Sunday 5 January 2014

ጨቅላዎች ሁካታ ! Source ECADF

ጨቅላዎች ሁካታ !

January 5, 2014
ከቴዎድሮስ ሐይሌ(tadyha@gmail.com)
ምንሊክ መጓዙን የምትጠይቁኝ፤
ፊትም አላለፈ ኋላም አይገኝ።
ካለፉት ሳምንታት ወዲህ የማንነት ቀውስ ዋግ እንደመታው አገዳ ያኮሰሳቸው የበታችነት ስነልቦናቸውን ታሪክ በማፍረስና ጀግኖችን በመዝለፍ የሚጠገን የመሰላቸው አንዳንድ ተማርን ነን ባይ ደካሞች ዛሬን በድቅድቅ የባርነት ጨለማ አሳራቸውን እያዩ ፤ በራሳቸው ላይ የተጫነውን የአገዛዝ የጭቆና ቀንበር ለማንሳት ብርቱ ጥረት ከማድረግ ይልቅ ወደኋላ ተጉዘው የነጻነትን ብርሃን ፤ የዘመናዊነትን ጎዳና፤ የአንድነትን መሠረት ከወረሪና ከተስፋፊ ቅኝ ገዠ አውሮፓውያን በብርቱ ታግለው የክብርን አክሊል፤ የኩራትን መንፈስ ያወረሱንን ደጋጎቹን አባቶች የሚያንጓጥጥ ከስደት ፤ ከረሃብና ፤ ከውርደት በዚህ ዘመን እንኳ ለራሱ መቀዳጀት ያልቻለ ደካማና ልፍስፍስ ህብረተሰብ ጀግኖች አባቶቻችንን ለመዝለፍ ሲንጠራራ ይበልጥ እየተዋረደ መሆኑን እንኳ አለመረዳቱ የሚያሳዝን ከመሆን አልፎ የዛችን ታላቅ ሃገር ኢትዮጽያዊ ዜጋ መጻዊ ሕላዌ ፈተና የሚደቅን በሌሎች ሃገሮች የታየው አይነት የእርስ በእርስ መተላለቅን የሚጋብዝ አደገኛ አካሄድ የጥቂት ጨቅላዎች ሁካታ ነው በሚል ልናልፈው ብንሞክርም እንኳ የዚህ የጥፋትና የጥላቻ ግብረሃይል ሃገሪቷን በሚመራው ወገን የጀርባ ድጋፍ ያለው በመሆኑ አሁን ባለው የጽንፈኝነት መንገድ ከቀጠለ የሚያስከትለው አደጋ ቀላል ባለመሆኑ በነዚህ ጨለምተኞች ዙሪያ ወገንን የማንቃት እንቅስቃሴ እንዲያግዝ ሁሉም የበኩሉን ማለት ይኖርበታል የሚል እምነት አለኝ ።Ethiopian king Atse Menelik
ውሃን ድንጋይ ያናግረዋል አበው እንዲሉ በአሮጌ የታሪክ ቡልኮ ተጀቡነው ዘመኑን መዋጀት ያልቻሉት በትላንትና የቅናትና ጥላቻ ችንካር ላይ ተቀርቅረው ዘመን ተቀባብሎ የለወጠውን በሃውርታዊ ውህድ ህብረተሰብ ለመበታተን በተጋነነና ሁን ተብሎ በተፈበረከ የጥላቻ ድርሰት ታውረው ለከፋፍለህ ግዛው ፋሽስታዊ የወንበዴዎች አገዛዝ ህዝብ ስቃዩ እንዲረዝም እያደረጉ ያሉት የምሁር ደንቆሮዎች ዘመናቸውን የፈጁበት የጥላቻ ጉዞ ጡረታም ሲወጡ ሊተዋቸው አለመቻሉ እጅግ የሚያሳዝን ከመሆኑም በላይ የግማሽ ክፍለ ዘመን የከሸፈና የዘቀጠ አስተሳሰባቸውን ለትውልድ ለማውረስ የተጀመረው መቃብር የመቆፈር ፖለቲካ አሳፋሪ ከመሆኑም በላይ ትርምስ የመፍጠር አላማ ያነገበ በመሆኑ አጀንዳቸው ውሃ የማይቋጥርና ፤ ለጆሮ የሚቆረፍድ ቢሆንም ልካቸውን እንዲያውቁና አደብ እንዲገዙ ለማድረግ እውነቱን ይነገራቸው ዘንድ ስልጡን በሆነ መንገድ መንገሩ ተገቢ ነው።
