Sunday 10 August 2014

የአንዳርጋቸዉ ትዉስታዎች

የአንዳርጋቸዉ ትዉስታዎች

“በእኛ እምነት ታሪክ ከነባራዊ ሁኔታ ዉጭ በምኞትና በዘፈቀደ አይሰራም። የሚሰራ ቢሆን ኖሮ ነገስታቱና አምባገነኖቹ ዘሬም በዙፋናቸዉ ላይ በተገኙ ነበር። ባለንበት ወቅት የኢትዮጵያ ህዝቦች መስቀለኛ መንገድ ላይ ቆመዉ ከዚህ ወዴት እንደሚሄዱ ግልጽ ኢየባልሆነበት ሰዐት ሥልጣን ላይ ያለዉም ሆነ የሌለዉም የግሉን የተስፋ ጎዳናን እዉነተኛዉ የወደፊት ጎዳና አድርጎ የሚያይ ከሆነ ዛሬም እንደ ትናንቱ ከታሪክ መማር አልቻልንም ማለት ነዉ”።
“ከዲሞክራሲ ጋር ሲወዳደር ፍትህ ለሚለዉ ጽንሰ ሀሳብ “ኢትዮጵያዊኛ” ቃላቶች ያሉን መሆኑ የሚያስረግጠዉ ነገር ቢኖር ፍትህ ከማንነታችን ጋር የተቆራኘ መሆኑን ነዉ። ኢትዮጵያዉያን ፍትህ ሲጓደል “በህግ አምላክ” ብለዉ በዳያቸዉን ለማስቆም የሚያሰሙት ጩኸት ፍትህ ከፈጣሪያቸዉ የተሰጠ ከሰብዓዊነታቸዉ ተነጥሎ የማይታይ እሴት አድርገዉ እንደሚመለከቱት የሚያመለክት ነዉ። በምድር ላይም ፍትህ የሚሰጥ ዳኛ ጠፍቷል ብለዉ ሲያስቡ እጃቸዉን ወደ ፈጣሪያቸዉ ዘርግተዉ አንተዉ ፍርዱን ስጠና የሚሉት ከፈጣሪያቸዉ ፍጹምነት የሚመነጭ እዉነተኛ ዳኝነት አለ ብለዉ ስለሚያምኑ ነዉ። ከዚህ በላይ ባጭሩ የተባለዉ የሚጠቁመዉ በኢትዮጵያዉያን ባህልና ስነ ልቦና ዉስጥ የፍትህ ጽንሰ ሀሳብ ያለዉን ትልቅ ትርጉምና ቦታ ነዉ”።
የታሪክን ነባራዊነት፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ለፍትህ የሚሰጠዉን ከፍተኛ ቦታና ለነጻነት ያለዉን አመለካከት በተመለከተ ከዚህ በላይ ያሰማናችሁን ሁለት አዉዶች በሁለት የተለያዩ መጽሐፎቹ ዉስጥ የጻፈዉ ዛሬ ፍትህ አልባ በሆነዉ የወያኔ ስርዐት ዉስጥ ለፍትህ፤ ለነጻነትና ለዲሞክራሲ ሲል ለፍተኛ ዋጋ እየከፈለ ያለዉ አንዳርጋቸዉ ጽጌ ነዉ። አዎ የፍትህና የነጻነት አርበኛዉ አንዳርጋቸዉ በግልጽ አንዳስቀመጠዉ ዛሬ ኢትዮጵያ ዉስጥ ፍትህ እስከነ ስሙ ሙልጭ ብሎ በመጥፋቱ የኢትዮጵያ ህዝብ ሁለት እጆቹን ወደ ሰማይ ዘርግቶ እባክህ አምላኬ “ወይ ዉረድ ወይ ፍረድ” እያለ ፈጠሪዉን እየተማጸነ ነዉ። በእርግጥም ፍትህ ፈጣሪያችን ያደለን ትልቅ ማህበራዊ እሴት ነዉ፤ ሆኖም ይህንን የፈጣሪ ስጦታ እኛን የመሰሉ ሌሎች ሰዎች መጥዉ ሲቀሙንና እንዳሰኛቸዉ ሰረግጡን አንረገጥም ብለን እራሳችንን ነጻ ማዉጣትና የተቀማነዉን ፍትህ ከወያኔ ዘረኞች ቀምተን መልሰን ማህበራዊ እሴት የማድረጉ ኃላፊነት የእኛ የራሳችን ነዉ እንጂ የፈጣሪ አይደለም። ፈጣሪያችን ፍትህና ነጻነትን አንዴ ሰጥቶናል እነዚህን የፈጣሪ ስጦታዎች እንዳንቀማ መጠበቅና ከተቀማን ደግሞ ታግለን ማስመለስ ያለብን እኛ ብቻ ነን።
አንዳርጋቸዉ ጽጌ የአማራዉ ህዝብ ከየት ወዴት በሚለዉ መጽሐፉ ታሪክ ከነባራዊ ሁኔታ ዉጭ በምኞት ወይም በዘፈቀደ እንደማይመራና ከትናንት ታሪካችን ካልተማርን የምንደግመዉ ትናንትናና ከትናንት ወዲያ የሰራናቸዉን ስህተቶቻችንን አንደሆነ በግልጽ አስገንዝቦናል። ይህ የአንዳርጋቸዉ ማስገንዘቢያ ያነጣጠረዉ ለመብቱና ለነጻነቱ መከበር ለሚታገለዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን ህዝብ ረግጠዉ እየገዙ ዝንተ አለም መኖር ለሚፈልጉ የወያኔ ዘረኞችም ጭምር ነዉ። ለመሆኑ አንዳርጋቸዉ ከታሪክ አልተማርንም ማለት ነዉ ሲል ምን ማለቱ ነዉ? . . . “አልተማርንም” የሚለዉ ቃል ለአንድ ሰዉ የሚነገር ቃል ሳይሆን ለብዙኋን የሚነገር ቃል ነዉ። በዚህ ብዙኋን ዉስጥ በአንድ በኩል በየዘመኑ እየረገጡ ከሚገዙት የገዢ መደቦች ጋር የሚታገለዉ የኢትዮጵያ ህዝብ አለ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ህዝብን ረግጠዉ እየገዙ መኖር የሚፈልጉ የገዢ መደቦች አሉ። የኢትዮጵያ ህዝብ በ1966 ዓም የፊዉዳል ገዢ መደቦችን አንኮታኩቶ ከጣለ በኋላ ለሚቀጥሉት 17 አመታት ሰዉ በላዉን የደርግ ስርዐት ተሸክሞ ኖሯል። በ1983 ዓም የኢትዮጵያ ህዝብ አሁንም ወታደራዊዉን የደርግ ሰርዐት በህዝባዊ አመጽ ማስወገድ ችሎ ነበር፤ ሆኖም አሁንም ይህ ህዝብ የታገለለት ድል ባለቤት መሆን ባለመቻሉ ዘረኛ አምባገነኖች መዳፍ ዉስጥ ገብቶ ቁም ስቅሉን እያየ ነዉ። አንዳርጋቸዉ ጽጌ ይህንን የጥፋት ዑደት በሚገባ ተገንዝቦ ነዉ ከታሪክ አልተማርንም ብሎ የነገረን።
