Monday 24 August 2015

ይህ ረሃብ “ፖለቲካዊ ችጋር” ነው!!

“በቀን ሦስቴ እንመግባችኋለን”

famine


ህወሃት ለአገራችን የቀመመው የበቀልና የተላላኪነት ፖለቲካ ገና ጦሱ አልጀመረም። ግን ሊመጣ ግድ ነው። በንጉሡ ወቅት ተርበናል። በደርግ ጊዜ ተርበናል። ኢህአዴግ ከመጣ ጀምሮ የታዩት ርሃቦች ግን ለየት ያሉ ናቸው። ስለዚህ ርሃቡም ሆነ ችጋሩ ፖለቲካዊ ነው ቢባል ያስማማል። ኢሣ የግጦሽ ሳር ሲያጣ ወደ ጎረቤቶቹ ያመራ ነበር። አፋር ተመሳሳይ ችግር ሲገጥመው ከብቶቹን እየነዳ ችግርን አሳልፎ ይመለስ ነበር። መጠነኛ አለመስማማት /በግጦሽ መሬት/ ከመፈጠሩ ውጪ “እገሌ ነህ” በሚል ጎጥ ለይቶ ሲጋደል አልተሰማም።
ዛሬ ህወሃት ሌሎችን እንደራሱ ለማሳነስና ለመበጣጠስ ሲል በዘርና በጎሳ መባላትን በአዋጅ ደንግጎ፣ በህግ አጽድቆ፣ ባገር ሚዲያ ጥላቻን እየሰበከ ተፋቅረው የኖሩትን አባልቷቸዋል። እያባላም ነው። ብዙ ሳይቆይ ራሱንም ጨምሮ የሚበላውን እሳት በየቀኑ እያጋመውም ይገኛል። እናም ሰሞኑን አደባባይ የወጣው ርሃብ ሰለባ ከሆኑት መካከል “እንደቀድሞ ከብት እየነዱ ምግብ ፍለጋ መጓዝ ስለማይቻል፣ ወገኖቻችን ውሃ እያሉ አለቁ። ተደብቆ እንጂ ብዙ ህዝብ አልቋል” ሲሉ ነግረውናል። ይህ ፖለቲካው ያመጣው ጣጣ ኩራት ለሚሆንላችሁ እንኳን ደስ አላችሁ፣ ገንቡ፣ ዝረፉ፣ ልጆቻቸሁን በዶላር አስተምሩ፣ አፈናቅሉ፣ የድሃውን መሬት በሽርክና ቸብችቡ፣ ራሳችሁም ኢንቬስተር ሆናችሁ አልሙ፣ ተንበሻበሹ፣ ስከሩ፣ ዘሙቱ፣ በራባቸው ላይ አስመልሱባቸው፣ … እነ ሬድዋንን ጨምሮ።
የመለስ ሙት መሃላ
“የሚሰሩ እጆች እያሉን፣ የሚያስቡ አእምሮዎች እያሉን፣ ይህን ወጣት ኃይል ይዘን ስንዴ መለመን እናቆማለን” በማለት ድርሰት ሲደርሱልን፣ ሲተርኩልን የነበሩት አቶ መለስ “የልማት አርበኞችን” ይዘው ገጠር ገቡ። የልማት ጀግኖች ከተማ ለቀው ገጠር ከተሙ። ዕድሜ “ለኤክስቴንሽን” አገሪቱና ገበሬው ምርት ማስቀመጫ ቦታ አጡ። በአገሪቱ ታሪክ እህል ወደ ውጪ መላክ ተጀመረ በማለት ደጋግመው ሰብከውን ነበር። መለስ “ገበሬውንና አርብቶ አደሩን ማእከል አድርገን ተነስተናል። ይህ አስተሳሰብ የሚቀየረው በኢህአዴግ መቃብር ላይ ብቻ ነው” እያሉ ሲምሉ ነበር። ነገር ግን ሲማልበት የነበረ ህዝብ መሬቱን ተቀማ። በሳንቲም ለሌባ “ባለሃብቶች” ተቸበቸበ። የህዋሃት ሰዎች በልማት ስም ተቀራመቱት። የኢንቨስትመንት ኤጀንሲ መረጃ አብይ ዋቢ ነው። እዩት!! በቀን ሶስቴ መብላት ቀርቶ አንዴውም እርም ሆነ። ነፍስ ይማር?!
የፖለቲካ ድርቅ – ፈጀን – ገና ይፈጀናል!
ሰዎች በዘራቸው ተለየተው ከሚኖሩበት ተፈናቅለዋል። እየተፈናቀሉ ነው። በሁሉም ክልሎችና ጎረቤት አገራት “ተከብረው” የሚኖሩት ህወሃት “ምርጥ” የሚላቸው ዜጎቹ ብቻ ናቸው። ይህንኑ ሃቅ የህወሃት አመራሮች በይፋ የሚናገሩት እንጂ እኛ የፈጠርነው አይደለም። መፈናቀል ለችጋር ይዳርጋል፤ የፖለቲካ ድርቅ ነው። ሰለባዎቹ ፍቺው ስለሚገባቸው ይብቃ!!
ለም መሬት በቅንጣቢ ሳንቲም እየቸበቸቡ ደሃውን ማፈናቀል ሌላው የፖለቲካ ቸነፈር ነው። ለአራት ዓመት ህጻን “ከክልላችን ውጣ” ብሎ ደብዳቤ መስጠት የከፋ የፖለቲካ ጠኔ ነው። “ባሪያ፣ አገልጋይ፣ አሽቃባጭ፣ ሎሌ … ካልሆንክ ሥራ አታገኝም” ብሎ ማለት ጠባሳው የማያሽር የፖለቲካ ችጋር ነው።
