Monday 13 January 2014

ሕገ- መንግስት ወይስ ዶክመንተሪ ፊልም? (ተመስገን ደሳለኝ) ....መቼም አገዛዙ ዓለማዊ ፍላጎታቸውን እስካሟላላቸው ድረስ ሀገር፣ ሕገ-መንግስት፣ ሕሊና… ደንታ ሳይሰጧቸው ሕዝብን በማሸበር የስርዓቱ ዕድሜ ይረዝም ዘንድ ‹ከፍርሃት ጋር ወደፊት!!› ለማለት የማያመነቱ ሰዎችን በዙሪያው የኮለኮለው ለእንዲህ አይነቱ ጊዜ ነው፡፡ ምንጭ ኢትዮሚድያ 12 01 2014



አምስተኛው ዙር አገር አቀፍ ‹‹ምርጫ›› እንደወትሮው ሁሉ በቀጣዩ ዓመት ሊደረግ በዕቅድ ተይዟል፤ ወሬውም ከወዲሁ ለፖለቲካ ፍጆታነት እየዋለ ነው፤ ኢህአዴግም በበኩሉ ‹አውራ ፓርቲ›ነቱን ከቀደመው በበለጠ አጠናክሮ የሚቀጥልበትን ሴራ ፈትሎ በመግመድ ውሎ ማደሩን ገና በማለዳ እያቀላጠፈው መሆኑን እየታዘብን ነው፡፡ አቶ መለስ ዜናዊ (ከልቡ ባይሆንም) በ1996 ዓ.ም ወርሃ ሐምሌ ላይ በተደረገ የግንባሩ ጉባኤ ‹‹የሚቀጥለው ምርጫ እንከን-አልባ ይሆናል›› ሲል ‹ቃል› ገብቶ የነበር ቢሆንም፣ ከስድስት ዓመት በኋላ በተካሄደው አራተኛው ዙር ‹‹ምርጫ›› በግላጭ ‹እንከን-አልባ ድል› በሚል ሲቀይረው ቅንጣት ታህል ሀፍረት አልተሰማውም ነበር፡፡ ግና! ‹አንድ ለእናቱ› እንዲል አቤ ጎበኛ፣ የተቃውሞውን ስብስብ የምትወክል አንዲት ወንበር ሾልካ ወደ ምክር ቤቱ በመግባቷ፣ ፓርቲው ዛሬም ድረስ እንደ እግር እሳት እያንገበገበችው መሆኑን በተለያየ መንገድ እያሳየን ነው፡፡ 

 የሆነው ሆኖ ኢህአዴግ ከዚህ ትምህርት በመውሰድ በሚቀጥለው ዓመት በሚደረግው ‹‹ምርጫ›› እንዲህ አይነት‹እንዝህላልነትን› ለማረም በከፍተኛ ዝግጅት መጠመዱን የሚጠቁሙ መረጃዎች እያፈተለኩ ነው፡፡ መቼም የጉዳዩ እውነትነት ከተረጋገጠ፣ ምናልባትም በ2012 ዓ.ም ልክ እንደ ኤርትራ ወይም እንደ ቻይና ‹ልማታዊ መንግስት እንጂ ምርጫ የሚባል ነገር አያስፈልግም! የምርጫ ፖለቲካ የኒዎ-ሊበራሊስቶች አጀንዳ ነውና!!› ከማለት የሚመለስ አይመስለኝም፡፡ ማን ያውቃል? …እንዲህ እንደዛሬው የሶስት ሺ ዓመት ታሪክ ያላትን እና የዘጠና ሚሊዮን ሕዝብ አገርን ፍርሃት በመንዛት አሸንፎ ከቆየ የምናየው ይሆናል፡፡ 

 ከዚህ ባለፈ ቀጣዩን ‹‹ምርጫ›› በፍፁማዊ ጠቅላይነት ለመጨረስ እያደረገ ያለው መሰናዶ በሶስት የተከፈለ ነው፤

 የመጀመሪያው ለመላው የድርጅቱ አባላት (የመንግስታዊ ተቋማት ኃላፊዎችን ጨምሮ) የተዘጋጀው ፓኬጅ ነው (ሰሞኑን በተለያዩ ከተሞች ስለ ‹አውራ ፓርቲ› አስፈላጊነት እና የ‹ልማታዊ መንግስት›ን ጠቀሜታ በተመለከተ እየተሰጠ ያለው ሥልጠናም የዚሁ አካል እንደሆነ ሰምቻለሁ)፤ 