በ1966 ዓም ጩኸታችን በሙሉ የፊዉዳሉ ስርዐት እንዲፈርስ ነበር እንጂ የምናፈርሰዉ ስርዐት በምን ይተካል ለሚለዉ ጥያቄ መልስ ስላልነበረን በወቅቱ በስራዉ ጠባይ የተነሳ ተደራጅቶ የነበረዉ የወታደሩ ክፍል ስልጣን ተረክቦ አገራችን 17 አመት ሙሉ የደም ባህር ዉስጥ እንድትዋኝ አድርጓታል። የደርግን ስርዐት ለማፍረስ በተደረገዉ ትግል ዉስጥም ከ1966ቱ ስህተታችን ምንም ባለመማራችን መሳሪያ ከታጠቀ ኃይል ሁሉ ጋር ጉሮ ወሸባዬ መዝፈን ጀመርን። ደርግን የሚዋጉ ኃይሎች ሁሉ የህዝብና የአገር ወዳጆች እየመሰሉን በየጫካዉ እየሄድን ተቀላቅለናቸዉና ዛሬ ይሄዉና እኛዉ እራሳችን ያጠናከርናቸዉ ኃይሎች ስልጣን ይዘዉ ካፈረሱት ስርዐት በከፋ መልኩ አገርንም ህዝብንም እያፈረሱ ነዉ። ደርግ ከፊዳሉ ስርዐት ዉድቀት ምንም ባለመማሩ ሃያ አመት ሳይሞላዉ እሱም እንደ ፊዉዳሉ ስርዐት የታሪክ ቆሻሻ ዉስጥ ተጥሏል። ከፊዉዳሉም ከደርግም ስርዐት ዉድቀት መማር ያልፈለጉት የዛሬዎቹ ዘረኞች ደግሞ የማይቀረዉን ዉድቀታቸዉን እየጠበቁ ነዉ። የወያኔ ዘረኞች ከታሪክ አለመማር ካሁን በኋላ ሊገርመን ወይም ሊያጠያይቀን አይገባም፤ እነሱ ወደዱም ጠሉ የኢትዮጵያ ህዝብ ያስተምራቸዋል። ዛሬ ዋናዉ ቁም ነገር ወይም ትልቁ ጥያቄ እኛ ካለፉት ሁለት ግዙፍ ስህተቶቻችን ተምረናል ወይ የሚለዉ ጥያቄ ነዉ፡፡ ስራችን የወያኔን ስርዐት ማፍረስ ብቻ ነዉ ወይስ ከወያኔ መፍረስ በኋላስ ለሚለዉ ጥያቄ መልስ አለን። ወያኔን እያፈረስን ስንሄድ ከማፍረስ ጎን ለጎን ወያኔን የሚተካ ስርዐት እየገነባን ነዉ ወይስ ሩጫችን ሁሉ ማፍረሱ ላይ ብቻ ነዉ ያተኮረዉ።
የወያኔን ስርዐት ለማፍረስ በሚደረገዉ ትግል ዉስጥ የተቃዋሚ ኃይሎች መሰባሰብና በአንድነት መቆም ቁልፍ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም፤ ሆኖም በእኛ እምነት እጅግ በጣም ከባዱና ዉስብስቡ ስራ ወያኔ የፈጠረዉን ዘረኛ ስርዐትና ቆሻሻ ባህል ማፈራረስና በምትኩ ሌላ መገንባት ነዉ እንጂ ወያኔን ማስወገዱ አይደለም። ወያኔ በህዝብ የተጠላና የተተፋ ስርዐት ስለሆነ በራሱ ዉስጥ በሚፈጠር ቀዉስ ወይም በአንድ እራሱን ለህዝባዊ አመጽ ባዘጋጀ ጠንካራ ድርጅት ተጠራርጎ ሊጠፋ የሚችል ድርጅት ነዉ። ለአገራችን ለኢትዮጵያ በጎ የምንመኝና ዛሬ ወያኔን በተለያየ መልኩ የምንፋለም የነጻነት ኃይሎች አጅግ በጣም ሊያሳስበን የሚገባና አገራችን ኢትዮጵያም በቀላሉ የማትወጣዉ ማጥ ዉስጥ የምትገባዉ ወያኔ ከእነዚህ ሁለት መንገዶች በአንዱ ከወደቀ ነዉ። ይህንን ታሪካዊ ጥፋት እዉን ከመሆኑ በፊት መቀየር የምንችለዉ ደግሞ ወያኔ ከወደቀ በኋላ ሳይሆን ዛሬ ለመዉደቅ ሲንገዳገድ ነዉ።
አንዳርጋቸዉ አገራችን ብዙ አደጋዎች ፊቷ ላይ አንደተደቀኑባት በትክክል ካሳየን በኋላ አደጋዎቹን አንዴት መከላከል አንዳለብንም በቃላትና በንድፈ ሃሳብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በተግባርም በረሃ ዉስጥ ገብቶ መሬት ላይ እየተኛ ያሳየን የተግባር ሰዉ ነዉ። ዛሬ የወያኔ ዘረኞች አንዳርጋቸዉን አስረዉ የሚያሰቃዩት የአንዳርጋቸዉ ዕቅድና የጀመራቸዉ ስራዎች የእነሱን ቆሻሻ ስርዐት ጠራርጎ ኢትዮጵያን እንደሚያጸዳ ከወዲሁ ስለተረዱ ብቻ ነዉ። በእርግጥም አንዳርጋቸዉ የሽብርተኞች ድርጅት መሪ ቢሆን ኖሮ ጨዋዉና አርቆ አስተዋዩ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያሸብረዉ ሰዉ ሲታሰር ደስታዉን ነዉ እንጂ ቁጣዉንና ሀዘኑን አይገልጽም ነበር። የአንዳርጋቸዉ መታሰርና አንደ ማዕበል ገንፍሎ የወጣዉ ህዝባዊ ቁጣ ወለል አድርጎ ያሳየን ነገር ቢኖር አትዮጵያ ዉስጥ አሸባሪዉ ማን እንደሆነ ነዉ።