ታላቁን ገናናውንና በጥቁር ሕዝብ ዘንድ የነጻነት ጮራ ፈንጣቂ ሞራሉ ለተሰበረው ውርደት እንደመጎናጸፊያ ለደረበው ተስፋው ተሟጦ በባርነት እንደ እንስሳ እየተረገጠ መኖርን ህይወቱ አድርጎ አያሌ ዘመናትን ለተሻገረው ድፍን የአፍሪካ ህዝብ የነጻነት ተምሳሌት በመሆን የአባቶቹን ታሪክ የደገመው ጀግናው የጣሊያን ጌታ የንጉሶች ንጉስ (King of Kings) የሆነው እምዬ ምንሊክ በማንም ወፍ ዘራሽ መደዴ የባንዳ ልጆችና የማንነት ቀውስ ባኮሰሰው ታሪክ በራዠ እንደ ጥጃ መለመላውን ከመሄድ ሱሪ እንኳ ያጠለቀለትን ጥቁሩን አንበሳ ሲሰድብ ዉሎ ሲሰድብ ቢያድር ሀውልት ቢያቆም ድርሳናት ቢጠረዝ አንዲት ጋት ያህል ክብሩን ሊቀንስ የማይችል በመሆኑ በዚህ የክፋት አቦከብሬ የጫጫታ ተግባር ለተጠመዳችሁ መድረሻቸው ሃፍረት ነው።
የገናናውን ታላቅ የጥቁር ሕዝቦች ንጉስ የእምዬ ሚኒሊክ መቶኛ አመት እና የታላቁ አፍረካዊ የነጻነት ታጋይ የማንዴላ እረፍት መገጣጠም ያጫራቸው የሃሳብ ንትርኮች ውስጥ በራሳችን ሃገር ዜጎች ምኒልክን በማሰነስ ማንዴላን የማወደስ ስራ የተጠመዱ የእንግዴ ልጆች የዘነጉት ወጣቱ የጥበብ ሰው (እድሜውን ያርዝምልን በጥበብና በማስተዋል አምላክ ያቆይልን) ጥቁር ሰው በሚለው የሙዚቃ አልበሙ ያሰፈረውን ታላቅ አባባል ልዋስና ‘’ የፊቱ ከሌለ የለም የኋላው ‘’ እንዳለው የማዴላን የትግል መንፈስ ያጠነከረው ሞራሉን የገራው ጥቁር የነጭ አሽከር ነው የሚለውን ዘመናት የተሻገረውን ክፉ መንፈስ እንዲሰበር የረዳው ነጭም ጥቁርም እኩል በአርአያ እግዚያብሄር የተፈጠረ እኩልነትና ነጻነት የመቀዳጀት መብት ያለው ሰብዓዊ ፍጡር መሆኑን ከማን ተማረ ፈር ቀዳጁስ ማን ሆነና ! ለመሆኑ ከጥቁር የአፍሪካ አሃጉር ከኢትዮጽያ በስተቀር ማነው ነጻ የነበረው ከመላው የእስያ የአፍሪካና የካሪቢያን ሃገራት ውስጥ የትኛው መሪ ነው የአውሮፓን ቅኝ ገዠ ወራሪ ሃይል አሸንፎ ያንበረከከው ከምኒሊክ ሌላ ማን የሚጠቀሰ አለ ነው፤ ለዚህ ነው ሚኒሊክ የኢትዮጽያ ብቻ ሳይሆን የዓለም ጥቁር ህዝቦች የነጻነት ፋና ወጊ ነው የሚያስብለው ። የማንዴላ ብርታት ፤ የነማርቲን ሉተር ኪንግ ሞራል ፤ የነማርኮስ ጋርቪ ፤ የነጆሞኬንያታ ፤ የነነኩሩሃማ በጭቆናው ዘመን ለነበሩት ተራማጆችና ፓን አፍሪካኒስቶች የትግል መነሻ የሞራላቸው መዳረሻ አድዋ ላይ የተገኘው አኩሪ ድል እኮ ነው። ይህ ዛሬ ባሪያ ነበርን ተረገጥን ጡታችን ተቆረጠ ፤ሱሪያችን ወለቀ ፤ ተዋርደን ነበር ወዘተ የሚሉት መቃብር ቆፋሪ የድኩማን ግሪሳዎች የራሳቸው አልበቃ ብሎ ታላቁን የኦሮሞ ሕዝብ በዚህ የቆረፈደ አሮጌ የተረት ቡልኮ ለመጨመር መመኮራቸው ሃገር ወዳዶች ተረድተው ይህን ሴራ የፖለቲካና የዘር ልዩነት ሳንል ማክሸፍ ካልተቻለ ሊፈጥረው የሚችለው አደጋ ቀላል አለመሆኑን መገንዘብ ይኖርብናል ።