ሁለተኛው መራጩ ሕዝብ ላይ በተናጥል አተኩሮ ለመተግበር እየተሞከረ ካለው ቀመር ጋር የሚያያዝ ሲሆን፤ ይህም እንደ ቀድሞው ሁሉ ለአቅመ-ምርጫ የደረሰውን ህዝብ በኮንዶሚንየም፣ በመልካም አስተዳደር እና በማይጨበጡ የተስፋ ፕሮፓጋንዳዎች ማማለልን የሚያካትት ነው፤ የመጨረሻው ደግሞ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና የግሉ የህትመት ሚዲያ ላይ ያነጣጥራል፤ በዚህ ፅሁፍም አጀንዳ የምናደርገው አገዛዙ በዚህኛው ግንባር ከሚያስወነጭፋቸው የ‹ጦር መሳሪያዎች› በዋነኛነት በዘጋቢ ወይም በዶክመንተሪ መልክ የሚያዘጋጃቸው ፊልሞችን የተመለከተ ነው፡፡ 

 ስውሩ አጀንዳ… 

 በርግጥ ይህ አይነቱ አሰራር ዛሬ የተጀመረ አይደለም፤ ባለፉት ሃያ ዓመታት በሙሉ ሲተገበር የነበረ ነው፡፡ በተለይ ሕዝባዊ ተቃውሞን የመሰለ ለሥልጣን የሚያሰጋ ድንገቴ አጋጣሚ ሲከሰት የሚመረቱት ፊልሞች ቁጥርም እንዲሁ ይጨምራል፤ እንደ ምሳሌም የ1993ቱን የህወሓት ክፍፍልን ተከትሎ በየአካባቢው የሕዝብ ማጉረምረም በበረታበት ወቅት፣ የሰሜን አፍሪካ አብዮት በጋመበት ማግስት እና የእስልምና እምነት ተከታዮች ሕገ-መንግስታዊው የኃይማኖት ነፃነት እንዲከበርላቸው በአደባባይ በጠየቁባቸው ጊዜያት በ‹‹ዘጋቢ ትዕይንት›› ስም የተሰራጩትን ብቻ መመልከቱ በቂ ነው ብዬ አስባለሁ (በነገራችን ላይ እንዲህ አይነት ጭብጥ ያላቸው ፊልሞች ደራሲያን፣ የስርዓቱ ዋነኞች ‹ኤጲስ-ቆጶሳት› እንጂ ተቋሙ የሰበሰባቸው ብላቴና ልማታውያን ጋዜጠኞች አይደሉም) 

 ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የመረጃ ምንጮቼ እንዳረጋገጥኩት ‹ዶክመንተሪ ፊልሞች› የሚዘጋጁት በሁለት መንገድ ነው፤ የመጀመሪያው በኢቲቪ ባልደረቦች ሃሳብ አመንጪነት በፕሮፓጋንዳ ላይ የሚያተኩር ሲሆን፣ በሚመለከታቸው ባለሥልጣናት ይሁንታን ሲያገኝ እንዲተላለፍ የሚደረግ ነው፡፡ ሌላኛው ደግሞ፣ በጉምቱ የፓርቲው መሪዎች የጭብጥ አሰናጅነት ሙሉ ድራማው አልቆለት በቀጥታ አየር ላይ እንዲውል ወደ ጣቢያው የሚላከው ነው፡፡ በዚህ ዘውግ የሚመደቡት አብዛኛዎቹ ፊልሞች ተቃዋሚ ፓርቲዎችን፣ በግል ሚዲያ ላይ የተሰማሩ ጋዜጠኞችን፣ የኃይማኖት መሪዎችን እና ዓለም-አቀፍ ተቋማትን በመወንጀልና በመዝለፍ ላይ የሚያውጠነጥኑ ናቸው (የቅርቦቹን እንኳ ለማስታውስ ያህል ብንጠቅሳቸው ይህንኑ ያስረግጣሉ፡- ‹አዲስ አበባን እንደ ባግዳድ›፣ ‹አኬልዳማ›፣ ‹ጀሀዳዊ ሀረካት›፣ ‹ሽብርተኝነት በኢትዮጵያ› እና የመሳሰሉት) 

