አገራችን ኢትዮጵያ በሕዝብ ብዛት ከአፍሪቃ ሁለተኛ ስትሆን በተባበሩት መንግሥታት መመዘኛ “ወጣት” ተብሎ በሚጠራው የኅብረተሰብ ክፍል ብዛት ግን አንደኛ ነች። እርግጥ ነው ወጣነት በእድሜ ብቻ የሚገለጽ የኅብረተሰብ ክፍል አይደለም። የሚከተለው የወጣት ትርጉም ሰፋ ያለ ተቀባይነት ያለው ይመስለኛል።
ወጣት፣ በማኅበረሰቡ አንኳር ጉዳዮች ላይ እየወሰነ ባለው “አዋቂ” ተብሎ በሚጠራው የኅብረሰተሰብ ክፍል እና ማኅበራዊ ፋይዳ ያላቸውን ውሳኔዎች ለመስጠት ገና ባልተዘጋጀው ሕፃን መካከል ያለ የኅበረተሰብ ክፍል ነው።
በዚህ ትርጓሜ መሠረት ወጣትነት የማኅበራዊ ግኑኝነት መገለጫ ጽንሰ ሀሳብ ነው። ይህ ማኅበራዊ ግኑኝነት ወደ እድሜ እንመዝረው ስንል ችግር ውስጥ እንገባለን፤ ምክንያቱም ወጣቱ ወደ አዋቂነት የሚሸጋገርበት ጊዜ እንደየአገሩ ባህሉና እንደ እድገቱ ይለያያል። በዚህም ምክንያት ነው የወጣትነት የህግ ትርጓሜዎች በየአገሩና ባህል የተለያዩ የሆኑት። ለምሳሌ፣ የተባበሩት መንግሥታት ወጣት ማለት “እድሜው 15 እስከ 24 ዓመታት ድረስ ያለው ሰው ነው” ሲል ይተረጉማል፤ ይሁን እንጂ የራሱ አካል የሆነው UN Habitat “ወጣት ማለት እድሜው 15-32 ዓመት ያለው ሰው ነው” ይላል። በአገሮች ትርጓሜ መካከል ያለው ልዩነት ደግሞ በጣም የተዘበራረቀ ነው። ዩጋንዳ ውስጥ እድሜው 12-30 የሆነ ዜጋ ወጣት ሲሰኝ ጎረቤትዋ ኬንያ ውስጥ 18-35 ነው። ስለዚህም አንድ የ16 ዓመት ወጣት ዩጋንዳዊ ድንበር ተሻግሮ ኬኒያ ሲገባ ሕፃን ይሆናል፤ አንድ የ 32 ዓመት ኬንያዊ ወጣት ዩጋንዳ ሲሻገር ጎልማሳ ይሆናል። ከአፍሪቃ ዝብርቅርቅ የወጣት ትርጓሜዎች ለአብነት ጥቂቶቹን ላንሳ: ሞውሪሸስ 14-29፣ ደቡብ አፍሪቃ 14-29፣ ናይጄሪያ 18-35፣ ጂቡቲ 16-30፣ ኬኒያ 18-35።
በ2004 ዓም የወጣው የኢትዮጵያ መንግሥት የወጣቶች ፓሊሲ ከ15 -29 ዓመታት ውስጥ የሚገኝን ኢትዮጵያዊን ዜጋን ወጣት ብሎ ይተረጉመዋል። በወጉ የሚያስተናግደው አላገኘም እንጂ ይህ ፓሊሲ በወጣበት ወቅት የኢትዮጵያ የወጣት ትርጓሜ እንደ ኬኒያና ናይጄሪያ 18- 35 መሆን ይገባዋል የሚል ሀሳብ ቀርቦ ነበር። የወጣቱ ከፓለቲካና ማኅበራዊ ውሳኔዎች መገለል መብዛትን በማጤን የላይኛው ጣራ እስከ 39 ከፍ ማለት አለበት የሚል ክርክርም ነበር። በበኩሌ ሥራአጥነትና ዘረኛ የህወሓት ፓሊሲ ያስፋፋው መድልዎና መገለል የወጣት የእድሜ ማዕቀፍ እንዲሰፋ አድርጓል ብዬ አምናለሁ። አርባ ዓመት አልፏቸው ከወላጆቻቸው ጥገኝነት ያልወጡ “ወጣቶች” ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ ነው። እኔ በዚህ አጭር ጽሁፍ ውስጥ ስለወጣት ስናገር እድሜው በ 18 እና 39 ዓመታት መካከል ያለውን ዜጋ እያሰብኩ ነው።
የዘመናችን ወጣት
