Saturday 20 December 2014

ዛሬም በዋልድባ እሥራቱ እንደቀጠለ ነው “አባት ሆይ ይሄ ሁሉ ግፍና በደል የሚቆመው መቼ ይሆን?"

ሁለት ታላላቅ ሊቀ አበው ባለፈው ሳምንት ወደ ማይጸብሪ ፖሊስ ተወስደው ታስረው ተፈቱ
የእነ አባ ገብረ ሕይወት መስፍን ስልታዊ የመንግሥት ተወካይነታቸው ቁልጭ ብሎ ታውቋል
ወታደሮች ዛሬም ድረስ በገዳሙ እንደሚገኙ አባቶች ይናገራሉ፣ ምክንያታቸው ግን ምን እንደሆነ አይታወቅም
የግድቡ ሥራ ከየትም ሊደርስ ባለመቻሉ የመንግሥት ሰዎች ዓይናቸውን ወደ ሌላ ለማዞር እየሞከሩ ነው
በመስከረም ወር ላይ በችግኝ ማፍያ አካባቢ የተነሳውን የአንበጣ መንጋ ለማጥፋት በሚል መንግሥት የሚረጨው መድሃኒት በርካታ የወልቃይት አውራጃ ነዋሪዎችን ከብቶች ፍጅቶባቸዋል
መንግሥት አሁንም 3900 የሚሆኑ አባወሮችን ከመዘጋ ወልቃይት እንደሚያስነሳ እየተነገረ ነው
ባለፈው ሳምንት መጨረሻ አካባቢ ነው ከማይጸብሪ ፖሊስ ጣቢያ የመጡ ታጣቂዎች እንደተለመደው ወደ ገዳሙ ዘልቀው በመግባት ሁለት ሊቃነ አበውን ምክንያት በሌለው ነገር እንደ ወንጀለኛ አስረው ወደ ማይጸብሪ አውራጃ ፖሊስ ጣባያ በመውሰድ በእስር ቤት አጉረው ከወንጀለኛ ጋር አሳድረው ለቀዋቸዋል፡፡ በሁኔታው ያዘኑ በርካታ መነኮሳት ምን በድለው ነው? ምን ጥፋት ተገኝቶባቸው ነው? በማለት ቢወተውቱም መልሱ ግን ግልጽ ነው። እንደሚታወቀው ዓመት ከመንፈቅ በፊት በአቶ ሲሳይ መሬሳ የሚመራው የአውራጃው አስተዳደር በአበንታንት ዋልድባ ገዳም ያለውን የነበረውን የአበውን ትውፊት ወደጎን ብለው፥ በጉልበታቸው እና በሥልጣናቸው የእግዚአብሔርን ቦታ እና ቤተመቅደስ የሚያስተዳድሩትን አባቶች በጉልባቱ መርጦ በማስቀመጥ
1ኛ/ አባ ገብረዋሕድ መምሕር የአበረንታንት መድኃኒዓለም ገዳም አበመኔት
2ኛ/ አባ ገብረሕይወት መስፍን (የቀድሞ ታጋይ) እቃ ቤት አድርጎ ከሾመ በኃላ ነው ችግሮች እየበዙ እና እየጠነከሩ የመጡት። በዚህም መሰረት በተለይ የቀድሞው ታጋይ እያንዳንዷን በገዳሙ ውስጥ የሚደረጉትን እና የሚታሰቡትን በሙሉ በመቅረጸ ድምጽ በተደገፈ ማስረጃ ለመንግሥት በማቀበል፥ በእነሱ አመለካከት “ጸረ ልማት” ወይም “ጸረ ሰላም” ናቸው ብለው የሚሏቸውን መናንያን፣ መነኮሳት እንዲሁም ባሕታውያን ጭምር በፈለጉ ጊዜ ወደ እስር እንዲጋዙ፣ በድብደባ፣ እና ለስደት እንዲዳረጉ ከኃላ ሆነው መመሪያውን እየሰጡ ያሉት እኒሁ በውስጣቸው ተቀምጠው ያሉት ጉዶች እንደሆኑ አባቶች በሐዘን ይናገራሉ። “መድኃኒዓለም ጥዋው የሞላለት . . . ወይውላቸው” ነበር ያሉት አንድ የገዳሙ አባት።
