Wednesday, 18 February 2015

እስኪ እንያችሁ

18 02 2015
ከዳንኤል ክብረት
እስኪ እንያችሁ
ከቀናት በፊት ሬዲዮ ማዳመጥ እስኪሰለቸን ድረስ ሁሉም ጣቢያዎችና ፕሮግራሞች ስለ ‹ቫላንታይን ደይ› ነበር የሚወተውቱን፡፡ ልክ ፍቅር በዚህች ሀገር እንዳልተወለደ፣ ድኾ እንዳላደገ፣ ለወግ ለመዓርግ ደርሶ ጎጆ እንዳልቀለሰ ይመስል ነበር፡፡ ቀይ ልብስ ያልለበሰ፣ አበባ ያልያዘ፣ በምሽት በሚደረጉት ጭፈራዎች ያልተገኘ፣ ማታም ጥንድ ሆኖ አልጋ ያልያዘ ሰው ሁሉ ፍቅርን እንደማያውቅ ተደርጎ ነበር የሚተረክልን፡፡
ዝንጀሮ ጠባቂ ላያድር ያመሻል፣
አፌ ፈራሽ እንጂ ልቤስ ከጅሎሻል፤
ዝንጀሮ ጠባቂ ላያድር ካመሸ
ከፈራህኝማ ነገር ተበላሽ፡፡
ተብሎ ያልተገጠመ፤
አቡኪ ወእምኪ ኢይፈቅዱ እንግዳ
ሰዐምኒ ንሑር በሳንቃው ቀዳዳ፤
ያልተባለ ይመስል ነበር በዚህች ሀገር፡፡ ‹ፍቅር እዚህ ቦታ ፈገግ ብሎ ነበር› አለ ኤፍሬም ሥዩም፡፡ መቼም ፈገግ ካለባቸው አጋጣሚዎች መካከል አንዱ በቀደም ጋዜጠኞቻችን ‹ፍቅር የመጣውኮ ከውጭ ሀገር ነው› ሊሉን ሲደርሱ ሰምቶ መሆን አለበት፡፡
ምዕራባውያን በአንድ ነገር ጎበዞች ናቸው፡፡ ባሕላቸውን ወደ ሸቀጥነት መቀየርና የገበያ ማሟሟቂያ ማድረግ ይችሉበታል፡፡ የካፒታሊስት ሥርዓት አንዱ መገለጫውም ሁሉን ነገር ሸቀጥ ማድረግ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ለእነርሱ ሃይማኖት እንኳን ቢሆን ሲታመንበት ሳይሆን ሸቀጥ ሆኖ ሲሸጥ ነው የሚያዋጣው፡፡ ‹የቫላንታይን ደይ›ን በዓል ከፍቅረኞች በላይ ባለ ሆቴሎችና ባለ ጭፈራ ቤቶች፣ አበባ ሻጮችና የስጦታ ካርድ አምራችና አከፋፋዮች፣ ቸኮሌትና ወይን አምራቾች ይፈልጉታል፡፡
እነርሱ ፍቅርን በእሴትነቱ ሳይሆን በሸቀጥነቱ ነው የሚፈልጉት፡፡ የሚሞቱለት፣ የሚሠዉለት ዓይነት ፍቅር ሳይሆን የሚያተርፉበት ዓይነት ፍቅር፡፡ እንዲያውም አንዳንድ የሚዲያ ባለቤቶች ስለ ቫለንታይን ሂስ ለማቅረብ የሚነሡ የፕሮግራም አዘጋጆችን ‹‹ስፖንሰሮቻችን ይቀየማሉ› በሚል ሲከላከሉ እንደነበር ውስጥ ዐዋቂዎች ይናገራሉ፡፡
ፍቅር እንደ ሸቀጥ ስለታየ ‹ቀይ ልብስ ለብሳችሁ ከመጣችሁ የክብር ሥፍራ አለን፣ ጥንድ ሆናችሁ ከመጣችሁ ቅናሽ እናደርጋለን፣ እኛጋ ጥንድ ሆናችሁ አልጋ ከያዛችሁ ግብዣ ላይ ዋጋ እንቀንሳለን› የሚሉ ዓይነት ማስታወቂያዎች ነበሩ አየሩን የሞሉት፡፡
ኢትዮጵያውያን ከውጭ መልካም ሐሳብ የያዙ በዓሎችን ሲያመጡ ሐሳቡን እንጂ ሙሉ ቅርጽና ይዘቱን አያመጡትም፡፡ ገና ኢትዮጵያዊ መልክ ነው ያለው፤ ግን ዓለም ዐቀፋዊ በዓል ነው፡፡ የጥምቀት በዓል በሌሎችም ክርስቲያን ሕዝቦች ዘንድ አለ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ኢትዮጵያዊ ቁመና፣ መልክና ባሕል አለው፡፡ የደብረ ታቦር በዓል በሌላውም ዓለም ይከበራል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ቡሄ ሆኗል፡፡