የዘመናችንን ወጣት የሚተቹ በርካታ ጽሁፎች የወጡ ቢሆንም እኔ ብዙዎቹ ትችቶች አግባብ መስለው አይታዩኝም። በአንድ በኩል ወጣቱ የማኅበረሰቡ አካል በመሆኑ በወጣቱ ውስጥ የሚታየው ክፉም ሆነ ደግ ከማኅበረሰቡ የወረሰው ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ነገሮች ሁሉ ወጣቱ ላይ ይጎላሉ። በሌላው ዓለም ያለው የመብቶች መከበር እና የኑሮ ሁኔታ ከራሱ እውነታ ጋር ሲያመዛዝን የአንዳንዱ ወጣት ልብ በረሀ ለማቋረጥ፣ ባህር ለመሻገር እንዲደፍር ያደርገዋል፤ የአንዳንዱ ወጣት ልብ ደግሞ የማዕከላዊ እስር ቤትና በውስጡ ያለውን ቶርቸር እንዳይፈራ ያፀናዋል። የዘመናችን ወጣት ሊወደስባቸው የሚገቡ በርካታ ነጥቦች ቢኖሩም የሚከተሉት ግንባር ቀደም ናቸው ብዬ አምናለሁ።
- የዘመናችን ወጣት ማሰብ ተከልክሎ ያደገ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ማሰብና መመራመርን የሚያበረታቱ ሁኔታዎች የሉም ማለት ሁኔታዉን አቅሎ መመልከት ይሆናል። ምርምር የሚጀምረው ከመጠራጠር ነው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ሥርዓቱ ትክክል ናቸው ያላቸውን ነገሮች መጠራጠር ወንጀል ነው። ኢትዮጵያዊ ወጣት “የምነግርህን ሳትጠራጠር አምነህ ተቀበል” ተብሎ ያደገ ነው። በዛሬቷ ኢትዮጵያ ውስጥ መረጃዎችን ማፈላለግ፣ ማንበብ፣ ማዳመጥ፣ ሀሳብ መለዋወጥ ወንጀል ነው። ወሳኝ በሆነ የፓለቲካና የፍልስፍና ጉዳዮች ላይ አቋም ይዞ መከራከር አይቻልም። በከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም የሚሰጠው ትምህርት እንደ ርዕዮተ ዓለም ቅስቀሳ ሁሉ “ያለቀለት እውነት” እንጂ ተማሪዎች በራሳቸው መንገድ ሊያረጋግጡት የሚገባ ጥሬ ሀሳብ ተደርጎ አይደለም። እንዲህ ዓይነቱ የአዕምሮ ውርጅብኝ የወረደበት ትውልድ ሆኖ እያለ ፈጽሞ አለመደንዘዙ፤ ዛሬም በየእውቀት ዘርፉ ጎበዞች የሆኑ ወጣቶች መኖራቸው ድንቅ ነው። የዛሬ ወጣት አስተማሪም ትምህርት ቤትም ሳይኖረው – ያለ አስተማሪ እና ያለ ትምህርት ቤት – አሁን እደረሰበት ደረጃ ላይ መድረሱ ሊያስመሰግነው ይገባል።
- ከሰማንያ በመቶ በላይ የሆነው ወጣት ከኢህአዴግ ሌላ መንግሥት ኢትዮጵያ ውስጥ ኖሮ አያውቅም። እድሜውን በሙሉ ኢህአዴግ እና መንግሥት አንድ ሆነው ነው ያደገው። ስለአገራዊ አንድነት ከሰማው ስለ “ብሔር”፣ “ብሔረሰቦች” የሰማው በእጅጉ ይበልጣል። የአሁኑ ወጣት የኢትዮጵያ ታሪክ ተብሎ እየተነገረው ያለው የቂምና የበቀል ታሪኮችን ነው። አንድ የሃያ አምስት ዓመት ወጣት ዛሬ ያሉት ክልሎች ከጥንት ጀምሮ የነበሩ ቢመስሉት እንኳን ልንፈርድበት አይገባም። ከሬድዮና ከጋዜጣ ብቻ ሳይሆን ከወላጆቹ ጭምር ሲሰማው የኖረው ይህንኑ ነው። ዘረኝነት መንግሥታዊ ፓሊሲ በሆነበት፤ “አዋቂ” የሚባሉት ታላላቆቹ ራሳቸው ዘረኞች አሊያም በፍርሀት ተሸብበው ዝምተኞች በሆኑት አገር አድጎ ኢትዮጵያዊነትን ፈጽሞ አለመርሳቱ ይህንን ትውልድ በእጅጉ ያስመሰግነዋል።