 በጥቅሉ እስከ 2004 ዓ.ም መገባደጃ ድረስ የእነዚህ ፊልሞች ደራሲ አቶ መለስ ዜናዊ የነበረ ሲሆን፤ ከእርሱ ህልፈት በኋላ የኮሚኒኬሽን መ/ቤት (ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የጠቅላይ ሚንስትሩ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር አማካሪዎች) በደህንነት እና ፀረ-ሽብር ግብረ ኃይል ስም እንደሚያዘጋጁት ውስጥ-አወቅ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ኢቲቪ በእንዲህ አይነት ጭብጥ ዙሪያ በሚያውጠነጥኑ ፊልሞች ላይ ምንም አይነት ተሳትፎ አያደርግም፤ ሳይቀንስና ሳይጨምር ለሕዝብ ማስተላለፍ አማራጭ ያልተተወለት ብቸኛ ግዴታው ነው፤ የህወሓቱ ሰው ገራገሩ የተቋሙ ስራ አስኪያጅ ዘርዓይ አስግዶምም ቢሆን ይህ ኃላፊነት ሲሰጠው ትጉህ አገልጋይነቱ ለማን እንደሆነ ጠንቅቆ ያውቀዋልና፣ 

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በፍፁም ፈቃደኝነት ሥራውን ከማሳለጥ በቀር የሚቃወምበት ወይም የኤዲቶሪያል ነፃነቴን አላስገፋም ብሎ የሚቀብጥበት አንዳችምክንያት የለውም፡፡ በግልባጩ ውዳሴ መለስ፣ ስደት፣ የአባይ ቁጭት፣ የኮንዶሚንየም ቤቶችንና መሰል ጉዳዮችን በተመለከተ ደግሞ ሩቅአላሚዎቹ ‹‹ልማታዊ ጋዜጠኞች››፣ እንቅልፍ አጥተው የሚጨነቁበትና እርስ በእርስ ለመቀዳደም የሚተጉበት አጀንዳ ስለመሆኑ ራሱ በረከት ስምዖንም ገና ድሮ የገባው ይመስለኛል (በነገራችን ላይ በየጊዜው ጥቂት የጣቢያው የተለያዩ ፕሮግራም አዘጋጆች እና የዘጋቢ ፊልም ባለሙያዎች የቻይናን የሚዲያ ተሞክሮ አጥንተው እንዲመጡ እንደሚደረግ ይታወቃል) 

 ለዚህ ፅሁፍም እንደ ማሳያ የምጠቅሰው፣ ባለፈው ሳምንት ‹‹ሽብርተኝነት በኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ ለተመልካች የቀረበው ዘጋቢ ፊልም፣ ሙሉ በሙሉ በብሔራዊ መረጃ መ/ቤት ስም የተዘጋጀ ሲሆን፣ በንባብ የተሳተፉት ሁለቱ ‹‹ጋዜጠኞች››ም የኢቲቪ መደበኛ ባልደረቦች እንዳልሆኑ ከምንጮቼ አረጋግጫለሁ፡፡ ምንም እንኳ የፊልሙ ‹ባለቤት› የሆነው የደህንነት ቢሮ በሽብርተኝነት ዙሪያ የሚያውጠነጥን ነው ቢለንም፣ እንዲተላለፍ የተፈለገው ዋነኛ መልዕክት በቀጥታ ከቀጣዩ ምርጫ ጋር የተያየዘ ነው ወደሚል ጠርዝ የሚገፉንን ማሳያዎች መምዘዝ የሚቻል ይመስለኛል፡፡ እንዴት ሆኖ? የሚለውን ጥያቄ በአዲስ ርዕስ ሥር እናፍታታው፡፡ 

 ከፍርሃት ጋር ወደፊት! 