ይህ ሁሉ መከራ እና ግፍ የሚፈጸምባቸው ፍቅረ ክርስቶስ ይዟቸው ይህን ጣፋጭ ዓለም ትተው እራሳቸውን ከዓለም ደብቀው በጸሎት፣ በስግደት ባሉበት ቦታ መጥተው እንዲህ ያለ ግፍ ሲፈጽሙባቸው እጅግ ያሳዝናል። በፍልሰት ከሚኖሩበት ተጎትተው ለእስር የበቁት ሁለቱ አባቶችም ይህው ነው የደረሰባቸው፥ እንደ ምክንያት የተሰጣቸውም
- ከቤተ ጣዕመ አባቶች ጋር በአንድነት አትሰሩም፣ አትጸልዩም
- መስቀላቸውንም አትስሙም
- በፍልሰት መቀመጥ አትችሉም (ዘግተው በጸሎት እና በስግደት ተወስነው መቀመት አትችሉም) ነበር ምክንያታቸው፤ እውን ይሄ ለእስር የሚያበቃ ጥፋት ነው? አምላከ አበው ፍርዱን ይስጥ
በማይጸብሪ ፖሊስ ጣቢያ ታጉረው የነበሩት ሁለት ሊቃነ አበው አባ ገብረ ኪዳን እና አባ ገብረ መስቀል ይባላሉ
በዋልድባ ገዳም ከሦስት ዓመት በፊት የወልቃይት ሥኳር ፋብሪካ ፕሮጀክት ከተጀመረ ወዲህ በርካታ የመንግሥት ታጣቂ ወታደሮች በገዳሙ አካባቢ መታየት ጀምረው ነበር፥ አሁንም ድረስ ከሦስት አበመት በላይ በገዳሙ የተለያዩ አካባቢዎች በርካታ ታጣቂዎች ሰፍረው ይገኛሉ፣ ገዳማውያኑም የተለመደ የቀን ተቀን ተግባራቸውን ይፈጽማሉ ሥራ የሚሰራውም ሥራዎን በጸሎትም ያሉት ጸሎታቸውን። ነገርግን ሁልጊዜም ጥያቄ ይፈጠራል እነኝህ ወታደሮች እኛን ነው የሚጠብቁት ወይንስ ? ጥያቄው መልስ ባያገኝም ዘወትር የሚያልፉት የሚያገድሙት ሁሉ እነሱን ሲመለከት ጥያቄ ማንሳቱ አይቀሬ ነው መልስ ባይኖረውም። ባለፉት ጥቂት አመታት መንግሥትም ይሄን አካባቢ በዓይነቁራኛ ከሚጠብቃቸው ጥቂት ቦታዎች አንደኛው እነመሆኑ መጠን ጥበቃው ያንን ፍራቻ ሊሆን ይችላል የሚሉም ብዞዎች ናቸው። ከአንድ አመት በፊትም የጃናሞራና የወልቃይት አርሶአደሮች በገዳሙ ላይ እየደረሰ ያለውን ችግር ለመንግሥት ተወካዮች ቢያሳስቡ እናንተ ጸረ ልማቶች ተብለው ሲወነጀሉ ጥቂት የማይባሉ የአካባቢው አርሶ አደሮች ሸሸተው ጫካ መግባታቸውን እና አልፎ አልፎ መንግስም ስጋቱን በተለያየ ጊዜ ሲገልጽ ቆይቷል፣ በዚህም ይሁን ወይም በሌላ በገዳሙ ክልል ውስጥ ያሉት ወታደሮች ለበረከት የመጡ ሳይሆን ለቅስፈት እግዚአብሔር ያውቃል።
ከዚሁ የዋልድባ ዜና ሳንወጣ ላለፉት ወደ አራት ዓመት ሊሞላው ጥቂት ወራት የቀሩት ጊዜ ውስጥ የወልቃይት ስኳር ፋብሪካ ግንባታ ጋር ተያይዞ የዛሬማ ወንዝን ገድቦ ወደ 40 ሄክታር የሚገመት መሬት ከአበረንታንት መድኃኒዓለም ገዳም ቀምቶ ሊገደብ የታሰበው ግድብ እስከ አሁኗ ደቂቃ ድረስ እንኳንስ ግድብ ቀርቶ፥ ጥቂት ውሃን እንኳን ሊያቁር የሚችል ነገር ለመስራት አለመቻላቸው መንግሥትንም ሆነ ለስራው ቅርበት ያላቸውን ሰዎች እራስ ምታት ሆኖባቸው ቀርቷል፣ ለዚህም ይመስላል የኢትዮጵያ ስኳር ልማት ኮርፖሬሽን ዳይሬክተር የነበሩት አቶ አባይ ጸሐዬ እራስ ምታቱ እንደ ትግል አጋራቸው ይዟቸው እንዳይሄድ በመስጋት