እነዚህ የመቶ አመት ሂሳብ ለማወራረድ በቧልት የተሞላ የታሪክ አዛባ የሚዝቁት ጥቂት የትላንት እስረኞች የዛሬም ተጨቋኞች ስለህብረተሰብ ጥንቅር ስለ ስነመንግስትና በአለም ውስጥ ያሉ ሃገራት በምን አይነት መንገድ የዛሬውን ቅርጽ ይዘው እንደወጡ ሊያውቁ የሚችሉበት የእውቀት አድማስ እንኳን ለምሁራን ለተራው ዜጋም ሊጠፋ የማይችል እውነት ሆኖ እያለ ህዝብን በህዝብ ላይ ለማነሳሳት በተዛባ መልኩ እየተረኩ ያለው አደገኛ ተረት ውሎ አድሮ እንወክለዋለን የሚሉትን ወገን አንገት የሚያስደፋና የማያኮራ የማይጠቅም በመሆኑ ከድርጊታቸው ቢታቀቡ መልካም ነው ። የአሁኒቷ አለም ሃገራት ከሞላ ጎደል አሁን የያዙትን ቅርጽ ይዘው እንዲገኙ ያደረጋቸው በጦርነትና በወረራ በተደረገ ደም አፋሳሽ በሆነ ወታደራዊ ንቅናቄ የመሆኑ እውነት በታሪክ የታወቀ ነው። በኢትዮጽያም የሆነው ይህው ነው። የኢትዮጽያ ደግሞ ከሌሎቹም በተለየ መልኩ የግዛት ወሰኗ ሰፊውን የአፍሪካን ቀንድ ያካለለ እንደነበር አያሌ የታሪክ ማስረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል። ኢትዮጽያ የግዛት ወሰኗን አስከብራና ነጻነቷን ጠብቃ ከመኖሯም በላይ ፍትህ የተጓደለባቸውን ህዝቦች ቀይ ባህር ተሻግራ የአሁኒቷ የመን ሃገረ ናግራን የሚኖሩ ወገኖችን ለመታደገ በአፄ ካሌብ ዘመን የተደረገው የድል ዘመቻ ኢትዮጽያ የአካባቢው ግዛቶች ባለቤት ከመሆኗም በላይ በአካባቢው ጂኦ ፖለቲካ ላይ የበላይነት የነበራት ሃያል ሃገር እንደነበረች ከታሪክ የሚረዳ ወገን አጼ ሚኒሊክ ከሰሜን ወደ ደቡብ ያደረጉት እንቅስቃሴ የቀደምት የአባቶቻቸውን የወሰን ግዛት የማስከበርን ታሪካዊ ሃላፊነት መወጣት እንጂ የዛሬዎቹ የፋሽስትና የባንዳ ርዝራዦችና ነጭ አምላኪ የታሪክ አተላዎች እንደሚቀባጥሩት የሚኒሊክ የደቡብ ወታደራዊ ንቅናቄ ወረራና ሌላ ሃገር ላይ የተደረገ ዘመቻ አለመሆኑን በብዙ ማስረጃ አቅርቦ ለመከራከር አዳጋች ባይሆንም የተጀመረው የጥላቻ ዘመቻ ኢትዮጽያዊነትን የካደ ስልጡን ውይይት የማያስተናግድ በጠባብነት የተመራ ጨለምተኝነት የነገሰበት በመሆኑ ሂደቱን በጥንቃቄ መከታተል ተገቢ ይመስለኛል።
