Sunday 11 May 2014

የአንድነታችን ደወል!! ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሊያነበው የሚገባ፡፡

የአንድነታችን ደወል!! 

ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሊያነበው የሚገባ፡፡
ተስፋ በላይነህ

አንድነት ከመቼውም በላይ እንደሚያስፈልገን ፤ አይደለም አሁን ላይ ወደኋላ ከመቶ ዓመታት በላይ ተጉዘን ብንመለከት እንኳ አስፈላጊነቱ ቁልጭ ብሎ የሚታይ ነው፡፡ ሸዋ፣ ወላይታ፣ ከፋ፣ ሶማልያ፣ትግሬ፣ጎጃም፣ ጎንደር ከመቶ ዓመታት በፊት አንድነትን ከሃይል በፊትም ሆነ በኋላ ቢሰብኩልን፤ At the surface level /ህዝቡ/ በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር መጠለል እየፈለገም ቢሆን የተነሳውና የፈረጠመው ገዥ ለማደብዘዝ ቢሞክርም፤ አንድነትን የመሰለ ጠቃሚ እና ብቸኛ አማራጭ አልተገኘም፡፡ በታሪካችን አንድነት የለም ብለን መደምደም የሚያስችል ልሳን የት አገኘን? የክህደት የቅጥፈት ልሳን እንደምን እንዲህ ተንሰራፋ? ኢህአዴግ በአብዮታዊ ዲሞክራሲና ልማታዊ መንግስት አስተሳሰብ እድገት ከትግል ጀምሮ፣ በሽግግር መንግስት ሂደት፣ በተሃድሶ ዋዜማ፣ በተሃድሶ እንቅስቃሴ ብሎ በሰየመው አራት ዓስርታት ውስጥ ልማት ቁልፍ መጠሪያ እና መዳረሻው እነደሆነ ሰብኮናል፡፡ ይህንንም በ24 ሰዓታት ውስጥ ከ24 ጊዜ በላይ እንድንሰማው በእቅዱ አቅርቧል፡፡ የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው እንዳለው ባል፤ ኢህአዴግም ከልምታዊ መንግስትነት መጠሪያ እስከ ታች ድረስ ልማታዊ ሌባን በሚያበረታታ መልኩ ማንነቱን የመሰከረበት ሂደቱ የማንክደው ሐቅ ነው፡፡ እስኪ ይህን ሐሳብ ማስረጃ እናቅርብበት ‹‹ለፍጆታ የሚውሉ የፍጆታ ዕቃዎች እስከ 12% የሚደርስ ጉቦ ይከፍሉ እንደነበር ታውቋል፡፡ ይህም ከመንግስት ኢኮኖሚያዊ ፓሊሲ ጋር የማይጋጭ የጉምሩክ ሰራተኞች የጣሉት የግል ግብር ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ሌባ ሣይቀር ሌብነቱን ልማትን በማይጎዳ መልኩ ለመፈጸም መሞከሩ የልማታዊነት አስተሳሰብ በህብረተሰቡ ውስጥ ምን ያህል ሰርፆ እንደነበር ሊያመለክት ይችላል፡፡ መንግስትም ህዝብም በልማታዊነት አላማ ዙሪያ በአንድ ልብ መሥራታቸው ለስራው ስኬታማነት አስተዋጽኦ እንዳበረከተ ጥርጥር የለውም፡፡ ገጽ 52 ይታያችሁ በተለይ ‹‹ሌባ ሳይቀር…›› ከሚለው ጀምራችሁ በድጋሜ አንብቡት…. ይህ እንግዲህ የተባለው ከዋናው ባለራዕይ መሪ ነው፡፡ በሌብነት የሚደገፍ ልማትንም እውቅና ከመስጠት ባሻገር ለአንድነት ተብሎ የሚደረግን የነገስታት ዘመቻ ቅኝ ግዛት ብሎ መፈረጅ፤ በሌብነት ልማት ላይ የተንጣለለን የምጣኔ ሐብት እድገት ምን ብለን እንፈርጀው? ሌባ ካልተያዘ ሌባ አይደለምን ልብ ይሏል!! በእጅጉ የሚገርመው ጥላቻው ከሰላማዊ/ከፍትሃዊ ልማቱ ሳይሆን ከአንድነቱ ነው፡፡ ይህንም በዚህቹ መጽሐፍ ላይ በሚገባ የምንመለከተው ነው፡፡ እንዲህ ይላል፡፡ “ተሃድሶውና የብሔር እኩልነት” በሚለው ንዑስ ርዕስ ስር በገጽ 99 እንዲህ ተቀምጧል፡፡ ካድሬዎች የታወረባቸውን የልብ ዓይን እንዲበራላቸው ተማጽነው ቢያበሩ እና ቢያነቡት ትልቅ እድገት የሚመጣ ይመስለኛል፡፡ ይህ ሁሉ የሚገኘው በባለራዕዩ መሪ በተጻፈው እና የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ዶግማ ወ ቀኖና ተብሎ ከሚነገረው ‹‹ልማት፣ ዴሞክራሲና አብዮታዊ ዴሞክራሲ›› መጽሐፍ ውስጥ ነው፡፡ ‹‹ኢህአዴግ መጀመሪያ መመለስ የነበረበት ጉዳይ የኢትዮጵያ ህዝቦች አንድነት ለምን ያስፈልጋል የሚለውን ጥያቄ ነበር፡፡ ›› /አንድነት ለምን እንደሚያስፈልግ መጠየቁ ምን አይነት ፍቺ አለው?/ ቀጠል ያደርግና ‹‹ይህንን ያህል ጊዜ አብረን የነበርን ስለሆን ለወደፊቱም አብረን መኖር አለብን ብሎ ታሪክን ያለፈው ሂደት መግለጫ ብቻ ሳይሆን የወደፊቱም ጉዞ የሚወስን አገር አድርጎ ማቅረብ የሚያስኬድ አይደለም፡፡ ታሪክ በራሱ ድርሻ ቢኖረውም ህዝቦች በዛሬውና በነገው ጉዳይ ላይ ተመስርተው እንጂ ያለፈውን ለማኖር ብቻ ብለው የሚወስኑት ነገር አይኖርም፡፡ በዚሁ ሂደት ህዝቡ ተዋውቋል፣ ተዋልዷል፣ ተሰባጥሮ መኖር ጀምሯል ስለዚህ አንድ ሆኖ መቀጠል አለበት ሚሉም አልጠፉም፡፡ ይህ ክስተት የራሱ ክብደት የሚሰጠው ቢሆንም፣ በእንደዚህ አይነት ሁኔታ መለያየት የራሱ ጣጣ ሊኖረው እንደሚችል ቢጠቁምም ለአንድነት በቂ ነው ሊባል አይችልም፡፡›› “በዛሬውና በነገው ጉዳይ ላይ ተመስርተው እንጂ ያለፈውን ለማኖር ብቻ ብለው የሚወስኑት ነገር አይኖርም…” የሚለው ሐሳብ የአባቶቻችንን ተጋድሎ ባለዕዳ የሚያደረግ ነው፡፡ ይህንን ሐሳብ ከፋሺሽት በቀር ማን ሰብከዋል?? ልብ ይበሉ፡፡ የመዋለድ፣የመተዋወቅ እና የመሰበጣጠር ትርጓሜ ኢትዮያዊነት መሆኑን ጸሐፊው እንደማይዘነጋው እንዳንሸወድ!! የመዋሃድ እና አድነትን የመፍጠር ማንነት ኢትዮያዊነት መሆኑን እንዳንክድ! ኢትዮጰያዊነት ለአንድነት መሰረት መሆኑ ባይጠቀስልን፣ ተድበስብሶ እና ተጨቁኖ ቢታለፍም አዳማዊነት/ሰብአዊነት ለአንድነት በቂ ምክንያትን ሊፈጥርልን ይችላል፡፡ በባቢሎን ውድቀት በደረሰው መለያየት/ቋንቋ፣ጎሳ…./ ላይ ተኮፋፍሰን/ተከፋፍለን ልዩነትን የምንሰብክ ከሆነ ከዲያቢሎስ ቁራጭነት የተለየ ስያሜ የሚያሰጠን ነገር አይኖርም፡፡ የሰው ልጅ በቀለም፣ በዘር፣ በቋንቋ እና በጎሳ ቢለያይ ‹‹የሰውነቱ›› ማንነት አንድ ሊያደርገው ይችላል፡፡ ፍትሃዊ፣ የሁሉም ዘር፣ ቋንቋ ጎሳ ስብጥር የሆነ መንግስታዊ አስተዳደር ከተፈጠረ ሊያበታትነን የሚችለው ምክንያት ምንድን ነው? ከኋላ ታሪካችን ውስጥ ያለያዩንን ህጸጾች እየጠቀስን አንድታችንን ከማናጋት እና የወደፊት እኛነታችንን ከማበላሸት ከኋላ ታሪካችን አንድነትን የሚፍሩብንን እሴቶች እየሰበክን አንድነትን ለምን አልመሰረትንም? አጼ ዮሐንስ በቦሩ ሜዳ የቆረጡትን ምላስ ሀውልት ከምንሰራ፣ አጼ ዮሐንስ አንገታቸውን የተቆረጡበትን ቦታ ሐውልት ብንሰራ አንድነታችን አይሰብክልንምን? አኖሌ ላይ ጡት እና እጅ ከምንገነባ አድዋ ላይ የአንድነታችንን ምስጢር ሐውልት ብንገነባ አይመረጥምን? ጣልያን አድዋን ሲያስብ እንደሚያንገፈግፈው ሁሉ እኛን ለምን አንገፈገፈን? አለም እየከዳው እና እየከደነው የሚሄደውን የአድዋን ድል በአፍሪካ አገራት ሁሉ ሐውልት ማስቆም ሲገባን አንድ የሚያደርገን በቂ ምክንያት የለም ብሎ መደምደም ኢትዮጵያዊነት ወይስ ጣልያናዊነት? አንድነታችንን እንደማይፈልጉት በግልጽ እየተነገረን እና ጊዜ እያሳየን እኛ ለምን አንድ አንሆንም? ከቦንጋ አድዋ የሚወስደው የንግድ መስመር ለአንድነታችን መሰረት ሆኖ ሊገነባ፣ ሊሰበክ እንዲሁም በርካታ የጥበብ ትሩፋቶች ሊለቀሙበት ሲገባው ለምን መስመሩ እንዲህ በእሾህ ታጠረብን? የአንድነታችን መሰረት ኋላቀርነትን ለማስወገድ ልማታዊነታችንን ለማስቀጠል ብሎ የሚሰብክ መሪ/ የሌባውን ልማታዊነትም ሳንዘነጋው/ ለዚህች አገር መሰረት ‹‹ትላንት ሳይሆን ዛሬ›› ብሎ መሸምጠጥ ‹‹የአንድነታችን መሰረትም ኢህአዴግ፣ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ነው!›› ብሎ ማፍጠጥ ምን የሚሉት የዘመን ውራጅ ነው? ከፋ፣ ቅማትን፣ ወይጦ፣ ወላይታ፣ ሲዳማ፣ ቦንጋ፣ አርሲ፣ ሸዋ፣ ጅጅጋ፣ ሀድያ፣ ሐረር፣ ጎንደር፣ መቀሌ፣ አስመራ፣ አፋር፣ ጎጃም፣ ወሎ፣ በአራቱ ብቻ ሳይሆን በስምንቱም ማዕዘን የምትገኝ ሰው መሰረትህ አዳም መሰረትህ ሰብኣዊነት፣ አንድነትህ ኢትዮጵያዊነት ነው!! ትላንትም ነበረ፣ ዛሬም አለ፣ ነገም የሚቀጥል ነው፡፡ የሚሰበክልንን ዘመነኛ ፖለቲካ ትተን አንድ ቀይ ደማችን፣ ስጋችን እና አጥንታችን በሰብኣዊነት መንፈስ ተዋህዶ አትዮጳዊነትን ሊፈጥርልን ይገባል!! እኔ ትግሬ ሆኘ ስለምን ኦሮምኛ ቋንቋን ለመቻል እና አንድ ለመሆን አይረዳኝም? ኢትዮጵያዊነት የኦሮሞት እና የትግራይነት ውህደት ነው!! “አማራ” እና ቅማንት ከሚያገናኛቸው እልፍ መስተጋብሮች አልፎ ልዩነቱ ለምን ተለይቶ ይሰበካል? ጎንደሬው ቅማንትኛ ለማጥናት እና ቅማንቱ ጎንደሬ ነኝ ብሎ መዋሃድን ለምን አልተሰበከም?? ነገሩ ሁሉ ግልጽ ነው! ጨቋኝ መሪዎቻችን የአንድነታችንን መሰረት እነደማይሰብኩልን 2 ዓስርታት መስክረውልናል፡፡ ከመቼውም የበለጠ የአንድነት ትርጉም እና ዘላለማዊ ዋጋ አሁን የምንንረዳበት ጊዜ ነው፡፡ ዋለልኝ መኮንን እንዲያ ጽፎ ያቀረበው የብሔር ጥያቄ የአንድነት መሰረት ቢታከልበት ኢትዮጵያ እንዲህ ባልተፈረካከሰች ነበር፡፡ አሁን ግልጽ ነው፡፡ የአንድነታችን መሰረት በተናጋ ቁጥር ገዥዎቻችን የጭቆና ወንበሮቻቸው ይበረታሉ፡፡ አንድነት አሁን ይደውላል!! ከተለያየን አለያዮቻችን በደወሉ ይጨፍራሉ፣ በእኛ እንባ እና ደም ይሰክራሉ… ኢትዮጵያ ትጮሃለች!! የአንድነታችን ደወል…!!

Posted by A.G

No comments:

Post a Comment