ይመስላል የስኳር ኮርፖሬሽን ሃላፊነታቸውን ጥለው ወደ ሌላ ቦታ የተዘዋወሩት። በርካታ ባሕታውያንም ገና ከጅምሩ ሲናገሩ እንደነበሩት ዛሬም ድረስ “በመድኃኒዓለም ቦታ ላይ ማንም ምንም አይሰራም” እግዚአብሔር ተዋጊ ነው ስሙም እግዚአብሔር ነው በማለት ዛሬም ድረስ በልበ ሙሉነት አባቶች ይሄን ሲናገሩ መስማት እጅጉን ያስደስታል። ዛሬ ዛሬ እንደውም እስከዛሬ ከተቋራጭ ተቋራጭ እየተቀያየረ በመምጣት በዛሬማ ወንዝ ላይ ግድብ ለመገደብ የሞከረም፣ ያሰበም፣ የስራ ተቋራጭ ሆኖ የሰራም በመድኃኒዓለም በትር ያልተቀጣ የለም። ያም ቁንጥጫው ነው በአግባቡ የሰሙ ፈጥነው ወጥተዋል አልሰማም ያሉትም ቀስ ብለው የሰሙታል፣ ያም ሆነ ይህ ግን ዛሬም ድረስ የስኳር ልማቱ የሚሆን የመስኖ ውሃ ለማዘጋጀት ግድቡ ወሳኝ ነው፣ ነገር ግን ግድቡም ሆነ ልማቱ ዋልድባን በሚያክሉ ታላቅ የቅዱሳን በፍለቂያ በሆነ ሳይሆን ሃገራችን ዓመቱን ሙሉ ሲፈሱ የሚኖሩ የበርካታ ወንዞች ባለቤት ናት ነገር ግን በእልህ እና በተልዕኮ የምነት ቦታችንን፣ ታሪካችንን፣ የቤተክርስቲያናችንን ይዞታ የሚነኩ ግን ይዋል ይደር እንጂ ከምድራዊውም ሆነ ሰማያዊው ፍርድ እንደማያመልጡ እምነታችን ነው።

በወልቃይት ተከስቶ የነበረው የአንበጣ መንጋ ይህን ይመስል ነበር?

ሌላው ከወደ ዋልድባ የመጣልን ዜና እንደሚያመለክተው ባሳለፍነው መስከረም ወር አካባቢ የተከሰተው የአንበጣ መንጋ ብዙ ውድመትን አድርሷል። ከዚህም መካከል የስኳር ልማት ኮርፖሬሽኑ ከታሊማ ወንዝ የተጠለፈ ውሃን ገድበው ወደ 30 ሄክታር የሚሆን መሬት ላይ የሸንኮራ ችግኝ ለማፍላት ሙከራ እየተደረገ ነበር። ከትቂት ወራት በፊት በግንቦት እና ሰኔ አካባቢ በአንዳንድ የአካባቢው ገበሬ መኅበር ታይቶ የነበረው የአንበጣ መንጋ ጊዜውን ጠብቆ በመስከረም እህል በሚያፈራበት ጊዜ ጠብቆ በመምጣት በ30 ሄክታር ላይ የተፈላውን የሸንኮራ ችግኝ እንዳልነበረ አድርጎታል፤ መንግሥትም በምላሹ በአካባቢው ላይ በርካታ ሰዎችን በማሰማራት መድኅኒት በመርጨት ወራሪን የአንበጣ መንጋ ለመዋጋት ሙከራ በሚያደርጉበት ጊዜ፥ በርካቶች የአባቢው ቀበሌ ገበሬ ማኅበር አባላት ከብቶቻቸው ግጦሽ በሚወጡበት ጊዜ ብዙ የመርዝ ክምችት ያለባቸው ቦታዎች ከብቶቻቸው እዛው በመብረቅ እንደተመታ እየሆኑ ወድቀው ተገኝተዋል፣ ደጋግመው አቤቱታቸውን ቢያሰሙም እንደከዚህ ቀደሙ ሰሚ ጆሮ ሳያገኙ ቀርተዋል። ለከብቶቻቸውም ካሳ ቀርቶ በአግባቡ አቤቱታቸውን ሊያዳምጥ የሚችል የመንግሥት አካል ሊገኝ አለመቻሉ በርካቶችን በእጅጉ አስቆጥቷል። የሆኖ ሆኖ በመንግሥት ላይ የደረውም ከባድ ኪሳራ ባያስደስትም ብዙዎችን ግን ትንሽ ሳያስፈግግ አልቀረም፣ ቀያችንን ለቀው ይሄዳሉ በማለት ነበር። ያም እንደታሰበው ሳይሆን የመንግሥት ሰዎች ላለፉት ጥቂት ወራት በእጅጉ ተያይዘው ያሉት በሌላ ጉዳይ በመሆኑ ችግሮችን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሳይሆንባቸው እንዳልቀረ ብዙዎች በምሬት ተናግረዋል።
