የጀግናው አትሌት አበበ ቢቂላ ልጅ በጎዳና ሕይወት – “የአበበ ልጅ ስለሆንኩ እርዱኝ አልልም; ግን መንከራተት ሰልችቶኛል”
አዲስ አበባ ስታዲየም … ዘወትር ማለዳ ለልምምድ የሚወጡና የሚገቡ ሯጮችን ማየት የተለመደ ነው፡፡ ከትንሽ እስከ አንጋፋ፤ ከጀማሪ እስከ ታዋቂ፤ ከእግረኛ እስከ ባለመኪና አትሌቶች ይመላለሱበታል፡፡ ሁሉም አንድ ህልም አላቸው፦በአለም አደባባይ ስኬታማ አትሌት መሆን፡፡ ህልማቸውን እንደሚደርሱበት ደግሞ እርግጠኞች ናቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ መነሻ አላቸው፡፡ እውነት አላቸው! ታሪክ አላቸው! አበበ ቢቂላ…የእነሱ እውነትና እምነት፡፡ የእነሱኩራትና ተስፋ! የዚህ ጀግና አትሌት ልጅ… ኢትዮጵያ አበበ… ግን እንደ ብዙዎች አትሌቶች በአባቱ ኩራትና ተስፋ ከልቡ ውስጥ የለም፡፡ ጀግንነቱን አልወረሰም፡፡ታሪኩንም የሚያካፍለው አላገኘም፡፡ መኖር የፈተነው ህይወት፣ ማንነት ያሰቃየው ሰውነት ይዞ ጎዳና ላይ ወጥቷል፡፡ ከእድሜያቸው በላይ በላይ ገርጅፈዋል፡፡ አዲስ አበባ ስታዲየም ሲወጡና ሲገቡ የሚታዩ አትሌቶች፣ የአበበ ቢቂላን ታሪክ ለአለም እያወሩ ኩራታቸውን የሚገልጹቱ፣ እርሱን ተስፋቸው ያደረጉ፣ ድልንም የተጎናጸፉቱ፣ አዲስ አበባ ስታዲየም ዋና መውጫያና መግቢያ በር ፊት ለፊት ተቀምጦ የሚውለውን ልጁን ማየት አልቻሉም፣ ወይም አልፈለጉም፡፡ ወይም… ወይም….ወዘተ… የጀግናው ልጅ ግን ያያሉ፡፡ ያያሉ… ሊያውም በአንክሮ ያያሉ፡፡ ግን አይናገሩም፡፡ በዝምታ ያያሉ፡፡ ይታዘባሉም፡፡ ‘የአበበ ቢቂላ ልጅ ነኝና እባካቹ እርዱኝ፣ ርቦኛልና አጉርሱኝ' ማለት ያሳፍራቸዋል፡፡ ብቻ ዝም ብለው ስታዲየሙ እያዩ ይተክዛሉ፡፡ አይናቸው እንባ እያቀረረ ወደ ፈጣሪያቸው ይማጸናሉ፡፡ “ፈጣሪ ሆይ አንተ ለኔ መሆን ከቃተህና ሰው ፊት የምታቆመኝ? እኔስ ምን በደልኩህ? አባቴን ፍቅርና ክብር ሳላጣጥም በስቃይ እንድኖር ስለምን ፈረድክብኝ? ብቻ ግን ተመስገን! ተመስገን!” ……………አሁን ኢትዮጵያ አበበ እድሜያቸው ገፍቷል፡፡ ኑሮ አድክሟቸዋል፡፡ ከአስር አመት በላይ የቆዩበት የጎዳና ህይወት አንገሽግሿቸዋል፡፡ ፍላጎታቸው ብዙዎች እንደሚያስቡት የአበበን ሀብትና ንብረት መውረስ ወይም እውቅና መፈለግ አይደለም፡፡ ማረፍ ነው የሚፈልጉት፡፡
“እኔ የአባቴን ሀብት ንብረት ስጡኝ፣ አካፍሉኝ ብዬ አልሟገትም፡፡ የአበበ ቢቂላ ስለሆንኩም እርዱኝ አልልም፡፡ በዚህ እድሜዬ የአዲስ አበባን ጎዳናዎች እየዞርኩ መለመን አቅቶኛል፡፡ ማረፍ ነው የምፈልገው”
ምንጭ:-yegara.com
No comments:
Post a Comment