- የዛሬ ወጣቶች በተለምዶ “ያ ትውልድ” የሚባለው ትውልድ ልጆች ናቸው። “ያ ትውልድ” ደግሞ ብዙ አልሞ የትም ያልደረሰ፤ ሊያጠፋው ከተነሳው አውሬ የባሰ ጭራቅ – ህወሓትን – ያነገሰ ነው። የዛሬ ወጣት ወላጆች በወጣትነታቸው የነቃ የፓለቲካ ተሳትፎ የነበራቸው ሊሆን ይችላል፤ ምናልባትም ማርክሲስትና ሌኒኒስቶች ሆነው ለላብ አደራዊ ወይም ወዛደራዊ ዓለም ዓቀፋዊነት ሲታገሉ ኖረው ይሆናል፤ አሊያም ነፃ አውጭዎች የነበሩ ሊሆኑ ይችላሉ። እርግጥ እነሱ በጽናትና ቆራጥነት ታግለው ሊሆን ይችላል። ያንን ስሜትና ጽናት ግን ወደ ወጣቱ አላስተላለፉትም። እንዲያውም “እኛም በጊዜዓችን ሞክረን አልቻልነውም” እያሉ የአዲሱን ትውልድ ሀሞት የሚያፈሱ ሆነዋል። እንደ “ያ ትውልድ” ሁሉ ዛሬም እስርና ግርፋትን የማይፈሩ ወጣቶች መኖራቸው የሚያስመሰግናቸው ነው። እንደ “ያ ትውልድ” አየር ላይ ለተንሳፈፈ ርዕዮተ ዓለም ሳይሆን ለራሳቸውና ለሀገራቸው ክብርና ነፃነት ሕይወታቸውን ለመስጠት የቆረጡ ወጣት ወንዶችና ሴቶችን ስናይ ተስፋችን ይለመልማል። እርግጥ ነው እንዲህ ዓይነት ወጣቶች ቁጥራቸው ጥቂት ነው፤ የታሪክን ቦይ የሚቀዱት ግን እነዚህ ጥቂቶች መሆናቸው ጥርጥር የለውም።
- ስለዛሬው ወጣት ምግባረ ብሉሽነት ብዙ ይወራል። እኔ ይህ ትክክል አይመስለኝም። የሥራ አጥ ብዛት እንደ አሁን የተስፋፋበት ጊዜ የለም። ዘጠና በመቶ ያህሉ ሥራ አጥ በወጣትነት የእድሜ ክልል ያለ ነው። “ትምህርቱን ጨርሶ” የሙሉ ጊዜ ሥራ አጥ ሆኖ የተቀመጠ ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ የከተማ ወጣት አለ። ሥራ አጥነት ከኢኮኖሚ ችግርነቱ የባሰው ማኅበራዊ ችግርነቱ ነው። ሥራ አጥ ሆኖ ኃላፊነት የሚሰማው እና በማኅበረሰቡ የሚደመጥ ዜጋ መሆን ከባድ ነው። ሥራ አጡን ወጣት ወደ አጓጉል ልማዶች የሚስቡት ክሮች ብዙ ናቸው። ኢትዮጵያ ውስጥ ስናይ ግን ሁኔታው በሚወራው መጠን ተስፋ አስቆራጭ አይደለም። ዛሬም ሥጋ ቤቶች በሽቦ አጥር አልታጠሩም፤ ወርቅ ቤቶች አርቲፊሻል ሳይሆን እውነተኛ ወርቅ በመስታወት ውስጥ ዘርግተው ይሸጣሉ፤ ብዙ ምግብ ቤቶች ዋጋ ሳይቀበሉ ያስተናግዳሉ። እነዚህ ነገሮች ስናስተውል የኢትዮጵያዊውን ወጣት ሥነምግባር ማድነቅ ይገባናል ብዬ አስባለሁ።
- በከተሞች ተቀጥሮ የመሥራት እድል እየጠበበ ከመምጣቱ በላይ ያች ጠባብ እድልም በህወሓትና አጫፋሪዎቹ መዳፍ ውስጥ ናት። ህወሓት እና አጋፋሪዎቹ እያንዳንዱን የሥራ እድል “ሰው መግዣቸው” ሆኗል። በመንግሥት ሥራ ለመቀጠር ከትምህርትና ሙያ ይበልጥ የኢህአዴግ አባልነት ወሳኝ መሆኑ አገር ያወቀው ሀቅ ነው። ወጣቶች የራሳቸውን የግል ሥራ የሚፈጥሩበት ሁኔታም የለም። ነፃ አስተሳሰብ፣ ነፃ የንግድና የፍትህ ተቋማት በሌሉበት ስለ “ኢንተርፕሪነርሺፕ“ መስበክ ባዶ ዲስኩር ነው። በአንድ በኩል የወጣቱ የፈጠራ ተነሳሽነት እንዲላሽቅ ተደርጓል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ከመንግሥት ሥራ ያልተናነሰ የወያኔ ጥቃት በግሉ የሥራ ዘርፍ ውስጥም አለ። አፍቃሪ ወያኔ ያልሆኑ ነፃ ዜጎች የግል ቢዝነስ ቢጀምሩ እንኳ ሳንካዎች ይበዙባቸዋል፤ ሳንካዎችን ተቋቁመው አንገታቸውን ብቅ ካደረጉ በግብር እና በቫት ይኮረኩሟቸዋል፤ አቤቱታ ማሰሚያ ቦታ የለም።
