መጋቢት ፯(ሰባት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ኦህዴድ የ25ኛ አመት በአሉን በትግራይ ክልል ውስጥ ለማክበር የነበረው ፍላጎት ከተደናቀፈ በሁዋላ፣ በደራ ወረዳ ጉንዶመስቀል ከተማ ለማክበር ከፍተኛ ዝግጅት እያደረገ ሲሆን፣ የተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶችተዘግተው ሰራተኞች የገጠሩን ህዝብ እንዲቀሰቅሱ ተሰማርተዋል። መጋቢት 10 የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ጉንዶመስቀል ይገባሉ ተብሎ በመጠበቁ እጅግ በርካታ የፌደራል ፖሊስ አባላትና የደህንነት ሰራተኞች ወደ ከተማዋ ገብተዋል።
የመንግስት መስሪያ ቤቶች ተዘግተው ሰራተኞች ህዝቡን እንዲቀሰቅሱ ወደ ገጠር ተልከዋል። የፊታችን ሀሙስ በሚከበረው ዝግጅት ላይ ከ10 ሺ በላይ ህዝብ ለመሰብሰብ ታስቧል።
የመንግስት ሰራተኞች፣ እኛ ከፖለቲካ ነጻ ናችሁ እየተባልን የአንድን ፓርቲ ልደት ለማክበር ስራ ቆሞ ለቅስቀሳ የምንሰማራበት አካሄድ ትክክል አይደለም በማለት ቅሬታቸውን ለኢሳት ገልጸዋል።
ህዝቡ በበአሉ ላይ እንዲገኝ ከመገደዱ በተጨማሪ እያንዳንዱ የክልሉ ገበሬ የበአሉን ወጪ ለመሸፈን በነፍስ ወከፍ 10 ብር በግዴታ ይከፍላል። የኦህዴድ አባል ያልሆነ የመንግስት ሰራተኛ 30 ብር እንዲከፍል ሲገደድ፣ የአንደኛ ደረጃ ግብር ከፋይ ነጋዴ 5 ሺ ብር፣ ሁለተኛ ደረጃ ነጋዴ 2 ሺ ብር እንዲሁም በሐ ደረጃ ያለ ነጋዴ ደግሞ 1 ሺ ብር እንዲከፍል ታዟል።
ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ወገኖች እንደሚገልጹት በኦሮሚያ ክልል እና በአዲስ አበባ በተለይ የመንግስት ሴክተር መ/ቤቶች ላይ የሚገኙ የኦህዴድ አባላት ከደመወዛቸው ላይ በፐርሰንት በአንድ ጊዜ እየተቆረጠ ገንዘብ ገቢ እንዲያደርጉ በማሰብ ድርጅታዊ ስብሰባ በማድረግ ለማግባባት የተሞከረ ቢሆንም አብዛኞቹ አባላት ፈቃደኛ ሳይሆኑ በመቅረታቸው በሌላ በኩልም ከደመወዝ የሚቆረጠው መጠን እንዲያንስ ፍላጎት ያላቸው በመሆኑ እስካሁን የተጠበቀውን ያህል ገቢ ሊገኝ አልቻለም፡፡
በተለይ አዲስ አበባ በየደረጃው የሚገኙ በኦህዴድ አባል የሚመሩ የሴክተር መ/ቤት አመራሮች ፈቃደኛ ያልሆኑትን ሠራተኛ አባላት ስም ዝርዝር አምጡልን በማለት አንዳንድ አባላትን እያስፈራሩ ይገኛሉ።
አንዳንድ የኦህዴድ አባላት ” እነዚህ ሰዎች ከህወሃት ጋር ከማን አንሼ አይነት ፉክክር ውስጥ የገቡ ይመስላል፣ ህዋህት እኮ መንግስት ነው፤ የእነሱን አይነት በዓል ለማዘጋጀት ደግሞ ከፍተኛ ገቢ መኖር አለበት፤ እኛ ከየት እናምጣላቸው? ለምን እኛ ላይ ጫና እንደሚያሳድሩ አይገባንም” የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።
አመራሮቹ የሚፈለገውን ያክል ገንዘብ ከመንግስት ካዝና በብድር መልክ ለማውጣት ጥረት ተደርጎ በኋላ ተስብስቦ ይከፈላል በማለት የመንግስትን በጀት ለድርጅት ድግስ ለማውጣት ሙከራ እያደረጉ መሆኑንም ለማወቅ ተችሎአል።
ኦህዴድ የህወሃት ተለጣፊ ድርጅት ነው እየተባለ በኦሮሞ ተወላጅ ኢትዮጵያውያን ዘንድ በተደጋጋሚ ይተቻል።
በአፈጉባኤ አባዱላ ገመዳና በክልሉ ፕሬዚዳንት ሙክታር ከድር መካከል ያለው ልዩነት እየሰፋ መምጣት የድርጅቱን ህልውና አደጋ ላይ እንደጣለው ለድርጅቱ ቅርበት ያላቸው ሰዎች ይገልጻሉ።
No comments:
Post a Comment