜና አዘጋጆች፣ የወቅታዊ ዘገባ አቀናባሪዎች፣ የስፖርት ጋዜጠኞች ፣ የካሜራ ባለሙያዎች፣ ቴክኒሻኖችና የተለያዩ የድጋፍ ሰራተኞች የህወሃት፣ የብአዴን፣ ኢህዴድ ወይም የደህዴግ አባላት መሆናቸው በሰነዱ ላይ በዝርዝር ተቀምቷል። ጋዜጠኞቹ የኢህአዴግን ፖሊስ ለህዝብ ከማስተዋወቅ ጋር በተያያዘ በየጊዜው በተደራጁበት ህዋስ ስር ግምገማ እንደሚደረግባቸውና ከኤ እስከ ዲ የሚደርስ ውጤት እንደሚሰጣቸው ከሰነዱ ለመራዳት ይቻላል።
የመንግስት የመገናኛ ብዙሃን በህዝብ ንብረት የሚተዳዳሩ ቢሆንም፣ የአንድ ፓርቲ አገልጋይ ለመሆናቸው ከዚህ በላይ ማስረጃ እንደሌለ አስተያየታቸውን የሰጡን አንድ የሚዲያ ባለሙያ ተናግረዋል።
ጋዜጠኞች የኢህአዴግ አባላት የሚሆኑት ጥቅማቸውን አስበው እንጅ በድርጅቱ አምነውበት ላይሆን እንደሚችል፣ ከሚሰሩት ስራ መናገር ይቻላል የሚሉት አስተያየት ሰጪው፣ አብዛኞቹ አጋጣሚውን ሲያገኙ ወደ ውጭ ወጥተው መቅረታቸው አባልነቱ ለጥቅም መሆኑን ያረጋግጣል ብለዋል፡፡ በሌላ ዜና ደግሞ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ህዳሴ የሚባለውን የኢህአዴግ አዲስ ልሳን ስፖንሰር እንዲያደርጉ እየታዘዙ ነው።
ኢሳት ከአዲስ አበባ ኢህአዴግ ኮሚቴ ጽ/ቤት በአስተዳደርና ፋይናንስ መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ ቅድስት ወ/ጊዮርጊስ ተፈርሞ በወጣ ደብዳቤ ላይ ለማረጋገጥ እንደቻለው፣  በሁለት ሳምንት አንድ ጊዜ ታትሞ የሚወጣው ህዳሴ የተሰኘው የኢህአዴግ የፖለቲካ ልሳን ጋዜጣ በስፖንሰር ሺፕ ሰበብ በመንግስት መ/ቤቶች ባጀት ወጪ እንዲታተም እየተደረገ ነው።
ከጽ/ቤቱ የካቲት 5 ቀን 2007 ዓ.ም ከ5 በላይ ለሚሆኑ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር መ/ቤቶች በአድራሻቸው ተጽፎ የተሰራጨው ደብዳቤ እንደሚያመለክተው እያንዳንዱ መ/ቤት ስፖንሰር ለማድረግ የተስማማበትን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አንድነት ቅርንጫፍ በአዲስ አበባ ኢህአዴግ ኮሚቴ ጽ/ቤት ስም ወደሚታወቀው ባንክ አካውንት ገቢ እንዲያደርጉ የሚያሳስብ ሲሆን ለአንድ ጊዜ ማሳተሚያ እስከ 300,000 ብር እንዲከፍሉ ታዘወዋል።

No comments:

Post a Comment