በገጠር ያለውም ሀቅ ተመሳሳይ ነው። የህወሓት የመሬት ፓሊሲ ግንባር ቀደም ሰለባ የሆነው የገጠር ወጣት ነው። መሬት ተሸንሽኖ አልቋል፤ ዛሬ ግማሽ ሄክታር መሬት ያለው ቤተሰብ ሀብታም ነው። በብዙ የአገራችን ክፍሎች ወጣት ገበሬዎች ከሩብ ሄክታር ያነሰ መሬት ይዘው ነው የራሳቸውን ትዳር የሚጀምሩት። ሩብ ሄክታር ለጓሮ አትክልት መትከያነት ቢሆን እንጂ ለሰብል አይበቃም። በአንፃሩ ደግሞ ግብርናንና ገበሬን የሚጠሉ “ኢንቬስተሮች” የሚይዙት መሬት የሚለካው በ10 ሺዎች ሄክታር ነው። ድሮ የማይታወቀው የገበሬ ሩቅ አገር መሰደድ አንዱ ምክንያት ይህ ነው። በገጠር ዘርን መሠረት ያደረጉ ግጭቶች ከሚያባብሱ ነገሮች አንዱ ይህ የመሬት እጥረት ነው።
በገጠርም በከተማውም ያለው ሀቅ ይህ ሆኖ እያለ ዛሬም አገሩን ከልቡ የሚወድ ወጣት መኖሩ የሚገርም ነው።
- አብዛኛው አዲስ ስደተኛ፣ ወጣት ነው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የኢትዮጵያ ስደተኛ ዓይነትና ስብጥር (demography) እና የስደተኛው መዳረሻ አገሮች ተቀይረዋል። ወደ ደቡብ አፍሪቃ፣ ሱዳን እና አረብ አገሮች ያለው ስደት “ፍልሰት” በሚባል መጠን ነው። ወጣት ወንዶችና ልጃገረዶች የማይታዩባቸው የገጠር መንደሮች ሞልተዋል፤ ወደ አረብ አገሮች አሊያም ደቡብ አፍሪቃና ሱዳን ነጉደዋል። አሜሪካ፣ አውሮፓና አውስትራሊያ የሚደርሰው ከስደተኛው ብዛት አንፃር ከቁጥር የማይገባው በጣም ትንሹ ነው። ታድያ በፓለቲካውም በኢኮኖሚውም ተደብድቦ፣ ተገፍቶ የወጣው ስደተኛ ወጣት ለአገሩ፣ ሕዝቡ፣ ባህሉና ታሪኩ ያለው ፍቅር የሚደንቅ ነው።
- የኢትዮጵያ ፓለቲካና ኢኮኖሚ አንድ መለያ ባህርይ “እጦት” deprivation ነው። የፍትህ እጦት፣ የነፃነት እጦት፣ የመረጃ እጦት፣ የሚዛናዊ ትምህርት እጦት፣ የመሠረታዊ የጤና አገልግሎት እጦት፣ የመብራት ኃይል እጦት፣ የማገዶ እጦት፣ የመኖሪያ ቤት እጦት፣ የሥራ እድል እጦት፣ የኔት ዎርክ እጦት፣ የታክሲ እጦት፣ የእለት ጉርስ እጦት …. እጦት … እጦት … እጦት … ። ህወሓት እጦቶችን ተጠቅሞ ነው ወጣቱን እመዳፉ ውስጥ ለማስገባት እየጣረ ያለው። (ህወሓት እና እጦት የረዥም ጊዜ ወዳጅነት እንዳላቸው የታወቀ ነው፤ በድርቅ ለተጎዳው ሕዝብ በመጣ እርዳታ ራሱን ያደራጀ እጅግ ክፉና መሠሪ ድርጅት ነው) በእጦቶች የተጎዳ ሕዝብ ለእጦቶቹ ደረጃ ያወጣላቸዋል። መሠረታዊ እጦቶችን (ለምሳሌ የእለት ጉርስ፣ ኮንዶሚኒየም) ለማሟላት “ትላልቅ” እጦቶች (ለምሳሌ የፍትህና የመብት እጦቶችን) ይታገሳል።
አገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ግን እጦቶችን በመሣሪያነት የሚጠቀም ፋሽስታዊ አገዛዝ ውስጥ አድገው እያለ ስለፍትህ፣ ስለነፃነት፣ ስለእኩልነት፣ ስለመብቶች የሚያሰላስሉ፣ የሚጽፉ፣ የሚታገሉ ብሩህ አዕምሮ ያላቸው ወጣቶች ያሉን መሆኑ መታደል ነው። ዛሬ ይህንን ማስታወሻ በምጽፍበት ወቅት በቃሊቲ፣ በቂሊንጦ፣ በዝዋይ እና በማይታወቁ በርካታ እስር ቤቶች ውስጥ በርካታ ወጣቶች ለፍትህ፣ ለሰብዓዊ ክብርና ነፃነት ዋጋ እየከፈሉ ነው። እነሱን የመሰሉ በርካታ ወጣቶች ከእስር ቤቶች አጥሮች ውጭ በከተሞችም በገጠሮችም መኖራቸውን ሳስብ ደግሞ በዚህ ትውልድ ወጣቶች እኮራለሁ። ከዚህ አልፎ በእጦቶች መታሰር መሯቸው ወደ ተራራዎች ያቀኑ ወጣቶች መኖራቸው እና ቁጥራቸውም እያደር እየበዛ መሆኑ ስሰማ በዚህ ትውልድ ላይ መቅናት ያምረኛል።
- ኅብረት መፍጠር ቀላል የሚሆነው በቃላት ነው። “ተባበሩ” ብሎ መስበክ እና “እንዴት መተባበር አቃታችሁ” ብሎ መዝለፍ በጨለማ ሌሊት ወደ ሰማይ አንጋጦ ከዋክብትን የመቁጠር ያህል አዝናኝ ነው። መተባበር የትም አገር ቢሆን ከባድ ነው። እኛ አገር ደግሞ ይበልጥ ከባድ የሚያደርጉት ሁኔታዎች አሉ። (በነገራችን ላይ ህወሓት፣ ኢህአዴግ ላይ እንዳደረገው ዓይነት የአፈና ጥርነፋን “ኅብረት” ብለው የሚጠሩ ሰዎች አሉ) የመተባበር ችግራችን ዛሬ የተጀመረ አይደለም። መተባበር ያስቸገረን በፓለቲካው መስክ ብቻም አይደለም። ሌላው ቀርቶ ስለ ኅብረት ሲሰብኩ ውለው ሲሰብኩ የሚያድሩ የሃይማኖት አባቶችም እርስ በርሳቸው መተባበር አልቻሉም።
የመተባበር ችግር ለህወሓት ምቹ ሁኔታ ፈጥሮለታል፤ ልዩነቶችን እያራገበ፤ በኢትዮጵያ ሕዝብ እየተሳለቀ ተዝናንቶ ይገዛል። ዉጣ ውረድ የበዛበት አስቸጋሪ መንገድ ቢሆንም እንኳን በዚህም ረገድ የተስፋ ጭላንጭል እየታየኝ ነው። ከሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ወጣቶች ወደ ፓለቲካ አመራር እየመጡ ነው። ከሰሜን፣ ከደቡብ፣ ከምሥራቅ፣ ከምዕራብና ከመሀል አገር የተወጣጡ ወጣቶች ለጋራ ኢትዮጵያ ሲሰለፉ፤ ያንንም ትግል በጋራ ሲመሩ ማየት የሚያኮራ ነው። የተለያዩ እምነቶች ተከታዮች የሆኑ ወጣቶች በፓለቲካ ድርጅት አመራርነት ተመርጠው በጋራ ሲሰሩ ማየት ተስፋ ሰጪ ነው። ለአንድ የጋራ ዓላማ ጉልበትን በማስተባበር ረገድ ብዙ ይቀረናል፤ ተግዳሮቶቹ በርካታ ናቸው፤ ያም ሆኖ ግን በወጣቱ በኩል እየታየው ያለው መናበብ ተስፋ ሰጭ ነው። የዛሬ ወጣት ውብ ኢትዮጵያን ከምናቦቻችን አውጥቶ በእውን ሊፈጥራት የታደለ ትውልድ ነው፤ ይህን ለማድረግ ደግሞ ብቃት አለው ብዬ አምናለሁ።
ቁጭት
ከላይ የዘረዘርኳቸው ስምንት መልካም ነገሮችን አዳብረናቸው፤ የወጣቱን ጉልበትና ተነሳሽነት በሚገባ ተጠቅመንበት ቢሆን ኖሮ እስካሁን የት በደረስን?