ወያኔን የሚተካ ጤነኛ አካል ሳናዘጋጅ በጅምላ ወያኔ ይወገድ አንጂ ከዚያ በኋላ ያለዉ አይቸግርም የሚለዉ አባባል አደገኛ አባባል ነዉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ መስማማት አቅቶን ለእነዚህ የቀን ጅቦች የምንሰጣቸዉ ግዜና በየግላችን በተናጠል የምናደርገዉ ጉዞ አገራችን ኢትዮጵያን ከድጡ ወደ ማጡ ይዟት የሚሄድ አጅግ በጣም አደገኛ ጉዞ ነዉ። “እኔም አንዳርጋቸዉ ነኝ” ስንል እናት አገራችን ኢትዮጵያን ከእንደነዚህ አይነት አደጋዎች ለማዳን ምንም አይነት መስዋዕትነት ለመክፈል ተዘጋጅተናል ማለት ነዉ።
የለበስነዉ ልብስ ከመጠን በላይ ሲቆሽሽ ያለን ምርጫ የተዘጋጀ ቅያሪ ካለን እሱን ቀይረን የቆሸሸዉን ማጠብ ነዉ፤ ቅያሪ ካሌለን ግን አዲስ ልብስ መግዛት ነዉ ያለብን እንጂ መቼም ካላበድን በቀር በቆሻሻ የጀቦደ ልብስ ለብሰን አደባባይ አንወጣም። ከ1966ቱና ከ1983ቱ ታሪካዊ ስህተቶች የተማርን ኢትዮጵያዉያንም ማሰብና ማድረግ ያለብን እንደዚሁ ነዉ። ኢትዮጵያ ዉስጥ ያለዉ ስርዐት ከመጠን በላይ ቆሽሿልና በበረኪና ታጥቦ የሚጸዳ ከሆነ በፍጥነት መታጠብ አለበት፤ አለዚያም ወያኔን ከማስወገዱ ሂደት ጋር ጎን ለጎን የሚሄድ አዲስ ስርዐት በጋራ መገንባት እንዳለብን ለአፍታም ቢሆን ልንዘነጋዉ የማይገባን ኢትዮጵያዊ አደራ ነዉ።
ዛሬ እጁ በዘረኞች ተይዞ የሚሰቃየዉ አንዳርጋቸዉ ጽጌ የኑሮ ጓደኛዉን፤ አንድ ፍሬ ልጆቹንና ወንድሞቹን ትቶ ከሞቀዉ የአዉሮፓ ኑሮ በረሃ ወርዶ የማደራጀትና የማስተባበር ስራ መስራት የጀመረዉ እነዚህ ከላይ የጠቀስናቸዉን የአገራቸን ዉስብስብ ችግሮች በሚገባ ስለተገነዘበና ያለፉት ስህተቶቻቸን ላለመድገም የቆረጠ ሰዉ ስለሆነ ነዉ። አንዳርጋቸዉ ከታሪክ እንማር ሲል የፍትህና የዲሞክራሲ ትግላችን አላማና ግብ ወያኔን መጣል ብቻ ሳይሆን ካሁን በኋላ በሰላምና በእኩልነት ሊያኖረን የሚችል ስርዐትም መገንባት አለብን ማለቱ ነዉ። አንዳርጋቸዉ ፍትህ የምንለዉ ጽንሰ ሃሳብ ከኢትዮጵያዊ ማንነታችን ጋር የተቆራኘ ነዉ ሲል ይህንን ከማንነታችን ጋር የተቆራኘ ትልቅና እጅግ በጣም አስፈላጊ ማህበራዊ እሴት በዘረኞች ተቀምተን እንኳን ሃያ ሦስት አመት አንድ ምሽትስ ቢሆን እንዴት ተኝተን እናድራለን ማለቱ ነዉ። አንዳርጋቸዉ ለአገራችን አንድነትና ለዲሞክራሲ መብታችን መከበር እስከ ሞት ድረስ መሄድ አለብን ሲል ዲሞክራሲ ያልሞረደዉ አንድነት ወይም አንድነት ያልሞረደዉ ዲሞክራሲ እስካልገነባን ድረስ ትግላችን አያቆምም ማለቱ ነዉ።
ዛሬ በአለም ዙሪያ በአራቱም ማዕዘን ኢትዮጵያዉያን “እኔም አንዳርጋቸዉ ነኝ” በሚለዉ መፈክር ዙሪያ የተሰባሰቡት የአንዳርጋችዉ አላማና የአርባ አመት ጉዞ የእነሱም አላማና የወደፊት ጉዞ ነዉ ብለዉ ስለሚያምኑ ነዉ። “እኔም አንዳርጋቸዉ ነኝ” ማለት እኔም ልክ እንደ አንዳርጋቸዉ ጽጌ፤ እንደ እስክንድር ነጋ፤ ሠላማዊት ሞላ፤ በቀለ ገርባ፤ አንዱአለም አራጌና ዞን ናይን ብሎገርስ የመብት፤ የነጻነት፤ እኩልነትና የአገር አንድነት ጉዳይ ያንገበግበኛልና ለእነዚህ እሴቶች መከበር እኔም አንደነዚህ ጀግኖች ኢትዮጰያዉያን መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነኝ ማለት ነዉ።በአለማዉ የሚጸና፤ ለአላማዉ ግብ መምታት የተዘጋጀና በህይወቱ የቆረጠን ሰዉ ደግሞ ከድል ወዲህ ማዶ የሚያቆመዉ ምንም ምድራዊ ኃይል የለም።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!
                                                                                         Posted By A.G