ባለፈው ዓመት አካባቢ በዚሁ በልማት ሰበብ በርካታ ነዋሪዎች ቀያቸውን ለቀው በምትኩ ሌላ ቦታ ይሰጣችኃል በማለት የትም ሜዳ ተበትነው እንደሚገኙ ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል። አሁንም የመንግሥት ሰዎች በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት ውስጥ 3900 አባወራዎችን ሊያነሳ እና ቦታቸውን ሊወስድ እንደሆነ በሰፊው እየተነገረ ነው። ነዋሪዎችም ከዚህ በፊት ተነስተው የት እንደደረሱ ያልታወቁት በርካታ ነዋሪዎችን እጣ ፈንታ በእነሱም ላይ ሊደርስ እንደሚችል በመገመት በርካቶች በከባድ ስጋት ላይ እንደሚገኙ ለመረዳት ችለናል። የሸንኮራው ጉዳይ አልሳካ ያላቸው የመንግሥት ሰዎች በርካታ የአውራጃውን ነዋሪ ካስነሱ በኃላ ሰሊጥ፣ ነጭ አደንጓሬ፣ እና ጥጥ የመሰሳሰሉትን እያለሙ እንደሚገኙ ከዚሁ ጋር ተያይዞ በመጣ መረጃ ለመረዳት ችለናል። እንደሚታወቀው በኢትዮጵያ በአሁን ሰዓት ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ ከሚያስገኙ ምርቶች መካከል ከቡና ቀጥሎ ሰሊጥ እና ጥጥ እንደሆነ ይታወቃል። ቻይና ብቻ ከኢትዮጵያ 30 እስከ 40 ሜትሪክ ቶን ሰሊጥ እና ጥጥ ወደ ሃገሯ እንደምትወስድ ቻይና ዴይሌ የተባለው በቻይና በየቀኑ የሚታተም ጋዜጣ ዘገቦ ነበር።
አሁንም የበርካቶች ስጋት የነዚህን ምርቶች በአካባቢው በማምረት ውጤት ካመጣ በዚህ ሰበብ ለበርካታ ነዋሪዎች መፈናቀል እና ለዋልድባ ገዳምም ይበልጥ አደጋው ከፍተኛ እንደሆነ ይገመታል። በተለይ በገዳሙ ሞፈር ውሃ በሚባለው አካባቢ በርካታ የእርሻ ቦታዎችን በመውሰድ ለእነዚህ እራዎች እንደሚያደርገው ስለታወቀ ስጋታችን ይበልጥ ጨምሯል በማለት ነዋሪዎች ይናገራሉ። መናንያኑም በበኩላቸው እንደ ከዚህ ቀደሙ፤ በዋልድባ ምድር ላይ ምንም ነገር ቢመጣ ሊሰሩም ሆነ ሊያደርጉ የሚችሉት ነገር እንደማይኖር ደጋግመው ይናገራሉ። “እኛ አፈር ጠባቂዎች ነን፥ ቦታው የመድኃኒዓለም ነው” ስለዚህ እርሱ ይጠብቀዋል ከእኛ የዘውትር መወድስ፣ ፀሎት እና ልመና ብቻ ነው የሚፈልገው፥ እኛም ጸሎታችንን ልመናችንን አናቆምም፤ እነሱም በሃይላቸው ተመክተው የክርስቶስን ቦታ ለመውሰድ በሚያደርጉት ተግዳሮት ቀስ በቀስ እየተቀሰፉ ስራውን እስኪያቆሙ ይቀጥላል ይላሉ ያነጋገርናው አባቶች።

No comments:

Post a Comment