የዛሬዎቹ የማንነት ቀውስ የደፈጠጣቸው በበታችነት የስነልቦና ደዌ የተጠቁት የምናባዊቷ ኦሮሚያ ደቀመዛሙርት በወያኔው የጥላቻና የተንኮል ታሪክ ጸሃፊ ተስፋዬ ገብረዓብ በተባለ ሃሳዊ ተፈብርኮና ተደርሶ የተሰጣቸውን የውርደት መድብል ታሪክ ብለው ትውልዱን በማደናገርና በቂም በቀል ተነስቶ እርስ በእርስ እንዲተላለቅ የጀመሩት ዘመቻ አስተዋዩ የኦሮሞ ሕዝብ ታሪኩንና ማንነቱን በቅጡ የሚያውቅ በመሆኑ በከሰሩ ኦነጎችና በተንበርካኪ የወያኔ ሎሌዎች የተጀመረው ሃገር አፍራሽ ዘመቻ ባለመተባበር እንደሚያከሽፈው የሚያጠራጥር ባይሆንም ይህን የባርነት መንፈስ የተጫናቸውን ታሪክ አርካሽ አልጫ ስብስብ ወደ ቀልቡ እንዲመለስ ለማስገንዘብ ጥቂተ ማለቱ ተገቢ ሲሆን ከዛ ባለፈ በወያኔ ምርኮኛ የደርግ አስር አለቆች የሚመራው ድኩማኑን የህወሃት አገልጋይ ኦህዴድ ሆነ ከ50 አመታት በላይ የአንድ ትውልድ እድሜ ያስቆጠረው ጡረተኛው የኦነግ ቡድን በአንድ ቀን ጀንበር መቶ ሃያ ሺ ጦሩን ያስማረከ ልፍስፍስና የተበታተነ የምሁር ሃይል በሚኒሊክ መቃብር ላይ ጡረታውን ላማስከበር የጀመረውን የጅል የወሬ ዘመቻ ፍጻሜው ከመሳቂያነት የማያልፍ በመሆኑ አጀንዳው ሳይንዛዛ በአጭር ዘግቶ የዚህን እኩይ ሴራ ቀማሪ በሆነው የወያኔን አገዛዝ ወደ ማስወገድ ትኩረታችንን ማድረጉ ላይ ሁሉንም ወገን ግንዛቤ ሊጨብጥ ይገባል።
ወገኖቼ በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ነጻ ከወጡ የአንደ ትውልድ ዘመን እንኳ ያልሞላቸው ሃገራት በአስተዳደር በኢኮኖሚና በስልጣኔ በልጠውን እኛ ግን ቢያንስ ሃሰባችንን እንኳ በነጻነት መግለጽ የማንችልበት ረሀብተኛ ስደተኛና በሃገሩም እስረኛ በሆንበት የውርደትና የጉስቁልና መቀመቅ ውስጥ መከራራችንን እያየን ያለን ህዝብ ሆነን ክብርን ኩራትን ሰው የመሆንን ጸጋ ትተውልን ያለፉትን አባቶች መልካም ስራቸውን አንግበን መጥፎ ስራቸውን ለታሪክ ትተን ከወደቅንበት ለመነሳት እጅ ለእጅ ተያይዘን መቆም ሲገባን በዘርና በጎጥ ተቧድኖ የእንካሰላምታ ግብግብ መግጠማችን ክብር የተውልንን አባቶች መስደብ ምን የሚባል ፖለቲካ ነው! ፋይዳውስ ምንድን ነው? ዛሬ በዚህ ዘመን ምን የተቀዳጀንው ነገር አለና ነው? ያሳዝናል በዓለም ቁጥር አንድ ከሆነ በምጽዋት ህይወቱን ከሚገፋ ህብረተሰብ የማይጠበቅ እንደ ህዝብ አሳፋሪ የታሪክ ጠርዝ ላይ ቆመናል። አፄ ሚሊክን በምንም አይነት ልሳን ብንሰድብ የጥቁር ሕዝብ ንጉስ የመሆናቸውን እውነት የአውሮፓ ሃያላንን የማንበርከኩን ሃቅ ማንም ቅናትና የበታችነት ስነልቦና የተጫናቸው እንጭጮች ጫጫታ ሊፍቀው አይችልም። ሃይለስላሴን ለማዋረድ የተነሳው ትውልድ ራሱ ተዋርዶ እርስ በእርስ ተባልቶ ማለቁን