Tuesday 5 August 2014

“ስለእኔ አታልቅሱ!”(ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ )

  1. “ስለእኔ አታልቅሱ!”(ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ )
August 5, 2014
“ዋይ ዋይ ከሚሉና ሙሾ ከሚያወጡ ሴቶችና ከሕዝቡ እጅግ ብዙዎች ተከተሉት፡፡ ኢየሱስ ግን ወደ እነርሱ ዘወር ብሎ እንዲህ አለ፡- እናንተ የኢየሩሳሌም ልጆች ለእኔስ አታልቅሱልኝ፤ ዳሩ ግን፡- መካኖችና ያልወለዱ ማኀፀኖች፣ ያላጠቡ ጡቶችም ብፁአን ናቸው የሚሉበት ጊዜ እነሆ ይመጣልና ለራሳችሁና ለልጆቻችሁ አልቅሱ፡፡” (የሉቃስ ወንጌል ም. 23 ቁ. 27-30) ከቅዱስ መጽሐፉ ይህን የመሲሁ የመጨረሻ ምክር የመረጥኩት (ምንም እንኳ ረቢው የተናገረው ስለመለኮታዊው ትምህርት ቢሆንም) ዓለማዊው ፍች የኢትዮጵያችንን የወቅቱን መንፈስ ለመረዳት ከማስቻሉም በዘለለ፤ በየጊዜው እያየን፣ እየሰማን ያለነውን የፖለቲካ ተቃውሞው የጥምዝምዞሽ መንገድ በአርምሞ ለመመርመር መልካም ምሳሌ ይሆናል በሚል እሳቤም ነው፡፡ 

የሠላማዊ ትግሉ መቀልበሻ ስልቶች
እፍኝ በማይሞሉ ፋኖዎች ከአርባ ዓመታት በፊት “ደደቢት” በተሰኘ የሰሜን በርሃ የተመሰረተው ህወሓት ከተራዘመ የትግል ጉዙ በኋላ፤ ታጋይ ሕላዊ ዮሴፍ “እልፍ ሆነናል” እንዲል፤ ራሱን አጠናክሮ “እልፍ” በመሆን ሥልጣን ይዞ፣ የሀገሪቷን አንጡራ-ሀብት አመራሩ መምነሽነሺያው ካደረገ፣ እነሆ ሃያ ሶስት ዓመታት እንደዘበት ነጎዱ፡፡ ርግጥ ነው ይህች የዳንኪራ እና ፌሽታ ዘመን እውን ትሆን ዘንድ፣ የቡድኑ ዋና ዋና መሪዎችም ሆኑ መላው ታጋይ (የበረከቱ ተቋዳሽ ባይሆንም) በቃላት ሊገለፅ የማይችል የመከራ ዓመታትን በቆራጥነት ማሳለፋቸው የሚስተባበል ታሪክ አይደለም፡፡ ሥልጣን እጃቸው ከገባ በኋላም የአገር ጥቅም መገበርን ጨምሮ እየገደሉ፣ እያሰሩና እያሰደዱ… በሕዝብ ላይ ወደር የለሽ ጭካኔን በመፈፀም ዘላቂነቱን እንዲህ ስለማስረገጣቸውም ተወርቶ የተዘጋ አጀንዳ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ ይሁንና ከዕለት ዕለት እየመረረና እየከፋ የመጣው ይህ ኩነት፣ ምድሪቷ የአንድ እውነት መዝጊያና የአዲስ ዓመት ምዕራፍ መክፈቻ ላይ መድረሷን ስለማመላከቱ ለመመስከር ጠቢብነትን አይጠይቅም፤ የዘመኑ መንፈስ እያሰማን ያለው “ፋኖ ተሰማራ”ም የሶስተኛው አብዮት ደውል ስለመሆኑ ለመረዳት የቀደሙ ነብያቶችን ትንበያ መጠበቅ አያሻም፡፡
ገዥዎቻችን፣ መግደልና ማሰርን ሱፍ ለብሶ፣ ከረባት አስሮ፤ ጠዋት ወደ ቢሮ ተገብቶ፣ ማታ የሚወጣበት መደበኛ ሥራ ከማድረጋቸውም ባለፈ፣ የሥልጣን ግዛታቸውን እንዲህ ነቅተው (ታጥበውና ታጥነው) ባይጠብቁት ኖሮ፣ ለሃያ ሶስት ዓመት ቀርቶ፣ ለሃያ ሶስት ሰዓት እንኳን በቤተ-መንግስቱ መቆየት እንደማይችሉ አብጠርጥረው ያውቁታል፡፡ የዚህ ጽሑፍ ፍሬ-ሃሳብም በዚህ መልኩ የሥልጣን ዕድሜውን ገና የማቱሳላን ያህል ማራዘም የሚፈልገው ኢህአዴግ፣ ተቃዋሚ ድርጅቶች የሚያቀነቅኑት የሠላማዊ ትግል አቅጣጫን የሚቀይስበትን እና የሚወስንበትን የሴራ ፖለቲካ፣ ለውጥ ፈላጊው ኢትዮጵያዊ ነቅቶ እንዲያከሽፈው መቀስቀስ ነው፡፡
ዛሬ በርካቶች በቁጭት እንደሚብሰለሰሉት ኢህአዴግ በመንበሩ ላይ ከሁለት አስርታት በላይ ተደላድሎ የመቆየቱ ምስጢር በውስጣዊ ጥንካሬው፣ አሊያም ሲቪል ጀግኖች በመጥፋታቸው ሳቢያ አይደለም (ወላድ በድባብ ትሂድና፤ ሀገሪቱ የሚሞትላት ጀግና ትውልድ ከመፍጠር መክና አታውቅም)፡፡ የግንባሩ ዋነኛ የጥንካሬ ምንጭ የተቃዋሚውንም ወገን የቤት ሥራ ጠቅልሎ እየሰራ በመሆኑ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ወደኋላ ሄደን በአደረጃጀትም ሆነ በድጋፍ መሰረታቸው ‹‹የተሻሉ›› ሊባሉ የሚችሉ ተቀናቃኝ ፓርቲዎችን ሂደት ብንመረምር፣ መራራውን እውነታ እየጎመዘዘንም ቢሆን መጋታችን አያጠራጥርም፡፡ ለማሳያ ያህልም በአገዛዙ የማስቀየሻ እርምጃ ተጠልፈው ከከሸፉ ሕዝባዊ ንቅናቄዎች መካከል ጥቂቶቹን በአዲስ መስመር እንመልከት፡  

ኦነግ

የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር፣ መለስ ዜናዊና ጓዶቹ ቆንጥረው ከሰጡት የሽግግር መንግስት ሥልጣኑ ተገፍቶ ከወጣ በኋላ ወደለመደው በርሃ በገባበት ወቅት፣ በአንፃራዊነት ቀድሞ መገንባት ከቻለው ጥንካሬ ባሻገር፣ በኦሮምኛ ተናጋሪው ማሕበረሰብ ዘንድ የሚሊዮኖችን ልብ ይበልጥ ማማለል ችሎ እንደነበረ የአደባባይ ሐቅ ነው፡፡ ወቅታዊውን የኃይል አሰላለፍ ጠንቅቆ የተረዳው “አባ መላ”ው ኢህአዴግም የጠብ-መንጃ ግብግቡ ከመጀመሩ አስቀድሞ፣ ከተማውን ለቆ ያልወጣውን የአመራር አባሉን ኢብሳ ጉተማን ወደ እስር ቤት ወረወረ፤ ይህንን ተከትሎም ኦነግ ከመቼውም ጊዜ በላይ በእልህና በቁጭት ተነሳስቶ አርሲና ሐረርን አስተባብሮ፣ ወለጋን በታንክ አቋርጦ፣ ባቱ ተራራን በመድፍ ጩኸት አንቀጥቅጦ፣ በባሌ ተሻግሮ ፊንፊኔ ላይ በድል ሊንጎማለል ነው ተብሎ ሲጠበቅ፤ በግልባጩ ዋና ፀሀፊው ሌንጮ ለታ እና የተወሰኑ መሪዎቹ በቦሌ በኩል በመመለስ “ወይ እኛንም አብራችሁ እሰሩን፤ አሊያም ጓደኛችንን መልሱልን?” በማለት ከመረጡት የኃይል ትግል ጋር የማይጣጣም ስልት ተግብረው አረፉት፤ በዚህም የልብ ልብ የተሰማው ኢህአዴግ፣ የድርጅቱን አባላትም ሆነ ኦሮምኛ ተናጋሪውን በጅምላ በ “ስመ-ኦነግ” እየወነጀለ ለአስከፊ እስር መዳረጉ፣ በክልሉ ላይ ከባድ ፍርሃት አነበረ፡፡ ይህ ፖለቲካዊ ስህተትም ለዛሬው ሽንፈቱ ዋነኛ ተጠቃሽ ሲሆን፤ የተቃውሞ ጎራ ትግሉንም ከሥርዓት ለውጥ ወደ እስረኛ ማስፈታት ያወረደ ቀዳሚ ኩነት ሆኖ በታሪክ ተከትቧል፡፡ 

