Tuesday, 17 February 2015

የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር የትግል ጥሪ አስተላለፈ

በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር
የ9ኙ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ትብብር ‹‹ነጻነት ለፍትሃዊ ምርጫ›› በሚል መርህ የሁለተኛ ዙር የሠላማዊ ትግል ጥሪውን 
ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች አስተላለፈ፡፡ ትብብሩ የካቲት 15 ቀን 2007 ዓ.ም በተመሳሳይ ሰዓት በ15 ከተሞች 
ሊያደርገው አቅዶት የነበረውን ሰላማዊ ሰልፍ በሳምንት አራዝሞ ለየካቲት 22 ቀን 2007 ዓ.ም ማስተላለፉንም 
አስታውቋል፡፡
ትብብሩ ዛሬ የካቲት 10 ቀን 2007 ዓ.ም በሰማያዊ ፓርቲ ጽ/ቤት በሰጣው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው፣ ገዢው 
ፓርቲ የቱንም ያህል አሰቃቂና አረመኔያዊ የአፈና እርምጃዎች ቢወስድም የህዝብ ጥያቄዎች እስካልተመለሱ ድረስ ህዝባዊ 
ትግሉን ማዳፈን እንጂ ማስቆም እንደማይችል ይልቁንም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ከተለያዩ የህዝብ እንቅስቃሴዎች መገንዘቡን 
ገልጹዋል፡፡ ትብብሩ ምርጫን በተመለከተ እንዳስታወቀው ኢህአዴግ ስለመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ከቃላት 
ያለፈ እምነትም ሆነ ቁርጠኝነት የሌለው መሆኑን በዚህ የምርጫ ወቅት በተፎካካሪ ፓርቲዎች ላይ እየወሰደ ያለው ህገ-ወጥ 
እርምጃ ማሳያ ነው ብሏል፡፡
‹‹ለውጡ የሚመጣባቸው አምባገነኖች ድንገተኛ ከፍተኛ 
ፍርኃትና ሥጋት በማሳደሩ ህገ-መንግሥቱን በመጨፍለቅ 
በግልጽና በአደባባይ ህገ-ወጥ ውሳኔዎችንና እርምጃዎችን 
ለመውሰድ መገደዳቸው፣ ይህም የህዝቡን የለውጥ ፍላጎትና 
የትግል ተነሳሽነት በማሳደግ ህዝባዊውን ትግል ወደ ላቀ 
ደረጃ ማሸጋገሩ የበለጠ ግልጽ ሆኗል›› ብሏል ትብብሩ፡፡
ትብብሩ አሁን ባለንበት ተጨባጭ ሁኔታ የአገራችንና ዜጓቿ 
ቀጣይ ዕጣ ፈንታ በሁለት አማራጮች ላይ የተንጠለጠለ 
ነው 
ያለው መግለጫው፣ አንድም ያለውን አምባገነናዊ ሥርዓት ተቀብሎ የጭቆና ቀንበር ተሸክሞ በከፋ ውርደት ሥር ሰጥ- ለጥ 
ብሎ መገዛት፣ አሊያም አምባገነንነትና ጭቆናን ‹‹በቃ›› በማለት በሕዝባዊ የተቀናጀ ሰላማዊ ትግል ለአገራችን ሉዓላዊነትና 
የዜግነት ክብራችንን ለማስመለስ በህገ መንግስታዊ መብታችን ተጠቅመን ትግላችንን እስከማይቀረው ለውጥ ድል ደጃፍ ድረስ 
በቆራጥነት መቀጠል ናቸው ብሏል፡፡
በዚህም ትብብሩ ህገ-መንግስታዊ መብትን በመጠቀም በህግና በሥርዓት ትግሉን ለመምራት መዘጋጀቱን በመግለጽ፣ የተለያዩ 
የህብረተሰብ ክፍሎች የትግል ጥሪውን እንዲቀላቀሉት አሳስቧል፡፡ ስለሆነም ትብብሩ ‹‹ኢህአዴግነት ከዜግነት በላይ›› 
ለሆነባቸው የሥራ ዋስትናቸው፣ ዕድገትም ሆነ ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች በሙያቸው፣ በልምዳቸው፣ ክህሎታቸው፣ በመሳሰሉት 
ባልተመሰረተ መልኩ በደል እየደረሰባቸው ላሉ ሁሉ የትግል ጥሪውን አስተላልፏል፡፡
‹‹የህወኃት/ኢህአዴግ ተራ አባላትና ካድሬዎች፤ የፖለቲካ ልዩነት የተለያየ አመለካከትና ሀሳብ ማራመድ ጤናማ የመድብለ 
ፓርቲ ፖለቲካ መገለጫ እንጂ እንደሚነገራችሁ ‹‹ጠላትነት›› ባለመሆኑ፣ ትግላችንም ለሠላማዊና ህጋዊ የሥልጣን ሽግግር 
እንጂ በናንተ ‹‹መቃብር›› ላይ አዲሱን ሥርዓት የማቆም፣ የነበረውን አጥፍቶ ከዜሮ የመጀመርና እናንተን የማጥፋት ዓላማ 
እንደሌለው ተረድታችሁ፣ ተቃዋሚዎች እንደናንተው ኢትዮጵያዊያንና ለኢትዮጵያና ህዝቧ የሚጨነቁ መሆናቸውን በመረዳት 
ተቃዋሚዎችን እንደ‹‹ ጠላት›› ከመመልከት አስተሳሰብ ራሳችሁን ነጻ እንድታወጡ›› ሲልም ትብብሩ መልዕክቱን 
አስተላልፏል፡፡
ወጣቶችና ሴቶች በተለይም የወጣቶችና ሴቶች አደረጃጀቶች፣ መምህራንና ተማሪዎች በተለይም የዩኒቨርስቲና የሁለተኛ ደረጃ 
ተማሪዎች፣ የእምነት ነጻነት መብት ጠያቂ የማኅበረሰብ አባላት፣ የመገናኛ ብዙሃን አባላት፣ የፍትህ አካላት፣ የዴሞክራቲክ 
ፓርቲዎች አባላት፣ የነጻነትና የዴሞክራሲ ሰላማዊ ታጋዮች፣ በውጪ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵዊያን/ዲያስፖራዎች እና ሌሎችም 
ጥሪው የተላለፈላቸው አካላት መሆናቸውን መግለጫው አትቷል፡፡
በመሆኑም፣ ‹‹በምናርገው አገራዊ፣ ሰላማዊና ሕዝባዊ ትግል በማይቀረው የሥርዓት ለውጥ ለሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር 
በአንድነትና በቆራጥነት እንድትሰለፉ፤ የካቲት 22/07 በየከተሞቹ በቦታውና በሰዓቱ እንድትገኙ ጥሪያችንን አበክረን 
እናቀርባለን›› ብሏል የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር፡፡

No comments:

Post a Comment