ለምን ተነፈሳችሁ በሚል ወኅኒ ተጥለው የሚሰቃዩ ወገኖች ጉዳይ ጊዜ መልስ የሚሰጠው የፖለቲካ ሽባነት ነው። ይህም ትልቅ ችጋር ነው። ሴት እህቶቻችን በዘራቸው ተመርጠው እንዲመክኑ ማድረግ ይቅርታ ለማድረግ የሚቸግር የፖለቲካው ተስቦ ውጤት ነው። እንዲህ ያለው የነጠፈ ኅሊና የሚነዳው ፖለቲካ ከችጋር በምን ይለያል?
ከድሃው ጉሮሮ በመንጠቅ በተዘረፈ ሃብት ድንጋይ መቆለል፣ ቪላ ማስገንባት፣ ዘመናዊ ተሽከርካሪ መዘወር፣ ጠግቦ ድሆችን መርገጥ … የፖለቲካው በሽታ ከመሆን ምን ያግደዋል? ከወገን ይልቅ ባእድ የሚያስቀድም የአገር ገዢ የፖለቲካ ችጋር ያጠናገረው እንጂ ሌላ ምን ሊባል ይችላል? እነዚህ ኅሊናቸው የሞተባቸውና ቂም ቀብትቶ የያዛቸው ክፍሎች የሚያሽካኩበት ህዝብ የፖለቲካው ችጋር አልመታውም? ቸነፈሩ ስንቱን ዘረረ?! የስንቱን ደጅ ዘጋ … እንዲህ እየኖርን ዛሬ ላይ ደረስን።
ዛሬም ተርበናል። ችጋር ይዞናል። ድርቅ እንስሶችን፣ ወገኖቻችንን እየቀጠፋቸው ነው። የቁጥር ጸብ ከሌለ በስተቀር ችጋሩም፣ ረሃቡም፣ ድርቁም ካቅም በላይ ሆኖ ህጻናትን፣ አረጋዊያንን፣ እንስሦችን እንደፈጀና እየፈጃቸው ስለመሆኑ መከራከሪያም ሆነ ማደናበሪያ ማቅረብ የሚቻለው የለም። ሊኖርም አይችልም።
በተመሳሳይ ጥጋብ ያሰከራቸውና በዝርፊያ ላይ ተጠምደው “ልማት ላይ ነን” የሚሉ አሉ። ሁሉም የዚያች መከረኛ አገር “እኩል ዜጎች” ተብለው ይቆጠራሉ፤ ይጠራሉ። የዚህን መጨረሻ ስናስብ እናፍራለን፣ እናዝናለን፣ አንደነግጣለን። ስጋት ያርደናል። በዚህ መልኩ አይቀጥልምና!! የቀን እንጂ የሰው ጀግና የለውም እንደሚባለው!!
“ድርቅና ችጋር ያሉ፣ የነበሩና የሚኖሩ ናቸው። አሜሪካም ሆነ አውስትራሊያ ድርቅ አለ፤ ለምን እንዲህ በመረረ መልኩ አያችሁት? ድርቅ ብርቅ ነው እንዴ?” በሚል ጥያቄ የሚያቀርቡ “የልማት መሪዎችና አርበኞች” መልሳችን “ቀን ይፍረድ” ብቻ ነው።
ረሃቡ የቆየ መሆኑ
እንደሚታወቀው የዘንድሮ ምርት ዘመን ገና መንገድ ላይ ነው። ክረምቱ አላበቃም። ስለዚህ አሁን ይፋ የሆነው ችጋር ካለፈው አመት ተንከባሎ የመጣ በመሆኑ አሁን ተከሰተ የተባለው “የዝናብ እጥረት” ምክንያት ሊሆን አይችልም። ለቪኦኤ አማርኛው ክፍል መግለጫ የሰጡት የሚቲዎሮሎጂ ባለስልጣን የዝናብ እጥረት እንደሚከሰት ለሚመለከታቸው ሁሉ አስቀድመው ማሳወቃቸውን ተናግረዋል። “የአየር ንብረት ድርቅ ገብቷል” ሲሉ አዙረውም ቢሆን ችግሩን አምነዋል። ግብርና ሚኒስቴርም ድርቅ ስለመከሰቱ ተጠየቆ አላስተባበለም። በዚህ መነሻ 14 ሚሊዮን ሕዝብ በችጋር እስኪገረፍ ድረስ፣ 24 ሚሊዮን ህዝብ ለችጋር እስኪጋለጥ “ልማታዊ ነኝ” የሚለው ህወሃትና አጫፋሪዎቹ የት ነበሩ? “ልማታዊ ነን፣ ስራ ላይ ነን” የምትሉት እናንተ “የህወሃት ምርጥ ዜጎችና አገልጋዮች” ምን መልስ ልትሰጡ ትችላላችሁ? “በቀን ሶስት ጊዜ ትበላላችሁ” በማለት በድሆች ላይ ሲሳፈጥ የነበረውን “ሌጋሲ” አምላኪዎችና የሙት መንፈስ ድቤ ደላቂዎች ራዕዩና “ከሦስት ዓመት በኋላ መልሳችሁ ምንድነው? “ከ … ጋር መጪው ጊዜ ብሩህ ነው”?!
ከፖለቲካ ችጋር ነጻ ካልወጣን ሁሌም ችጋር ነው!! መልከ ብዙ ችጋር!! (ፎቶ: ለማሳያ የቀረበ)

No comments:

Post a Comment