ይህ መሆኑ በሦስት ነገር ሲጠቅመን ኖሯል፡፡ በአንድ በኩል የራሳችን መገለጫ፣ የማንነታችን ማነጫና መግለጫ ሆኖ እንዲኖር አድርጎታል፡፡ ለዚህ ነውኮ መስቀልን አዲስ አበባ፣ ገናን ላሊበላ፣ ጥምቀትን ጎንደር ላይ ለማየት የአገር ፈረንጅ የሚጎርፈው፡፡ እዚያ የሚሄደው ኢትዮጵያዊውን መልክ ለማየት እንጂ ጌታ መወለዱን፣ መጠመቁንና መስቀሉ ከተቀበረበት መገኘቱን እንደ አዲስ ለመማር አይደለም፡፡ ይህን ሐሳብ ወደ ሕልው ባሕል የቀየርንበትንና ያንንም የጠበቅንበትን መንገድ ለማየት እንጂ፡፡ አንድን ሐሳብ የሕዝብ ባሕል ማድረግ በሰው ልጅ ጉዞ ውስጥ ወሳኙና እጅግ አስፈላጊው የሰብእና ክፍል ነው፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ከኢትዮጵያዊ ማንነት ጋር የተዋሐደ በመሆኑ ገጠር ከከተማ፣ ሰሜን ከደቡብ ሳያነቅፈው ተጣጥሞ እንዲሄድ አድርጎታል፡፡ ከደኻ እስከ ሀብታም፣ ከማይም እስከ ምሁር፣ ከደቂቅ እስከ ሊቅ እንደ ዐቅሙ ያከብረዋል፡፡ ሦስተኛው ደግሞ በዓሉ ቤተኛ መሆኑ ነው፡፡ ቤተኛ በዓል ማለት ቤተሰብን የሚመለከት፣ ሁሉም የሚሳተፍበት፣ የሀገር ቤቱን ሰው ተሳትፎ የሚጠይቅ ማለት ነው፡፡ ለገና ዳቦ የሚሆነውን እህል፣ በግና ዶሮውን ገበሬ ያመጣል፤ ነጋዴ ለበዓሉ የሚያስፈልገውን ነገር ያከፋፍላል፡፡ የሴቶች ሞያ በጠላው በዶሮው፣ የወንዶቹ ሞያ በእርዱ በሥጋው ይታያል፡፡ እንኳን አደረሰህ የሚለው ዘመድ አዝማድ መልእክቱን ይልካል፡፡ ከጉልት ገበያ እስከ ‹ሱፐር ማርኬት› አገሩ ሸብ ረብ ይላል፡፡ በዓል መሆኑን አካባቢውም ይናገራል፡፡ ልጅ ዐዋቂው፣ ያገባው ያላገባው፣ ነባሩና አዲስ መሽራው፣ መናኙና ከተሜው፣ ሁሉም ይሳተፋል፡፡ ለዚህ ነው እነዚህ ሀገርኛ በዓላት የመከራ ዘመናትን ሁሉ አልፈው በየጊዜው እየበለጸጉ እዚህ ዘመን የደረሱት፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ የ‹ቫለንታይን ደይ› ኢትዮጵያኛ ሆኖ ቢሆን ኖሮ በየካቲት አበባዉ ሁሉ ረግፎ ባለቀበት በየካቲት ወር አልነበረም መከበር የነበረበት፡፡ በጥቅምት እንጂ፡፡ አበባ መስጠት ያለባችሁ የግድ ገዝታችሁ ነው ካልተባልን በቀር፡፡ አገሩ በሙሉ በአበባ የሚያሸበርቅበትን የጥቅምትን ወር አሳልፎ የአበባን በዓል በመከር ጊዜ ማክበር ምን ያህል በዓሉ ኢትዮጵያዊነት እንደሚጎድለውና ተገንጥሎ ብቻውን እንደቆመ የሚሳየን ነው፡፡
ምንም እንኳን ቀይ ሽብር፣ ቀዩ ጦር፣ የቀይ ኮከብ ጥሪ፣ የሚሉ መጥፎ የቀይ ቀለም ትዝታዎች ቢኖሩብንም ያ ሁሉ ቀይ ወይን፣ ቀይ ምንጣፍ፣ ቀይ መብራት፣ ቀይ አበባ፣ ለጦርነት፣ ለሽብርና ለጠብ አይደለም፤ ለፍቅር ነውና ኩነቱን ሳይሆን ምክንያተ ክዋኔውን ተመልክተን ስለ ፍቅር አምላክ ስንል ይሁን ብለን እዚህ ላይ እንለፈው፡፡