እነዚህን ስምንት አበረታች ነገሮች በሚገባ አሳድገናቸው ቢሆን ኖሮ:
- ሰዎች ለመናገር፣ ለማንበብ፣ ለመስማት፣ ለመፃፍ የሚሸማቀቁበት አገር ዜጎች ባልሆንም ነበር፣
- በራስ መተማመንን ያዳበሩ በርካታ ድንቅ የተፈጥሮና የማኅበራዊ ሳይንስ ባለሙያዎች፣ የፈጠራ ሰዎች በሕዝብ የተወደዱ ወጣት መሪዎች፣ በጥረታቸው የተሳካላቸው የቢዝነስ ሰዎች፣ … ወዘተ በኖሩን ነበር፣
- ትምህርት፣ አዕምሮን ማደንቆሪያ መሆኑ ቀርቶ የምርምን አድማስን ማስፊያ፣ አዕምሮን ማበልፀጊያ እና ሙያ መቅሰሚያ ይሆን ነበር፣
- ኢትዮጵያችን እንደአሁን የተማረው የሚሸሻት ሳይሆን የወጣው የሚመለስባት አገር ትሆን ነበር፣
- የኢትዮጵያ ሕዝብ የህወሓት መጫወቻ፤ የአገሪቱ ሀብት ደግሞ የሹማምንቱ መድለቢያ ባልሆነ ነበር፣
- የዘር ፓለቲካ መንግሥታዊ ፓሊሲ ሆኖ እርስ በርሳችን መግባባት እስከሚያቅተን ድረስ ለራሳችን ወንድሞችና እህቶች ባዕዶች ባልሆንም ነበር፣
- ገበሬው ከማሳው ባልተፈናቀለ፤ በድህነት፣ በስደተኛና በእስረኛ ብዛት ብዛት ዓለምን መምራታችን ይቀርልን ነበር፣
- በሀገራችንም በውጭ አገራትም ወጣቶቻችን አንገታቸውን ቀና፣ ደረታቸውን ነፋ አድርገው በሄዱ ነበር፤ እህቶቻችን በአረብ ጎረምሶች ከሚደርስባቸው ስቃይ በተገላገሉ ነበር፣
- አገሪቱን የሚመሯት እኛው ፈልገንና ፈቅደን የመረጥናቸው፤ ካልተስማሙን የምንሽራቸው፤ የምናከብራቸው እንጂ የማንፈራቸው፤ በፓሊስና በወታደር የማያስደበድቡን “የኛ” የምንላቸው ሰዎች በሆኑ ነበር፣
- ሌሎችም ብዙ መልካም ነገሮችን ባየን ነበር፣
ምልከታ
ባለፈው መቆጨት መልካም የሚሆነው ለወደፊቱ ምልከታ ሲያገለግል ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ አዎንታዊ ለውጥ በፍጥነት እንዲመጣ የወጣቱ ተሳትፎ አሁን ካለበት በጣም መጨመር ይኖርበታል። ይህን ማድረግ ደግሞ ይቻላል፤ ወጣቱ፣ አቅም፣ ችሎታውና ተነሳሽነቱ አለው። ወጣቱ በራሱና በአገሩ የወደፊት እጣ ፈንታ ላይ አዎንታዊ ሚና እንዲኖረው በራሱ ላይ ያለውን መተማመን ማዳበር ይኖርበታል፤ አፈናን በሚሰብር መልኩ ራሱን ማደራጀት ይጠበቅበታል። እንዲህ በተጠና መንገድ የሚንቀሳቀስ ከሆነ ትናንንሽ የሚመስሉ ጥረቶች ተብላልተው ትልቅ ሕዝባዊ ማዕበልን መፍጠር ይችላሉ። ይህንን ትግል አሁን በኢትዮጵያ ፓለቲካ ውስጥ በተለያዩ ስልቶች በሚንቀሳቀሱ የፓለቲካ ድርጅቶች ውስጥ በአመራር ጭምር በመሳተፍ ሊደረግ ይችላል። ይህ በማይመችበት ጊዜ ደግሞ የተለያዩ የአደረጃጀት ስልቶችን መጠቀም ይገባል።
የኢትዮጵያ ወጣት ሁሉ አንድ ዓይነት አመለካከት ወይም የተቀራረበ አመለካከት ይኖረዋል የሚል ብዥታ የለብኝም። ሆኖም ግን ከዚህ በታች ያለው ጽሁፍ የሚያተኩረው ተስፋው በህወሓት የተነጠቀው አብዛኛውን ወጣት እያሰብኩ ነው።
የኢትዮጵያ ወጣትን ትግል ለማገዝ ሶስቱ የመዳረሻ (tipping point) ህግጋትን በሚገባ መረዳት እና በሥራ ላይ ማዋል ይጠቅማል ብዬ አምናለሁ። ሶስቱ የመዳረሻዎች ህግጋት (1) የአናሳዎች ህግ (Law of the Few)፣ (2) መጣበቅ (Stickiness Factor) እና (3) የሁኔታዎች ህግ (The Law of Context) ናቸው።
- የአናሳዎች ህግ፣ በሚገባ የተደራጁ ጥቂት ሰዎች ትልቅ ሕዝባዊ ማዕበልን ማስነሳት ይችላሉ የሚለው መርህ ነው። ይህ በማኔጅመንት ውስጥ “መርህ 80/20” (The 80/20 Principle) ከሚባለው ጋር ይዛመዳል። ለምሳሌ በ 20% ጥረት 80% ውጤት እንደሚገኘው ማለት ነው። በአንድ የሥራ ቦታ 100 ሠራተኞች ቢኖሩ አብዛኛውን ጊዜ 80% ያህሉ የሥራ ሸክምና ኃላፊነት የሚወድቀው ከ 20 ባልበለጡ ሠራተኞች ላይ ነው። እነዚህ 20 ለይቶ ማወቅ፣ መሸለም፣ ማሰልጠንና ማበረታታት የጥሩ ማኔጀር ሥራ ነው። በማኅበራዊ ንቅናቄዎችም እንደዚሁ ነው። ጥቂቶች ናቸው ወሳኙን ሥራ የሚሰሩት – ወሳኝ ጥቂት ሰዎች (the vital few).