 በዚህ ፊልም ላይ ዋነኛ አጋፋሪ ሆነው የቀረቡት ሶስት ሰዎች ናቸው፤ የኮሚኒኬሽን ጽ/ቤት ሚኒስቴር ሚንስትር ዲኤታ ሽመልስ ከማል (ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በእንዲህ አይነት ፊልሞች ላይ የመሪ-ተዋናይነትን ገፀ-ባህሪ ወክሎ መጫወቱን እየተካነው እንደሆነ እኔም ራሴ እመሰክርለታለሁ¡)፣ የፌደራሉ ዋና ዓቃቢ-ሕግ ብርሃኑ ወንድማገኝ እና አቶ ዘሪሁን ተሾመ (ይህ ሰው ደግሞ አሉባልታና ጠቀሜታቸው ረብ-የለሽ የሆነ ወሬዎችን በማቅረብ የሚታወቀው የ‹ዛሚ-90.7› ሬዲዮ ባለቤት ሚሚ ስብሃቱ የትዳር አጋር ነው) ከትዕይንቱ መካከል የሚታወሱ ፊቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ድራማው ተጀምሮ እስኪያልቅ ድረስ ተሰፍሮ የተሰጣቸውንና በፈጠራ ታሪክ የተሞላውን ‹ስክሪፕት› ቃል-በቃል ሸምድደው መምጣታቸውን በግልፅ በሚያሳይ መልኩ ሲያነበንቡ ላስተዋላቸው ተመልካች ‹‹ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች›› የጣሉባቸውን ግዴታ በቁርጠኝነት ለማስፈፀም ‹ቀራኒዮ› ድረስ የሚጓዙ ሊመስለው ቢችል አይፈረድበትም¡ መቼም አገዛዙ ዓለማዊ ፍላጎታቸውን እስካሟላላቸው ድረስ ሀገር፣ ሕገ-መንግስት፣ ሕሊና… ደንታ ሳይሰጧቸው ሕዝብን በማሸበር የስርዓቱ ዕድሜ ይረዝም ዘንድ ‹ከፍርሃት ጋር ወደፊት!!› ለማለት የማያመነቱ ሰዎችን በዙሪያው የኮለኮለው ለእንዲህ አይነቱ ጊዜ ነው፡፡ 

 የሆነው ሆኖ ፊልሙ ከቀድሞዎቹ አንፃር እንኳ ሲመዘን የወረደና አሰልቺ ቢሆንም፣ ያን ያህል ከተደሰኮረለት የ‹‹ሽብርተኝነት ጉዳይ›› ባሻገር ሁለት ያደፈጡ ስውር ዓላማዎች ያሉት ይመስለኛልና፣ እነርሱን ነጣጥለን እንመልከት፡፡ 

 ፩ 
 የቀደሙ ልምዶችን ተንተርሰን ስናብሰለስለው፣ የዘጋቢ ትዕይንቱ ድብቅ ዓላማ ተደርጎ ሊጠቀስ የሚችለው የመጀመሪያው የቢሆን ሃሳብ፣ ኢህአዴግ ከምርጫው መዳረሻ በፊት በተቃውሞ ፖለቲካው ውስጥ ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ ያሉ የተወሰኑ የአመራር አባላትን እና ጥቂት ጋዜጠኞችን እንደተለመደው ከግንቦት 7 ጋር አቆራኝቶ ለማሰር እየተዘጋጀ ነው የሚል ይሆናል፡፡ በርግጥም ይህንን መከራከሪያ ከመቀበል ሌላ አማራጭ የሚያሳጡ ሁለት ገፊ ምክንያቶች አሉ፤ አንዱ ፓርቲው ቀጣዩን ምርጫ ከትግል ዘመኑ ጀምሮ ይመራው ከነበረው ጉልበታሙ አቶ መለስ ውጪ የሚያደርገው መሆኑ ያሳደረበት ስጋት ወደ ጭፍን አምባገነንት እንዲቀየር ከማስገደድ አልፎ፣ ይህንኑ የሰውየውን ህልፈት ተከትሎ የተከሰተው የኃይል መከፋፈል ያነበረው የመሳሳት ተፅእኖ ይመስለኛል፤ እነዚህ ኩነቶችም ስርዓቱ ህልውናውን ካፀናበት አምባገነናዊ ባህሪው አኳያ ድንገቴ እርምጃ እንዲወስድ መግፋታቸው የሚጠበቅ ነው፡፡ 

