Friday 4 December 2015

የወገኖቻችን ስቃይ፣ ችግርና ብሶት በያለንበት ይሰማን፤ ለመፍትሔውም በጋራ እንነሳ!

 የአርበኞች ግንቦት 7 መግለጫ


December 3, 2015

በአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ሰበብ በከተማዋ ዙርያ ያሉ ወገኖቻችንን ማፈናቀል በመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የተፈፀመ ጥቃት ነው። በማስተር ፕላኑ ሰበብ የሚፈናቀሉ ገበሬዎች የሁላችን ወላጆች፣ ወንድሞችና እህቶች ናቸው። በማስተር ፕላኑ ሰበብ የምንፈናቀለው ሁላችንም ነን። ይህን መሰሪ ፕላን በመቃወም ላይ ያሉት የኦሮሞ ተወላጅ ወገኖቻችን ትግል ፍትሀዊ በመሆኑ አርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ ከጎናቸው ይቆማል።


በዚሁ ወቅት በጎንደር ሌላ አሳዛኝ ጉዳይ ተከስቷል። ህወሓት ከሶስት ሺህ በላይ ዜጎቻችንን ያጎረበት እስር ቤት በእሳት ሲጋይ ዜጎች ተቆልፎባቸው እንዲነዱ ተደርጓል። ከእሳቱ በእድል ያመለጡት በጥይት ታድነዋል። ኢትዮጵያዊያን እንዲህ ዓይነቱን ጭካኔ የሚያውቁት በፋሺስት ጣሊያን ወረራ ጊዜ ነው። ይህን ጥቃት በመቃወም ላይ ያሉ የአማራ ተወላጅ ወገኖቻችን ትግል ፍትሀዊ በመሆኑ አርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ ከጎናቸው ይቆማል።



ግፍ ያልተፈፀመበት የኢትዮጵያ ክፍል ባይኖርም ሰሞኑን በአማራና በኦሮሚያ ላይ በርክቷል። በሁለቱም የአገራችን ክፍሎች የንፁሀን ደም እየፈሰሰ ነው፤ በሁለቱም ቦታዎች የእናቶች ዋይታና እሪታ ጎልቶ እየተሰማ ነው። የህወሓት አገዛዝ የትውልድ ቦታ፣ ቋንቋና ዘር ሳይለይ በኢትዮጵያዊያን ሁሉ ላይ የተደቀነ አደጋ መሆኑ ከምንጊዜውም በላይ ዛሬ ግልጽ ሆኗል።

ለዚህ የምንሰጠው ምላሽ ምንድነው? ዛሬም ኦሮሚያ ውስጥ የሚፈፀመው በደል የኦሮሞ፤ አማራ ውስጥ የሚፈፀመው በደል የአማራ ጉዳይ አድርገን እንወስዳለን? መቸ ነው ኦሮሚያ ላይ ለደረሰው ጥቃት አማራዉ፤ አማራ ላይ ለደረሰው ጥቃት ኦሮሞው የሚቆረቆረው?

የሁላችን የጋራ ጠላት የሆነው ህወሓት መኖሩ በዘውግ የተከፋፈለውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ወደ አንድነት የሚያመጣ ታላቅ ኃይል ሊሆን ይገባል። ይህ የመከራና የመጠቃት ወቅት የምንቀራረብበት ወቅት ሊሆን ይገባል። ይህ የመከራ ወቅት በህወሓት ላይ በጋራ የምንነሳበት ወቅት ሊሆን ይገባል። ዛሬ በኢትዮጵያ ያሉ የተለያዩ ማኅበረሰቦች በሙሉ በፀረ-ህወሓት ትግል መቀናጀት ይኖርባቸዋል። ይህ ማድረግ ግዴታችን ነው።

ለችግሮቻችን መፍትሄ የምናገኘው ችግሮቹ ከተፈጠሩበት እርከን በላይ ሆነን ስናስብ እንጂ ችግሮቹ በፈጠሩበት ደረጃ ላይ ቆመን መሆን አይችልም። ችግሮቹ ከተፈጠሩበት እርከን በላይ ለመሆን አገር አቀፍ እይታ መኖሩ እጅግ ተፈላጊ ጉዳይ ነው። ኢትዮጵያን ሁሉ በተለይም የአማራና የኦሮሞ ልሂቃን ይህንን ጉዳይ አበክረው እንዲያስቡበት አርበኞች ግንቦት 7 በጽኑ ያሳስባል።

ግፍ ሞልቶ የፈሰሰበት ወቅት ላይ እንገኛለን። የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች የሆኑት ሕፃናት በፌዴራል ፓሊስ ጥይት የሚገደሉበት አሳዛኝ ወቅት ላይ ነን፤ ዜጎች በር ተዘግቶባቸው በእሳት እየጋዩ ነው። ሰፊ እና ለም የእርሻ መሬት ለሱዳን በስጦታነት ለመስጠት ዝግጁቱ የተጠናቀቀበት ወቅት ላይ ነን። 

ከአስር ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ተርቧል። በፍትህ እጦት እስር ቤቶች በንፁሃን ዜጎች ተሞልተዋል። ውሀ፣ መብራትና የቴሌፎን አገልግሎት ብርቅ ሊሆኑ ነው። ይህ ሁሉ እየሆነ ግን የሥርዓቱ አገልጋዮችና ደጋፊዎች በህንፃ ላይ ህንፃ እየገነቡ በድሀው ላይ ይሳለቃሉ። የህወሓት አገዛዝ ድህነትን፣ ችጋርን፣ ስደትን፣ የእርስበርስ ግጭቶችን እያባባሰ ኢትዮጵያን እየጋጠ የሚኖር አገዛዝ ነው። 

አገዛዙ በቀደደልን ቦይ ከተጓዝን ችግሮችን ማባባስ እንጂ ማርገብ እንኳን አንችልም። ይህንን ሥርዓት በቃህ ማለት የአማራ ወይም የኦሮሞ አጀንዳ አይደለም፤ ይህ የሁላችንም – የኢትዮጵያዊያን – ጉዳይ ነው።

ለቀምት፣ ሀረር፣ ሱልልታ እና ሌሎች በርካታ የኦሮሚያ ከተሞች ውስጥ ለደረሱ ጥቃቶች ባህር ዳር፣ ጎንደር፣ ደሴ፣ ሀዋሳ፣ መቀሌ፣ አሶሳ፣ ሁመራ፣ ጋምቤላ ውስጥ ተቃውሞ መሰማት አለበት። በጎንደርና ባህርዳር ለደረሰውም ጥቃት አዳማ፣ ጅማ፣ ሆሳዕና፣ ጅግጅጋ፣ አክሱም ላይ ተቃውሞ መሰማት አለበት። በማንኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ለሚደርሰው በደል መላዋን ኢትዮጵያ ሊያሳምም ይገባል። መከፋፈላችን መከራችን አብዝቶታል፤ የህወሓት እድሜን አርዝሟል፤ ይብቃ!

አርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ የመከራ ጊዜዓችን እንዲያጥር በዘውግ ሀረግ፣ በብሔርና እና በሀይማኖትና ሳንታጠር የወገናችን ህመም ይሰማን፤ ተሰምቶንም ለጋራ ትግል እንነሳ ይላል።

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!

No comments:

Post a Comment