መአሕድ
የፕ/ር አስራት ወልደየስ የመላው አማራ ሕዝብ ድርጅት (መአሕድ) ውድቀትም ከኦነግ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ መአሕድ በምስረታው ማግስት ያገኘው መጠነ-ሰፊ የሕዝብ ድጋፍ፣ ህወሓት/ኢህአዴግ በ17 ዓመታት ከሰበሰበው ሁሉ ይልቅ እንደነበረ አይዘነጋም፡፡ ይህ አይነቱ ፈጣን ግስጋሴም ሊያስከትለው የሚችለውን የቁጣ ናዳ አስቀድሞ የተረዳው ‹‹ብልጣ-ብልጡ›› ኢህአዴግ፣ ሊቀ-መንበሩን ጉምቱ የሕክምና ሊቅ ጨምሮ ጥቂት የአመራር አባላቱን እስር ቤት ወረወረ፡፡ ከዚያማ ድርጅቱ ‹‹እታገልለታለሁ›› የሚለውን የፖለቲካ ሥልጣን የመቆጣጠር ዓላማውን ‹‹መሪዎቻችን ይፈቱ!›› ወደሚል አኮስሶ ባለበት ሲረግጥና ሲዳክር ለ13 ዓመታት ከቆየ በኋላ፣ በስተመጨረሻ ህላዊነቱ አክትሞ ወደ ሕብረ-ብሔር (መኢአድ) ድርጅትነት መሸጋገሩ ታወጀ፡፡ ክስተቱም አብዮታዊው ግንባሩ የተቃውሞ ጎራውን እንቅስቃሴ ወደፈለገው አቅጣጫ መዘወሩን በሚገባ እንደተካነበት ያስረገጠ ሆኖ አልፏል፡፡ 

ቅንጅት
ዛሬ ዛሬ እንደ ንግስት ሳባ ዘመን የሩቅ ጊዜ ታሪክ ያህል ይሰማኝ የጀመረው ምርጫ 97ም ሌላኛው የነገረ-አውዱ አስረጂ ነው፡፡ በጥቂት ወራት ውስጥ ከጫፍ ጫፍ ሀገራዊ ንቅናቄ መፍጠር የቻለው ግዙፉ ቅንጅት በአብዛኞቹ የምርጫ ጣቢያዎች በይበልጥ ደግሞ በገጠር አካባቢዎች አሸናፊ መሆኑ በተለያዩ አጣሪ አካላት በመረጋገጡ፤ የኢህአዴግን‹‹መንግስት ለመመስረት የሚያስችለኝ ድምፅ አግኝቻለሁ›› ጨዋታን ከውስጥም ከውጭም አምኖ የተቀበለ አንድም እንኳ አልነበረም፡፡ በአዲስ አበባ አንዳንድ አካባቢዎች ይህንንዓይን ያወጣ ስርቆት በሠላማዊ መንገድ ለመቃወም በሞከሩ ዜጎች ላይ በተወሰደው ርህራሄ አልባ የኃይል እርምጃ በርካታ ንፁሀን ለህልፈት እና ለአካል ጉዳት ሲዳረጉ፣ በተወሰኑየክልል ከተሞች ደግሞ ከፍተኛ ሕዝባዊ ማጉረምረም ተፈጥሮ እንደነበረ ይታወሳል፡፡ ግና፣ ‹‹ብልሆቹ›› የኢህአዴግ ኤጲስ ቆጶሳት በተካኑት ስልት የቅንጅቱን መሪዎች ከያሉበትሰብስበው እስር ቤት ከተቱ፤ ትግሉም ከተነሳበት ‹‹የገጠሩ ወገኖቻችን ድምፅ ይመለስ!›› ወደ ‹‹መሪዎቻችን ይፈቱ!›› ቀኝ ኋላ ዞሮ፣ የሥርዓቱ ዕድሜ እንዲቀጥል ስለመፍቀዱ የእኔ ትውልድ የአይን ምስክር መሆኑ ርግጥ ነው፡፡ 

