Tuesday 23 June 2015

አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ በወያኔ የታፈኑበትን አንደኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ በኖርዌይ፣ ኦስሎ ተካሄደ

June 23, 2015

የግንቦት 7 ዋና ፀሀፊ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ በየመን የፀጥታ ሃይሎች ታግተው ለዘረኛውና አፋኙ የወያኔ ቡድን ተላልፈው የተሰጡበትን አንደኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ በኖርዌይ ደረጃ የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ የድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ በወጣቶች ክፍል አስተባባሪነት በጁን 23/ 2015 በእንግሊዝ ኢምባሲ ፊት ለፊት እልህና ቁጭት የተሞላበት ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ ተካሂዷል።

በሰልፉ ላይ ከተለያዩ የኖርዌይ ከተሞች የተገኙ በርካታ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በኖርዌጅያን የሰአት አቆጣጠር ከ13፡30 ስዓት ጀምሮ ታላቋ ብርታኒያ ለዜጋዋ አቶ አንዳርጋቸው ልዩ ትኩረት አድርጋ ከዘረኛው ወያኔ ነጻ በማውጣት ወደ ቤተሰቡ እንዲመለስ ለማሳሰብ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው የነጻነት ታጋዩን አንዳርጋቸውን በተመለከተ የተለያዩ መፎክሮችን አሰምተዋል።
በዝግጅቱ ወቅት ከተሰሙት መፎክሮች መካከል “አንዳርጋቸው የነጻነት ታጋይ እንጂ አሸባሪ አይደለም” አንዳርጋቸው ነጻ ይወጣ ዘንድ እንግሊዝ ግፊት ታድርግ”፣ “በአንዳርጋቸው ላይ ለአንድ ዓመት ሙሉ እየደረሰበት ያለው የስቃይና የመከራ ዘመን ይብቃ”፣ እንግሊዝ ዜጋሽ የት ነው?”፣ “እንግሊዝ! ዜጋሽ አደጋ ውስጥ ነውና ደህንነትና ጥበቃ ያዝፈልገዋል፣ የህግ ከለላም እንዲሁ” “አዎ! እኛ ሁላችን አንዳርጋቸው ነን!” ነጻነት፣ ፍትህና ዲሞክራሲ ያስፈልገናል” በማለት ከፍተኛ ሀገራዊ ስሜት በተንጸባረቀበት መልኩ ጩኸታቸውን አሰምተዋል።

በመቀጠልም አርበኞች ግንቦት ሰባት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የታፈኑበትን አንደኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የተሰጠውን መግለጫ ለተሳታፊዎች በድምጽ ተነቧል። መግለጫውም የአቶ አንዳርጋቸው በወያኔ መታገት ንቅናቄው የበለጠ እንዲጠነክርና ከሌሎች ድርጅቶች ጋር ውህደት በመፍጠር ትግሉን ወደፊት እንዲሄድ አድርጎታል እንጂ ወያኔ እንዳሰበው ትግሉ ወደ ኋላ እንዳልቀረ ይጠቅሳል።
በመግለጫው ማጠቃለያም በአቶ አንዳርጋቸው ላይ በአፈናው የተነሳ የደረሰው መከራ ስቃይ ብቻ ሳይሆን በአሁኑ ጊዜ ለፍትህ ፣ ለእኩልነትና ለነፃነት በመቆማቸው በወያኔ አረመኔዎች ቁም ስቅላቸውን የሚያዩ በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎች ሰቆቃ የሚያበቃው የኢትዮጵያ ህዝብ ተባብሮ በሚያደርገው ሁለ ገብ ትግል በመሆኑ ማንኛችንም በአቶ አንዳርጋቸውም ሆነ በሌሎች ወገኖቻችን ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት እንደራሳችን አድርገን የሚሰማን ወገኖች በሙሉ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ከታፈኑበት አንድ አመት ወዲህ የተጀመረውን ተስፋ የሚሰጥ እንቅስቃሴ አጠናክረን ወደ ውጤት በማድረስ የመጪው ዘመን የህዝብ የፍትህ የእኩልነትና የነፃነት ተስፋ የሚለመልምበት የወያኔ አምባገነን ስርአት እድሜ የሚያጥርበት ዘመን እንዲሆን ሁላችንም የምንችለውን ሁሉ እንድናደርግ ወገናዊ ጥሪ አስተላልፈዋል።
በመጨረሻም በዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ የተዘጋጀውን ደብዳቤ በተወካዮች አማካኝነት ለኢምባሲው ከተሰጠ በኋላ የተለያዩ መፈክሮችን በማሰማት ዝግጅቱ በታቀደለት ስዓት በተሳካ ሁኔታ ተጠናቋል።

የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ የድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ

No comments:

Post a Comment