የካቲት ፲፫ (አስራ ሦስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪ ልማት ሚኒስትሩ አቶ መኩሪያ ሃይሌ ከስነ ምግባር እና ፀረ ሙስና ኮሚሺን አጣሪ ቡድን ጋር ባደረጉት ውይይት ከመንገድ ስራ ፣ ከባቡር መስመር ዝርጋታና፣ ከቤቶች ልማት ፕሮጀክቶች ጋር በተያያዘ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ እየተዘረፈ መሆኑን አምነዋል።
የፀረ ሙስና ኮሚሽን ባካሄደው ጥናት በባቡር መስመር ግንባታ 2.3 ኪሜ የባቡር ሃዲድ መስመር በሙስና ምክንያት ከደረጃ ውጭ እንዲሆን በመደረጉ የ124 ሚልዮን በር ኪሳራ ደርሷል። የአደጋ መከላከያ ብረቶች የተሰሩት ከወጣላቸው የጥራት ደረጃ በሶስት እጅ ያነሱ ሆነው በመገኘታቸው ጉዳዩ ለቦርድ ሰብሳቢው ዶ/ር አርከበ እቁባይ ቢቀርብም ምላሺ ሰይሰጠው በመቅረቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የት እንደገባ ማወቅ አለመቻሉን ገልጿል።
የስነ ምግባር እና ፀረ ሙስና ኮሚሺን ያቀረበውን ሪፖርት ተከትሎ ምላሺ የሰጡት ሚኒስትር መኩሪያ ሃይሌ ፣ ችግሩ የተፈጠረው ለምርጫው ሲባል የባቡሩ ግንባታ እንደ ትልቅ የምርጫ ማሰመኛ በመያዙ ነው ።
የግንባታ ኢንዱስትሪው ከሚያወጣው ወጪ ከ30 እስከ 60 በመቶ የሚሆነው በሙስና ይባክናል ሲሉም ሚኒስትሩ አክለዋል።
በተመሳሳይ ዜናም በአማራ ክልል በመንግሥት በጀት እየተከናወኑ ያሉ ግንባታዎች የጥራትና በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ ያለመጠናቀቅ ችግር አሳሳቢ ደረጃ መድረሱን በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች በምሬት ተናግረዋል።
ሰሞኑን በባህርዳር ከተማ የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ ከህንፃ ተቋራጮችና ሙያተኞች ጋር ባደረገው ውይይት የግንባታ የጥራት ችግር ምክንያቱ ተቋራጮች በቤተ ሙከራ ባልተፈተሸና እውቅና ባልተሰጣቸው ቁሳቁስ ግንባታ በመፈፀማቸው እና የመንግስት አካላትም የራሳቸውን ድርሻ በማንሳቱ ረገድ ከፍተኛ ሩጫ በማድረጋቸው እንደሆነ ተወስቷል::
የህንፃ ተቋራጭ የሆኑት አቶ አረጋይ ወልደ ፋኑኤል ግንባታዎች ተሰርተው መጠናቀቃቸውን ያበሰረው ዜና በደንብ ተደምጦ ሳይጠናቀቅ መርዷቸው ይደርሳል:፣ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ በአሰሪ መስሪያ ቤቶችና በተቋራጮች መካከል የሚፈጠረው “የእከከኝ ልከክልህ” የአሰራር ሰንሰለት አለመበጠስ ነው ብለዋል።
አቶ አረጋይ “የአገር ሀብት ተቆጣጣሪና ‘ሀይ ባይ’ በማጣቱ ለዘራፊዎች እየተዳረገ ነው:: የህዝብ ሀብት የሆኑት ግንባታዎች እየፈረሱ ነው:: የህዝብ ፍላጐትን የሚያሟላለት እየጠፋ ነው:: ዋናው ስጋት ደግሞ የሚገነቡት ህንፃዎች ጥራት መጉደል ጋር ተያይዞ ቀጣይ የሰው ህይወት የማያጠፉበት ምክንያት አይኖርም” በማለት ተናግረዋል፡፡
አቶ አረጋይ “ዛሬ ባለ ገንዘብ እናንተ ናችሁ ሆኖም ገንዘብ ቢኖራችሁም የስልጣን መንበሩን የያዛችሁት ህዝቡን እንድታገለግሉ ተሾማችሁ እንጅ እንደፈለጋችሁ በማድረግ ህዝቡን ገደል ግባ ማለት የለባችሁም፡፡”በማለት የተናገሩ ሲሆን በራሳቸው በኩል ያለውን አቋም ሲገልጹ “አኔ ኢምንት ታህል ገንዘብ አልሰጥም ፡፡ሰርቄ መስራት አልፈልግም፡፡አሁንም ሰርቄ ልጫረት አልችልም ፡፡ካሻሻላችሁ ተሻሽየ እቀርባለሁ ፡፡ካላሻሻላችሁ ግን ወደ ጨረታው አልቀርብም ፡፡ከአሁኑ ሰዓት ጀምራችሁ ወስዳችሁ እሰሩኝ ፡፡” በማለት በድፍረት ተናግረዋል፡፡
አቶ አረጋይ “ከረሜላና ሳሙና ሲሸጡ የነበሩ ኮንትራክተር በመባል የሚጠሩበት ጊዜ ምናለ ቢበቃ” በማለት የተማጽኖ ጥያቄ አቅርበዋል።
በህንፃና የመንገድ ግንባታዎች ውስጥ በተቆጣጣሪ መሀንዲስነት ላለፉት 10 አመታት ያገለገሉት አቶ አህመድ ሲራጅ :በተለይ በመንገድ ግንባታ በቆዩባቸው አምስት አመታት ያስተዋሉትን ስርቆትና ብልሹ አሰራን ለማጋለጥ ሲሞክሩ ከስራ ገበታቸው እስከመነሳት ደረጃ መድረሳቸውን ተናግረዋል።
ሁኔታውንም ለከፍተኛ ባለስልጣናት ቢያሳውቁም “መጀመሪያውንም ተግባብተህ አትሰራም ነበር፤ ነገር ማመላለስ ደመወዝህ ነው” እንደተባሉ ተናግረዋል።
እንደ ክልሉ ኦዲት ባለስልጣን ሪፖርት በአማራ ክልል የሚታየው የግንባታ መጓተትና የጥራት ችግር አሳሳቢ በሚባል ደረጃ በመድረሱ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር የአገር ሀብት ለምዝበራ እየተጋለጠ ነው:: በአሁኑ ወቅት 354 ፕሮጀክቶች በግል የስራ ተቋራጮች በግንባታ ላይ ሲሆኑ፣ ከ43 በላይ ፕሮጀክቶች ግንባታቸው ተቋርጧል:: ከ129 በላይ የሚሆኑት ደግሞ በከፍተኛ መጓተት ላይ ይገኛሉ:: በዚህ ሁሉ ችግር የገዢው መንግስት ባለስልጣናት የወሰዱት እርምጃ አለመኖር ምዝበራው ቀጣይነት ያለው መሆኑን እንደሚያመላክት የክልሉ ዘጋቢያችን ገልጻለች።
No comments:
Post a Comment