Thursday 2 April 2015

የሰማያዊ ፓርቲ አደራጅና ቤተሰቦቹ ድብደባ ተፈፀመባቸው


በባሶ ሊበን ወረዳ የላም ደጅ ቀበሌ የሰማያዊ ፓርቲ አደራጅ የሆነው እንዳለማው ደመላሽ በብአዴን ካድሬዎችና ፖሊሶች ከፍተኛ ድብደባ እንደደረሰበት የወረዳው አደራጆች ለነገረ ኢትዮጵያ ገለጹ፡፡ 

አቶ እንዳለማው ደመላሽ በተደጋጋሚ ‹‹ከሰማያዊ ፓርቲ ልቀቅ፡፡ መሬትና ሌሎች ጥቅማጥቅሞችን እንሰጥሃለን፡፡ ይህን ካላደረክ ግን እርምጃ እንወስዳለን›› የሚል ማስፈራሪያ ሲደርስበት እንደነበር የገለጹት የወረዳው አመራሮች ትናንት መጋቢት 23/2007 ዓ.ም ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ ካድሬዎችና ፖሊሶች ‹‹በተደጋጋሚ ከፓርቲው እንድትለቅ ብንነግርህም ልትሰማ አልቻልክም›› ተብሎ ድብደባ እንደፈጸሙበት ገልጸዋል፡፡

ካድሬዎችና ፖሊሶች በአቶ እንዳለማው ደመለሽ ላይ ድብደባ በፈፀሙበት ወቅት ልጃቸውን ለማስጣል የጣሩት የአቶ እንዳላማው እናትና አባትም ከፍተኛ ድብደባ እንደተፈፀመባቸው ከቦታው የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡ 


በተለይ የአቶ እንዳላማው እናት ከፍተኛ ድብደባ ስለተፈፀመባቸው በአሁኑ ወቅት ሀኪም ቤት ውስጥ እንደሚገኙ ተገልጾአል፡፡ በትናንትናው ዕለት እንዳላማውና ቤተሰቦቹ በወረዳው ቀጠና ፖሊስ ጣቢያ እንደታሰሩ ታውቆ የነበር ቢሆንም ዛሬ አቶ እንዳላማውን የት እንዳደረሱት ለማወቅ አልቻልንም ሲሉ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡

No comments:

Post a Comment