ከእነዚህ ጥቂት ሰዎች መካከል በወጣቱና በማኅበረሰቡ ተሰሚነት ያገኙ፤ ሲናገሩ የሚደመጡ፤ ንቅናቄውን ወደ በጎ ነገር ይመሩታል ብለው ተከታዮቻቸው እምነት የሚጥሉባቸው “አውራዎች” ወይም የኔታዎች (Mavens) ያስፈልጋሉ። በእድሜ ከወጣትነት የዘለሉ ዜጎች አንዱ ገንቢ ሚና ይህንን ቦታ መሙላት ነው። ሌላው እጅግ አስፈላጊ ነገር የግኑኝነት መረብ (Network) መዘርጋት ነው። እያንዳንዱ የትግሉ ተሳታፊ ከበርካታ ሰዎች ጋር በመገናኘት አድማሱን ማስፋት ይገባል። ግኑኝነት ለመፍጠር ወጣቱ የሚወዳቸውንና የሚያዘወትርባቸው መስኮች ማወቅና አክብሮት ለሚገባቸው አክብሮት መስጠት ያስፈልጋል። ስፓርት፣ ኪነ ጥበብ፣ የእምነት ተቋማት፣ ት/ቤቶች … ሊዳሰሱ ይገባል። አንዳንድ ወጣቶች በተፈጥሮዓቸው ብዙ ኔትዎርክ አላቸው። እንዲህ ዓይነቶቹን ወጣቶች የንቅናቄው አካል ማድረግ በጣም ጠቃሚ ነው፤ ያለ ብዙ ድካም ወጣቱን የማገናኘቱን ሥራ ያቀላጥፉታል። በሶስተኛ ደረጃ ደግሞ የቀስቃሾች መኖር እጅግ አስፈላጊ ነው። ቀስቃሾች ንግግርን፣ ሙዚቃን፣ ስዕልን … ወዘተ በመጠቀም ቁጥሩ እጅግ በርካታ የሆነ ሕዝብን በአንድ መስመር ውስጥ ማስገባት ዋነኛው ሥራቸው መሆን ይኖርበታል።
“መሰብሰብ ወንጀል በሆነበት አገር እነዚህ ‘ጥቂቶች’ እንዴት ይገናኛሉ? እንዴትስ ይደራጃሉ?” የሚል ጥያቄ እንደሚነሳ እገምታለሁ። ስለወጣት ድርጅቶች ስናስብ በሃሳባችን መምጣት ያለባቸው አባላትን መዝግበው፣ መዋቅር አዘጋጅተው ተመዝግበውም ሆነ ሳይመዘገቡ የሚሠሩ መደበኛ ድርጅቶችን ብቻ አይደለም። አፈና በበዛበት ሥርዓት ውስጥ ኢመደበኛ ድርጅቶች (informal organisations) ከመደበኛዎቹ የተሻለ ሊያገለግሉ ይችላሉ። የስፓርት ቡድን ደጋፊዎች፣ የመፃህፍት አፍቃሪያን ስብስቦች፣ የአገርህን እወቅ ክበባት፣ የአካባቢ ጥበቃ ማኅበራት፣ የቴኳንዶና ማርሻል አርት ክበባት፣ የሙዚቃ ክበባት፣ የማርያም፣ የሥላሴ፣ የገብሬል … ጽዋ ማኅበራት፣ ደብተሮች፣ እርሳስና እስክሪብቶዎችን ለድሆች ተማሪዎች አሰባሳቢ ክበባት፣ በረንዳ አዳሪዎችን አልባሽ ማኅበራት፣ እቁቦችና ትናንሽ እድሮች እና የመሳሰሉት ሁሉ የመደበኛ የወጣት ድርጅት ምትክ ሆነው ሊያገለግሉ ይችላሉ።
- መጣበቅ (Stickiness Factor)፤ ይህ ህግ የመልዕክቱ ይዘትና አቀራረብን የሚመለከት ነው። መልዕክቱ በቀላሉ መዳረስ ብቻ ሳይሆን ከተቀባዩ ጋር “መጣበቅ” አለበት። መልዕክት በብዛት ቢዳረስም ሆነ በተከበሩ ሰዎች አንደበት ቢነገርም እንኳን አድማጩ አዕምሮ ውስጥ የማይቀር ከሆነ ማዕበል የማስነሳት አቅም አይኖረውም። የመልዕክቱ ይዘት ደግሞ ቀላልና ግልጽ ብቻ ሳይሆን ወደሌሎች ለማዳረስም የሚያጓጓ መሆን ይኖርበታል።
ወጣቱ የትግሉን ግብ በግልጽ ቢያስቀምጥ ይጠቅማል ባይ ነኝ። መልዕክቶች አጭርና ቀላል ሆነው ወደ ተግባር የሚመሩ መሆን ይኖርባቸዋል። ለምሳሌ የወጣቱ እንቅስቃሴ ዓላማ በሚከተለው አኳኋን በአጭሩ ማቅረብ ይቻላል።
ህወሓት በሕዝባዊ እምቢተኝነትና አመጽ ይወገዳል፤ ሰፊ ውክልና ያለው የሽግግር መንግሥት ይመሠረታል። የዜጎች፣ የሃይማኖቶች፣ የብሄር/ብሄረሰቦች፣ የቋንቋዎች እኩልነት ይከበራል፤ ገለልተኛ ተቋማት ተመሥርተው በሁሉም እርከኖች የመንግሥት ሥልጣን በነፃ የሕዝብ ምርጫ ይወሰናል። አዲሱ ሥርዓት ለሁላችንም የሚበጅ ስለሆነ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጎናችን ይቁም። በተለይ የመከላከያ ሠራዊትና ፓሊስ ከሕዝብ ጋር ወግኑ፤ የኢህአዴግ አባላትም በሕዝብ ጎን በመቆም ታሪክ ስሩ።
መልዕክቶችን በምስል፣ በተረት፣ በምሳሌ፣ በቀልድ ወዘተ ማስተላለፍ መለመድ ይኖርበታል። !!
- የሁኔታዎች ህግ (The Law of Context)፤ አካባቢያዊ ሁኔታዎች በእንቅስቃሴዎቻችን ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንዳላቸው ማመን ተገቢ ነው። የትግል ስትራቴጂና ስልት በአብዛኛው የሚወሰኑት በሁኔታዎች ነው። እኛ በሁኔታዎች ላይ ሙሉ ቁጥጥር የለንም። በዚህም ምክንያት ከአንድ ዓይነት የትግል ስልት ጋር “መቁረብ” በጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል። ወጣት መሪዎች ሁኔታዎችን እያጠኑ ተስማሚ ስትራቴጂዎችንና ስልቶችን መቀየስ መልመድ ይኖርባቸዋል። በአንዱ ቦታ የሠራው በሌላ ቦታ ላይሰራ እንደሚችል፤ የነጠረ፣ ብቸኛ የሚባል ስትራቴጂ እንደሌለ መገንዘብ ይጠቅማል።
አጣዳፊ ሥራዎች
ሁሉንም ሥራዎች በአንድ ጊዜ መፈፀም የማንችል በመሆኑ ቅደም ተከተል ማውጣት ግድ ነው። በኔ ግምት አሁን የለውጥ ዋዜማ ውስጥ እንገኛለን። በዚህ ወቅት በስፋት መሠራት ያለባቸው ሁለት ነገሮች ወጣቶችን ማንቃትና ለለውጥ ማዘጋጀት እና ኔትዎርኮችን ማስፋት ናቸው። በሌላ አነጋገር መቀስቀስ እና ማደራጀት የወቅቱ ሁለት አጣዳፊ ሥራዎች ናቸው።
ወጣቱን ለመቅስቀስ ያሉት የመቀስቀሻ መሣሪያዎችን ሁሉ – ቴሌቪዥን፣ ሬድቶ፣ ጋዜጣ፣ ማኅበራዊ ሚዲያዎች፣ በራሪ ጽሁፎች፣ ስብሰባዎች፣ የሰው ከሰው ንግግሮች እና ሌሎችም መንገዶች ሁሉ መጠቀም አለብን። ለማደራጀት ደግሞ ከላይ እንደተገለፀው መደበኛ ድርጅቶችን ብቻ ሳይሆን ኢመደበኛ ድርጅቶችን መጠቀም መልመድ አለብን።
ከኢትዮጵያ ወጣት 10% እንኳን በዚህ ሁኔታ ቢዘጋጅ የህወሓት አገዛዝ ሊሰነብት አይችልም፤ ይህ ደግሞ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊፈፀም የሚችል ነው።
No comments:
Post a Comment