ግን እስኪ ልክ እንደ ቫላንታይኑ ሁሉ ለራሳችንም ጉዳይ ትኩረት እንስጥ፡፡ አሁን ነገ የካቲት 12 ቀን ለዚህች ሀገር ሕይወታቸውን የገበሩ፣ በፋሽስቶች የተጨፈጨፉ፤ ዛሬ እኛ ዘና ብልን በቀይ ወይንና በቀይ ምንጣፍ የ‹ቫላንታይን ቀንን› እንድናከብር ያደረጉ ሰማዕታት በዓል ይከበራል፡፡ ከቫለንታይን ይልቅ የካቲት 12 የራሳችን ጉዳይ ነው፡፡ ለዛሬ ማንነታችን ወሳኝ ምዕራፍ ነው፡፡ እንዲህ በነጻነት ቀና ብለን እንድንሄድ ዋጋ ከከፈሉ ሰዎች መካከል ናቸው የየካቲት 12 ሰማዕታት፡፡ ይኼው ዛሬ ዋዜማው ነው፡፡ ማንም ግን ስለ ነገው በዓል እየተናገረ አይደለም፡፡ ነገም ከአንዲት ዜና በቀር ማን ስለ ጉዳዩ ጣል እንደማያደርግ እገምታለሁ፡፡
የትናንት ታሪኩን በሚገባ የማያውቅ፣ የማይተነትንና የማይገነዘብ የትናንቱን ስሕተቱን በከፋ መንገድ ለመድገም የተረገመ ነው፡፡
ከትናንት የተሻለ ለመሥራት በትናንቱ መሠረትም ላይ ለመገንባት ትውልድ የተሠራበትን የታሪክ ጡብ ማወቅ አለበት፡፡ በርግጥ እንደ ቫለንታይን ቀን በስፖንሰር አያንበሸብሽም፣ በርግጥም ቀይ ወይንና ቀይ ምንጣፍ የለውም፡፡ አበባ ለመሸጥና ጭፈራ ለመጨፈር አይመችም፡፡ ግን ከቫለንታይን ቀን ይልቅ የካቲት 12 ቀን እኛነታችን ነው፡፡ መነሻ የሌለው መንገድ፣ መንገድ የሌለውም መድረሻ የለም፡፡ ለመንገዱ ዋጋ ነሥቶ፣ ለመድረሻው ተስፋ ማድረግን የመሰለ ዕብደትም የለም፡፡ ለመንገድ ሠሪው ዋጋ ነሥቶ በመንገዱ ላይ ለሚሄደው መኪና ምስጋና ማዥጎድጎድን የመሰለ ክፉ ዐመል የለም፡፡ በትናንቱ ላይ ለመግባባት አለመቻላችን ነው በዛሬውም ላይ ሊያግባባን ያልቻለው፡፡
እናም እናንት ‹ሚዲያዎች›፣ እናንት በዓለ ሚዲያዎች
የኢትዮጵያ ነን ካላችሁ
እስኪ እንያችሁ
ኢትዮጵያዊ ለሆኑ በዓሎችና ጉዳዮች እንደ ቫለንታይን ቀን ሁሉ አገሩን በሚዲያ ስታውዱት፣ እንደ ቅዱስ ቫለንታይን ሁሉ ስለ የካቲት 12 ሰማዕታት፣ ስለ አድዋ ጀግኖች፣ ስለ ማይጨው ዘማቾች ስትተርኩ እንስማችሁ፡፡
የኢትዮጵያ ነን ካላችሁ
የኢትዮጵያ ጉዳዮች ላይ፣ ባሕሎች ላይ፣ ታሪኮች ላይ፣ በዓሎች ላይ፣ ጀግኖች ላይ፣ ቦታዎች ላይ አጥንታችሁ፣ አንብባችሁ፣ ስታቀርቡ እስኪ እንያችሁ፡፡
ርግጥ ነው ዊኪፒዲያ ላይ አይኖር ይሆናል፣ ኢንተርኔት ላይ በክሊክ አይገኝ ይሆናል፣ ጎልጉል ሲጎለጎል በቀላሉ አይመጣ ይሆናል፡፡ ግን የራሳችን ጉዳይ ነው፡፡ ‹ራሴን በራሴ ካላንቆለጳጰስኩት ማን ያንቆለጳጵስልኛል› ነውና እኛ ለእኛ እንሥራ፡፡ ሌሎችም ስለ ሠሩ ነው ዛሬ ስለ እነርሱ በቀላሉ የትም የምናገኘው፡፡ እኛም ብንሠራ የኛ ጉዳይ በቀላሉ እንዲደረስበት ማድረግ እንችላለን፡፡
የኢትዮጵያ ነን ካላችሁ
እስኪ እንያችሁ፤

No comments:

Post a Comment