አይተናል። የተረፈውም ያራገበው አብዮት ተቀልብሶና ተሸንፎ በቁሙ በውርደትና በእስር ማቆ አይቶታል። ሃይለስላሴ ግን ከማክበርም አልፎ የሚያመልካቸው የጥቁር ሕዝብ እንዳይኖር ከቶስ ማድረግ የሚችለው ማነው? በዋልጌ ዜጋው የተዋረደው የሃይለስላሴ አጥንት እንደ አማልክት እንዲከብር ራስ ተፈሪያውያንና የካሪቢያንና የአፍሪካ ሕዝቦች ልብ ውስጥ የኩራት ሃውልቱን አኑሮ ይኖራል። በዘረኞችና በበታችነት ስነልቦና እስረኞች ንጉሰ ነገስት ሃይለስላሴ ብርቱ ጥረትና ትግል ለመመስረት የበቃው የአፍሪካ ህብረት የዚህን የአፍሪካ ኩራትና ሃዋርያ በገዛ ሃገሩ ሃውልቱ እንዳይቆም ቢደረግም ውለታቸውን ባልዘነጉ መላው ጥቁር ሕዝቦች የማይዘነጋ አሻራ ከማኖሩም በላይ በናይሮቢ ኬንያ በስሙ ጎዳና ተሰይሞ (Haile Selassie Avenue) ስሙ እንዳይጠራ ማስቀረት የሚችለው ማን ነው?።
የሻብያ ፍጥረት የወያኔ አሽከር የሆኑት አንዳንድ በአሮሞ ስም የሚነግዱት ተንበርካኪ የእንግዴ ልጆች ሳይወለድ የሞተው ሊሳካም ከቶም የማይችለው ተምኔታዊው የጽንፈኞቹ የህልም አለም ምናባዊቷ የኦሮሚያ ሉዓላዊነት እንደለመዱት በአሶሳ በወተር በአርባጉጉ በአሰቦት ሰውበላው ድርጅታቸው ኦነግ አሮጊቶችና ሴቶች ላይ የፈጸመውን የጭካኔ ተግባር እንደግመዋለን የሚለው የሜንጫ ፉከራቸው በዚህ ዘመን ለመድገም መሞከሩ ሊያስከትል የሚችለው ዋጋ ቀላል አለመሆኑን የሚረዱት ይመስለኛል ። ከዛ ባለፈ መቶ አመት ወደ ኋላ ተጉዘው የጀመሩት ተረትና እያቆሙ ያለው የተንኮል ሃውልት የሚኒሊክን ስም የሚያጎድፍ ከመሰላቸው በጣም ተሳስተዋል። ንጉስ ሚኒሊክ ጠላቱም የመሰከረለት ጀግናና ለአሸነፋቸው ምህረትን ማድረግ ልምዱ ያደረገ ለመሆኑ ለተሸናፊው ንጉስ ጦና እና ለምርኮኛው የፋሽስት ጣሊያን ጀነራሎች ያሳየው ምህረትና ደግነት ዓለም የመሰከረለት በመሆኑ ሚኒሊክን ለማሳነስ ጡት ቆረጣ የከተቱት ኦነጎች የዘነጉት ያለና የነበረ አጉል ባህልና ታሪካቸው እና ያፈሰሱት ደም ያልደረቀ በብዙ ማስረጃ የተደገፈ መረጃ ያለ በመሆኑ አጀንዳው ወደእናንተ ተመልሶ ክስም ሆነ ክርክር ለመክፈት ከበቂ በላይ በመሆኑ ባለፈ ጉዳይ መነታረኩ ሊጠቅማችሁ እንደማይችል ወገናዊ ምክሬንም ልገልጽ እወዳለሁ።
ታሪክ እንምዘዝ ከተባለም አይጠቅምም እንጂ ብዙ ነገሮች ማንሳት ይቻላል። እዚህ ላይ ከመቶ አመት በፊት በነበረው የአመለካከት ኋላ ቀርነት አንጻር በዘመኑ ይካሄድ ከነበረው አስገራሚ ነገር አንደ መጽሄት ላይ ያነበብኩትን ብቻ ጠቅሼ ማለፍ እወዳለሁ ፤ የጅማው ባላባት አባ ጅፋር በአስተዳደራቸው ዘመን አምስት ባርያ (በአምስት ሰዎች) በአስራሁለት