 ሁለተኛው ደግሞ ካደረ ተሞክሮው የሚነሳ ነው፤ ይኸውም በ2002ቱ ምርጫ ዋዜማ በተልካሻ ምክንያት የአንድነት ለፍትሕና ዴሞክራሲ ሊቀ-መንበር የነበረችውን ብርቱካን ሚደቅሳን እስር ቤት በመክተት ፓርቲውን እና የተቃውሞ ደጋፊ ኃይሉን እስረኛ በማስፈታት አጀንዳ እንዲጠመድ ያደረገበት ስልት እና ሁነቱ የፈጠረው ማሕበረሰባዊ የፍርሃት ድባብ ያስገኘለት ጠቀሜታን ሊከልሰው መሞከሩ አይቀሬ መሆኑ ነው፡፡ በአናቱም በወቅቱ ከፍተኛ ተነባቢነት የነበራትን የ‹‹አዲስ ነገር›› ጋዜጣ አዘጋጆች ምርጫው አራት ወር ብቻ ሲቀረው በግልፅና ስውር ጫና ጋዜጣውን ዘግተው ከሀገር እንዲሰደዱ ያደረገበት መንገድም የዚሁ አፈና ጉትያ እንደነበረ አለመዘንጋቱ፣ በቅርብ ከሚፈጠሩ ተመሳሳይ ክስተቶች ጋር ለማያያዝ ያስችላል፡፡ 

 ፪ 
 ሌላኛው የዘጋቢ ፊልሙ ዓላማ በቀጣዩ ምርጫ ለውጥ ፈላጊውን የህብረተሰብ ክፍል ወደ ተቃውሞ ጎራ ሊያሰባስብና መነቃቃት ሊፈጥር ይችላል የሚል ብርቱ ጥርጣሬ ያሳደረበትን የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን (ኢሳት) ጣቢያን በመርገም (በሽመልስ ከማል አነጋገር ‹‹ውጉዝ ከመአርዮስ›› በማለት) የተቀናቃኝ ድምፆች በተከበበላቸው ሞገድ ብቻ እንዲሰሙ ማስገደድ ነው፡፡ ይህ ሁናቴ አገር ውስጥ ያሉ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች እና ጋዜጠኞች ለጣቢያው ቃለ-ምልልስ እንዳይሰጡ በፍርሃት ቆፈን መሸበብንም ያከተተ ነው፡፡ 
አስደንጋጩ ጉዳይ ደግሞ መከራከሪያ ሆኖ የቀረበው ሕገ-መንግስታዊው ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ሳይሆን፣ ለሚዲያ ተቋሙ የብሶት መግለጫዎችን መስጠትም ሆነ ኢ-ፍትሀዊ አሰራርን ማጋለጥ በሽብርተኝነት እንደሚያስከስስ የሚተርክ ‹‹ዶክመንተሪ ፊልም›› መሆኑ ነው፡፡ በርግጥ ለዚህ ማስፈራሪያ እንደ መደገፊያ የተጠቀሙት ፀረ-ሽብር ሕጉ በግብረ-አበርነት ተጠያቂ የሚያደርግበትንየተለጣጭነት ባህሪውን አፅንኦት በመስጠት እንደነበረ ታዝበናል፡፡

 በፊልሙ ላይ አቶ ዘሪሁን ምሬት በዋጠው ድምፅ ‹‹ኢሳት የግንቦት 7 ወፍጮ ነው!›› የሚል መፈክር ሲያሰማ፣ ሽመልስ ከማል ደግሞ የአዋጁ ዋነኛ ዓላማ ከዚህ ቀደም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ‹አሸባሪ› ተብለው ከተፈረጁት ድርጅቶች ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንዳይኖር ለማድረግ እንደሆነ ምሎ-እየተገዘተ ተመልካቹን በፍርሃት ለማንበድበድ ሲሞክር ተስተውሏል፡፡ ይሁንና የአቶ 
ሽመልስን እርግጠኛነት ለማመን አመክንዮ መጠቀም የግድ ይሆናል፤ እናም ኢሳት የእነዚህ ድርጅቶች ዓላማ አራማጅ መሆኑን ለማሳየት ምን ተጨባጭ ማስረጃ አቀረባችሁ? ለሚለው ጥያቄ እየነገሩን ካለው እንቶ-ፈንቶ ባለፈ በማስረጃ የተደገፈ መልስ መስጠት የሚኖርባቸው ይመስለኛል፡፡ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የኤርትራ መንግስት ከሰጠው አምስት መቶ ሺህ ዶላር ውስጥ ሁለት መቶ ሺውን ለኢሳት ሥራ ማኪያሄጃ እንዲውል መወሰኑን በስልክ ሲናገር ከማሰማት በዘለለ ማለቴ ነው፡፡ 