ሕዝበ-ሙስሊሙ
ለሶስት ዓመት ተመንፈቅ (ከ‹‹እፎይታ ጊዜ››ው በቀር) ካለማቋረጥ በተቀጣጠለው የሙስሊሙ ኃይማኖታዊ ነፃነትን የማስከበር ትግልም፣ የንቅናቄው አስተባባሪዎች ‹ቃሊቲ የታጎሩትን መሪዎች የማስፈታት ዓላማ በአራተኛነት የተያዘ ነው› ቢሉም (‹‹አህባሽን በግዴታ ማጥመቅ ይቁም››፣ ‹‹መጅሊሱ ወደ ሕዝቡ ይመለስ›› እና ‹‹ነፃ ሕዝባዊ ምርጫ ይካሄድ›› የሚሉት ሶስቱ መሪ ጥያቄዎች የተቃውሞ መነሾ እንደሆኑ ልብ ይሏል)፤ የሕዝበ-ሙስሊሙ በተለይም የቅርብ ጊዜዎቹ የመስጂዶቹ እምቢ-ባይነቶች፣ ሥርዓቱ ለማደነቃቀፍ (ዓላማውን ለማስቀየስ) ባዘጋጀው የ‹‹ይፈቱ›› ማዕቀፍ ስር የተገደበ የመምሰል አዝማሚያው ነው በዚህ አውድ እንድጠቅሰው ያስገደደኝ፡፡ በርግጥ የሁለት አስርታቱን የተቃውሞ ልምድ በቅጡ የመረመሩ የሚመስሉት የ‹‹ድምፃችን ይሰማ›› ወጣቶች፣ በዚህ የተለመደ የትግል ቅልበሳ ላለመጠለፍ የሚያደርጉት ብርቱ ሙከራ እንዳለ ብገነዘብም፣ ከቀደመው ‹‹ጥቁር ሽብር›› ወዲህ በቀጣይ በሚኖሩት የትግል ወቅቶች ዋነኛ የትግል ጥያቄያቸውን ነፃነታቸውን በማስከበር ማዕቀፍ ስር እንደሚያደራጁት አምናለሁ፡፡ 

ማልቀስስ ለማን?
በ1983ቱ የመንግስት ለውጥ ዓለም አቀፋዊው አውድ፣ ለሽፍቶቹ ስብስብ እርግማንም በረከትም ይዞ ነበር፡፡ እርግማኑ፣ በቀደመ-ፖለቲካዊ ዝማሜያቸው ዝግ ሶሻሊስት ሥርዓት መመስረት አለመቻላቸው ሲሆን፤ በረከቱ ደግሞ በረዥሙ የእርስ በእርስ ጦርነት ክፉኛ የተመታችውን አገር በተለይም ተቋሞቿን ለመገንባት ከሚያስፈልገው ጊዜ አኳያ የምዕራባውያኑን ‹‹ዕድል እንስጣቸው›› የድጋፍ ልብ ማግኘታቸው ነው፡፡ በእነ ሳሙኤል ሀንቲንግተን ‹‹መድበለ-ፓርቲ ሥርዓትን እርሱት፤ አውራ ፓርቲነት ያዋጣችኋል›› ምክረ- ሐሳብ አማካኝነት የወቅቱ ምዕራባውያን አለቆቻቸውን መንፈስ መረዳታቸውን ወደኋላ ስንገነዘብ፤ ቢያንስ እስከ 97 ድህረ-ምርጫ ውጥንቅጥ ድረስ በተጓዙበት የአምባ-ገነንነት መንገድ በጥብቅ አለመወገዛቸውን እንረዳለን፡፡ በአናቱም በህወሓትና መሰል ነፍጥ አንጋቢ የድህረ-ቀዝቃዛው ጦርነት ቡድኖች ላይ ተስፋ የነበራቸው ዓለም አቀፍ ተቋማት እና ምሁራንም ዘግይተውም ቢሆን ቡድኖቹ ወደ ቋሚ ሽፍትነት መቀየራቸውን ከመመልከት አልዳኑም፡፡ የዚህ አይነት ስብስብ ቋሚ መለዮ፣ በመሰረተ ልማት ግንባታዎች ላይ ሙሉ ሀገራዊ ሀብት ማፍሰስ ነው፤ መግፍኤውም ግልፅ ነው፤ የሕብረተሰቡ የአምራችነት ማሕበረ-ኢኮኖሚያዊ አቅም ሲጎለብት፣ እነርሱም የሚያግበሰብሱት ሀብት እየሰፋና እየበዛ እንዲሄድ የማስቻሉ ሀቅ ነው፤ እንደ ህወሓት ያሉ የነፃ-አውጪነት የኋላ ታሪክ ያላቸው ገዢ ቡድኖች፣ በምርጫ ፖለቲካ የማይነቀነቁባቸው ምክንያቶችም ከዚሁ ጋር ይተሳሰራል፤ ከሰላማዊ ሕዝባዊ ዓመፅ ውጪ ይህን ነውረኛ ቡድን ማስቆም እንደማይቻል በ‹‹ሕዳሴ አብዮት›› ርዕሰ-ጉዳይ ለመከራከር የሞከርኩትም ለዚሁ ነው፡፡ እንግዲህ ከእስክንድር ነጋ እስከ ርዕዮት አለሙ፤ ከውብሸት ታዬ እስከ የሱፍ ጌታቸው፤ ከአንዱአለም አራጌ እስከ በቀለ ገርባ፤ ከጦማሪያኑ እስከ እነ ሐብታሙ አያሌው… ድረስ ዘርዝረን የማንጨርሳቸው የእልፍ አእላፍ ለውጥ ፈላጊ ኢትዮጵያውያን መታሰር አሳዛኝ ቢሆንም፤ ለእነርሱም ሆነ ለሀገር የሚበጀው ‹‹ታጋይ እንጂ ትግል አይሞትም!›› የሚለውን የጊዜውን አስገዳጅ ሕዝባዊ ጥሪ በመቀበል አደባባዩን በቁጣ ማጥለቅለቅ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ዛሬ እያየነው እንዳለው የግፉአኑን መፈክር አንግቦ መነሳትን ገሸሽ አድርጎ፣ የ‹‹ይፈቱ›› ጥያቄ የትግሉን መንፈስ ይመራው ዘንድ መፍቀድ ሂደቱን ለሥርዓቱ ሴራ አሳልፎ እንደመስጠት የሚቆጠር ይመስለኛል፡፡
መግቢያዬ ላይ የጠቀስኩት የመምህሩ ቃል የሚነግረንም ለእነሱ ከማልቀስ ይልቅ፣ የአምባ-ገነኑን ሥርዓት ቀንበር ተሸክመን በአሳረ-ፍዳ ኑሮአችንን ስለምንገፋው ስለራሳችን ብናለቅስ የተሻለ መሆኑን ነው፡፡ ከዚህ ጎን ለጎንም አብዝተን ነፃነታቸውን የምንሻላቸው ጀግኖቻችን እንደምኞታችን ቢፈቱና መፃኢ ዕድላቸው ምን ሊሆን እንደሚችል ራሳችንን ብንጠይቅ፣ የምንፋጠጠው ‹ተመልሰው በኢህአዴግ የብረት ጫማ ስር ለጥ-ሰጥ ብሎ ማደር› ከሚል እውነታ ጋር ብቻ ነው፡፡የተለመደውን ‹‹የይቅርታ ቃጭል›› አጥልቀው፣ በተሰበረ መንፈስ ከትግሉ ርቀው አንደበታቸውን ሸብበው አሊያም ከሀገር ወጥተው ቀሪውን ህይወታቸውን በስደት እንዲያሳልፉ ከማድረግ ያለፈ የምንፈጥርላቸው ወይም የምናመቻችላቸው ምንም ነገር አለመኖሩ ርግጥ ነውና፡፡ ያውም ብርቱካን ሜደቅሳን ለቅቆ፤ ርእዮት ዓለሙን የሚያስርበትን የቆየ የፖለቲካ ጨዋታውን ሳንዘነጋ፡፡ ይህም ነው ሕዝብን የማዳመጥ አንዳችም ልምድ ለሌለው ሥርዓት ‹‹ይፈቱ!››፣ ‹‹ይለቀቁ!›› እያልን ከመጮኽ በመቆጠብ፣ ታሳሪዎቹ ስለተዋደቁባቸው የነፃነት እሴቶች መተግበር መታገልን ግድ ያደርገው፡፡
በጥቅሉ በመከራው ዳገት ላይ ያሉት ወገኖቻችን የገጠማቸውን ሁነት ያስነሳው፣ ማናችንም በነፃነትና በእኩልነት ልንኖርባት የምትገባዋን አገር የመናፈቅ እንደሆነ ከተስማማን ዘንዳ፣ በየእስር እርምጃው የተፈጠሩትን ክፍተቶች እየደፈንን፣ የነፃነቱን ቀን ለማቅረብ መታተር የወቅቱ አስገዳጅ ጉዳይ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ በቀድሞው የቅንጅት አመራሮች የገፍ እስር ማግስት፣ የከተሞቹን ንቅናቄዎች ከ‹‹ይፈቱልን›› ይልቅ፣ ‹‹ድምፃችን ይመለስልን!›› በሚለው መሠረታዊ ጥያቄ አጥብቀን ይዘን ትግላችንን ብናራዝመው ኖሮ፣ ፖለቲካዊ ለውጦችን መጨበጥ እንችል እንደነበር ማናችንም ብንሆን የምንጠራጠር አይመስለኝም፡፡ ከዚህ አኳያም የሚያስማማን ዋነኛ ጭብጥ፣ ቢያንስ የ2002ቱ ምርጫ በተካሄደበት አስቂኝ ድራማ ልክ ተከናውኖ እና ተቀልዶብን የማለፉ ዕድል እጅጉን ያነሰ የመሆኑ ጉዳይ ነበር፡፡
ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ ያየናቸው የጦማሪያኑና የሶስቱ ፓርቲዎች ወጣት አመራሮች እስር፣ በተለመደው የ‹‹ይፈቱ›› ደካማ የትግል ስልት የመሄድ ዳርዳርታውን ገርተን፣ ከአደባባዩ መራቃቸውን ተከትሎ እየተፈጠረ ያለ የሚመስለውን (ከማሕበራዊ ድረ-ገፆች እስከ የዕለት ተዕለት የፓርቲዎቹ እንቅስቃሴ ድረስ) ክፍተት መሻገሩ፣ የተሻለ ብቻም ሳይሆን ገዢዎቻችን እንድንሰምጥበት ከሚሹት የሽንፈት ማጥ ውስጥ ከመነከርም የሚገታ አማራጭ ነው፡፡
እነሆም ለማንስ ማልቀስ ይገባል? የሚለውን ጥያቄ መመለስ የሚያስፈልገን እንግዲህ በዚህ ከባድ ወቅት ላይ ነው፡፡ …እንደየተነሱበት አውድ ለሚያምኑባቸው ክቡድ ዕሴቶች ዘብጥያ ለተጣሉት ዜጎች መብሰልሰልን በመምረጥ ከጎናቸው መሰለፍን ላንገራገርነው ለኛ ማዘን የበለጠ የተገባ ነውና፣ እነርሱ ድርሻቸውን ስለመወጣታቸው እያመሰገንን፣ ፍትሃዊ አቋሞቻቸውን በገዘፈ ጉልበት ወደፊት መውሰድ ብቸኛው ምርጫችን መሆን ይኖርበታል፡፡ የ‹‹ሕዳሴው አብዮት›› ተግባሮትም አስፈላጊው ሥነ-ልቦና ይኸው ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ 

ድል ኢትዮጵያውያን ! 

Posted  by A.G