ሶሎግ ውሻ እንደለወጡ የሚነገር ታሪክ ተጽፎ አይቻለሁ። ይህ ማለት እኝህ የጅማ ባላባት ከዘመኑ ከነበረው የአስተሳሰብ ሚዛን አንጻር እንደታላቅ ወንጀል ሊቆጠርና ሊያወግዛቸው የሚሞክር የዚህ ዘመን ሊቅ ቢኖር መሣቂያ ከመሆን አያልፍም። በዚያ ዘመን ባርያ መሸጥና መለወጥ ፋሽን የነበረበት የሰው ልጅ የአመለካከት አድማሱ ያልሰፋ በነበረበት በዚያ ግዜ የተደረጉትን በዛሬ ሚዛን እንለካ ከተባለ ማለቂያ ወደሌለው ትርምስ የሚከት በመሆኑ ታሪክን ለ ታሪክነቱ መተው ይገባል። ይህን መንገድ የተከተሉት የዛሬይቱ ልዕለ ሃያሏ አሜሪካ ትላንት የጥቁር ሕዝቦች የቁም መቃብር የሰቆቃ ምድር እንዳልነበረች ዛሬ ያንን አሮጌ ታሪክ ወደኋላ ትተው በፍቅርና በአንድነት የዓለም መሪ የሆኑበት አቅም ገንብተዋል ። ትላንት በጥቁር ወንድሞቻችን በባርነት ሰንሰለት ታስረው የገነቡት ቤተመንግስት ታሪክ ተለውጦ በቆዳ ቀለም ይሰጥ የነበረው የመሪነት ቦታ የሃሰብ የበላይነት መሰረት ባደረገ ዘመናዊ መስፈሪያ መለካት በመቻላቸው ያ ርኩስ ታሪክ ተሽሮ ይህው ተምሳሌትነቱ ለዓለም ያንጸባረቀው የፕሬዘደንት ኦባማ ምርጫ አይተናል። ኦባማ ኦቫል ቢሮ ውስጥ ተሰቅሎ የሚታየው የጆርጅ ዋሽንግተን ፎቶ ከተሰቀለበት የቆየው ለኦባማ ነገድ ለጥቁር አፍሪካውያን የተመቸ ሆኖ አልነበረም ፤ እንዲያውም ጆርጅ ዋሽንግተንና የቀደሙት ዝነኞቹ የሜሪካ መንግስት ቀራጮች አብዛኞቹ የባሪያ አሳዳሪዎች እንደነበሩ የሃገሪቱ ታሪክ ሰነድ ውስጥ በይፋ ተቀምጦ ይገኛል። ዛሬ ዲሞክራት መሆን የመሰልጠን ምልክት የመሆኑን ያህል ከዛሬ መቶ አመት በፊት የባሪያ አሳደሪ መሆን እንደ ዘመኑ አመለካከት የጨዋነት መግለጫ ነበር። ነጻነቱን ያስከበሩለት ክብሩን የጠበቁለት የዛሬው የኔ አልጫ ትውልድ የሚዘለፉት የፖለቲካ ጨቅላዎች የሚያውካኩባቸው የትላንት መሪዎቻችን ይህን አይነት ተግባር ያልነበራቸው ጀግንነትን ከሃይማኖት የተላበሱት የኢትዮጽያ ነገስታት የባሪያ ንግድን በአዎጅ ከልክለው ስለመኖራቸው ታሪክ ምስክር ነው።
በአሁኑ ወቅት በሃገራችን አጀንዳ በመፈብረክ የስልጣን እድሜውን ለማርዘም የማይፈነቅለው ድንጋይ እንደሌለ የተረጋገጠለትና ማናቸውንም አይነት እርምጃ በመውሰድ ለስልጣኑ ሕልውና ዘብ በመቆም ሃይማኖትን በሃይማኖት ብሄርን በብሄር በማናከስ የመጣበትን ተጽዕኖ ለማለፍ ዛሬን ብቻ በማየት ሃገር አፍራሽ በሆነ ተግባር የተጠመደው ታሪክ አርካሹ የሱዳን አሽከር የአረብ አገልጋይ የሆነው የወያኔ ማፍያ ቡድን ሰሞኑን ከጀርባ በመሆን ተላላኪዎቹን መቃብር እንደ ፍልፈል እያስቆፈረ የሚኒሊክን ዘመን አስታኮ የተጀመረው የፀረ አማራ ፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ተጠናክሮ የቴዲ አፍሮን የፍቅር የሙዚቃ ጉዞ ለማደናቀፍ ስፖንሰሩን ቢራ ጠማቂ ድርጅት በተጽዕኖ ስር በማዋል ጥቂት ጽንፈኛ የኦሮሞ ብሄርተኞችን በማነቃቃት እየተካሄደ ያለው ዘመቻ ወያኔዎች ያስደሰታቸው መሆኑን ከልሳኖቻቸው የሰሞኑ ዘገባ መረዳት ይቻላል። አበው የቆጡን አወርድ ብላ የብብቷን ጣለች እንዲሉ ወያኔዎች ኦሮሞውን በአማራው ላይ በማነሳሳት በዳር ተመልካችነት የሰላም ግዜ ለማግኘት እያቀናበረች ያለችው ሴራ በቀጣይ ምን ሊያስከትል እንደሚችልና የሚነደው እሳት ራሷን ወያኔንም ጭምር ይዞ ሊያወድም የሚችል መሆኑን ያልተረዱት የጥላቻ መንፈስ አይናቸውን የጋረዳቸው ወያኔዎች አማራውን ለማስጠቃትና ምኒልክን ለማወረድ የተነሳውን መንጋ ጽንፈኛ በልምድ ታጅቦ ወደ እነሱ የዘርና የሃይማኖት አጀንዳውን ይዞ ወደ እነሱ ሊመለስ እንደሚችል አለማረዳታቸው ምን ያህል የወያኔን የፖለቲካ ዘገምተኛነት የሚያሳይ ነው።
የተጀመረው ጉንጭ አልፋ ፖለቲካ መሬት ከረገጠ የጥላቻው ቅስቀሳ ወደ ግጭት ካመራ የአማራው ህዝብ ላለፉት 22 አመታት ታግሶና ችሎ እንደተቀመጠው የሚፈጸምበትን ጥቃት ዝም ብሎ እንደማያየው ሊረዱት ይገባል። አማራው በታሪኩ ራሱን ሲከላከል የኖረና ሃገሩንም ከሌሎች ወንድሞቹ ኢትዮጽያውያን ጋር በጋራ እንደጠበቀ ሁሉ ዛሬ ትጥቁን ፈቷል አልተደራጀምና በቀላሉ ልናጠቃው እንችላለን በሚል መንገድ የሚቃጣበትን ጥቃት ሕልውናውን ለማስጠበቅ ማናቸውንም ዋጋ ከፍሎ በአሸናፊነት እንደሚወጣ የማያጠራጥር ቢሆንም ፤ ይህ ህዝባዊ ቁጣ ከተቀጣጠለ ለማንኛውም ኢትዮጽያዊ ዜጋ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ቀንድ ጭምር የሚተርፍ ሰደድ እሳት እንደሚያስነሳ ቅን የሆነ ዜጋ ተገንዝቦ ይህን የክፋትና እርስ በእርስ እንድንጫራረስ የተሰጠንን ርኩስ አጀንዳ በግዜ አደብ እንዲይዝ መደረግ የሚገባው ጥረት ማድረግ በሁሉም ጽንፎች ያሉ ወገኖች እርጋታ እንዲያደርጉና በተለይ ወጣት ምሁራኖች በዚህ የወንድማማቾች ፖለቲካዊ ጡዘት ለማርገብ ከስሜት ባሻገር ስልጡን የሆነ ውይይት በየማህበራዊ መድረኮች በማድረግ ሰላም ለማስፈን የሚቻለውን ማድረግ ይኖርብታል።
ኢትዮጽያ በክብር ለዘላለም ትኑር!!!
አሜን
                                                                                                                  Posted by A.G

No comments:

Post a Comment