 እግረ-መንገድ ለመጥቀስ ያህል የዚህ ፅሁፍ ዓላማ ኢሳትን መንግስት ለምን ወነጀለው በሚል ግብረ-መልስ መስጠት አለመሆኑን 
ማስገንዘቡ አስፈላጊ ይመስለኛል፤ መነሻ ምክንያቴ እንደ ሚዲያ ተቋምነቱ ከእኔ ሞያ ጋር በቀጥታ መገናኘቱ ሲሆን፤ ለምን ይህ ሆነ? 
ያልኩበት ተጠየቅም የሕግ የበላይነት ጉዳይ ብቻ በመሆኑ ነው፡፡ ምክንያቱም የተመለከትነው ፕሮግራም ኢሳት እስከ ዛሬ ባሰራጨው ዘገባ ላይ ‹አሸባሪ› ሊያስብለው የሚያስችል ትዕዛዝ ያስተላለፈበትን ወይም ንፁሃን ኢትዮጵያውያንን በተጠመደ ፈንጂ ዶግ-አምድ እንዲሆኑ መቀስቀሱን የሚያጋልጥ ሳይሆን፣ በሰላማዊም ሆነ በትጥቅ ትግል ከተደራጁ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር አባላት ጋር ያደረገውን ቃለ-መጠይቅ ብቻ በመደጋገም ነው፡፡ ለዚህም ይመስለኛል የዘጋቢ ፊልሙ ድብቅ ዓላማ ስርዓቱ በሀገር ውስጥ ያሉትን ጥቂት የግል የሕትመት ሚዲያዎች በፈርጣማ የፖለቲካና ቢሮክራሲ ክንዱ ደቁሶ ካኮሰመነ በኋላ፣ በተወሰነ መልኩም ቢሆን ድምፅ ላጡት ድምፅ መሆን እየቻለ የመጣውን እና ለተፎካካሪ ፓርቲዎች አማራጭ የሚዲያ ምህዳር የፈጠረውን የቴሌቪዥን ጣቢያ ከተለመደው የአፈና መንገድ /ጃሚንግ/ በተለየ ስልት ከጨዋታ ውጪ ለማድረግና በቀጣዩ ምርጫ ‹አውራ ፓርቲ›ነቱን ለማስጠበቅ የሚያደርገው ዝግጅት ነው እንድንል 
የተገደድነው፡፡ 

 ከዚህ ቀደም እነ እስክንድር ነጋ በግንቦታ 7 አባልነት ተወንጅለው በታሰሩበት ወቅት አቶ መለስ ዜናዊ ለፓርላማው ‹‹ክምር ማስረጃ አለን›› ቢልም፣ ጉዳዩ ፍርድ ቤት ሲቀርብ ግን በጨበጣ እንደገባበት ማየታችን አደባባይ የወጣ ሀቅ ነበር፤ በርግጥም ማስረጃ ሆኖ የተቆጠረው ራሱ ያዘጋጀው ‹‹አኬልዳማ›› የሚል ‹‹ዘገቢ ፊልም›› እንደነበረ ስንመለከት፣ ይህ ስርዓት አስቀድሞ የተናገረበት ጉዳይ ስህተት መሆኑ እንዳይጋለጥ ምንም ነገር ከማድረግ እንደማይመለስ እንታዘባለን (በነገራችን ላይ በወቅቱ በፍትህ ጋዜጣ ‹‹አኬልዳማው! የአይሁድ ወይስ የኢህአዴግ?›› በሚል ርዕስ የዘገባውን ፈጠራነት በተጠናከረ ማስረጃ ለማጋለጥ ከተሞከረ በኋላ እንዲህ የሚል ምክር አዘል ቁም-ነገር ተላልፎ እንደ ነበር አይዘነጋም፡- 

‹‹ሆሊውድ የሚሰሩ አስፈሪ (ሆረር) ፊልሞች እንኳ ቢያንስ ከ16 ዓመት በታች ያሉ ልጆች እንዳያዩአቸው የሚከለክል ሕግ አለ፣ ኢቲቪ ግን የተበጠሰ አንገት፣ የተገነጠለ ክንድ፣ የተቆረጠ እጅ፣ የተፈረከሰ ጭንቅላት… እያሳየ፣ ‹13 ዓመት የሞላው ሕፃን በሙሉ ሊያየው ይችላል› ማለቱ ኃላፊነት የጎደለው አሰራር ነው›› 

 ባለፈው ሳምንት በቀረበው ፊልም ላይ ቢያንስ ይህ ሁኔታ ታርሞ ከ16 ዓመት በታች ያሉ ልጆች ሊያዩት እንደማይገባ ከሚያስጠነቅቅ መልዕክት ጋር መተላለፉ ስርዓቱ ምክር መስማት ጀመረ እንዴ? እንድንል የሚያጭር ነው፡፡ በርግጥም በሌሎች ጉዳዮችም እንዲህ ቢያዳምጡን ኖሮ፣ እየዋጣቸው ካለው ጥልቅ ጨለማ ራሳቸውን መታደግ የሚችሉበት በርካታ ዕድል ነበር፡፡) 

 የሆነው ሆኖ በዚህና መሰል ፊልሞች ላይ የሚነሳው ሌላው ለትዝብት የሚያጋልጠው ጉዳይ የደህንነት ተቋሙ ሁሉንም ዜጋ 
አብጠርጥሬ አውቃለሁ የሚለው ማንአህሎኝነቱ ነው፡፡ አስቂኙ ጉዳይ ግን በአዋጅ የተቋቋሙት የመረጃው መስሪያ ቤት እና የፀረ-ሽብር ግብረ-ኃይል፣ ያሻቸውን ዜጋ ቤት (በስውርም በግልፅም) መበርበር፣ ስልክ መጥለፍ፣ የኢ-ሜል እና የማሕበራዊ ሚዲያዎችን አካውንት ‹የሚስጥር ቁልፍ ቃላት› ሰብሮ መፈተሽ… ከሚያስችል ያልተገደበ ሥልጣን ጋር የሚንቀሳቀሱ ቢሆንም፣ ሽብርተኝነትን ለመከላከል እንደ አዋጭ መፍትሄ የወሰዱት ‹ዶክመንተሪ ፊልም›ን እስኪመስል ድረስ በሳምንት አንዴ መመልከቱ የተለመደ መሆኑ ነው፡፡ ርግጥ እንዲህ አይነት ትዕይንቶች ተጨማሪ ስርዓታዊ ጠቀሜታቸው ማህበራዊ ተቀባይነታቸው የጎላ ዜጎችን በስቅየት (ቶርቸር) እያንበረከኩ በቴሌቭዥን መስኮት አንገት አስደፍተው በማቅረብ ትውልዱ ተጠራጣሪና ድንጉጥ እንዲሆን ያላቸው አስተዋፆኦ አንዱ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ይህው ቃል በሚከሰሱት ንፁሀን ላይ ተመልሶ እንደ ማስረጃ ተቆጥሮ፣ ከአስር ዓመት እስከ ዕድሜ ልክ የሚደርስ ቅጣት በ‹ካንጋሮው› ፍርድ ቤት እንዲጣልባቸው የሚያደርገው ግፈኝነት ነው፡፡ ለዚህም ቅጥ ያጣ አምባገነንነት አይደፈሬ ሥልጣኑ የሰጠውና ገና ሲረቅቅ ጀምሮ ጠንካራ ተቃውሞ ሲቀርብበት የነበረውን የፀረ-ሽብር አዋጅን የሕጋዊነት ከለላ አድርጎ እየተባባሰ በመጣ መልኩ መጠቀሙን መቀጠሉ ነው፡፡ 
ከጥቂት ሳምንታት በፊት የታተመው ‹‹ኒውስ ዊክ›› መፅሄት ‹‹Ethiopia declares war on gay men›› በሚል ርዕስ ባስነበበው አደገኛ መጣጥፍ አዋጁን ያብጠለጠለበት ሀረግ የትችቶቹን ሙሉ መንፈስ የሚጠቀልል ይመስለኛልና እዚህ ጋር ልጥቀሰው፡- ‹‹የፀረ-ሽብር ሕጉ መንግስት ሽብርተኝነት ብሎ የሚያስበውን ጉዳይ በ‹መፃፍ፣ ማቀናበር፣ ማተም ወይም ማሰራጨት› የሚከሰውን ዜጋበሃያ ዓመታት እስር እንዲቀጣ ፈቅዶለታል፡፡›› 

 እነዚህን ነገሮች ጠቅልለን ስንመለከት ገዥው ፓርቲ ለሀገሪቱ ስጋት እንደሆነ የሚነግረንን ሽብርተኝነት ራሱ ባዘጋጀው ሕገ-መንግስት ሳይሆን፣ በዶክመንተሪ ፊልም ጎርፍ ለመግታት ነው የተዘጋጀው ወደሚል ጠርዝ ይገፋናል፡፡ በርግጥ የፓርቲው አላማ ሥልጣኑን መጠበቅ ነውና ሕገ-መንግስቱን ወዲያ ጥሎ ዘጋቢ ፊልሞች ላይ ቢንጠለጠል እንዴት ልንገረም እንችላለን?! 

 ወደ የፍርሃት ‹ሪፐብሊክ› 

ይህች መከረኛ ሀገር በደርግና በኢህአዴግ ከተሠጣት ቅጥያዎች አንዱ ‹‹ሪፐብሊክ›› የሚል እንደሆነ ይታወቃል (የደርጉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሲል፤ ይህኛው ደግሞ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ነች ይለናል)፡፡ ዝርዝር ሃተታውን ትተን ከዚህ ፅሁፍ አውድ አንፃር የሪፐብሊክን ብያኔ ሕዝባዊ መንግስትነት የሚል ትርጓሜ ሰጥተን ማለፍ ይበቃል፡፡ ይሁንና የተሻገርናቸው ሁለት አስርታት የሚያስረግጡት ብቸኛ እውነት ቢኖር ሀገሪቱ ከዚህ የተጠያቂ መንግስት ምስረታ ተፃራሪ የሆነውን መንገድ መምረጧን ነው፡፡ ከላይ ለማሳያነት የጠቀስኩት ዶክመንተሪ ፊልምም ሆነ ተያያዥ አፋኝ ሕጎቹ እና ፖለቲካዊ አተገባበራቸው በፍርሃት የሚርድ ማሕበረሰብ በመፍጠር፣ ቀጣይ አስርታቱን ካለአንዳች መደነቃቀፍ ረግጦ መግዛትን ዋነኛ ግብ ያደረጉ ናቸው፡፡ ይህን ተቋማዊነትን ተደግፎ የሚካሄደው መንግስታዊ ሽብር፣ በአንዳች ክስተት ብርክ በሚያናውጣቸው ዜጎች ማሕበረሰቡ እየተሞላ እንደሚሄድ ግልፅ ነው፤ ከፌደራላዊ ወደ ፍርሃት ሪፐብሊክ እየተደረገ ባለው በዚህ ጉዞ፣ ሀገሪቱን ከዝግመታዊ ሞት ለመታደግ የበረቱ መዳረሻቸውን ስርዓቱ አዘጋጅቷል፡፡ እናም ዋጋው ምንም ቢሆንም በአደባባዩ ላይ የሚደረግ የተቃውሞን እንቅስቃሴ፣ ኢህአዴግን ከሥልጣን የማውረድ ብቻ ከመሆን መታለፉን በሚገባ ልናስብበት እንደምንገደድ ይሰማኛል፡፡ እነርሱ ከሚቀጥለው ምርጫ በፊትም ሆነ በኋላ ሕዝባዊ ምህዳሩን ምንም አይነት የተቃውሞ ድምፅ የማይሰማበት ምድረ-በዳ ለማድረግ ይህን ያህል ርቀት መጓዛቸውን ስንመለከት ምርጫችን ሁለት ብቻ ይሆናል፡፡ ቀጣዩን ትውልድ በፍርሃት ሪፐብሊክ ውስጥ ትቶ ማለፍ፣ አሊያም አደባባዩን በጨኸት መሙላት፡፡ 



                                                                                      posted by A.G










No comments:

Post a Comment